ግብረ ሰዶማውያንን ከሚቃወሙ 10 አገራት መካከል ኢትዮጵያ የለችም

0
2143

ወደኪስ የሚገባ ትርፍ አልያም የብዙኀንን አድናቆት፣ እውቅናና ጭብጨባ ለማግኘት ሳይሆን፣ ስለአገር በማሰብና በመጨነቅ ለትውልድም በመሳሳት እድሜ፣ ጊዜና ጉልበት እንዲሁም እውቀታቸውን የሚሰጡ ሰዎች ብዙ ናቸው ለማለት አያስደፍርም። እርሳቸው ታድያ ከጥቂቶቹ መካከል ይመደባሉ፣ መምህር ደረጀ ነጋሽ (ዘወይንዬ)።

ላለፉት 25 ዓመታት የ‹ወይንዬ አቡነ ተክለሃይማኖት ማኅበር› ሰብሳቢ፣ የወይንዬ የጉዞ ወኪል ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ፣ በበርካታ ኮሚቴዎች ውስጥ በኃላፊነት ሲያገለግሉ፣ የገዳማትን ታሪክ በምስል አስደግፎ በማቅረብ ጥቂት የማይባሉ ቪሲዲዎችን ሠርተው ለዕይታ አቅርበዋል። በተለያዩ ገዳማት በመንቀሳቀስ 32 ዓመታትን አስቆጥረዋል። በአሐዱ ራድዮን ቅዳሜ ምሽት ላይም ከጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ ጋር ገዳማትን በምናብ የሚያስጎበኙበት ሳምንታዊ መሰናዶ አላቸው።

‹‹ለራሴና ለቤተሰቤ አልኖርኩም። ለቤተክርስትያን እና ለአገሬ ኖሬአለሁ።› የሚሉት ደረጀ፣ በ2012 መጀመሪያ ‹ስለኢትዮጵያ ዝም አንልም ትውልድን ከግብረ ሰዶም እንታደግ› ማኅበርን ከመመሥረታቸው አስቀድሞ፣ ላለፉት 12 ዓመታት በግላቸው በኢትዮጵያ ያለውን የግብረ ሰዶም እንቅስቃሴ በመታገል፣ ሊደርሱ ያሉ ጥፋቶችን በማጋለጥና በመሞገት ቆይተዋል። ‹ዝም ማለት ጉዳት የሚያመጣ ከሆነ፣ እየተጎዱም ቢሆን መሥራት እመርጣለሁ። ነገ ለውጥ እንደሚያመጣ አምናለሁ› ይላሉ።

መምህር ደረጀ ነጋሽ (ዘወይንዬ) የግብረ ሰዶምን እንቅስቃሴ ለመታገል ማኅበሩ ስለሚያደርገው እንቅስቃሴ፣ በኢትዮጵያም ስላለው ሁኔታና መሰል ጉዳዮችን በማንሳት ከአዲስ ማለዳዋ ሊድያ ተስፋዬ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርገዋል።

መምህር ደረጄ በኢትዮጵያ ግብረ ሰዶም እንዳይስፋፋና ሰዎች እንዲነቁ ለማድረግ እንቅስቃሴ የጀመሩበት ጊዜ ጉዳዩ ብዙም የማይነሳበትና ትኩረት ያልተሰጠበት ወቅት ነው። መነሻ የሆነዎት ምክንያት ምን ነበር?
መጀመሪያ የገዳማት ታሪክ ላይ ነበር የምሠራው። ለዚሁ ሥራ ወደተለያዩ አብያተ ክርስትያናትና ክፍለ አገራት ስሄድ ሰዎች እየተደፈሩ ነው ብለው መጥተው ይነግሩኛል። እናም ይህ ነገር እንዴት ነው ብዬ ጥናት ጀመርኩኝ። ይህ የሆነው ከ12 ዓመት በፊት ነው።

ድርጊቱም በጣም ስር እየሰደደ መጣ። እና ለኢትዮጵያ ዝም ማለት የለብኝም፣ የእኔ ዝም አለማለት የሕዝቡም ዝም አለማለት ነው ብዬ ‹ለኢትዮጵያ ዝም አንልም› ስል ራሴ ባወጣሁት ርዕስ ቪሲዲ ሠራሁ። ይህም የመጀመሪያው በ2003 የተሠራ ሲሆን፣ የግብረ ሰዶምን አስከፊነት የሚያሳይ ነው። ዮሴፍ የማነብርሃን የሚባል በዛ ሕይወት ከኖረ ኤርትራዊ ስ

ደተኛ ጋር ነው የሠራነው።

በዛም ግብረሰዶምን እያስፋፉ እንዳለ፣ የሃይማኖት ተቋማትና መንግሥት ትኩረት እንዲሰጥበት ብዬ ቀረብኩኝ።

ከዛ ሦስት ዓመትና ሦስት መቶ ሺሕ ብር የፈጀ፣ በኢትዮጵያ ከሰባት እስከ 32 ዓመት በዛ ሕይወት ውስጥ የቆዩ ሰዎችን በማነጋገር፣ አኳኋናቸውን በመቅረጽ በመጽሐፍ የሚወራውና እውነታው ነው ወይ የሚለውን ለማሳየት ያንን አደረግን።

በጊዜው የወንድ ሕጻናት ጥቃት 22 በመቶ ደርሶ ነበር፣ 2005። 28 ጋዜጠኞች ባሉበት ሠኔ 23 ቀን 2005 ላይ ‹ለኢትዮጵያ ዝም አንልም› የሚለው ቪሲዲ ወጣ።

አንድ ሰው 34 ሕጻናትን እንዳጠቃ፣ በኤን.ጂ.ኦ. 300 ሕጻናትን አሳድጋለሁ ብሎ 50 ሕጻናት ላይ ግብረ ሰዶም እንደፈጸመባቸው የሚሳይ ነው። ይህን ሁሉ ለሕዝብ ይፋ አደረግን። ያኔ በርካታ ግብረ ሰዶማውያን ከዛ ሕይወት ውስጥ ወጡ። አውሮፓ የተሰባሰቡም በሙሉ መውጣት ጀመሩ። አገር ውስጥም እንደዛው።

እንቅስቃሴው ቀጠለ። በማኅበረ ወይንዬ ሰላማዊ ሰልፍ ለማዘጋጀት ከአዲስ አበባ ወጣቶች ፎረም ጋር ተነጋግረን ፈቃድ ከተሰጠ በኋላ ተከለከልን። ቀጥሎ ያሰብኩት ወይንዬ አቡነ ተክለሃይማኖት ማኅበር ሃይማኖታዊ ተቋም ነው፣ ስለዚህ አገራዊ ተቋም ያስፈልጋል። በዚህም ሃይማኖት፣ ብሔርና ፖለቲካ ሳይለየው ወደ እንቅስቃሴ መግባት አለባቸው በሚል አጠናሁና፣ ይህን ጳጉሜ 3/2011 ላይ አዲስ አበባ አቀረብኩኝ።

ይህም አስከፊነቱን፣ በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ፣ የጤና በኩል ጠንቅነቱን፣ ለሴቶች የማሕጸን ካንሰርና የጎሮሮ ጨብጥና ቂጥኝ የመሰሉ ጉዳቶችን ያመጣል። ስንት ሰው ነው የጎሮሮ ጨብጥና ቂጥኝ እንዳለ የሚያውቀው። ይህም በአፍ በሚፈጸም ግንኙነት (ኦራል ሴክስ) የሚመጣ ነው። እነዚህን ጉዳቶችና በሃይማኖት የተወገዘ መሆኑን አቀረብኩኝ። ባለሞያዎችም ትንታኔ እንዲሰጡበት አደረግን። ይህ ማኅበር በዛ መልክ በይፋ ተመሠረተ።

በዓለም ላይ አይ.ኤል.ጂ.ኤ ILGA (International Lesbian and Gay Association) ከተመሠረተ 40 ዓመት ሲሆነው ግብረ ሰዶምን የሚያስፋፋበት ወደ አንድ ሺሕ ቅርንጫፍ አለው። ለምሳሌ በሰሞኑ አዲስ አበባ ውስጥ ግብረሰዶማውያን እየተመዘገቡ፣ ሬሽን እየተሰጣቸው፣ ቤት ኪራይ ይከፈልላቸዋል፣ ዘይት እንዲሁም ሳኒታይዘር ሳይቀር ይሰጣቸዋል። ከዛ ሕይወት የወጡትን ግቡ እያሉ ነው።

ግብረሰዶምነት በሕግ ወንጀል በተባለበት አገር ላይ በጀት ተበጅቶላቸው እንዲንቀሳቀሱ እየተደረገ ነው። እና ዩኔስኮ ከአንደኛ እስከ 12ኛ ክፍል እንዲሰጥ ያሰበውን የሥነ ጾታ ትምህርት (Comprhensive Sexual Education) እኔ ነኝ ያጋለጥኩት። ሚኒስቴር ዴኤታውም የተቃወሙት ነው።

እንቅስቃሴያችን እየሰፋ አሁን በርካታ አርቲስቶች፣ ጋዜጠኞች፣ አትሌቶች፣ ስፖርተኞች፣ ደራስያንና ሌሎችም ጋር አብረን እየሠራን ነው። በዓለም ላይ ብቸኛ ፈቃድ ያለው ማኅበር ይህ ማኅበር ነው። ከማኅበራት ኤጀንሲ ኅዳር 9/2012 ሕጋዊ የምስክር ወረቀት አግኝቷል። በዓለም ከግብረ ሰዶም ሕይወት የሚያወጣ ተቋም አይደለም ደፍሮ የሚናገር ሰው አይገኝም።

ሲጀመር የነበረው እንቅስቃሴ ጠንከር ያለ ይመስላል። ግብረ ሰዶም በኢትዮጵያ እንዳይስፋፋ ለማድረግ የተደረጉ ጥረቶች ምን ነበሩ? የገጠሟችሁ እንቅፋቶችስ?
ነበሩ። እኔን ለመግደል ሙከራዎች ተደርገዋል። በመኪና ለመግጨት የተደረገ ሙከራ እንዲሁም መሣሪያ ያስፈራሩኝ አሉ። የእነርሱ የመጀመሪያ ዓላማ እኔን መግደል አልያም ማሳሰር ነው። ካልሆነ በሞራል ጫና አድርሰው ማስቀመጥ ነው። እና የማይደረግ ጥረት የለም።

ለዚህ ጥናት 19 የዓለም አገራት ሄጃለሁ። ሳጠና ጉግል ማድረግ ይቻላል፣ እኔ ግን ቦታው ላይ በመገኘት ነው የማጠናው። ለምሳሌ መጀመሪያ ግብረ ሰዶም ሕጋዊ ፈቃድ የሰጠችው አገር ኔዘርላንድ ናት። ኔዘርላድን ማዘጋጃ ቤቱ ድረስ ሄጂ፣ ‹ጌይ ፕራይዳቸው› ላይ ተገኝቼ ነው። ስዊድንም እንደዛው ነው። አሜሪካን አገር ስሄድም በተመሳሰይ። አትላንታ ስሄድ ጋብቻ የሚፈጽሙበት ‹ቤተክርስትያን› ቦታቸው ላይ ተገኝቼ ነው።

በፊልም ሥራ ከመቶ በላይ ሰዎች ከዛ ሕይወት ወጠተዋል። 35 ዓመት በግብረ ሰዶም ሕይወት የቆየ ሰውም እንደዛው ከዛ ሕይወት ወጥቷል። የ7 ዓመት ልጅ ሆኖ በአጎቱ የተደፈረ ነው። እና ብዙ ዋጋ አስከፍሏል።

የጥናቱ ውጤት መፍትሄው ምንድን ነው ስንል፣ አገራዊ ማኅበር ማቋቋም የሚል ነው። እሱ ተሳክቶልናል። ማኅበሩም ዐስር ዓላማዎችን ይዞ ነው የተነሳው። ግንዛቤ ማስጨበጫዎችን በመስጠት ሰዎች ከዛ ሕይወት እንዲወጡ ማድረግ፣ ከዛ ሕይወት ሲወጡ ማዋረድና ማግለል ሳይሆን በፍቅር መቀበልና ሌሎች እንዳይገቡ መጠበቅ። የሥነ ልቦና እና ሥነ አእምሮ ጉዳት ያለባቸውን በባለሞያዎች እንዲታዩ ማድረግ።

በኢኮኖሚ ችግር ያለባቸው ወንደኛ አዳሪዎች አሉ፣ እነርሱን አሠልጥኖና አስተምሮ፣ ሙያዊ እገዛ አድርጎ ራሳቸውን እንዲችሉ ማመቻቸት።
እነዚህን ሰዎች በኹለት መንገድ መርዳት ይቻላል። አንደኛ ባሉበት መርዳት ነው፤ አልያም ማገገሚ ማእከል ማስገባት ይቻላል። ማገገሚያ ማእከል የሚያስፈልገው ለምሳሌ በቅርብ ሰው የተደፈረ ሰው ተምልሶ ቤቱ መግባት አይችልም።

በትምህርት ቤት ደረጃ ሥነ ጾታ፣ ሥነ ምግባርና ሥነ ዜጋ ትምህርት እንዲሰጥ ማድረግ። ኢትዮጵያዊ ሥነ ዜጋና ሥነ ጾታ እየጠፋ ስለሆነ ነው። ሌላው ደግሞ የኢትዮጵያ ሕግ እንዲሻሻል ማድረግ ነው።

በነገራችን ላይ ስለሕጻናትና ሴቶችም ይመለከተናል። ማኅበሩ ራሱ ‹ስለኢትዮጵያ ዝም አንልም፣ ከግብረ ሰዶም እንታደግ ማኅበር› ነው። ትውልድ ሲባል ሕጻን፣ ወጣት፣ ሴትና ወንድ ሁሉንም ያካትታል። እና ሕጉ እንዲስተካከል። ከ629-632 ያለው አንቀጽ እንዲሻሻል ነው።

ምክንያቱም ኢራን ስቅላት ትላለች፣ ኡጋነዳ ሞት ትላለች። የኢትዮጵያ ሕግ ግን ቀላል እስራት ይላል። የኢትዮጵያ ሕዝብ 97 በመቶው ግብረ ሰዶምን አይቀበልም። በኢንተርኔት መረጃውን ስትመለከቺ ግን፣ ግብረ ሰዶምን ከሚቃወሙ ዐስር አገራት መካከል ኢትዮጵያ የለችም። ምክንያቱም የሕጉ መላላት ነው። ሕዝቡ ባይቀበለውም ሕጉ የላላ በመሆኑ ነው። እናም መሻሻልና መስተካከል አለበት።

ሌላው በግብረ ሰዶማውያን ከተደፈሩ ሕጻናት በ72 ሰዓት ውስጥ መጠረግ መቻል አለባቸው፣ ያንን ሕክምና ያገኛሉ ወይ። ማስረጃ መወሰድ አለበት፣ የዘረመል ምርመራ አለ፣ ይህን መንግሥት ለምንድን ነው የማይችለው? ሌላው ውጪ አገር ሕጻናት እንዲህ ጥቃት ሲደርስባቸው 911 ደውለው ይናገራሉ። እኛ ጋር ግን ጥቃት ተፈጽሞባቸውስ የሚቀበልና የሚያበረታ የሚደወልለት አካል አለ ወይ?

ፖሊስ ዐቃቤ ሕግና ፍረድ ቤትስ በቂ ግንዛቤ አላቸው ወይ? ምክንያቱም በኢትዮጵያ ሕግ ውስጥ ያልተካተቱ ብዙ አሉ። ለምሳሌ ትራንስ ጀንደር አለ፣ ግብረሰዶም ነው። ኦራል ሴክስ ግብረ ሰዶም ነው። እነዚህ ነገሮች በወንጀል ደረጃ ተካተዋል ወይ? እንዴት ነው የሚቀጣው?

አንድ ትራንስጀንደር (ጾታውን የቀየረ ሰው) ወደ ኢትዮጰያ ቢመጣ በምን ሕግ ነው የሚቀጣው? አንድ ወንድ ከሴቷ ጋር በፊንጢጣ ቢገናኝ ዐቃቤ ሕጉ ደፈረ አለ። ፈቅዳ ቢሆን ይቻላል ማለት ነው? እኛ ደግሞ ደፈረ ግብረ ሰዶምም ፈጸመ አልን። እነዚህ በውጪ አገራት ተቀባይነት ያገኙት እንኳ በእኛ አገር ሕግ በዝርዝር አልተቀመጠም። ይህም መስተካከል አለበት።

ሕጉ በወጣበት ሰዓት ያለው የግብረሰዶም እንቅስቃሴና አሁን ያለው በጣም የተለያየ ነው። ኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ 1949 ነበር መጀመሪያ፣ ቀጥሎ በደርግ በ1974 ተሻሻለ። በ1996 ደግሞ ድጋሚ በኢሕአዴግ ተሻሻለ። በ1996 የነበረው የግብረ ሰዶም ቁጥርና አሠራሩ ከአሁን ጋር ሰማይና ምድር ነው።

ያኔ ሕጉን ሲያወጡ የግብረሰዶም ቁጥሩም ሥሙም ትንሽ ነበር። ከዛ በኋላ 13 ሺሕ ገቡ። በ2005 ደግሞ 30 ሺሕ ደረሱ። አሁን መቶ ሺሕ ግብተዋል። ስለዚህ ሕጉ የወጣው ገና ዐስር ሺሕ በታች እያሉ ነው። ሕግ የሚሻሻለው ከነባራዊ ሁኔታ፣ ከታሪክ፣ ከባህል ከእሴትና ከትውፊትና መሰል ሁኔታዎች አንጻር። የአሜሪካን ሕግ ለአሜሪካ ነው የሚሠራው፣ ለኢትዮጵያ አይሠራም። እናም ካለው ድርጊት መስፋፋትና ጉዳት አኳያ ሕጉ መሻሻል አለበት የሚል አቋም ይዘን እየሠራን ነው።

ተጋላጭ የሚባሉና ትኩረት የምታደርጉባቸው አካባቢዎች ወይም ተቋማት አሉ?
እነርሱ ዐስር ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት መቆጣጠር ነው ዓላማቸው፣ ከጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ጀምሮ። አካሄዳቸው ሦስት አይነት ነው። አንደኛ ግብረሰዶም የሆነ ባለሥልጣን እንዲሾም ማድረግ፤ ኹለተኛ ግብረሰዶም ባይሆንም በገንዘብ የእነርሱን ዓላማ የሚያራምድ እንዲሾም ማድረግ ነው። ሦስተኛው ደግሞ ወንጀል ያለበት ሰው እንዲሾም ማድረግ ነው። ያ የጋሪ ፈረስ ነው፤ እናገራለሁ ካለ ያጋልጡታል።

ሊይዙ የሚፈልጓቸው ተቋማት ለምሳሌ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴርን ሊይዙ ይፈልጋሉ፣ ከቪዛ ጋር በተገናኘ። ትምህርት ሚኒስቴር ገና ሕጻናት ግብረሰዶማውያን እንዲሆኑ፣ ባህልና ቱሪዝምን ይፈልጋሉ፤ ሴክስ ቱሪዝም እንዲስፋፈ፣ ሴቶችና ሕጻናትን ይፈልጋሉ። ስለሴትና ሕጻናት ይላሉ ግን ስለወንድ ሕጻናት ጥቃት አይነገርም።

ወንድ ልጅ ከተደፈረ በግብረሰዶም ነው። ያውም አደገኛና አስገዳጅ ነው። ምክንያቱም በፈቃዳቸው ካደረጉ ወንጀል ነው፣ ሕጻናት ላይ በግዳጅ ሲፈጸም ደግሞ አስገዳጅም ነው፣ ሕጻናት ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ከፍ ያደርገዋል።

ሰብአዊ መብት ከሚሽንንም መያዝ ይፈልጋሉ። ኮሚሽኑ አንድ ጋዜጠኛ ታስሯል ብሎ ይናገራል። አንድ ሰው 34 ሕጻናት ሲደፍር ግን ምንም አይልም፣ አላለም። መብት ነው ማለት ነው የኢትዮጵያ ሕጻናት መደፈር? አሜሪካ አገር ሚኒሶታ ላይ ሲኒማ ቤት ውሻ ከአጠገቤ ተቀምጦ ፊልም አይቷል።

የኢትዮጰያ ሕጻናት ግን ከዛ ውሻ ያነሰ መብት ተሰጥቷቸው ነው ያለው። የናሁ ቲቪ ላይ ስመለከት፣ የ12 ዓመት ሕጻን ልጅ አስተማሪው ተንበርከክ ስትለው መንበርከክ ያቅተዋል። ከዛ ሲጣራ ልጁ ግብረ ሰዶም ነው። የ10 ዓመት ልጅ ሆኖ ነው የጀመረው። ደወሉልኝና ተከታተሉ አልኳቸው። ሲከታተሉ 20 ሕጻናት ተገኙ። ከዛ ውስጥ ሦስቱ የሰባት ዓመት ሴቶች ናቸው፣ በፊንጢጣቸው ነው የተገናኛቸው። ሁሉም የአባላዘር በሽተኞች ሆነዋል።

ይህን አንስተን ቲቪ ላይ ጮኽን። ስለዚህ የሕጻናት መደፈር ኢትዮጵያ ውስጥ መብት ነው ማለት ነው? አንድ ሰው አንድ ቦታ ላይ ከሰባት ዓመት እስከ 14 ዓመት ያሉ 18 ሕጻናትን አጠቃ። ዘጠኝ ወር እስር ተፈረደበት። ዶክተር የውብነሽ አስናቀ ተከራክራ 16 ዓመት እንዲፈረድበት አደረገች። እስኪ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ስለሕጻናት መደፈር የጮኸበት ጊዜ አለ ወይ?

እንዲህ ያሉ መሥሪያ ቤቶችን ጨምሮ ስፖረት ኮሚሽንን መያዝ ይፈልጋሉ። ከሚስፋፋባቸው ቦታዎች አንዱ የእንግዳ ማረፊያዎች፣ ኮንዶሚኒየም ቤቶች፣ መታጠቢ ቦታዎች ላይ ነው።

እነዚህን የሚቆጣጠር አካል ንቁ አይደለም። ለምሳሌ ባህልና ቱሪዝምን ሲይዙ በሆቴሎች ደረጃ የሚቆጣጠረው እሱ ነው። እኛ ሌላ አገር ጉዞ ስናዘጋጅና ስንሄድ ጥበቃ ተደርጎልንና በክትትል ውስጥ ሆነን ነው። እኛ አገር ግን አይጠበቅም። አንድ ቱሪስት ኹለት ወንዶችን ይዞ አድሯል። ያን መቆጣጠር የነበረበት ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ነበር።

ባለኮከብ የሚባሉ ሆቴሎቻችን ምን እየሠሩ ነው ሲባል ገንዘባቸውን ነው የሚፈልጉት። ለዚህ ነው ቶቶ ቱርስ 7900 ዶላር ተምኖ ተነጋግሮ ነው፣ ከማን ጋር ነው የተነጋገረው? ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ይህን አያውቅም ነበር? ስለዚህ ከውጪ እየመጡ ፕሮግራማቸውን ዘርተውና ሠርተው ይሄዳሉ።

እነዚህን መሥሪያ ቤቶች ሲቆጣጠር ዓላማውን በቀላል ማድረግ ይችላል።
በሕግ ደረጃም ሕግ እናስቀይራለን በሚል በአሜሪካ በከፍተኛ ደረጃ እየተንቀሳቀሱ ነው ያሉት። ሕጉ ይኑር ነገር ግን በፍቃዳችን ለምናደርገው ሳይሆን በግዳጅ ለሚያደርጉ ይቀመጥ የሚል ነው። ሌሎቹ ደግሞ ሕግ ቢኖርም ባይኖርም ምን ችግር፣ ምክንያቱም ሕግ የምንፈልገውን ከማድረግ አግዶን አያውቅም የሚል ነው።

በኖርዌይ በተካሄደ ሰልፋቸው ላይ ሰንደቅ ዓላማቸውን ይዞ ይመራ የነበረው ኢትዮጵያዊ ነበርና ‹የኢትዮጵያ መንግሥትን እናመሠግናለን፣ እንድንስፋፋ ረድቶናልና› ብሎ ጋዜጣ ላይ ወጥቷል። ይህ ሰው ትክክል ነው። ወንጀል የሚበረክተውኮ መከላከል ሲያንስ ነው።

የእኛ መንግሥት እሳት አደጋ ማጥፊያ እንኳ መሆን አልቻለም። እሳት አደጋ ሲያያዝ፣ ንብረት ከወደመ በኋላ ነው የሚመጣው። መከላከል ላይ አልተሠራም። ግንዛቤ ማስጨበጥኮ መከላከል ነው። ሰዉ እንዲህ ባለ ነገር እንዳይገባ አስከፊነትና ጎጂነቱ፣ በታሪክ፣ በባህል፣ በሃይማኖት ተቀባይነት የተወገዘ መሆኑን ካላስተማርሽው እንዴት ይጠነቀቃል።

ትምህርት ሲኖር ነው መጠንቀቅ ሊኖር የሚችለው። ማስተማር ስለሌለ ይህች 9 እና 11 ዓመት ሃያት አካባቢ የተደፈረባቸው ሴቶች ውስጥ አንደኛዋ ልጇን የወለደችው አገር ቤት ተደፍራ ነው። ከዛ እዚህ መጥታ ልጇ ተደፈረ። ሲነገራት ‹ወንድ ልጅ ይደፈራል ወይ? የኔ ልጅ ወንድ ነው።› አለች። ይህ ጥቃት መኖሩም የማያውቁም ሰዎች አሉ።

አሁን የምንሠራው ሴትም፣ ወንድም ሕጻናትና ሁሉም ላይ ነው። ከዚህም አልፎ ስለአባይ ዝም አንልም፣ ስለጣና ዝም አንልም፣ ስለሰላም ዝም አንልም፣ ኢትዮጵያን የሚመለከት ማንኛውም ጉዳይ ላይ ዝም አንልም። በአንድ ውስን ነገር የሚካተትም አይደለም።

ኢትዮጵያዊ የስርዓተ ጾታ ትምህርት ምን ማለት ነው?
በውጪው ዓለም ሕጻናትን ሦስት ዓይነት ጋብቻ አለ ብለው ነው የሚያስተምሯቸው። ወንድና ሴት፣ ወንድና ወንድ እንዲሁም ሴትና ሴት ብለው። ስለጾታም ሲያስተምሯቸው አንድ ሰው አካሌ ወንድ ሆኖ አስተሳሰቤ የሴት ነው ብሎ ሴት ነኝ የማለት መብት አለው ብለው ነው። አንዳንዶች ደግሞ ጾታዬን ገና አልወሰንኩም የሚሉ ናቸው።

በኢትዮጵያ ሕግ ደግሞ እናት እንኳ አትጠየቅም። እንደወለደች አዋላጅ ነርሷ ጾታውን ትሞላለች። ይታወቃል።
እነርሱ ሽንት ቤት ሲጠቀሙ ራሱ ሴት፣ ወንድ እና ‹ሌሎች› የሚል አለ። በጉግል የሚሰጡ የተለያዩ መጠይቆችም ጾታ የሚለው ስር ‹ሌሎች› የሚል እናያለን። ይህ እኛ አገር መምጣት የለበትም። እኛ አገር አንድ ጋብቻ ነው ያለው፣ ወንድ እና ሴት። ያውም የእድሜ ገደብ ራሱ አለ፤ 18 ዓመት ተብሎ ተቀምጧል።

በዚህም የጋብቻውን ሁኔታ ጠንቅቀው እንዲያውቁ ነው። ሌላው ኢትዮጵያዊ የጋብቻ ባህል ምንድን ነው? በሃይማኖት ደረጃ በእስልምና እንዲሁም በክርስትና ጋብቻ ክቡር ነው። ያንን ተረድተው እንዲያድጉ።

ፌሚኒስቶች ትዳር እንዲኖር አይፈልጉም። ሴት ወንድን እንድትጠላ ማድረግ ነው። ሦሰት ሺሕ ዶላር እየተከፈለ ሥልጠናዎች እየተሰጡ ነበር። ትዳር እንዲህ ከሆነ ቢቀርስ ነው። የግብረሶዶም ምክንያት ትዳር አንዱ ነው። ይህን የሚሠሩት ደግሞ አውሮፓውያን ናቸው። በአውሮፓ የኮንትራት ትዳር፣ ለወራትና ለዓመት ብሎ መጋባት አለ። አንድ ቤት ሆኖ እርሱም የፈለገውን ሴት እረሷም የፈለገችውን ወንድ መምጣት ትችላለች፣ ስትፈላለጊ ብቻ መገናኘት።

ድሮ ክላስ ሜት እንደሚባለው አሁን በኢትዮጵያ ‹ሴክስ ሜት› አለ። በየመገናኛ ብዙኀኑ አባት ልጁን ደፈረ የሚባለው ትዳር እንዲጠላ፣ አባት እንዲሸማቀቅ የሚደረግ ኣካሄድ ነው። የፌሚኒዝም መነሻ ሐሳብ ሴቶችን በእውቀት ማብቃት ነው። አሁን ግን ያ ሳይሆን ትዳርን በማፍረስ ብቻዬን ብኖር እችላለሁ፣ ምን ችግር አለ የሚለውን ማንሳት ነው።

ሰው ብቻዬን መኖር እችላለሁ ካለ፣ አምላክ ደግሞ ሰው ብቻውን ይኖር ዘንድ መልካም አይደለም ብሏል። ስለዚህ የእግዚአብሔርን ሐሳብ ማፋለስ ነው። ይህ ደግሞ 666ን ያመጣል። ቤተሰብን መበተንና ብቸኛ ማድረግ ነው። ሌላው ደግሞ ከሃይማኖት ውጪ እንድትሆኚ ማድረግ ነው።

እና አራቱ ትምህርት ቤቶች ፈርሰዋል። አንደኛው የቤተሰብ ትምህርት ቤት ነው። በጋራ ይበላል፣ በጋራ ጸሎት ይደረጋል፣ በጋራ ይወራል። አሁን ግን ቁርጥ እንጀራ ነው፣ ለየብቻ ነው የምትበይው። የጋራ ጸሎትና መብል ቀረ። አሁን ሞባይል አለ፣ አራት ሰዎች ሞባይል ይዘው አይነጋገሩም። የጋራ ወሬ ቀረ። አብሮነት ጠፋ።

በፊት ወላጆች ኮስተር ሲሉ ዞር ትያለሽ። አዋቂ ሲያወራ ልጅ አያዳምጥምም ይባላል። አሁን ግን አባት ወይም እንግዳ ሲመጣ ኖር ቀርቶ እግሩን ሰቅሎ ነው የሚጠብቀው።

ኹለተኛው ትምህርት ቤት የሰፈር ትምህርት ቤት ይባላል። ይህም ማለት ጎረቤት የጎረቤቱን ልጅ ይቀጣል። ባታጠፋ ኖሮማ አይመታህም ይላል ወላጅም። ሲጋራ እንኳ የሚያጨስ ጎረምሳ ጎረቤቱን ካየ ይደብቃል። አሁን እንኳን የጎረቤቱን የራሱ ልጅ መቅጣት አልቻለም።

በፊት ቤቴ ክፍት ነው ቤቴን እይልኝ ብለሽ ትወጪያለች፣ እንግዳ ሲመጣ እንጀራ ይዘሽ ወጥ ወይም ወጥ ኖሮ እንጀራ ፍለጋ ጎረቤት ጋር ትሄጃለች። ልጆች ጎረቤት ጋር ይቀመጡ ነበር። አሁን ያ የለም። ቤትሽን ክፍት አድርገሽ መሄድ አትችይም፣ ይህ ትምህርት ቤት ፈረሰ።

ሦስተኛው የሃይማኖት ትምህርት ቤት ነው። መድረሳ አለ እንዲሁም ቤተክርስትያን የኔታ የሚያስተምሩት አለ። ትምህርቱም ትርጉም አለው፣ ፈርሃ እግዚአብሔርም አለ፤ ታላቅን ማክበር ጨምሮ። ያኛውም ፈረሰ።

አራተኛው የመንግሥት ትምህርት ቤት ነው። በመንግሥት ትምህርት ቤት የግብረገብ ትምህርት ቀረ። በፊት የክፍል አለቃ የረባሽ ሥም ይመዘግባል። ስለዚህ እንኳን መምህሩን የክፍል አለቃ ይፈራል። አሁን ግን ተማሪው መምህሩን ስትወጣ እንገናኝ የሚል ነው። መምህሩም ለተማሪው አረአያ አይሆንም።

የእነዚህ ትምህርት ቤቶች መፍረስ ኢትዮጵያን አደጋ ውስጥ ከተታት። ትውልድ ኢትዮጵያዊነቱን እንዳያውቅ ተደረገ። በዛ ላይ አልሠራንም። ዘረኝነት ላይ ነው የሠራነው። የዘረኝነት ወተት ግተናቸው ዛሬ ሰው እየገደለና ንብረት እያወደመ ፎቶ የሚነሳ፣ ማንነቱን የጠላ፣ የሚሰደድ፣ በሊቢያ ተሰዶ ሄዶ ተምልሶ ሲመጣ እንኳ ደግሞ የሚሰደድ፣ በልቡ የተሰደደ ትውልድ ነው ያፈራነው።

ቪዛ ቢፈቀድ ኢትዮጵያ ውስጥ ማን ይቀራል? አራትና አምስት መቶ ሺሕ በውሸት ጋብቻ በዲቪ ይወጣ የለ? ይህን ያፈራነው ኢትዮጵያዊነት ላይ ስላልሠራን ነው።

እነ አጼ ምኒልክ ጣልያንን ድል ያደረጉት በመሣሪያ ኃይላቸው አይደለም፣ ኢትዮጵያውያን አንድ ልብ ስለነበሩና እምነት ስለነበራቸውም ነው። አጼ ምኒልክም ‹ጥቅምት እኩሌታ ወረኢሉ ከተህ ጠብቀኝ፣ ስትወሰልት ባገኝህ ስመለስ ማርያምን አልምርህም› አሉ። ስመለስ የምትለው ምን ማለት ነው? ገና ሊዋጉ ሲሄዱ ነው። ጠላት ውሃ አይደለም ይዞ የሚጠብቃቸው። ግን ድል እንደሚያደርጉ አውቀዋል። በመሣሪያቸው ሳይሆን በሃይማኖታቸውና በኢትጵያዊነት። ኢትዮጵያዊነት ላይ ከተሠራ ሁሉንም ድል ማድረግ ይቻላል።

ይህን ማምጣት የሚቻለው የግብረገብ ትምህርት ሲሰጥ ነው። ለምሳሌ አትግደል የሁላችንም ነው። ሁሉም ሃይማኖት አይደግፈውም። በእነዚህ የጋራዎቹ ላይ በጋራ መሥራት ይቻላል። የግብረገብ መጥፋት የዘቀጠና ተስፋ የቆረጠ ትውልድ እንዲወጣ አድርጓል። ሺሻና ጫት ቤትኮ ዩኒቨርስቲ አካባቢ ነው የሚከፈተው። ድንግልና ለጨረታ እየቀረበ ነው። ሴት ልጅ እርቃኗን በጨረታ እየተሸጠች ነው።

ኹለተኛ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ኢትዮጵያ ውስጥ የሚሠሩ ኤን.ጂ.ኦ.ዎች አብዛኛው የሚደገፉት በግብረሰዶማውያን ነው። ስለዚህ አንዳንድ ድርጅቶች ተቃወሙ ብትያቸው እንቢ ይላሉ፣ ምክንያቱም እርዳታው ይቋረጥብናል ይላሉ።

አባይ በራሳችን አቅምና ጥረት እንደገነባን ሁሉ ትውልድን መገንባት አለብን። አባይን ለማን ነው የምንገነባው? ችግኝ እየተከልን ነው፣ ጥሩ ነው። ግን ትውልድ እየተነቀለ ነው ወይ? ጉዲፈቻ በአገር ውስጥ የውጪ እርዳታ ቀርቶ በራሳችን አቅም አገር በቀል ኤን.ጂ.ኦ ብናቋቁም የተሻለ ነው። እናም ኢትዮያዊነት ላይ፣ ሰው ላይ እንሥራ። ያልተሠራ ሰው የተሠራን ነገር ያፈርሳል።

የሃይማኖት መምህራን የዓለም ነገር ላይ መግባት ቆጥረው በየአውደ ምህረታቸው ከማውገዝ አልፈው እንዲህ በአደባባይ አይናገሩም። ምን ያህል ሠርተዋል?
መንግሥትም የሃይማኖት ተቋማትም አልሠሩም። የአንድ ሰሞን ውግዘት ካልሆነ በቀር፣ በማስተማር ደረጃ እስልምናም ሆነ ክርስትና አይቀበለውም። ግን አላስተማሩበትም። ኃጢአት እንደሆነ፣ ከፈጣሪ መዓት የሚያመጣ እንደሆነ አላስተማሩበትም። ውግዘት እንኳ ሲባል መንግሥትን ሃይማኖትን መፍራት ሲኖርበት ሃይማኖት መንግሥትን ይፈራል። እያስፈቀደ ነው ያለው። ይህ ትልቁ ስህተት ነው።

ኹለተኛ መንግሥት ለእርዳታው ሲል ያደርጋል። መንግሥት ብቻ ሳይሆን ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ግብረ ሰዶምን ሲቃወሙ ሰምተሸ ታውቂለሽ? የትኛው ፓርቲ መሪ ነው ሲቃወም የሰማነው? በአሜሪካ ዴሞክታርና ሪፐብሊካን አሉ፣ የሚደግፈውና የሚቃወመው ይታወቃል።
በኢትዮጵያ አንድም ፓርቲ እቃወማለሁ አልደግፍም ሲል አልተሰማም። ብልጽግናም ጨምሮ ከመቶ በላይ ፓርቲዎች አይናገሩም።

ምክንያታቸውም ነገ እርዳታ ከውጪ እንዳናጣ ብለው ነው። በራስ መተማመን ማጣት ነው። 97 በመቶ በላይ ሕዝብ የማይቀበለውን፣ እነርሱ የሕዝብ አፍ እንሆናለን ያሉት ሲናገሩ አይሰማም።

የትኛው ተቋምስ ነው ሲቃወም ያየነው? የትኛው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ነው? ግለሰቦች ናቸው እየሠሩ ያሉት። የግል ሚድያዎችም እንደዛው። የመንግሥት ሚድያዎች እኮ ‹አንዘግብም፣ ግብረሰዶምን ማስፋፋት ነው› ብለዋል።

በነገራችን ላይ ይህ ብቻ አይደለም። የኢትዮጵያ በአፍሪካ የራሷ ቁጥር ያላት ብቸኛ አገር ናት። ግን የኢትዮጵያን ቁጥር ማን ነው የሚያውቀው፣ የመኪና ታርጋ ቁጥር በምን ይጻፋል። ሥያሜዎቻችንን ስናይ፣ ውሃዎች፣ ትምህርት ቤቶቻችን፣ የቴሌዥቭን ጣቢያ ሥሞች ሳይቀር ኢትዮጵያዊ ሥሞችን ትተናል። ቅኝ ግዛት በፊት በመሣሪያ ነበር አሁን በቴክኖሎጂ ሰበብ እየገዙን ነው። ማንነታችን ከአንደበታችን ጀምሮ እያጣን ነው። ትውልዱ ላይ አልተሠራም።

ይህ ሥራ ግን ከየት ነው የሚጀመረው?
ከእኛ እንጀመር። እኔ ቤቴ ውስጥ ልጆቼን ኢትዮጵያዊ አድርጌ ከሠራሁ፣ ትንሿን ኢትዮጵያ ሠራሁ ማለት ነው። እኔ አራት ልጆች አሉኝ። አንደኛዋና ኹለተኛው ልጆቼ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ናቸው። እርሷ ታላቅ ናት፣ እርሱ እህቱን ያከብራል። ታላቅ እንደሆነች አስተምሬው ስላደገ ያከብራታል፣ ሌሎችም እንደዛው።

መጀመር ያለብን ዛሬ ነው። ብዙ ትላንቶች አልፈውብናል። እኛ በትላንትና እና ነገ መካከል ያለን ድልድይ ነን። የአባቶቻችንን ታሪክ ካፈረስን ነገ የእኛ ታሪክ በልጆቻችን ይፈርሳል። ከጠበቅን ይጠብቁልናል። ብዙ ትላንቶች ስላለፉብን፣ ዛሬ ላይ ሆነን ነገን መሥራት አለብን። የማኅበራች መሪ ሐሳብም ዛሬ ላይ ሆነን ነገን እንገንባ የሚል ነው።

እና ከቤት መጀመር ነው። ኹለት ቻይናውያን አንድን ተራራ አጠገብ ቆመው እናፍርሰው አሉ። አንጨርሰውም ሲል፣ እኛ እንጀምረው የሚቀጥለው ትውለድ ይጨርሰዋል አሉ። እኔ 12 ዓመት ብቻዬን ስጮኽ ይህ ቀን እንደሚመጣ አውቃለሁ። ይህን ከማርቲን ሉተር ኪንግ ነው የተማርኩት። ‹ሕልም አለኝ!› ብሎ ነው የተነሳው። የእሱ እንቅስቃሴ ኦባማን 44ኛ ጥቁር የአሜሪካ ፕሬዝዳንት አድርጎታል።

ተስፋ ሳትቆርጪ መጀመር ነው። ያኔ ለውጥ ይመጣል። ግለሰብ ቤተሰብን ይፈጥራል፣ ቤተሰበ ማኅበረሰብን ሲፈጥር፣ ማኅበረሰብ ደግሞ መንግሥትን ይፈጥራል። እንዲህ ያሉ እንቅስቃሴዎች ማድረግ ነው እንጂ የውጪ ተጽእኖ፣ ገንዘብና መሰሉን የምንሰጋ ከሆነ ተገዢ ነው የምንሆነው።

በዛ ላይ ቁጥራቸው ጥቂት ነው [ግብረሰዶማውያን]፤ ቦታ ስለያዙ ነው። በአሜሪካ ከ328 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ አለ፣ ከዛ ውስጥ 4.5 በመቶው ብቻ ነው ግብረ ሰዶም። 95.5ቱ አይቀልም። እነዚህ ትንሾቹ ግን ያራግቡታል፤ ቦታ ስለያዙ። የተለያየ ስፍራ ቦታ አላቸው። ‹ምን ቸገረኝ መብታቸው ነው!› እንድትይ ያደርጋሉ እንጂ ከብዛታቸው አይደለም።

በዓለምም ከ197 አገራት ውስጥ 28 አገራት ብቻ ናቸው የተቀበሉት። በ28ቱም ውስጥ ደግሞ የማይቀበለው ሕዝብ ይበዛል። ቁልፍ ቦታ ስለያዙ፣ የተባበሩት መንግሥታት፣ ዩኔስኮና መሰል ድርጅት ቦታ ሰው ስላላቸውና የተማረ የሰው ኃይል ላይ ስለሠሩ ነው የሚያንጫጩት።

ዶክተር ቴዎድሮስ አድኃኖም ‹ፕራይድ መንዛቸው› ላይ ጻፈ። ስህተት ነው። ጥቂት ግብረ ሰዶማውያን መብት ከታየ የብዙኀኑ የማይቀበለው ሕዝብ መብትስ? እነ ፕፌሰር ሰናይት ፍስኃ አሳፋሪ ሥራ ነው የሠሩት። ከዚህ በፊት ሜክሲኮ ኤምባሲ ባንዲራቸውን ሰቅለው ተቋማችን እንከሳለን አለ። እናም ከፌስቡከ ገጻቸው አንስተው ይቅርታ ጠይቀዋል። ከበረታን ለውጥ እናመጣለን።

መናገር እውቅና እንደመስጠትና እንደማስፋፋት ነው ብሎ በማሰብ የማይናገሩና ዝምታን የመረጡ አሉ። እንዲህ ያለውን ዝምታ እንዴት ያዩታል? እውነት በይፋ መናገር ማስፋፋት ነው ማለት ይቻላል?
አይደለም። ሲጀመር እነርሱ የሚሉት በጥናት የተደገፈ አይደለም። ስለ ግብረ ሰዶም መናገር ማስፋፋት ነው የሚል ያጠና ሰው ሚድያ ላይ ይቅረብ። ማስፋፋት አይደለም ብለው ያጠኑ ብዙ ሰዎች አሉ። ይህ በኢንግሊዝ አገር ከሆነው ጋር ተመሳሳይ ነው። ኢንግሊዝ አገር ግብረሰዶም ሰው ሲገኝ ይገደል ነበር። በኋላ ጸጥ አሉና ተጽእኖ ፈጣሪዎችን፣ አርቲስቶችን፣ ገንዘብ ያላቸውን ከያዙ በኋላ ፈቃድ ጠየቁ። ሁሉም ተሳካላቸው። አሁን እነርሱ ጫና መፍጠር ጀመሩ።

አካሄዳቸው ዘመናዊ ቅኝ ግዛት ነው። ኹለተኛ ድምጽ አልባ ገዳይ ነው። ቀስ ብለው ውስጥ ውስጡን ሕግ አርቃቂና አውጪ፣ ባለሀብት ታዋቂ ሰው ይዘው ሕግ ይሻሻል ስትይ ሁሉም ቦታ እነርሱ ናቸው። አንድ ሺሕ ሰው ባዶ እጁን ቢመጣና እና አንድ ሰው ብቻውን መሣሪያ ቢይዝ፣ የትኛው ይሻላል? አንዱ ሰው በመሣሪያው ያሸንፋል።

ስለኤችአይቪ እናንሳ። ኤድስ የሚይዘው በዚህ መንገድ ነው፣ በዚህ መንገድ መከላከል ይቻላል፣ ሲይዛችሁ ደግሞ ይህን ማድረግ አለባችሁ ስትይ ነው ጥሩ የሚሆነው ወይስ ጸጥ ተብሎ ከተናገርን ይስፋፋል በሚል ነው? ኤችአይቪ እንደውም በሃይማኖት የተወገዘ ወይም ወንጀል አይደለም። በቫይረሱ የተያዘ ሰው ወንጀለኛ አይደለም። ግብረሰዶም ግን በሃይማኖት የተወገዘ፣ ወንጀልና የጤና ጠንቅ፣ ትውልድ እንዳይቀጥል የሚያደርግ ነው።

ስለዚህ ለትውልዱ መንገር ነው ማነጽ ወይስ መደበቁ? አንዳንዶች ካለማወቅና ከግንዛቤ እጥረት፣ አንዳንዶች ደግሞ በዓላማ ነው የሚሠሩት። ለጋዜጠኞች ሥልጠና ሲሰጥ ከማይነገሩና አይነኬ ከሆኑ ጉዳዮች አንዱ ግብረሰዶም ነው ይላሉ። የማይነካ ምንድን ነው ያለው? እውነት የሆነ ነገር ሁሉ ይነካል።

ሚድያ ላይ ራሱ ግብረ ሰዶም የሚለው ቃል ይቆረጣል። ግብረ ሰዶም ማለት የሰዶም ሥራ ማለት ነው። በእሳት ከጠፉት በእሳት ከጠፉት አምስቱ አውራጃዎች መካከል ሰዶም ይገኛል። ይህም የሰዶም ሥራ ይባላል እንጂ ኃጢአቱ ሥም እንኳ የለውም። የሚሰርቀው ሌባ፣ ዝሙት የፈጸመው ዘማዊ ይባላል። ይህ ግን ሥም እንኳ ያልተሰጠው ኃጢአት ነው።

አስቀድሞ እንዳሉት አስተሳሰብ ላይ መሥራት ወሳኝ ነው። ይህን በሚመለከት ሥልታዊ እቅድ አላችሁ ይሆን?
አንዱ የእነርሱን ዘዴ ማየት ነው። ለምሳሌ ዜጋ ነኝ ይላል። ግብረሰዶም ነኝ ማለት ነው። ላባ ይላሉ፤ ይህ ማለት ቦሌ ያለው ሀብታም ግብረ ሰዶም ነው። ቻይና ደግሞ ደሃው ነው። ቀጥ የሚባልም አለ። ይህም ወንድና ሴት ጾታ ጾታ ያለው (Bisexual) ነው። ትዳር ይዞ፣ ልጆች ወልዶ እዚህ ባል ነው። እዛ ደግሞ የወንድ ባል ወይም የወንድ ሚስት ሊሆን ይችላል። እነዚህ ቀጥ የሚባሉት ናቸው።

እና ነጭ ቀበቶ ማድረግ። ሌላው ሳያውቅ ያደርጋል፣ እነርሱ በዓላማ ነው የሚያደርጉት። ጥብቅ ያለ ሱሪ ማድረግ፣ ጫማ ያለካልሲ ማድረግና መሰል የእነርሱ መገለጫ ነው። ሰዓት በተደጋጋሚ ማየት፣ ስጦታ መስጠት፣ ሴቷ ሴቷን ልክ ወንድ ሴትን እንደሚያደርው ማድረግ፣ ማሻሸት፣ ማማለል የመሰሉ ነገሮች አሉ። እነርሱን በዛ መለየትና ማወቅ ይቻላል።

የመንግሥት ተቋማት ጋር በቅንጅት የመሥራት እድሉ አለ፣ የሚያግዙ የመንግሥት ተቋማትስ አሉ?
አሁን ከሰላም ሚኒስቴር ጋር እያወራን ነው፣ ከዐቃቤ ሕግ እንዲሁም ሕጻናት ሴቶችና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር፣ እንዲሁም ከሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጋር አውርተናል። ቀጣይ ደብዳቤ ያስገባንባቸው ቦታዎች አሉ።

ለምሳሌ ኢራን ትከላከላለች [ግብረ ሰዶምን]። አንድ መኝታ ክፍል ኹለት ወንዶች ማደር አይችሉም። በሞት ያስቀጣል። እኛ አገር ግን ወንድና ወንድ ወይም ሴትና ሴት ካደረ ሒሳብ ይጨምራል። በአንጻሩ ባህርዳር፣ ኮምቦልቻ እንደሁም ደሴ ላይ ያገኘኋቸው ሆቴሎች አሉ። በእነዚህ አይደለም ተመሳሳይ ጾታ ያለው፣ ተቃራኒም ሆኖ ባልና ሚስት ካልሆነና ለዛም የምስክር ወረቀት ካላሳየ አያሳድሩም። በራሳቸው ያደረጉት ነው።
ትልቁ ነገር ግንዛቤ ማስጨበጫን ለመንግሥት አካላትም መስጠት ነው። የጉዳቱን ጥልቀት ማሳየትና ከዛ ሚድያው ተጽእኖ መፍጠር ይችላል። በራድዮን፣ ጋዜጣ፣ በቴሌቭዥን፣ በቤተ እምነት፣ በገበያው፣ በእድሩና በየቦታው ሰው ግንዛቤን ካገኘ ጥንቃቄ ያደርጋል።

እንዳሉት እነርሱ ከፍተኛ አቅም አላቸው፣ በገንዘብ። የእናንተስ ያንን ለመዋጋት አቅማችሁ ምን ያህል ነው?
ማኅበሩ በአቅም ደረጃ የለውም። ቢሮ እንኳ የለውም። ካዛንችስ ጋር በእኔ የግል ቢሮ [ካዛንችስ በሚገኘው ወይንዬ አስግብኚ ድርጅት ቢሮ] ነው የምንጠቀመው። ሠራተኛ እንኳ መክፈል አቅቶን ከኪሳችን እያወጣን ነው እያደረግን ያለነው። ወደፊት ሰው ጉዳዩ ሲገባው በደንብ ያግዘናል ብዬ አስባለሁ። የተማረ የሰው ኃይል በብዛት አለን።

ሂሳብ ክፍል፣ ሕዝብ ግንኙነት፣ በጎ አድራጎት፣ የጤናና ትምህርት እንዲሁም መሰል ክፍል አለን። አቅም የመገንባት ሁኔታን ከመንግሥት ጋር ተነጋግረን፣ ሰዎች እንዲያግዙን በማድረግ በኹለት እግር ለመቆም ጥረቶችን እናደርጋለን። ሰው ሲገባውና እንደገባው መጠን ነው የሚረዳው።
ኹለተኛ እነርሱ ከያዙት ይልቅ እኛ የያዝነው እግዚአብሔር ይበልጣን። ኢትዮጵያውያንንም አሳልፎ ስለማይሰጠን እናሸንፋቸዋለን። አድዋ ላይ በእግዚአብሔር ኃይል እንዳሸነፉ፣ አባይንም የገደብነው አቅም ኖሮን አይደለም፣ በቸርነቱ ነው። እግዚአብሔር ባይፈቅድልን አንችልም ነበር።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ደግሞ ኩሩ እና ጽዩፍ ሕዝብ ነው። አንድ ብርጭቆ ሙሉ እርጎ ላይ ዝንብ ጠብ ካለ አይነካምም። በዚህ ጉዳይ ላይ ሕዝቡ ሲገባውና የሚድያውን ማነቆ ሰብረን ግንዛቤ ካስጨበጥን፣ በአንድ ጊዜ መቋቋም እንችላለን።

ቅጽ 2 ቁጥር 91 ሐምሌ 25 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here