ባለሥልጣኑ ከሰባት ሚሊዮን ብር በላይ ካሳ ሰበሰበ

0
952

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መንገዶች ባለሥልጣን በሚያስተዳድራቸው የመንገድ መሰረተ ልማቶች ላይ በተከሰተ 331 የተሽከርካሪ አደጋዎች ሳቢያ ለደረሰው ጉዳት ከሰባት ሚሊዮን ብር በላይ ካሳ መሰብሰቡን አስታወቀ። ባለሥልጣኑ ከ100 በላይ የመንገድ ግንባታ እና ተያያዥ ፕሮጀክቶች እያከናወነ እንደሚገኝም ተጠቁሟል።
የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ኢያሱ ሰለሞን እንደገለጹት፣ በ11 ወራት ውስጥ ባለሥልጣኑ በሚያስተዳድራቸው የመንገድ መሰረተ ልማቶች ላይ በጥቅሉ 331 የተሽከርካሪ አደጋዎች ተከስቷል። በአደጋው ሳቢያም በመንገድ መሰረተ ልማቱ ላይ በደረሰው ውድመት 7 ሚሊዮን 771 ሺሕ 206 ብር ካሳ ጉዳቱን ካደረሰው አካል መሰብሰቡን ተናግረዋል።
የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክትር እንዳብራሩት ባለሥልጣኑ በአምስት ሪጅኖች የተከፈለ የመንገድ ሀብት አስተዳደር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ያሉት ሲሆን፣ በግንቦት ወር ብቻ እነዚህ ጽሕፈት ቤቶች በሚያስተዳድሯቸው የመንገድ መሰረተ ልማቶች እና ሀብቶች ላይ አምስት በቀለበት እና 16 ከቀለበት መንገድ ውጪ ባሉ በጥቅሉ በ21 የተሽከርካሪ አደጋዎች ደርሰዋል።
በቀለበት መንገድ ላይ በደረሱ አደጋዎች 414 ሺሕ 753 ብርና ከቀለበት ውጪ ባሉ መንገዶች ላይ በደረሱ አደጋዎች 75 ሺሕ 365 ብር በድምሩ 490 ሺሕ 118 ብር የሚገመት ውድመት በአንድ ወር ውስጥ የደረሰ ሲሆን፣ በዚህ ጊዜ በመንገድ መሰረተ ልማቶች ላይ ለደረሰው ውድመት ከአንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር በላይ ካሳ እንዲሰበሰብ ለሕግ ክፍል ትዕዛዝ ተላልፎ፤ ጉዳት ያደረሱ ግለሰቦች ላይ ክትትል ተላልፎ እየተደረገባቸው እንደሚገኝ ጨምረው ተናግረዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 87 ሠኔ 27 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here