ዘመናዊነት እናኢትዮጵያዊነት!

0
983

ሰዎች ዘመናዊነትን የሚረዱበት መንገድ የተለያየ ነው። ለዛም ነው ኢትዮጵያዊ ወይም አፍሪካዊ የሆነን ነገር (ቁስ አካልም ይሁን አመለካከት) ‹የእኛ ባህል› ከማለት ይልቅ ‹ኋላቀር ባህል› የሚለውን ሐረግ መጠቀም የሚቀናቸው። ቀድሞ ነገር ‹ዘመናዊነት› የሚለው አስተሳሰብ ባህልን ለመቀየር የተፈጠረ ነው ወይ የሚለው አሟጋች ይመስለኛል።

በዚህ መሠረት ታድያ ዘመናዊነት ‹ዘመናዊ ነን› ያሉ ሰዎች የተቀበሉትን ሁሉ መቀበል እንደሆነ የሚያምኑ ጥቂት አይደሉም። ለራሳቸው አቋምና አመለካከት ማጣቀሻቸው በ‹ዘመናዊ ሰዎች› የተጻፉ አጀንዳዎች ናቸው። አገር በቀል የሆነው ሁሉ ኋላቀር እንደሆነ ያምናሉ። ከባህል ምግብና ከባህላዊ ልብስ በቀር!
በአንጻሩ በሌላ ጽንፍ ባህል የማይለወጥና የማይቀየር ‹ዶግማ› አድርገውየሚያስቡ አሉ። ባህል ያድጋል፣ ይለወጣል፣ ይሻሻላል ወዘተ። የሰው ልጅ አእምሮ ከዘመን ዘመን እየሰፋና እያደገ የሚሄድ እንደመሆኑ፣ ባህልም አብሮ ሊያድግና ሊለወጥ እንደሚችል መቀበል ግድ የሚለን ጉዳይ ነው። ያንን የማይቀበሉ ግን ጥቂት አይደሉም።
ኹለቱ ጽንፍ የያዙ ጉዳዮችን ማናበብና እኩል ማስኬድ መቻል በብዙ መልኩ የሚያከራክሩንን ጉዳዮች ወደ አንድ ማምጣት ያስችለናል ብዬ አምናለሁ። ዘመናዊነት ሚዛኑ ምንድን ነው? ባህልን ማክበርስ ምን ማለት ነው?

ባህል ሲባል ደርሶ ወደ አእምሯችን ማሳያ ላይ የሚከሰተው ምስል ጎጂው ብቻ ከሆነ፣ ትክክል አይደለም። ግን እርግጥ ነው ጎጂው ባህል ሊስተካከልና ሊቀረፍ ይገባል። ለዚህ ዘመናዊነት ያስፈልገናል። ግን አንድ ማኅበረሰብ በጊዜ ብዛት ሠርቶና ደክሞ ያበጃጀውን ስርዓት፣ ያለጥናት፣ ያለማገናዘብና ትኩረት ሳይሰጥ፣ እንደው በወፍ በረር ፈርጆ አውጥቶ መጣል አግባብ አይደለም።

የሰው ልጅ በአኗኗሩ ማኅበራዊ ስሪት ነው። የሚሠራውና የሚገነባው ማኅበረሰቡ ነው። ይህን ማንነት ወርሶ የራሱን ማንነት ይገነባል። የእኔ የሚለው ስርዓት መኖሩም አፈር የሆነ ሰውነቱ ክብርን እንዲያገኝ ያደርገዋል። ኋላቀር ከሚባለው ዘመን ይልቅ ዘመናዊ በሚባለው በአሁኑ ጊዜ ማንነት ወሳኝ ጉዳይ ሆኗል። እናም ለዛ ነው ማንነትን መጠበቅና ማክበር አስፈላጊ የሚሆነው።

ኢትዮጵያዊ ማንነት በረጅም ዘመናት ሂደት የተገነባ ነው። የመቶና የሃምሳ ዓመት ታሪክ ያላቸው አገራት ሳይቀሩ የሚታወቁበትን ማንነት ገንብተዋል። ‹ኢትዮጵያዊ› ሲባል የራሱ የሆነ መገለጫዎች አሉት፣ ይህም የአገርም መወከያ ነው። ታድያ በዘመናዊነት ጥማት ውስጥ ኢትዮጵያዊነት ቦታው የቱ ጋር ነው?

ፌሚኒዝም በሚል ሥያሜ የሚታወቀው የሴቶች ንቅናቄ ሴቶች የተነፈጉትን መብትና እኩልነት ለማስመለስ ጥሩ የሚባል ርዕዮት ቢሆንም፣ ብዙዎች ግን ሲቀበሉት አይስተዋልም። ለምን? ኢትዮጵያዊነትን እናገኝበታለን ብለው ስለማያምኑ።

ይህ ኢትዮጵያዊነት ሴትን ወደ ማጀት፣ አደባባይ አትውጣ፣ አትችልምና አትሥራ፣ ደካማና ጥገኛ ፍጡር ናት ወዘተ የሚለው ግን አይደለም። ይልቁንም ትዳርን የሚያከብር፣ የልጅ አስተዳደግን በስርዓት የሚቀርጽ፣ ሰውነትን የሚያስቀድም ወዘተ ነው።

የቀደሙ ኢትዮጵያውያንን ማሞገስን የሚቃወሙ ሰዎች አሉ። ዛሬ ትውልድ የሚኮነንባቸውን ነጥቦች ሁሉ ድሮ አልነበሩም ወይ? ብለው የሚጠይቁም አሉ። እውነት ነው ነበሩ። የቀደሙ ኢትዮጵያውያን ሰዎች እንጂ መላእክት አልነበሩም። ነገር ግን ቢያንስ ኢትዮጵያዊ የሆነና ትክክለኛ ስርዓት እንዳለ እኛ ዛሬ ላይ ሆነን ካወቅን፣ በአንዳች መንገድ ይህን ሊያወርሱን ችለዋል ማለት ነው። ወደ እነርሱ ስንጠቁም ግን የነበረውንም አሻራ አጥፍተን ምንም እንዳናስቀር፤ እኛ የበለጠውን የምናሰጋ ነን!
ሊድያ ተስፋዬ

ቅጽ 2 ቁጥር 92 ነሐሴ 2 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here