ዐይናችንን ከዋናው መዳረሻችን ላይ አንንቀል!

የኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ፣ የአንበጣ መንጋ፣ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብና ድርድሩ፣ 2012 አገራዊ ምርጫ ጉዳይ፣ የፌዴራልና በክልል መንግሥታት መካከልና ውስጥ የሚነሱ ውዝግቦች ወዘተ በኢትዮጵያ የጉዳይ ገበታ ላይ በየዓይነቱ ተቀምጠዋል። ሁሉንም ችግር የመፍታት ግቡ ደግሞ የኢትዮጵያን ሕዝብ ኑሮ ከድህነት ወለል አሻግሮ ከከፍታው ማድረስ ነው። ሽመልስ አረአያ ይህን ጉዳይ በማንሳት፣ ከዋናው ግብ ላይ ዐይንን ለማስነቀልና ጉዞን ለማደናቀፍ የሚነሱ አደናጋሪ ጉዳዮችን እንለይ ሲሉ፣ እነዚህኑ አደናጋሪ ወሬዎች ጠቁመዋል።

ዝምተኝነት የአዋቂነት መገለጫ እንደሆነ ለማሳየት የተለያየ አገርኛ አገላለፆችን እንጠቀማለን። ከእነዚህም ውስጥ ‹ዝም ባለ አፍ ዝንብ አይገባበትም› እንዲሁም ‹በርሜሉ ለምን ይጮኻል ቢሉት ባዶ ስለሆነ› … ወዘተ ሲጠቀሱ፣ በእነዚህ የዝምታን ሸጋነት ለማጉላት እንጥራለን። ብዙኀኑ በዋናነት በእነዚህ አባባሎች ገፊነት የተነሳ ይመስል፣ በዝምታ ሲሸበብ ነገር ግን በመደበኛውም ሆነ በማኅበራዊ ሚዲያው በጣም ጥቂቶች በመጮኻቸው አቧራ ሲያስነሱ እየተስተዋለ ነው። ይህ እንዲህ ሳለ፣ አብዛኛው ሰው እውቀት እያለው እንዲሁም እውነታው ማጥራት እየቻለ፣ ብዥታው ላለማጥራትና በዝምታ ለማሳለፍ የተማማለ ይመስላል።

በመሆኑም የጥቂቶች ጩኸት ከመንደር አልፎ አገርን ያውካል። ብዙውን ጊዜ በማኅበራዊ ሚድያው ለሚቀርበው ኃላፊነት የሚወስድ አካል ባይኖርም፣ በውሸት መረጃ ሰዎች ከአካባቢያቸው ተፈናቅለዋል። አንዳንዶች ሕይወታቸውንም ገብረዋል። በጊዜ ነቅተን በእንደዚህ ሁኔታ የሚተላለፉ አሳሳች ወሬዎች እንዳንወናበድ ካልተጠነቀቅን፣ ውሸትና አደናጋሪ መረጃዎች ዓላማቸው የተለያየ ቢሆንም፣ ሲጠቃለል ዋና ግባቸው ለግል ጥቅም መሳካት እንዲያመቹ ተደርገው የተቀረፁ ናቸው። ሕዝቡን በማደናገርም እንዳየነው ሰላምን በማናጋትና የዜጎችን ሕይወት በመቅጠፍ የከፋው እንዲፈፀም ነው።

እንደ አንድ ዜጋ ከታዘብኳቸው ቢያንስ ባለፉት አንድ ወይም ኹለት ወራት ወዲህ ከተነዙት አሳሳችና አወናባጅ የፈጠራ ወሬዎች በተመለከተ በዚህ ርዕስ ዙሪያ ይህን አጭር ጽሑፍ ለማካፈል ወደድኩ።

ቀዳሚ ጉዳይ
አደናጋሪ ወደሆኑት ወሬዎች ከማለፌ በፊት በዚህ ወሳኝ ወቅት በእኔ እይታ በዋናነት የሁላችንም ትኩረት መሆን የነበረበትና ሊሆንም የሚገባው ጉዳይ ለመግለፅ እፈልጋለሁ። ይኸውም በአጭር ጊዜ ድል መንሳት ያለብን ከፊት ለፊታችን የተደቀነው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ አደጋ ነው። ወረርሽኙ እንደሌሎች ተጎጂ አገራት የብዙ ዜጎቻችን ሕይወት ሳይቀጥፍ እንዲሁም የአገራችን ኢኮኖሚ ሳይጎዳና እጅ ሳያሰጠን በጥበብ የምናልፍበትን መላ ማበጀት ነው።

የረጅም ጊዜ ግባችን ደግሞ ድህነትን ያህል ጠላት የለብንምና፣ ድህነትን ትርጉም ባለው መልኩ ከአገራችን መቀነስ መቻል ነው። ከዚህ በፊት በመንግሥት የሚወጡት ሪፖርቶች እንደሚያመለክቱት በተከታታይ በተመዘገበው አገራዊ የኢኮኖሚ እድገት በፈጠረው ምቹ ሁኔታ ከድህነት በታች ይኖር የነበረው ሕዝባችን በግማሽ ቀንሰናል የሚል ነበር። ይህን ‹ስኬት› ብዙ ትችቶች የሚቀርቡበት ቢሆንም አገሪቷ አመርቂ የሆነ የኢኮኖሚ እድገት እያስመዘገበች እንደሆነ የሚታወቅ ሃቅ ነው።

ነገር ግን ከመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር በሽርክና የሚሠሩና የጥቅም ትስስር ያላቸው አካላት ካልሆኑ በቀር ብዙኀኑ ኅብረተሰብ ከእድገቱ ትሩፋት እምብዛም ተጠቃሚ የሆነ አይመስልም። በአጭሩ ዐይን ያወጣና በግልጽ የሚታይ በድሃውና በሀብታሙ መካከል እየሰፋ የሚሄድ ፍትሃዊ ያልሆነ የሀብት ክፍፍል አለ። በዚህ ላይ ሙስናውና ዘረፋው ሲታከልበት የእድገት ትሩፋቱ ውጤት የዜሮ ድምር ጨዋታ ያደርገዋል።

ይህም ኢኮኖሚው የሚታይ እድገት ቢያስመዘግብም በመልካም አስተዳደር እጦት ብዙኀኑ በፍትሃዊነት ተጠቃሚ የማይሆን ከሆነ ማለት ነው። በመሆኑም ከሀብቱ ሁሉም እንደዜጋ በፍትሃዊነት ተጠቃሚ እንዲሆን በማድረግ ድህነትን መቀነስ ያስፈልጋል። ይህ ከባድ ፕሮጀክት እንደመሆኑ በረጅም ዓመታት ሁላችንም ተረባርበን የምናሳካው አገራዊ ግብ ነው።

በአገራችን አንቆ የያዘንን ድህነት እንዲቀረፍ ሁነኛ ሚና ይጫወታል በማለት በሁሉም አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ተስፋ የተጣለበት የህዳሴው ግድባችን ነው። ስለዚህ ለሕዳሴው ግድብ ትኩረታችን የበዛ መሆን አለበት።

በመሆኑም ከላይ በአጭርና ረጅም ጊዜ የምናሳካቸው ኹለት ግቦች ላይ ያለማመንታት የኹለቱንም ዐይናችንን ሙሉ ትኩረት በእነዚህ ላይ ማድረግ እንዳለብን እሙን ነው። ምክንያቱም እንደአገር አንድና ኹለት ተብለው የሚጠሩ ጠላቶች ቢኖሩ ቫይረሱ የሚያስከትለው ዳፋና ለዘመናት ተጣብቆን የከረመው ድህነት እንዲሁም ከእነዚህ የሚወለዱ ፍሬዎች ናቸው።

ከእነኚህ ወሳኝ ጉዳዮች ዐይናችንን ነቅለን ከዚህና ከዚያ በሚወረወሩልን አሳሳች የሆኑ የፈጠራ ወሬዎችና አጀንዳዎች ሳንጠለፍ ዋናው ትኩረታችን በዋናው ጠላታችን ድል መንሳት ላይ ማድረግ አለብን። ይህ ሳይሆን ቀርቶ ያለልማዳችን ድል ተነስተን ለተመልካች መሳቂያና መሳለቂያ እንድንሆንና በዚህ አግባብ እንድንጓዝ አጀንዳ የሚቀርፁልንን አካላት እንዳሉ በሚገባ ተገንዝበን፣ ራሳችንን ከሚወረወሩ የፈጠራ ወሬዎች እየጠበቅንና መሳሪያ ላለመሆን እየተጠነቀቅን አንድ በአንድ ማምከን አለብን።

አገሪቱን የሚመራው መንግሥትም ዳግም የከፋ ሁኔታ ተፈጥሮ ዜጎቻችን በማያውቁት ያለጥፋታቸው፣ ያለበደላቸው የሚጋፈጡት የሰላም እጦት ፈተና እንዳይኖር፣ ሕግና ስርዓትን ከማስከበር አልፎ ተዓማኒነት ያለው መረጃ ለዜጎች እንዲደርስ ማድረግ አለበት። ከዚህ በፊት የገጠሙን አሉባልታዎች፣ ለማሳሳትና ለማወናበድ ተብለው የቀረቡ አጀንዳዎች ትኩረታችንን ከዋናው ጉዳያችን ለማስለቀቅ ከእለት ወደእለት እየጨመሩ እንደሚመጡ በመገንዘብ፣ በተቀደደልን መፍሰሱን በመተው ግራ ቀኙን በማገናዘብ እየተጓዝን የዜግነት ግዴታችን ለመወጣት በቻልነው አግባብም ለጥፋት ላለመተባበር መሰለፍ አለብን።

ለዚህ አጭር ጽሑፍ መነሻነት የሆኑኝ በመደበኛውና በማኅበራዊ ሚዲያው የተወረወሩ የማደናገሪያ ወሬዎች የተወሰኑትን ለማመለከት እፈልጋለሁ።

ማደናገሪያ ወሬ አንድ
በመጀመሪያ ልጠቅስ የምፈልገው የመስከረም 30ን ጉዳይ ነው። የተጠቀሰው ጊዜ ከመድረሱ በፊት ምርጫ ካልተካሄደ እውቅና ያለው መንግሥት ሊኖር ስለማይችል አሁን በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት በሕግ ዘንድም ቅቡልነት ስለሌለው የግድ ምርጫውን አሁን መደረግ አለበት አልያም ሥልጣን ሊያጋራን ይገባል በማለት በኮሮና ቫይረስ ድንጋጤ ውስጥ የሚገኘው ሕዝብ ‹‹ከኮሮና ብተርፍም ከመስከረም 30 መትረፌን እንጃ›› አሰኝተውታል።

እነዚህ የተወሰኑ በተቃውሞ ላይ ያሉ የፖለቲካ ልሂቃን እስካሁኗ ድረስ ያልነው ካልሆነ ገመድ በአንገታችን ይገባል በማለት ከመንግሥት አካላት ጋር በቃላት እየተጠዛጠዙ ይገኛሉ። ሁሌም እንደሚባለው የዝሆኖች ጥል የሚተርፈው ለእኛው ለሳሩ ነው። በዚህ ወቅት ምርጫ ካልተደረገ አልያም ሁላችንም የሚያሳትፍ መንግሥት ካልተመሰረተ እንተያያለን ማለትን በቅንነት አይቶ ለአገሪቷ አልያም ለሕዝቡ ታስቦ ነው የሚል ካለ፣ እሱ ስለምኑም አልገባውም ማለት ነው።

የዚህ አቧራ ማንሳት ዋናው ግብ ኅብረተሰቡን በማደናገር ብዥታ ውስጥ በመክተት በሚፈጠር ግብግብ ሁላችንም ዐይናችንን በዋናው ጠላታችን ላይ እንድንነቅል በማስገደድ፣ ኢትዮጵያ በታሪኳ ዐይታው የማታውቀው ሽንፈት እንድትጎነጭ፣ ሕዝቡም በሃፍረት ቀና እንዳይል የተሸረበልን ደባ ይመስለኛል። ለዚህ አገር አፍራሽ የሆነ የጥፋት አጀንዳ ከዋና ጠላታችን ካልናቸው ላይ የትኩረት ዐይናችን በመንቀል በፍፁም ተባባሪ መሆን የለብንም።

አገሪቷ ምርጫን በወቅቱ ልታከናውን እንደሚጠበቅባትና የፖለቲካ ሥልጣን ምንጩ በሕዝብ በተገኘ ይሁንታና የምርጫ ውጤት መሆን እንዳለበት ባምንበትም፣ ኢትዮጵያውያን በታሪካችን ለዚህ ዴሞክራሲያዊ ስኬት አልበቃንም። በመሆኑም የፖለቲካ ሥልጣን በምርጫ ተገኝቶም አይታወቅም።

አገሪቷ ያለምርጫ ዘመናትን ተሻግራለች። በዚህ ዓለማቀፍ የሆነ ወረርሽኝ ባንዣበበብን ወቅት ከዚህ በፊት ያላየነውን እንከን አልባ ምርጫ ይደረግ ዛቻ መቼም በአቋራጭ የታቀደልን ጥፋት መኖሩ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። ስለዚህ የአገርና ሕዝብ ደኅንነት ይቅደም ማለት ያስፈልጋል። የተመኙት ሥልጣን የሚገኘው አገር ስትኖር መሆኑን ለማመላከትም እፈልጋለሁ።

ማደናገሪያ ወሬ ኹለት
ሌላው አየሩን ይዞ የነበረው አደናጋሪ ርዕስ ‹ኢትዮጵያ ከኬንያና እንዲሁም ከሱዳን ጋር ወደለየለት ጦርነት ልታመራ ነው› የሚል ነበር። የዐቢይ አሕመድ መንግሥት አገራችን ከጎረቤት አገራት ጋር የነበራትን መልካም ጉርብትና በመሸርሸር ላይ እንደሚገኝና ጦርነት ውስጥ መግባታችን አይቀሬ መሆኑን ከሚገባው በላይ ሲራገብ ታዝበናል። ከዚህ ጋር በተያያዘ የተበተነው አሳሳችና አደናጋሪ ወሬ አገራቱን እንደተባለው ሳያታኩስና ውድመት ሳያስከትል በአጭር ጊዜ የሚረግብም አይመስልም ነበር።

ነገር ግን ለአጀንዳው ፈጠሪዎች በለስ ሳይቀናቸው ቀርቶ በዚህ አጀንዳ ዙሪያ ሊያገኙት የቋመጡለት ግባቸው ያሳኩት አይመስልም። ዋናው ግባቸው ከላይ እንዳልኩት ኅብረተሰቡን ብዥታ ውስጥ በመክተት በዚህም ፍርሃትን በማንገስ መንግሥት የበለጠ ጫናና ውጥረት ውስጥ እንዲገባ፣ እንደዚሁም በጎረቤት አገራትም በጥርጣሬ እንዲታይ ማድረግ ነው። በእነዚህ ድምር ውጤት ዋናው ግብ አገሪቱን የሚመራው መንግሥት ዋናው ትኩረት ከሆነው ጉዳይ ላይ ዐይኑን በማስነቀል በሚፈጠር የኅብረተሰቡ ኢኮኖሚያዊና ከጤና ጋር የተያያዙ ችግሮች እንዲሁ ለሌላ የውስጥ አጀንዳ መፈብረኪያነት ለመጠቀም እንደነበር እገምታለሁ።

ማደናገሪያ ወሬ ሦስት
እንዳሰቡት ስላልሆነላቸው ወዲያው ሌላ ማሳሳቻና ማደናገሪያ አጀንዳ ተፈለገና እንደተለመደው በሚድያው በኩል እንዲደርሰን ተወረወረልን። ይህ አጀንዳም የዘረመል ልውጥ ሕያዋን (GMOs) አዝዕርት ቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ጉዳይ የተመለከተ ርዕስ ነበር። የአሁኑ አስተዳደር በኢትዮጵያ ከዚህ በፊት እንዳይገባ የተከለከለን ጎጂ ቴክኖሎጂ እንዲገባ በመፍቀድ የሕዝቡን ጤንነት እንዲሁም የአርሶ አደሩን የማምረት አቅም ላይ የከፋ አደጋ በመፍጠር አገሪቷን ውሎ ሲያድር የሚጎዳት ስምምነት አደረገ የሚል ነበር።

ይህ የተጣመመ አደናጋሪ ክስ የቀረበበት አግባብ ስንመለከት እንዲህ ይላል፤ ‹‹ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አገራት ቀድማ በዘርፉ ከነበራት ሚና አፈግፍጋ በዚህም በረጅም ዓመታት በአኅጉር ደረጃ ይዛ የነበረውን ከበሬታ ልታጣ ተቃረበች።›› ነገር ግን ስለዘርፉ በትንሹ ከማውቀው ቴክኖሎጂው እንደተወራበት መአት ብቻ ሳይሆን እንዲያውም የበዛ ሲሳይም ያለው መሆኑን ነው።

ወደዚህ ማርሽ ቀያሪ ቴክኖሎጂ ዘርፈ ብዙ ትሩፋቶችና በቴክኖሎጂውም ተጠቃሚ የሆኑ አገራትን ዳሰሳ ጉዳይ እመለስበታለሁ። እንደሚታወቀው የታመመ ሰው በሕክምና የታዘዘለትን መድኃኒት የጎንዮሽ ጉዳት እንዳለው ብንነግረውም መድኃኒቱን ከመጠቀም የማያመነታው የሚያስገኝለት ጥቅም (በሕይወት መቆየት) አነስተኛ ከሆነው የጎንዮሽ ጉዳት በጣም የተሻለ ስለሆነ ነው። ስለዚህ በዘረመል ልውጥ ሕያዋን ምህንድስና የተፈጠሩ የእፅዋት ዝርያዎች ከተለመደው መደበኛ የምርምር ማእከላት ከሚወጡት ዝርያዎች የሚለያቸው ዋና ነገር ቢኖር በቤተሙከራ ውስጥ በከፍተኛ ጥበብና ምርምር የሚሠሩ ግኝቶች መሆናቸው ነው።

በመሆኑም ለጥፋት እንጂ ለጥቅም አይውሉም ማለት እጅጉኑ የተሳሳተ መደምደሚያ ነው። የቴክኖሎጂው ትሩፋት ሁሉም የዓለም አገራት በተለያየ አግባብ ለሕዝባቸው ጥቅም እንዲውል እያደረጉት ይገኛሉ። አገራችንም ከውጭ የምታስገባቸው መድኃኒቶችና ምግብ-ነክ ምርቶች የዚህን ቴክኖሎጂ ግኝት ግብዓት ሳይጥቀሙ የተመረቱ ስለመሆናቸው ምንም ማረጋገጫ የለንም። በአውሮፓ በሰፊው ባይመረቱም በየሱፐርማርኬቱና ምግብ መደብሮች ለተጠቃሚ እንዲውሉ ከሌሎች አምራች አገራት በማስመጣት በአነስተኛ ዋጋ እየተቸበቸቡ ይገኛሉ።

አብዛኛው ተጠቃሚም ያለምንም ብዥታ የሚሸምታቸው እንደሆነ ማንም በዐይኑ አይቶ የሚያረጋግጠው ጉዳይ ነው። እንደዚሁም የቴክኖሎጂው ጥቅም በሚገባ የተገነዘቡ አገራት ለምሳሌ ሕንድ ከወቅቱ የአፍሪካ ሕዝብ ቁጥር ጋር የሚስተካከል አንድ ነጥብ ሦስት ቢሊዮን ሕዝብ ተሸክማ በተነጻጻሪነት ከአፍሪካ አኅጉር እዚህ ግባ በማይባል የቆዳ ስፋት ሕዝቧን በሚገባ መመገብ የቻለችው ዘመኑ የደረሰበትን የግብርና ቴክኖሎጂ በሚገባ መጠቀም በመቻሏ እንጂ ሌላ ተዓምር የለም።

ከበለፀጉት አገራት አሜሪካ፣ ካናዳ እንዲሁም ከደቡብ አሜሪካ ትልቋ ብራዚል ቴክኖሎጂው በሰፊው እየተጠቀሙበት እንደሆነ በሚገባ ተሰንዶ ተቀምጧል። ወደ አፍሪካ ብንመጣ በዋናነት ደቡብ አፍሪካ፣ ግብጽ እንዲሁም ጎረቤታችን ኬንያ የቴክኖሎጂው ተጠቃሚ መሆናቸውን እንጂ እንደተባለው እውነታው ሲመረመር ከአፍሪካ አገራት በመቅደም የተሰጠንን አደራ የበላን ሆኖ አይደለም። እውነታው ይህ አይደለም እንጂ ለአገራችንና ሕዝባችን የሚጠቅም መሆኑን እስካመንን ድረስ ምን ይሉናል በሚል ፍርሃት እንደአገር ልናገኘው የሚገባን ጥቅም ማሳለፍ ያለብንም አይመስለኝም።

በዚህ አሉባልታ አብዛኞቹ ተጠልፈው በማህበራዊ ሚድያው በግሌ የታዘብኳቸው አንዳንድ ወዳጆቼ በጉዳዩ ላይ ምንም አይነት እውቀት ሳይኖራቸው ለያዥ ለገናዥ ሲያስቸግሩ አይቻለሁ። ከጉዳዩ ጋር ምንም ዝምድና የሌላቸው ብቻ ሳይሆን ዋና ተግባራቸው የገበሬዎቻችንን የዘር ዋስትና ለማረጋገጥ አርሶ አደሩ የፈለገውን የዘር አይነት እንዲቀርብለት አበክረው የሚሠሩ የልማት አጋሮች ሳይቀር፣ የዚህ አደናጋሪ አጀንዳ ሰለባ ሆነዋል።

ከሁሉ በጣም የሚገርመው ደግሞ በዚህ ሙቀት ተገፋፍተው በዘርፉ የተከበረ ስም ያላቸው ሳይቀሩ (የዘረመል ምህንድስና ቴክኖሎጂው ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳይገባ ከሚከላከሉት ዋነኛ ተቃዋሚዎች) ወጥነት ያለው ሐሳብ መሰንዘር ሲያዳግታቸው ታዝበናል። ኢትዮጵያን ወክለው በደኅንነተ-ሕይወት ስምምነቶች (Bio-safety conventions) ላይ ቁልፍ ተደራዳሪ የነበሩት ተወልደ ገ/እግዚአብሔር (ዶ/ር) እ.ኤ.አ በ2015 ፓርላማው ከዚህ ቴክኖሎጂ ጋር በተያያዘ ሕጉን ባላላበት ወቅት ‹የሕግ ማሻሻያው ለምርምር ዓላማ ብቻ የታሰበ ስለሆነ ምንም ችግር የለውም› ነበር ያሉት።

ነገር ግን ባለፈው ወር ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በፃፉትና፣ ከሳይንሳዊ እይታ ይልቅ ስሜታቸውን ባንፀባረቁበት ደብዳቤያቸው ቴክኖሎጂው በኢትዮጵያ ለማልማት ዝግጅት መደረጉ ስጋት እንዳላቸው አብራርተዋል። ለአካባቢ ደኅንነትና ብዝኀነት ተቆርቋሪ መሆናቸው እጅግ ቢያስመሰግናቸውም፣ እንግዲህ እርስ በርሱ የሚጣረሰው ሐሳባቸው ስናስተያየው ‹በአንድ ራስ ኹለት ምላስ› እንደሚባለው ሆነው እናገኛቸዋለን።

በአጭሩ የሕዝብ ቁጥራችን ማደጉን ተከትሎ ቴክኖሎጂው በአግባቡ ፈትሸን ከተጠቀምንበት ብዙ እናተርፍበታለን። እውነታው ይህ በሆነበት ያለ እውቀት ይነዛ የነበረው ያልተጨበጠ አሉባልታ በሕዝቡ ዘንድ እንደተለመደው ፍርሃትን በማንገሥ አገሪቷ እንዲሁ እንዳትረጋጋ በማድረግ ዐይናችን ከዋናው ጠላታችን ላይ ማስነቀል ነበር፣ ዓላማው።

እዚህ ጋር ሳልጠቅሰው የማላልፈው በጉዳዩ ዙሪያ አብዝተው ይዘግቡ የነበሩ አንዳንድ የመገናኛ ብዙኀን ሰዎች ተቃውሞውን ብቻ ለማጋጋል ሲተጉ ታዝበናል። ይህንን ለማለት ያስቻለኝ እውነታውን ለማጥራት በሚል በዘርፉ ከብዙኀኑ ኅብረተሰብ አንፃር የተሻለ ግንዛቤ ያላቸው ባለሙያዎች ለህትመት እንዲሆን ያዘጋጁትን ጽሑፍ ላለማተም የተለያየ ምክንያት በማቅረብ ወገቤ ሲሉ እንደነበር በጉዳዩ ዙሪያ ምን መደረግ እንዳለበት ከጓደኞቼ ጋር በተወያየንበት አጋጣሚ መስማቴ ነው።

የሐሳብ ጥይት የለውምና ሚድያው ሁሉንም ሐሳቦች አንባቢው እንዲዳኛቸው ማቅረብ ያለባቸው ይመስለኛል። ይህ ክልከላ ግን ለአገር ጥቅም ከማሰብ ይልቅ ከግል ጥቅም አኳያ እንደታየ መታዘብ ይቻላል። ክስተቱም በምዕራባውያን አገራት አንዳንድ ለግል ጥቅማቸው ያደሩ ግለሰቦች ለሰብዓዊ መብት መከበር የሚከራከር የሚመስል ተቋም ይከፍቱና በአዳጊ አገራት የሚገኙ መንግሥታትን ‹‹በዜጎችህ ላይ የፈፀምከውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሪፖርት እጄ ላይ ስላለ ከማወጣውና ዓለም ከሚያይህ የምትለውን በል” እንደሚሉት ‹ፌክ› የመብት አስጠባቂ ነጋዴዎች እንደሆኑ ይሰማኛል።

ይኸውም ይህንን ቴክኖሎጂ የሚያቀርቡ ትላልቅ የዘር ኩባንያዎች ለኅብረተሰቡ እየተላለፈ ባለው መረጃ፣ ሕዝቡ ስለቴክኖሎጂው ጥላቻ እንዳያድርበት የተወሰነ እጅ መንሻ ሊያቀርቡልን ይችላሉ ከሚል ስሌት የተዘየደ የግል ጥቅም ማጋበሻ ሊሆን እንደሚችልም መገመት ይቻላል። አልያም የበለጠ ለሕዝብ ጥቅምና ደኅንነት አሳቢ ተደርጎ ለመቆጠር ለወደፊቱ ተመራጭ ሚድያም ለመሆን ታስቦ ሊሆን ይችላል።

ነገር ግን ትርፉም ጥቅሙም የሚኖረው አገር ስትኖር፣ እንዲሁም ሕዝብ ተጠቃሚ ሲሆን ነው። የፖለቲካ ትርፍ ለማግኝት በሚል መረጃውን አጣመውና አዛብተው ያቀረቡት የአጀንዳ ቀራጮቹ ተልዕኮ ከዚህ የግል ጥቅም ካነገቡ አካላት ፍላጎት ጋር ተዳምሮ በወቅቱ አቧራው ከመጠን በላይ ማቡነን ተችሎ ነበር። በሂደት እየጠራ እየሄደ ያለ ጉዳይ ይመስለኛል።

የአፍሪካን አደራ በላች ሲሉን የነበሩት ግለሰቦች አሁን ተመልሰው እነኚህ የዘር ኩባንያዎች የፖለቲካ ሽግግር ሲደረግ ጠብቀው ለመግባት የሚያደርጉት ጥረት ከዓመታት በፊት በደቡብ አፍሪካ ታይቷል እያሉ ይገኛሉ። እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ የዚህ ከእውነታው በጣም የተጣመመ አሳሳች መረጃ ዋናው ግቡ ከዋናው ትኩረታችን ላይ ዐይናችንን እንድንነቅል ለማስገደድ ነበር።

ማደናገሪያ ወሬ አራት
በመቀጠል የተነሳው አቧራ ግብፅንና ደቡብ ሱዳንን ያገናኘ ሲሆን፣ ለሰሚው እንኳን ለማመን እንዲከብድ ያደረገው የደቡብ ሱዳን ባለሥልጣናት በጉዳዩ ዙሪያ አሉት እየተባለ የሚወራው የማይሆን ወሬ ነው። ይሄ የሰሞኑ አጀንዳ ስለሆነ አሁንም ጨርሶ የረገበ አይመስልም። ወሬው ተዓማኒ እንዲመስል ከደቡብ ሱዳን የሚታተም በሚመስል ጋዜጣ እንዲናፈስ ተደርጓል።

ይህም ግብፅ ከደቡብ ሱዳን መንግሥት ጋር በመስማማት ወታደራዊ ሰፈር ከግድባችን ተጠግታ ልትመሰርት እንቅስቃሴ መጀመሯን ያረዳል። የደቡብ ሱዳን ባለሥልጣናት እንዲያረጋግጡ ሲጠየቁ ስለዚህ ጉዳይ መንግሥታቸው የሚያውቀው እንደሌለ መግለፃቸው ይታወሳል። ወሬው በዚህ ሳይገታ ከቀናት በኋላ የአገሪቱ የጦር ሚኒስትር ‹‹እኛ ከግብፅ ጋር በሚኖረን ግንኙነት ኢትዮጵያ ጣልቃ ልትገባ አትችልም›› በማለት መግለጫ ሰጡ ተባለ።

እየተከታተለ የውሸት መረጃዎችን ከመንግሥት በበለጠ እያመከነ ላለው ጋዜጠኛ ኤልያስ መሰረት ምስጋና ይድረሰውና፣ ለዚህ ጉዳይ ከሚገለገልበት የማኅበራዊ ሚድያ ገፁ በኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳን አምባሳደር አነጋግሮ ባለሥልጣኑ እንዳሉትም ‹‹ተናገረች የተባለችው የመከላከያ ሚኒስትር በኮቪድ 19 ተይዛ በማገገም ላይ የምትገኝ ሲሆን፣ ሥራው በምክትሏ ነበር እየተሠራም የነበረው። በመሆኑም በአጭሩ ይህ እየተወራ ያለው የፈጠራ ወሬ መሆኑን ያረጋግጥልሃል።›› ብለውታል።

አምባሳደሩ አያይዘውም ‹‹የእንዲህ አይነት ሐሰተኛ መረጃዎች ምንጭ የደቡብ ሱዳን ተቃዋሚዎች እንዲሁም ሌላ አላማ ያላቸው ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ሰዎች ሊሆኑ ይችላሉ›› ሲሉ እንደገለፁለትም ጋዜጠኛው ጽፏል። እንዲያው ምልክት ካላየን አናምንም እንጂ እንዲሁ ይህንን መረጃ እውነትነት ይኖረዋል ብሎ ለመቀበል ይከብዳል። የዓለማቀፍ ሕግ የሚያመጣባቸውን ተጠያቂነት ላይ እንዲያው በግርድፉ ከመስማት ይልቅ የጠለቀ እውቀቱ ስለሌለኝ ምንም ማለት ባልችልም፣ የደቡብ ሱዳን መንግሥት ይህንን በጎረቤቱ ላይ ለመፈፀም ይደፍራል ብሎ ለመቀበል እጅጉኑ ይከብዳል።

የደቡብ ሱዳን ባለሥልጣናት ከግብፅ የባሰ በወራሪነት አገራቸው በኢትዮጵያውያን ዘንድ በመታየት የጦስ ዶሮ ሆነው ለመቅረብ እንዴት ይፈልጋሉ? እንዲህ እንዲሆን ደግሞ ሁሉም ባለሥልጣኖቿ ጨርሰው ማበድ ይጠበቅባቸዋል። አምባሳደሩ እንዳሉት የዚህ ‹የሐሰት መረጃ› ጋጋታ ኢትዮጵያውያን ዐይናቸው ከዋናው ትኩረታችው ላይ ለአፍታም ቢሆን እንዲነቅሉና በዚህም ወዳልተፈለገ ቀውስ እንዲያመሩ ነው። እንደ አምባሳደሩ ገለፃ ይህ የጥፋት ተልዕኮ ያነገቡ ኢትዮጵያውያንም ሊሆኑ እንደሚችሉ ነው። በገዛ አገሩ ላይ እንዲህ አይነት ደባ ለመፈፀም መትጋት ግን ምን ይሉታል? ይሄ በእውነቱ መረገም ነው።

ማደናገሪያ ወሬ አምስት
በቅርቡ ቢቢሲ አፍሪካ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር በፓርላማ ባደረጉት ንግግር ‹‹በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ግብፅን መለመን ሰለቸን›› አሉ የተባለው ሌላው አዲስ የቀረበልን አደናጋሪ አጀንዳ እንደሆነ ልብ በሉልኝ። እነዚህ የሐሰት የፈጠራ ወሬዎች በአዕምሮዬ ሳሰላስል ለእኔ የዘመኔ ጠቢብ የሆነው ከዲያቆን ዳንኤል ክብረት በአንድ ወቅት ለሚድያ ሲናገር ከእሱ የሰማሁት የሚመስለኝ ታሪክ ድቅን አለብኝ። የጠቀስኳቸውን ትዝብቶቼንም ይህ ታሪክ ይጠቀልልልኛል።

ታሪኩ በአንድ አገር ለረጅም ዓመት በንግሥና ስለቆየ ሰውና ስለዚሁ የረጅም ዘመናት ንግሥና ምስጢር ማወቅ ስለፈለገ አንድ ግለሰብ ነው። ይህ ግለሰብ ለንጉሡ ጥያቄውን ያቀርባል። ንጉሡም ለረጅም ዓመታት በንግሥና የቆየበትን ጥበብ ለማስረዳት በቅድሚያ ሰውዬውን አንድ ነገር እንዲከውን ትዕዛዝ ይሰጠዋል። ይኸውም ውሃ በብርጭቆ እስከ አፉ ድረስ ሞልቶ ይሰጥውና ‹‹ቤተመንግሥቱን ዞረህ ተመለስ፣ ነገር ግን አንዲት ጠብታ ውሃ መሬት ላይ የወደቀብህ እንደሆነ ምስጢሩን አታገኘውም›› በማለት ያስጠነቅቀዋል።

እንደተባለው ሰውዬው እስከአፉ ተሞልቶ የተሰጠውን ብርጭቆ ይዞ ዐይኑን ከብርጭቆው አፍ ላይ ሳይነቅል ቀስ እያለ በመጓዝ የቤተመንግሥቱን ዙርያ በማካለል በስተመጨርሻ ከንጉሡ ዘንድ ይደርሳል። የታዘዘውን በሚገባ መከወኑን ያውቃልና ጥበቡን ለማወቅ ንጉሥ ሆይ አሁን ይንገሩኝ አለ።

ንጉሡም ወደ መልሱ የሚያመላክቱ ጥያቄዎችን መጠየቅ ፈለገና ‹‹በመንገድህ የሚጨፍሩ ሴቶችን አይተሃል?›› በማለት ሲጠይቀው ሰውዬው ‹‹በፍፁም አላየሁም›› አለው። ንጉሡ ቀጠለና ‹‹ሜዳው ላይ የሚግጡ እንስሳትና እነሱን የሚጠብቁትን ልጆች አይተሃል?›› ሲለው ሰውዬው አሁንም ደገመና ‹‹አላየሁም›› አለ። በመጨረሻ ‹‹መትረየስ ተጠምዶ ኢላማ የሚያስተካክሉ ወታደሮችስ አይተሃል?›› ሲለው ሰውዬው በመሠለስ ‹‹ኧረ በፍፁም›› አለ።

ንጉሡም መልሶ እንዲህ አለው፤ እነኚህን የጠየቅሁህን ሁሉ አይተኻቸው ቢሆን ኖሮ ዉሃው ጠብ ሲል ኢላማ ያነጣጠሩብህ ወታደሮች ተኩሰው ይገድሉህ ነበር። ነገር ግን በኹለቱም ዐይኖችህ ትኩረትህ የብርጭቆው አፍ ላይ በማድረግህ በሰላም ተመልስህ ልትመጣ ችለሃል። ስለዚህ ዋናው ጉዳይ ላይ ትኩረት ማድረግህ እድሜህ እንዲቀጥል ምክንያት ሆኖልሃል። የእኔም የንግሥናዬ ምስጢሩ ንግሥናዬን በሚያስቀጥለው ላይ ትኩረቴን አለመንቀሌ ነበር አለው።

አንድ ያጣላልና ለምርቃት እንዲሁ ከሰማሁት ከጉዳዩ ጋር የሚመሳሰል ልጨምር። የዚህ ታሪክ ደግሞ ከትራፊክ ፖሊስ ሪፖርት ጋር የሚገናኝ ነው። ይኸውም በጠዋት የቀደመው ቀን የትራፊክ ፍሰቱ ሪፖርት የሚያቀርበው ባለሙያ የሚያስተላልፈው መረጃ እውነትነት ቢኖረውም በጣም ቁንጽል የሆነው ነገር የበለጠ ትኩረት የሚስብ መሆኑን ነው።

ለምሳሌ በአዲስ አበባ ብቻ ብዙ ተሽከርካሪ ወደጎዳና ወጥቶ ሲሽከረከር የሚውል ሲሆን፣ በዕለቱ አንድ ወይም ኹለት አሊያም ቢበዛ አምስት የመኪና ግጭት አደጋ ሊያጋጥም ይችላል። በዚህ አይነት አሳዛኝ አደጋ እንዲሁ ኹለት ወይም ሦስት ሰው ሊሞት ይችላል። የአንድም ሰው ሕይወት ቢሆን በምንም ነገር አይተመንም። ዋናው ነጥብ ግን ርዕስ የሚሆነው በሰላም የገቡት በሺሕዎች የመቆጠሩ ተሽከርካሪዎች አልያም በሚሊዮን የሚገመቱት ተሳፋሪዎች ሳይሆኑ፣ የአንድ ወይም ኹለት ሰዎች መሞት ይሆንና ኅብረተሰቡ ‹‹ዘንድሮማ ከሌላው ብንተርፍ በመኪና አደጋ ማለቃችን አይቀርም›› የሚለውን አብዝቶ ይናገራል። እምብዛም ርዕስ የማይሆነው ርዕስ ይሆንና ዐይናችንን ከዋናው ስዕልና እውነታ ላይ (በሰላም ከገቡት በሚሊዮን ከሚገመቱትና ከሚጠቅመን ላይ) እንድንነቅል እንገደዳለን ማለት ነው።

ለማጠቃለል
እኛ ከሌለን ኢትዮጵያ ልትኖር አትችልም በሚመስል መልኩ የሚነዛ አደናጋሪና አሳሳች የፈጠራ ወሬ አቅራቢ አጀንዳ ፈጣሪዎች ‹‹አገሪቷ ከሌለች የእኔስ መጨረሻ መጥፋት አይደል!›› ብለው እራሳቸውን መጠየቅ አለባቸው። እውነታውም ይሄ ነው። አገርና ሕዝብ ሁሌም ቋሚና ዘላቂ ነው። ተቋማትና ፓርቲዎች ጊዜ እንዳመጣቸው ከጊዜው ጋር ተመልሰው ይሄዳሉ። ለዚህ ለሦስት አስርት ዓመታት የዘለቀውና በቅርቡ የከሰመው ኢሕአዴግ ምስክር ነው።

የሁሉም እጣ ፈንታ ከዚህ የተለየ አይደለም። መኪናዋን እኔው እራሴ መሪዋን ይዤ ካልሾፈርኳት እሰባብራታለሁ አልያም እንድትገለበጥ አደርጋታለሁ ማለት መኪናዋ ስትገለበጥ ሁሉም አብሮ የሚጠፋ መሆኑን ዝንጉነት ያለበት ይመስላል። እሳቱ እኔ ዘንድ አይደርስም ማለት ሞኝነት ነው። በመሆኑም ዳፋው በአገርና ሕዝብ ላይ የሚተርፍ ሴራ ከመጎንጎን የአገርንና ሕዝብን ጥቅም በማስቀደም በኃላፊነት ስሜት ዘመኑን በዋጀና በሠለጠነ አግባብ በመነጋገር ልዩነትን መፍታት ይገባል።
በተያያዘም ሁሉም ጠቅልሎ ለእኔ ይገባል ማለትን ሳይሆን የሚገባንን ድርሻ ይዘን ቦታችን ላይ ተቀምጠን በመሳፈር በሰላም መጓዝ ለሁሉም ይበጃል። በየጊዜው የሚነዛው ውዥንብርና አደናጋሪ የፈጠራ ወሬዎች ከድል ለማድረስ ከጀመርናቸው የአጭርና የረጅም ጊዜ መዳረሻ ግባችንና የስኬት መንገድ አስወጥቶን እጣ ፈንታችንም አሁን በአዲስ አበባ ጎዳናዎች የምናያቸው በአለመረጋጋት የተነሳ አገራቸውን ጥለው እንደኮበለሉት የሶርያና የየመን ስደተኞች እንዳንሆንም ያሰጋል። ይህ እንዳይሆን ዐይናችንን ከዋናው ትኩረታችን ላይ በፍፁም መንቀል የለብንም።

ሽመልስ አርአያ በጀርመን አገር ከሚገኘው ጊሰን ዩኒቨርሲቲ በግብርና ኢኮኖሚክስ፣ ባዮኦኮኖሚ እና በገጠር ልማት የዶክትሬት ዲግሪ አግኝተዋል። ከዚህ ቀደም በሐዋሳ ዩኒቨርስቲ በኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል በመምህርነት አገልግለዋል። በaraya.gedam@gmail.com አድራሻቸው ማግኘት ይቻላል።

ቅጽ 2 ቁጥር 84 ሠኔ 6 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here