ፍርድ ቤቱ ጃዋር መሀመድን ጨምሮ በ14 ተጠርጣሪዎች ላይ የአቃቤ ህግ የቅድመ ምርመራ ምስክሮችን ለመስማት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጠ። በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት በልደታ አዳራሽ ጃዋር መሀመድን ጨምሮ በ14 ተጠርጣሪዎች መዝገብ የአቃቤ ህግ የቅድመ ምርመራ ምስክሮችን ለመስማት ችሎት ተሰይሞ የነበረ ቢሆንም፣ አምስት ተጠርጣሪዎች ከህክምና ጋር በተያያዘ ፍርድ ቤት ስላልቀረቡ እነሱ በሌሉበት ምስክሮች ሊሰሙ አይገባም የሚል አቤቱታን ተጠርጣሪዎቹ አቅርበው ነበር።
ፍርድ ቤቱም ጉዳዩን መርምሮ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቶበታል። ሀሙስ ሐምሌ 7/2012 ባዋለው ችሎት ከስምንት የሀገር ውስጥና የውጭ መገናኛ ብዙሃን የተገኙ ጋዜጠኞች ችሎቱን እንዲከታተሉ የተደረገበት የፕላዝማ ቴሌቪዥን አገልግሎት ባለመስጠቱ መከታተል አልተቻለም ነበር።
ሆኖም ከአቃቤ ህግ እና ከተጠርጣሪ ጠበቆች እንደጠቆሙት አቃቤ ህግ ያቀረበውን የምስክርነት ይሰማልኝ ተለዋጭ ቀጠሮን ፍርድ ቤቱ ተቀብሎ በሌሎች ተጠርጣሪዎች ላይ የአቃቤ ህግ የቅድመ ምርመራ ምስክሮችን ለመስማት ለፊታችን ሰኞ ነሐሴ 11/2012 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
ተጠርጣሪዎች ከቤተሰብ ጋር እንድንገናኝ እና ምግብ ቢገባለን የሚል አቤቱታ ማቅረባቸውን ተከትሎም ፍርድ ቤቱ በጥንቃቄ ከቤተሰብ ጋር እንዲገናኙ እንዲደረግ አዟል።
ቅጽ 2 ቁጥር 93 ነሐሴ 9 2012



