የኢትዮጵያ ፌዴራሊስት ኃይሎች ጥምረት ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) እና የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሕብረት (ኢዴሕ)ን ከጥምረቱ መተዳደሪያ ደንብ ውጪ ሆነው ተገኝተዋል በሚል ከአባልነት መሰረዙን አስታወቀ።
ጥምረቱ በአደረጃጀቱ ላይ ውይይት ሲያደርግ ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ጥምረቱ ውስጥ ወዥንብር እየፈጠረ ነው ብለዋል። የጥምረቱ የአደረጃጀት ኮሚቴ ሰብሳቢ ቶሎሳ ተስፋዬ “ፓርቲው የጥምረቱ አባላትን ለመከፋፈል የተለያዩ ጫናዎች እየፈጠረ ነው” ብለዋል። “ይህ ብቻ ሳይሆን ህወሓት ጥምረቱን እንደ ሽፋን ተጠቅሞ አገርን ለማወክ እየተንቀሳቀሰ ነው” ሲሉም ገልጸዋል። በተጨማሪም ፓርቲው በጥምረቱ ሰብሰባ ላይ እንደማይገኝና የጥምረቱ ስብሰባም መቀሌ ካልተካሄደ ተቀባይነት እንደሌለው እየገለጸ ነው ሲሉ ከስሰዋል። ቶሎሳ “ህወሓት እኔ ያልኩት ካልሆነና እኛ ካልመራን ትክክል አይደለም የሚል” ግትር አቋም ያራምዳል ሲሉም ክሳቸውን ያቀርባሉ።
የጥምረቱ ሊቀ-መንበር ደረጄ በቀለ እንደሚሉት ህወሓትና ኢዴሕ ሕገ ወጥ በሆነ መልኩ እየተንቀሳቀሱ በመሆኑ ታግደዋል፣ ይህንንም ሁሉም የጥምረቱ አባላት የተስማሙበት ጉዳይ ነው ይላሉ።
አቶ ደረጄ ”ሁሉም የጥምረቱ አባላት በሁለቱ ፓርቲዎች መሰረዝ ላይ ስምምነት ላይ ደርሰዋል” በማለት ከጉባኤው በኋላ የደረሱበትን ስምምነት ገልጸዋል።
ጥምረቱ 24 ፓርቲዎችን ያቀፈ ሲሆን በትናንቱ ጉባኤው 22 የፖለቲካ ፓርቲዎች ተገኝተዋል፤ ሌሎች አምስት የፖለቲካ ፓርቲዎች ደግሞ ጥምረቱን ተቀላቅለዋል።
ቅጽ 2 ቁጥር 86 ሠኔ 20 2012



