‘አንተ’ እና ‘አንቺ’

Views: 453

“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።

አንድ ርዕሰ ጉዳይ ከሳምንት የዘለለ ዕድሜ አልኖር ብሎት እንጂ አንድ ሰሞን ይህም መነጋገሪያ ሆኖ ነበር። እንዲህ ነው፤ ብዙ ነገሮችና ምሳሌዎች ጭምር የሚገለፁት በወንድ አንቀጽ ነው። እኔም እንኳን ስለዚህ ነገር ስፅፍ በወንድ አንቀፅ እየፃፍኩ ነው። የሃይማኖት መጻሕፍትም የሰውን ልጅ አንተ ይሉታል። በምድርም ምክረ ሐሳብ የሚሰጡ ሰውን ‘አንተ’ እያሉ ነው።

እና በመንፈስም ሆነ በሥጋ ሕግ፤ “አድርግ አታድርግ” የተባለው ለወንዶች ብቻ ነው? በአማርኛ ስንናገር ነገሩ ሁሉ በወንድ አንቀጽ፤ መልዕክቱ ሁሉ ለወንድ ይመስላል። ለሴቶች ምንም ተነግሮ አያውቅም ማለት ነው? ለምንስ “አድርጊ አታድርጊ” አይባልም? ምናልባት ልማድ ነው። ከፍ ሲል ግን ነገሩ የቋንቋ ችግር እንጂ ሰው ሆነ ብሎ አላደረገውም። አይመስላችሁም?
በማውቀው ላብራራ፤ ለምሳሌ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች አገር አንቱ ማለትም መባልም አይታሰብም። ወዲህ በግዕዝ ቋንቋ ደግሞ አንቱታ ባይኖርም ሴቶችን እንዱሁም ወንዶችን እያንዳንዳቸውን በብዙ ቁጥር የሚገልፅ፤ አልፎም ኹለቱንም ፆታ የቀላቀለ ብዙ ቁጥር የሚሸከም ቃል አለ። በብሔራዊ የሥራ ቋንቋችን አማርኛ ደግሞ ነገሮችን ለመግለፅ በወንድ ወይም በሴት አንቀጸ ኹለት ምርጫ ይገኛል።

ከዚህ አንጻር የሚታዩ ቋንቋዎች ይኖራሉ። በእርግጥ በየነገራችን መካከልም በወንድ አንቀጽ የጠራነውን ሁሉ በሴት አንቀጽ መድገም፤ ወይም ነገሩን ሁሉ በብዙ ቁጥር እናንተ እያልን ልንገልፅ እንችላለን። ይህ ግን ተናጋሪንም ሆነ ፀሐፊን ማድከም ነው ብዬ አምናለሁ።

ጉዳዩ ከቋንቋ ነው። አማርኛ ቋንቋ የታደለውና ያለው አቅም ቢኖርም፤ ነገሮችን ግዑዝ አድርጎ መግለፅ ግን አይችልም። ስለአንድ ነገር ለማብራራት ‘ጉዳዩ’ ሲል አንባቢ ወይም አድማጭ ቢላመደውም ትኩረት በሰጠ ጊዜ ግን ገለፃው በወንድ አንቀጽ የተደረገ እንደሆነ መረዳት ይቻላል። በየዕለት እንቅስቃሴና ንግግራችንም ተመሳሳይ ነው።

እንግዲህ እህቶቼ…በስምምነት የሚደረጉ አሠራሮች አሉ። ለምሳሌ በተለያዩ በሕገ መንግሥትና በተለያየ መመሪያዎች ላይ በተናጠልና በአንደኛ እንዲሁም በኹለተኛ መደብ የሚገለፁት ነጥቦች ላይ ይህን እናያለን። በየነገሩም ‘ባለጉዳዩ’ ሲል በኅዝባር አስከትሎ ‘ባለጉዳይዋ’ ይላል። እንግዲህ ከግማሽ በላይ መሆናችን እሙን ነውና ቅደም ተከተሉ ይስተካከል ይሆናል።

ሰው መስማት የተሳነው እንደሆነ በምልክት ቋንቋ በሚጠቀምበት ዓለም፤ ቋንቋን መሰረት አድርጎ አውራጃና ቀበሌን በድንበርና ክልል ከፍሎ መቧቀስ የሞኝ ጨዋታ ነው። እንደዛው ሁሉ እኛም በነገሮች አጠራርና አሰያየም መነጋገር የለብንም። ብንችል የሚያስማማን ቃላትን እንፍጠር። ሰው ሲል ወንድን ብቻ እንዳይደለ እንደምናውቅ ሁሉ ቋንቋውም ያንን እንዲነግረን ማድረግ እንችላለን።

መቅደስ /ቹቹ/
mekdichu1@gmail.com

ቅጽ 1 ቁጥር 32 ሰኔ 8 2011

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com