የሰላም ሚኒስቴር በአደጋ ጊዜ ቅድመ ማስጠንቀቂያ የሚሰጥ አንቂ ሰርዓት አበለጸገ

0
288

የኢትዮጵያ የሰላም ሚኒስቴር ኢትዮ አለርት ሲስተም የተባለ በአደጋ ጊዜ ቀድሞ የማንቂያ መልዕክት ለኅብረተሰቡ ማድረስ የሚያስችል ስርዓት ማበልጸጉን አስታወቀ። ስርዓቱ የሰላም ሚኒስቴር ለሚያከናውናቸው የሰላም ሥራዎች ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው የሰላም ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ከሚል ተናግረዋል።
ኢትዮ አለርት ሲስተም አደጋ ከመከሰቱ በፊትና አደጋ ከተከሰተ በኋላ በኅብረተሰቡ እና በሚያስተዳድረው ተቋም መካከል የኹለትዮሽ መልዕክት ማድረስ የሚችል ነው ተብሎለታል። የማንቂያ ስርዓቱን በማንኛውም አይነት ሞባይል መጠቀም የሚቻል ሲሆን፣ ስርዓቱ ለኅብረተሰቡ የሚደርሰውን መልዕክት ግለሰቡ በሚችለው ቋንቋ በድምፅና በጽሑፍ ማድረስ እንደሚችል ሰላም ሚኒስትሯ ገልጸዋል።
ኢትዮ አለርት ሲስተም የቋንቋ ችግር እንደሌለበትና ኢትዮጵያ ውስጥ በሚነገሩ በሁሉም ቋንቋዎች መልዕክቱን ማድረስ መቻሉ እና ለተማረውም ላልተማረውም ኅብረተሰብ በሚፈልገው መልኩ መቀበል ማስቻሉ ለትግበራ የበለጠ ጉልህ ሚና እንዳለው ሚኒስቴሯ አክለው ተናግረዋል።
ስርአቱ ዘመናዊና ስማርት ስልክ አለመፈለጉና በማንኛውም ሞባይል መተግበር የሚቻል ከመሆኑ ባሻገር እንደ ሌሎች የመረጃ መለዋወጫ ስርዓቶች የበይነ መረብ አገልግሎት የማይጠይቅ መሆኑ ተመላክቷል። ይህም ማንኛውንም ሰው በማንኛውም ቦታና ጊዜ መረጃ መቀበልና መላክ ያስችላል።
የቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃ ማሰራጫ ስርዐቱ በአገሪቱ የሚከሰቱ አደጋዎችንና ጥቃቶችን ከመከሰታቸው ቀድሞ ለኅብረተሰቡ በማድረስ የኅብረተሰቡን ለአደጋ ተጋላጭነት ይቀንሳል ተብሎ ይጠበቃል።

ቅጽ 2 ቁጥር 89 ሐምሌ 11 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here