በኮሮና የተያዙ ሐኪሞችን በሥራ ላይ አሰማርቷል መባሉን ሆስፒታሉ አስተባበለ

0
610

በዘውዲቱ ሆስፒታል ውስጥ የሚገኙ የሕክምና ባለሞያዎች የኮሮና ቫይረስ ተገኝቶባቸው በለይቶ ማቆያ ውስጥ መቀመጥ ሲገባቸው ሕመምተኞችን እያከሙ ይገኛሉ በሚል የተነሳውን ቅሬታ ሆስፒታሉ አስተባብሏል።

አስተያየት ሰጪዎች ይህን ይበሉ እንጂ፣ የዘውዲቱ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ኤደን ዓለማየሁ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ ጥቆማው ሐሰት እንደሆነ እና የሆስፒታሉ ባልደረባ የሆነ አንድ የጤና ባለሙያ በቫይረሱ መጠቃቱ በምርመራ ከተረጋገጠ በኋላ በሆስፒታሉ ቅጥር ጊቢ ውስጥ በሚገኝ የለይቶ ማቆያ እና የሕክምና እርዳታ መስጫ ማእከል ተለይቶ እንዲቀመጥ ተደርጓል።

ምንጮች ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቁት፣ በሆስፒታሉ ውስጥ በቁጥር የበዙትን ሕመምተኞች በበቂ መንገድ ማስተናገድ በማያስችል ሁኔታ የሕክምና ባለሙያዎች ዕጥረት ከመኖሩ ጋር ተያይዞ፣ በምርመራ የኮቪድ 19 ቫይረስ የተገኘባቸው በሆስፒታሉ ውስጥ አገልግሎት የሚሰጡ የሕክምና ባለሙያዎች በሥራ ገበታቸው ላይ እንዲቆዩ ተደርገዋል።

በቫይረሱ ተይዘዋል የተባሉ እነዚህ የጤና ባለሙያዎች የሚገቡበት እና የሚወጡበት በር የተለየ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ከፍተኛ የሆነ ጥንቃቄ የሚያደርጉ ቢሆንም፣ ከበሽተኞች እና ከተቀሩት የሆስፒታሉ ሠራተኞች ጋር በሥራ አጋጣሚ ሊገናኙ ስለሚችሉ የቫይረሱን ስርጭት ከፍ ሊያደርገው ይችላል ብለዋል። እንዲሁም በሌላ የጤና እክል ወደ ሆስፒታሉ የሚያቀኑ ሰዎች በቫይረሱ መያዝ ዕድላቸው ከፍተኛ ሲሆን፣ ላያገግሙም የሚችሉበት አጋጣሚም ከፍ እንደሚል ምንጮች ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ዶክተሯ አያይዘውም በለይቶ ማቆያ ውስጥ የሚገኘውን የጤና ባለሙያን በሥራ ገበታው ላይ እንዳይገኝ የተገለለ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት የማገገም ደረጃ ላይ በመሆኑ ድጋሚ ምርመራ ተደርጎለት በመጪዎቹ ኹለት እና ሦስት ቀናት እንደሚታወቅ ጠቅሰዋል። ይህም ከታወቀ በኋላ ከለይቶ ማቆያው በመውጣት ወደ ማኅበረሰቡ እንዲሁም ወደ ሥራ ገበታው እንደሚመለስም ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ከዚህም በተጨማሪ አዲስ ማለዳ ከሜዲካል ዳይሬክተሯ ያገኘችው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ቁጥራቸው በውል የማይታወቁ እና በሌላ የጤና ተቋማት ባልደረባ የሆኑ የጤና ባለሙያዎችም በኮሮና ቫይረስ ተይዘው በዘውዲቱ ሆስፒታል ውስጥ በሚገኘው የለይቶ ማቆያ እና የሕክምና መስጫ ማእከል ውስጥ ይገኛሉ።
በሆስፒታሉ የኋለኛ እና ለቫይረሱ ተጠቂዎች ብቻ የተለየ መግቢያ እና መውጪያ በር አለ ስለተባለው ጉዳይም ሲያብራሩ፣ በለይቶ ማቆያ ውስጥ የሚገኙት የጤና ባለሙያዎች የሚጠቀሙባቸው እና ከጤነኛ ሰዎች ጋር ግንኙነት እንዳይኖራቸው በሚል የተዘጋጀ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ለአዲስ ማለዳ ጥቆማቸውን የሰጡ የሕክምና እርዳታ ለማግኘት ወደ ዘውዲቱ አቅንተው የነበሩ ዕድሜያቸው የገፋ አንዲት እናት እንደሚናገሩት፣ ከነርሶች በኩል በሆስፒታሉ ውስጥ በበሽታው የተጠቁ የሕክምና ባለሙያዎች መኖራቸውን እና እርሳቸው ደግሞ ከዕድሜያቸው መግፋት ጋር ተያይዞ ለበሽታው ተጋላጭ የሚሆኑበት አጋጣሚ ከፍተኛ እንደሆነ እንደተነገራቸው ነው። በዚህም ምክንያት ሕክምና ሳያገኙ መመለሳቸውን አስታውቀዋል።

በተመሳሳይ ጉዳይ በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የሕክምና አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩ ባለሙያዎች በቫይረሱ ከተያዘ ሰው ጋር ንክኪ እንዳላቸው በመግለጽ ወደ ለይቶ ማቆያ እንዲወሰዱ ቢጠይቁም፣ መከልከላቸውን በተለያዩ ሚዲያዎች ሲያስተጋቡ መቆየታቸው ይታወሳል።

በኢትዮጵያ በጤና ተቋማት የሚሠሩ 65 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ እንደተገኘባቸው የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ያስታወቁ ሲሆን፣ እስከ አሁን ባለው ሂደት 49 የጤና ባለሙያዎችና 16 ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች ላይ ቫይረሱ መታየቱ ተገልጿል።

ባለሙያዎቹ በአብዛኛው በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ የጤና ተቋማት እየሠሩ መሆናቸውም የተገለጸ ሲሆን፣ የጤና ባለሙያዎችና የጤና ተቋማት ሠራተኞች የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት እያደረጉት ላለው ተጋድሎም ሚኒስትሯ ምስጋና አቅርበዋል። ከዚህ ጋር ተያይዞ ከቀናት በፊት በመጪዎቹ አራት እና ከዛ በላይ ወራት በጤና ተቋማት ብቻ የሕክምና ባለሙያዎችን ከቫይረሱ ተጋላጭነት ለመቀነስ ሲባል 130 ሚሊዮን የፊት መሸፈኛ ማስክ እንደሚያስፈልግም የጤና ሚኒስቴር ይፋ አድርጓል።

ቅጽ 2 ቁጥር 83 ግንቦት 29 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here