የኮሮና ቫይረስ ወረርሺን ወደ ኢትዮጵያ በመግባቱ ሳቢያ ከውጪ የሚመጡ ዜጎች ለ 14 ቀን በለይቶ ማቆያ እንዲቆዪ መወሰኑን ተከትሎ በጊዮን ሆቴል በለይቶ ማቆያ ያሉ እንግዶችን ሠራተኞች ያለ በቂ የራስ መጠበቂያ ግብዓት እንዲያስተናግዱ መደረጋቸውን አስታወቁ።
የተሟላ እራስን የመጠበቂያ መሳሪያዎች ሳይሟሉልን ሥራችንን ግን እንድንሠራ እየተገደድን ነው ሲሉ ማንነታቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የጊዮን ሆቴል ሠራተኞች ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
‹‹ሆቴሉ ለሠራተኞቹ በተለይም (ለአስተናጋጆች እና ለፅዳት ሠራተኞች) የተሟላ መሳርያ የለውም ማለትም የፊት መሸፈኛ ጭምብል እና የእጅ ጓንት አያሟላልንም ይህንን ሳያሟላ ነገር ግን እንግዶችን 14 ቀን ሞልቷቸው ነፃ ሆነው ነው የሚወጡት። ስለዚህ ኬሚካል ቢረጭም ባይረጭም ክፍሉ ውስጥ ገብታችሁ ሥሩ እንባላለን›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ጨምረው ተናግረዋል።
ከአስተዳደር አካላት የሚተላለፈውን ውሳኔ ሠራተኞች በቀጥታ እየተገበሩት እንደሚገኝ እና ይህም ሠራተኞች የሥራ ደኅንነት ስለማይሰማቸው መሆኑንም አዲስ ማለዳ ከድርጅቱ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል። የተወሰኑ ሰራተኞች ደኅንነቱ ባልተጠበቀ ሁኔታ መስራት እንደማይችሉ የሚያሳውቁበት እና ትዕዛዙን ላለመቀበል የሚሞክሩበት አጋጣሚ መኖሩ የታወቀ ሲሆን ገሚሶቹ ደግሞ በግድ እንዲሰሩ እንደሚደረጉ ሰራተኞች ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።
ሰራተኞቹ እንደሚሉት በጊዮን ሆቴል ውስጥ ኳራንታይን ከተደረጉ ሰዎች መካከል በመጀመርያ ዙር ላይ ናሙና ተወስዶላቸው ወደ ቤታቸው ሄደው ከወጡ በኋላ እንደገና ፖዘቲቭ ሆኖ ውጤታቸው (የኮሮና ቫይረስ ተገኝቶባቸው) ወደ ማቆያ እንዲሄዱ የተደረጉ ሰዎች መኖራቸውን አስታውቀዋል።
‹‹ ሆቴሉ ለሰራተኛ ዝንጉ ነው የግድ መደረግ እያለበት የፊት መሸፈኛም የእጅ ጓንትም በጭቅጭቅ ነው የሚሰጠን ከዛም በተጨማሪ በተደጋጋሚ በጤና ሚኒስቴር እንደሚገለፀው ሰራተኛውን የሚያሰጋው ነገር በሽታው የመደበቅ አጋጣሚ ስላለው እነሱ ለ 14 ቀን ተቀምጠው ምንም ምልክቱን አላሳዩም ነጻ ናቸው ገብታቹ ስሩ የሚባለው ነገር ያስፈራናል›› ያሉ ሲሆን ወደ ሆቴሉ በእርዳታ መልክ በርካታ የፊት መሸፈኛዎች ሲገቡ እንደሚታይ እና ነገር ግን መዳረሻ የት እንደሆነ እንደማያውቁም ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
በተደጋጋሚ ለአስተዳደር ሰራተኞች ተደጋጋሚ ጥያቄ የሚቀርብላቸው ቢሆንም ነገር ግን ጉዳዩ አስቸኳይ ሆኖ ሳለ እንመለከተዋለን ከማለት ውጪ ምንም መፍትሄ እየሰጡበት እንዳልሆነም አዲስ ማለዳ ከቅሬታ አቅራቢዎች ያገኘችው መረጃ ያመላክታል ።
አሁን ኮሮና ቫይረስ መጣ እንጂ የሚሉት የሆቴሉ ሰራተኞች ከዚህ ቀደምም የመልካም አስተዳደር ብሎም የወገንተኝነት ችግር በስፋት ይታይበት ነበር ብለዋል። ድርጅቱ የልማት ድርጅት እንደመሆኑ ብዙ ትርፍ አለው በዛው ልክ ግን ያሉትን ሰራተኞችም ተጠቃሚ የማድረግ ልምድ የለውም ሲሉም ሰራተኞች ይናገራሉ ።
ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የጊዮን ሆቴል የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ የሆኑት ቀለም ኤልያስ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት ከሆነ ድርጅቱ በተገቢው መንገድ ለሰራተኞቹ እንክብካቤ እያደረገ መሆኑን እና ሆቴሉ ከሰራተኞች ጋር በመናበብ የሚሰራ ነው ሲሉ ተናገረዋል።
የጊዎን ሆቴል ሙሉ በሙሉ የለይቶ ማቆያ አገልግሎት እየሰጠ ነው የሚገኘው የሚሉት ቀለም፤ ከዛም በተጨማሪ ሆቴሉ ለሰራተኞቹ ተገቢውን እንክብካቤ እያደረገ መሆኑን እና ነገር ግን እንደ አገር መጀመርያ አካባቢ የፊት መሸፈኛ እና የጓንት እጥረት እንደነበር አውስተዋል ።
በለይቶ ማቆያ እንዲቆዩ የሚደረጉትን ሰዎች ክፍላቸው ውስጥ ከገቡ በኋላ ከዛ ውጪ በስልክ ነው ግንኙነት የሚያደርጉት ካዛም በተጨማሪ እነርሱ የሚጠቀሙበትን ማንኛውም እቃዎች ይቃጠላሉ ብለዋል።
ተያይዞም ማንኛውም ተገልጋይ የቆይታ ጊዜውን ጨርሶ ከወጣ በኋላ ክፍሎቹ ኬሚካል ይረጫሉ ተብሏል። ሁሉም አይነት ጥንቃቄዎች በተገቢው መንገድ ለኹለቱም ወገኖች ማለትም ለሰራተኞች እና ለተስተናጋጆች እንደሚደረግ ቀለም ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ቅጽ 2 ቁጥር 84 ሠኔ 6 2012



