ለኹለት ዓመታት የውሃ ክፍያቸውን ያልፈፀሙ ተቋማት መኖራቸው ታወቀ

0
595

• እስከ 6 ሚሊዮን ብር ድረስ ውዝፍ ዕዳ ያለባቸው ተቋማት አሉ

የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ኹለት ዓመት ሙሉ የውሃ አገልግሎት ክፍያቸውን ያልፈፀሙ ከ3 ሺሕ 5 መቶ በላይ ትላልቅ ተቋማት መኖራቸውን አስታወቀ።
ባለሥልጣኑ ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቀው፣ ውዝፍ ዕዳ ያለባቸው እነዚህ የተለዩ ተቋማት ከዚህ በኋላ ከኹለት ወር በላይ ክፍያቸውን የማያጠናቅቁ ከሆነ አገልግሎቱን የማቋረጥ እርምጃ እንደሚወስድም አስጠንቅቋል።

ብዛታቸው 3 ሺሕ 543 የሆኑት ትልልቅ ተቋማት ብዙ የውሃ ተጠቃሚ ያላቸው ሲሆን፣ በዚህም በአንድ ተቋም እስከ 6 ሚሊዮን ብር ውዝፍ ክፍያ ያለባቸው እንዳሉም ተናግረዋል። ደምበኞቹ ወርሃዊ የአገልግሎት ከፍያቸው በጊዜ ባለመፈፀማቸው ምክንያት የኮሮና ቫይረስ ኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመከላከል እየተከናወነ ያለው ሥራ ፈታኝ እንዳደረገበት ነው ባለሥልጣኑ ያስታወቀው።

ባለሥልጣኑ አነስተኛ ከፋይ የሆኑት ክፍያቸውን በተገቢው መንገድ እንደሚያጠናቅቁ ጠቅሶ፤ ነገር ግን ይሄ ችግር በተደጋጋሚ እየታየ ያለው ከፍተኛ ተቋማት ላይ እንደሆነም አስታውቋል።

በተጨማሪም ባለሥልጣኑ ካሉት 570 ሺሕ ደምበኞች ውስጥ ከመጋቢት 26 እስከ ሚያዚያ 18 ቀን 2012 ድረስ የአንድ ወር አገልግሎት ክፍያ የፈፀሙት 28 በመቶ የሚሆኑት ብቻ እንደሆነ አስታውቋል። ባለሥልጣኑ አያይዞም ዋና ዋና የአገልግሎት ተጠቃሚ ናቸው ከተባሉት መካከል ሆስፒታሎች፣ የመንግሥት መሥርያ ቤቶች፣ የግል እና የመንግሥት ሆቴሎች ሲሆኑ ክፍያቸውንም በጊዜ የማይፈፅሙት እነዚሁ ተቋማት እንደሆኑም ጠቁሟል።

የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ሰርካለም ጌታቸው ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፤ ባለሥልጣኑ በአሁኑ ወቅት ከኮቪድ-19 ቅድመ መከላከል ጋር በተያያዘ አገልግሎቱ እንዳይቋረጥ 24 ሰዓት እየሠራ እና ለደንበኞቹ ተገቢውን አገልግሎት እየሰጠ ነው። ሆኖም ግን ተገልጋዮቹ ወቅቱን ጠብቀው የአገልግሎት ክፍያ እየፈጸሙ እንዳልሆነ አንስተው፣ ከኹለት ወር እስከ ሦስት ዓመት የሚደርስ ውዝፍ እዳ ያለባቸው መሆናቸውን ነው የተናገሩት።

በተጨማሪም እንደ ሰርካለም ገለፃ፣ የብዙ ጊዜ ውዝፍ ካለባቸው ተቋማት አጠቃላይ ከ64 ሚሊዮን ብር በላይ ክፍያ አለመፈጸሙን ተናግረዋል። ከውዝፍ እዳ ጋር በተያያዘ ከዋና ዋና ተቋማት እና ከመደበኛ ደንበኞቹ ደግሞ ከ362 ሚሊዮን ብር በላይ አለመከፈሉን ገልፀዋል። በመሆኑም ባለሥልጣኑ ለዋና ዋና የተቋማት ደንበኞቹ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤዎችን በተለያየ ጊዜ ከመላክ ባሻገር በየተቋማቱ የውሃ ቆጣሪ አንባቢዎችን በመላክ ያለባቸው እዳ እየተከማቸ እንደሆነ ለማሳወቅ እየተሞከረ እንደሆነም ታውቋል።

ይሁን እንጂ እስከ አሁን ከተቋማቱ ምላሽ ባለመሰጠቱ አገልግሎቱን ለማቋረጥ እንደሚገደድ የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣን መሥርያ ቤት የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሯ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ባለሥልጣን መሥርያ ቤቱ 80 በመቶ የሚሆነውን ገቢ የሚያገኘው ከደንበኞች በሚሰበስበው የአገልግሎት ክፍያ እንደሆነ የገለጹት ዳይሬክተሯ፤ ‹‹ክፍያው በአግባቡ እስካልተፈጸመ ድረስ አገልግሎት መስጠት እያዳገተን ይገኛል›› ብለዋል።

ነገር ግን አሁንም የአገልግሎት ክፍያቸውን በወቅቱ የፈጸሙት ደንበኞች የማይቋረጥ የውሃ አቅርቦት እንደሚኖራቸው በመግለጽ፤ ‹‹የአገልግሎት ክፍያቸውን ያልፈጸሙት ግን ከቅጣትና ከባንክ ወለድ ጋር እንዲከፍሉ ይደረጋል›› ብለዋል። በዋናነት ተቋሙ ራሱን በራሱ የሚያስተዳድር እንደመሆኑ መጠን የራሱን ገቢ ይሰበስባል። የተሰጡት ኃላፊነቶችም በዛው ልክ ናቸው።

ነገር ግን ለሰጠው አገልግሎት ተገቢውን ክፍያ ካላገኘ ደግም ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ማከናወን የሚጠበቅበትን ተግባር ይገድበዋል የሚሉት ዳይሬክተሯ፣ መሥርያ ቤቱ ከፍተኛ የሆነ የነዳጅ ወጪ እንዳለበት አውስዋል። በዚህም ‹‹አብዛኛውን ጊዜ ኤሌክትሪክ ሲቆራረጥ ጄነሬተሮችን ስለምንጠቀም፤ የተሽከርካሪዎች የነዳጅ፣ ለተለያዩ አቃዎች ጥገና የምናስፈፅምበት ወጪ በዋነኛነት ደግሞ የሠራተኛ ደሞዝ ክፍያን ለማስፈፃፀም ከፍተኛ ችግር ውስጥ ተቋሙን እያስገባው ነው።›› ሲሉ ሰርካለም ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 82 ግንቦት 22 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here