በተግዳሮቶች መካከል ተስፋን ማስቀጠል

0
1192

ዳረል ዊልሰን የኢስት አፍሪካ ቦትሊንግ አክሲዮን ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ናቸው። ባለፈው ዓመት በሹመት ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣታቸው በፊት ጎረቤት አገር ኬንያ በናይሮቢ ቦትለርስ ለዘጠኝ ዓመታት አገልግለዋል። የደቡብ አፍሪካ ተወላጅ የሆኑት ዳረል ዊልሰን፣ የለስላሳ መጠጥ ሥራን ለ27 ዓመታት ስለሚያውቁት በኢንዱስትሪው የካበተ ልምድ እና እውቀት ባለቤት ናቸው።

የኢስት አፍሪካ ቦትሊንግ አክሲዮን ኩባንያ በ300 ሚሊዮን ዶላር ወጪ አዳዲስ የማምምረቻ ግንባታዎችን እያከናወነ ይገኛል። ይህም ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የምርት መጠን በሦስት እጥፍ ያሳድገዋል። ዋና ሥራ አስፈጻሚው እንደሚሉት፣ ኢትዮጵያ ለለስላሳ መጠጥ ምርት እጅግ አጓጊ ገበያ ያላት አገር ናት። ቢሆንም በቅርቡ ተግባራዊ የተደረገው ተጨማሪ እሴት ታክስ 15% የሚሆን የሽያጭ ገቢ ኩባንውን አሳጥቶታል።

ይህንና የኮሮና ቫይረስ መከሰት በድርጅቱ ያደረሰውን ጫና በሚመለከት ከአዲስ ማለዳ እህት መጽሔት ኢትዮጵያነ ቢዝነስ ሩቪው ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርገዋል።

የኮሮና ቫይረስ ከምርት እንዲሁም ከሽያጭ አንፃር ድርጅቱ ላይ ያስከተለው ተፅዕኖ ምን ይመስላል?
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የመላውን ዓለም ሁሉንም ነገር ነው ያስተጓገለው። በኢትዮጵያም ተመሳሳይ ነው።በበሽታው የሚጠቁ ሰዎች መጠን በፍጥነት እየጨመረ ነው። ኢኮኖሚው ለማገገም ረጅም ጊዜ ይፈልጋል። እንደ እኛ ድርጅት አስቀድመን ተነሳሽነቱን በመውሰድ ሠራተኞቻችንን ከወረርሽኙ ለመጠበቅ አመርቂ ሥራ ሠርተናል።
ከዚህም ሌላ ኅብረተሰቡ ጋር በመድረስ በተለይም ማምረቻ ፋብሪካዎቻችን በሚገኙባቸው አዲስ አበባ፣ ድሬ ዳዋ እና ባህር ዳር ከተማ ለሚገኙ ነዋሪዎች ሳኒታይዘር እንዲሁም የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛዎችን የማዳረስ ሥራ አከናውነናል። በዚህም ኃላፊነት እንደሚሰማው ትልቅ ድርጅት ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሚጠበቅብንን ተወጥተናል ብለን እናምናለን።

የቫይረሱ ተፅዕኖ ከፍተኛ በመሆኑ ከ110 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ለጉዳት የዳረገ በመሆኑ፣ መሠረታዊ የሆኑ የምግብ ፍጆታዎችን ማለትም እንደ ዱቄት፣ ፖስታ እና የፋብሪካችን ውጤት የሆኑ ምርቶችን ቤት ለቤት በነፃ ስናድል ነበር። በተለይ ወረርሽኙ ጫና ላደረሰባቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ያንን አድርገናል።
ወረርሽኙ የተጠቃሚዎችን ባህርይ ቀይሮታል። ከምግብ ይልቅ ወደ መጠጥ ፊታቸውን እንዲያዞሩ አስገድዷል።እኛም መዳረሻዎቻችንን ለመከለስ ተገድደናል። ከግማሽ በላይ የምርቶቻችን መዳረሻዎች የሆኑት ሆቴሎች፣ምግብ እና መጠጥ ቤቶች በመዘጋታቸው ወይም ብዙ ሰዎች ወደ እነዚህ ቦታዎች መሄድ በማቆማቸው፣ እንዲሁም ቤት መቆየትን በመምረጣቸው እኛም በዚህም የሽያጭ መዳረሻችንን ወደ መኖሪያ አካባቢዎች እንድናዞር ሆኗል። በእውነት ይህ እጅግ አስቸጋሪ ሁኔታ ነው። ግን የተሻለ ነገን እንድምናይ ተስፋ አለኝ።

የቫይረሱ ተጠቂ ቁጥር እየጨመረ በመሄዱ የስጋት ስሜት ውስጥ ብንሆንም፣ የገበያው ሁኔታ ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተሻሻለ መጥቷል።
ምንም እንኳ የኮቪድ ወረርሺኝ መጥፋቱ የማይቀር ቢሆንም፣ የአገራት ኢኮኖሚ ለማገገም ግን ረጅም ጊዜ ይወስድባቸዋል። ነገር ግን እኛ እንደ ኢስት አፍሪካ ቦትሊንግ ኩባንያው ወረርሽኙን ለመከላከል የወጡ መመሪያዎችን ከመተግበር ጎን ለጎን፣ ከወቅቱ ጋር የሚሄዱ አዳዲስ ስልቶችን በመንደፍ፣ ለደንበኞቻችን ምርቶቻችንን በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ እየሠራን እንገኛለን።

በዚህ ወረርሽኝ ምክንያት አሁን ብዙ ሰው ከቤት አይወጣም፣ የግለሰቦች ገቢም ቀንሷል። የለስላሳ መጠጥ ፍጆታ ቀንሷል ወይስ ጨምሯል?
የተጠቃሚዎች ቁጥር ቀንሷል። ምግብ እና መጠጥ ቤቶች ለተጠቃሚዎች እንደ ልብ ክፍት አይደሉም፣ በዚያ ላይ ከወረርሽኙ አስቀድሞ በለስላሳ እና በሌሎች ምርቶች ላይ የተጣለው የተጨማሪ እሴት ታክስ ሽያጫችንን ጎድቶታል። ከ14 ወደ 25 በመቶ በአንድ ጊዜ በመጨመሩ የምርቶቻችን ዋጋ ከፍ እንዲል አድርጎታል። ጭማሪውን ለመቋቋም ከብዶናል።

ከሰሀራ በታች ካሉ አገሮች ከፍተኛውን ግብር የምንከፍለው እኛ ነን። እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ የዋጋ ግሽበቱ ከ25 በመቶ በላይ ነው። ይህ ደግሞ የምርቶቻችንን ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር ያደርገዋል። እዚህ ላይ ነው እንግዲህ ወረርሽኙ የተደረበው።

በእነዚህ ሁኔታዎች ምክንያት የፍላጎት መቀዛቀዝ አስከትሏል። እኛም የምንፈልገውን ማሳካት አልቻልም። የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እና የተጨማሪ እሴት ታክስ የተሻለ ውጤት እንዳናስመዘግብ አድርጎናል። በተለይ የተጨማሪ እሴት ታክሱ ጉዳይ ከፍተኛ ድባቴ ውስጥ ከቶናል። ትርፋችንም በእጅጉ አሽቆልቁሏል።

በቅርቡ ተግባራዊ የተጨማሪ እሴት ታክሱ መመሪያ የኩባንያውን ገቢ ምን ያህል ጎድቶታል?
በጣም ክፉኛ ጎድቶታል። ተጨማሪ እሴት ታክሱ ገቢያችንን እስከ 15 በመቶ ይቀንሰዋል ብለን ለገንዘብ ሚኒስቴር አቅርበን ነበር። አሁን ስናየው ግን ከዚያም በላይ ነው። የተሻሻለው ተጨማሪ እሴት ታክስ፣ ኮካ ኮላ የለስላሳ መጠጥ ከሚንቀሳቀስባቸው 13 የአፍሪካ አገራት ኢትዮጵያን ከፍተኛ ግብር ከሚያስከፍሉ አገራት ግንባር ቀደም ይደርጋታል።

ለአብነት ኬንያ 8 በመቶ፣ ኡጋንዳ ደግሞ 11 በመቶ ነው የምንከፍለው። ኢትዮጵያ ደግሞ 25 በመቶ ሆኗል። በፊትም ቢሆን 14 በመቶ ነበር። አዲሱ የተጨማሪ እሴት ታክስ መመሪያ ተግባራዊ ከመደረጉ በፊትም፣የምርት ውጪን 30 በመቶ ወይም 14 በመቶ አጠቃላይ ግቡን መሰረት ያደረገ ነበር።

ባለፉት ዐስር ዓመታት የለስላሳ መጠጦች ዋጋ በእጥፍ ጨምሯል። ይህ ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው የዋጋ ግሽበት የተነሳ ነው ወይስ ከዓለማቀፍ ሁኔታ ጋር የተያያዘ ነገር አለው?
በዓለማቀፍ ገበያ የለስላሳ መጠጥ ግብአቶች እና የሌሎች ሸቀጣ ሸቀጦች ዋጋ በአስደንጋጭ ሁኔታ ነው የጨመረው። ይህ በኢትዮጵያ ካለው የውጪ ምንዛሪ እጥረት ጋር ተደምሮ የምርቶቹ ዋጋ እንዲጨምር ሆኗል።በተለይም የውጭ ምንዛሪ ማሽቆልቆል ባለፉት ስድስት ወራት ለተስተዋለው ጭማሪ ዋናው መንስኤ ነው።

ስለዚህ በዋጋ ግሽበት፣ ከብር መግዛት አቅም መዳከም እና ከታክስ ጭማሪ ጋር በተገናኘ የመጣውን ጭማሪ፣ወደ ተጠቃሚው ሳይወርድ ባለበት እንዲቆም የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራን እንገኛለን። ከላይ በጠቀስናቸው መንስኤዎች፣ ለዓመታት የቀጠለውን የዋጋ ንረት ተከትለን የዋጋ ማስተካከያ ሳናደርግ ቀጥለናል።

አሁንም የተደረጉት ጭማሪዎች እዚህ ግባ የሚባሉ አይደሉም። በኢትዮጵያ የመጠጥ ኢንዱስትሪው ትልቅ አቅም፣ እድል እና ተስፋ እንዳለው እናምናለን። በዚህም ደስተኞች ነን። ገበያውም፣ የሕዝቡም ቁጥር እያደገ ነው። ኢኮኖሚውም ትልቅ ተስፋ ሰጭ ነው። በአገሪቱ እየታየ ያለው የለውጥ አቅጣጫ በተመሳሳይ። ኢስት አፍሪካ ቦትሊንግም ትልልቅ ማስፋፊያዎችን እየሠራ ነው።

ከገቢ፣ ከትርፍና የሥራ እድል ከመፍጠር አንፃር ኢስት አፍሪካ ቦትሊግ ኩባንያ ምን ያህል ግዙፍ ነው?
ኢትዮጵያ ውስጥ 60 ዓመታትን አስቆጥረናል። በአሁኑ ወቅት 2040 ለሚሆኑ ሰዎች በቀጥታ የሥራ እድል ፈጥረናል። ከ50 ሺሕ በላይ ደግሞ በተዘዋዋሪ የሥራ እድል ያገኙ ዜጎች አሉ። ባህር ዳር፣ ድሬ ዳዋ፣ እና አዲስ አበባ ፋብሪካዎች አሉን። በተጨማሪም በሰበታ እና በሐዋሳ አዲስ ፋብሪካ እየገነባን ነው። አምቦ የሚገኘው የማእድን ውሃ ፋብሪካም አለ።

ከገቢም አንፃር ስኬታማ ነን። ለዚያም ነው 60 ዓመታትን የዘለቅነው። አሁንም 300 ሚሊዮን ዶላር መዋዕለ ንዋይ እያፈሰስን ነው። እንደ አውሮፖውያን አቆጣጠር ከ2010 ጀምሮ ኮካ ኮላ በኢትዮጵያ ብቻ 150 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የሚጠጋ መዋዕለ ንዋይ አፍስሷል።

በንግድ እንቅስቅሴአችን፣ በደሞዝ፣ በግብር፣ በማምረት፣ በማከፋፍል እና በትርፍ ክፍፍል ሂደት ውስጥ፣ በዓመት እስከ 217 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ወደ ኢኮኖሚው እንዲገባ አስትዋፅኦ እናደርጋለን።

ኢትዮጵያ ትልቅ የገበያ አቅም ያላት አገር በመሆኗ መዋዕል ንዋይ ማፍሰስና ማስፋፊያዎችን መገንባታችንን እንቀጥላለን። ከሌሎች ተመሳሳይ ኩባንያዎች ጋር ሲነጻጸር ኢትዮጵያ ውስጥ ያለን የገበያ ድርሻም ትልቅ የሚባል ነው። ያንንም ድርሻችንን ለማስቀጠል አዳዲስ ምርቶችን በማካተት እንተጋለን። ለምሳሌ ከስኳር ነጻ ምርቶችን በማምረት እያቀረብን እንገኛለን።

ከስኳር ነጻ የሆኑ ምርቶችን ማምረት የጀመራችሁት በስኳር እጥረት የተነሳ ነው እንዴ?
አይደለም። ነገር ግን ከኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን የምናገኘው ድርሻ ትንሽ ነው። ለዚያውም በየጊዜው እየቀነሰ ነው። ስኳር ከውጪ ማስገባት ደግሞ ውድ ነው። ቢሆንም ከስኳር ነጻ የሆኑ ምርቶችን የጀመርነው በደንበኞቻችን ፍላጎት የተነሳ ነው። በተደጋጋሚ ምርቶቻችንን የሚጠቀሙ ሰዎች ይህን አይነት ምርት እንደሚፈልጉ ይነግሩን ነበር። እንጂ ከስኳር እጥረቱ ጋር የተገናኘ አይደለም።

በአሁን ወቅት የኢትዮጵያ መንግሥት የስኳር ፋብሪዎችን ለመሸጥ እቅድ እንዳለው ይታወቃል ስኳር ዋነኛ ግብአት እንደመሆኑ፣ ፋብሪካዎቹን ለመግዛት እቅድ አላችሁ?
ለሽያጭ ከሚቀርቡ ፋብሪካዎች አንዱን እንኳን ብናገኝ ደስተኛ ነን። ስኳር አንዱ አስፈላጊ ግብአት ነው።ምርቶቻችን ላይ ጥሩ እሴት መጨመር እንፈልጋለን። ለዚህ ደግሞ ደረጃውን የጠበቀ ስኳር በአገር ውስጥ ብናገኝ እንመርጣለን። ስለዚህ መንግሥት ፋብሪካዎቹ ወደ ግል ይዞታ ለማዘዋወር እየሄደበት ያለውን መንገድ በንቃት እንከታተላለን። ከተሳካልን ብንገዛ እንወዳለን።

ፋብሪካዎቹን መግዛት እንደምትፈልጉ ለመንግሥት ጥያቄ አቅርባችኃል?
አዎን። ያለንን ፍላጎት በሚገባ ገልጸናል። እናም መንግሥት ወደ ግል ይዞታ የሚያሸጋገርበትን ሂደት እየተጠባበቅን ነው። እናም በዚህ ወር መጨረሻ መንግሥት ያለውን ነገር ያሳውቀናል ብለን እናምናለን።

ኢስት አፍሪካ ቦትሊንግ አክሲዮን ማኅበር ከአምቦ ማዕድን ውሃ ጋር ተዋህዷል እንዴ?
የቀድሞው ኮካ ኮላ አፍሪካ መጠጦች ከሌሎች ኩባንያዎች ጋር ተዋህዷል። ከደቡብ አፍሪካው መጠጦች ኩባንያ እና ከጉቼ ኢንቨስትመንት ጋር። የደቡብ አፍሪው መጠጦች ነው አምቦ የማዕድን ውሃ ፋብሪካን የገዛው። ስለዚህ እናት ኩባንያው ሲዋሃድ፣ የማእድን ውሃ ፋብሪካው የትልቁ የኮካ ኮላ አፍሪካ አካል ይሆናል ማለት ነው። በዚህ መሠረት አምቦ የማዕድን ውሃ ፋብሪካ እህት ኩባንያ ነው ማለት ነው።

በነገራችን ላይ እህት ኩባንያ የሆነውን አምቦ የማዕድን ውሃ ከሌሎቹ ኩባንያዎች ጋር ለማዋሃድ እየሠራን ነው። ስለዚህ ኮካ ኮላ አፍሪካ መጠጦች የኢስት አፍሪካ ቦትሊንግ መጠጦች እና የአምቦ የማዕድን ውሃ ፋብሪካ ባለቤት ነው ማለት ነው።

በኢስት አፍሪካ ቦትሊንግ አክሲዮን ያላቸው ግለሰቦች እንዳሉ እውቃለሁ። ለመሆኑ በአሁን ወቅት የአክሲዮን ድርሻ ያላቸው እነማን ናቸው?
ኮካ ኮላ አፍሪካ መጠጦች ዋነኛው ባለድርሻ ነው። ሊቀ መንበሩ ትንሽ ድርሻ አለው። ነገር ግን ኢስት አፍሪካ ቦትሊንግ አክሲዮን ማኅበር የኮካ ኮላ አፍሪካ መጠጦች ሙሉ ባለ ድርሻ ነው።

ኮካ ኮላ አፍሪካ መጠጦች የዛሬ ሦስት ዓመት ከግማሽ ገደማ ነው የተቋቋመው። አሁን በ13 የአፍሪካ አገራት ውስጥ እስከ 50 በመቶ የሚሆን የገበያ ድርሻ አለው። በኢትዮጵም 60 በመቶ የሚደርስ የገበያ ድርሻ አለን። በአጠቃላይ 16 ሺሕ የሚሆኑ ሠራተኞችም አሉን።

የገበያ አመራር መርህ ወይም ፍልስፍናችሁስ ምን ይመስላል?
ደንበኞቻችንን ለማግኘት ጠንክረን እንሠራለን። ማስታወቂያዎችን በመሥራትም ምርቶቻችንን ወደ ደንበኞቻችን እንዲደርሱ እንጥራለን። ይህ ነው የእኛ መርሕ። የትኞቹንም ምርቶቻችንን ወደ ደንበኞቻችን በፍላጎቶቻቸው ማቅረብ ነው የኛ የገበያ መርህ።

የኢትዮጵያ የገበያ ሁኔታን እንዴት አገኙት?
ገና ብዙ ያልተሠራበት ገበያ እንደሆነ ይሰማኛል። ውድድር ያለብን ቢሆንም ብዙ ተመሳሳይ የምርት አማራጭ የለም። 15 ዓይነት የምርት አማራጭ ብቻ ነው ያለው። ይህ ደግሞ እንደ ኬንያ ካሉ አገራት ጋር ሲነፃፀር ዝቅተኛ የሚባል ነው። ምንም ያልተነካ እያደገ የሚሄድ ገበያ አለ።

በአንፃራዊነት የለስላሳ መጠጦች ፍጆታ ዝቅተኛ የሚባል ሲሆን በሌላ በኩል ወደ መካከለኛ ገቢ እያደጉ ያሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች መኖራቸው ጥሩ የገበያ እድል ይፈጥራል። የገበያውን እድል ለመጠቀም አዳዲስ ምርቶችን ወደ ገበያ እናስገባለን። የገበያ ስልታችን፣ አካባቢን እና የደንበኞችን ፍላጎት መሰረት ያደረገ ነው። ለዚህም ኩባንያችን በግምት እስከ 10 ሚሊዮን ዶላር ለገበያ ጥናት እና ለማስታወቂያ ወጪ ያደርጋል።

ኩባንያው ለገበያ አስተዳደር እና ለቅርንጫፍ ሥራ አመራሮች ከፍተኛ ደሞዝና ጥቅማ ጥቅም ይከፍላል። ይህ ክፍያ ውጤትን መሰረት ያደረገ ነው ወይስ የኩባንያው የአከፋፈል ስርዓት ነው?
በመጀመሪያ ሠራተኞቻችንን ለማሠልጠን ብዙ ገንዘብ እናወጣለን። ጠቀም ያለ ደሞዝና ጥቅማ ጥቅም እንዲያገኙ እናደርጋለን። ሁሌም ደስተኛ እንዲሆኑ እንፈልጋለን። ይህም የደንበኞቻችንን ፍላጎት ለማርካትና ተወዳዳሪነታችንን ለማስጠበቅ ይረዳናል።

ሠራተኞቻችንን ማበረታታት የመጨረሻ ግባችን ነው። የስኬታችንም ምስጢር ይህ ነው። ከማንኛውም ስኬታማ ኩባንያ ጀርባ ሰዎች አሉ። የኮካ ኮላ ኩባንያም ስኬት ይሄው ነው። ብዙ ኩባንያዎች እየተፈተኑበት ባሉበት ወቅትም ቢሆን ሠራተኞችን የተሻለ ጥቅማ ጥቅም እንዲያገኙ እያደረግን ነው። ሠራተኞች በድካማቸው ልክ እንዲያገኙ እናደርጋለን።

በቅርብ ጊዜ የቢራና የታሸገ ውሃ የገበያ ድርሻ እያደገ መጥቷል። በተለይ የቢራ አምራች ኩባንያዎች መጠጥ ቤቶችን በማደስ፣ ፍሪጅ እና ሌሎችንም ቁሳቁሶች በማቅረብ ምርቶቻቸውን በብዛት እንዲወጡ እየሠሩ ነው። ይህ አካሄድ የለስላሳ መጠጥ ደንበኞችን ወደ ቢራ እንዲዞሩ አድርጓል ብለው ያምናሉ?
እኛም እኮ ምግብና መጠጥ ቤቶች እያደስን፣ ፍሪጅ እና ሌሎች ቁሳቁሶችን እየሰጠናቸው ነው። የሚያደርጉትን እያደረግን ነው። እኛም እነርሱም እያደግን ነው። ለዚህ ነው ኮካ ኮላ 300 ሚሊዮን ዶላር እያፈሰሰ ያለው።

በእርግጥ የደንብኞች ቁጥር እየቀነሰ ነው። ይሄ ግን ከተጨማሪ እሴት ታክሱ መጨመር ጋር የተገናኘ ነው። ሆኖም ደግሞ አዳዲስ ደንበኞችም ምርቶቻችን እየተጠቀሙ ነው።

አልፎ አልፎ የተበላሹ እና በምርት ሂደት ችግር ያገጠማቸውን ምርቶች ገበያው ላይ እናገኛለን።እንደዚህ አይነት ምርቶች እንዴት ሊፈጠሩ ይችላሉ? ችግሩን ተገንዝባችሁታል?
የመጠቀሚያ ጊዜ (expire date) ለኩባንያችን ዋናው ጉዳያችን ነው። ይህንንም ጥንቃቄ በተሞላበት አኳኋን እየሠራን እንገኛለን። ከሌሎቹ አገራት እንሻላለን ብለን እናምናለን። አከፋፋዮቻችን እና ደንበኞቻችን እስከ ታች ድረስ በመውረድ አጥብቀው ይሠራሉ። በምርት ሂደት ችግር ያገጠማቸውን ምርቶች (defective products) ምርቶችን በተመለከተ ላነሳኸው ግን እንደዚህ ያሉ ምርቶችን ጨርሶ ማጥፋት አስቸጋሪ ነው።

አሁን በቅርብ ጊዜ ለገበያ ለመቅረብ እየተዘጋጁ ያሉ ምርቶች አሉ?
አዎ። የሰበታው ፋብሪካ ወደ ምርት ሲገባ፣ የምርቶቻችን መጠን ከመጨመር ባሻገር አዳዲስ ምርቶችን ወደ ገበያ ለማቅረብ ያስችለናል።

የኩባንያው የማስፋፊያ ሥራዎችስ በምን ሁኔታ ላይ ይገኛሉ? የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ተፅዕኖ አሳድሮበታል?
የሰበታ ማስፋፊያ በሚቀጥለው ዓመት ምርት ይጀምራል። በአሁኑ ጊዜ 60 በመቶ ደርሷል። ምንአልባት ኹለት ወራት ቢዘገዩ ነው። አሁን ባሉን ማምረቻዎች የደንበኞቻችንን ፍላጎት ለማርካት እየሠራን ነው። በኢትዮጵያ ያለንን የማስፋፊያ ሥራዎች እቅድ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ውስጥ ሆነንም አላጠፍነውም።

የሰበታው እና የሐዋሳው ማምረቻ ፋብሪካዎች ግንባታ ምን ያክል ወጪ ያስወጣል?
ለኹለቱም የማምረቻ ፋብሪካዎች 300 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ይጠይቃሉ። የሐዋሳው ፋብሪካ ግዙፍ ነው። ነገር ግን የሰበታውም ቢሆን ስድስት የማምረቻ መስመሮች የሚኖሩት ሲሆን በጣም ትልቅ የሚባል ነው።

የሰበታው ፕላስቲኮችን መልሶ መጠቀም የሚያስችል ፋብሪም አለው። ፋብሪካዎቹ ወደ ምርት ሲገቡ በኢትዮጵያ የሚኖረንን የምርት መጠን በሦስት እጥፍ ያሳድገዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የኢንቨስትመንት ሁኔታ እንዴት አገኙት?
ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት ተመራጭ ናት። ኮካ ኮላ ትልቅ ኩባንያ ነው። የፈለግንበት አገር ሄደን ኢንቬስት ማድረግ እንችላለን። ኢትዮጵያ ውስጥ እየሆነ ባለው ነገር ተስፋ አለን። ለዚህ ነው ኃላፊነት እንደሚሰማው ኩባንያ 300 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስት እያደረግን ያለነው። ይህ እንደ ቀላል ውሳኔ የሚቆጠር አይደለም።
ኢትዮጵያ ትልቅ ተስፋ አላት። መካከለኛ ገቢ ያለው የኅብረተሰብ ክፍል እየጨመረ ነው። እየተደረጉ ያሉ የለውጥና ማሻሻል ሥራዎች አሉ። ሰለዚህ እዚህ ኢንቨስት በማድረጋችን ደስተኞች ነን።

የኮካ ኮላ ኩባንያ የኢስት አፍሪካ ቦትሊንግ አክሲዮን ኩባንያ ኢትዮጵያ ውስጥ ኢንቨስት ለማድረግ ያላቸውን ቁርጠኝነት ማሳያ ናቸው። የኢንቨስትመንት ቁርጠኝነታችን በትርፍ እናገኘዋለን ብለን ከምናስቀምጠው ገንዘብ 25 በመቶ ነው።

ይሄ ከተጨማሪ እሴት ታክሱ መጨመር በፊት የነበረ ቁጥር ነው። አስተማማኝ ፖሊሲ መኖርና የግብር አስተዳደር ስርዓት ማንኛውንም የንግድ ሥራ ለመሥራት ወሳኝ ጉዳይ ነው። መንግሥት ለእነዚህ ነገሮች ትኩረት እና ዋስትና መስጠት አለበት።

ኢትዮጵያ ውስጥ በተደጋጋሚ እያጋጠማችሁ ያለው ችግር ምንድን ነው?
ዋናው እና ትልቁ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ነው። ለምርት የሚሆኑ ግብዓቶችን ከውጭ እያስመጡ መሥራት አስቸጋሪ ነው። የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ራሱ ከባድ ነው። በተለይ ላለፉት ስድስት ዓመታት የውጭ ምንዛሪ እጥረት ፈተና ሆኖብናል። እንደገና ወረርሽኝ ነገሩን ከባድ አደረገብን።

ሌላው አስቸጋሪ ሁኔታን የፈጠረብን የተጨማሪ እሴት ታክሱ መጨመር ነው። የታክስ ስርዓት ማሻሻያውን እንደግፋለን። የሚጠበቅብንን ግብር በወቅቱና በኃላፊነት እንከፍላለን። የተጨማሪ እሴት ታክሱ ጭማሪ ግን ከፍተኛ ነው። እየሠራን ካሉባቸው ሌሎች 13 የአፍሪካ አገራት ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ ግብር ነው እዚህ ኢትዮጵያ የሚከፍለው።

የኃይል መቆራረጥ ጉዳይስ? ኩባንያችሁ በራሱ ሃይል ለማመንጨት ጥረት እንደነበረው ይታወቃል። ምን ላይ ደረሳችሁ?
የኃይል እጥረት በመላ አገሪቱ ያለ ችግር ነው። በአብዛኛው በጀነሬተር ነው የምንጠቀመው። ይህ ግን ትክክለኛው የአመራረት አካሄድ አይደለም። ውድ ነው። ቢሆንም ግን ምርጫ የለንም። በአሁኑ ወቅት በሰበታ እና በሃዋሳ በፀሐይ ኃይል ለማመንጨት ጥረት እያደረግን ነው። የውሃ አጠቃቀማችንንም እየሠራንበት ነው። መልሰን ለመጠቀም በሚያስችሉ አሰራሮችን ላይ ውሃን በአግባቡ ለመጠቀም እየሠራን ነው።

በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ተፅዕኖ ምክንያት የተፈጠረውን የገበያ መዋዠቅ ለማስተካከል ምን አማራጭ አስቀምጣችኋል?
በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጊዜ ትልቅ ፈተና የሆነብን ደንበኞቻችን ጋር መድረስ ነው። ወረርሽኙ የአመጋገብ ሁኔታውን ቀይሮታል። አስቀድሞ እንዳነሳሁት ሰዎች ምግብ እና መጠጥ ቤት መሄድ አቁመው ቤት ነው ያሉት። ስለዚህ እኛም የስልክ ጥሪ ማዕከል በማቋቋም ለደንበኞቻችን ተደራሽ ለመሆን እየሠራን እንገኛለን።
በተጨማሪም ምርቶቻችን በሁሉም አካባቢዎች ተደራሽ እንዲሆኑ እየሠራን ነው። ደንበኞቻችን የሚፈልጉትን ምርት በተገቢው ዋጋ እና በትክክለኛው ጊዜ እንዲቀርብላቸው እያደረግን ነው። አሁን ኢኮኖሚው ትንሽ ከፈት እያለ ነው። በቅርቡም ጥሩ እንደሚሆን እምነት አለኝ። ግን አሁንም ቢሆን ደንበኞቻችን ቤት ለመድረስ እንሠራለን።

ከፈጣን ምግብ አምራች ኩባንያዎች ጋር አብሮ የመሥራት እቅድ አላችሁ?
አዎ። እየተሠራ ያለ ሥራ አለ። ጥሩ የሆነ ኩባንያ እና ስምምነት ከተገኘ፣ የኢትዮጵያ መንግሥትም የአክሲዮን ገበያ ከሦስት ዓመት በኋላ ለመክፈት ሐሳብ አለው።

ኩባንያው ምርጥ ኩባንያ ተብሎ የሚጠራ ይሆናል ብለው ያምናሉ?
በእርግጥም እንሆናለን። አፍሪዊ ኩባንያ ነን። ሁኔታዎቹ ካጋጠመን ለመጠቀም ዝግጁ ነን።

ፕሮጀክቶቹን ከመደገፍና ከማበረታታት አንፃር የኢትዮጵያ መንግሥት ድጋፍ ምን ይመስላል?
ትልልቅ ማስፋፊያዎችን ነው እየሠራን ያለነው። ይህ 300 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የሚጠይቁትን አዳዲስ ፋብሪካዎችን ይጨምራል። ይህ ትልቅ ኢንቨስትመንት ነውና ለዚህ ነው የተጨማሪ እሴት ታክሱ ጉዳይ ከፍተኛ ስጋት የሆነብን። አዳዲስ ኢንቨስትመንቶችን ይጎዳብናል።

የክልል መንግሥታት እያደረጉልን ባለው ድጋፍ ደስተኞች ነን። በተለይ ግንባታው የሚገኝባቸው እንደ ባህር ዳር ሰበታ እና ሀዋሳ ያሉ ከተሞች ጥሩ ግብረ መልስ አሳይተዋል። እኛም የአካባቢው ማኅበረሰብ የሚፈልገውን እገዛ እያደረግን እንገኛለን። ትምህርት ቤት፣ የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ወዘተ ለኅብረተሰቡ ለማቅረብ እንሠራለን።

በለስላሳ መጠጦች ዘርፍ ትልቅ ኩባንያ እንደመሆናችን፣ ከመንግሥት ጋር በመሆን ልንሠራቸው የምንችላቸው በርካታ ሥራዎች እንዳሉ ይሰማናል። ምንም እንኳ ገበያው አስተማማኝ ባይሆን ትላልቅ ማስፋፊያ ሥራዎችን እየሠራን እንገኛለን። መንግሥት እያደረገልን ላለውም ድጋፍ ምስጋና አለን።

ውድድር መኖሩን እንወደዋለን። ምክንያቱም ውድድሩ በቴክኖሎጂ ለመዘመን እድል ይሰጣል። ገበያ ውስጥ የሚታዩትን የተበላሹ ምርቶች በተመለከተ ግን ጨርሶ ማስቀረት አይቻልም።

ነገር ግን በክልል ከተሞች የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸው ምርቶች ይስተዋላሉ። ኩባንያው እንዴት ነው ቁጥጥር የሚያደርገው?
የምርት ዘመን ማብቂያ ጊዜ ለኩባንያው እጅግ ወሳኝ ጉዳይ ነው። ጊዜ ያለፈባቸውን ምርቶች በመከታተል የሽያጭ ወኪሎቻችን እና ደንበኞቻችን ምርቶች ጥቅም ላይ እንዳይውሉ ይሠራሉ። ኩባንያውም ከገበያ ላይ የሚሰበስብበት አሰራር አለው።

ትርፋችሁን ወደ ውጪ ይዞ ከመውጣት እንፃር ምን ፈተና አለባችሁ?
እሱ አስቸጋሪ ነው። ያለው የውጪ ምንዛሪ እጥረት የትርፍ ክፍፍል ይዘን እንድንወጣ አድርጎናል። ይህ ለበርካታ ዓመታት እየሆነ ያለ ጉዳይ ነው። ለዚህም ነው መልሰን እዚሁ ኢንቨስት እያደረግን ያለነው።

የኢኮኖሚ ሪፎርሙ ሲሳካ እና የውጪ ምንዛሪ እጥረት ሲቀረፍ፣ ነገሮች ይለወጣሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን። የውጭ ምንዛሪ እጥረት ሲቀረፍ ደግሞ የትርፍ ክፍፍል ይዘን እንድንወጣ ይሆናል ማለት ነው።

ማኅበራዊ ኃላፊነትን ከመወጣት አንፃር እንደ ትልቅ ኩባንያ ምን ምክር ሐሳብ አልዎት? ኩባንያዎች ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ነው ብለው ያምናሉ? ኅብረተሰቡንስ ተጠቃሚ እያደረጉ ነው ብለው ያስባሉ?
እኛ ትምህርት ቤቶችን፣ የንፁህ መጠጥ አቅርቦቶችን እና የሥራ እድል ፈጠራ ላይ ኃላፊነታችንን እየተወጣን ነው ብለን እናምናለን። ለማኅበረሰቡም የሚጠበቅብንን እየሰጠን ነው። ለዚያም ነው ፋብሪካዎቻችን ያሉባቸው አካባቢዎች ያሉ የማኅበረሰብ ክፍሎች በሚገባ የተቀበሉን። በየዓመቱም ሚሊዮኖችን ማሳተፍ ችለናን። ለኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ድርጅም ድጋፍ አድርገናል።

ብዙ ኩባንያዎች ሲመቻቸው ብቻ ነው ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን የሚወጡት። ለምንድን ነው ከገቢ ወይንም ከትርፋችሁ በቋሚነት የሚሰላ ገንዘብ መድባችሁ ወጥ በሆነ መልኩ ማኅበራዊ ኃላፊነታችሁን የማትወጡት?
ትርፍ ሰብስቦ በመሮጥ አናምንም። ለማኅበረሰቡ መልሶ በመስጠትም ጭምር እንጂ። ማኅበረሰቡን እያገዝን ነው። በተለይም ወጣቶችን ልዩ ማዕከል አድርገን የምንሠራቸው ሥራዎች አሉ። ለወጣቶች የትምህርትን አስፈላጊነት እናውቃለን።

በ220 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ባህር ዳር ከተማ ውስጥ እጅግ ደረጃውን የጠበቀ ‹ሽምቢት› የሚባል የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ገንብተናል። በተመሳሳይ መልኩ ደረጃውን የጠበቀ ትምህርት ቤት በሰበታ ከተማ በ236 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የኅብረተሰቡን ፍላጎት አገናዝበን ገንብተናል።

አነስተኛ ገቢ ካላቸው ቤተሰብ ወጥተው ዩኒቨርሲቲ ለሚማሩ ተማሪዎችም እገዛ ሊሆን የሚችል 31 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ እንዲደርስ አድርገናል። ላለፉት 11 ዓመታትም 275 ዶላር ወጪ በማድረግ ተመርቀው የወጡ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን የኮምፕዩተርና ኢንፎርሜሽን ሥልጠና ሰጥተናል።

የኅብረተሰቡን ችግር ሊቀርፉ የሚችሉ በርካታ ሥራዎች ሠርተናል። ለአብነትም የፕላስቲክ ምርቶችን መልሶ ጥቅም ላይ እንዲውል የሚያደርግ ፋብሪካ የዛሬ አምስት ወራት ገደማ ገንብተናል። ለዚህም ኩባንያችን 160 ሚሊዮን ዶላር ወጪ አውጥተናል።

ፕላስቲክ ጥሩ የሚባል ምርት ማሸጊያ ቢሆንም አካባቢን ይበክላል። ስለዚህ ራሱን የቻለ የፕላስቲክ መልሶ ጥቅም ላይ እንዲውል የሚያደርግ ግብረ ሰናይ ድርጅት አቋቁመናል። በአጠቃላይ 70 የሚደርሱ ፕላስቲክ መሰብሰቢያ ማዕከላትን በመላ አገሪቱ አቋቁመናል። በተለይ ለሴቶች ቀለል የሚል ሥራ በመሆኑ እየሠሩ ይገኛሉ። ለዚህም ድጎማ እናደርጋለን።

ወደ ስድስት ሺሕ የሚጠጋ የተጣሉ የፕላስቲክ ጠርሙሶችን መሰብሰብ ችለናል። በተጨማሪም የአካባቢውን የመንግሥት አካል ከቆሻሻ አወጋገድ ስርዓት ጋር በተገናኘ እና ቆሻሻን መልሶ ጥቅም ላይ እንዲውል ለማድረግ አብረን መሥራት እንፈልጋለን።

እስከ 2030 ድረስ የኮካ ኮላ አፍሪካ መጠጦች የወዳደቁ ፕላስቲክ ጠርሙሶችን ሙሉ ለሙሉ መልሰው አገልግሎት ላይ እንዲውሉ እንሠራለን። እንደምናሳካውም እናምናለን። የታሸገ ውሃ ምርት ከፍተኛ ውድድር ቢኖርበትም ጥራት ያለው ውሃን በተመጣጣኝ ዋጋ ከማቅረብ ባሻገር ለተጠቃሚዎች አማራጭ ውሃን ለማቅረብ እንሠራለን። በሚቀጥሉት ኹለት ወራት ውስጥም ተጨማሪ ምርቶችን ወደ ገበያ ይዘን እንቀርባለን።

ቅጽ 2 ቁጥር 92 ነሐሴ 2 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here