ኤርሚያስ አመልጋ የኢንቨስትመንት ባንክ እያቋቋሙ ነው

0
1183

የበርካታ የአዳዲስ ንግድ እንቅስቃሴዎችን በመጀመር የሚታወቁት ኤርሚያስ አመልጋ በኢትዮጵያ በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነ የኢንቨስትመንት ባንክ ለመጀመር በሂደት ላይ መሆናቸውን አስታወቁ።
ኤርሚያስ በአይነቱ ልዩ የሆነውን ባንክ ለመመስረት የተሠሩ ሥራዎች መኖራቸውን ለአዲስ ማለዳ ጠቅሰው፣ ይህም በቅርቡ አዲስ የንግድ እንቅስቃሴን ይዞ ብቅ እንደሚልም ተናግረዋል። አያይዘውም ኢንቨስትመንት ባንኩን ሥራ እምብዛም ባይገፉበትም በቅርቡ ግን ተጠናክሮ እንደሚቀጥል እና ለሕዝብ ይፋ እንደሚሆን ገልጸዋል።

ከኢንቨስትመንት ባንኩም በተጨማሪ በርካታ የንግድ ዘርፎች ላይ በስፋት ለመሰማራት በሂደት ላይ መሆናቸውን ለአዲስ ማለዳ የተናገሩት ኤርሚያስ፣ በቅርቡም ‹ኤርሚያስ አመልጋ› የሚል ትልቅ ድረ ገጽ በመጀመር ወደ ሕዝቡ እንደሚደርሱና በተለይም የተለያዩ የንግድ ሐሳቦችን እና ተጨማሪ ሐሳቦችን በድረ ገጹ ላይ እንደሚገልጹም አስታውቀዋል።

ኢንቨስትመንት ባንክ የንግድ ተቋማትን እና ገንዘብ ይዘው በምን የንግድ ዘርፍ እንደሚሰማሩ የጠራ ሐሳብ የሌላቸውን አካላት አቀራርቦ በማገናኘት የተሻለ የንግድ ግንኙነት እንዲሁም ኹለቱንም አካላት በጥቅም ማስተሳሰር አንደኛው ሥራው እንደሆነ የሚታወቅ ነው። ከዚህም በተጨማሪ የንግድ ተቋማትን ያሉበትን ደረጃ በማየትም የማማከር እና ሌሎች አማራጮችንም እንዲከተሉ የሚመክር እንደሆነም ይታወቃል።

በኢትዮጵያ በአይነቱ ልዩ የሆነው ይኸው ኢንቨስትመንት ባንክ በቅርቡ በይፋ ሥራውን እንደሚጀምር እና ከፍተኛ የሆነ ለውጥም በንግድ እንቅስቃሴው ላይ እንደሚፈጥር የሐሳቡ ባለቤት እና የባንኩ መሥራች ኤርሚያስ አመልጋ ጠቁመዋል። ኢንቨስትመንት ባንክ በተለያዩ ንግድ ዘርፎች ለሚሰማሩ የንግዱ ማኅበረሰብ፣ በዘርፉ የሠለጠኑ እና ጥልቅ እውቀት ያላቸውን ሰዎችን በማሳተፍ ለተገልጋዮች ነባራዊውን የአገርም ሆነ የዓለም ዐቀፍ የንግድ እንቅስቃሴን ታሳቢ እያደረጉ ሰፊ ምክር በመስጠት፣ የንግድ እንቅስቃሴውን በማየት ወደ ፊት ከመሔዳቸው አስቀድሞ ሌላ አማራጮችን እንዲወስዱም ምክር እንደሚለግስ እና ካፒታል የመፍጠር ሥራም እንደሚሠራ ለማወቅ ተችሏል።
የኢንቨስትመንት ባንክ ለትርፍ የሚሠራ እና ትርፍን መሰረት አድርጎ የሚቋቋም ባንክ ነው።

ከኢንቨስትመንት ባንክ በተጨማሪም ኤርሚያስ አመልጋ በሰቆጣ የብረት ማዕድን ለማውጣት እና መቀመጫውን ቻይና ካደረገው ግዙፉ የበይነ መረብ የግብይት ስርዓት አሊባባ ጋርም በጋራ ትልቅ የንግድ ስምምነት ለመፈጸም በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ምንጮች ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ኤርሚያስ አመልጋ በባንክ ኢንዱስትሪው ዘርፍ የዘመን ባንክ መሥራች ባለአክሲዮን እና የቦርድ ሊቀመንበር የነበሩ ሲሆን፣ ከዓመታት በፊትም በተለያዩ ምክንያቶች ከባንክ ኢንዱስትሪው ለአምስት ዓመታት እንዲታገዱ በብሔራዊ ባንክ በኩል ውሳኔ ታላልፎባቸው እንደነበር የሚታወስ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ከአክሰስ ሪል እስቴት ጋር በተገናኘ በማረሚያ ቤት ውለው ነበር። ከእስር በመፈታት ከዓመት ተኩል በፊትም በድጋሚ ከኢምፔሪያል ሆቴል ሽያጭ እና ከሜቴክ ጉዳይ ጋር በተገናኘ ለእስር ተዳርገው እንደነበርም አይዘነጋም።

ቅጽ 2 ቁጥር 86 ሠኔ 20 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here