የአዲስ ዘመን ጋዜጣ 79 ዓመታት በነጻነት ወይስ በፍረጃ?

0
1709

በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኀን ታሪክ ይልቁንም በኅትመት በኩል ሥማቸው ከሚነሳ ቀደምት ከሆኑና ሦስት መንግሥታትን ዘልቀው ካለፉ መካከል አዲስ ዘመን ጋዜጣ ይጠቀሳል። ከዚህ ጋዜጣ በቀር ይህን ያህል ዘመን የተሻገረ ጋዜጣም የለም። ጋዜጣው በየጊዜው በተለያየ አንጻር ሥሙ የሚነሳ ሲሆን፣ የተጠበቀበትን አልሠራም ከሚሉ ጀምሮ፣ እንዳይሠራ የመንግሥት ጫና አለበት የሚሉ እይታዎች ይሰነዘሩበታል። ለሥነጽሑፍ ያበረከተው አስተዋጽኦ የሚወደሰውን ያህል፣ በአንጻሩ የመንግሥት ልሳን ነው ተብሎ ይወቀሳል።
ነጻነት የለውም የሚሉ በርካቶች ሲሆኑ፣ በአንጻሩ ተፈርጄ እንጂ ሥራዬን በአግባብ እየሠራሁ ነው ይላል፤ ጋዜጣው። በተመሳሳይ በአንድ በኩል የመንግሥት ባለሥልጣናት ጫናና ‹በራሴ ጋዜጣ አትንኩኝ› ባይነት አመራሮችን በየጊዘው ሲያስጨንቅ ሲታይ፣ በሕዝብ በኩል ደግሞ ‹ስለእኛ አልተነገረም› የሚል ክስ አለ። ጋዜጣው በዚህ ሁሉ መካከል ዘመናትን ኖሯል። ከታሪክ ሰነድነትም አልተቀነሰም።
ከባህር በቅርፊት የመጨለፍ ያህል ከታሪኩ በጥቂቱ፣ እንዲሁም ከጋዜጣው ጋር በተያያዘ የፈጠረውን ተጽእኖ፣ ችግሮቹንና ምን ይጠበቃል የሚለውን በሚመለከት በማንሳት፣ የአዲስ ማለዳዋ ሊድያ ተስፋዬ ጉዳዩን የሐተታ ዘ ማለዳ ጉዳይ አድርጋዋለች።

በነበር አምድ
ግንቦት 30 ቀን 1933፤ ከፊት ገጹ ላይ ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በአውቶሞቢል ሆነው በአጀብ የሚሄዱበት ምስል ተሰይሟል። ይኸውም አርበ ጠባብ ቁመቱ 42፣ ስፋቱ ደግሞ 31 ሴንቲ ሜትር የሆነው ከራሱ ላይ ‹አዲስ ዘመን› የሚል ርዕስ በጉልህ የታተመበት ብሔራዊ ጋዜጣ ነው። አዲስ ዘመን ጋዜጣ።።
የጋዜጣው ምሥረታ ኢትዮጵያ ከጣልያን ነጻነቷን ማስመለሷን ተከትሎ ንጉሠ ነገሥቱ ወደ መንበራቸው ሲመለሱ ከከወኗቸው ቀዳሚ ተግባራት መካከል ተጠቃሹ ነው። ሥያሜውም የተወሰደው አፄ ኃይለሥላሴ ካደረጉት ንግግር ሲሆን፣ ይህም «ከማናቸውም አስቀድሞ ለሁላችሁ ልነግራችሁና ልትረዱት የምፈልገው ይህ ቀን ለአዲሲቱ ኢትዮጵያ የአዲስ ዘመን መክፈቻ መሆኑን ነው። በዚሁ በአዲሱ ዘመን ሁላችንም መፈጸም ያለብን አዲስ ሥራ ይጀመራል» የሚል ነበር።

አዲስ ዘመን ከዛን ጊዜ የጀመረ ጉዞው ቀጥሎ በጊዜ ሂደት ጉዞውን ከተቀላቀሉት ኢትዮጵያን ሄራልድ፣ በሪሳ ጋዜጣ፣ ዘመን መጽሔት፣ አልዓለም ጋዜጣ ጋር፣ በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ስር ታቅፎ ዘንድሮ (2012) ልክ ነገ እሁድ፤ ግንቦት 30 ሲሆን 79ኛ ዓመቱን ይደፍናል።

ጋዜጣው ከይዘት አንጻር አብዛኛው የሚይዛቸው ጽሑፎች ስለ ንጉሠ ነገሥቱ ክብርና ስለ አገር ፍቅር የሚሰብክ እንደነበር ይነገራል። የጋዜጣው 75 ዓመት ልዩ ሕትመት ላይ እንደሰፈረውም፣ በኋላ ላይ የግሪክ ፈላስፋዎችን ሥራዎች በተከታታይ በማተም ሕዝቡ እንዲያውቅና እንዲመራመር ሰፊ ጥረት ይደረግ ጀመር። «ይሁን እንጂ…» ይላል ጽሑፉ፤ «ይሁን እንጂ የዜናም ሆነ የርዕሰ አንቀጽና የአስተያየት ገጽ አልነበረውም። አንዳንድ ጽሑፎችም ልክ እንደ ሃይማኖታዊ መጻሕፍት «በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ» ብለው የሚጀምሩ ነበሩ»

የዚህ ምክንያቱ ምንድን ነው ከተባለ፣ ዋና አዘጋጆቹም ሆኑ ሠራተኞቹ የቤተክህነት ሰዎች ስለነበሩ ነው። የመጀመሪያው የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዋና አዘጋጅም ብላታ ወልደጊዮርጊስ ወልደዮሐንስ ነበሩ። እርሳቸውም በጋዜጣው ታሪክ ለረጅም ጊዜ በአዘጋጅነት የቆዩ ሲሆን ይህም በዘመን ከምሥረታው ዓመት 1933 እስከ 1953 ድርስ የዘለቀ ነው።

ጋዜጣው መጀመሪያ ይታተም የነበረው በየሳምንቱ ሲሆን፣ ከ15 ዓመታት በኋላ ግን ወደ እለታዊ ጋዜጣነት ተሻገረ። ዋጋውም በተመሳሳይ በ79 ዓመታት ውስጥ በጣም በጥቂት ሳንቲዎች ነው ለውጥ ሲያሳይ የኖረው። አሁን ላይ ጋዜጣው በ5 ብር ከ75 ሳንቲም እንደሚሸጥ የጋዜጣው የፊት ገጽ ላይ ሰፍሮ የሚገኝ ሲሆን፣ በአምስት ሳንቲም የተሸጠበት ጊዜም ነበር። ከ1938 ጀምሮ አርበ ሰፊ ሆኖ እንዲሁም የገጹ ብዛት ወደ ስምንት ሲያድግም፣ ዋጋው ያው አምስት ሳንቲም ነበር። ለውጪ አገር ደንበኞች ደግሞ በእጥፍ ይጨምራል፣ ዐስር ሳንቲም።

በ2006 ግንቦት 30 ቀን፣ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አሁን የሚገኝበትን ሕንጻ አስገንብቶ ጨርሶ ባጠናቀቀበት ጊዜ [ከምሥረታው ጀምሮ ለ73 ዓመታት ቋሚ መሥሪያ ቦታ አልነበረውም] ያስነበበው ‹አንፀባራቂ ተስፋ› የተሰኘ ልዩ እትም ስለጋዜጣው ታሪክ አትቷል። በዛም መሠረት ጋዜጣው ከተመሠረተ ጀምሮ እስከ 1953 ድረስ እጅግ አድካሚ ጉዞ እንደነበረው ይጠቅሳል። ይህም የሆነው በጋዜጠኝነት ሙያ የተደገፈ ባለመሆኑ ነው ይላል። ጋዜጣው በባለሙያ ደረጃ ጋዜጠኞችን አሰማርቶ መንቀሳቀስ የጀመረው በጋዜጠኝነት ትምህርት ሠልጥነው ወደ አገራቸው የተመለሱት ነጋሽ ወልደማርያም ዋና አዘጋጅ ሆነው በተመደቡ ጊዜ ነው፣ እንደ ጽሑፉ ገለጻ።
ነጋሽ በጋዜጣው 75ኛ ዓመት ላይ ይህን ጉዳይ ሲያወሱ፣ አዲስ ዘመን አዘጋጅ ተብለው መሰየማቸውን ተከትሎ በጋዜጣው የፊት ገጽ ላይ የሚወጡ ንጉሡን ብቻ የተመለከቱ ዜናዎች ናቸው ሲባሉ ደንግጠው እንደነበር ጠቅሰዋል። ይልቁንም ሕዝባዊ ጉዳዮችም መስተናገድ አለባቸው ሲሉ ሞገቱ። ይሁንና ሐሳባቸው በቀላሉ ተቀባይነትን እንደማያገኝ ስላወቁ፣ ቀስ በቀስ ለማድረግ ወሰኑ።

እናም የወትሮው ንጉሡን የተመለከቱ ዜናዎች ከፊት ገጽ ሳይቀሩ፣ ከግርጌ ሌሎች ዜናዎችን ማስገባት ጀመሩ። ያም እያደር ሲለመድ፣ አልፈው የአስተያየት ገጽን በኹለተኛው ገጽ ላይ እንዲሆን አደረጉ። በሂደትም የጋዜጣውን ቅርጽና ይዘት ቀይረው ዘመናዊ መልክ አስያዙት። የተለያዩ አምዶች እንዲጨመሩም አስቻሉ።
በዚህ ሂደት የተጀመረ ለውጥ ቀጠለ። የጋዜጣው አዘጋጆች ሲቀየሩ ሁሉም የየራሳቸውን አሻራ ማሳረፍን ቀጠሉ። ብርሃኑ ዘሪሁን፣ በዓሉ ግርማ፣ ማዕረጉ በዛብህ፣ ጎሹ ሞገስ፣ መርዕድ በቀለ፣ ፀሐዬ ደባልቀው፣ እምሩ ወርቁ፣ ደምሴ ጽጌ፣ ሐሰን ኡስማን፣ አንተነህ ኃይለብርሃን፣ ወንድምኩን አላዩ፣ ንጉሥ ወዳጅነው፣ ፍቃዱ ሞላ እንዲሁም አሁን ላይ በዋና አዘጋጅነት በድጋሚ እየመሩ ያሉት አንተነህ ኃይለብርሃን እና ሌሎችም በዋና አዘጋጅነት በቅብብል አዲስ ዘመንን አዘጋጅተዋል።
ታዛቢ ሊረዳ እንደሚችለው ዛሬ ላይ ቀላል የሚመስሉ የተለመዱ ጉዳዮች አስቀድሞ ለማምጣት ብዙ ሂደቶችን ማለፋቸው ነው።

ጋዜጣው ታድያ ይበልጥ ከሥነ ጽሑፋዊ አበርክቶው አንጻር ሲመሰገን ይሰማል። ከላይ የተጠቀሱት በዋና አዘጋጅነት ጋዜጣውን የመሩት፣ አብዛኞቹም በሥነጽሑፍ አንቱታን ያገኙ ተጠቃሽ ሰዎች ናቸው።

የአዲስ ዘመን ስድሳኛ ዓመት ልደት የተከበረ ጊዜ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ጽሑፍ ባለሙያ ዘሪሁን አስፋው ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፍ እንዲህ ሲሉ አስፍረዋል፤ «…አዲስ ዘመን የዘመኑን የሥነጽሑፍ አቅጣጫ ማስያዝና ሥነጽሑፋዊ ሂስን ለማስለመድ በር ከፍቷል። ብዙ መጻሕፍት ባይታተሙም ያሉት እንዲነበቡ በማስቻል ጉልህ ሚና ነበረው»

ይህንኑ ለኪነጥበብ ዘርፍ ያበረከተውን አስተዋጽኦ በሚመለከት፣ የጋዜጣው 78ኛ ዓመት ላይ መዓረጉ በዛብህ ጥቂት ብለዋል። ብርሃኑ ዘሪሁንን እንዲሁም በዓሉ ግርማን የጠቀሱት መዓረጉ፣ ‹‹ብርሃኑ ትልቅ የሥነ ጽሑፍ ሰው ስለነበር ጋዜጣውን ትልቅ ያደርገዋል፣ በዓሉም ተነባቢ ርዕሰ አንቀጾች ነበሩት።›› ብለዋል። እርሳቸውም በ1970 ወደ አመራርነት ሲመጡ፣ የጋዜጠኝነት ተማሪ ስለነበሩ የገጽ አቀማመጥ፣ አሠራር፣ ፎቶዎች እንዴት እንደሚታረሙና መሰል አዳዲስ እይታዎችን በማምጣት ከሥራ ጓደኞቻቸው ጋር ለውጥ እንዳመጡ ያስታውሳሉ።

ከይዘት አንጻር ታድያ የልጆች፣ የሴቶች፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ አዲስ አበባን በየእለቱ፣ እሁድ እንዴት አለፈ፣ አንድ ጥያቄ አለኝ፣ መድረክ፣…ወዘተ ተጠቃሽና የማይረሱ የጋዜጣው አምዶች ናቸው።

በድምሩ አዲስ ዘመን በቆይታው ከ60 በላይ አምዶችን ያቀረበ ሲሆን፣ ከ1.7 ሚሊዮን በላይ ዜና እና ጽሑፎችን አትሟል። በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ስር የሚገኘው አዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዲሁም የኢትዮጵያን ሔራልድ ጋዜጣ፣ ከ11 እና 12 ሺሕ ሲታተም፣ ሳምንታዊው በሪሳ 9 ሺሕ፣ አረብኛው አልዓለም 2 ሺሕ፣ ዘመን መጽሔት ደግሞ 2 ሺሕ ይታተማሉ። የጋዜጣው ሕትመት በተጀመረ ጊዜ የዘውድ በዓል፣ የንግሥ ቀን፣ በበዓላት እስከ 40 ሺሕ ኮፒ ሲታተም በአዘቦቱ እስከ 10 ሺሕ ይታተም ነበር።

ዕድሜና አገልግሎት
ከላይ እንደተጠቀሰው ታድያ ‹አዲስ ዘመን ጋዜጣ› አዲስ ዘመን የሚለውን ሥያሜ ያገኘበትን ምክንያት የመጀመሪያው የጋዜጣው ሕትመት ላይ ሲብራራ እንዲህ ተበሏል፤ «ይህ አዲስ ዘመን ተብሎ የተሰየመው ጋዜጣ ከዛሬ ጀምሮ ወደፊት ለመላው ለኢትዮጵያ ሕዝብ የረዳትነቱን ሥራ ይሠራ ዘንድ ተመሠረተ።» ታድያ ዛሬ ላይ የብዙዎች ይልቁንም ጋዜጣውን በሥምና በዝና የሚያውቁት ይህን ጥያቄ ያነሳሉ። ዛሬ አዲስ ዘመን ያለበት ደረጃ ምንድን ነው? የተባለለትን የረዳትነት ሥራ እየሠራ ነው ወይ?

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት ትምህርት ክፍል መምህርት አጋረደች ጀማነህ (ዶ/ር) ሥራ የጀመሩት በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ነው። አሁን ላይ ታድያ እንደ ጋዜጠኝነት ባለሞያና እንደ መምህርነት ጋዜጣው ስላበት ሁኔታ ትዝብትና ሙያዊ እይታቸውን አዲስ ማለዳ ጠይቃቸዋለች።

አንድ የሕዝብ መገናኛ ብዙኀን ትክክኛ መልኩና መገለጫው ሕዝብን ማገልገል መሆኑን አንስተዋል። ይህም ሲባል የሕዝብን ጥያቄና ጉዳይ እንዲሁም ስጋት ለሚመለከታቸው አካላት ማቅረብ፣ ለፖሊሲ አውጪዎች የሚረዱ ሐሳቦችን ማቅረብ፣ የሕዝብን ጉዳይ አጀንዳ አድርጎ እያነሳ ሕዝብን ወግኖ መሥራትም ይጠበቅበታል። ከሕዝብ ጋር ወግኖ ለሕዝብ የሚያስፈልገውን ሲያነሳና ችግሮችንም ሲጠቅስ፣ በዚህ ከመንግሥትም ጋር እየሠራ ነው ይባላል። ይህ ታድያ ከመንግሥት የሚሰጠውን ወደታች ማውረድ ብቻ ሳይሆን የሕዝብንም ሐሳብ ለመንግሥት ማቅረብንም ይጠይቃል፤ እንደ አጋረደች ገለጻ።

ያም ብቻ ሳይሆን ሕዝብን የሚያስተዳድሩ መሪዎች ያሉትን ፈጽመዋል ወይ፣ መመሪያና ደንቦች ተተግብረዋል ወይ፣ ሕጎች ተፈጻሚ ሆነዋል ወይ የሚሉትን ጥያቄዎች ያነሳል። ይህ የአንድ መንግሥት መገናኛ ብዙኀን በጽንሰ ሐሳብ ደረጃ ያለው መልክ ነው።

ታድያ ከዚህና ረጅም ዘመን ከማስቆጠሩ አንጻር፣ አዲስ ዘመን ጋዜጣ የሚጠበቅበትን ተወጥቷል ወይ ቢባል፣ ‹‹ተወጥቷል ብሎ መደምደም አይቻልም። አልተወጣም ማለትም አይቻልም።›› ሲሉ ነው አጋረደች የመለሱት። እንደ እርሳቸው ገለጻ፣ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ኹለቱንም አቅጣጫዎች ይዞ ሲሠራ ነበር። ‹‹እንደ መንግሥት ጋዜጣ የሠራው አለ፤ ያልተወጣባቸውም መስመሮች አሉ።›› ሲሉ በአጭሩ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅና የዘርፍ ጉዳዮችን በዋናነት የሚከታተሉት ሔኖክ ስዩም (ዶ/ር) ከአዲስ ማለዳ ጋር አጠር ያለ ቆይታ አድርገዋል። በዚህም አዲስ ዘመንን ጨምሮ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋዜጦች በተለያየ ጊዜ የተለያየ ደረጃ ነበራቸው በማለት ይጀምራሉ። በየወቅቱ ተቀባይታቸው ይለያይ ሲሉም፣ ምንም ተወዳዳሪ ያልነበረበትና አዲስ ዘመን ጋዜጣ ብቻውን ተነባቢ የነበረበት ጊዜም እንደነበር አውስተዋል።

እንደ ሔኖክ ገለጻ፣ በይዘት ደረጃ አገር ውስጥ ካሉ ጋዜጦች አዲስ ዘመን ጋዜጣን የሚስተካከል የለም። ‹‹ባደረግነው ለውጥ ምክንያት፣ በይዘት ደረጃ ተወዳዳሪ ብቻ ሳይሆን የሚደርስብን የለም ብለን ነው የምንይዘው።›› በማለት ገልጸዋል።

‹‹የፕሬስ ድርጅት ሕትመቶች ትክክለኛ ሥያሜ የሕዝብ የሚል ነው። ስለዚህ ያንን እናስጠብቃለን።›› ያሉት ሔኖክ፣ ሕዝብ በመንግሥት ይወከላልና፣ የመንግሥትን ፍላጎት በማንጸባረቅ ውስጥ የሕዝብ ፍላጎት ይገኛል ሲሉ ጠቅሰዋል። ‹‹በተጨባጭ ያሉንን አምዶችን ማየት ይቻላል። አንደኛው ሕዝብ የሚፈልገው ጉዳይ ችግሩን መግለጥ፣ እንግልቱን ማውጣት ነው። ለዚህ የዋለ አምድ አለን። ለምሳሌ ፍረዱኝ የሚል አምድ አለ። ያሉትን ችግሮች የምናሳይበት ነው። ተቋማት ከተልዕኳቸው አንጻር ሥራቸውን እየሠሩ ነው ወይ ብለን እንጠይቃለን።›› ሲሉ አስረድተዋል። ይሁንና ከዚህ በላይ መሄድ አለብን የሚል አቋም አለን ሲሉ አክለዋል።

እድሜና ግብር
እድሜ ሲጨምር መብሰል ይከተላል። ትላንት ለዛሬ የበለጠ ማጠናከሪያ እየሆነ፣ ዛሬ ደግሞ ለነገ መሠረቱን እያጸና የሚቀጥለውን ጉዞ ለመቀባበል ያግዛል። አዲስ ዘመን ጋዜጣ ብዙ ጋዜጣዎች ብቅ ብለው ሲጠፉ፣ አብበው ሲረግፉ፣ ደርሰው ሲመለሱ የታዘበ፣ ብዙ ያሳለፈ ጋዜጣ ነው። ለዚህ የመንግሥት ጋዜጣ መሆኑ ጠቅሞታል፣ ለሁሉም አገልጋይ መሆኑ አትርፎታል የሚሉ ጥቂቶች አይደሉም። ያም ሆነ ይህ ግን፣ አሁን ላይ የሚገኝበት አቋምና ቁመና እንደ 79 ዓመት በሳል አዛውንት ነው ወይ?
ዋለልኝ አየለ በጋዜጣው በሪፖርተርነት ለአራት ዓመታት አገልግሏል፣ አሁንም በማገልገል ላይ ይገኛል። ጋዜጣውን ከዩኒቨርሲቲ ተማሪነት ጀምሮ እንደሚያውቀው የሚያስታውሰው ዋለልኝ፣ በተማረበት የጋዜጠኝነት ትምህርት መምህራን የሚሰጣቸው ሥራ ብዙውን ጊዜ አዲስ ዘመንን እንዲያገላብጥ ምክንያት እንደሆነው ያወሳል። ለንባብ ካለው ቅርበት የተነሳ በግሉም ቢሆን ጋዜጣውን የማገላበጥ ልማድ አለው። ታድያ ትኩረቱ ጥበባዊ ጉዳዮች፣ መዝናኛ ገጾችና በአንጋፋው ጋዜጠኛ ሐዲስ እንግዳ የሚዘጋጁ የውጪ አገር ዜናዎች ነበሩ ።

በእርሱ አስተያየት ከኹለት ዓመት ወዲህ በጋዜጣው ላይ ያሉ ጥሩ የሚባሉ ለውጦች ቢኖሩም፣ አዲስ ዘመን እንደ እድሜው አይደለም። ‹‹ምክንያቱም 79/80 ዓመት የቆየ ጋዜጣ ነው። ሦስት ስርዓት አሳይቷል። ከንጉሡ ጀምሮ እስከ አሁን። ሰንዶ ታሪክን በማስቀመጥ ሰነድ መሆን ችሏል። በዛ ልክ ግን ተጽእኖ አልፈጠረም። አሁንም ላይ የሚጠራው በፊት የነበሩ ጸሐፊዎች ሥም ነው።›› በማለት ያነሳው።

እርሱ እንደሚለው ከሆነ ጋዜጣው ባለው አቅም የምርምር ዘገባዎችን በመሥራት ተጽእኖ መፍጠር ይችል ነበር። አንጋፎችና ተነባቢ፣ ተሰሚ የሆኑ አቅም ያላቸው ሰዎችንም ለመሳብ ጫና አላደረገም ባይ ነው። የዜና አጻጻፍን ጨምሮ የተለያዩ ሥልጠናዎችን መስጠት አለመቻሉ በዚህ እድሜው የሚጠበቅ አልነበረም። በቤተ መጻሕፍትና በአርካይቭ ደረጃ ሰዎች ምርምር የሚያደርጉበት የታወቀ ቤተ መጻሕፍት ሊኖረው ይገባ ነበር በማለትም ያነሳል። አሁን ባለው ሁኔታ እድሜውን በትክክል ተጠቅሟል ማለት እንደሚከብድም ነው ያነሳል።

አጋረደችም በዚህ ላይ ተመሳሳይ አስተያየት ሰጥተዋል። በንግግራቸውም ጋዜጣው አሁን ላይ የሚጠበቀውን ሆኗል ወይ ከተባለ አይደለም ወይም አልሆነም ብለዋል። ይህንንም ከጋዜጠኞች አቅም፣ ከተቋሙ የሙያ ተቋም አለመኖር፣ ጋዜጠኞች በሙያው ራቸውን የሚያሳድጉበት መንገድ አለመኖርና ወዘተ ምክንያት ነው ብለዋል። አሁን ላይ በሰው ኃይል በማጠናከርና በሙያም በመምራት፣ ዳግም የቀድሞ ተቀባይነቱን እንዲያገኝ ማድረግ እንደሚቻል ግን ሳይጠቅሱ አላለፉም።
‹‹አዲስ ዘመን ብዙ ጋዜጦችን አልፎና አሳልፎ ነው እዚህ የደረሰው። ጥንካሬውም ድክመቱም ዘመንና ወቅትን እንዲሁም ማኅበረሰቡን ነው የሚመስለው። 79 ዓመቱን እንደ መማሪያ ሊጠቀምበት ይችላል። እንደ እድል ተጠቅሞበት ለሌሎች አረአያ ሊሆን የሚችልበትን መንገድ ማውጣት አለበት። በዛም ወደፊት የጋዜጠኝነት ሙያ ሥነምግባርን ሊያርቅና ሊመራ የሚችል ሆኖ ሊያድግ ይችላል።›› በማለት ሐሳባቸውን ገልጸዋል።

ችግር 1 – ነገረ ፍረጃ
ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጁ ከአዲስ ማለዳ ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ ጋዜጣው ያሉበትን ችግሮች አንስተዋል። ከሁሉም ከሁሉም ግን የመፈረጅን ነገር አጥብቀውና ደጋግመው አንስተዋል። በተለይም ለአንባቢ ተመራጭ ከመሆን ጋር በተያያዘ ጋዜጣው መፈረጁ ፈተና እንደሆነባቸው ነው የጠቀሱት። ‹‹የመንግሥት አንደበት ናቸው የሚል ፍረጃ አለ። ይዘትን ገምግሞ ከማየት ይልቅ በነበረው ፍረጃ ሳያዩ መሄድ ይስተዋላል። በዚህ ምክንያት በሚፈለገው ደረጃ ተነባቢ ነን ማለት አንችልም። በዚህ አጋጣሚ አንባቢዎች ከመፈረጃቸው በፊት አንዴ እዩን እላለሁ።›› ሲሉም መልእክት አስተላልፈዋል።

ዋለልኝም ይህን ሐሳብ ይጋራል። ምንም እንኳ በድርጅቱ (የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት) እንዲሁም ከሚጠበቁ ውጤቶች አንጻር በአሠራር ላይ ብዙ ክፍተቶች ቢኖሩም፣ ፍረጃው እንዳለ አጽንኦት ይሰጣል። ‹‹በዚህ ጊዜ ለሚዲያ ሚዛናዊ መሆን ከባድ ነው። ማኅበራዊ ሚዲያና የፖለቲካ መበሻሸቅ አለ። የትኛውም ወገን ሥሙ ቢነሳ ሌላው መሳደቡ አይቀርም። እውነታን ይዞ መሄድ እንጂ መመስገን አይኖርም።›› ሲል ትዝብቱን ያነሳል።

በአገር ውስጥ ያለውን የማኅበረሰብን የሚድያ ግንዛቤም ዝቅተኛ መሆኑ፣ አሉባልታ፣ በጣም የሚጮኸ [ከተለመደው ወጣ ያለ] ነገር እንዲወደስ አድርጓል ባይ ነው። ‹‹ይህ [አዲስ ዘመን ጋዜጣ] ደግሞ እንደ መንግሥት ጋዜጣ ሕዝባዊ ኃላፊነት ስላለበት ውስጥ አዋቂ ምንጮች ነገሩኝ እያለ መጥቀስ የለበትም። በዛ መልኩም ዘገባ አያወጣም። ያንን ጠንካራ ጎኑን ሰዎች አያዩም። በጥቅሉ የመንግሥት አንደበት ነው ይሉታል። ሐሰተኛ ዜና የሚሠሩት ሳይቀሩ ‹እሱማ የመንግሥት ልሳን ነው› ነው የሚሉት። እናም ጭፍን ፍረጃው አለ።›› በማለት ሁኔታውን ያስረዳል።

የጋዜጠኝነት መምህርቷ አጋረደች ግን በዚህ ሐሳብ አይስማሙም። ‹‹ከተነበበ ተነቧል ነው። ሰው ሳያነበው ነው የሚተቸው የሚል ሐሳብ ማስረጃ አይሆንም።›› ሲሉ ተናግረዋል። ይህን ለማለትም ሕዝቡ ውስጥ ገብቶ ጥናት ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

‹‹አይነበብም ማለት አይቻልም። በነበዓሉ ጊዜ በጣም የተነበበ ነው። በጣም የተነበበበት [በአዘጋጆች ለውጥ] ጊዜ አለ። የሰዎች ትኩረት ይቀያየራል። የስርጭት ጉዳይም መወሰን አለበት። ሕዝብ ጋር ሳይደርስ ተነቧል አልተነበበም ማለት አይቻልም።›› ሲሉ ነው ያስረዱት።

ነገር ግን አመራሩ ጋር እንደዛ ዓይነት ጫና እና ስሜት ካለ፣ እቅድ ነድፎና ገፍቶ አንባቢ ጋር መድረስ ያስፈልጋል ሲሉም ይሞግታሉ። ‹‹ሰዎች መረጃ ይፈልጋሉ። አሁን በቅርብ ጊዜ እንዳየሁት አዲስ ዘመን ጋዜጣ ምንጭ ተብሎ በተለያየ ቦታ ይጠቀሳል። የምርመራ ዘገባ እየጀመሩ ነው ያሉት። አሉባልታን መስበር የሚቻለው የግድ ሕዝቡ ጋር መድረስ ሲቻል ነው።›› ብለዋል።

ፍረጃ ግን በጋዜጠኛ ባለሞያ ደረጃም እንደሚኖር አልደበቁም። የመንግሥት ጋዜጠኛም ‹የመንግሥት ጆሮ ጠቢ፣ የመንግሥት ሰባኪ› እንደሚባል ያነሳሉ። ፍረጃ እንደ አገር በባህላችን ውስጥ ያለ እሳቤ ነው ያሉ ሲሆን፣ ዓለም ዐቀፍ የሆኑ መገናኛ ብዙኀን ሳይቀር ከፍረጃ እንደማይወጡ ጠቅሰዋል። ለምሳሌም በአሜሪካ መገናኛ ብዙኀን ተጠቅሶ ‹እገሌ የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ደጋፊ ነው፣ እገሌ ተቃዋሚ ነው› እንደሚባል አያይዘው አንስተዋል።

ሕዝብ ግን የሚፈልገውን ካገኘና ከተሰጠው ከማንበብ ወደኋላ እንደማይመለስ፣ የግል ጋዜጦችን ማንበብ በሚያስቀጣበት ጊዜ ሳይቀር ብሶባቸው ተደብቀው ገዝተውና ደብቀው የሚያነቡ ሰዎች መኖራቸውን አውስተዋል።

ሙያተኝነት በጋዜጣው አመራር
ከላይ በታሪኩ ክፍል እንደተነሳው ጋዜጣው አስቀድሞ በቤተክህነት ሰዎች ይመራ ነበር። በወቅቱም የጋዜጠኝነት ሙያ የታወቀ ነገር አልነበረም ማለት ይቻላል። ምንአልባት በሙያተኛ ቢመራ ከሚቀየረው መንግሥት ጋር አብሮ አቋሙንም የሚቀያየር እንዳይሆን ይረዳዋል ብለው የሚያምኑም ጥቂት አይደሉም።

በዚህ ጉዳይ ላይ የዘርፉ ባለሞያዎች አስተያየት የበለጠ ጠንከር ያለ ምላሽ ሊሆን እንደሚችል የጠቀሰው ዋለልኝ በበኩሉ፣ ከሥነ ጽሑፍ በኩል እንጂ ከጋዜጠኝነት ሙያ አንጻር በአስተዳደር ደረጃ ሙያተኛ አግኝቶ ያውቃል ብሎ አያምንም። ጋዜጣው አሁን ድረስ የሚደነቅበትና የሚወሳበት የነበዓሉ ግርማ አመራር ወቅት ቢነሳ እንኳ፣ ያኔም የነበረውን ስርዓት አወዳሽ እንደነበር ከንባብ መረዳት ይቻላል ሲል ይጠቅሳል።

‹‹ምንአልባት በደርግ ጊዜ መድረክ የሚባል አምድ ነበረው። ይህም መንግሥትን ተቃዋሚ ሰዎች የሚጽፉበት ነው። እንደዛ ዓይነት አምድ ደግሞ አሁንም አለ።›› ሲል ያነጻጽራል። ባይሆን አሁን ከኹለት ዓመት ወዲህ ያለውን አሠራር ጠቅሶ፣ ‹‹አሁን ግን የሚሻል ይመስለኛል። ቢያንስ መከራከር የሚቻልበት፣ ቢያንስ አስተያየት ለመስጠት እድል የሚሰጥ ነው።›› በማለትም ያስረዳል። ይህን ለውጥ በጋዜጣው በቆየበት አራት ዓመታትና ባያቸው ኹለት አመራሮች ውስጥ እንደታዘበም ነው የጠቀሰው።

አጋረደች በበኩላቸው ጋዜጣው ባሳለፋቸው ዓመታት ትክክለኛ የሕትመት ሚድያ ባለሞያ አግኝቷል ወይስ አላገኘም የሚለው ጥናት ይፈልጋል ይላሉ። ‹‹የቀድሞዎቹ ረጅም ዓመት ሚድያ ላይ ይቆያሉ። ከዛ አዙሪት ስለማይወጡ ልምድ ያገኛሉ። በሙያው ደግሞ ወሳኙ ልምድ ነው።›› ሲሉ ጠቅሰዋል። በአሁን ጊዜ ውስጥ ግን በተለያየ ምክንያት ጋዜጠኞች ከቦታ ቦታ ይንቀሳቀሳሉ። ይህም በመደበኛ ደረጃ የሚያውቃቸው አድማጭ፣ ተመልካች ወይም አንባቢን ስለሚቀንስ፣ ለሙያው የመጨነቅ ነገርም አብሮ ሲቀንስ ይስተዋላል ይላሉ።

ለዚህም የደሞዝ ክፍያ፣ በጠቅላላ በኢትዮጵያ ያለው የሚድያ እውቀት፣ ገበያ ለማግኘት የመሥራቱ ነገር፣ መረጃ እንደልብ አለማግኘት፣ በተጨማሪ በኃላፊነት የሚሾሙ ሰዎች ለሙያው ያላቸው ግንዛቤ፣ የወረቀትና የሕትመት ዋጋ መወደድ፣ የጋዜጣ ስርጭት መጠን ወዘተ ተጽእኖ እንዳላቸው አስረድተዋል።

ሔኖክ ከባለሞያ አንጻር ባነሱት ሐሳብ አዲስ ዘመን ጠንካራ ጋዜጠኞች አሉት ብለዋል። ‹‹አብዛኛው የሚተጋ ስለሆነ ሌላውን የሚያሻግር ነው።›› ሲሉም የጋዜጣውን ሠራተኞች አሞግሰዋል። ከአመራር ጋር ያላቸውን ግንኙነትም ጠንካራ እንደሆነ የጠቀሱ ሲሆን፣ ‹‹ተቀበል የሚባል ነገር የለም። ሐሳብ ይቀርባል፣ ሙግት አለ። እኛ የፈጠርነውን ነጻ የሆነ አካባቢ በመረዳት የመሰላቸውን ሐሳብ ያንጻባርቃሉ፣ የሁሉም ፍላጎት ጥሩ ጋዜጣ እንዲሆን ነው።›› ሲሉ፣ አያይዘውም፣ ‹‹ከዚህ መቀራረብ የተነሳ ብዙ የሐሳብ ልዩነት የለንም። ዓላማችንን [ጋዜጠኛው የአመራሩን] ተረድተዋል።›› ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሀብቶች በአዲስ ዘመን አምዶች
በአዲስ ዘመን ገጾች ውስጥ የኢትዮጵያ ታሪክ ተጽፏል። በእርግጥ በየወቅቱ ከነበሩ መንግሥታትና መሪዎች አንጻር ነው በየጊዜው ዘገባዎች፣ ሐተታዎችና ትንታኔዎች የሚጻፉት የሚል ሙግት በማንሳት፣ በትክክል የታሪክ ማኅደር ብሎ ለመጥራት አያስደፍርም የሚሉ ሙግቶች ይነሳሉ። ያም ሆነ ይህ ግን፣ በየዘመናቱ በኢትዮጵያ ፖለቲካና ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች ላይ የነበረውን የልቦና ውቅር ለመረዳት አንድ እርምጃ የሚሆኑ ዘገባዎች በጋዜጣው ገጾች ላይ ይገኛሉ።

ያም ሆኖ እነዚህን መረጃዎች አገላብጦ አንዳች ጥናታዊ ሥራ ለመሥራት የተቀናጀና የተሰናዳ የቤተ መጻሕፍት አጠቃቀም ስርዓት የለም። ጋዜጣው በ79 ዓመቱ ያለው ቤተመጻሕፍት አንገት የሚያስደፋ ነው። አርካይቭ ተደርገው በጥንቃቄ መቀመጥ ያለባቸው ሀብቶችም ያሉበትን ሁኔታ መገመት ከባድ ነው። የትም የማይገኙ ፎቶዎች ቢኖሩም፣ አልታዩም። በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያን ሔራልድ ጨምሮ፣ በሪሳ እና በአረብኛ ቋንቋ የሚታተመው አልዓለም ዛሬ ያልተሰሙ ታሪኮችን በየገጾቻቸው ይዘዋል። ግን ሁሉም ተደብቀዋል።

ከመደበቃቸው በላይ ብዙዎች የሚሰጉት ጠፍተው እንዳይሆኑ ብለው ነው። በተለይም ድርጅቱ እስከ 2006 ድረስ ቋሚ መሥሪያ ቦታ የሌለውና ከቦታ ቦታ የሚንከራተት ስለነበር፣ በመካከል ሊከሰት የሚችለውን የሀብት ውድመት መገመት ‹ክፉ አሳቢ!› አያሰኝም። ከዛም በላይ ደግሞ ድርጅቱ ሀብቱን በአግባቡና ጋዜጣው ከአንጋፋነቱ ሳይወርድ እንዲቆይ ይህን ሀብት አለመጠቀማቸው የሚያስወቅስ ነው።

ዋለልኝ ከአዲስ ማለዳ ጋር ባደረገው ቆይታ እንዳነሳው፣ ድርጅቱና በየጊዜው የሚመጣው አመራር ሁሌም የሚወቀስበት ጉዳይ ይህ የቤተመጻሕፍትና አርካይቭ ጉዳይ ነው። ይህን ሀብት መጠቀም ቢቻል፣ ከ‹መፈረጅ› ጀምሮ እንደ ችግር የሚነሱ ብዙ ጉዳዮች ሊቀረፉ እንደሚችሉ ያምናል። ይህ ግን መች ይሆን እውን የሚሆነው? ያልታዩ ምስሎች፣ ዐይን ካረፈባቸው ሃምሳ ዓመት በላይ የዘለቁ በድርጅቱ ውስጥ ያሉ ሀብቶች መቼ ነው ለሕዝብ የሚደርሱት? መች ነው አዲስ ዘመን ጋዜጣን እንዲሁም በድምሩ ድርጅቱን የሚመጥን ግዙፍ ቤተመጻሕፍት የሚከፈተው? ከ79 ዓመታት በኋላም የሚነሳ ጥያቄ ነው።

ሔኖክ እንዳሉት ከሆነ፣ ይህን በሚመለከት ኹለት ሥራዎች እየሠሩ ነው። አንደኛው ቤተ መዘክር (ሙዝየም) ማዘጋጀት ነው ብለዋል። ይህም ለብዙዎች መረጃ ሰጪና ታሪክ ነጋሪ ከመሆኑ በተጨማሪ ለድርጅቱ ገቢ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። ሌላው ደግሞ ያሉትን ሀብቶች በዲጂታል አርካይቭ ማድረግ ሲሆን፣ ወደዛም ተግባራዊ እንቅስቃሴ ጀምረናል ብለዋል።

‹‹በቂ የሰው ኃይል አለኝ የሚል ተቋም የለም።›› ያሉት ሔኖክ፣ ‹‹ቤተመጻሕፍት አካባቢ በቤተመጻሕፍት ሳይንስ የሠለጠነ ባለሞያ የለንም። እንደ አገርም ያንን ማግኘት አይታሰብም።›› ሲሉ አገራዊ ችግር መኖሩንም ጠቅሰዋል።

ሌሎች ችግሮች
በኢትዮጵያ በየዘርፉ አሻራውን በጽኑ ማሳረፍ የሚችለው ትልቁ ጉዳይ ፖለቲካው ይመስላል። በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ደረጃም ሆነ መልክ ላይም ይኸው የፖለቲካ ገጽ ይታያል። አሁንም እንኳ ትክክለኛ መስመር ላይ ነው በሚባልበት ወቅት የፖለቲካውን ቀለም በሚገርም መልኩ ማየት ይቻላል።

በእርግጥ ከኹለት ዓመት በፊት በፖለቲካው የመጣውን ለውጥ ተከትሎ በርካታ መገናኛ ብዙኀንም መልካቸው ተቀይሮ ነጻነትን እንደተነፈሱ ሲገለጽ ነበር። የአዲስ ዘመኑ ዋለልኝ ታድያ ይህን ለውጥ በሚመለከት ከአዲስ ዘመን ቢሻሻል ያለውን ሐሳብ አያይዞ አንስቶታል። ከመጡ ስርዓቶች ጋር አብሮ አቋም ይቀያይራል የሚባለው አዲስ ዘመን፣ አሁንም ያንን እየደገመ ይመስላል ሲል ነው ትዝብቱን ያካፍላል።

በፊት ማለትም ከኹለት ዓመት ቀደም ብሎ ግንቦት 20ን ያወድስ የነበረ ጋዜጣ አሁን ወቃሽ፣ አብዮታዊ ዴሞከራሲን ይደግፍ የነበረ፣ አሁን አብዮታዊ ዴሞክራሲን ‹ጸረ ዴሞክራሲ› የሚል ሆኗል። እንዲህ መሆኑ ታድያ በታሪክ ምንጭነት ሊጠቅሱት ለመረጡት የሚያስወቅስ እንደሚሆን ነው ያነሳው። ጋዜጣው ከዚህ ወቀሳ ለመውጣት ጥረት ቢያደርግ ሲልም አስተያየቱን ሰጥቷል።

በተለይም ጋዜጣው ራሱን ማስተዋወቅ ላይ ደካማ ነው ያለ ሲሆን፣ ከሌሎች መገናኛ ብዙኀን አንጻር በዚህ ላይ በጣም እንደሚቀረው ነው ያስረዳው።
አጋረደችም በበኩላቸው በጋዜጠኝነት ሙያ ውስጥ የተፈጠሩ አፍራሽ ነገሮች ነበሩ ይላሉ። እነዚህም በተለይ ጋዜጠኛው እቀጣለሁ፣ እታሰራለሁ፣ ከደረጃዬ እወርዳለሁ፣ እባረራለሁ ብሎ እንዲሰጋና፣ በራስ የመተማመን ችሎታ እንዳይኖረው እንዳደረገ ነው።

ታድያስ?
አጋረደች በጋዜጣው ስለነበራቸው ቆይታ ያወሳሉ። ‹‹እኔ የነበርኩበት ጊዜ፣ ረጅም ዓመት በዛው ያሳለፉ ሰዎች የነበሩበት ነው። ብዙ ተምሬአለሁ። እናም እንደማስታውሰው የጋዜጣ ሥራ የቡድን ሥራ እንደሆነ ነው። የግል ስሜት የሚንጸባረቅበት አይደለም። የሆነ ስህተት ቢወጣ የሚጮኸው ብዙ ነው። ብዙ ሰው ግብረ መልስ ይሰጥ ነበር። ለአንድ ጋዜጣ መነሳትም መውደቅም ይህ ወሳኝ ነው። አንድ ሐሳብ በአንድ ሰው ብቻ የሚያልፍም ሲሆን፣ የዛ ሰው ተገዢ መሆን ይመጣል። የተለያየ ሐሳብ መነሳቱ የተለያዩ እይታዎችን ለማግኘት ይረዳል።›› ሲሉ ከልምዳቸው ያካፍላሉ።

ዋለልኝ በበኩሉ፣ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ብዙ ዓመት ያስቆጠረ እንደመሆኑ አመራር ላይ ያሉ ሰዎች የራሳቸውን ጥንካሬ የሚያሳዩበት እንዲሆን ጥሪ አቅርቧል። ‹‹በእነርሱ ጊዜ እንደዚህ ተሠርቶ ነበር፣ ይህን ያህል የምርመራ ዘገባ ይሠራ ነበር እንዲባል ማድረግ አለባቸው።›› ሲልም አስተያየቱን ሰጥቷል።

ነገር ግን በአመራር ብቻ ሳይሆን የጋዜጠኛውን ትጋት ጠይቋል። ‹‹ጋዜጠኞች የፈለጋችሁትን የምርመራ ዘገባ ሥሩ ተብሎ ሙሉ ነጻነት ቢሰጥ፣ እንችላለን ወይ? ብቃትስ አለ ወይ?›› ሲል ይጠይቃል። እናም ጋዜጠኞች ወደ ሞያው ቅርብ መሆን አለባቸው ሲልም ምክረ ሐሳቡን ይሰጣል።

ነገር ግን የሚነበቡ ጋዜጦችም መኖራቸውንና፣ የሕትመት ሚድያ በኢንተርኔት ዘመን ተቀባይነት የለውም የሚለውን ውድቅ እንደሚያደርጉ ያነሳል። ‹‹አዲስ ዘመን ራሱ አነጋጋሪ ጉዳይ ይዞ ሲወጣ ሲነበብ አይተናል።›› ሲልም ያወሳል።

ከኹለት ዓመት ገደማ በፊት በምክትል ዋና አዘጋጅነት ወደ ተቋሙ ያቀኑት ሔኖክ፣ ንባብ የጀመሩት በአዲስ ዘመን እንደሆነ ያስታውሳሉ። ወደ መሥሪያ ቤቱም ሲመደቡ ተሰምቷቸው የነበረውን የእድለኝነት ስሜት አንስተዋል። ‹‹ስንመጣ ሐሳባችን የሕዝብ እንዲሆን ነው። በአስተሳሰብ፣ በማንነት ሳይገደብ የኢትዮጵያ ጋዜጣ ማድረግ ነበር፣ እንደ አመራር የጋራ እሳቤያችን። ይህን ለማድረግ የተለያየ እቅድ ነድፈን ሠርተናል።›› ሲሉ አሁንም በዛው መንገድ እየቀጠሉ እንደሆነ ጠቅሰዋል። ጋዜጣው ግን ከፍረጃ እንዳላመለጠ ደጋግመው የጠቀሱት ሐሳብ ነው።

አያይዘውም አንባቢዎች ጋዜጣውን እንዲከታተሉ ሲጠይቁ፣ አንባቢዎች መጻፍ የሚችሉባቸው ነጻ አምዶች መኖራቸውንም ጠቁመዋል። ‹‹እባካችሁ ሐሳባችሁን አንጻባርቁ።›› ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 83 ግንቦት 29 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here