ግልጽ ደብዳቤ ይድረሰ ለኦሮሞ የፖለቲካ ልሂቃን፣ ምሁራን፣ አባገዳዎች እንዲሁም ቄሮዎች

0
1098

በቅድሚያ የአክብሮት ሠላምታ አቀርባለሁ። ይህቺን የግሌ የሆነች አጭር መልዕክት ከቁም ነገር አስገብታችሁ በጥሞና እንደምትመለከቷት ስለማምንም ቀድሜ ምስጋናዬን አቀርባለሁ።

አባቶቼና ወንድሞቼ፣ እህቶቼ እንዲሁም ልጆቼ ለምትሆኑ ሁሉ በቅድሚያ ለመልዕክቴ መነሻ የሆነኝን ምክንያት እንድገልጽ ፍቀዱልኝ።
ዛሬ እየተከናወነ ስላለው አገራዊ ጉዳይ የተለያየ አመለካከት ቢኖርም ከሞላ ጎደል በለውጥ ሂደት ውስጥ መሆናችን የሚያስማማን ይመስለኛል። ቢያንስ በኢትዮጵያ እንዲኖር በሚፈለገው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግምባታ ላይ አደናቃፊ የነበሩ እንቅፋቶች (road blocks) ተነስተዋል። ከነዚህም አንዱ እንቅፋት የነበረው ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትን ማፈንና የሚዲያ በነፃነት መሥራት አለመቻል ነበር ማለት ይቻላል።

ዛሬ ላይ ግን በሚፈለገው ደረጃ አስተማማኝ መሠረት ላይ ቆሟል ባይባልም መልካም ጅማሮ ላይ መሆኑ የሚስተዋል ይመስለኛል። ሚዲያው የሐሳብ ልዕልናን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ውስጥ አጀንዳዎችን በመቅረጽ ረገድ ጠቋሚና ፊት ፊት እየቀደመ መሪ የመሆን ብቃቱ ገና ያልዳበረ ቢሆንም፣ የተባለውን የማስተጋባት ሚናው ግን (Reactive Role) የተሳካለት ይመስላል።

ከለውጡ ጅማሮ በኋላ በወጣ ገባም ቢሆን በትኩረት ከምከታተላቸው የሚዲያ አውታሮች መካከል አንዱ ኦ.ኤም.ኤን (OMN/Oromo Media Network) የቴሌቪዥን ጣቢያ ነው። ከሱም ቢሆን ሁሉንም ፕሮግራሞቹን ሳይሆን የተለያየ አመለካከት እንዲንፀባረቅባቸው ታስቦ የሚተላለፉትን የውይይትና ቃለመጠይቅ ፕሮግራሞች ነው። በተለይ የኦሮሞ ልሂቃን ተጋብዘው የሚሳተፉባቸውን በአንክሮ እከታተላለሁ።

ከውጭም ከውስጥም ለኦሮሞ ሕዝብ እጅግ ተቆርቋሪ የሆኑ ልሂቃን እየተጋበዙ ሲሳተፉ አስተውያለሁ። ጣቢያው በአቶ ጀዋር መሐመድ የተያዘ ወይም የሚመራ መሆኑን ሲወራ ሰምቻለሁ። ለኔ ይሄ ችግር አይደለም። ጃዋር በኤል ቲቪና በሌሎችም የሚዲያ አውታሮች ቃለመጠይቅ እየተደረገለት የራሱን አመለካከት ሲገልጽ ሰምቻለሁ። ይህም ሊያስመሰግነው እንጂ ሊያስወቅሰው ይገባል ብዬ አላምንም። የኔ ነው ብሎ የያዘውን እውነትና እምነት መግለጽ መብቱ ነውና።

ዛሬ ኢትዮጵያን አስጨንቀው በያዝዋት ጥያቄዎች ላይም የራሴ አቋም አለኝ። በተለይ ደግሞ በብሔር ጥያቄ ላይ ዛሬ ሳይሆን ከወጣት የዩኒቨርሲቲ ተማሪነቴ ጊዜ አንስቶ ግልጽ አቋምና የጥያቄውም አረዳድ አለኝ። እኔ የብሔር ጥያቄን ተገን አድርጎ በፖለቲካው ዐውድ ላይ ተገሽሮ የቆመውን ብሔርተኝነት በተለይም ነገዳዊ ብሔርተኝነት (Ethno nationalism) በኢትዮጵያ ሊገነባ ለሚታሰበው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ዋነኛ ተግዳሮቱ (Main Challenge) ሆኖ እንደቆመ ነው የምረዳው። ብሔርተኝነት እንደጃኑስ ጣኦት ወደኋላ ሳያይ ወደፊት የማያይና ኅብረተሰቡንም “እኛና!” “እነሱ!” በሚል ካምፕ ስለሚከፋፍል ነው።

ብሔርተኝነትም ሆነ ዴሞክራሲ ትኩረታቸው የሉዓላዊነትና እኩልነት ጥያቄዎች ናቸው። ብሔርተኝነት ሉዓላዊነቱም ሆነ እኩልነት በብሔሩ ተመን መሆን አለበት ወይም ለብሔር ብሔረሰቦች መረጋገጥ አለበት ሲል ዴሞክራሲ ደግሞ የሁሉም ብሔር/ብሔረሰቦች አባል ለሆኑት ዜጎች ይገባል ይላል። ይሄ ፉክክር የፈጠረውን ርዕዮታዊ መስመረ ተከትሎ በርካታ የፖለቲካ ድርጅቶችም ተፈጥረዋል።

ይህም በመሆኑ በኢትዮጵያ የሚገነባው ዴሞክራሲ የብሔር/ብሔረሰቦችን የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት ረግጦ ማለፍ እንዳይችል ስላደረገው ብሔርተኝነት ተግዳሮቱ ነው ብዬ አምናለሁ። የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታችንም ልዩ ፈተና ይኸው ነው። ይህንኑ እሳቤዬንና አመለካከቴን ‹ምሁሩ!› በሚል ሥያሜ በለውጡ ዋዜማ ላይ ባሳተምኩት መጽሐፌ ምዕራፍ ስድስት ላይ ‹‹የኢትዮጵያ ምሁራን በዴሞክራሲና ብሔርተኝነት መንታ መንገዶች ላይ›› በሚል ርዕሰ በዝርዝር ገልጫለሁ።
ወንድሜ አቶ ጃዋር መሐመድ ወይም ሌሎች የኦሮሞ ፖለቲካ ልሂቃን በዴሞክራሲና በብሔር ጥያቄ በተለይም በነገዳዊ ብሔርተኝነት ላይ ያላቸውን አቋም በዝርዝር አላውቅም። ነገር ግን የኦሮሞን ሕዝብ በተመለከተ የያዟቸው አመለካከቶች ከማሳሰብ አልፈው ያስጨንቁኛል።

አንተ ማነህና ነው የኦሮሞ ልሂቃን አመለካከቶች የሚያስጨንቁህ ትሉኝ ይሆናል። ‹የኦሮሞ ጥያቄ በኦሮሞ ብቻ ይፈታል› የሚል ቅዠት ሊኖር ስለሚችል ማለት ነው። ለዚህም ምላሽ አለኝ።

ሲጀመር ስለአንድ ማኅበረሰብ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት መከበር ለመደገፍም ሆነ በአጋርነት ለመቆም የግድ የዚያ ማኅበረሰበረ አባል መሆን አያስፈልግም። በዚህ ዘመን ጥያቄውን በአግባቡ የተረዳ ሰው መሆን ወይም ግፋ ቢል ዴሞክራት መሆን ይበቃል። የጭቆናን አስከፊነት ለመረዳት በማንም ላይ ይድረስ በማን፣ ሰው መሆን በቂ ነው።

ሲቀጥል እኔ በኢትዮጵያ የብሔር/ብሔረሰቦችን መብት የረገጠ ሳይሆን ያስከበረ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲገነባ እፈልጋለሁ። ከተማሪነቴ ዘመናት ጀምሮም አቋም ይዤ ታግዬለታለሁ ማለት እችላለሁ። ይህን ለማድረግ ደግሞ ዘር ወይም ብሔር መምረጥ አስፈልጎኝ አያውቅም።

ሲሠልስ የኦሮሞን ሕዝብ በሥማ በለው፣ በተራ ተረክ ወይም ባነበብኩት ታሪከ አይደለም የማውቀው። ተወልጄ ያደኩበት ማኅበረሰብ ነው። የኦሮሞን ሕዝብ ከመሬት አዋጅ በፊት በተፈፀመበት ግፍና በደልም አውቀዋለሁ። መሬቱን ተነጥቆ ጢሰኛ ከዚያም ከጢሰኝነት ወርዶ የባለሀብት እርሻ አራሚነት ተሸጋግሮ የቀመሰውን አበሳ፣ ሀብትና ንብረቱን ተዘርፎ በፍጹም ድህነት የኖረበትን ታሪክ በዐይኔ እያየሁ ነው ያደኩት። ይኸው ግፍና በደል እንዲወገድ ደግሞ ከሌሎች ጭቁን የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ጋር በመሆን የኦሮሞ ሕዝብ ያደረገውን ተጋድሎና የከፈለውን መስዋዕትነትም አውቃለሁ።

በሌላ ገጽ ደግሞ የዛሬይቱን ኢትዮጵያ በመገንባት ታሪክ ውስጥ የኦሮሞ ልጆች የከፈሉትን መስዋዕትነትም አውቃለሁ። ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወገኖቻቸው ጋር ሆነው የኦሮሞ ልጆች አድዋን ሠርተዋታል። በማይጨው ጦርነት ጀግኖቹ የኦሮሞ ልጆች ግምባር ቀደም ነበሩ። ኢትዮጵያ እንደ አገር ጸንታ የቆመችበትን መሠረት ካኖሩት ጀግኖች አያቶቻችን መሃል የኦሮሞ ልጆች በመጀመሪያው ረድፍ ላይ የተሰለፉ እንደነበሩ ታሪክ ይመሰክራል።

የኦሮሞ ሕዝብ ልክ እንደሌሎቹ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች በዘመናት ትግሉና ልፋቱ በፈጠራት አገር ተበዳይ ሆኖ መኖሩን እረዳለሁ። ኦሮሞ መብቶቹ በምልዐት ተከብረው በሠላም መኖር ካልቻለ ኢትዮጵያም ሠላም አትሆንምና ያስጨንቀኛል። ኦሮሚያ ውስጥ ተወልጄ ዘር ቀለም ሳይለይ ሰው አክባሪና አቃፊ የሆነውን የኦሮሞ ሕዝብ በማወቄ ልዩ ክብር ይሰማኛል። ለዚህም ነው የኦሮሞ ልሂቃን የተበታተነና የጠብ መስመር አመልካች የሆነ አመለካከት የሚያስጨንቀኝ። ንትርካቸው ሁሉ፣ ለኦሮሞ ሕዝብ ብለው የሚያደርጉት ከሆነ አካሄዳቸውን ቆም ብለው ይፈትሹ። አሁን ይህን ሁሉ ወዳስባለኝ ቁም ነገር ልለፍ።

ከላይ እንደነገርኳችሁ OMN (ኦ. ኤም. ኤን) በወጣ ገባ እከታተላለሁ። በዕለተ ቅዳሜ ግንቦት 29 ቀን 2012 (June 6, 2020) ምሽት ላይ (ሰዓቱ ወደ እኩለ ሌሊት ይጠጋል) አቶ ጃዋር ቃለመጠይቅ እየተደረገለት ነበር። ቃለመጠይቅ አድራጊው ወንድ ጋዜጠኛ ነው። ጃዋር እንደተለመደው በምሬትና በኃይለ ቃላት በታጀበ ንግግሩ አየሩን ውጥረት በውጥረት አድረጎታል። በቃለመጠይቁ የሚነሱት ጥያቄዎች ጃዋር ምላሹን በሰፊው ለጥጦ በርካታ ነገሮች እየደበላለቀ እንዲናገር ዕድል የሚሰጡ ይመስላሉ።

ጃዋር የንግግሩ ፍጥነት ከሚናገረው ነገር ጋር ሲነፃፀር አእምሮው ምን ያህል መረጃ እንደተሸከመ ብቻ ሳይሆን የንግግር ፍሰቱ ሳይጣረስ ባልተሰባበሩ ዐረፍተ ነገሮች የሚሰነዝራቸው ሐሳቦች ‹መጥኔ ለአንጎሉ!› ያሰኛል። ጃዋር በኦሮሚፋ ነው የሚናገረው። በቋንቋው የሱን ያህል ችሎታ አለኝ ብል ነውር ይሆናል። ለመናገር ምላሴ እንደሱ በፍጥነት ባይርገበገብም በመስማትና በመረዳት ግን ችግር የለብኝም። ንግግሩንም ቃል በቃል ሳይሆን በተረዳሁት መጠንና ጥቂቱን ክፍል ብቻ ነው ልተረጉመው የሞከርኩት። እንዲህ ይላል ጃዋር፣

ከምኒልክ አንስቶ እስከ ዛሬ ያሉት የኢትዮጵያ መንግሥታት ለብሔራዊ መንግሥት ግንባታ ዓላማቸው ዋነኛ ግብ ያደረጉት የኦሮሞን ሕዝብ ማሳነስ፣ መግፋት፣ ማንነቱን እንዲንቅና ለነሱ ዓላማ ተገዢ እንዲሆን ማድረግ ነበር። ዛሬም ነው!

ኦሮሞን ይገድላሉ፣ ከመሬቱ ይነቅሉታል፣ ያፈናቅሉታል፣ ዘመቻቸው ሁሉ ማንነቱን ማጥፋት ነው፣ በተለይ ዛሬ ጃዋር እንደሚለው ከኬሚሴ እስከ ጉጂ፣ ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ፣ በፌዴራልም ይሁን በክልል ደረጃ ያለው መንግሥት ኦሮሞ ላይ ጦርነት ከፍተዋል። የገደሉትን ሰው ሬሳ እንኳ እንዳይነሳ እስከመከልከል ደርሰዋል። ዛሬም እንደትናንቱ የእስር ቤቶች ቋንቋ ኦሮሚፋ ነው። ምክንያቱም እስር ላይ ካለው ሰው ዘጠና በመቶ የሚሆነው ኦሮሞ ስለሆነ ነው።

በኦሮሞ ወጣቶች (ቄሮዎች) ትግል ሥልጣን ላይ የወጡ የኦሮሞ ልጆች ሥልጣኑን ካገኙ በኋላ ኦሮሞን ክደውታል። ከኦሮሞ መብት ይልቅ ለነፍጠኛ ሥርዓት መመለስ ነው የሚሠሩት ወዘተ እያለ ጀዋር ምሬቱን ይዘረግፋል።

እነዚህ የኦሮሞን ማንነት ለማጥፋት እየሠሩ ያሉ ባለ ሥልጣናት ከቀበሌ አንስቶ እስከ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት ድረስ ያሉት ይጠየቁበታል። የጊዜ ጉዳይ ነው። ለዚህ የሚረዳ ማስረጃ ደግሞ በውጭም ሆነ በአገር ውስጥ በመሰብሰብ በደንብ ተዘጋጅተንበታል። ወንጀላቸው የማይታወቅና ከተጠያቂነት የሚያመልጡ ከመሰላቸው ተሞኝተዋል። በዚህ ረገድ ዝግጁ ነን።

ወገኖቼ እንግዲህ የጃዋርን ንግግር ከቲቪ እየሰማሁ በሕሊናዬ የቋጠርኩትን ነው ቆንጠር አድርጌ ያጋራኋችሁ። ንግግሩን አግኝታችሁ ብትሰሙት እኔ ካቀረብኩት በላይ እጅግ የከረረና አሳሳቢ እንደሚሆን ትገምቱ ይሆናል።

ጃዋር ከተናገራቸው ነገሮች ውስጥ ኹለቱ ልቤን ነክተውታል። አንዱ የኦሮሞን ሕዝብና የነባር አሜሪካውያንን (Native Americans) የጭቆና ደረጃ ማመሳሰሉ ሲሆን፣ ኦሮሞ በአገሩ እንደ አሜሪካ ሕንዶች ያውም ዛሬ ላይ ሆኗል ማለቱ ይገርማል። ሌላው በዚህ በኮሮና ወረርሺኝ ወቅት እንኳ ታማሚ ሆነው ከሚቀርቡ ሰዎች መሃል ኦሮሞውን በሥሙ እየለዩ ቆይ አንተ/አንቺ በኹለተኛ ደረጃ ነው የምትታየው/ይው ይባላል ማለቱ ነው።

ይህን ትክክል ነው ብሎ ለመቀበል ይከብዳል። ኦሮሞ ዛሬ በኢትዮጵያ እንደ ኹለተኛ ዜጋ ይታያል ሲባል መስማቴ በእጅጉ አስደንቆኛል። የጃዋር አባባል ምንም የማያስደንቃቸው፣ ንግግሩም የተለመደ ነው የሚሉ ብዙ ናቸው። እኔም በተደጋጋሚ ሰምቼዋለሁ። ነገር ግን ንግግሮቹም እንደቀላል ነገር ወስጄ አላውቅም።
ለምን ቢባል ጃዋር የኢትዮጵያን ፖለቲካ ወደ ግራም ወደ ቀኝም ለመዘወር የራሱ የሆነ አቅም አለው፣ ብዬ ስለማምን ከውስጥም ይሁን ከውጭ ኢትዮጵያን ማተራመስ ስለሚመኙ ኃይሎች መሣሪያ ሊሆንም እንደሚችል ስለማስብ ነው። ጃዋርን መጥላትና እንደተራ በጥባጭ መቁጠር ቀላል ነው። የሱን አመለካከት ግን በዕውቀትና በስልት እንጂ በጥላቻ ማሸነፍ የሚቻል አይመስለኝም። ይህን እውነት ደግሞ በክልሉም ሆነ በፌዴራል ደረጃ ያሉ ኃላፊዎች ይረዱታል ብዬ አስባለሁ።

ጃዋር የሚናገረውን ዓይነት ንግግርም ከተለያዩ ልሂቃን በድምጸ ወያኔና በOMN ሲናገሩ ሰምቻለሁ። አቶ በቀለ ገርባ አንዱ ተጠቃሽ ሊሆን ይችላል። የዲያስፖራ አባላት የሆኑ የኦሮሞ ምሁራንም በልዩ ልዩ መድረኮች ላይ ተመሳሳይ ምሬታቸውን ሲገልጹ ተመልክቻለሁ። ሁሉም የኦሮሞ ማንነት መጨፍለቅ በጣም ያንገበግባቸዋል። የሚሉት ነገር ልክ ነው ወይም ልክ አይደለም የሚል ብያኔ ማሳለፍ የኔ ፍላጎትም ሆነ መነሻ ምክንያት አይደለም።

እኔን የሚያስጨንቀኝ የዚህ ዓይነት ባላንጣዊ አመለካከት በኦሮም ልሂቃን ዘንድ ለምን ኖረ? ብሎ ለመጠየቀም ሆነ ለመፍትሔ ፍለጋ በቂ ምክንያት ሆኖ መወሰድ መቻል አለመቻሉ ነው። የተባለው ሁሉስ እውነት ቢሆን? ብዬ ነው ማሰብ የምፈልገው። የተባሉት ነገሮች ልክም ይሁኑ አይሁኑ ወይም ማንም ይበላቸው ማን በግልጽ እወጃ፣ በትግል ቅስቀሳ መልክ የሚቀርቡ አመለካከቶች ስለሆኑ፣ በጥንቃቄና በያገባኛል ስሜት መያዝ አለባቸው። የዚህ ዓይነት አመለካከት ባለቤቶች ስሜት በጦዘው መጠን የኛም ከጦዘ የችግሩ እንጂ የመፍትሔው አካል አንሆንም።

እናም የተከበራችሁ የኦሮሞ ልሂቃን፣ አባገዳዎች፣ ምሁራን፣ ቄሮዎች ይሄ ንትርክ እስከመቼ ነው የሚቀጥለው? መቼ ነው ኦሮሞ እፎይታ የሚያገኘው? የፖለቲካ ልሂቃኑ ባልተስማሙበት መጠን ዘላለሙን ሲታመስ መኖር አለበት? ሕዝቡን ብዙም ትርፍ ወደሌለው የእርስ በእርስ ጦርነት አደፋፍሮ የሚያስገባው ስሜታዊ ሰው ሳይሆን፣ አሉ የሚባሉትን ችግሮች ሁሉ በባሕላዊ ሥርዓቱ አማካይነት እየተወያየ የሚፈታለትና ሠላሙን የሚያሰፍንለት ብልህ የልሂቃንና የምሁራን ስብስብ ነው የሚፈልገው። እስኪ ግራ ቀኝ ያላችሁት ተፋላሚዎች ገለልተኛ ነው በምትሉት ሦስተኛ አካል እየተረዳችሁ ተወያዩ የሚል ነው የኔ ጥሪ።

ጃዋርና ሌሎችም ባሉት ልክ ኦሮሞ ማንነቱን እንዲጠየፍ እየተዘመተበት ከሆነ፣ ከአገሪቱ ጫፍ እስከ ጫፍ ኦሮሞ እየተገደለ ከሆነ፣ ሀብቱ ንብርቱ እየተዘረፈ ከሆነ፣ በገዛ አገሩ ‹ሬድ ኢንዲያን› ተደርጎ ከሆነ፣ የእስረኛው ዘጠና በመቶ ኦሮሞ ከሆነ፣ ወይም ለኮሮና ቫይረስ እንኳ በኹለተኛ ደረጃ ትታያለህ እስከመባል ከደረሰ፣ ኦሮሞው ብቻ ሳይሆን ሌላውስ ሕዝብ ቢሆን ምንድነው እየተባለ ያለው? ብሎ መጠየቅ አይገባውም? ዛሬ ላይ የኦሮሞን ሕዝብ መብት የሚረግጥ የነፍጠኛ ሥርዓት የሚፈልግ ኢትዮጵያዊ ማነው?

እንደ ፈረንጆች አባባል ‹መልዕክቱን ከጠላህ መልዕክተኛውን ማጥፋት!› ወይም ደግሞ ‹መልዕክተኛውን ከጠላህ መልዕክቱን አትስማ› ዓይነት እንዳይመስል ሰጋሁ። ጃዋርንና መሰሎቹን እንደ መአት ጠሪ አድርገን አንያቸው። እናም በኦሮሞ ሕዝብ ላይ ዛሬ ይፈፀማል የሚባለው በደል ቢያንስ ከአብራኩ በወጡ ልሂቃንና ምሁራን መጣራትና መፍትሄ ማግኘት የለበትም ትላላችሁ? ሕዝቡስ ቢሆን የከሳሾቹን ጩኸት በሰማበት መጠን ምላሹን ከሚመለከታቸው መስማት የለበትም? ውሸትስ ከሆነ? ውሸትነቱ መረጋገጥ የለበትም? ስለሆነም የኦሮሞ ልሂቅና ምሁር ጊዜው ሳይረፍድ ሕዝቡ እውነቱን ተነጥቆ ከሆነ ፈልግ። ለሕዝብ ደግሞ ከማንነቱ በላይ እውነት የለውም።

ይሄ የኢትዮጵያ ንጣፍ የሆነ ሕዝብና ክልል የሚገባውን ክብር ያገኝ ዘንድ መተባበር፣ መደማመጥ፣ በአንድነት መቆም እንጂ ተበታትኖ በየጥጉ በመመሸግ በሆነው ባልሆነው መነታረክ አይደለም መፍትሔው። በክልልም ይሁን በፌዴራል ደረጃ ሥልጣን ላይ ያላችሁት ወደ ሥልጣኗ ሰገነት የደረሳችሁበትን ታሪክ አትርሱ። ከሥልጣኑ ምንም ስላልደረሳችሁ የተከፋችሁት ደግሞ የወጣውን ለመዘርጠጥ በምታደርጉት ጥረት ‹ሕፃኑን ከነታጠበበት ቆሻሻ ውሃ ጋር ልትደፉት› ነውና ተጠንቀቁ።
የኦሮሞ ሕዝብ በኢትዮጵያ ሥርዓታዊ ግንባታ ታሪክ ውስጥ ሊጫወት የሚችለውን አይተኬ ሚናና ማዕረግ አትርሱ። ኦሮሞ የኢትዮጵያም ተስፋ መሆኑን አትርሱ። ኦሮሞን ከአሜሪካ ‹ኢንዲያን› ሕዝቦች ጋር ማነፃፀር በፍጹም ተገቢ አይደለም። ንግግርን ለማሳመር ካልሆነ ለምንም አይፈይድም። በኮሮና ቫይረስ ሕክምናም ኦሮሞ ኹለተኛ ደረጃ ያዘ አይባለም። የማይመስል ነገር ነው። መልዕክቴ ይኸው ነው። አቀራረቤ ስህተት ከተገኘበት ብትተቹት ቅር አይለኝም። በኦሮሞ ጉዳይ ግን አያገባህም እንዳትሉኝ።

ለጃዋርም ሆነ ለማንኛውም የኦሮሞ ልሂቅ ያለኝ መልዕክት እርስ በእርስ ተፋልማችሁ የምታመጡት ለውጥ ኦሮሞን አይጠቅምም። ኢትዮጵያንም ይጎዳል። እርስ በእርስ ተከባበሩ፣ ተከራከሩ፣ ጠላትነትን ግን አስወግዱ። እናንተ በሆነው ባልሆነው ስትናከሱ ሕዝቡን ላደፈጠ አውሬ አሳልፋችሁ እንዳትሰጡት ተጠንቀቁ የሚል ነው። መልካሙን እመኝላችኋላሁ!

ቅጽ 2 ቁጥር 85 ሠኔ 13 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here