ኢትዮጵያ እውነት ‹የውሃ ማማ›?

0
1245

ጣና ሐይቅ ለወትሮ የነበረውን ግርማ ሞገስና ውበት፣ ይሰጥ የነበረው አገልግሎትና ጥቅም እያደር እየቀነሰ መሄዱ ብዙዎችን ከስጋት ጥሏል። ከዚህ በኋላም ነው ‹ጣናን እንታደግ› የሚል እንቅስቃሴ ከየአቅጣጫው የሚሰማው። ነገር ግን የጣና ነገር ሲነሳ በተያያዘ የጣና ገባር የሆኑ በርካታ የኢትዮጵያ ወንዞችም በዕይታ ውስጥ መግባታቸው አይቀሬ ነው።

በተያያዘ ካላት የውሃ ሀብት አንጻር በሚገባ ተጠቃሚ እንዳልሆነች የሚነገርላት ኢትዮጵያ፣ ካለመጠቀም በላይ የውሃ ሀብቷ እየተመናመነ፣ ሐይቆቿም እየተጎሳቆሉና እየተጎዱ መሆኑም ይነሳል። ለተቀሩት የውሃ አካላትስ ታድያ ምን ያህል ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው፣ ያሉ ነባራዊ እውነታዎችስ ምን ይመስላሉ፣ የውሃ ሀብት አያያዝ በኢትዮጵያ ምን መልክ አለው፣ ምንስ መምሰል አለበት በሚሉና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ፣ ባለሞያዎችን በማነጋገር፣ የሚመለከታቸውን በመጠየቅና መዛግብትን በማገላበጥ የአዲስ ማለዳዋ ሊድያ ተስፋዬ ጉዳዩን የሐተታ ዘ ማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አድርጋዋለች።

‹የአፍሪካ የውሃ ማማ› ይሏታል፤ ኢትዮጵያን። እንዲህ ተብላ ለመጠራቷ ምክንያቱ አንድም ከጉያዋ ወጥተው ድንበር ተሻግረው ወደ ተለያዩ አገራት በሚጓዙ ወንዞቿ፤ አንድም ምድሯንና ዙሪያዋን የሚያረሰርሱ በርካታ የውሃ አካላት፣ ወንዞችና ሐይቆች ያሏት ናት ሲባል ነው። በአንጻሩ ታድያ ይህ ‹የውሃ ባለሀብት› መሆኗ ተጨባጭ እውነታ ነው ወይ በሚለው ላይ በተለያየ ጊዜ ሙግት ይነሳል።

በተፈጥሮ ሳትታደል ቀርታ ሳይሆን አጠቃቀም ላይ የሚታዩ ግድፈቶች ይህን ጉዳይ አጀንዳ ሊያደርጉት ችለዋል። በተጓዳኝ የውሃ ሀብቷን በሚገባ እየተጠቀመች ነው ወይ፣ ቀድሞስ ነገር አያያዟ እንዴት ነው የሚለው በቅድሚያ ይነሳል።

የውሃ ሀብት አያያዝ ባህል
የኢትዮጵያ የውሃ ሀብት አጠቃቀም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ልማት ላይ ያተኮረ፣ ለግንባታ ሥራዎች የበለጠውን ትኩረት ይሰጥ የነበረ ነው። በኋላ የአንዳንድ ውሃ አካላት ብክለትና ጥፋት እንዲሁም ስጋት ሲደቀን፣ ወደ አስተዳደሩ ጉዳይ መለስ ማለትን ጠይቋል።ግን ኹለቱም ጎን ለጎን መሄድ ነበረባቸው። አንዳንዴም የአስተዳደሩ ሥራ ቀድሞ ሊገኝ ይችላል።

ይህን ሐሳብ ያነሱት ፈቄ አሕመድ በበናይል ተፋሰስ ኢኒሺዬቲቭ ዳይሬክተርና የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ተደራዳሪ ቡድን አባል ናቸው። አክለውም አንድ የግድብ ሥራ ራሱ ከመጀመሩ አስቀድሞ ከስድስት እስከ ስምንት ዓመታት የተፋሰስ ልማት ሥራ ላይ በሚገባ መሥራት ተገቢ ነው ብለዋል።

በአገሩ ውሃ ላይ ባለሥልጣንና ባለቤት የሆነው ሕዝብ ሲሆን፣ የአስተዳደር ሥራውን በበላይነት የሚሠራው ደግሞ የውሃና መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ነው። ይህ ተቋም የተለያዩ ተቋማትን በስሩ በማቋቋም የውሃ አካላት እንዲለሙ እየሠራ መሆኑንም ፈቄ ጠቅሰዋል።

ጋዜጠኛና ‹የአባይ ፖለቲካና የባዕዳን ተልዕኮ› የተሰኘ መጽሐፍ አዘጋጅ ስለአባት ማናዬ፣ የውሃ ሀብት አያያዝ መጀመሪያ ያለውን ሀብት ከማወቅ የሚነሳ ነው ባይ ነው። ኢትዮጵያ ‹ይህን ያህል የውሃ ሀብት አላት› ከማለት ይልቅም በተለምዶው ብቻ እየተጓዙ ‹የውሃ ማማ ናት› ማለቱ አግባብ እንዳልሆነም አጽንዖት ሰጥቶ አንስቷል። በሌላ አቅጣጫ የኢትዮጵያ ውሃ ሀብት ‹ብዙ ነው› ተብሎ የሚጋነን አይደለም። ካለው ሀብትም ስትጠቀም አይታይም፤ የስላባት ገለጻ ነው።

ፈቄም በዚህ ሐሳብ ይስማማሉ። ይህም በአገራችን ያለ የተሳሳተ አመለካከት ነው ሲሉ አስረድተዋል። ‹‹ብዙ ሰው አገራችን በውሃ ሀብታም ነች የሚል እምነት አለው። እውነቱ ግን እንደዛ አይደል። በአጭር ጊዜ የውሃ እጥረት ውስጥ ልንገባ እንችላለን።›› ሲሉ ከአዲስ ማለዳ ጋር ባደረጉት ቆይታ ተናግረዋል።

ለዚህም ማሳያ አቅርበዋል። ‹‹በተፋሰስ ደረጃ ካሉት 12 ወንዞች 9 የሚሆኑት የውሃ እጥረት ውስጥ ገብተዋል። የውሃ ሀብታም ነን የሚለውን ትቶ እጥረት አለብን የሚለውን በማሰብ ላሉ የውሃ ሀብቶች የምንሰጠው እንክብካቤ ሊጨምር ይገባል። ሀብታም ነን ብንል ያዘናጋናል እንጂ አይጠቅምም።›› ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ምን ያሰጋል?
አዲስ ማለዳ በጉዳዩ ላይ ካነጋገረቻቸው ባለሞያዎች መካከል ዘውዱ ሰይፉ ይገኙበታል። ዘውዱ ሰይፉ በኢትዮጵያ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የውሃ ቴክኖሎጂ ትምህርትና ሥልጠና ኃላፊ፣ አሠልጣኝና ተመራማሪ ናቸው። ‹ውሃ ያልቃል ወይ?› በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሻቸውን መሠረታዊ የውሃ ዑደትን በመጥቀስ ጀምረዋል። እንደሚታወቀው ውሃ ከምድር ገጽ በሙቀት አማካኝነት በትነት መልክ ወደ አየር ከወጣ በኋላ በተወሰነ የከፍታ ደረጃ ላይ ሲደርስ ቀዝቅዞ መልሶ በዝናብ መልክ ወደ ምድር ይደርሳል።

እናም ይህ ዑደት ጤናማ ሆኖ እስከቀጠለ ድረስ፣ ውሃ ማለቅ አይደለም፤ አይቀንስም። ሆኖም ግን ዋናው ነጥብ ወዲህ ነው። ሰዎች ከሁሉም የውሃ አካላት አይጠቀሙም። ይልቁንም ለመጠጥና ማብሰያ አገልግሎት የሚውል ንጹህ ውሃን (fresh water) ይፈልጋሉ። የተቀረው ጨዋማ ውሃ ግን ከንጹህ ውሃ ልክ አገልግሎት የሚሰጥ አይደለም። እናም ውሃ ጨርሶ ባይጠፋም እየቀነሰ ሊሄድ የሚችል ሀብት መሆኑ እሙን ነው።

የኢትዮጵያ የሕዝብ ቁጥር ከዓመት ዓመት እየጨመረ፣ የእድገት መጠኑም በዛው ልክ እየሰፋና እያደገ ነው።ይህም የውሃ አቅርቦት ደኅንነት ጉዳይን አሳሳቢ ያደርገዋል።ይህም ብቻ አይደለም የሚሉት ዘውዱ በበኩላቸው፣ ከሕዝብ ቁጥር መጨመር ጎል ለጎን የከተማ ልማትና የኢንዱስትሪ መስፋፋት የውሃ አቅርቦት ፍላጎትን ከፍ ያደርገዋል። ከዛም አልፎ ተያይዘው የሚጨምሩት የዝቃጭና ቆሻሻዎች መጠን ብክለት እንዳያስከትሉ ክትትል ማድረግም የሚያያዝ ነው።

ብዙውን ጊዜ የገጸ ምድር ውሃ ጉዳይ የሚነሳ ቢሆንም፣ የከርሰ ምድር ውሃም አብሮ ሊጠቀስ ይችላል።የከርሰ ምድር ውሃ የሚገኝባቸው ስፍራዎችም በተለያዩ ምክንያቶች እየተመናመኑ እንደሆነ ነው ዘውዱ ያነሱት። በበርካታ ስፍራዎች የተቆፈሩ የጉድጓድ ውሃ መገኛ ስፍራዎችም ከእለት እለት የውሃ መጠናቸው እየቀነሰ ነው።
ከዛም አልፎ የከርሰ ምድር ውሃ ይኖርባቸዋል ተብለው የተለዩ ስፍራዎች ላይ ግንባታዎች እየተከናወኑና ሰዎች እየሰፈሩባቸው ነው። ውሃ ሊሄድ የሚችልባቸው ስፍራዎችም በዚህ መልክ የተያዙ በመሆኑ ጎርፍ በተለያዩ አካባቢዎች ስጋት ሆኖ ይስተዋላል።

ይህ እንደ አገር የሚጠቀስ ሆኖ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ የአየር ንብረት ለውጥ አለ። እንደ ዘንድሮ /2012/ የክረምት ወቅት ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ በየጊዜው ላይገኝ ይችላል። እንደ ዘውዱ ገለጻ፣ ቀደም ያሉ ዓመታት በአምስትና በዐስር ዓመት ልዩነት መለስ ብሎ ለቃኘ፣ ድርቅና የዝናብ እጥረት የተከሰተባቸውን ጊዜያት ያስታውሳል። እናም ዛሬ የሚገኘውን ውሃ በአግባብ መጠቀም ካልተቻለ፣ በቀጣይ ጊዜያት ጉዳዩ አስጨናቂ ሊሆን እንደሚችል ከወዲሁ ጠቁመዋል።
ፈቄ በበኩላቸው የውሃ አስተዳደር ጉዳይ ወሰብሰብ ያለ መሆኑን አመላክተዋል። የትኛውም ልማት ውሃ የሚፈልግ እንደመሆኑ፣ ሌላ ልማት አስቦ ውሃን አለመንካት፣ የውሃ ልማትን አስቦ ደግሞ ሌሎች ጉዳዮችን መዘንጋት የሚቻል አይደለም ሲሉ ያስረዳሉ።እናም ጥንቃቄ የሚፈልግ ጉዳይ ነው ሲሉ ይቋጩታል።

በኢትዮጵያ ከጠፉ ሐይቆች መካከል ሐሮማያ ተጠቃሽ ነው። እንደ አብያታ ያሉ ሐይቆች ደግሞ አሁንም ከባድ ችግር ላይ መሆናቸው በተደጋጋሚ ይነገራል። ፈቄ ታድያ ያም ብቻ ሳይሆን ከልክ በላይ የሚሞሉ ወንዞችም በዛው መጠን ስጋት ናቸው ይላሉ።

ለምሳሌም የበሰቃ ሐይቅን ጠቅሰው፣ ይህ ሐይቅ መጠኑ በመጨመሩ ምክንያት መሠረተ ልማቶች ላይ ችግር እየፈጠረ እንዳለአውስተዋል።

ወንዞቻችን ምን እየሆኑ ነው?
ይህን ስጋት ምን ወለደው የተባለ እንደሆነ፣ የውሃ ብክነት እንዲሁም ብክለት ተጠቃሽ መንስኤዎች ናቸው። ኬሚካሎችና ከፋብሪካ የሚወጡ ፍሳሽ ቆሻሻዎች በብክለት በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው።የመሬት አጠቃቀምም በተመሳሳይ አውድ ላይ ይነሳል።

‹‹ውሃንና መሬትን ለይቶ ማየት አስቸጋሪ ነው።›› የሚሉት ፈቄ፣ በአፈር መጎዳት ምክንያት በውሃ አካላት ላይ የሚደርስ ተጽእኖም እንዳለ አያይዘው ጠቅሰዋል። ኢትዮጵያ ደጋማው ክፍል ላይ የሚገኘው መሬት ለብዙ ሺሕ ዓመታት ያለማቋረጥ ሲታረስ የቆየ በመሆኑ፣ በጣም መጎሳቆሉንም አስታውሰዋል። ‹‹የባለቤነት ጉዳይም ራሱን የቻለ ተጽእኖ አለው›› ሲሉም ያክላሉ።

ኢንዱስትሪዎች ከመስፋፋታቸው ጋር ተያይዞ በቂ የፍሳሽ ማስወገጃ ባለመኖሩ በካይ ቆሻሻ የሚጣለውውሃ ውስጥ ነው። ‹‹ለጊዜው አደገኛ ደረጃ ለይ አልደረሰም ተብሎ ነው የሚታወቀው። በቅርቡ የከተማ መስፋፋት ሲጠነክርግን ወደኋላ መመለስ የማይቻልበት ደረጃ ላይ ይደርሳል። እንዲያገግም ለማድረግ የሚወጣው ወጪም ከፍተኛ ይሆናል።ዋጋም ሊያስከፍል ይችላል።›› ሲሉም የውሃ አካላትን የመጠበቅና የመንከባከብ ሥራ ምን ያህል ወሳኝ እንደሆነ ፈቄ ተናግረዋል።

በዚህ ላይ ሐሳባቸውን ያከሉት ዘውዱ፣ እንደማሳያ የዝዋይ ሐይቅን ያነሳሉ። የባቱ ከተማ አስተዳደር ለአካባቢው ነዋሪ ንጹህ የመጠጥ ውሃን ከዝዋይ ሐይቅ እያጣራ ያቀርብ የነበረ ሲሆን፣ ነገር ግን በሐይቁ ውስጥ በገባው ኬሚካል ምክንያት በቀላል ዘዴ ውሃውን አጣርቶ ለተጠቃሚ ማድረስ ፈታኝ ሆነበት። እናም ብዙ ርቀት ሄዶ ውሃን ለተጠቃሚ ለማቅረብ ግድ አለ።

ከውሃ ብክነት ጋር በተያያዘም ዘውዱ ጥሩ የሚባል የውሃ አጠቃቀም ተሞክሮ ምን ያለ ነው በሚለው ላይ ሐሳባቸውን ለአዲስ ማለዳ አካፍለዋል። እርሳቸውም ጥሩ የሚባል የውሃ አጠቃቀም የውሃ ሚዛንን የጠበቀ ነው ብለዋል።ይህም ማለት፣ ኢትዮጵያ ከዝናብ የምታገኘውን፣ በከርሰ ምድር ያለውን፣ በገጸ ምድር የሚገኘውንና፣ ድንበር አልፎ ወደ ጎረቤት አገራት የሚፈሰው ውሃ ገና ሳይሻገር እንዴት እየተጠቀመች ነው የሚለውን ይመለከታል።

በገጸ ምድር ያለውን ውሃ በሚገባና በአግባቡ መጠቀም ካልተቻለ፣ የከርሰ ምድር ውሃን ወደመጠቀም መሻገር ይከተላል።አሁንም ኢትዮጵያ በተለያዩ ስፍራዎች የከርሰ ምድር ውሃን እየተጠቀመች ሲሆን፣ ከእነዚህ የውሃ ጉድጓዶች ውሃ መውሰድ እንጂ ለጉዳጓዶቹ ውሃ ማቆየትና መስጠት ካልተቻለ፣ በባንክ ያለ ተቀማጭ ሀብትን ወጪ እንደማድረግ ነው። ስለዚህም ከላይ እንደተጠቀሰው የውሃ እጥረት ስጋት እውን የመሆን እድሉ ይጨምራል።

በ2012 መጀመሪያ አካባቢ የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ይፋ ካደረጋቸው መረጃዎች መካከል በኢትዮጵያ ከሚመረተው ንጹህ ውሃ ውስጥ በአማካይ 40 በመቶው እንደሚባክን ነበር።በአንጻሩ አድገዋልበሚባሉ አገራት ቢበዛ 3 እና 4 በመቶ ውሃ ነው ለብክነት የሚጋለጠው። በአዲስ አበባ ደግሞ ይህ ብክነት 45 በመቶ ይደርሳል።

ይህም ከአገልግሎት አሰጣጥ እስከ አጠቃቀም ባለው መስመር ውስጥ የሚከሰት ሲሆን፣ የቧንቧ መቀደድ፣ የማጠራቀሚያና ማምረቻ ጥራት መጓደል፣ የውሃ መስመሮች ማርጀት ወዘተ ምክንያት እንደሆኑ ዘውዱ አክለው ጠቅሰዋል። የውሃ ስርቆት ሳይቀር እንዳለና እንደውም በአዲስ አበባ ከሚከሰተው 40 በመቶ የውሃ ብክነት ውስጥ 15 በመቶ አካባቢ በዚህ ምክንያት የሚደርስ እንደሆነ ነው ያነሱት።

‹‹ካለው ንጹህ የመጠጥ ውህ ወስጥ 40 በመቶ እየባከነ ነው። የውሃ መስመሮች ይፈነዳሉ፣ በየመንገዱም ውሃ ይፈሳል። የሚሠሩ ወንጀሎችም ጭምር አሉ። 40 በመቶ ንጹህ ውሃን ማጣት ማለት 10 ሺሕ ሜትር ኩብ ከሚይዝ ታንከር ውስጥ አራት ሺውን ሜዳ ላይ ማፍሰስ ነው። ይህ ብክነት ከፍተኛ ነው። ሚዛኑን እንጠብቅ ብንል እንኳ እንዲህ ሰው ሳይጠቀምበት ይባክናል።›› ሲሉም ዘውዱ አብራርተዋል።

ስለአባት በበኩሉ ከውሃ ብክነት እንዲሁም ብክለት ጋር በተያያዘ ያለውን ሁኔታ አያይዞ አንስቷል። ብክለትን በሚመለከት ጥቂት የማይባሉ የኢትዮጵያ የውሃ መገኛ አካላት በመጤ አረም እየተወረሴ፣ በኬሚካል እየተበረዙ፣ በአየር ንብረት ለውጥ እየደረቁና በደለል እየተሞሉነው ብሏል። የአፈር መሸርሸርም ከዚህ ጋር በቀጥታ የሚገናኝ ነው።

ከዚህም ጋር በተገናኘ በደብረማርቆስ ዩኒቨርስቲ የቀረቡ ጥናታዊ ጽሑፎችን አውስቷል። አንደኛው ጥናት በታደለ አምደማርያም (ዶ/ር) የተሠራ ሲሆን፣ በጮቄ ተራራ ላይ በሚገኘው ተፋሰስ ዙሪያ የተከናወነ ነው።ጮቄ ተራራ 149 ሺሕ ሔክታር መሬት የሚሸፍን፣ ለአባይ ወንዝ ገባር ከሆኑ 59 የሚደርሱ ወንዞች ውስጥ 273 ምንጮች የሚገኙበት ነው። በዚህ ተፋሰስ ዙሪያ ጥናታቸውን ያደረጉት የተፈጥሮ ሀብት ጥናት ተመራማሪ የሆኑት ታደለ፣ በወንዞች ላይ እየደረሰ ያለውን ተጽእኖ በኹለት ከፍለው አስረድተዋል።

በአንድ ጎን መካከለኛ ጉት የደረሰባው ሲሆኑ የተቀሩት ደግሞ ከፍተኛ ጉዳት ያረፈባቸው ናቸው። መካከለኛ ጉዳት ያለባቸው የውሃ አካላት ላይ በዓመት በሔክታር 42 ቶን አፈር ሲታጠብ፣ ከፍተኛ ባሏቸው ደግሞ 302 ቶን አፈር በሔክታር ታጥቦ ይሄዳል።በድምሩም 1.3 ቢሊዮን ቶን አፈር ይሄዳል።‹‹ኢትዮጵያ ይህን በማጣቷ1.2 ሚሊዮን ቶን የሰብል ምርት አጥታለች።›› ጥናቱ እንደጠቀሰው።

እነዚህ ጥፋቶች ታድያ ከላይ እንደተጠቀሰው በተለያየ ምክንያት የሚከሰቱ ሆነው፣ በዘመቻ መልክ የሚሠሩና በሳይንስ በእውቀት ላይ መሠረት ያላደረጉ መንገዶችም አንድ ምክንያት እንደሚሆኑ ተጠቅሷል። ‹‹የአየር ንብረት ለውጥም እየተባባሰ ነው። እነዚህን ለመከላከል የተራቆቱትን በደን መሸፈን፣ ባዶ መሬቶች ላይም ደን ማልማት አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበታል።›› የስለአባት ገለጻ ነው።

በሌላ በኩል በቂና ተገቢ ልማት ሳያለሙ ውሃን አብዝቶ መጠቀም ለውሃ ብክነት እንደሚዳርግም ስለአባት አንስቷል። ይልቁንም በባህዳር ዩኒቨርሲቲ የመጠጥ ውሃና የውሃ ነክ ጉዳዮች ተባባሪ ፕሮፌሰር ዳኛቸው አክሎግ (ዶ/ር) ያጠኑትን ጥናት በመጥቀስ፣ ጣና ላይ ‹ሰራባ› የሚባ ፕሮከክት መኖሩና ይህም ጓያ የሚያለማ እንደሆነ ተጠቅሷል። ይህ ፕሮጀክት ከመጠን በላይ ውሃን የሚጠቀም ሲሆን ለውሃ ልማት ግን ቅንጣት አያበረክትም።

በኢትዮጵያ ያሉ የውሃ አካላት እንዲህ ባሉ የብክለትና የብክነት ምክንያቶች ጉዳት እየደረሰባቸውና ለሰዎች ጥቅም ሊሰጡ የሚችሉ የውሃ አካላት በመመናመንና በመጥፋት ላይ ይገኛሉ። የሐሮማያ ሐይቅ መጥፋት በተደጋጋሚ የሚጠቀስ ሲሆን፣ አዲስ ማለዳ የዛሬ ዓመት ግንቦት ወር አጋማሽ ላይ በ29ኛ እትሟ ባስተናገደቸው ዜና የዝዋይ ሐይው ጥልቀት ከ12 ሜትር ወደ አራት ሜትር መቀነሱን መዘገቧ የሚታወስ ነው።

ይህም የሆነው በስምጥ ሸለቆዎች አካባቢ ካለው ከፍተኛ የእሳተ ገሞራ ክምችት የተነሳ እንደሆነ ተጠቅሷል። በሐይቁ ላይ እየደረሰ ያለው ሰው ሠራሽ ጉዳትም መፍትሄ ካልተበጀለት የሐይቁ መኖር ጥያቄ ውስጥ ሊገባ እንደሚችል ባለሞያዎችም አብራርተዋል።

የነበሩና ያሉ እድሎች
በኢትዮጵያ 40 ቢሊዮን ሜትሪክ ክዩብ የከርሰ ምድር ውሃ ሲገኝ፣ በገጸምድር 122 ቢሊዮን ሜትሪክ ኪዩብ የሚጠጋ ውሃ አለ። ከዚህ በተጓዳኝ ኢትዮጵያ በውሃ ሀብት እጅግ የታደለች እንደሆነች በአዘቦት ቢነገርም፣ አሁንም ግብርና ሥራው ዝናብን የሚጠብቅ መሆኑ ብዙዎችን የሚያስገርም ነው። ኢትዮጵያም የውሃ ሀብቷን በሚገባ እንዳልተጠቀመች ከሚጠቁሙ ኹነቶች መካከል ይህኛው በራሱ ቀዳሚ ነው።

ብዙ የውሃ ሀብት ያላቸው አገራት ውሃውን ለምን ሊጠቀሙበት ይችላሉ ቢባል፣ አንደኛው በውሃ ኃይል የሚመነጭ የኤሌክትሪክ ኃይል (hydroelectric power) ነው። የኢትዮጵያ ወንዞችም ይህን ኃይል ለማመንጨት አቅም እንዳላቸው ይጠቀሳል።

ኢትዮጵያ መላ ኃይሏን ብትጠቀም እስከ 45 ሺሕ ሜጋ ዋት ኃይል ማመንጨት የሚያስችል የውሃ ሀብት እንዳላትም ነው የሚጠቀሰው። ከዚህ ጋር በተያያዘም አሁን ላይ ወደ ውሃ ሙሌት ሥራ የገባውንና የመጀመሪያ ዙር ሙሌት ያጠናቀቀውን ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጥቀስ ይቻላል።

በተያያዘየአባ ሳሙኤል ሐይቅን ጨምሮ፣ ቆቃ፣ ጢስ አባይ፣ አዋሽ፣ መልካዋከና፣ ሶር፣ ፊንጫ፣ ጊቤ/ኦሞ፣ ጣና በለስ እና ተከዜ በድምሩ እስከ 4 ሺሕ ሜጋ ዋት ኃይል ያመነጫሉ። ይህ በኤሌክትሪክ ኃይል ጋር በተገናኘ ሆኖ፣ ለመስኖ አገልግሎት እየዋሉ ያሉ የውሃ አካላትም አሉ።

በዚህም ባሮ አኮቦ እና ገናሌ ዳዋ የተባሉ ወንዞች ተጠቃሽ ናቸው። የትራንስፖርት አገልግሎትን በተመለከተ ግን አብዛኞቹ ወንዞች ለትራንስፖርት ምቹ አይደሉም። በአንጻሩ የኢትዮጵያ ሐይቆችለትራንስፖርት ምቹ ናቸው። እንደ ጣና እና አባያ ያሉትም ለዚህ ማሳያ ይሆናሉ።

ሌላው ከአሳ ሀብት ጋር የሚያያዝ ነው። አብዛኛው የኢትዮጵያ ሐይቆች በአሳ ሀብት የታደሉ ናቸው። አሁንም ታድያ በጥቅም ላይ እየዋለ ካለው በበለጠ እየባከነና እየተበከለ፣ እየጠፋና እየተጎዳ ያለ ሀብት እንዳለ ነው ባለሞያዎች የሚጠቁሙት።

እንደ ስለአባት ማናዬ ገለጻ ታድያ፣ ኢትዮጵያ ለኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫነት እየተጠቀመችበት ያለው ከጠቅላላ አቅሟ 10 በመቶውን ብቻ እንደሆነ ጠቅሷል። ይህንንም በውሃ አጠቃቀም ረገድ ብቻ በንጽጽር፣ በጥሩ የውሃ ሀብት አጠቃቀም ከምትወደሰው ጃፓን ጋር ሲታይ አንድ ስድስተኛውን እንደሆነ ነው ያነሳው።
2016 የተከወነ ጥናትን ጠቅሶ ሲያስረዳም፣ኢትዮጵያ ለመስኖ የተጠቀመችው 10.5 ቢሊዮን ኪዮቢክ ሜትር ውሃ ነው ይላል። ይህም ለመስኖ መጠቀም ከምትችለው 8 በመቶ ብቻ ነው። የመጠጥ ውሃ ተደራሽነትም ከላይ እንደተጠቀሰው ሁሉ ዝቅተኛ ሆኖ ይገኛል።

በዚሁ የንጹህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነትን እናንሳ። ኢትዮጵያ ያላትን ለአገልግሎት ሊውል የሚችል ውሃ ለዜጎቿ እንዴት እያዳረሰች ነው? የውሃ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስቴርን ጠቅሶ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባለፈው በጀት ዓመት ማብቂያ ላይ ያወጣው ዘገባ እንደሚያስረዳው፣ የኢትዮጵያ የመጠጥ ውሃ ተደራሽነት ከቀደመው ዓመት አንጻር 4.8 በመቶ እድገት አሳይቷል። ይህም ከከተማ ይልቅ በገጠራማ የኢትዮጵያ ክፍሎች በስፋት የተስተዋለ ነው።

ዘውዱ የዓለም ጤና ድርጅትን መስፈርት ያነሳሉ። ድርጅቱ የውሃ ተደራሽነትን በአራት ደረጃ ያስቀምጣል። እነዚህም ምንም አይነት ውሃ ተደራሽ ያልሆነላቸው፣ መሠረታዊ ተደራሽነት ያላቸው፣ መካከለኛ እንዲሁም በቂ የሚባል ደረጃ ላይ ያሉ የሚሉ ናቸው። በቂ ውሃ አለ ወይም እጥረት የለም ለማለት ቢያንስ በነፍስ ወከፍ ለአንድ ቀን 100 ሊትር ውሃ ያስፈልጋል። እነዚህም ለንጽህና፣ ለምግብና ለመጠጥ ነው።

የኢትዮጵያ የኹለተኛው የትራንስፎርሜሽን እቅድም ላይ በከተማ 75 እና በገጠር 85 ሊትር በነፍስ ወከፍ እናደርሳለን የሚል እቅድ ነበር።
መካከለኛ የሚባለው ደረጃ ደግሞ 50ሊትር ውሃ በነፍስ ወከፍ ሲገኝ ሲሆን፣ መሠረታዊ ተደራሽነት የምንለው አንድ ሰው ምግብ ለማብሰልና ቢያንስ እጅና መመገቢያ ቁሳቁስ ለማጠብ 20 ሊትር ውሃ ያስፈልገዋል፤ በቀን። የቀረውን ግን በቅርበት በሚገኝ ሌላ አማራጭ መጠቀም ግድ ይላል፤ ሰውነትን መታጠብና ልብስን ማጠብ ጨምሮ።

ምን ይበጃል?
ፈቄ በበኩላቸው ሐሳባቸውን ሲያካፍሉ የእኔነትና የባለቤትነት ስሜት ሊፈጠር እንደሚገባ ነው የጠቀሱት። ‹‹ውሃን በአብዛኛው እየተጠቀምን ያለነው ለመጠጥ ነው። ያም ቢሆን በቧንቧ መጥቶ መክፈቱን ነውየምናየው እንጂ እንዴት እንደሚመጣና የሚከፈልበትን ዋጋ፣ ውስብስብ ጉዳይ በውሰጡ እንዳለ ልብ አንልም። ኤሌክትሪክም ቢሆን በየቤታችን ማብራትና ማጥፋትን እንጂ እንዴት ውስብስብ ጉዳይ ውስጥ አልፎ እንደሚመጣ አብዛኛውን አይታወቅም። እዛ ላይ መሠራት አለበት።›› ሲሉ ግንዛቤ ማስጨበጥ ላይ ብዙ መሠራት እንዳለበት አመላክተዋል።

አልፎም የረጅም ጊዜ እቅድ ነድፎ በየአንዳንዱ ተፋፈስ ላይ መሠራቱን ጠቅሰው፣ በተወሰነ ደረጃ ተቋማትም እየተቋቋሙ ነው ሲሉ እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎችን አድንቀዋል። ‹‹ያለንና እንደ አገር የምንተማመንበት ሀብት ውሃ ነው። ውሃን በደንብ መጠበቅ፣ መንከባከብና በዘላቂነት መልማት አለበት። ለዚህ የሁሉም ተሳትፎ ይፈለጋል።›› ሲሉም አሳስበዋል።

ዘውዱ በበኩላቸው ከውሃ አካላት ብክለት ጋር በተገናኘ፣ ልማት ሳይቋረጥ የውሃ አካላትም ደኅንነታቸው ተጠብቆ እንዲሄዱ ስልታዊ አካሄድ ያስፈልጋል ባይ ናቸው። ለዚህም ብዙ የተዘጋጁ ሕግጋት መኖራቸውን አንስተው፣ ይልቁንም የልማት ፕሮጀክቶች ወደ ሥራ ሲገቡ በካባቢ ላይ የሚያደርሱትተጽእኖ ታይቶና ተጠንቶ፣ አልፎም ከስር ከስር ክትትል ማድረግ አስፈላጊ መሆኑ መከተቡን ጠቅሰዋል።

ነገር ግን ማስፈጸም ላይ ክፍተት አለ።ጉዳዩን ሁሉ ከድህነት ጋር በማያያዝና ዝቃጮችን በወንዞች ላይ በሚጥሉ ኢንዱስትሪዎች ላይ እርምጃ መውሰድ ባለሀብቶችን እንደማስቀየምና የአገርን ልማት እንደማጓተት ይቆጠራል።

‹‹ከመነሻውም ኃላፊነት ወስደው የሚሠሩ [ፋሪካዎች] አሉ።›የሚሉት ዘውዱ፣ በዓለም ዐቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ ለመሆን ሲሉም ለአካባቢ ደኅንነት ትኩረት የሚሰጡት እንዳሉ ጠቅሰዋል።በተጓዳኝ ግን የኢንዱስትሪ መንደሮች መፈጠር ይህን ችግር ሊያቀለው ይችላል ባይ ናቸው። በተለይም በመንደሩ የሚገኙ አምራቾች የፍሳሽ አወጋገድ ላይ የተቀናጀ መንገድን ተጠቅመው፣ መልሶ ለጥቅም መዋል የሚችል ተረፈ ምርትንም ቢሆን ለአገልግሎት አመቺ በሚሆን መልኩ ለማስወገድ ሁኔታዎች እድል ይሰጧቸዋል።

የውና፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር በበኩሉ የሕዳሴ ግድቡን ዘጠነኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ባወጣው መግለጫ፣ ወንዞችን ማልማት የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሲጠናቀቅ የሚቆም ተግባር እንዳይደለ አጽንዖት መስጠቱ ይታወሳል። የሕዳሴው ግድብ ግንባታ ለሌሎች ወንዞች ልማት ትልቅ ማሳያ መሆኑም በመሥሪያ ቤቱ የተገለጸ ሲሆን፣ ሌሎች ወንዞችን የማልማት ሥራው ወደፊት የሚቀጥል ነው ተብሏል።

ዘውዱከዚህ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት 10 ዓመታት ጥሩ ለውጦች ታይተዋል ብለዋል፤ በተለይም በመጠጥ ውሃ ዘርፍ። ‹‹በመጠጥ ውሃ ላይ ሥራ ተሠርቷል። እየዘነጋን ያለነው ግን አዳዲስ ለመገንባት እንጂ ያሉትን በዘላቂነት መጠቀምላይ ችግር አለ።›› ሲሉም አስረድተዋል።

አያይዘውም አሉ፤ ‹‹ከአግልግሎት ውጪ የሆኑ የውሃ ጉድጓዶ እየጨመሩ ነው። እንዲህ ያሉ ችግሮች የሚስፋፉ ከሆነ ‹ውሃ የለም› ወደሚለው ያመጣናል። በዘላቂነት ለውጥን የሚያመጡ ሥራዎች መሠራት አለባቸው። የተፋሰስ ልማትም ወሳኝ ነው።››

አጽንኦት ሰጥተው ያነሱት ሐሳብም የውሃ መገኛ የሚባሉ ቦታዎች መጠበቅ አለባቸው የሚለውን ነው። የከተማ አስተዳደሮች መሬት በፈለጉ ጊዜ ሁሉ እነዚህን በተለይም የከርሰ ምድር ውሃ ይገኝባቸዋል ተብለው የተለዩ ስፍራዎችን ሊያጥር አይገባም።

‹‹ወርቅ ያለበት ወይም ነዳጅ ያለበት ቦታ ላይ ቤት አይሠራም።›› ያሉት ዘውዱ፣ ውሃም እንደዛው ውድ ሀብት መሆኑን በመረዳት የከርሰ ምድር ውሃ መገኛ ስፍራዎች ጥበቃ ሊደረግላቸው እንደሚገባ አሳስበዋል።በዚህም በአንዳንድ ክልል ከተሞች አመርቂ ሥራ መሠራቱን አንስተው፣ ለእነዚህ አካባቢዎች ካርታ ሁሉ የሚሰጡ አሉ ብለዋል።

የውሃ መገኛ ምንጮችን በፕሮጀክት ማልማትና በዛም ላይ በትኩረት መሥራት አስፈላጊና ወሳኝ መሆኑንም ዘውዱ አያይዘው አንስተዋል። እንደ ፈቄ ሁሉ ዘውዱም በአስተያየታቸው ውሃን ከብክነት ለመታደግም የአስተሳሰብ ለውጥ ማምጣት ያስፈልጋል ባይ ናቸው።

የተፋሰስ ልማት ላይ መሥራት፣ የችግኝ ተከላ፣ የእጽእዋት ልማት ላይ መሥራት ያስፈልጋል። ሕገ ወጥ የደን ጭፍጨፋና ሕገወጥ ሰፈራን መከላከልም ተገቢ ነው። ችግሩ ምንድን ነው የሚለውን ቀርቦ በማየት መገናኛ ብዙኀንን ጨምሮ የሚመለከታው ተቋማት ሁሉ ጉዳዩን በትኩረት እንዲከታተሉም ይጠበቃል።

ጥናትና ምርምሮች በተገቢው መንገድ ተከናውነው ወደ መሬትም ወርደው ተግባራዊ መደረግ አለባቸው። ማኅበረሰብ ተኮር ሥራዎች በፍጥነትና በአግባቡ ሊሠሩ ይገባል። የመረጃ ክፍተቶችም ሊቃኙ ያስፈልፈልጋል የሚሉ ሐሳቦችንም ለአዲስ ማለዳ ሐሳባቸውን ያካፈሉት እነዚህ ባለሞያዎች በየበኩላቸው ከሰጧቸው የመፍትሔ እርምጃዎች መካከል ናቸው።

ከማጠቃለላችን በፊት ዘውዱ ስላነሱትና መረጃን በሚመለከት ስላለው ጉዳይ እናንሳ። አዲስ ማለዳ ይህን ሐተታ ለማዘጋጀት ባለሞያዎችን ከማነጋገር ባለፈ የተለያዩ ሰነዶችን ያገላበጠች ሲሆን፣ የውሃ ሀብት አላት እንደምትባል አገር መረጃዎች በበቂ ሁኔታ ሰፍረው አይገኙም። አልያም በየባለሞያዎች የመረጃ ቋት ውስጥ ተለይተው ተቀምጠዋል።

ይህን ጉዳይም ዘውዱ አንስተውታል። የውሃ አካላትን በሚመለከት የተቀናጀ የመረጃ አሰጣጥ የለም። አዲስ ማለዳም በጉዳዩ የሚሠሩ ተቋማትን ድረገጽ ብትቃኝም አገልግሎት ከማይሰጡ ድረገጾች ባለፈ ያገኘችው በቂ ግብዓት የለም። የመረጃ ስርዓት ደካማ መሆኑን አንድ አገር በጉዳዩ ልትሠራ ከምትችለው የሚያጎድል ነው። በሐተታው መግቢያ እንደተጠቀሰው፣ ሀብቱን በሚገባ የማያውቅ ሰው ሀብቱን መጠበቅም ሆነ በሀብቱ ውጤታማ ሥራን መሥራት አይችልም።

በተጓዳኝ በ2011 መግቢያ አካባቢ ‹የተፋሰስ ልማት ባለሥልጣን› የሚባል አደረጃጀት በውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ስር ተቋቁሟል።ባለሥልጣኑ አስቀድሞ በሥራ ላይ የነበሩ የአዋሽ፣ የአባይ እና የስምጥ ሸለቆ ተፋሰስ ባለሥልጣን የሚባሉትን መሥሪያ ቤቶች እንዲሁም በእቅድ ይጨመራሉ ተብለው የተያዙ አራት አደረጃጀቶችን ትቶ የተመሠረተ ነው። ይህም በተፋሰስ ደረጃ ይገኙ የነበሩ መረጃዎችን ወደ አንድ ማእከል ያመጣ ሲሆን፣ የራሱ የሆነ ተጽእኖ እንደሚኖረውም ዘውዱ ስጋታቸውን ገልጸዋል።

ፈቄም ከመረጃዎች ጋር በተገናኘ ሐሳባቸውን ሲሰጡ፣ መረጃዎች ይፋ መደረግና መውጣታቸው የውሃ ሀብትን ጊጊው ሳይረፍድ ለመንከባከብና በጥንቃቄ ለመጠቀም ይረዳል ብለዋል። በኢትዮጵያ ያለው ታዳሽ የገጸ ምድር ውሃ 122 ቢሊዮን ሜትሪክ ኪዩብ መሆኑን የጠቀሱት ፈቄ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ብዛት ቁጥር በቅርቡ 122 የሚደርስና ከዛም የሚልቅ መሆኑ ተደራሽነት ላይ የሚያሳድረው ስጋት ቀላል እንዳይደለ አመላክተዋል። ለዚህም ነው ከወዲሁ ጥንቃቄና ማስተዋል አይለየን ሲሉ ያሳሰቡት።

ቅጽ 2 ቁጥር 92 ነሐሴ 2 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here