ሰኔ 15 ሲታወስ

0
1485

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ከተካሄዱ ለውጦች ተርታ ይመደባል፤ ከኹለት ዓመት በፊት የተከናወነውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን መምጣትን ተከትሎ የታየው ለውጥ። ከዚህም ኹነት ቀጥሎ ኢትዮጵያ የተለያዩ ክስተቶችን ስታስተናግድ የቆየች ሲሆን፣ ብዙዎቹም ‹ለውጥ የሚያመጣቸው ናቸው!› በሚል ሲታለፉ ነበር። ሰኔ 15 ቀን 2011 የሆነውን ክስተት ግን ከየትም መመደብ የሚከብድና የሚያሳዝን ሆኖ አልፏል።
ሰኔ 15 በአማራ ክልል ባህርዳር ከተማ የክልሉ አመራሮች እንዲሁም በአዲስ አበባ የመከላከያ አባላትና ጄነራሎች ሕይወታቸውን ተነጥቀዋል። ለእነዚህ ሰዎች ኅልፈት ምክንያትነት የተቀመጡ ምክንያቶችም የሚያዙ የሚጨበጡ አልነበሩም። ‹ገድለዋል፣ አስገድለዋል፣ ግድያውን አቀነባብረዋል› የሚባሉ ግለሰቦችም በሰዎች የፖለቲካ እይታ መሠረት ሲበየኑ ይሰማ ነበር። የጠራና ይህ ነው የሚባል መረጃ ግን አልተሰማም። ይህ ከሆነ ከነገ በስቲያ ሰኞ ሰኔ 15 ቀን 2012 ልክ አንድ ዓመቱ ነው። የአዲስ ማለዳው ኤርምያስ ሙሉጌታ መዛግብትና አገላብጦ በሰኔ 15 ክስተት የተገደሉትን ባለሥልጣናትና ጄኔራሎች ሕይወት መለስ ብሎ ያስቃኛል። ባለፈው አንድ ውስጥ ምን ተባለ? ምን ተከናወነ? የሚለውንም በሚመለከት በግድያ ተጠርጥረው ታስረዋል ከተባሉ ግለሰቦች ጀምሮ የሚመለከታቸውን በማነጋገር፣ ጉዳዩን የሐተታ ዘ ማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አድርጎታል።

ቀናት ነጉደው ሳምንታትን ተክተው፣ ሳምንታት ወራትን አዋቅረው አንድ ዓመት ሊሞላው ጥቂት ቀናትን ብቻ መሻገር ቀርቶታል፤ ሰኔ 15/2011። ይህ ቀን አገራዊ መራር ሀዘን የሆነበት እና የድንጋጤ ቀን ነበር። አንድ ዓመት እንደ አንድ ቀን፣ አንድ ቀን እንደ አንድ ዓመት ሆኖ ይኸው አንደኛ ዓመት የሙት ዓመት ለማውሳት ቀናት ቀርተዋል። አዲስ ማለዳም በእለቱና በሰሞኑ የነበረውን የሕዝቡን እንዲሁም አገራዊ ድንጋጤውን በሚመለከት ሰፊ ሽፋን ይዛ መውጣቷ የሚታወስ ነው።
ሰኔ ወር አሥራ አምስተኛው ቀን በ2011፤ ከፌዴራል እስከ ክልል ድረስ የተደራጀ በሚመስል መልኩ ታላላቅ የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች በተመሳሳይ ጊዜ እና ሰዓት በጭካኔ በተሞላበት መልኩ እንዲያልፉ ያደረገ ክስተት ነበር።

ከአንድ ዓመት በፊት ከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት መናገሻ ከሆነችው ባሕር ዳር እስከ ኢትዮጵያ መዲና አዲስ አበባ ሰሚን የሚያደነዝዝ ዜና በአገሩ ናኘ። ሰባት የአማራ ክልል ቁንጮ ባለሥልጣናት ስለ ክልሉ መፃኢ እና ነባራዊ ሁኔታ እየመከሩ ባሉበት ወቅት ባመኑትና እነሱን ብቻ ሳይሆን ክልሉንም በፀጥታውና ደኅንነቱ ረገድ ይደግፋል ባሉት የሥራ ባልደረባቸው የክልሉ የሰላምና ደኅንነት ቢሮ ኀላፊ ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ፅጌ ፊት አውራሪነት የተቀነባበሩ የተባሉ ጥቃቶች ተሰነዘሩባቸው።

የነገዋን ኢትዮጵያ ለመገንባት አንገታቸውን ደፍተው ሥራ ላይ የነበሩ የክልሉን ርዕሰ መስተዳደር አምባቸው መኮንንን (ዶ/ር) ጨምሮ ሦስት የሥራ ባልደረቦቻቸው አሻግረው የተመለከቷትን የተስፋዋን ምድር ኢትዮጵያን በርቀት እንደተመለከቱ፣ ሳይረግጧት እስከ ወዲያኛው አሸልበዋል።
ከባዱ ሐዘን በባሕር ዳር ብቻ የተገደበ አልነበረም። ከባሕር ዳር 525 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው የአፍሪካ መዲና አዲስ አበባ ላይም በተመሳሳይ ቀን አመሻሽ ላይ በቅርብ በሚያውቋቸው ‹ጭምት፣ ጀግና ተዋጊ እና አዋጊ፣ በሰንደቅ ዓላማ እና በአገር ጉዳይ የማይደራደር› የሚሉላቸው፣ በመከላከያ ሚኒስቴር ጦር ኀይሎች ኢታማዥር ሹም ጄነራል ሰዓረ መኮንን ከልጆቻቸው ለይተው በማያዩት የቅርብ የጥበቃ ጓድ መኖሪያ ቤታቸው ከባልንጀራቸው ጡረተኛ ሜጀር ጄነራል ገዛኢ አበራ ጋር እየተጨዋወቱ ባሉበት ወቅት ተገድለዋል።

በቅጽበት ሟች፣ ቀጠል ሲልም የቀድሞው ለመባል የበቁትን የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርእሰ መስተዳደር አምባቸው መኮንን (ዶ/ር) በወፍ በረር እናወሳለን። በተፈጠረው አጋጣሚ ከጓዳቸው ጋር በምድር የጀመሩትን በዘለዓለም ውስጥ ለመጨረስ በሚመስል መልኩ አብረው ለመጓዝ የሞት ጽዋቸውን የተጎነጩትን የሥራ ባልደረቦች እና ክልሉን በቅንነት አገልግለው ሳይጨርሱ ተቀጭተዋል የሚባልላቸውን ግለሰቦችም በጨረፍታ እናነሳለን።

አምባቸው መኮንን (ዶ/ር)
በሥራ ባልደረቦቻቸው ፊት የመከፋትን ስሜት ላለማሳየት የሚጥሩ እና ፈገግታቸውን ለመሸፈን የሚታገሉ፣ ጨዋታቸው የማይጠገብ እንዲሁም ቤተሰብ አክባሪ ለመሆናቸው በተለያዩ የክልል እና የፌዴራል መሥሪያ ቤት አብረዋቸው የሠሩ የስራ ባልደረቦቻቸው ይመሰክራሉ። አምባቸው በኢሕአዴግ ውስጥ ለመጣው ለውጥም ከፍተኛ ተጋድሎ ማድረጋቸውን ወዳጆቻቸው ይናገራሉ።

በተለይም የአማራ እና የኦሮሚያ ክልል ወጣቶች ለሰላማዊ ሰልፍ ወጥተው መገደል የለባቸውም በማለት በማእከላዊ ኮሚቴ ስብሰባዎች ላይ አንዳንዴም ሕይወታቸውን ለአደጋ ጥለውም ጭምር ሲታገሉ እንደነበር የቅርብ ወዳጆቻቸው ያወሳሉ።

በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በ1990 በኢኮኖሚክስ ትምህርት ያጠናቀቁት አምባቸው፥ በልጅነታቸው መምህር መሆን ይፈልጉ እንደነበርም የቅርብ ጓደኞቻቸው ከእርሳቸው ባለፈ ምስክር ናቸው። የኹለተኛ ዲግሪያቸውን በሰሜን ኮርያ በኢኮኖሚክስ ትምህርት ያጠናቀቁት አምባቸው፣ ለ11 ዓመታት በተለያዩ የሥራ መስኮች ላይ ካገለገሉ በኋላ የዶክትሬት ዲግሪ ዕድል አግኝተው ወደ እንግሊዝ አገር ማቅናታቸውን የሕይወት ታሪካቸው ያስረዳል።
ለኹለተኛ ዲግሪያቸው ነጻ የትምህርት ዕድል የሰጣቸው ኬንት ዩኒቨርሲቲ፣ ለሦስተኛ ዲግሪ ሌላ ዕድል በመስጠት ተቀበላቸው።

አምባቸው በእንግሊዝ የነበራቸውን ቆይታ ብዙ ጓደኞቻቸውም ሆኑ እርሳቸው አይረሱትም። ትምርታቸውን መከታተል ከጀመሩ በኋላ ከመንግሥት ጥለው እንዲመለሱ ትዕዛዝ የደረሳቸው ሲሆን፣ እርሳቸው ግን አሻፈረኝ በማለት ትምህርታቸውን ራሳቸውን በመደጎም እና ወዳጆቻቸውም ከአገር ውስጥ ሆነው በሚያዋጡት ገንዘብ ተከታትለው አጠናቀቁ።

በኢኮኖሚክስ የሦስተኛ ዲግሪያቸውን ከያዙ በኋላም በተለያዩ የፌዴራል የሥራ ኃላፊነት ላይ የነበሩት አምባቸው፥ ባለፈው 2011 ዓመት በየካቲት ወር ገዱ አንዳርጋቸውን በመተካት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር በመሆን ሕይወታቸው ከኹለት የሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር እስካለፈበት ጊዜ ድረስ በማገልገል ላይም ነበሩ።

ምግባሩ ከበደ
ከአምባቸውም ባለፈ የአማራ ክልል የአቃቤ ሕግ ምግባሩ ከበደንም እንጥቀስ። የፖለቲካ ብቃትን ከግሩም ሰው አክባሪነት እና ጨዋነት ጋር አጣምረው የያዙ እንደነበሩ ይነገርላቸዋል። ገና በለጋ ዕድሜያቸው እና ብዙ ሊሠሩ በሚችሉበት ጊዜ በአጭር መቀጨታቸውም የበርካቶችን ልብ የሰበረ ኹነት ነበር። በተለያዩ ደረጃዎች በዐቃቤ ሕግነት እና ከ1998 ጀምሮ ረዘም ላሉ ጊዜያት በምሥራቅ ጎጃም አስተዳደር ዞን በተለያዩ የመሪነት ቦታዎች ያገለገሉት ምግባሩ፥ በ2008 የክልሉ ርዕሰ መስተዳድሩ አማካሪ ሆነው ተሹመዋል።

ቀጥሎም በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ሆነው በማገልገል ላይ እያሉ በተፈፀመው ጥቃት ሕይወታቸው ያለፈ ሲሆን፣ ሰኔ 19/2011 ከአጋሮቻቸው ጋር በባሕር ዳር ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስትያን ስርዓተ ቀብራቸው ተካሒዷል። የሦስት ወንድ እና የኹለት ሴት ልጆች አባት የሆኑት ምግባሩ በተወለዱ በ45 ዓመታቸው ነበር ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት።

ምግባሩን በሥራቸው የሚያደንቋቸው በርካቶች ናቸው። ‹‹ሕግን አክብሮ የሚያስከብር ትጉህ›› ሲሉም ያሞካሿቸዋል፣ በዙሪያቸው የነበሩ የሥራ ባልደረቦቻቸው። በደቡብ ጎንደር አስተዳዳር ዞን ደራ ወረዳ ከአባታቸው ከከበደ እውነቱ እና ከእናታቸው ከየሺ ውበቱ በ1966 የተወለዱት ምግባሩ፥ ልክ እንደ ዘለዓለም ጓዳቸው አምባቸው ሁሉ ትምህርታቸውን ፋታ እንኳን ሳይወስዱ ረጅሙን ትምህርት ጉዞ ማጋመስ እንደቻሉም ግለ ታሪካቸው ያስረዳል።

የሕይወት ታሪካቸው መዝገብ እንደሚያስረዳው ከሆነ የሕግ የመጀመሪያ እና ኹለተኛ ዲግሪያቸውን ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ማግኘት ችለዋል። ታድያ በትምህርት ቤት ቆይታቸውም ትንታግ ከሚባሉ ተማሪዎች ተርታ ይመደቡ እንደነበርም አዲስ ማለዳ ከቀድሞ ትምህርት ቤት ጓደኞቻቸው ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።

እዘዝ ዋሴ
በክልል የአስተዳደር እና ጸጥታ ዘርፍ ግንባታ ኃላፊ ብርጋዴር ጄነራል አሳምነው ጽጌ ተቀነባብሯል ተብሎ ከመንግሥት ወገን በተነገረው እና ከክልል እስከ ፌዴራል ድረስ የተዘረጋው እና በተመሳሳይ ወቅት የተፈጸመው ግድያ ታዲያ በአማራ ክልል ሌላም የክልሉን ሕዝብ ሕልም በጫንቃው የተሸከመ እና ሩቅ አልሞ ቅርብ ለማደር የተገደደ ሌላ ሰማዕትም አለ። እዘዝ ዋሴ።

የክልሉን ርዕሰ መስተዳደር አምባቸውን በቅርብ በመሆን ሲያማክሩ እና ስለ ክልሉ መጻኢ ዕድል ሲጨነቁ የኖሩ ባለ ምጡቅ አዕምሮ ነበሩ፣ እዘዝ። በደቡብ ጎንደር ዞን እስቴ ወረዳ በ1957 ከአባታቸው ከዋሴ መንግሥቱ እና ከእናታቸው የውብዳር ቢወጣ የተወለዱት እዘዝ፣ እስከ 1982 ድረስ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ ቆይተው ከጓደኞቻቸው ጋር ደርግን በመቃወም ወደ ትግል ገቡ። ከትግሉ በኋላም በተለያዩ ወረዳዎች የሰላም እና የመረጋጋት ሥራዎች በብቃት መምራታቸውን የሕይወት ታሪካቸው ያትታል።

እዘዝ ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በቢዝነስ ማኔጅመንት እና የማስተርስ ዲግሪያቸውን በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን አጠናቀዋል። የኹለት ሴት እና የሦስት ወንድ ልጆች አባት የነበሩት እዘዝ፥ ከ1998 እስከ 2002 ድረስ የእስቴ ወረዳ ሕዝብን በመወከል በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አገልግለዋል። የደቡብ ጎንደር ዞንን በዋና አስተዳዳሪነት በመሩበት ወቅትም የራሳቸውን አሻራ አሳርፈዋል።

በክልሉ ርዕሰ መስተዳደር እና ከፍተኛ ሥራ ኃላፊዎች ላይ ከተፈጸመው ግድያ እና በተመሳሳይ ቀን የብርጋዴር ጄነራል አሳምነው ፅጌ ስርዓተ ቀብርም በላሊበላ ከተማ ከተፈጸመ እነሆ ዓመቱን ደፍኗል። አሳምነው መርተው እና አስተባብረውታል በተባለው ጥቃት አምባቸው በሚመሩት የክልሉ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣኖች በተገኙበት ስብሰባ ቅዳሜ ከቀኑ 11 ሰዓት ገደማ መጀመሩን ሕይወታቸው የተረፉ የኮሚቴው አባላት በወቅቱ በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን በመቅረብ ኹነቱን ሲያወሱ እንደነበር የሚታወስ ነው።

በተመሳሳይ በክልሉ የፖሊስ ኮሚሽን ቅጥር ግቢ ውስጥ ግድያዎቹን አስተባብሯል የተባሉት ብ/ጄኔራል አሳምነው ሌላ ስብሰባ ጠርተዋል። እዛም የክልሉን የፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነርን ጨምሮ የተለያዩ የፀጥታው ዘርፍ አመራሮች ተሰብስበው ባሉበት እንደተቆለፈባቸው እና የፖሊስ ኮሚሽኑም የመጀመሪያው ዒላማ ሆኖ ጄነራሉ አሰማርተዋቸዋል በተባሉ የልዩ ፖሊሶች ተከበው እንደነበርም ለአዲስ ማለዳ የዐይን እማኞች አስረድተው ነበር።

በመቀጠልም የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጽሕፈት ቤት ተከቦ ከባድ የተኩስ ድምፅ መሰማት መጀመሩን ተከትሎ በስብሰባው ላይ የነበሩት አመራሮች በተለያየ አቅጣጫ ከአደጋው ለመራቅ ጥረት ቢያደርጉም ጥረታቸው ሳይሳካ ቀርቶ አምባቸውን እና አማካሪያቸውን እዘዝ ዋሴን እንዲሁም ምግባሩ ከበደ ላይመለሱ አሸልበዋል። ጊዜውም ሰኔ 15/2011 የዛሬ አንድ ዓመት ነው።

ከዛም በዛው ሳምንት ሰኞ፣ ሰኔ 17 በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ምግባሩ ከበደ ሕይወታቸው ማለፉ ታውቆ በሰዓታት ልዩነት የጥቃቱ አቀነባባሪ እና መሪ የተባሉት ብርጋዴር ጀነራል አሳምነው ፅጌ ከፀጥታ ኃይሎች በተከፈተ ተኩስ ሕይወታቸው አለፈ የሚል ዜናም ከአድማስ አድማስ ናኘ። ይኸው ወቅቱም በክልሉ ጠባሳ ጥሎ ካለፈ የአንድ ዓመት ዕድሜ አስቆጠረ።

የክልሉ ነባራዊ ሁኔታ ምን መልክ ያዘ?
ከዚሁ አስደንጋጭ ክስተት በኋላ የአማራ ክልል በተለይም የክልሉ መናገሻ ከተማ ባህር ዳር የቀደመው ሰላሟ በውጥረት እና በጥርጣሬ የተሞላ ለመሆኑ አዲስ ማለዳ በተደጋጋሚ በተመላለሰችበት ወቅት ለመታዘብ ችላለች። ከአፍ እስከ አፍንጫ በወታደራዊ ትጥቅ የደመቁ የክልሉን የልዮ ኃይል አባላት በከተማዋ ዋና ዋና እና ሰዋራ ስፍራዎች ሲንቀሳቀሱ እና በንስር ዐይን ከተማዋን ሲጠብቁ ውለው ሲጠብቁ ሲያድሩ መታዘብም እምብዛም የሚገርም ላይሆን ይችላል።

ይህን የከተማዋን ውጥረት እና የእርስ በርስ ጥርጣሬ የተሞላበትን እንቅስቃሴ ታዲያ ነዋሪዎችም ይስማሙበታል። ከዚህ ቀደም በዘፈቀደ ይከወን የነበረ የትኛውም እንቅስቃሴ ከአንድ ዓመት በፊት በክልሉ ከተከሰተው አስደንጋጭ ኹነት ወዲህ የትኛውም አይነት እንቅስቃሴ እና ኹነት ከመንግሥት ወገን በአንክሮ የሚጤን ጉዳይ እንደሆነም አዲስ ማለዳ ለመታዘብ ችላለች።

ከአንድ ዓመት በፊት በዚሁ ወቅት በአማራ ክልል የደረሰው ድንጋጤ የፌዴራል መናገሻ የሆነችው አዲስ አበባንም አልማራትም ነበር። የአገሪቱን የጦር ኃይል በመምራት ሲያገለግሉ የነበሩት ጄነራል ሰዓረ መኮንን እና በጡረታ ተገልለው የነበሩት ሜጀር ጄነራል ገዛኢ አበራም የሞትን ጽዋ ከትግል ጓዳቸው ጋር ከተጎነጩ እነሆ አንድ ዓመት ተቆጠረ።

ጄነራል ሰዓረ መኮንን
በዐሥራ ስድስት ዓመታቸው በ1969 ነበር ‹‹ኧረ ጥራኝ ጫካው፣ ኧረ ጥራኝ ዱሩ›› ብለው ወታደራዊ አገዛዙን ለመፋለም የታላላቆቻቸውን ፈለግ ተከትለው ደደቢት ላይ የከተሙት። የያኔው አፍላ ወጣት ሰዓረ የጀመሩት የትጥቅ ትግል ሕይወታቸው ከአጋዚ ኦፕሬሽን እስከ ዘመቻ ዋለልኝ፣ ከዘመቻ ቴዎድሮስ እስከ ሰርዶ ኦፕሬሽን ያልመሩትና ያልተሳተፉበት ዓውደ ውጊያ አልነበረም።

ጄነራል ሰዓረ ከራስ ዳሽን ተራራ እስከ ዳሎል ረባዳ መሬት፣ ከጋምቤላ ጫፍ እስከ ሱማሌ አሸዋማ መሬቶች ደረታቸውን ለጦር እግራቸውን ለእሾህ ገብረው የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ አንግበው በርካታ ገድሎችን መፈፀማቸውን በመዋዕለ ዜናቸው ተከትቧል። ይሁን እንጂ በሐሩር እና በቁር እየተጠበሱ ከደማቸው እና ከላባቸው እያጠቀሰ ደማቅ ታሪክ የጻፉላት ኢትዮጵያ ብድሯን በሞት ከፈለቻችው፤ ጄነራል ሰዓረ ወደማይቀርበት ከሔዱ እነሆ አንድ ዓመት ሆነ።

የግድያቸው ዜና ከተሰማበት ደቂቃ አንስቶ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዳር እስከ ዳር በሐዘን ከተሰበረም የአንድ ዓመት እድሜ ሆነው። በተለይ በወቅቱ የቆፍጣና መኮንናቸውን አስከሬን ቆሞ ማየት የተሳናቸው የመከላከያ ሠራዊት አባላትን ላየ፣ ሀዘኑ መሪር እና ከልብ እንደማይወጣ ያስታውቅ ነበር።

ጄነራል ሰዓረ ከወታደራዊ ሳይንስ ባሻገር ከአገረ እንግሊዝ ግሪንዊች ዩኒቨርሲቲ በሥራ አመራር የኹለተኛ ዲግሪያቸውን በላቀ ውጤት በማጠናቀቅ ከውትድርናውም ባለፈ በሲቪል ትምህርት ግንባር ቀደም እንደሆኑ አሳይተዋል። ይህ ሁሉ ግን ጄነራሉን ሩቅ አሳቢ ቅርብ አዳሪ ከመሆን አልከለከለላቸውም። ሰኔ 15 /2011 በዱር በገደሉ አፍንጫው ስር ሔደው ምንም ያላላቸው ሞት፣ አርፈው ከተቀመጡበት መኖሪያ ቤታቸው ድረስ ሰተት ብሎ መጥቶ አገኛቸው። ከሚወዷቸው እና ኹሌም በሰቀቀን ከሚናፍቋቸው ቤተሰቦቻቸው ጋር ከለያያቸው አሁን አንድ ዓመት ሞላ።

ሜጀር ጄነራል ገዛኢ አበራ
ሌላው በዘርፉ እምብዛም ሥማቸው የማይነሳ ነገር ግን አንገታቸውን ደፍተው የመከላከያን ሎጅስቲክ በተገቢው መስመር ሲዘረጉ እና ሲያጎለብቱ የነበሩ የዘመናችን ትጉህ ሜጀር ጄነራል ገዛኢ ናቸው። ጄነራሉ የጡረታ ወጉ ነበርና ወደ ወዳጃቸው፣ የትግል ጓዳቸው እና አብሮ አደጋቸው ጄነራል ሰዓረ ቤት በመሔድ የልብ የልባቸውን በሚያወጉበት ወቅት ነበር የተገደሉት።

ገና ወደ ትግል ጎራው በተቀላቀሉበት የለጋነት ዕድሜያቸው ላይለያዩ እና ላይከዳዱ ጓዳዊ ጥብቅ መሐላ ነበራቸው እና ሞታቸውም ከሕይወት ዘመን ጓዳቸው፣ የትግል አጋራቸው፣ ወንድማቸው ጄነራል ሰዓረ ጋር በአንድ ቅፅበት ሆነ። ሞትም የኹለቱን መሐላ አለማክበር አልቻለም፤ ሊለያያቸውም አቅም አልነበረውም። የሽራፊ ሰኮንዶች መቀዳደም እንጂ ምድር ላይ የነበረው አብሮነታቸው የዘላለም ጉዟቸውም ላይ አልተቀየረም።

ሰርክ በባልንጀራቸው ጄነራል ሰዓረ ቤት መገኘት የሚያዘወትሩት ጡረተኛው ጄነራል፣ ሰኔ 15 ግን እንደሌላው ጊዜ አመሻሽተው በጨዋታ ረክተው ወደ መኖሪያቸው አልተመለሱም። በባልንጀራቸው የቅርብ ጠባቂ የሞትን ፅዋ ተጎንጭተው አምስት ልጆቻቸውን እና ባለቤታቸውን፣ የበርሃ ጓዳቸውን አበባ ዘሚካኤልን በወጉ ሳይሰናበቱ በጄነራል ሰዓረ ቤት ካሸለቡ እነሆ ሰኔ 15 ሲመጣ ድፍን አንድ ዓመት ተቆጠረ።

ገዛኢ አበራ እስከ ሕልፈተ ሕይወታቸው ድረስ በፐብሊክ ሰርቪስ ውስጥ በቦርድ አመራርነት በማገልገል ሕዝቡን ከትራንስፖርት እጦት እንዲገላገል የበኩላቸውን ጥረት በማድረግ እናት አገራቸውን ሲያገለግሉ ነበር። ሜጀር ጄነራል ገዛኢ አበራ በተወለዱ በ58 ዓመታቸው ከዚህ ዓመት በሞት ተለይተዋል።

የኹለቱን ጄነራሎች ሞት በተመለከተ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የጄነራሎች የቅርብ ቤተሰቦችም ከመንግሥት በኩል ምንም አይነት ምላሽ እያገኙ እንዳልሆነ እና ይህም ተስፋ እንድንቆርጥ አድርጎናል ሲሉ ተናግረዋል። ሥማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ የሜጀር ጄነራል ገዛኢ ቅርብ ቤተሰብ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት፣ ‹‹ከተራዘመው የምርመራ እና የሕግ ሒደት ጋር ተያይዞ ጄነራሎችን እና ክልል መንግሥታትን ገዳዮች በትክክለኛው እና በአጭር መንገድ ለሕግ አቅርቦ ተገቢው ቅጣት ባለመሰጠቱ እንደቤተሰብ ልባችን ተሰብሯል፤ እንባችንም አልታበሰም›› ሲሉ አስረድተዋል። አያይዘውም መንግሥት በዚህ በኩል ተገቢውን ትኩርት እና ርብርብ አድርጎ በአጥፊዎች ላይ የተፋጠነ ፍርድ እንዲሰጥ እንደሚማጸኑም ጨምረው ገልጸዋል።

አንድ ዓመት እንደ ቀልድ ያስቆጠረው እነዚህ የአማራ ክልል ፈርጦች በወገናቸው ተገድለዋል። ታድያ ባመኑት እና ክልሉን በጸጥታው ዘርፍ ይመራሉ ተብሎ ዕምነት በተጣለባቸው ብርጋዴር ጄነራል አሳምነው ተገድለዋል መባሉን ግን አሁንም አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ግለሰቦች አይዋጥላቸውም።

በተለይም ደግሞ ከግድያው ወዲህ በክልሉ እና በአዲስ አበባም በቁጥጥር ስር ውለው የነበሩ ግለሰቦችን በመንተራስ ከፍተኛ የሆነ ጥርጣሬ እንዳላቸው እና ለዚህም ደግሞ በቁጥጥር ስር ውለው የነበሩ ሰዎችን ከጉዳዩ ጋር ያላቸውን ተያያዥነት ለመናገርም አስቸጋሪ መሆኑን ይናገራሉ።

በባህር ዳር ከተማ ነዋሪ የሆኑ እና ከአንድ ዓመት በፊት በክልሉ በተደረጉ ግድያዎችን በተመለከተ ሥማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አስተያየት ሰጪ እንደሚናገሩት ‹‹ሲጀመር እኔ ጄነራል አሳምነው ገደለ በሚል የሚነዛውን አሉባልታ ማመን ይቸግረኛል›› ሲሉ ይጀምራሉ። አስተያየት ሰጪያችን ሲቀጥሉ ከዚሁ ኹነት ጋር ተያይዞ እጃቸው ይኖርበታል በሚል በጥርጣሬ ተይዘው የነበሩ ሰዎች ከወራት እስር በኋላ በነጻ መለቀቀዘቸው ራሱ በጥናት የተወሰደ እርምጃ እንዳልነበር እና የ‹አሳምነው ገደለ› ተብሎ የተነሳውም ሐሳብ ግለሰቡ ከመሞቱ ጋር ተያይዞ ምላሽ መስጠት በማይችልበት ሁኔታ ጋር በማያያዝ የተለጠፈበት ሥም ነው ሲሉም ያክላለሉ።
እንደ አስተያየት ሰጪው አነጋገር በተለይም ደግሞ ብርጋዴር አሳምነውን የመንግሥት የጸጥታ ኃይላት ከገደሉት በኋላ በተንቀሳቃሽ ምስል እየቀረጹ ሲዘባበቱበት የነበረውም አግባብነት የሌለው እና ለቤተሰቦቹ ከባድ የሥነ ልቦና ጫና እንደሚደርስባቸውም ማሰብ ያልተቻለበት ድርጊት መሆኑንም ያስታውሳሉ።

ለመሆኑ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ምን ተከናወነ?
የባለሥልጣናቱ ግድያ ከተሰማበት ቅጽበት ጀምሮ መንግሥት አፋጣኝ እርምጃዎችን በመውሰድ እና በተለያዩ አካባቢዎች በተለይም ደግሞ በአማራ ክልል ከፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች እስከ ክልሉ ከፍተኛ የጸጥታ ኃይል አመራሮች ድረስ በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ ሲያደርግ እንደነበር የሚታወስ ነው። በመንግሥት እና በጸጥታ ኃይል ቅንጅት ቁጥራቸው የበዛ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው እንደነበርም ይታወሳል።

በአዲስ አበባ ከጄነራል ሰዓረ መኮንን የግል ጠባቂ አስር አለቃ ጥጋቡ እስከ አዲስ አበባ ባላደራ ባልደራስ ፓርቲ አመራር ስንታየሁ ቸኮል እና ባልደረባው ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩም የዚሁ እስር ተጠቂ ነበሩ። አማራ ብሔራዊ ንቅናቄ አመራር እና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው ክርስቲያን ታደለ ወይም በቅጽል ሥሙ ገብርየም በዚሁ ክስተት ዘብጥያ ወርደው ከነበሩት ውስጥ ይጠቀሳሉ።

በእስር ውስጥ ከነበሩት እና ለወራት በጨለማ ቤት ታስሪያለሁ የሚሉት ስንታየሁ ቸኮል ከአዲስ ማለዳ ጋር አጭር ቆይታ አድርገው ነበር። ‹‹በመጀመሪያ ደረጃ አሁን ያለው መንግሥት ሳናጣራ አናስርም ብሎ በተናገረበት በአጭር ጊዜ ነው እኛን ሳያጣራ አስሮን አምስት ወራት በእስር እንድንቆይ አድርጎናል›› ይላሉ። በወቅቱ ምንም የሚያውቁት ነገር እንዳልነበረ እና ወደ እስር ቤት መወርወራቸው ግርምትን እንደሚጭርባቸውም ይናገራሉ።

‹‹በዶክተር ዐቢይ አሕመድ የሥልጣን ዘመን እኔ የመጀመሪያው ነኝ በጨለማ ቤት የታሰርኩት ብዬ መናገር እችላለሁ›› የሚሉት ስንታየሁ፣ በጉዳዩ ላይ ምንም የማይመለከታቸው ግለሰብ እንደነበሩም ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል። በአሁኑ ሰዓት ከአምስት ወራት እስር በኋላ በነጻነት በመንቀሳቀስ ላይ እንደሚገኙ እና ከወደ ሕግ አካልም ምንም አይነት መጥሪያ ደርሷቸው እንደማያውቅም አስታውቀዋል።

ስንታየሁ በዚህ ብቻ አያበቁም፤ ከዓመት በፊት ተፈጸመ ስለተባለው ጉዳይ እና አሁንም ድረስ ከመንግሥት ወገን ትክክለኛ ፍርድ አልተገኘለትም ስለሚባለው ጉዳይ ሲናገቱ ‹‹ጉዳዩ እና አሁን የተደረሰበት ደረጃ እኮ ለቤተሰቦቻቸውም ግልጽ አይደለም፤ ኹሉም ነገር ድፍን እንዳለ የተቀመጠ ጉዳይ እኮ ነው›› ሲሉ ይናገራሉ።
ሌላው አስተያየት ሰጪ ደግሞ በዚሁ ጉዳይ በእስር ላይ የነበረው ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ ነው። ከተያዘበት ቀን ጀምሮ እስኪ ለቀቅበት ባሉት ወራት ውስጥ በመጀመሪያ ከተያዘበት ምክንያት ጋር የማይያያዙ ጉዳዮች በመርማሪዎች በኩል ይቀርቡለት የነበሩትን ጥያቄዎች ለአዲስ ማለዳ ሲናገር ‹‹አንድም ቀን ተጠርጥረን በተያዝንበት ጉዳይ ጥያቄ አቅርበውልን አያውቁም፤ በጠቅላላው ሲጠይቁን የነበረው ስለ ባልደራስ ብቻ ነበር›› ሲልም ቆይታውን ያስታውሳል።

‹‹ምንም እንኳን በቁጥጥር ስር ስንውል እንደማይመለከተን ቢያውቁትም ግን ጉዳዩን አልጠየቁንም። እንዲህ አይነት አካሔድ ደግሞ ከለውጡ በፊት የነበረው አይነት አካሔድ ነው። አንድ አጋጣሚ ሲፈጠር ቂም የተያዘበትን ሰው በግርግር አስገብቶ ማሰቃየት የቆየ እና ለውጥ በሚባለው መንግሥትም የሚከወን ተግባር ነው። አሁን በእርግጥ ለውጥ በተወሰነ መልኩ ቢኖርም ግን ገና መሻሻል ያለበት እና ረጅም ጉዞ የሚያስፈልገው ጉዳይ ለመሆኑም አያጠራጥርም›› ሲል ይናገራል።

ሰኔ 15 ሲባል ኤልያስ ወደ አዕምሮው ከባድ የሐዘን ጊዜ እና አስደንጋጭ ወቅት ብቅ እንደሚሉበትም ይናገራል። ከፌዴራል እስከ ክልል ድረስ በተፈጸመው ግድያ ሕይወታቸውን ያጡ ሰዎችን በሚመለከትም መሪር ሐዘን እንደሚሰማው ይናገራል። ‹‹በኹሉም አካባቢ የሞቱት ሰዎች በጣም ያሳዝናሉ። ግን የውስጥ ፖለቲካው ውጤት ነው ብዬ ነው የማስበው›› ሲልም ይናገራል።

ዐቃቤ ሕግ
በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ከፍተኛ አመራሮች እና በኹለቱ ጄነራሎች ግድያ ጋር በተያዘ የፌደራል ዐቃቤ ሕግ በርከት ያሉ ተግባራትን እና እልህ አስጨራሽ ሥራዎችን ማካሔዱን እና አሁንም እያካሔደ እንደሚገኝ ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል። በዚህም ረገድ በፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች ቁጥጥር ዋና ዳይሬክተር ፍቃዱ ለአዲስ ማለዳ እንደሚናገሩት፤ በአሁኑ ሰዓት መንግሥት ከበርካታ እልህ አስጨራሽ ጉዳዮች በኋላ ክስ መመስረቱን እና ምስክሮችም እየተሰሙ እንደነበር ጠቅሰዋል።

ነገር ግን በአሁኑ ሰዓት በዓለም ዐቀፍ ብሎም በአገራችን በተከሰተው ኮቪድ 19 የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ ፍርድ ቤቶች በመዘጋታቸው፣ እምብዛም እየተከናወነ እንዳልሆነ ጠቁመዋል። ምስክሮችን የማዳመጥ ጊዜ ላይ የነበረው ጉዳዩ በክልልም ሆነ በፌዴራል ደረጃ የተዘጋው ፍርድ ቤት ያስተጓጎለው ሲሆን፣ ይህም ለግንቦት 26/2012 ተቀጥሮ የነበረው የምስክሮች ማዳመጥ ሒደት ለሐምሌ 1/2012 መተላለፉንም ፍቃዱ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 85 ሠኔ 13 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here