የሞተር ተሽከርካሪዎች ላይ እስከ መውረስ የሚደርስ እርምጃ ሊወሰድ ነው

0
1007

ከክልሎች ወደ አዲስ አበባ የሚገቡ የሞተር ሳይክሎችን ጨምሮ በአዲስ አበባ በሚንቀሳቀሱትም ላይ ከትራንስፖርት ባለሥልጣን ፈቃድ ያልተሰጠው ከሆነ መንቀሳቀስ እንደማይቻል እና ቅጣቱም እስከ መውረስ የሚደርስ እንደሚሆን ተገለፀ።

አዲስ አበባ ትራስፖርት ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ ኮማንደር አህመድ መሐመድ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ እርምጃው ደንብ በመተላለፍ ተብሎ ቅጣቱ በገንዘብ እንደሚጣልባቸው እና በወንጀልም ይጠየቃሉ።

ሕጉን በማያከብሩት ላይ እርምጃ መውሰድ ያስፈለገበት ዋና ምክንያትም ባለፉት ኹለት ዓመታት ከተፈጸሙ ወንጀሎች ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዙት በሞተር ሳይክል የተከናወኑ ዝርፊያዎች መሆናቸው እንደሆነ አንስተዋል።

ለከፍተኛ ወንጀል መበራከት እና አጠቃላይ መንጠቅን ጨምሮ እስከ ውንበድና ድረስ የሚፈፀሙ ወንጀሎች በባለ ኹለት እግር ተሽከርካሪዎች እንደሆነ መታወቁን የባለሥልጣኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። የተደራጀ የወንጀል ዝርፊያ የመኖርያ ቤት እና ተቋማትን ሰብሮ በመግባት ዘርፎ በሞተር ሳይክል የማምለጥ ጉዳዮች በስፋት ታይተዋል ሲሉ አስታውቀዋል።

በተደጋጋሚ የትራፊክ ፖሊሶችም እርምጃ እየወሰዱ ቢሆንም ነገሩ ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከአቅም በላይ እየሆነ እንደመጣ እና እንዳስቸገራቸው ዋና ስራ አስኪያጁ ጨምረው አስረድተዋል።

ከዚህ በፊት ፈቃድ የተሰጣቸው በአግባቡ እየተንቀሳቀሱ ቢሆንም ነገር ግን አሁን በብዛት ከፍቃድ ውጪ ሆነው ከተለያዩ ክልሎች እየመጡ እንደሚንቀሳቀሱ መስተዋሉን እና እርምጃ እየተወሰደባቸው መሆኑን አሕመድ ተናግረዋል። በዋናነት ቅድመ ጥንቃቄ ላይ ነው የምንሠራው ያሉት ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ ነገር ግን ቁጥጥር ማድረጉ ላይም ከፍተኛ ሥራ እንደሚሠራም ተናግረዋል።

ከዛም በተጨማሪ በከተማው የሌሎች ተሽከርካሪዎችን የትራፊክ እንቅስቃሴ እያወከ መሆኑ እና መንገድ መዘጋጋት በሚኖርበት ሰዓትም ቢሆን በእግረኛ መንገድ ላይ በመግባት በእግረኞች ላይ አደጋ የማድረስ እና የእግረኛ እንቅስቃሴን የማወክ ሁኔታ መስተዋሉን ጠቅሰዋል።

ይሄም በፀጥታ ኃይሎችም ጭምር የተገመገመ እንደሆነ በንግግራቸው ያመላከቱ ሲሆን ለቁጥጥርም አስቸጋሪ በመሆን ፈታኝ እየሆነ ስለመሆኑም አያይዘው ተናግረዋል።
ዝርፊያን ጨምሮ ሌሎች ወንጀሎችን ከመሥራት በላይ ደግሞ ከሚስተዋሉ ችግሮች መካከል የሞተር ሳይክሎች አደጋ ከፍተኛውን ቁጥር ማለትም ከጠቅላላው አደጋ 20 በመቶ የሚሆነውን እንደሚይዝ ተገልጿል።

ይህም የሆነበት ምክንያት ሞተር ሳይክሎች አሽከርካሪውንም ሆነ ሌሎች አሳፍረዋቸው የሚሄዱ ሰዎችን የሚጠብቁበት የጭንቅላት መከላከያ (ሄልሜት) ስለሌላቸው የአደጋው መጠን ከፍ ሊል እንደሚችል ተጠቅሷል። በተለይም በሕገ-ወጥ መንገድ ላይ እየተደበቁ የሚሄዱና ተገቢው የአሽከርካሪነት ፈቃድ ሳይሰጣቸው የሚያሽከረክሩ፣ ተሽከርካሪም ስለሆነ ለትራፊክ አደጋ መበራከት ዋነኛው እና ትልቁ ምክንያት ይሆናል ተብሏል።

ባለፈው 2011 ሞተር ሳይክሎችን በተመለከተ መመርያ ቁጥር ኹለት እና መመርያ ቁጥር አራት ወጥተዋል። የመጀመርያው መመርያ ቁጥር የወጣው አጠቃላይ አዲስ አበባ ከተማ ላይ ሞተር ማንቀሳቀስ የሚከለክል ሲሆን፤ ኹለተኛው ደግሞ ተሻሽሎ በመመርያ ቁጥር አራት ፍቃድ የተሰጣቸው እና ጂፒኤስ ተገጥሞ የራሱ የሆነ ስርዓት ተዘርግቶለት እንዲሁም መለየት እንዲያስችል አንድ ዓይነት አልባሳት እንዲለበሱ ሆኖ እንዲንቀሳቀሱ ተፈቅዷል።

ነገር ግን ከዛ ውጪ የሆኑት ፈቃድ እንደማይወስዱ እና እንደማይካተቱ፣ ተጠያቂም እንዲሆኑ እየተደረጉ ነው። በዚህ መካከል ግን አሁን አሁን ከተለያዩ ክልሎች ወደ አዲስ አበባ እየመጡ ተቀላቅለው እየተንቀሳቀሱ መሆኑ፣ እንዲሁም ወደ ቀድሞው ስርአት የመመለስ ሁኔታ መስተዋሉ ነው የተገለፀው።

ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ አዲስ ማለዳ ምን ያህል የሞተር ሳይክል አሽከርከሪዎች በወንጀል ተይዘዋል የሚለውን በሚመለከት የአዲስ አበባ ትራፊክ ባለሥልጣንን ለማናገር ብትሞክርም ሳይሳካላት ቀርቷል

ቅጽ 2 ቁጥር 90 ሐምሌ 18 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here