በሥነምግባር የታነጹ፣ አምላካቸውን የሚፈሩ፣ ለሰው ክብር ያላቸው፣ ትሁትና ደግ ናቸው ይባላል። ሲመራ የኖረበት ስርዓት ሰብአዊነትን ያከበረ፣ ከተፈጥሮ የማይጋጭና ትክክለኛ እንደሆነ ይታመናል፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ። ድፍን አገርን ይወክላል ማለት ባይቻልም፣ እየሆነ የሚታየው ግን ከዛ ፍጹም…ፍጹም ተቃራኒ ነው።
በመዲናይቱ አዲስ አበባ ጎዳናዎችና ጓዳዎች፣ ጨለማን ተገን አድርገው የሚፈጸሙ ተግባራት ‹እውነት ይህ ኢትዮጵያ ውስጥ ነው?› የሚሰኙ ናቸው። በተለይም ሴት ልጆች ላይ የሚደርሱ በደሎችና ጥቃቶች፣ እናቱን በሴት አንቀጽ የሚጠራ ለሞላባት፣ ለእናት የተዘፈነ እልፍ ሙዚቃ በሚንቆረቆርባት አገር፣ እጅግ አሳዛኙ ኹነት ነው። ከዚህ የባሰም ግን አለ። በዚህም አውድ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ መከሰት ስጋት አይደለም፣ ይልቁንም ወጣትና አዳጊ እድሜ ክልል ላይ የሆኑ ሴቶች በቀላሉ እንዲገኙ ያስቻለ መልካም አጋጣሚ እንጂ!
አዲስ ማለዳ በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች ተንቀሳቅሳለች። የራቁት ጭፈራ ቤቶች፣ ሴቶች እንደ እቃ ለጨረታ የሚቀርቡበትና የሚሸጡበት፣ በእድሜ የገፉ ሰዎች ለመዳራት ንቁ የሚሆኑበትና ከዛም አልፎ ግልጽ ወሲባዊ መዳራቶችን ታዝባለች። ጉዳዩንም የሐተታ ዘ ማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አድርጋ፣ ለጋዜጣ በሚመች መልኩ እንዲህ ከትባዋለች።
ከሰሞኑ ምሽቱን ሲያደበዝዝ እና በቆፈን ሲሞላው የነበረው ዝናብ ረገብ ብሏል። አዲስ አበባ ከተማ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያንም ጨምሮ የተከሰተውን የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ተከትሎ ውሎ እና አዳሯ ቀዝቀዝ ያለ ይመስላል። በተለይ ደግሞ ዝናብ እና የብርዱ ሁኔታ ሲታከልባት መልዓከ ሞት ሰይፉን ይዞ የሚንጎራደድባት በሚመስል አኳኋን ጭርታዋ ሆድን ያሸብራል።
በተለይ ደግሞ የአዲስ አበባን ግርግር በተመስጥኦ ለሚከታተል እና የዕለት ተዕለት ባተሌነቷን እና ጩኸቷን እንደ ጥዑም ዜማ ሲዝናናበት ለኖረ፣ የአሁኑ ዝምታዋ ቢያስጨንቀው አይገርምም። እንደምን ቢሉ ቅንጡ ሆቴሎቿ በእንግዳ ዕጦት ፈዘው ውለው፣ ጨምተው ያድራሉ። ከተማዋ በምሽት እንዳትጨልም ድምቀት የሆኑት የምሽት ክበቦች ልሳናቸው ተዘግቶ ከተማዋን አስከሬን የወጣበት ሰፊ ድንኳን ማስመሰል ከጀመሩ ዋል አደር ብለዋል።
ነገር ግን ኮቪድ 19ኝን ለመከላከል በወጣው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በግላጭ የተከለከለው የአዲስ አበባ የአስረሽ ምችው ፈንጠዝያ በአንዳንድ ስፍራዎች የሰሚን ጆሮ ጭው በሚያደርግ ሁኔታ መከናወኑ አልቀረም። ይህ ብቻ ሳይሆን በዋናነት የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ባይኖር፣ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁንም ባይንተራስ፣ ከባድ ወንጀል እና ሕግ መተላለፍ ለመሆኑ ጥርጥር የሌላቸው ጉዳዮች እየተካሔዱ ይገኛሉ።
መሠልጠን መሰይጠን የሆነብን ይመስል ከባህል፣ ከወግ እና ልማድ ከኢትዮጵያዊነት ስነ ስርዓት በእጅጉ ያፈነገጡ እና ከአዲስ አበባ ጉያ አልፎም ከኢትዮጵያ ሰማይ ስር ይህ ይደረጋል ወይም እየተደረገ ነው ቢባል ለማመን የሚቸግር ከባድ፣ አሳፋሪና አሳዛኝ ድርጊቶች ይከናወናሉ።
አዲስ ማለዳ ይህን ጉዳይ በአካል በመገኘት ለመታዘብ እና የተለመደውን የምርመራ ሪፖርት ለመሥራት እጅግ ጥብቅ እና ምስጢራዊ የሆኑ ስፍራዎችን በተለመደው ሁኔታ እና ጥንቃቄ በተሞላበት አካሔድ ለመከወን ሞክራለች፤ አብራችሁን ዝለቁ።
በአገር ዐቀፍ ደረጃ ከተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር በተገናኘ የምሽት ቤት እና ሌሎች በርካታ ሰዎች መሰብሰቢያዎች አገልግሎት የሚሰጡት እስከ ተወሰነ ሰዓት አንዲሆን መደንገጉ ይታወቃል። ይሁን እንጂ ገንዘብ የማይሠራው ጉድ የለም እና በአዲስ አበባ አንዳንድ ቦታዎች በተለይም ደግሞ አዲስ ማለዳ በአካል ተገኝታ ለመታዘብ የቻለቻቸው ሦስት ጥብቅ እና ምስጢራዊ ስፍራዎች ግን ጉዳዮ ከወቅታዊ ሁኔታው በእጅጉ የተለየ ነው።
ምስጢራዊው የምሽት ቤት ቁጥር 1
ቦሌ ከወሎ ሰፈር ወደ ጎተራ በሚወስደው ኢትዮ ቻይና ወዳጅነት ጎዳና አካባቢ። ስፍራው ከጸጥታው እና ከጨለማነቱ የተነሳ በአካባቢው ምን እየተደረገ ለመሆኑ ማንም ምንም አይነት እውቀት እንደውም ግምት ይኖረዋል ተብሎ አይታሰብም። የአካባቢው ጸጥታ ከገዳም የሚያስንቅ ሲሆን እንዲያ ባለ እና ቅንጡ መኖሪያ ቤቶችን አቅፎ ለያዘ መንደር ግን በአንዲት የመንገድ ላይ መብራት ማጣት ጽልመት ሲውጠው መመልከት ትንሽ ግርታን የሚፈጥር ጉዳይ ነው። ቢሆንም ጉድ እና ጅራት ወደ ኋላ ነው እና ቆይተን እንመለስበታለን።
የምስጢራዊው ምሽት ቤት መከፈቻ ሰዓት ከምሽቱ አራት ሰዓት በመሆኑ ምሽቱን ገፋ አድርጌ ነበር የደረስኩት።
ወደ ቤቱ ለመዝለቅ አስቀድሜ በተወዳጀሁት እና ውሎ እና አዳሩን ለማየት በጓጓሁለት የከፍተኛ ኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ባልንጀራዬ እና በአሁኑ ሰዓት ከቤተሰብ ጋር ባለው ንግድ ሀብት ማማ ላይ በተቀመጠው ሰው በኩል ስሜ ተላልፎ ጠብቆኛል። ከባልንጀራዬ ጋር በአንድ መኪና እንደመጓዛችን ደጅ ላይ ስንደርስ ባልንጀራዬን ሞቅ ባለ ሰላምታ እኔን ደግሞ ከእግር እስከ ራስ በሚያመሰቃቅል ፍተሻ እና አፈር ከድሜ በሚደባልቅ ግልምጫ መግባት ቻልኩ።
የጊቢውን ዙሪያ ገባውን ቆሞ መመልከትም ሆነ በጊቢው በረንዳ ላይ ወይም ቢያሻችሁ ሳር ላይ ተቀምጦ መጠጣት ፍጹም መብት ነው። ጊቢው ፈረስ ያስጋልባል ቢባል ማጋነን አይሆንም። እጅግ ሰፊ እና ማራኪ ሲሆን መንደር ውስጥ ያለው ጽልመት እዚህ ጊቢ ውስጥ ዕጣ ፋንታ እንደሌለው ያሳያል። የሆነው ሆኖ አሁን ወደ ቤቱ ውስጠኛ ክፍል በመግባት ላይ ነን።
ወደ ውስጠኛው ክፍል አልፎ ለመግባት በር ላይ መስታወት በመስታወት በተሠራች አነስተኛ ክፍል ላይ ካለች እንስት ትኬት መቁረጥ ያስፈልጋል። የትኬት ቆራጯን ትህትና እና መልከ መልካምነት እንዲሁም የሽቶዋን መዐዛ ለታዘበ የቤቱ ትኬት ቆራጭነት ሥራን ቢመኝ አይፈረድበትም። ወደ ውስጠኛው ክፍል ለመግባት 1 ሺሕ 500 ብር መክፈል ግዴታ ነው። ‹አይ! አይሆንም› ላለ ውጪ በረንዳ ላይ ብርድ እያንዘፈዘፈው የመጠጣት መብቱ የተጠበቀ ይሆናል ማለት ነው። በነገራችን ላይ የአንድ ሺሕ አምስት መቶ ብር ለተከፈለበት አንዲት ከጉሮሮ የማትወርድ የራሺያ አረቄ ‹‹ስሚርኖፍ›› በጠረጴዛው ላይ በነጻ ይቀመጥለታል።
ወደ ዋናው ጉዳይ ስንገባ፣ ቤቱ ከሮዛማ እና ከፊል ቀይ ደብዛዛ መብራቶች ባለፈ እምብዛም ብርሃን አይታይበትም። እየቆዩ ሲሔዱ ደብዛዛውን ውስጣዊ ክፍል ተላምደው እርስዎም የዛው አካል እንደሚሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም። በቤቱ ውስጥ ለጆሮ በሚመጥን የተከፈተውን ለስላሳ ሙዚቃ በቄንጠኛ ምት እየተከተሉ በቤቱ መሀል ላይ በዝግታ የሚደንሱ ኃፍረታቸውን በእራፊ ጨርቅ የሸፈኑ የሃያዎቹ መጀመሪያ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ቆነጃጅት አሉ።
ይህ አዲስ አበባን ቀዳሚ የራቁት ዳንስ ቤቶችን ታሪክ ላነበበ እና በአካል ተገኝቶ ለታዘበ የሚገርም ጉዳይ ላይሆን ይችላል። ነገር ግን አስገራሚው ጉዳይ በሌላኛው የቤቱ ክፍል የሚከናወነው የጨረታ እና የዋጋ ድርድር ሒደት ነው። በዚህኛው ክፍል መጠጡም ይቀየራል፤ የዋጋውን ውድነትም አይቶ መለየት አያስቸግርም። በዚህ ክፍል ውስጥ ሴት ልጅ እንደ ዕቃ ዋጋ ይተመንላታል፣ ገዢዎቿ ይደራደሩባታል፣ ሻጮቿም አብልተው እንዳሳደጉት እንስሳ ዋጋውን እሷን ተክተው ይደራደራሉ።
የሴቶች ዋና ተግባርም እናቶቻቸው እንደወለዷቸው ራቁታቸውን ሃፍረተ ስጋቸውን እንኳን ሳይሸፍኑ በተዘጋጀላቸው መድረክ መሳይ ከፍ ያለ ስፍራ ላይ ረጅም ታኮ ባለው ጫማ መንጎራደድ እና አንዳንዴም በፎርም መቆም ብቻ ነው።
በዚህ ስፍራ ድንግልና ከባዱን ስፍራ የሚይዘው መደራደሪያ ነጥብ ነው። በአጋጣሚ ሆኖ በስፍራው በተገኘሁበት ወቅት ድንግልናዋን በእነዚህ ደላሎች አማካኝነት ለመሸጥ በስፍራው የተገኘች ሴትን ማግኘት አልተቻለም ነበር። ይሁን እንጂ በስፍራው ከሚገኙ ግለሰቦች እና ፍትወትን ጮክ ባለ ደምጸት ከሚያወሩት ሰዎች ለመረዳት እንደተቻለው፣ በቀደሙት ጊዜያት ድንግልና በዚህ ቤት ውስጥ እስከ 55 ሺሕ ብር እንደተሸጠ ለመታዘብ ተችሏል።
ስፍራው ባለ አንድ ፎቅ ሰፊ መኖሪያ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የአልጋ አገልግሎትም ይሰጣል። በጨረታው የተስማሙ እና ሴቷን የወሲብ ባሪያ ለማድረግ እና ከኹለት ቀን እስከ አንድ ሳምንት ድረስ አብሮ ለማሳለፍ ከ10 እስከ 30 ሺሕ ብር ድረስ ጨረታው ሊቀጥል ይችላል። በዚህም መንገድ ኹለት በገንዘብ ብዛት አቅላቸውን የሳቱ የሚመስሉ ባለሀብቶች እያንዳንዳቸው አንድ አንድ ታዳጊ ሴቶችን በ20 እና በ23 ሺሕ ብር በመግዛት ለቀጣይ ሦስት ቀናት በዛው ቤት ውስጥ ለማሳለፍ እና ምግብና መጠጣቸው እንዲመቻችላቸው ከቤቱ ሥራ አስኪያጅ ጋር በግልጽ ትዕዛዝ ሲሰጡ ተመልክቻለሁ፡፡
በስፍራው የተደረገውን ሴት እህቶቻችንን ለግልጽ ጨረታ አውጥቶ መሸጥ መለወጥ ሲካሔድ በፍትወት ላበዱት ትልቅ ደስታ፣ ሁኔታውን ረጋ ብሎ በሰከነ አዕምሮ ለሚታዘብ ግን ትልቅ ሕመም ነው።
የመጀመሪያውን ምስጢራዊ የምሽት ቤት ለቀን እየወጣን ነው። አሁንም አሁንም ሲጋራውን ከሚለኩሰው ባልንጀራዬ ጋር ስለ ምሽት ቤቱ ድብቅነት እና ምስጢራዊነት እያወራን ‹‹እዚህ እየመሸግህ ነዋ የምትጠፋው›› በሚል በቀልድ እያወጋን ከጊቢው ወጣን። በዚህ ወቅት ታዲያ አንድ ጉድ ታዝቤያለሁ።
አስቀድሜ እንደነገርኳችሁ የአካባቢውን ጽልመት እና ከመኖሪያ መንደሩ ጋር ሲነጻጸር ማስታረቅ አቅቶኝ እንደነበር ጠቁሜያለሁ። እንዴት እንኳን ለመንደራቸው ለአገር መብራት ማስገባት የሚችል ሀብት ኖሯቸው በጨለማ መንደር ውስጥ ይኖራሉ ብዬ የጠየኩበት ሁኔታ አሁን ተገልጦልኛል። መኪናችንን ወደ አቆምንበት ስፍራ ስናመራ በኹለት ተከታታይ መኪኖች ውስጥ ከምስጢራዊው ምሽት ቤት ወጥተው መኪና ውስጥ ግብረ ስጋ ግንኙነት ሲፈጽሙ ተመለከትን። የጽልመቱን መነሻ እና ዓላማም በግልጽ ለመረዳት ቻልን።
ምስጢራዊው ምሽት ቤት ቁጥር 2
አዲስ ማለዳ አሁንም ወደ ድብቅ እና እጅግ የተጠበቁ መኖሪያ ቤቶች በሚመስሉ ነገር ግን በውስጣቸው የሚካሔደውን ለመገመት የሚከብድ ስፍራዎች በመገኘት ትዝብቷን እና ምርመራ ዘገባዋን ቀጥላለች። በዚህ ድብቅ እና ምስጢራዊ የምሽት ክበብ ለመግባት እንደ መጀመሪያው ቤት በሰው በኩል ወይም ከአንድ ውስጥ አዋቂ ሰው ጋር ሳይሆን በግል ለመግባት የሚያስችለኝን መረብ ከመጀመሪያው ቤት ካገኘሁት ወጣት ጋር ዘርግቻለሁ።
ከወጣቱ ጋር ያደረግነውን ጨዋታ እመለስበታለሁ። ነገር ግን በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ልዩ ሥሙ ብስራተ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው፤ አካባቢው። ወደዛ ለመምጣት በፈለኩኝ ጊዜ የኮድ ሥሙን በመጠቀም ማስጠራት እንደምችልና ተገቢውን እንክብካቤ እንደሚለግሰኝ ተጨዋውተናል።
አሁን ከዚህ ቀደም ከነበረው ቤት ይልቅ ከፍተኛ ጥንቃቄ እና ራስን በገንዘብም የማደርጀት እንዲሁም ሌሎች አስፈላጊ መንገዶችን መጠቀም እንደሚኖርብኝ ተገንዝቢያለሁ። ይህንንም በመጠቀም ቅንጡ አሜሪካ ስሪት ሆንዳ ተሽከርካሪን በመያዝ በስፍራው የዘወትር ተጠቃሚዎችን ቢያንስ ለመምሰል፣ ካልሆነም ለመቀራረብ ያደረግኩት ሙከራ የተሳካ ይመስላል።
በተነገረኝ ምልክት መሰረት ወደ ስፍራው ለመድረስ ትንሽ ተደናግሮኝ ነበር፣ በመሆኑም አንድ ወጣት በደቡብ አፍሪካ ኤምባሲ አካባቢ እንደሚጠብቀኝ ተነግሮኝ ስፍራውን በማሳየት ተባብሮኛል። ደፍሮ መኖሪያ ቤት ብሎ ለመጥራት ትንሽ የሚከብድ ግን ደግሞ ስሪቱ የመኖሪያ ቤት የሆነ በቅርቡ የገበያ ማዕከል ተብለው ከተሰየሙ ሕንጻዎች ጋር ሊስተካከል ምንም የማይቀረው ባለ ሦስት ደርብ መኖሪያ ቤት ነው።
በቀጥታ ወደ ጊቢው ውስጥ መግባት እንደምችል በመንገድ አመላካቼ በኩል ስለተነገረኝ የመኪናዋን ጥሩምባ አሰምቼ በሩን አስከፈትኩ። ከበር ጠባቂው የመጣው የቁጣ መልክ እና ድምጸት የሚያስበረግግ ቢሆንም ጨዋታው ተጀምሯል እና መደንገጡ አያዋጣም። ስሜን እና የተሽከርካሪዬን የሰሌዳ ቁጥር ቀድሞ የደረሰው ቢሆንም፣ ጥሩምባ ማሰማቴ ከፍተኛ ብስጭት ውስጥ እንደከተተው ለመረዳት አልከበደኝም።
ሽንጠ ረጅሟን ተሽከርካሪ ቦታ አስይዤ በተረጋጋ አካሔድ ወደ መኖሪያ ቤቱ የውስጥ ክፍል ለመግባት አምስት ያህል ደረጃዎችን መውጣት ጀመርኩ። በደረጃዎቹ መጨረሻ እና በውቡ የመኖሪያ ቤቱ መግቢያ የእንጨት በር ላይ ግዙፍ የሆነ ወንድ እና እንደ መጀመሪያው ቤት ተመሳሳይ ዘናጭ ሴት ቆመው በትህትና ተቀብለው ወደ ውስጠኛው ክፍል ጋበዙኝ። እንዴት የመግቢያ እንዳልከፈልኩኝ እያሰላሰልኩኝ ነበር ከቤቱ እንግዳ መቀበያ የደረስኩት። በአርምሞ የተሞላው የጊቢው ዙሪያ ገባ እዚህ ቦታ ላይ ሲደርሱ ግን ፍጹም ይለያል። የሴቶች ሳቅ መስኮቱን በሩን ግድግዳውን አልፎ ከወንዶች ጭብጨባ ጋር ተዳምሮ ጆሮዎት ጋር ይደርሳል።
በእንግዳ መቀበያው ደርሼ ‹‹ወዴት መሔድ ይፈልጋሉ›› ዓይነት ጥያቄ ሲቀርብልኝ፣ የአገልግሎታቸውን ዝርዝር እንድታስረዳኝ በር ላይ ካየኋት ሴት እጥፍ የምትቆነጅ ሴትን ጠየኳት። ቤቱ ሦስት ፎቅ እንደመሆኑ የተለያዩ አገልግሎቶች እንደሚሰጥ እና ከራቁት ጨፋሪዎች እስከ ምንም ልብስ የማይለብሱ የሴት አስተናጋጆች ብሎም በቀጥታ ወሲብ እስከ ሚከናወንበት ክፍሎች መኖራቸውን አረዱኝ።
ጆሮዬን ለማመን እና ራሴን እንደመሳት ያደረገኝ በቀጥታ በሰዎች ፊት ወሲብ እንደሚፈጸም የሰማሁበት ቅጽበት ነው። እውነትም ራስን የሚያስት ነበር። መግቢያው ይለያያል፣ ቢሆንም ከራቁት ጨፋሪዎች ዘንድ ለመግባት 500 የኢትዮጵያ ብር ይከፈላል። ከፍ ያለው ጋር ለመግባት ደግሞ 1000 ብር እና መጨረሻው ግን ኹለት ሺሕ ብር መሆኑን ከሚሰጡት አገልግሎቶቻቸው አንጻር አስረዱኝ።
በዚህ ወቅት ታዲያ ቤታቸውን ያወኩት አንድ ወጣት የኮድ ስሙን በመጥቀስ እንድመጣ እንደነገረኝ እና እርሱን ማግኘት እችል እንደሆነ ጠየኩኝ። በአጋጣሚ በቤቱ አንደኛው ክፍል ከእንግዶች ጋር ኖሮ ሲደወልለት አፍታም ሳይቆይ ነበር ወደ እኔ በመምጣት በሞቀ የወዳጅነት ሰላምታ የተቀላቀለኝ። የእርሱ እንግዳ መሆኔን በመናገር 1 ሺሕ ብር ብቻ በመክፈል የቤቱን የትኛውም ክፍል ላይ የመዝናናት ሙሉ መብት እንዳለኝ ነግሮኝ በልዩ እንክብካቤ ወደ ራቁት ጭፈራ ቤቱ ውስጥ ይዞኝ ገባ።
አሁን የባለሀብት እንቅስቃሴ ነው የሚከወነው። እኔም ወደ ከፍተኛ ከበርቴነት ተለውጫለሁ። በቤቱ ውስጥ ከመጀመሪያው ቤት ይልቅ የሙዚቃው መጠን ከፍ ያለ ከመሆኑ የተነሳ በአስጎብኚዬ የሚነገረኝን ሁሉንም ጨዋታ ለመስማት በከባዱ ወደ ወጣቱ ልጅ መጠጋት ይኖርብኛል።
ይህ ወጣት ልጅ በከተማችን አሉ ከሚባሉ እና ለታላላቅ የከተማችን ባለሀብቶች ለጋ ሴት ልጆችን በማቅረብ ከፍተኛ ገቢ የሚያገኙ የከተማችንን እንስቶች ከአርቲስት እስከ ቢሮ ሠራተኞች ድረስ ጠንቅቆ የሚያውቅ ወጣት ነው። የጨዋታውን ፍሰት ላለማቋረጥ እና የሚናገረው ላሰብኩት ዓላማ እጅግ ጠቃሚ ነበርና አምስት ባለ መቶ ብር ኖቶችን ጉርሻ መስጠት ነበረብኝ። ምሽቱንም ብቸኝነት እንዳይሰማኝ ከእኔ ጋር እንደሚያሳልፍ ቃል ገብቶልኛል።
አሁን ወዳጅነታችን ጠንክሮ በከተማው ስማቸው የናኘ ባለሀብቶችን እና የከተማችንን ውብና ታዋቂ ሴቶች ቅሌት በፎቶ እያስደገፈ ሲያስኮመኩመኝ ጨዋታችንም እየተጋጋለ ሔደ። በነገራችን ላይ እዚህ ቤት ሲገባ ምንም አይነት ስልክም ሆነ ኤሌክትሮኒክስ ይዞ መግባት ክልክል ነው። በቤቶቹ በሴት አቅራቢነት የሚታወቀው ወጣት ግን ከዚህ ገደብ ነጻ ነው፡፡ ፍተሻው እንደመጀመሪያው ምስጢራዊ ምሽት ቤት ምስቅልቅል የሚያደርግ ፍተሻ ባይከናወንም፣ ግን የተባሉትን ዕቃዎች ለዘናጯ እንግዳ ተቀባይ በማስረከብ የመለያ ቁጥር ወስደው እንዲገቡ ይደረጋሉ።
አብሮኝ ስለ ቤቱ ታሪክ ምንነት እና ስለ ሥራው ሲያጫውተኝ የነበረው ወጣት ታዲያ ወደ ቀጣዩ ክፍል እንድንሔድ ባቀረበው ሐሳብ ተስማምተን ወደ ቀጣዩ ክፍል ገባን። እያንዳንዱን እንቅስቃሴ በተገቢው መንገድ ሳይዛነፍ ለመከተብ እና ትንሽ ስህተት ከፍተኛ ዋጋ እንደሚያስከፍል በማመኔ እርምጃዎቼ ሁሉ የተመጠኑ፣ ንግግሬም የተወሰነ ነበር።
ኹለተኛው ፎቅ ላይ የሚገኘው ክፍል ሲገባ ከመጀመሪያው ክፍል እጅግ የቀዘቀዘ እና ተስተናጋጆች በለሆሳስ የሚያወሩበት፣ አንዳንዶች ጠረጴዛ ላይም ዱቄት መሳይ ሐሽሽ ለማስተዋል ችያለሁ። በዚህ ስፍራ ግን ሴት ልጅ ባልወለድኩ የሚያስብሉ ዘግናኝ እና ጸያፍ ተግባራት በዚህ ጽሑፍ ሊካተቱ የማይገባቸው ድርጊቶችን ለመታዘብ ችያለሁ።
አሁንም አስጊብኚዬ ጨዋታውን እንደቀጠለ ነው። በእርግጥ አይጠገብም፤ እኔም ለሆዴ እርሱም ለሆዱ ነው እና የተገናኘነው፣ እኔም የመረጃ ከርሴን ልሞላ እርሱም ከእኔ የሚሰጠውን ጉርሻ ለማሳደግ የባጥ የቆጡን በኩራት ሲተርክ ማድመጥ የኹለት ወገን የአሸናፊዎች ግንኙነት ነው።
አሁን ያለሁበት ስፍራ በሴቶች እና ከሴቶች ቁጥር ባነሱ ወንዶች የተያዘ ነው። አንድ ወንድ ከኹለት እና ሦስት ሴቶች ጋር ሲዳራ መታዘብ እዚህ ስፍራ ያልተጻፈ መብት ነው። ዋናው ገንዘብን ይጭነቀው እንጂ። እዚህ ጋር ግን አንድ አስደንጋጭ ሁኔታ ተከሰተ። ከፍተኛ ኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በምማርበት ወቅት ልጆቻቸውን ከእኛው ጋር ያስተምሩ የነበሩ የከተማዋ ከበርቴ የልጆቻቸው እኩያ ከምትሆን ሴት ጋር ሲቀብጡ ተመልክቻለሁ፡፡
በዚህ ስፍራ ሴቶችን ለጨረታ የሚያቀርቡበት አጋጣሚ እንዳለ ለማወቅ አስጎብኝዬን በሌላ ጥያቄ አስታክኬ መጠየቅ ነበረብኝ። ‹‹የሚገርምህ ነገር አዲስ አበባ ውስጥ ይህን የሚያክል ምሽት ቤት የለም። ኹለቱም ጾታዎች የፍላጎታቸውን የሚያገኙበት ስፍራ ነው። በዚህ ቤት ተመሳሳይ ጾታዎችም የሚጣበሱበት እና ከፍ ሲልም አልጋ ይዘው የሚዳሩበት አገልግሎትን ይሰጣል›› ሲል መለሰልኝ። የሰማሁትን ማመን አልቻልኩም። በእርግጥ ኢትዮጵያ ውስጥ ይህ ይካሔዳል?
ተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት የአማኞች አገር የቃልኪዳን ምድር በምትባል አገር ያውም በመናገሻዋ ይካሔዳል? አስገራሚው ነገር ደግሞ ኢትዮጵያን ከተለያዩ ጥቃቶች በተለይም ደግሞ ከሳይበር ጥቃቶች እከላከላለሁ በሚለው የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ ዋና መሥሪያ ቤት በ200 ሜትር ርቀት ላይ መሆኑ ደግሞ ይበልጥ ግርምትን እና ድንጋጤን የሚያጭር ነው።
ይህን ሁሉ እያሰብኩ ርቄ ሔጂ ኖሮ ‹‹ምነው ደበረህ እንዴ እንውጣ?›› በሚለው የአስጎብኚዬ ጥያቄ ነበር ወደ ቀልቤ የተመለስኩት። እንደ ደከመኝ ሌላ ቤት ሙዚቃው ከፍ ያለ እና ተመሳሳይ የሆነ ቤት ይወስደኝ እንደሆነ ጠየኩት። አላቅማማም፤ ጉዞ ወደ ሦስተኛው ምስጢራዊ ምሽት ቤት (ኳራንታይን ቤት)።
በጉዟችን ወቅት ስለሚያቀርባቸው ሴቶች ከምን ያህል እድሜ ክልል ጀምሮ እንደሚመጡ፣ ምን ያህል ብርስ እንደሚከፈለው ስጠይቀው ሲመልስ ‹‹ትምህርት ቤት በመዘጋቱ ሴቶችን ለማግኘት እጅግ ቀሎኛል። ከዚህ ቀደም ከትምህርት ቤት ለማስፎረፍ እና ለማስወጣት ከባድ ነበር። አሁን ግን ቤታቸው ስለሚውሉ የመውጫ ሰበብ ሳያስፈልጋቸው ነው ማግኘት የምችለው። ከ17 እና 16 ዓመታቸው ጀምሮ ወደዚህ ቢዝነስ ለመግባት የሚፈልጉ ይኖራሉ። ግን ከተያዝን ቅጣቱ ከፍተኛ ስለሚሆን በጥንቃቄ ነው የምናሠራቸው። ነገር ግን 29 እና 30 ዓመታቸው ላይ የደረሱ ልጆችን ተፈላጊነታቸው ስለሚቀንስ ከዚህ ቢዝነስ ሳንወድ እንቀንሳቸዋለን›› ሲል ይናገራል።
እኔንም በተራዬ ሲጠይቀኝ ስመልስ በኮቪድ 19 ምክንያት ቤት መቀመጥ የሰለቸኝ እና ለከተማዋ አዲስ እንደሆንኩኝ ነገርኩት፣ ሳያቅማማ ተቀብሎኛል ወይም የተቀበለ መስሏል።
ምስጢራዊው ምሽት ቤት 3 (ኳራንታይን ቤት)
ቦሌ ከሳይ ኬክ ቤት ወደ ሸገር ሕንጻ በኩል የሚወስደው ጸጥታ የሞላበት እና አልፎ አልፎም የከፍተኛ ባለሥልጣናትን መኖሪያዎች የሚጠብቁ የፌዴራል ፖሊስ አባላት የሚታዩበት የዝምታ መኖሪያ መንደር ነው። በዚህ አካባቢ አይደለም ዘፈን ቀርቶ ጮክ ብሎ መወያየት ራሱ ጸጥታውን ስለሚያደፈርስ ለሆሳስ የመግባቢያው መንገድ ነው። አካባቢውን እንደ እጄ መዳፍ የማውቀው ቢሆንም ስፍራውን ግን በአስጎብኚው እርዳታ ራሱ ማግኘት ተቸግሬ ነበር።
ኳራንታይን ቤት የተባለበትን ምክንያት አስጎብኛችን ሲናገር ኮሮና ኢትዮጵያ ከተከሰተ ጀምሮ መጠጥ ቤቶች አና የከተማዋ ቅንጡ ክበቦች በመዘጋታቸው የለመዱት የቀረባቸው ሰዎችን በማሰባሰብ ደብቅ እና ምስጢራዊ ምሽት ቤት በመከፈቱ እንዲሁም ለቀናት እና ለሳምንታት እንደ መጀመሪያው ምስጢራዊ ቤት ሁሉ እዚህም መቆየት እና መሰንበት የሚቻልበት አሰራር መኖሩን ጠቆመኝ።
ሴቶችም እንደ መጀመሪያው ቤት ውስጥ እዚህም ከሳምንት እስከ ሳምንት በተለይም ደግሞ ረቡዕ እና አርብ ለጨረታ የሚቀርቡበት ጊዜ እንደሆነ ለአዲስ ማለዳ ይናገራል። አሁንም ወደ ሦስተኛው ምስጢራዊ ቤት ለመግባት ተመሳሳይ ቅደም ተከተሎች እና ተቀራራቢ የመግቢያ ክፍያዎች የሚከፈሉ ሲሆን ቤቶቹ በቅርጻቸው የተለያዩ መሆናቸው እንጂ ምንም ልዩነት የላቸውም።
በዚህኛው ቤት 1 ሺሕ ብር የመግቢያ መክፈል ግዴታ ነው። ይሁን እንጂ ወደ ውስጠኛው ክፍል ከመግባታችን በፊት በጊቢው ውስጥ ባለው ነፋሻማ እና ብርሃናማ ስፍራ እሳት እየነደደ እሳት ከቦ መጠጣት የሚቻል ሲሆን፣ የአስተናጋጆቹ እና ሴቶቹ አለባበስ ግን እጅግ የተራቆተ ነበር። የዚህኛው ምስጢራዊ ቤት ባለቤት ከውጭ አገር ኖሮ የተመለሰ እና በኢትዮጵያ በሀብታቸው ከሚጠቀሱ ግንባር ቀደም ሰዎች ውስጥ አንደኛ የሆኑ ግለሰብ ልጅ እንደሆነ ለመረዳት ችያለሁ።
በዚህኛው ምስጢራዊ ቤት ከሌሎች ተመሳሳይ ቤቶች በተለየ ሁኔታ ውስጥ የሚሰማው ከፍተኛ ድምጽ ያለው ሙዚቃ ወደ ውጭ እንዳይወጣ የተደረገበት መንገድ እጅግ አስገራሚ ነው። ሌላው ደግሞ ከሌሎች ቤት በተለየ በዚህ ቤት ውስጥ ሴቶችን ለመጫረት ሌላ ክፍል ውስጥ መሔድ አይገባም። ወደ ውስጠኛው የቤቱ ክፍል በዘለቅን ወቅት ቤቱ በከፍተኛ ማሪዋና ጭስ ሽታ እና ከሴቶች እና ከወንዶች በሚወጣ የሽቶ ጠረን ታፍኖ ነበር።
የተለመዱት ዘናጭ ሴት እንግዳ ተቀባዮች በዚህ ስፍራ የሉም። ነገር ግን የሚሰጣቸውን ትዕዛዝ በለሰለሰ አንደበት እና በታላቅ ትህትና የሚቀበሉ እንደ እንዝርት የሚሾሩ ማራኪ ወጣት ሴቶች በስፍራው መገኘታቸው ግን ክፍተቱን የሚሞላ ነው። ካለፉት ቤቶች ይልቅ በዚህ ቤት የተስተናጋጅ ቁጥር ከፍ ያለ ሲሆን ምንም የዕድሜ ገደብ አለመኖሩ ደግሞ ግርምትን የሚያጭር ነው።
‹‹አባትህ ደህና ነው››? የሚል በእድሜ የጠኑ ሰዎች ለወጣቶች ከሚያቀርቡት ሰላምታ ጀምሮ አጭር የወጣት ሰላምታ ድረስ እየታዘብን፣ ኹሉም የዕድሜ ክልል ግን በአስራዎቹ መጨረሻ እስከ ሃያዎቹ አጋማሽ ድረስ ያሉ ሴቶችን ለመጫረት እጃቸውን እያወጡ በፍትወት ሲነድዱ መመልከት የተለመደ ነበር።
አሁን ምሽቱ ገፍቷል፤ ዕኩለ ሌሊት ካለፈ ቆይቷል። የመጠጡም ሆነ የስካሩ መጠን እየጨመረ ሲመጣ ጨረታውም መጋል ጀመረ። በ2500 የጀመረው የመጀመሪያዋ ሴት ዋጋ በ13 ሺሕ ብር ተጠናቆ በአንድ ለሰማይ ለምድር ለከበዱ ባለሀብት ተሸጠች። ጭብጨባው እና ፉጨቱ ደራ። እንኳን ደስ አለህ ድምጾች ተሰሙ። ለኹለት ቀናት በዚሁ ስፍራ ከእኛ ወፍራም ቱባ ባለሀብት ጋር በዛው ስፍራ ትቆያለች ማለት ነው።
ነገሩን ኹሉ ተመልክቼ እና ለዚህ ጽሑፍ የማይመጥኑ ጸያፍ ተግባራትንም ከማየት በማይጎድለው ዐይን ቃኝቼ ለጋዜጣ በሚመች መልኩ ለማስተላለፍ ለእራሴ ቃል ገብቼ፣ ከስፍራው በመውጣት አስጎብኚዮን ተሰናብቼ በመውጣት ወደ መኖሪያዬ በውድቅት ተመልሻለሁ።
እዚህ ጋር አንድ መታወቅ ያለበት ጉዳይ እና እጅግ አስፈሪው ነገር በሔድኩባቸው ስፍራዎች ኹሉ ኮሮናን በሚመለከት ምንም አይነት ጥንቃቄ አለመደረጉን ነው። ከዛም በላይ በሰዎች ዘንድ ሲታይ የነበረው መጎነታተል፣ መላፋት፣ መዳራት ሁሉ ከልክ ያለፈ መሆኑ ላይ በዛ ተግባር ውስጥ የሚገኙት ሰዎች ኮሮና በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ለመከሰቱም መረጃው ያላቸው አይመስሉም። በእነዚህ ስፍራዎች ከኮሮና ይልቅ ጋዜጠኛ፣ ከኤችአይቪ ይልቅ ለሥራው ታማኝ የሆነ ፖሊስ እንደሚፈራ ነው መመልከት የቻልኩት።
ቅጽ 2 ቁጥር 84 ሠኔ 6 2012



