የኢትዮጵያ ኢንሹራንስ ታሪክን የኖሩት ባለሞያ

0
1357

የአዋሽ ኢንሹራንስ ኩባንያን ከምሥረታው ጀምሮ ለ25 ዓመታት ከዋና ሥራ አስፈጻሚነት ሲያገለግሉ፣ በኢንሹራንስ ዘርፍ ከ40 ዓመታት የዘለቀ ቆይታ አድርገዋል፤ ፀጋዬ ከምሲ። በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት በንግሥ ሥራ ኮሌጅ ካገኙት ዲፕሎማ ባሻገር በመደበኛ ትምህርት የገፉ ባይሆንም፣ ዓመታትን በዘለቀው ልምዳቸው ግን ዘርፉን አንዳች ሳያስቀሩ በሚገባ የሚያውቁት ሰው ሆነዋል። በኢንሹራንስ ዘርፍ ስኬታማ ከሆኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚዎች መካከልም ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ናቸው።
በፀጋዬ 25 ዓመታ በዘለቀ የሥራ ዘመን አዋሽ ኢንሹራንስ አንዴም እንኳ ኪሳራ አላስመዘገበም። ይልቁንም በኢትዮጵያ ካሉ የግል ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ትልቁ ሊሆን ችሏል። ኩባያው ባለፈው የ2011 በጀት ዓመት እንኳ 160 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ በማመዝገብ ቀድሞ ከነበረው በጀት ዓመት 25 በመቶ ከፍ ያለ ትርፉ ለዚህ ምስክር ይነሳል።
ፀጋዬ ምንም እንኳ ከኃላፊነታቸው የለቀቁ ቢሆንም በተቻለ መጠን ከዘርፉ ግን እንደማይወጡ ጠቅሰዋል። ‹ከ40 ዓመታ በላይ የሠራሁበትና የኖርኩበት ሙያ ነው። እድሉን ባገኝ ለዘርፉ እድገት ከሆነ ያለምንም ክፍያ ብሳተፍም ደስ ይለኛል› ሲሉ ለሙያው ያላቸውን ፍቅር ያነሳሉ። የሦስት ልጆች አባት፣ የአራት ልጆች ደግሞ አያት ናቸው።
የኖሩበትን የሥራ ልምድና ለዛሬ ያደረሳቸውን መንገድ፣ የኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ዘርፉን ውጣ ውረድና ፈተናዎች እንዲሁም ነባራዊ ሁኔታዎችን በሚመለከትም ከአዲስ ማለዳ እህት መጽሔት ‹ኢትዮጵያን ቢዝነስ ሪቪው› ዋና አዘጋጅ ሳምሶን ብርሃኔ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርገዋል።

በኢንሹራንስ ዘርፉ የቆዩ ጥቂት ሰዎች ናቸው ያሉት፤ መጀመሪያ ጀምሮ እንዴት ገቡ ያኔ ዘርፉ እንዴት ነበር ከሚለው እንጀምር
እኔ የኢንሹራንስ ዘርፍ ሥራ የጀመርኩት በ1966 አካባቢ ነው። ያኔ የገባሁበት ኩባንያ ኢምፔርያል ኢንሹራንስ ይባል ነበር። በወቅቱ የመግሥት ኢንሹራንስ የለም፣ ሁሉም የግሎች ነበሩ። ይህ እንግዲህ በንጉሡ ዘመን ነው። ከዛ በፊት አራት ዓመት ንግድ ሥራ ትምህርት ቤት አስተምሬ ነበር። አንድ ጓደኛዬ የሥራ ማታወቂያ መውጣቱን ነግሮኝ አመልክቼ፣ ጠርተው ፈትነውኝ ገባሁ።

የዛን ጊዜ የነበሩ 13 የግል ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ነበሩ። በጊዜው ግልጽ የሆነ ሕግ ስላልወጣም አንዳንዶቹ እንደ ‹ብሮከር›ም ሆነው ለውጪ ኩባንያዎች ይሠሩ ነበር። በኋላ ግን አንድ የኢንሹራንስ ሕግ ወጣ። ያም ለብሮከሮች አይፈቅድም፣ ሙሉ ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ለሆኑ እንጂ። ‹ካፒታልም› ላይ ገደብ አደረገ። በሕይወት ኢንሹራንስ ላይ ለሚሠሩና በዛ ላይ ለማይሠሩ ይህን ያህል ተብሎ ዝቅተኛው ካፒታል መጠን ተወሰነ።

ያኔ በንግድ ሚኒስቴር ውስጥ የኢንሹራንስ ቁጥጥር ክፍል አለ። ያ መሥሪያ ቤት በአዋጅ ተቋቁሞ ኢንሹራንስ ኩባንያዎችን ይቆጣጠር ነበር። ባወጣው አዋጅ መሠረት አንዳንድ ኩባንያዎች ካፒታል ስለማያሟሉ በአጭር ጊዜ ሥራ ለማቋረጥ ተገደዋል። በ1974 መስከረም ላይ ወታደራዊ መንግሥት ሥልጣን ከያዘ ሦስትና አራት ወራት በኋላ ኢንሹራንስ ኩባንያዎችና ባንኮችን ወረሰ።

ቀጥሎም ተቆጣጣሪ መሥሪያ ቤቱ ቆሞ የኢንሹራንስ ቦርድ ተቋቁሞ፣ የብሔራዊ ባንክና ከኢንሹራንስ ከዘርፉ ታዋቂ ግለሰቦች ያሉበት ቦርድ ተቋቋመ። ይህም የተወረሱትን የኢንሹራንስ ኩባንያዎች እንዲቆጣጠር ነው። ወዲያው እሱም ቀረና ባንኮችና ኢንሹራንሶች በብሔራዊ ባንክ ስር እንዲሆኑ የሚል አዋጅ ወጣ። እስከዛሬ ድረስም የኢንሹራንስ ኩባንያዎችን የሚቆጣጠረው ብሔራዊ ባንክ ነው።

ኢምፔርያል ኢንሹራንስ ኩባንያ ፈርሶ በመንግሥት በተወረሰበት ጊዜ የእርስዎ የሥራ ኃላፊነት ምን ላይ ነበር?
በምንወረስበት ጊዜ በኩባንያው ለዋና ሥራ አስኪያጁ የቅርብ ረዳት እና የሰው ኃይል አስተዳደር ኃላፊ ነበርኩኝ። የሥራ አስኪያጁን ፕሮግራሞች ማዘጋጀት፣ ሥራዎቹን በቅርብ ሆኖ መርዳትና የሠራተኞች ጉዳይ ኃላፊ ነበርኩ። ከዛ በኋላ ግን እንደገና ሲዋቀርና አዳዲስ ሥራ አስኪያጆች ሲመጡ፣ ሁሉም ሥራ አስኪያጆች የራሳቸውን የአሠራር መንገድ ስለሚፈልጉ፣ እንደገና የሰው ኃይል አስተዳደርና ጠቅላላ አገልግሎት ኃላፊ ሆንኩኝ።

በደርግ ጊዜ ብዙ ግርግር ስለነበርና እኔም ወጣት ስለነበርኩ፣ ባለው የፖለቲካ ቡድን ተጽእኖ ስር ሆኜ ለተወሰኑ ዓመታት ሥራ ላይ አልነበርኩም። ስድስት ወይም ሰባት ለሚሆኑ ዓመታት በእስራትም፣ በስደትም በማመጽም ቆይቻለሁ። ከእስር ስፈታና ስመለስ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ወዲያው ቀጠሩኝ። እንደ አጋጣሚ እኔን የሚያውቁኝ ሰዎች በተለይ ዋና ሥራ አስኪያጅ ጋር በቅርብ እንሠራና በደንብ ያውቁኝ ስለነበር፣ ተመልሼ እንድቀጠር ወዲያው ትዕዛዝ ሰጠልኝ።

ስመለስ አሁንም የአንድ ቅርንጫፍ የሰው ኃይልና የጠቅላላ አገልግሎት ኃላፊ ሆንኩኝ። በዚህ ቦታ ብዙም አልቆየሁም፣ ወዲያው ወደ ሕይወት ኢንሹራንስ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ሆንኩኝ። በዛም አምስት እና ስድስት ዓመት አካባቢ ከሠራሁ በኋላ፤ የሰሜን ምሥራቅ የሚባል ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ ሆንኩኝ።

በዛም አራትና ሦስት ዓመት ነወ የቆየሁት። ኢሕአዴግም ገብቶ ነበር። ታድያ ኢሕአዴግ የግል ኢንሹንስ ኩባንያዎች ይቋቋማሉ የሚል የኢኮኖሚ ማኒፌስቶ አወጣ። የግል ባንክና ኢንሹራንሶች የሚቋቋበት እድል እንዳለ የሚጠቁም ነው። በዛ ጊዜ ነው አዋሽ ባንክና አዋሽ ኢንሹራንስን ከሚመሠርቱ ሰዎች ጋር ተገናኝቼ፣ የኢንሹራንሱን የአዋጭነት ጥናት እንድሠራ ተደረገ፣ እሱን አዘጋጀሁ፣ ጨረስኩ። እንደጨረስኩም አደራጆቹም አዋሽ ኢንሹራንስና ኩባንያን አደራጅተው እንደጨረሱ፣ ኩባንያውን በዋና ሥራ አስፈጻሚነት እንድሠራ እድል ተሰጠኝና፣ የኩባንያው የመጀመሪያ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆኜ ጀመርኩ። ይህ እንግዲህ ከ25 ዓመት በፊት ነው። ከአዲስ ማለዳው ሳምሶን ብርሐኔ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርገዋል።

በ25 ዓመት ውስጥ የአዋሽ ኢንሹራንስ ጉዞ እንዴት ነበር?
ሁሉም አልጋ በአልጋ ነበር ማለት ያስቸግራል። ብዙ ችግሮችም፣ የተመቻቹ ሁኔታዎችም እያጋጠሙን ነው እዚህ የደረስው። መጀመሪያ ጥቂት ሆነን ነው ዘርፉን የተቀላቀልነው። አሁን 17 የግል ኢንሹራንስ ኩባንያዎች በዘርፉ ይንቀሳቀሳሉ። በዚህ ጊዜ ውስጥ በብዙ ነገር መፎካከር አለ፣ በምንሰጠው አገልግሎት፣ በምናስከፍለው ክፍያ፣ ሠራተኛ ከምንቀጥርበት ሁኔታ ጭምር ነው። የምንተባበርበት ብዙ ሁኔታም አለ።

እንደ እድል ሆኖ በትንሽ የጀመርነው፣ በተለይ እኔ የአዋጭነት ጥናት ላይ አስቀምጬው አሁን ያለንበትን ስመለከት፣ የተለየ ስሜት ይሰማኛል። ቀላል አይደለም ያለፍንበት። ምንአልባት በጣም የምንጣጣር ቢሆን ከዚህም በላይ ልናገኝ እንችል ነበር።

የዛሬ 26 ዓመት ቢሮ ማግኘት ራሱ አስቸጋሪ ነው። አሁን የሚታዩ ሕንጻዎች ያኔ የሉም። ከተማው ለ20 ዓመት አካባቢ እንቅስቃሴ ሁሉ የቆመበት አገር ነው። ቢሮ ማግኘት አስቸጋሪ ነበር። የአንበሳ ጫማ ቢሮ ነበር፣ ቄራ አካባቢ። እሱም ያልተመቻቸ ቢሮ ነበር፣ ተከራይን ባኩንም ኢንሹራንሱንም ልንጀምር ያሰብነው እዛ ነበር።
በአጋጣሚ ቦሌ ያለው ዐቢይ ቅርንጫፍ ያለበት ሕንጻ ገና በግንባታ ጅምር ላይ ነበር። እናም ከባለቤቶቹ ጋር ተነጋግነን እኛ ኹለተኛውን፣ ለባንኩ ሦስተኛውን ፎቅ ራሳችን ጨርሰን ለመግባት ተስማምተን፣ እኛው በራሳችን ገንዘብ ሠርተን ጨርሰን ገባንበት። ሥራ የጀመርነው በዛ ቢሮ ነው።

በጣም አስቸጋሪው ነገር ካፒታል ማሰባሰብ ነበር። የምንጠየቀውም ብዙ ገንዘብ አልነበረም። የሕይወት ኢንሹራንስ ከሌለበት ሦስት ሚሊዮን ብር በቂ ነበር። ያን ያህል የተከፈለ ካፒታል ካለ ወዲያው ፈቃድ ይሰጥ ነበር። ግን ያንን ብር ለማግኘት የነበረው ውጣ ውረድ ከባድ ነው። አንደኛ ገንዘብም የለም። ብዘ ሰው ገንዘብ የለም። ከዛ በፊት በነበረው ስርዓት ገንዘብ ያላቸው ሁሉ ተወርሶባቸዋል። ሰዎች ደግሞ ገንዘብ ያላቸው መሆኑ ከታወቀ እንወረሳለን የሚል ስጋት ስለነበር፣ ብዙ ሰው ገንዘብ እንዳለውም ማሳወቅ አይፈልግም፣ ቢኖረውም እንኳ።

እኛ ካፖታል መሰብሰብ ስንጀምር ይህ አገር ወደ 20 ዓመት እንዲህ ካለ ነገር ተለይቶ ስለኖረ፣ ባንክ ከፍተው፣ ትርፍ አምጥው ገንዘቤ እዚህ ላይ ማስቀመጥ አዋጭ ነው ወይ የሚለው ስጋትም ቀላል አልነበረም። አንዳንዶቹ እንደውም ዛሬ ሲነግሩን ‹ያኔ እንዲህ የሚያድግ አልመሰለኝም እንጂ፣ ያኔ የገዛሁትን 10 እና 20 እጥፍ መግዛት እችል ነበር።› የሚሉን ሰዎች አሉ። ስጋት ነበር። ለዛም በቂ ምክንያት አላቸው። ሥራው ለረጅም ጊዜ ተቋርጧል። ሰዉ አስተሳሰቡ ተቀይሯል፣ መንግሥት ብቻ ነው ባንክና ኢንሹራንስ የሚሠራው። ከእድሜም አንጻር ገንዘብ የሚኖራቸው ሰዎች የ30 እና 40 ዓመት ናቸው፣ የድሮውን ስርዓት አያውቁም፣ አያስታውሱም።
እናም በጣም አሰቸጋሪ ነበር። በኋላ ግን አትራፊ መሆኑ፣ እንደሚጠቅምና እንደሚያድግ ሲታይ፣ ግዙ ብለን የለመናቸው ሁሉ ብዙ እጥፍ ከፍለው ገዝተዋል።
የሰው ኃይል ማግኘቱም እንደዛው ነው። በጊዜው የነበረው የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ብቻ ነበር። ድርጅቱ ለዘርፉ መቋቋም ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል። እኔም ከዛ ነው የመጣሁት። ከዛ አንድ ሰው ብቻ ነው ቴክኒካሊ አቅምና ችሎታ ያለው ሰው አግኝቼ የወጣሁት። እኔና እሱ አንድ ላይ ሆነን አዳዲስ ልጆችን እያሠለጠንን፣ እያስተማርን፣ በእረፍትና በሥራ ሰዓትም እየሠራን እያሳየናቸው ነው ያሳደግናቸው።

በቁጥር የቴክኒክ ሥራ የምንሠራው አምስት አካባቢ ነበርን፣ በጠቅላላ ሙሉ ከጥበቃው ጀምሮ 12 ሆነን ነው የጀመርነው። እንደ አጋጣሚ ሆኖ ብዙ የማስታወቂያ ሥራ ስንሠራ ነበር፣ በመጀመሪያ ዓመት። እንደ ጥናቱ ቢሆን ኖሮ ከሦስት ዓመት በፊት ትርፍ እናገኛለን ብለን አላሰብንም። እንደ እድል ወይም እንደ አጋጣሚ ሆኖ ግን ከመጀመሪያ ዓመት ጀምሮ ነው አትራፊ የሆንነው።

ስለዚህ ከዛ ጊዜ ጀምሮ አዋሽ ኢንሹራንስ አንድም ጊዜ ኪሳራ አስመዝግቦ አያውቅም?
ከስረን አናውቅም። የመጀመሪያ ዓመት እንኳ አትራፊ ነበርን። አንድ ሚሊዮን ብር አካባቢ ነው የመጀመሪያ የተጣራ ትርፍ ያገኘነው።
ኢንሹንስ ኢንዱስትሪዎች አዳዲስ አገልግሎት አያስተዋውቁም የሚል ወቀሳ ይነሳል። አዋሽ ኢንሹራንስ ከዚህ አንጻር ሌሎቹ ጋር የሌለ ምን አዲስ ነገር አምጥቷል?
መጀመሪያ አዲስ አገልግሎት ወይም ምርት ብዙ የለም የሚባለው ነገር እውነት ነው። ነገር ግን አዲስ ገበያ እንዲኖር ገበያው ራሱ ማደግና መዳበር አለበት። አዲስ ነገር አምጥተህ እሸጣለሁ ስላልክ ብቻ አይገዙህም። የኢንሹራንስ ፍላጎት መኖር አለበት። ብዙ ጊዜ ብዙ ነገሮች አንዱ ይጀምራል ሌላው ይከተላል። አዳዲስ ነገር በፍጹም አልተዋወቅም አይባልም፤ ተደርጓል።

ለምሳሌ የፖለቲካ አደጋ ኢንሹራንስ ባለፉት አምስትና ስድስት ዓመታት ብዙ ንብረት ሲወድምና ሲቃጠል ስለነበር፣ ሰዎች ደግሞ ኢንሹራንስ ፈልገው የለም እየተባለ ይቸገሩ ነበር። ያንን እኛ ሥራ ላይ አውለናል፣ አሁን ብዙዎችም እያዋሉት ነው። ቀድሞ በተረጋጋ ሁኔታ የተነሳ ቢሆን ኖሮ ግን፣ ችግሩ ከሌለ ሰው አይፈልግም።
ለምሳሌ በፊት በሰሜን በኤርትራ ጦርነት የነበረ ጊዜ፣ ከሽፍታ ጋር በተገናኘ ሽፋን የሚሰጥ ኢንሹራንስ አገልግሎት ነበር። ልክ ኤርትራ ስትገነጠልና ጦርነቱ ሲያበቃ ግን ሰዎች ይህን ኢንሹራንሽ አንፈልግም አሉ። ዓላማው በእነዚህ ሰዎች [ሽፍታዎች] የሚደርሰውን ጉዳት ለመሸፈን ነበር። እና ዋናው ሕዝብ የሚገዛው ሲሆን ነው።
ከኢኮኖሚ እድገትና ከአካባቢ ሁኔታም ጋር የሚያያዝ ነው። እኛ ያደጉ አገራት የሚሸጧቸውን አይነት ኢንሹራንሶች አንሸጥም። ከዚህም አንዱ ምክንያት የካፒታል ገበያው ገና አላደገም። ሲያድግ የሚፈጠሩ የኢንሹራንስ ፍላጎቶች አሉ። እስከዛ ግን ገበያ ላይ ብታውልም ገዢ አታገኝም።

እርስዎ 25 ዓመት ረጅም ጊዜ ነው የቆዩት፣ በምን ምክንያት እንዲህ ሊቆዩ ቻሉ?
አሁንምኮ በቃኝ፣ ሰው አዘጋጅቻለሁ ብዬ ነው የተውኩት። እንዴት ቆየህ ለሚለው ያቆዩኝን መጠየቅ ይሻላል (ሳቅ)። ሥራ ትሠራለህ ተብዬ ነው፣ በየጊዜው ትርፉም እድገቱም ትርጉም ያለው ስለሆነ በዛ ምክንያት ይመስለኛል። ሰው የማዘጋጀት ነገር ግን ከ6 እና 7 ዓመት በፊት የሚተኩኝን አዘጋጅቻለሁ። ያዘጋጀኋቸው ሰዎችም በወጣትነት ዘመናቸው ይሥሩ ብዬ በፈቃዴ ነው ሥራ የለቀኩት። እንደውም አልበቃህም ተብዬ ከቦርድ ጋር ብዙ ተነጋግሬ ነበር። እና 25 ዓመት የቆየሁት ምንአልባት እድለኛ ሆኜ ወይም የማላስቸግር ሰው ሆኜም ይሆናል።

ብዙ ጊዜ የቦድርና የአመራር ክፍሉ ግንኙነትና ሥራ ላይ ያለመጣጣም ችግር አለ። ይህም ብዙ ጊዜ በባንኮች የሚነሳ ቢሆንም በኢንሹራንስ ኩባንያዎችም ያጋጥማል። ይህ ምን ያህል ፈትንዎታል?
ከብዙ የቦርድ አባላት ጋር ሠርቻለሁ። ቦርዱ በየሦስት ዓመቱ ይቀየራል። በእርግጥ ሁሉም ላይቀየሩ፣ አንዳንዶች 6 ዓመት ይሠራሉ። በዚህ ሁሉ ጊዜ ውስጥ እኔ ከቦርድ ጋር ይህ ነው የምለው በሐሳብ የመለያየት ወይም የቦርድ አባላት በሥራዬ ጣልቃ የመግባት ነገር አላየሁም፣ አልታየም። ጥያቄዎች ይኖራሉ፣ አንዳንዴ ወሬና አሉባልታ ይኖራል። ግን እውነት ከያዝክ ማንም ሰው ይቀበልሃልና አላስቸገረኝም፣ አላጋጠመኝም።

ግን በጣም የሚያስተውል ቦርድ ለማንኛውም ኩባንያ አስፈላጊ ነው። ድርሻውን አውቆ ማድረግ ያለበትን፣ አመራን ማገዝ ያለበትን ስልታዊ እቅድና አመራር ላይ ቢያተኩር ተግባብቶ መሥራት ይችላል።

ሆኖም ግን ቦርድኮ ሥራው ውስን አይደለም፣ ይሁነኝ ብለው ካልወሰኑት በቀር። ባለድርሻዎች ቦርድ የሚመርጡት ሁሉንም እንዲያይ ነው። የሚያየው ግን አመራሩን ለመረበሽና አሠራሩን ሰላም ለማሳጣጥት ሳይሆን ለድርጅቱ ጥቅም ከሆነ አያጣልም። አመራሩም ወደው ነው መቀበል ያለባቸው። ዓላማው እነዙን ገዝና ሥራው እንዲያድግ ማድረግ ከሆነ።

እኔ ግን በ25 ዓመት የሥራ ዘመኔ እንዲህ ያለ ነገር አልገጠመኝም። እድለኛ ሰው ሳልሆን አልቀርም።

በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ደሞዝዎ ምን ያህል አድጓል?
ደሞዝ ይነገራል እንዴ? የተቀጠርኩት በ2 ሺሕ 500 ነው። አሁን መጨረሻ ላይ 160 ሺሕ ብር ደርሻለሁ። ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞችም አሉ። የሕክምና፣ የትራንስፖርት የቤትና የመሳሰለው።

ምን ዓይነት የአመራር ስልት ነው የሚከተሉት፣ አንዳንዶች ቁጡ ናቸው ይላሉ?
ያሙኛል ማለት ነው (ሳቅ) ቁጡ መሆን የሚያስፈልግበት ሁኔታ ግን አለ። እኔ ለነገ የሚባል ነገር አልቀበልም። ነገ ስል በአንድ ሳምንት ወይም በወር ማለቅ ያበት ነገር በዛ ጊዜ ውስጥ ማለቅ አለበት። ካላለቀ የነገ ወዲያን ሥራ ትተህ እሱን ትጎትታለህ። እንዲህ ያ ነገር አልፈቅድም። ሥራ በወቅቱ መሠራት አለበት። ልጆችን ሳሠለጥን ያንን እንዳይቀበሉ በማድረግ ነው። አለበዚያ የምትመኘው ጋር መድረስ አትችልም።

የተለየ የአመራር ስልት የለኝም። ወቅቱ የጠየቀውን ነው የምሆነው፣ እንደ ሁኔታው ነው የምመራው። ዛሬ መሠራት አለበት የምለው ነገር ካለ ምክንያት ቢሰጡኝ አይሆንም። የማይሆን ከሆነ ለእኔም ይሰማኛል። የሚሆን ከሆነ ግን ይሆናል። ዛሬ ትንፋሽ ለማግኘት እንጂኮ ጨርሱ ከተባለ ሥራውን ይጨርሳሉ።

የኢንሹራንስ ዘርፉ ውስጥ 16 የሚሆኑ ኩባያዎች ተቀላቅለዋል። አሁንም ግን ድርሻው ለአገራዊ ጠቅላላ ምርት አንድ በመቶ እንኳ አይሞላም። ኢትዮጵያ ደግሞ በኹለት አሃዝ የኢኮኖሚ እድገት እንዳስመዘገበች ይነገራል። ኢንሹራንስ ዘርፉ እንዴት ከኢኮኖሚ እድገቱ ጋር አብሮ መራመድ አቃተው?
ኢትዮጵያ በሕዝብ ብዛት ከአፍሪካ ኹለተኛ ናት። ከዚህ ሕዝብ የሚገኘው የሕይወት ኢንሹራንስ ግን ኬንያ ከእኛ በግማሽ በሚያንስ የሕዝብ ብዛት ከሚገኘው በጣም ያነሰ ነው። ግን በተለያየ መንገድ የሚገደዱበት ሁኔታ ከሌለ፣ ለምሳሌ ከባንክ የማይበደር ሰው ቤቱን ኢንሹራንስ አያስገባም። ከተበደረ ብቻ ነው ቤቱን ኢንሹራንስ የሚያስገባው።

ትንንሽ ፋብሪካ ያለውም ሰው ቢሆን የባንክ ብድር ሲፈልግ ነው ኢንሹራንስ የሚታየው፣ እንጂ በራሱ ተነሳሽት ኢንሹራንስ አያስገባም። ስለዚህና የሕይወት ኢንሹራንስ ደግሞ በጣም ዝቅተኛ ደረጃ ያለ ስለሆነ፣ አንድ በመቶ አይደለም ከዜሮ ነጥብ አምስት በመቶ በታችም በታች ነው። ይህ መቀየር አለበት። ለዚህ ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያደርገው የኢንሹራንስ ግንዛቤ ማሳደግ ነው።

ስለዚህ የሚወቅሱት ሕዝቡን ነው ማለት ነው?
ሕዝቡን አይደለም። ዘርፉን ነው። ግንዛቤን የማስፋት ኃላፊነት የዘርፉ ነው፣ በጋራ፣ መንግሥትም ተባብሮት። ለመንግሥት የሚያደርገውን አስተዋጽኦ አክብዶ ለማየት እድል አልተገኘም፣ ለመግለጽም አልቻልንም። ለምሳሌ የሕይወት ኢንሹራንስ ላይ ለኢንሹራንሱ ከሚከፈል ፕሪምየም ላይ ታክስ እንዳይከፈል መንግሥት ቢፈቅድ ቀላል እድል አይደለም። መንግሥት ይህን አላደረገም፣ እኛም በበቂ ይህን ለመንግሥት አልገለጽንም።

የኢንሹራንስን ጥቅም ሕዝብ እንዲያውቅ ለማድረግ የሚኖረው እድል በመገናኛ ብዙኀን መጠቀም ነው። መገናኛ ብዙኀን ትኩረታቸው መዝናኛው ነው። ስለኢንሹራንስ እናስተዋውቅ ብንል ከፍተኛ ክፍያ ካልከፈልን እሺ አይሉም። ከኢንሹራንስ የሚሰበሰበው ገንዘብ ለአገር እድገት ይጠቅማል የሚለውን አስተሳሰብ በሕዝብም፣ በመንግሥትም፣ በመገናኛ ብዙኀንም፣ ሁሉም ላይ መፍጠር ኢንዱስትሪው አልቻለም።

በጋራ መሥራት ይጠበቅበታል፤ ለማስተማር። እንጂ ሕዝብማ በማያውቀው ነገር አይወቀስም። እንዲያውቅ በበቂ ሁኔታ አልተሠራም።

ማኅበሩ ይህን ማድረግ አልቻለም?
ሁሉም ሐሳቡን ይገዛል። ወደ ተግባር ልንገባ ስንል ግን በብቃት ማድረግ አልተቻለም። አንድ ቀን ግን መደረጉ አይቀርም። ጠቃሚና አስፈላጊ ነው።
የግል ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ፕሪምየም ሬታችሁ አነስተኛና ያልተለመደ፣ ትርጉም የማይሰጥም ነው ይባላል። በዚህ ላይ ምን ይላሉ?
ይህ በጣም እውነት ነው። የፉክክርን ዓላማ በአግባቡ ካለመረዳት ይመጣል። ማንም ኢንሹራንስ ኩባንያ፣ ትርጉም የለውም ብሎ በሕዝብ እስኪወቅስ ድረስ ያነሰ ፕሪምየም ማስከፈሉ፣ ለዘርፉም አሳዛኝ ነው። አንዱ ፉክክሩ ሲሆን ሌላው የሚሸጡትን አገልግሎት ወይም ምርት፣ የትኛው ነው ትክክለኛ ፕሪምየም፣ ምን ብቀበል ነው ካሳ ሲመጣ ልከፍል የምችለው ብሎ የማሰብ፣ እርግጠኛም ሆኖ ለመወሰን እውቀት ይፈልጋል።

ፉክክሩ መኖሩ በእርግጥ ለተጠቃሚ በጣም ጥሩ ነው። በመጨረሻ ግን የሚጎዳው ተጠቃሚውም ጭምር ነው። እነዚህ ሰዎች ካሳ መክፈል ባይችሉ፣ አንድ አደጋ ቢደርስና ኢንሹራንስ ለገባው ሰው የሚጠብቀውን መክፈል ባይቻል ያ ትንሽ ፕሪምየም ትርጉም አይኖረውም። ለዚህ መነሻው አንደኛው የእውቀት ቸግር ነው። ኹለተኛ ተስፋ የመቁረጥ ነገር ይነሳል፣ ሥራ ሲጠፋና ምርት ከሌለ ምንም ክፍያ መፈጸም አይቻልም። ስለዚህ ከሌላው ያነሰ ቆርጦ ለመግባት ይገደዳል። ትልቅ ጥንካቄና የሙያ ታማኝነት ይፈልጋል። ሕዝቡ እንዲህ እስኪል ድረስ መውረድ የለበትም።

መንግሥት በአንዳንድ ፖሊሲዎች ላይ ኢንሹራንስን አስገዳጅ ማድረግ አለበት ብለው ያስባሉ?
ቢያደርግ ለሕዝብ ጥሩ ነው። ለምሳሌ የቤት ኢንሹራንስ። ብዙ ሰዎች ቤታቸውን ያከራያሉ፣ ሌላም ነገር ይሠሩበታል። ኢንሹራንስ ግን አያስገቡም። አንድ ኮንዶሚንየም ቢቃጠል ያን ቤት መልሰው ካልሰሩት ያ ሁሉ ሰው ችግር ውስጥ ነው የሚገባው። እንዲህ ላሉት አዋጥተውም ቢሆን ኢንሹራንሰ ቢገዙ ተስፋ አለ። የተወሰኑ ወራትን ዘመድ ወይም ኪራይ ቤት ቆይተው ሊገቡበት ይችላሉ። እና ለሕዝብም ለመንግሥትም ጥቅም አላቸው።

እና በምሳሌ ያነሳነው የቤት ኢንሹራንስ አስገዳጅ ቢሆን ጥቅም አለው። በዚህ ላይ ዋጋውም በጣም ይቀንሳል። ብዙዎች በተሳተፉ ቁጠር ፕሪምየሙ እየቀነሰ ይሄዳል። ብዙ የማይጎዳ ፕሪምየም ለመክፈልም ያስችላል። እና አስገዳጅ መሆን ያለባቸው አንዳንድ ጉዳዮች ይኖራሉ።

የሕይወት ኢንሹራንስ ያላደገበት ምክንያት ምንድን ነው ብለው ያስባሉ፣ የግንዛቤ ችግር እንዳለ ሆኖ?
አንዱ የግንዛቤ ችግር ነው። የባህልም የሃይማኖትም ተጽእኖም አለ። እግዚአብሔር ያውቃል፣ በእድሉ ያድጋል ይላል። በእድሉ ሊያድግ ይችላል፣ እንደሚፈለገው ግን አያድግም። ማደግ ያልቻለው ዋናው ነገር እንዳልነው ግንዛቤ ነው። ከዛ በኋላ ግን ለቤተሰብ የምናሳየው ፍቅር ምንድን ነው? አንድ አባት እኔ አንድ ነገር ብሆን ልጆቹ በምን ያድጋሉ ብሎ ለምን አያስብም? ለምን ኬንያዊ አባት እንደዛ አያስብም፣ ለምን ኢትዮጵያዊ አባት በእድሉ ያድጋል ይላል። ይህ በጣም የሚያሳስብ ነው።
ምናልባት ችግሩ ደግሞ የሕይወት ኢንሹራንስን አንድ አሻሻጭ ሲሸጥ፣ ብዙ የሚያስከፍሉትን ስለሚያነጋግሩ ሊሆን ይችላል። በትንሽ ፕሪምየም የሕይወት ኢንሹራንስ የሚሸጥበት ‹ተርም ኢንሹራንስ› የሚባል አለ። ይህም ሰው ሲሞት ብቻ የሚከፈል ነው።

ይህን ዓይነቱን ኢንሹራንስ መሸጥ አይደለም የተለመደው። የተለመደው በመሃሉ ብድር ብትፈልግ ልትበደርበት የምትችል፣ ውልህን ብታቋርጥ በየጊዜው የሚጠራቀምና የሚያድግ ወዘተ የሚባለው ነገር ገዢውንም ሻጩንም ስለሚስብ፣ ለሞት ብቻ የሚከፈለውን ኢንሹራንስ ብዙ አናስተዋውቅም፤ ማንም አያስተዋውቅም። አሻሻጩ ኮሚሽን ላይ ነው የሚያተኩረው።

ሰፋፊ የንግድ አሠራር ይዘህ ሕዝብ የምታሳውቅበት፣ ክፍያን በባንክ የምታደርግበት መንገድ ቢሆን ሁኔታዎች ይመቻቻሉ። ግን ጥቂት ሰው ብቻ ከሆነ ለዚህ የሚወጣው ወጪ ራሱ ከፍተኛ ይሆናል።

ኢንሹራንስ ጥቂት ሀብታሞችን የሚያሳስብ ጉዳይ አይደለም። እነርሱ ገዙም አልገዙም ሀብታሞች ናቸው፣ ልጆቻቸው የሚማሩበት አያጡም። ግን ብዙ ከቤተሰብ የተወረሰ ወይም በራሱ ሀብት የሌለው፣ መካከለኛ ገቢ የሚያገኘው በብዙ ሺሕ የሚቆጠር ነው። እነዚህ ለቤተሰባቸው የሕይወት ኢንሹራንስ ቢገዙ ቀላል ገበያ አይደለም።

ኢንሹራንስ እንደ ዘርፍ በቂ ትኩረት ሲሰጠው አይታይም። በብሔራዊ ባንክ ራሱ የበለጠ ትኩረት የሚሰጠው ለባንክ ነው እንጂ ለኢንሹራንስ አይደለም። ይህንን ክፍተትስ እንዴት ያዩታል?
በአንድ ወቅት አንድ የብሔራዊ ባንክ ገዢን ‹ትኩረታችሁ ሁሉ ባንክ ላይ ነው። ኢንሹራንስም በእናንተ ስር እንዳለ የምታውቁ አትመስሉም› ስለው፣ አንድ በመቶ እንኳ ለጠቅላላ አገራዊ ምርት የማታበረክቱ፣ ምን ተብሎ ነው ስለእናንተ ብዙ የሚወራው ዓይነት መለስ ሰጠኝ። እውነት ነው። ግን ዘርፉ በአንዳንድ አገሮች ጠቅላላ ዓመታዊ ምርት 15 እና 16 በመቶ ያበረክታል።

እና እድሉ ከተሰጠውና ካደገ፣ 10 በመቶ እንኳ ቢያበረክት፣ በዚህች አገር እድገት ላይ የሚኖረውን ጠቅላ አስተዋጽኦ ማየት ይችላል።ይህ ደግሞ የጥሬ ገንዘብ ነው። ያም ለብዙ ሥራ ማስፋፊያ ይውላል። እናም ይህን ማበረታታት በጣም ጠቃሚ መሆኑን ተቆጣጣሪ መሥሪያ ቤቱ ብዙ ትኩረት እንደማይሰጠው መሆኑ ይሰማል።
ሕዝቡም ቢሆን እኔና የባንክ ፕሬዝዳንት አብረን ስንሄድ፣ እኔን ዞር ብሎ አያይም፣ የባንኩን ፕሬዝዳንት እንጂ። አሁን ያለው እይታ ይህ ነው። ይህም አብረን የምንኖረው እውነት ነው። ግን መንግሥት ትኩረት መስጠትና እንዲያድግ አስተዋጽኦና እገዛ ማድረግ አለበት። ለዚህ መሠረት የሚፈጥሩ ነገሮችን ማሰብ አለበት። በመገናኛ ብዙኀን ስለዚንሹራንስ ሊነሳ ይገባል። ያኔ ሕዝቡም እንዲያውቀው ይደረጋለ። ኢንሹራንስ በጣም ትኩረት ያልተሰጠው ነው፣ በመንግሥትም፣ በጋራም። በጋራ ብንጮኽምኮ መንግሥት ይሰማን ነበር፣ ግን አልጮኽንም።

አሁን ባለው ሁኔታ ምን ፖሊሲ ለውጥ ይጠብቃሉ?
ለሕይወት ኢንሹራንስ የሚከፈል ፕሪምየም ላይ ግብር እንዲቀር። ሌላ ተለይ በከተማ ያሉ ቤቶች የግዴታ ኢንሹራንስ እንዲገቡ ቢደረግ። ይህን ማድረግ ሕዝብን ይጠቅማል፣ የሚከፍሉትንም ፕሪምየም እንዲያንስ ያደርጋል። በተጨማሪ ቢያንስ የመንግሥት መገናኛ ብዙኅን የተወሰነ ሰዓት ኢንሹራንስን ለማስተማር ቢሰጡ። ለዚህም ዘፍሩ ብዙ ሳይጠየቅ በጋራ መጠነኛ እንዲከፍሉና ሕዝቡ ስለኢንሹራንስ የሚሰማበት የሚውቅበት መድረክ እንዲኖር ግዴታ ቢደረግ።

የፖለቲካ አለመረጋጋትና ሽብርተኝነትን በሚመለከት ኢንሹራንስ ከወጣ መጀመሪያ ፍላጎቶች ነበሩ። በኋላ ግን ምንም እንኳ አለመረጋጋቶች ቢቀጥሉም ባለሀብቶች መልሳቸው እንደተጠበቀው አልሆነም። ለምን ይሆን?
ሰዎች ሁልጊዜ አደጋ ካለ ነው፣ ከሌለ ኢንሹራንስ አይገዙም። የእሳት ኢንሹራንስ ግዙ ስትላቸው፣ የሚቻል ቢሆን እሳት ሲቃጠል ቢገዙ ይሻላቸዋል። ሌላ ጊዜ ገዝተው፣ ኹለትና ሦስት ዓመት ‹ቤቱ አልተቃጠለም፣ ዝም ብዬ ነው የምከፍለው› ይላሉ። ነጋ ጠባ የሚደጋገም ችግር ካልሆነ በቀር ለምን እከፍላለሁ የሚል ስሜት ነው ያለው።
ይህ የፖለቲካ አለመረጋጋትና የሽብርተኝነት ኢንሹራንስ ሲጀመር፣ መጀመሪያ በየቦታው ብዙ ነገር ይቃጠል ነበር። ያኔ የብዘ ሰው ጭንቀትም ይህ ነው። ሲረጋጋ ግን የሚቀጥለው ላይ አንፈልግም ይላሉ። የዚህ ዓይነት ፖሊሲዎች ባህሪያቸው ይህ ነው። ሰዎች የኢንሹራንስ ፍላጎታቸው የሚቀንሰው አደጋው የማይታይና ሩቅ ሲመስላቸው ነው።

በኢትዮጵያ በዘርፉ የሠለጠነ የሰው ኃይል ማግኘትን በሚመለከት፣ ባንክና ኢንሹራንስ ላይ በተቋም ደረጃ ትምህርት አይሰጥም። ያስ ችግር አይደለም?
ችግር ነው። ዘርፉ የባለሞያ ማሠልጣኛ የለውም። በፊት በብሔራዊ ብንክ ስር የኢትዮጵያ ኢንሹራንስና ባንኪንግ የሚባል ተቋም ነበር። እሱም ተሻሽሎና አድጎ ኢንሹራንስ ትምህርት ማሠልጠኛ ተቋም ይቋቋማል ሲባል ቆየና፣ ከፍተኛ ትምህርት ኮሚሽን ለሚባል ተቋም ይመስለኛል፣ ተሰጥቶ ሥልጠናውም ቆመ።
እርግጥ ብዙ ባለሞያ አይደለም የሚፈልጉት። ሰው በገፍ ተመርቆ ባንክና ኢንሹራንስ የሚቀጥርበት ሁኔታ አልተፈጠረም። ይሁንና ዘርፉን የሚያግዝ ማሠልጠኛ ተቋም ያስፈልጋል። ይህን ከብሔራዊ ባንክ፣ ከሚመለከታቸው ጋር ንግግር ተደርጓል። በቅርቡ ሥራ ላይ ያሉ ሰዎች የተወሰነ ሥልጠና የሚያገኙበት፣ የኢንሹራንስ እውቀታቸውን የሚያሳድጉት ቦታ ቢኖር፣ አዳዲስ ሠራተኞች ሲገቡ ደግሞ ኢንሹራንሽ ምንድን ነው፣ እንዴት ይሠራል የሚል ሥልጠና ቢወስዱ፣ የበለጠ ጥሩ ነው። የዚህ አለመኖር ዘርፉ በልድም እንጂ በትምህርት የታገዘ እንዳይሆን አድርጓል።

አዋሽ ኢንሹራንስስ የትምህርት እድል በውጪ እንዲገኝ በማድረግ፣ በ25 ዓመት ቆይታ እንዴት ይህን መፍጠር ሳይችል ቀረ?
ለአንድ ኩባንያ የተወሰነ ሥራ እንዲሠራ ካልሆነ በቀር፣ በዓመት አንዴ ነው ቅኝት የሚያስፈልገው። ለዘርፉ ግን ያስፈልጋል። ለአዋሽ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም። ተጋላጭነቱ አንድ ዓይነት ነው። ስለዚህ ለዘርፉ ያገለግላል። ለአንድ ተቋም ግን ብዙም ወሳኝ አይደለም። ለዘርፉ የሚሰራውም ነው ተጨባጭ ለውጥ ሊያመጣ የሚለው።
አንዳንድ በጣም ትልልቅ ኢንሹራንስ ኩባንያዎች፣ በብዙ ሺሕ የሚቆጠር ሠራተኛ ያለቸው፣ እንዲህ ያለ አንድ ወይም ኹለት ባለሞያ ይኖራቸዋል። ግን የኢትዮጵያን ኢንሹራንስ ዘርፍን የሚቃኝና የሚገመግም፣ የሚመዝን ባለሞያ ያስፈልጋል። ለአንድ ኩባንያ ግን በቋሚነት አያስፈልግም።

ለምን እንደኩባንያ እናንተ አልፈጠራችሁም ከተባለ፣ አላውቅም፤ ያንን ያሰበ ኩባንያ ያለም አይመስለኝም። ግን ኢንሹራንስን በተመለከተ የሚማሩና ፈቃደኛ የሆኑትን ገንዘብ እየከፈልን ውጪ ድረስ እናስተምራለን።

ቅጽ 2 ቁጥር 82 ግንቦት 22 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here