የግል ድርጅቶች የክፍያ ማሽኖችን ማስተዳደር የሚችሉበት መመሪያ ወጣ

0
846

ብሔራዊ ባንክ በባንክ የደንበኞች ገንዘብ መክፈያ ስርዓት የሆኑት ኤትኤም፣ ፖስ ማሽን እና ብሔራዊ የመቀየሪያ ስርዓት (National switch system) የግል ድርጅቶች መሥራትና ማስተዳደር እንዲችሉ የሚፈቅድ አዲስ መመሪያ ማውጣቱን አስወቀ፡፡

ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጀው አዲስ የደንበኞች ገንዘብ የክፍያ ስርዓት መመሪያ፣ ከዚህ በፊት ለባንኮች እና ለማይክሮ ፋይናንሶች ብቻ የተፈቀደ የነበረውን የኤቲኤም እና ፖስ ማሽን ገንዘብ ክፍያ እንዲሁም የሒሳብ ማጣሪያ ሥራዎችን የግል ድርጅቶች መሥራት እንዲችሉ የሚፈቅድ ነው። በቅርቡ ጸድቆ ሥራ ላይ ይውላል ተብሎ የሚጠበቀው ይህ መመሪያ፣ በሽርክና በሚቋቋሙ (Share Company) የግል ድርጅቶች የኤቲኤም እና የፖስ ማሽን የገንዘብ መክፈያ ስርዓቶችን በማንኛውም ቦታ በመክፈት መሥራትና ማስተዳደር የሚችሉበትን እድል የሚፈቅድ መሆኑን ባንኩ ገልጿል፡፡

ባንኩ ያወጣው አዲስ መመሪያ ‹የክፍያ ስርዓት መመሪያ› (Payment system directive) በሚል የተዘጋጀ ነው። ሦስት የገንዘብ መክፈያ ስርዓቶችን በመዘርጋት የግሉ ዘርፍ መሥራት እንዲችል ፈቃድ የተሰጠባቸው ኤትኤም፣ ፖስ ማሽን እና የአንድ ባንክ ኤትኤም ካርድ በሌላ ባንክ ኤቴኤም ላይ እንዲሠራ የማናበብና የሒሳብ ማጣራት ሥራ የሚሠራው ማሽን (National switch system) በመሆኑ ታውቋል፡፡ በጥቅሉ ለግሉ ዘርፍ የተፈቀዱ የክፍያ ስርዓቶች በባንኩ አጠራር (ATM, POS, SWITCH Operator/ Three Operators) ተብለው እንደሚጠሩም ለማወቅ ተችሏል፡፡

ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ምንጮች ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት ብሔራዊ ባንክ የገንዘብ መክፈያ ስርዓቶች በመዘርጋትና በማስተዳደር የግል ድርጅቶች ተሰማርተው መሥራት የሚያስችላቸውን መመሪያ የፈቀደበት ምክንያት አለው። ከምክንያቶቹም ዋናዎቹ የአገልግሎት ተደራሽነትን ማሳደግ፣ የአገልግሎት አሰጣጥ ቅልጥፍናን መጨመር፣ የግሉን ዘርፍ ማሳተፍና ማገዝ እንዲሁም በብቃት የተመዘነ ውድድር እንዲኖር ማድረግ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

ከዚህ በፊት የነበረው የኤቲኤምና የፖስ ማሽን የገንዘብ ክፍያ ስርዓት በባንኮች ብቻ የሚተዳደር በመሆኑ እና ሌላ ተወዳዳሪ ባለመኖሩ ምክንያት ደንበኞች አገልግሎቱን በማንኛውም ቦታ ማግኘት እንዳይችሉ ማድረጉን የብሔራዊ ባንክ ምንጮች ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም አዲስ የወጣው መመሪያ ደንበኞች በማንኛውም ቦታ አገልግሎቱን ማግኘት የሚችሉበትን እድል እንደሚጨምረው እና ባንኮችም ተወዳዳሪ በመሆን የተቀላጠፈ አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያስችል እንደሚሆን ተጠቅሷል፡፡

መመሪያው በሚፈቅደው መሰረት በጋራ ተመስርተው ወደ ሥራው የሚገቡ ድርጅቶች ከባንኮች ጋር የሚኖራቸው ትስስር የሚከፍሉትን ገንዘብ ከባንኮች የማግኘት መሆኑን ባንኩ አመላክቷል፡፡ የግል ድርጅቶቹ ባንኮች ባልደረሱበት ቦታ ተገልጋዮች በሚፈለጉት መጠን በተለይም በገጠራማ ከተሞች ኤቲኤም ማሽኖችን ተክለው የመቆጣጠርና የማስተዳደር ሥራው የግላቸው ነው ተብሏል፡፡ የግል ድርጅቶቹ በሚያስተዳድሯቸው የገንዘብ ክፍያ ስርዓቶች ላይ ለሚደርሰው ጉዳት ተጠያቂነቱን የሚወስዱት ራሳቸው የግል ድርጅቶቹ መሆናቸውም በመመሪያው ላይ ተጠቁሟል፡፡

አዲስ የተዘጋጀው መመሪያ የተፈቀደው ለአገር ውስጥ የግል ድርጅቶች ብቻ ሲሆን፣ ለጊዜው ለውጭ ድርጅቶች አለመፈቀዱን አዲስ ማለዳ ከባንኩ ባገኘችው መረጃ አረጋግጣለች፡፡

መመሪያው ባንኮች ከዚህ በፊት ለደንበኞቻቸው አገልግሎት ሲሰጡባቸው የነበሩ የኤቲኤም እና ፖስ ማሽኖችን እስከ አሁን የነበራቸውን የማስተዳደርና የባለቤትነት ኃላፊነትን የሚፈቅድ መሆኑም ባንኩ ለአዲስ ማለዳ ጠቁሟል፡፡

የኢትዮጵያ ባንኮች ማኅበር በበኩሉ ስለ አዲሱ ክፍያ ስርዓት መመሪያ መረጃ እንደሌለው እና በጉዳዩ ላይ አስተያየት መስጠት እንደማይችል ለአዲስ ማለዳ ገልጿል፡፡

ቅጽ 2 ቁጥር 90 ሐምሌ 18 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here