ኮቪድ 19 እና የኢኮኖሚ ማሻሻያ

0
526

በኢትዮጵያ አሉ ከሚባሉና በወጣት እድሜ የሚገኙ፣ በአገሪቱ ጽንፍ የወጣ ነው ተብሎ በሚታማ ፖለቲካ ውስጥም በጎ ጎኖችን በማየት ለመልካም ውጤት ከሚሠሩ መካከል ተጠቃሽ ናቸው። የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከመቀሌ ዩኒቨርስቲ በኢኮኖሚክስ ሲያጠናቅቁ፣ ኹለተኛ ዲግሪያቸውን በዓለማቀፍ ፖሊሲ በአሜሪካ ከጆርጅ ዋሺንግተን ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም ሦስተኛ ዲግሪያቸውን በፖለቲካል ኢኮኖሚ በዛው አሜሪካ ከሚገኘው ሜሪላንድ ዩኒቨርስቲ ተቀብለዋል። አሁንም ላይ የገንዘብ ኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ በመሆን እያገለገሉ ይገኛሉ፤ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)።
ከዚህ ቀደምም በማኅበረሰብ አገልግሎት አመራር ዘርፍ በኢትዮጵያ እንዲሁም ከኢትዮጵያው ውጪ በተለያዩ አገራ አገልግለዋል። በአማካሪነትም በተለያዩ የመንግሥት እንዲሁም ዓለማቀፍ ተቋማት ድርሻቸውን ተወጥተዋል። ዓለማቀፍ በሆኑት በተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን፣ የምሥራቅና ደቡብ አፍሪካ የጋራ ገበያ፣ እንዲሁም በተባበሩት መንግሥታት የንግድና ልማት ኮንፈረንስ በሙያቸው አገልግለዋል።
በቀድሞው አጠራሩ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር እየሠሩ በነበረ ጊዜ፣ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱና በንግድ ምክር ቤት መካከል የመግባቢያ ሰነድ እንዲፈረም ትልቅ ሚና የተጫወቱ ሲሆን፣ ይህንንም ተከትሎ የተመሠረተው ‹Ethiopian Public Private Consultative Forum› የተባለ መድረክ በመንግሥትና በግል ዘርፉ መካከል ለፖሊሲ ጉዳዮች መነጋገሪያ አውድ ሆኖ የሚያገለግል ነበር። ችግሮችንም በጉልህ በማውጣትና በድፍረት በመግለጽ፣ የሰላ ትችትንም በማቅረብ ይታወቃሉ።
የአዲስ ማለዳ እህት መጽሔት ኢትዮጵያን ቢዝነስ ሪቪው ባደረባ ተወዳጅ ስንታየሁ ከኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርጓል።

በኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የተነሳ የኃይል ሚዛን ለውጥ ይኖራል ብለው ያስባሉ?
አይመስለኝም። ሚዛኑን ጠብቆ የሚሄድ ነው የሚመስለኝ። ምክያቱም በአንድ በኩል አገራት አንዳንድ ወሳኝ ነገሮች ላይ ያላቸውን ብቃት በደንብ መገምገማቸው አይቀርም። ይህ ግን ከወረርሽኙ መከሰት በፊትም ጠቃሚ የፖሊሲ እቅድ መሆን ነበረበት። እንደ ኢትዮጵያ ያለ አገር በምግብ ራስን አለመቻል፣ ለምሳሌ በሎጂስቲክስ ችግር ምክንያት ስንዴ ባይመጣ ምን ሊፈጠር ይችላል ብለህ የምታስብበት ሁኔታ እንዳይደገም፣ በእኛ በኩል አሁን የጀመርነውን ማሻሻያ አጠንክረን ነው የምንሄደው።

በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ግን ኹለት መልእክት ያለው ነው። በአንድ በኩል ምን ያህል እንደተሳሰርን ያሳየ ነው። አንዱ ጋር የሚፈጠረ ችግር እዛው አንዱ ጋር ብቻ ታፍኖ የማይቀር መሆኑን ያሳየ ነው። አሁን ሁሉም ሰው ስጋት ላይ ነው ያለው። አገራትም ሕይወት ማዳን ሥራ ላይ ነው ያተኮሩት። ስለዚህ በጣም ወደ ውስጥ የማየት ነገር ይኖራል። ይህ ነገር ሲያበቃ ግን፣ የሚቀጥለው ወረርሽኝ ይህን እንዳያመጣ እንዴት በተሻለ ትስስር መሠራት አለበት የሚለው መታሰብ አለበት ብዬ ነው የማስበው።

የፈለገ ወደ ውስጥ ብታይ የማትቆጣጠረው ነገር አለ። መቼስ ከዓለም ተዘግተህ መቀመጥ አትችልም! የዓለም ኢኮኖሚ እርስ በእርሱ የተሳሰረና አንዱ በሌላው ጥገኛ ነው። ይህ እውነት መቼም የሚቀየር አይደለም። እንደውም ለእኔ የበለጠ ሰዋዊ የሆነ ዓለማቀፍ እይታው፣ እኔ ብቻ ልበልጽግ ወይም እኔ ብቻ ልደግ ሳይሆን፣ የሁሉንም የጤና ዝግጅትና የኢኮኖሚ አቅም አሟጦ ሊያወጣ የሚችል፣ ሰብአዊነት ላይ ያተኮረ ኅብረት ያመጣል ብዬ ነው የምገምተው።

በዚህ ወረርሽኝ ምክንያት ለምሳሌ የኒዮ ሊብራል እሳቤ ተፈትኗል። የመንግሥት ሚና ተጠናክሮ ሲታይ የግል ዘርፉ በአንጻሩ ያሉትን ችግሮች መድፈን እንደማይችል ታይቷል። እንዲህ ያሉ አመለካከቶች በወረርሽኙ የተነሳ ተጽዕኖ ሊኖራቸው አይችልም?
የመንግሥት ሚና በኢኮኖሚ ውስጥ የሚለውን ጥያቄ እያነሳህ ከሆነ፣ ድሮም ቢሆን ከወሬ ባለፈ በተግባር የትኛውም አገር የኢኮኖሚ እድገት ከምጣኔ ሀብት ታሪክ ብታይ፣ መንግሥታት በጣም ትርጉም ያለው ሚና ነው በምጣኔ ሀብት ውስጥ የተጫወቱት። የመንግሥት የአመራር ድርሻ ኢኮኖሚውን አንድ ላይ የማንቀሳቀስ ጠንካራ ሚና ሊጫወት ይገባል የሚል ጠንካራ እምነት አለኝ። መንግሥትም ይህ እምነት አለው። የዓለም ተሞክሮም ይህን ነው የሚያሳየው።

 

በተግባር የየትኛውንም አገር የእድገት ተሞክሮ ብታይ፣ መንግሥት ጠንካራ ተሳትፎ ነበረው፣ በኢኮኖሚ እድገት ላይ። ምንአልባት ‹rhetoric› ይቀንሳል ወይ ከሆነ ጥያቄው፤ አዎን ይቀንሳል። ይህ ደግሞ ከፋይናንስ ቀውሱም በኋላ የመጣ ነው። በ2008 ከተከሰተው ቀውስ በኋላ፣ አጠቃላይ ኢኮኖሚውን ማረጋጋት ላይ መንግሥት የሚኖረው ሚና ጎልቶ እየወጣበት የታየበት ነው የነበረው። አገራት ጠንካራ መንግሥት የሚያስፈልጋቸው መሆኑም እሙን ነው። ግን የምርት ኃይሎች አደረጃጀት ወደ መንግሥት ይዞታነት ይቀየራል ማለት አይደለም።

እዚህ ላይ መንግሥት አስቀድሞ ከነበረው ድርሻ አንጻር ወደ ማእከልነት አይመልሰውም?
አዎን! ለምሳሌ ፈረንሳይን ብታይ ብሔራዊ ማድረግም ቢያስፈልግ፣ አንዳንድ ቁልፍ የሆኑ አገራዊ ሀብቶች ወደ ሌላ ቦታ እንዳይሄዱ ማንኛውንም እርምጃ እንወስዳለን እያሉ ነው። እንዲህ ያለ ‹ሪቶሪክ› መምጣቱ አይቀርም። በተለይ ቁልፍ የሚሏቸው ዘርፎች መንግሥታት በአገር ደረጃ መያዛቸውን ማረጋገጣቸው የሚቀር አይመስለኝም። እናም ትክክል ነው፣ ይህ የችግሩ ውጤት ነው።
ግን ሰዎች ደጋግመው የሚስቱትና ማጉላት የምፈልገው ነገር፣ የመንግሥትን ሚና በኢኮኖሚ ውስጥ አሁን የመጣና አዲስ አድርገው የሚያዩበትን አተያይ ስለማልደግፈው ነው። የመንግሥት ሚና በኢኮኖሚ ውስጥ ትልቅ ነበር፣ ሆኖም ይቀጥላል። ምንም ጥያቄ የለውም። የኢትዮጵያ መንግሥት አሁን ጠንካራ ሥራ እየተሠራ ነው። ኢኮኖሚክ ዞን ስለመገንባት እየተወራ ነው።

ይህ ግን የግል ዘርፉን እንዳያድግ መከልከል አለብን ማለት አይደለም። የምርት ኃይሎች አደረጃጀት ወይም ኢኮኖሚውን የምታቀናጅበት መንገድ ብቁ የሆነ፣ የግል ዘርፉ እንዲጥር የሚያደርግ፣ መንግሥት ደግሞ አጠቃላይ የመሪነት ድርሻውን እየተጫወተ ይቀጥላል ማለት ነው።

በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት በ2008 ከተከሰተው የማይተናነስ የምጣኔ ሀብት ቀውስ ሊከሰት እንደሚችል ከወዲሁ እየተገመተ ነው። ያኔ ታድያ በቀውሱ ምክንያት አገራት ሉዓላዊነታቸውን ማጣት ደረጃ የሚያደርስ የዕዳ ችግር ገጥሟቸዋል። አሁንስ እንዲያ ያለ ችግር ይገጥም ይሆን? ኢትዮጵያስ የሚያሰጋት ነገር አለ?
ይህም ትልቅ ስጋት ነው። በተለይ ከፍተኛ የዕዳ ጫና ያለባቸውና ኢኮኖሚያቸውን በአግባቡ መምራት ያልቻሉ አገራት፣ ይህ ስጋት ጎልቶ ቢወጣባቸው የሚገርም አይደለም። በኢትዮጵያም ማሻሻያ ባናደርግ ኖሮ፣ ምንአልባት ይህ እጣ ፈንታ አይቀርልንም ነበር። ሆኖም ባለፉት ኹለት ዓመታት ያደረግናቸው በጣም ወሳኝ የሆኑ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዎች፣ አንደኛ ጠንካራ ‹ፊስካል ስፔስ› እንዲኖረን አድርጓል። ኹለተኛ አጠቃላይ የእዳ ጫናችንን በሚመለከት መዋቅራዊ ለውጦች ሠርተናል። እናም በኢትዮጵያ በኩል እንዲህ ያለ ስጋት አይኖርም።

እንደውም ኢትዮጵያ ከራሷ አልፋ ለአፍሪካ አጠቃላይ ቀውሱ ኢኮኖሚ ላይ ዘላቂ አሉታዊ ተፅእኖ እንዳያሳርፍ፣ አገራትም ከዚህ ችግር ብዙም ሳይጎዱ እንዲወጡ በማድረግ፣ የማስተባበር ሚና እየተጫወተች ነው። ኢትዮጵያን ብቻ ነጥለህ ካነሳን፣ ምንም ዓይነት የሉዓላዊነት ስጋት የሚያመጣብን ነገር የለም።

ያም ብቻ ሳይሆን በተሻለ ሁኔታም ውስጥ ነን። የተሻለ ለመደራደር፣ የተሻለ ስፍራ ለማግኘት፣ ይህን ክስተት እንደ እድል እንጠቀምበታለንም ማለት ነው። ወሳኝ የሆኑ ዘርፎች ላይ ተጨማሪ ኢንቨትመንት ለማድረግ እንደሚያግዘን ነው። አንዳንድ በጣም አስፈላጊ የሆኑ ዘርፎች ላይ፣ ተጨማሪ ኢንቨስትመንትና ኃይል እንደሚያስፈልገን ያሳያል።

በዚህ ኹለት ዓመት የተደረጉ ማሻሻያዎች ውስጥ የውጪ ምንዛሬን የሚመለከት ለውጥ ተጠቃሽ ነው። ይህም በአይኤምኤፍ በኩል የመጣ ለውጥ ነው። እንዲህ ያሉ ኹነቶችስ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ስጋት ውስጥ አይጥሉም?
እኛ ያለን አቋም በአንድ ጊዜ የሚደረግ ትልቅ ዲቫሉዌሽን አግባብ አይደለም የሚል ነው። ይህ ከለውጡ በፊት የተደረገ ነበር፣ ውጤታማ እንዳልነበርም ነው ያየነው። ምክንያቱም ዲቫሉዌሽን ብቻ የዚህን አገር ችግር አይፈታም። አጠቃላይ መዋቅራዊ ችግሮችንም ነው ማየት ያለብን።

አስቀድሞ እንዳልኩት ምጣኔ ሀብት ውስጥ ያለውን መዋቅራዊ እጥረት የሚፈታ ለውጥ ካላደረግህ በቀር፣ ምርት ላይ አተኩረህ ምርታማነት ካልጨመረ፣ ዋጋ በማስተካከል ብቻ የውጪ ንግድ ሊያድግ አይችልም። ስለዚህ እያልን ያለነው በአንድ በኩል ትኩረታችን ምርታማነት ላይ ብቻ ነው መሆን ያለበት። አጠቃላይ የውጪ ምንዛሬአችንን በሚመለከት ደግሞ በአስተዳደር አንጻር መስተካከል አለበት። አጠቃላይ ደግሞ የአቅርቦትና የፍላጎት ችግሩም መፈታት አለበት።

በድምሩ ማክሮ ኢኮኖሚውን በአጠቃላይ ማስተካከል አለብን። ይህ ማለት የገንዘብ ፖሊሲውን ማዘመን እንዲሁም በጥንቃቄ የተዘጋጀ የበጀት ፖሊሲም ያስፈልገናል። በድምሩ እነዚህ ሁሉ ትኩረታቸው ምርታማነት ላይ መሆን አለበት።ግብርና ላይ ምርታማ ሆነህ፣ አሁን በዚህ አካሄድ ከቀጠልን፣ የውጪ ንግድ ገበያው ይሰፋል። ከዚህ ቀደም ያላየናቸው ምርቶች ይገባሉ። አቮካዶ ብቻውን ከቡና ሊበልጥ ይችላል፣ በኹለትና በሦስት ዓመት።

ከውጪ የምናመጣቸው በርካታ ምርቶች፣ እንደ ዘይት ዓይነት፣ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በአገር ውስጥ ምርት ይተካሉ። በእነዚህ ነገሮች ነው አጠቃላይ የማክሮ ኢኮኖሚ እንዲሁም የምንዛሬ ችግሩን የምትፈታው፣ እንጂ በዲቫሉዌሽን አይደለም። ይህን እንኳን ለመደገፍ እንደውም የማንቀበለው ነው።

በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት አገራት የተለያዩ የፖሊሲ ማሻሻዎችን አድርገዋል። ለወትሮው ከራሳቸው ሐሳብ ይልቅ የውጪ ተጽእኖና እንደ አይኤምኤፍ ያሉ ተቋማት ግፊት ይስተዋል ነበር። አሁን ግን ከፖሊሲ አንጻር አገራ ለችግሩ ምላሽ ለመስጠት ያስችላል ያሉትን የመሰላቸውን ነው እያደረጉ ያሉት። ይህ አካሄድ ምንአልባት የዓለማቀፍ ተቋማትን ተጽእኖ ሊያስቀር ይችላል?
እውነት ለመናገር በኢትዮጵያ ሁኔታ የዓለም ባንክ እና የአይ ኤም ኤፍ ሚና ከልክ ያለፈ ነው ብዬ ነው የማየው። እንደ አገሩ ጥንካሬ ነው የሚለካው። አንተ በራስህ ቅድሚያ የምትሰጠውን የምትለይና ያንን ጥርት አድርገህ መያዝ የምትችል፣ ያንንም ደግሞ ለመከላከል የሚያስችል በቂ አቅምና ዝግጅት ካለህ፣ ግፊቱ በጣም አናሳ ነው። የውስጥ ጥንካሬህ ነው የሚወስነው ማለት ነው።
በእኛ በኩል ለምሳሌ፣ ኢኮኖሚያችንን በአግባቡ ዘርዝረን ማየት በመቻላችንና ለዚህ ኢኮኖሚ ይረዳል ያልነውን የፖሊሲ ሐሳብ አድምቀን ማውጣት በመቻላችን፣ በማንኛውም ሁኔታ የምንከላከልለት ነው የሚሆነው። ከዚህ የተለየ ነገር ከየትኛውም አካልና ተቋም አንቀበልም ማለት ነው።

እውነት ነው! እነዚህ ተቋማትም ተሳትፎ እያደረጉ መጥተዋል። ይህን ችላ እያልኩኝ አይደለም። ለምሳሌ አይ ኤም ኤፍ ለኮሮና የሰጠው ምላሽ አስገራሚ ነው። ፍጥነቱም፣ ከተቋሙ የምትጠብቀው አይደለም። ገንዘብ ሰጡ፣ ስለ ኢኮኖሚ እድገት አነሱ፣ ይህ ምንአልባት የአመራር ለውጥን ተከትሎ የመጣም ሊሆን ይችላል። ግን በእኛ አውድ በተግባር ያየነው ነገር፣ ቅድሚያ ልትሰጠው የሚገባውን ነገር ካወቅህና እሱን መጠበቅ ከቻልክ፣ ሁሉም ከዛ ጀርባ የሚመጣ ነው።

የዘርፉ ምሁራን ኢትዮጵያ ተለዋዋጭ የሆነ የውጪ ምንዛሬን መቀበሏ እንደ አይኤምኤፍ ላሉ ዓለማቀፍ ተቋማት እጅ እንደሰጠች ይቆጠራል የሚል እምነት አላቸው። ይህን እንዴት ያዩታል?
በእኛ አውድ ኢኮኖሚው በቀጣይነት ማደግ መቻል አለበት። ኢኮኖሚው በቀጣይት እንዲድግ ደግሞ የነበሩበት ችግሮች መፈታት አለባቸው። አንዱና ዋናው ችግር የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባት ነው። እሱን ማስተካከል አለበት። በዚህ ላይ ማንም ሐሳብ ሰጠበት ወይም አልሰጠም አይደለም ጉዳዩ፣ ምክንያቱም እዚህ ያለውን የማክሮ ኢኮኖሚክ ሚዛን ካላስተካከልክ፣ የፋይናንስና የኢኮኖሚ ቀውስ የሚያመጣው ነገር ነው።

ሌላው እኛ ስለቀጣይ ዘላቂ ልማትና እንዴት አዳዲስ የእድገት ምንጭ እንለይ የሚለውን ነው የምናወራው። ይህ የአይኤምኤፍ ቋንቋ አይደለም። የእድገት ምንጩ አንድ ዘርፍ ላይ የተንጠለጠለ ነበር፣ አሁን ስለ ዲጆታል ኢኮኖሚ እናውራ፣ ቱሪዝማችንን በአዲስ መንገድ እንየው፣ ግብራችንን አልነካነውምና የበለጠ ምርታማ እንሁን እያልን ነው።

ለምሳሌ ጎጃም ላይ የምግብ ዘይት ፋብሪካ በቅርብ ወራት ውስጥ ይመረቃል። ከኢትዮጵያ የፍላጎት መጠን በላይ የሆነና ለውጪ ገበያ የሚቀርብ የዘይት ምርት እየመጣ ነው። በዚህ የገቢ ምርትን ስለመተካትና አዳዲስ የእድገት ምንጭ ነው የምናነሳው። እንዳልኩት እነዚህ በምንም መለኪያ የአይኤምኤፍ ቋንቋ አይደሉም፣ አልነበሩምም።

ግን ይህን ሁለገብ ለውጥና ማሻሻያ መደገፍ እንዲችሉ ማድረግ ከቻልክ፣ ያ የፖሊሲህ ጥንካሬ መገለጫ ነው ብዬ ነው የማስበው። የአይኤምኤፍ ተለዋዋጭ ምንዛሬ የሚባለውን አያስፈልገንም እያልን ነው። በአንዴ የሚደረግ ዲቫሉዌሽን በኢትዮጵያ አውድ አያስፈልግም እያልን ነው። ይህም የሚሳየው የተቋሙን የፖሊሲ ሐሳብ አልቀበልም የሚል አመራር እንዳለ ነው።

በኢኮኖሚ ውስጥ ያለው መዛባት፣ የውጪ ምንዛሬ እጥረቱን ጨምሮ ግን መፈታት አለበት። ይህ መዛባት ደሃውን እንዴት እየጎዳ እንዳለ ማንም ሰው የሚረዳው ነው። ይህን ማስተካከል ግዴታ ነው። ይህ ግን በእኛ በራሳችን መንገድ የሚሆን ነው። ምርታማነት ላይ አተኩረን፣ የውጪ ገበያውን ጨምረን፣ ለውጡ ሁሉንም አካታች ነው መሆን ያለበት።

የኢኮኖሚን መሠረታውያን እያነበብን ነው መመለስ ያለብን እንጂ ግልብ መሆን የለበትም ነው። ይህን አካሄድ እንደ ጠንካራና ከውስጥ የወጣ አገር በቀል አቅም አድርጎ ማየት ያልቻለ ሰው፣ የኢኮኖሚን መሠረታውያን አላነበበም ማለት ነው። የምነግህ ይህ ስሜት የሚሰጥና የተጠና አካሄድ ነው። አንድ ሰው ያመኛል ሲል ሐኪሙ በደንብ ውስጥህን ማየት አለበት። እንጂ ኩላሊቴን ያመኛል ስትል፣ ኩላሊትህን አድናለሁ ብሎ ሌላውን ሊያሳምምህ አይገባም። እናም አጠቃላይና አካታች መሆን አለበት።

እዚህ ላይ ግን አይኤምኤፍ ለኢትዮጵያ ለሦስት ዓመት የሚቆይ ሦስት ቢሊዮን ዶላር ሰጥቷል። ይህም ኢትዮጵያ ተለወዋጭ የውጭ ምንዛሬን የምትተገብር ከሆነ ነው። ይህ የተለዋዋጭ የውጪ ምንዛሬ በተሰጠው የጊዜ ገደብ ተግባራዊ መደረግ የለበትም?
እንደዛ አይደለም። አገር በቀል ኢኮኖሚውንና ያንን በገንዘብ ለመደገፍ የሚደረገውን ጥረት ቀላቅለኸዋል። አጠቃላይ ማሻሻያዎችን ስናደርግ፣ መዋቅራዊና ዘርፍ ተኮር ማሻሻያዎችን አካታች በሆነ መንገድ ነው ሠራን። እነዚህ ማሻሻያዎች ደግሞ የገንዘብ ድጋፍ ያስፈልጋቸው ነበር። ያንን ስናደርግ ከውስጥ ምን ያህል እናገኛለን፣ ከውጪስ ምን ያህል እናገኛለን ብለን በኹለቱም በኩል ቅስቀሳ አደረግን። የሚያስፈልገው 10 ቢሊዮን ዶላር ነው፣ እናም ይህን ማሻሻያ ደግፉ ብለን ጠየቅን።

እናም አጋሮች መልስ መስጠት ጀመሩ። በዛም 10 ቢሊዮን ዶላሩን ማግኘት ቻልን። ያነሳኸው ሦስት ቢሊዮን ዶላር ከአይኤምኤፍ የተገኘው የዚህ አካል ነው። ማሻሻያውን ለማድረግ የሚስችለንን ሙሉ የገንዘብ አቅም ማሰባሰብ ችለናል። ይህን ሥራም በጊዜና በወጪ አጥር ውስጥ ነው የምንሠራው። አጋሮቻችንም ያቀረብነውን ሐሳብ ተቀብለው ለማገዝ ወሰኑ።

ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገዳ ኮቪድ 19 በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ስለሚኖረው ተጽእኖ ባነሱበት ጽሑፍ፣ የብድር አገልግሎት መሻገር አልያም መሰረዝ አለበት ብለዋል። ከዚህ ጋር በተገናኘ ምን ዓይነት ለውጦች አሉ?
የብድር አገልግሎት በተመለከተ ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን አፍሪካን በሙሉ አስተባብረን በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ ውስጥ አበዳሪ አገራት የብድር ስረዛ ድረስ መሄድ አለባቸው የሚል ገፊት መንግሥት እያደረገ ነው። ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፊት ሆነው የአፍሪካ ድምጽም ሆነው እየተናገሩ መሆኑ የሚታወቅ ነው።

ይሄ ከኢትዮጵያ በላይ ለሌሎች የአፍሪካ አገራትም የደኅንነት ስጋትም ስለሚሆን ማለት ነው። ስለዚህ ይህን አጠናክረን እንቀጥላለን። በጣም ጠቃሚ አጀንዳ ነው። ግን ኢትዮጵያ በማንኛውም አስቸጋሪ ጊዜ እዳ የመክፈል ችግር ኖሮባት አያውቅም። አሁን ደግሞ አጠቃላይ የለውጣችን አካል ነው። እንደውም አሁን ላይ በቀጣይ ኹለት ዓመት ውስጥ ከከባድ የብድር ጫና ወጥቶ ወደ መካከለኛ ለመድረስ ነው እየሠራን ያለነው።

ይሄ የንግድ ብድሮችን ላለመውሰድ ከመወሰናችን ጋር የሚገናኝ ነው። ኹለተኛ የውጪ ምርት አቅርቦታችንን በማሳደግ ነው። ስለብድር መመለስ ስታወራ ትልቁ ነገር የውጪ ንግድ ነው። የውጪ ንግድ እንዲሁም ምርታማነት ላይ ማተኮር አለብን።

ግን የእዳ ስረዛ ዛሬ ካልመጣ ኢትዮጵያ የሉዓላዊነት ስጋት አለባት የሚል ነገር በእኛ ሁኔታ የለም። በብዙ መልኩ ይገታናል፣ አቅማችንን በጣም ይፈታተናል፣ ጠቃሚ የሆኑ የምጣኔ ሀብትና ድንገተኛ ጉዳዮች ላይ መዋዕለ ነዋይ ከማፍሰስ ይልቅ፣ እዳ ለመክፈል ማዋል ትክክል አይደለም። ስለዚህ አገራት አስፈላጊ የሆነ የእዳ ስረዛና ቢያንስ የፓሪስ ክለብ እንዳደረገው እስከ ቀጣይ ዓመት ወይም ለዘጠኝ ወራት ክፍያን ማራዘምም አለ። ይህ ግን አሁንም በቂ አይደለም።

ለኮቪድ 19 ወረርሽኝ ከሚሰጡ ምላሾች መካከል አንደኛው ከውጪ የሚገቡ የነበሩ ምርቶችን በአገር ውስጥ ምርት መተካት ነው። አገራትም ይህን መንገድ ሲጠቀሙ ይስተዋላል። በኢትዮጵያም ከዘይት ጀምሮ የመተካት ሥራ እየታየ ነው። ይህ ማለት ፖሊሲውም ከውጪ የሚገባ ምርትን ወደመተካት ይቀየራል ማለት ነው?
አይ! መቀየርም የለበትም፣ አይቀየርምም። አንድ መቀየር ያለበት የተሳሳተ እይታ አለ። ምርትን ወደ ውጪ ልከህ የምታኘው አንድ ዶላራ እና ምርትን ወደ ውስጥ ለማስገባት የምታወጣው አንድ ዶላር እኩል፣ ያው አንድ ዶላር ነው። የእኛ ፖሊሲ ችግር የነበረው የትኞቹ ምርቶች በመተካት እንሥራ፣ የትኞቹን ደግሞ ለውጪ ገበያ ልሥራ የሚል ጥርት ያለ ነገር አልነበረውም። በጣም የተቀላቀለ እቅድ ነው የነበረን። አሁን ነው ያንን ነው ያጠራነው።

ማለትም በምርት ደረጃ፣ በዘርፍ ደረጃ፣ የትኞቹ ዘርፎች ለውጪ ገበያ፣ የትኞቹ የውጪ ምርትን ለመተካት መዘጋጀት አለባቸው የሚለውን መለየት። ያለጥርጥር የውጪ ምርትን በአገር ውስጥ መተካት ትልቅ እቅድ ነው። በኢትዮጵያ ሁኔታ ስንዴ ገቢ ማድረግ በምንም መንገድ አሳማኝ አይደለም፣ በየትኛውም ማስረጃ። ይህን ያህል የሚታስ መሬትና አምራች ሕዝብ እያለህ መቀጠል ያለበት ነገር አይደለም። እንደዛም ሆኖ የውጪ ንግድም ወሳኝ ነው።

እና ኹለቱንም አመጣጥነን ነው የምንሄደው። ይህም የኢንዱስትሪ ፖሊሲያችንን ጠንካራ እንዲሆን ያስችለዋል።

በዚህ መሠረት ታድያ የትኞቹ ዘርፎች ናቸው ለውጪ ንግድ ያስኬዳሉ ተብለው የተለዩት? የትኞቹስ ናቸው ከውጪ ይገባ የነበረን ምርት ለመተካት የተመረጡት?
በግብርና ዘርፍ ፍራፍሬ፣ አበባ፣ እንዲሁም ቡና ለውጪ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶች ናቸው። ነገር ግን ወሳኝ የሆኑ የምግብ ዓይነቶች ዘይትን ጨምሮ፣ እሴት የተጨመረባቸው ምርቶች፣ ለምሳሌ ጁስ ኢትዮጵያ ውስጥ ከውጪ እንዲገባ ማድረግ የለብንም። ትልልቅ የግብርና ማቀነባበሪያ አካባቢዎችን እያዋቀርን ነው ያለነው። ይህ ማለት ግብርናችን እና ኢንዱስትሪው እንዲተሳሰር አድርገን የግብርና ማቀነባበሪያ ላይ እንሠራለን ማለት ነው። እነዚህን በቀላል መተካት የሚቻል ምርቶችን መተካት አለብን።

ግን ለውድድር የሚቀርቡ ዘርፎችም አሉ። ለምሳሌ የቆዳ ዘርፉ ትኩረቱ የውጭ ገበያ መሆን አለበት። ግን አስቀድሞ እንዳልነው ያልተናበበ ፖሊሲ ስለነበረን የቆዳ ኢንዱስትሪውን ገድለነው ነው የቆየነው። ስለዚህ ይህ ዘርፍ አሁን ለውድድርም ተጋላጭ ሆኖ ለውጪ ገበያ እንዲዘጋጅ እናደርገዋለን ማለት ነው።

ሌላው ግብርና ላይ እሴት መጨመር በአግባቡ የተበረታታ አልነበረም። ለምሳሌ ሰሊጥ ከመላክ ይልቅ በምርት ሂደት ያለፈ ነገር ለውጪ ገበያ መላክ ትልቅ ዋጋ አለው። አሁን እሱ ላይ እንሠራለን ማለት ነው። እንዲህ እያልን መዘርዘር እንችላለን። በድምሩ ግን እያደረግን ያለነው ታሪፋችን የዛም ፖሊሲ መጠንከር እንዳለበት የሚያሳይ ነው።

በመንግሥት በኩል ለወረርሽኝ ምላሽ ለመስጠት የተሻለ ቅንጅትና ሀብት ማሰባሰብም ይታያል። ይህ ምንአልባት ለወደፊት የኢትዮጵያ ምጣኔ እንደ መልካም አጋጣሚ፣ ጥሩ ነገር የሚገኝበት ሊሆን ይችላል?
ጥያቄው ኹለት አንጻር አለው። በአንድ በኩል ጦርነት ነው ይሄ የሚል ነው። ከዚህ የከፋ ጦርነት የለም፣ እያየነው ነው። ዜጎችን የሚቀጥፍ፣ በተለያዩ አገራት እንዳየነው የሰው አስክሬን በየመንገድ እንዲጣል ያደረሰ አስከፊ ክስተት ነው። ስለዚህ ጦርነት ነው።

ኹለተኛ ከኅብረተሰብ ጤና ባልተናነሰ ደግሞ ኢኮኖሚ ላይ የሚያመጣው ጉዳት በዛው መጠን ከፍተኛ ነው። በእኛ አንጻር ስናይ፣ በከፍተኛ ችግር ያመጣናቸውን ለውጦች እንዳይሸረሽርብን በጣም መጠንቀቅ አለብን። በዛ መልኩ የጦርነት ውስጥ ያለን ያህል ትብብር ያለው ጠንካራ ሥራ እየተሠራ ነው።

ስለዚህ ጥሩ ነገሩ ምንድን ነው ለሚለው፣ የሰብአዊነት ስሜት ነው። ሁሉም ሰው ሰው መሆኑን እንዲያይ እድል የሰጠ ይመስለኛል። ባለሀብቱም እኔ ቤት በቀን አምስት ጊዜ እየበላሁ፣ ጎረቤቴ አንዱንም ካላገኘ ብሎ እንዲስብ ያደረገ ይመስለኛል። ያ ኅብረትና የመረዳዳት ስሜት ትልቅ ዋጋ የሚሰጠው ነገር ነው።

ሌላው ለአንድ ነገር በጋራ ስንቆም፣ እንዴት ጠንካራ አቅም እንዳለንም ያሳየ ነው። ይህ በጣም ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ነገር ነው የሚሆነው።
በኢትዮጵያ ከለውጡ በኋላ በእርግጥ እንዲህ ያለ ኅብረት ታይቷል። ባለፈው ዓመት ኢትዮጵያውያን ከየቦታው ተነስተው በአንድ ቀን አራት ቢሊዮን ችግኝ የተከሉበትን አጋጣሚ የምትረሳው አይደለም። ያ የማስተባበር አቅምን የሳየ ነው። ይህም ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ነው። እንደ ግለሰብ ለአገር እድገት የጋራ ሥራ ወሳኝ ነው የሚል እምነት አለኝ። አገር ሲተባበርና ያለንን አቅም አሟጠን መጠቀም ስንችል፣ የማንንደው ተራራ የለም ብዬ አስባለሁ።

ቅጽ 2 ቁጥር 86 ሠኔ 20 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here