ሕዳሴው ግድብ፡- የኢትዮጵያ፣ ግብፅ እና ሱዳን ፍጥጫ

0
495

ከተደጋጋሚ የሦስትዮሽ ድርድር ክሽፈት በኋላ በግብጽ ተጽዕኖ ፈጣሪነት ድርድሩ በአሜሪካ መንግሥት እና በዓለም ባንክ ‘‘ታዛቢነት’’ (በሒደት ምንም እንኳን ታዛቢነቱ ወደ አደራዳሪነት ብሎም እጅ ጥምዘዛ ቢለወጥም) በድጋሜ በዋሽንግተን ዲሲ ላይ ኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን እንዲቀጥሉ ቢደረግም ድርድሩ በኢትዮጵያ ተቃውሞ መቋረጡ ይታወሳል። የድርድሩ መቋረጥ በተለይ ግብጽ የምትይዝ የምትጨብጠውን አሳጥቷታል፤ ከላይ ታች አባትቷታል። ግብጽ ኢትዮጵያ ላይ አንዳንዴ የጦር ነጋሪት ለመጎሰም ዝግጅት እያደረገች መሆኑን በመለፈፍ እና በማስለፈፍ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ በዲፕሎማሲው መስክ ተጽዕኖ ለማድረስ በመቅበዝበዝ እንዲሁም የተሳሳቱ መረጃዎችን በዓለም ዐቀፍ መደበኛ ብዙኀን እንዲሁም ማኅበራዊ ትስስር መድረኮች በመንዛት ኢትዮጵያ በመጪው ሐምሌ ላይ ልትተገብር ያቀደችውን ግድቡን ውሃ የመሙላት ሒደት ለማደናቀፍ ክፉኛ ባዝናለች።

ግብጽ የሱዳን መንግሥት ላይ ተጽዕኖ በማሳደርም አቋማቸውን እንዲላዋውጡ ብርቱ ጫና አሳድራለች። የሱዳን መንግሥት እንደቄጠማ እጥፍ ዘርጋ እያለ አቋሙን እየለዋወጠ ይገኛል። አንዳንዴ ከኢትዮጵያ ጎን መሆኑን ይገልጻል፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ የግብጽን አቋም እንደ ገደል ማሚቶ ያስተጋባል። በርግጥ ኢትዮጵያ በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሱዳን ሰላማዊ ሽግግር እንድታደርግ አይተኬ ሚና ከመጫወታቸው ባሻገር ከእርስበርስ ጦርነት ታድገዋታል። በአጭሩ ሱዳን የኢትዮጵያ ውለታ አለባት ለማለት ይቻላል። ከሕዳሴው ግድብ ከምታገኘው ትሩፋት ባሻገር ይህ ውለታ ሳይሆን አይቀርም ከኢትዮጵያ ጎን እንድትሰለፍ ያደረጋት፤ በሌላ በኩል ደግሞ የግብጽ ጫና ሲበረታ ደግሞ በአቋም መዋዠቅ ትላጋላች።

የሱዳንን ፖለቲካ ውስጥ አዋቂ ነን እንደሚሉት ከሆነ ሱዳን የሕዳሴ ግድብን በተመለከተ ውልውል ውስጥ የገባችው በትረ መንግሥቱን በያዙት ሲቪሎች እና ወታደራዊ መኮንኖች ባላቸው የአቋም ልዩነት መሆኑን ያሰምሩበታል፤ ሲቪሎቹ ከኢትዮጵያ ጎን ሲሆኑ ወታደሮቹ ደግሞ ከግብጽ ጎን መሆናቸውን በመጥቀስ። ይሁንና ሱዳን የሦስትዮሽ ድርድሩ እንዲካሔድ ከማሳሰብ አልፋ ለተባበሩት መንግሥታት በጻፈችው ደብዳቤ ኢትዮጵያ ሐምሌ ላይ ከምታካሒደው የውሃ መሙላት ሒደት በፊት የሦስትዮሽ ድርድሩ መካሔድ አለበት፤ በፍትሐዊ የውሃ ክፍፍሉም ላይ ስምምነትም ላይ መድረስ አለብን ብላለች።

ሌላው ሰሞነኛ ከሕዳሴው ግድብ ቱማታ ጋር ተያይዞ ሥሟ ሲነሳ የነበረችው ደቡብ ሱዳን ነች። ‘ጁባ’ በሚባል የቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ የተላለፈው እና በሰፊው በማኅበራዊ ትስስር መድረኮች የተሰራጨው ግብጽ በደቡብ ሱዳን ግዛት የጦር ሰፈር እንድታቋቋም ፈቀደች የሚለው ‘‘በሬ ወለደ’’ ዜና ነው። ይሁንና ደቡብ ሱዳን አፍታም ሳትቆይ በውጪ ጉዳይ ሚኒስቴሯ በኩል አስተባብላለች። በተጨማሪም መቀመጫቸው አዲስ አበባ የሆኑት የደቡብ ሱዳን አምባሳደር በኤምባሲያቸው በጠሩት እና የዓለም ዐቀፍ እና የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኀን በተገኙበት የመንግሥታቸውን አቋም በማያወላዳ ሁኔታ አስታውቀዋል።

አምባሳደሩ ደቡብ ሱዳን ለማንኛውም የውጪ ኀይል የጦር ሰፈር እንደማትሰጥ አበክረው ገልጸዋል። አምባሳደሩ ኢትዮጵያ ለደቡብ ሱዳን መንግሥት እና ሕዝብ የዋለችውን ወለታ አንረሳም፤ በአሁኑ ወቅት እንኳን በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች ኢትዮጵያ ውስጥ ተጠልለው ይገኛሉ በማለት ኢትዮጵያ ተፈጥሮ የሰጣትን ውሃ በፍትሐዊነት ለመጠቀም የምታደርገውን ጥረት እውቅና መስጠት ብቻ ሳይበቃቸው መብቷ ነው ሲሉ በአጽንዖት ገልጸዋል። ‘‘ኢትዮጵያን ለማጥቃት ያሰበ ኀይል በደቡብ ሱዳን በኩል ሊመጣ ቢያስብ እንኳን ቀድሞ የሚጋፈጠው የደቡብ ሱዳን መንግሥት እና ሕዝብ ነው’’ ሲሉም ድጋፋቸውን ለኢትዮጵያ ገልጸዋል።
ይሁንና አንዳንዶች ግብጽ በአባይ ወንዝ ላይ ኢትዮጵያ እየገነባችው ያለውን የሕዳሴ ግድብ ለማደናቀፍ የማትፈነቅለው ድንጋይ የለም ሲሉ በደቡብ ሱዳን ላይ የተናፈሰውን የጦር ሰፈር ግንባታ በቀላሉ መታለፍ የለበትም ሲሉ አሳስበዋል።

በሕዳሴው ግድብ ዙሪያ የኢትዮጵያ መንግሥት፣ ምሁራን፣ ፖለቲከኞች እና ተርታው የኅብረተሰብ ክፍል እንደ አንድ ልብ አሳቢ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ‘‘አባይ የኔ ነው’’፣ ‘‘የግድቡን ውሃ ሙሌት በተመለከተ እና የውሃ ክፍፍል ድርድር ይሉት ብሎ ቧልት የለም’’ ሲሉ ፍፁም ተመሳሳይ አቋማቸውን አንጸባርቃወል። አንዳንዶች ጉዳዩ ውሾቹ ይጮሀሉ ግመሉ ግን ጉዞውን ቀጥሏል ሲሉ ሌሎች ደግሞ ጅብ ከሔደ ውሻ ጮኸ ነው ሲሉ የግብጽን መፍጨርጨር አቃልለዋል።
የአባይ ወንዝ ጉዳይም ሆነ ወንዙን ተንትርሶ በመገንባት ላይ ባለው ታላቁ የሕዳሴው ግድብ አነጋጋሪነት አሁንም ሆነ ወደፊትም ማብቂያ ያለው ግን አይመስልም።

ቅጽ 2 ቁጥር 83 ግንቦት 29 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here