የሹመኞች እንቆቅልሻዊ ስንብት

0
1050

ጠንካራ ተቋም በመገንባት ረገድ ከፍተኛ ሆነ እንቅስቃሴ እያደረኩ ነው የሚለው የለውጡ መንግስት በትረ ስልጣኑን ከያዘበት ከመጋቢት 2010 ወዲህ በርካታ ሽግሽጎችን ያደረገ ሲሆን ይህም በበጎ የመኪታይለት እንዳልነበር የየውይይት መድረኩ ሀሳብ ማድመቂያ ሆኖ ከርሟል። ከዚህም በተጨማሪ ደግሞ በተደጋጋሚ ከዚህ ቀደም ታይተው በማይታወቁ ሁኔታዎች ከፍተኛ የሆነ ከፍተኛ ኃላፊዎች መልቀቅ ደግሞ ሌላው የመነጋገሪያ ርዕስ እና ጎራ ከፍሎ ማከራከሪያም ከሆነ ሰንበትበት ብሏል። ወደ ኃላፊነት ስፍራ ሲመጡ በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነታቸው የጎላ እንዲሁም ከመንግስት በኩል በችሎታ እንጂ በፓርቲ አባልነት ሹመት ከእግዲህ ወዲህ አይሆንም ያለውንም ጉዳይ እየተገበረ መሆኑን ማሳያ ተደርጎም የተወሰደበት ወቅት ነበር። ሹመኞችን ድንገተኛ ስንብት በተመለከተም የአዲስ ማለዳው ኤርሚያስ ሙሉጌታ ከፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች እና ከተቋማዊ ስራ አመራር ባለሙያዎች እዲሁም ጥናታዊ ጽሑፎችን በማገላበጥ ሐተታ ዘማለዳ ጉዳይ አድርጎታል።

በኢትዮጵያ ባለፉት ኹለት ዐኣመታት የታዩትን የሽግሽግ የስልጣን እርካብ የሹመኞች መቀያየር በአብዛኞች ዘንድ ትዝብትን የጣለ እና በከፍተኛ ኃላፊነት ደረጃ ተቀምጠው ነገር ግን ቀጣይነት በሌለው ሁኔታ የካቢኔው ሽሽግም ሆነ ከአንዱ መስሪያ ቤት ወደ ሌላው መዘዋወር በውጤታማነት ላይ ጥያቄን ሚያስነሳ ጉዳይ ለመሆኑ ብዙዎች የሚስማሙበት ጉዳይም ነው።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ ካለፉት ረጅም ኢህአዲግ ጉዞ ላይ ታይተው የማይታወቁ ግን ደግሞ በቅርበ ለውጥ በሚል አካሔድ ኢትዮጵያን ለማስተዳደር ወደ አራት ኪሎ የገባው የአብይ መንግስትን ተከትሎ ታዲያ በካቢኔው ውስጥ የተዋቀሩት መንግስት ተቋማት በበርካታ የተለያዩ የስራ ኃላፊዎች እንዲመሩ መደረጋቸው የሚታወቅ ነው።

አብይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ መንበር ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሙገሳን ከተቸሩበት አንዱ የሆነው ግማሽ እና ከዛ በላይ የሆነውን የካቢኔያቸውን በሚኒስትር ደረጃ ግን በግማሽ ሴቶችን ማድረጋቸው አንደኛው ጉዳይ ነበር።

በዚህም ጋር ተያይዞ ታዲያ ኢትዮጵያ በታሪኳ አይታው የማታውቀው የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ፕሬዘዳንት ሴት መሆናቸው ደግሞ አድናቆትን በዓለም አቀፍ ደረጃ የተናኘበት አንዱ እና ዋነኛው ጉዳይ ነው። ሴቶችን ከማብቃት ጋር ብቻም ሳይሆን ወደ ውሳኔ ሰጪነት በማምጣቱም ረገድ የማይናቅ አሰራሮች መከናወናቸውን በርካቶች በዓለም አደባባይ የመሰከሩት ጉዳይ ለመሆኑ መገናኛ ብዙኃን ምስክር ናቸው።

ይሁን እንጂ ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ በተለያዩ ጊዜያት የመንግስት መስሪያ ቤቶችን በመምራት እና ሕዝብን እንዲሁም የመንግስትን ኃለፊነት በመሸከም በተመደቡብ የሚንስትር መስሪያ ቤቶች አልረጋ ባለ ሁኔታ ከፍተኛ የሆነ ዝውውር እና መተካካትም የሚስተዋልበት እንደሆነ ለመታዘብ የሚከብድ አለመሆኑ ደግሞ የዶክተር አብይን ካቢኔ በስፋት ከሚያስተቹበት ሁኔታዎች ውስጥ መሆኑን ይነገራል።

አዲስ ማለዳ በዚህ ጽሑፍ ለመዳሰስ የሞከረችው የካቢኔ የሹምሽር ጉዳይ ወይም የሚኒስትሮች ከአንድ ሚኒስትር መስሪያ ቤት ወደ ሌላ መስሪያ ቤት የመዘዋወር ጉዳይ ሳይሆን በእነዚህ ኹለት ዓመታት ውስጥ በአንጻራዊነት በስፋት ስለሚታየው የስራ ኃላፊዎች የስራ መልቀቅ ጉዳይ ነው።

እምብዛም ሳይነገርላቸው እና በመገናኛ ብዙኃን ሳይሰራጭ በለሆሳስ ከመንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊነት ገሸሽ ብለው በአንድ ዓለም አቀፍ ድርጅት ውስጥ ገቡትን በለውጡ አመራር ዘመን የመጀመሪያው የፌደራ ፖሊስ ኮሚሽነር እና በኋላም ላይ የሰላም ሚኒስቴር ሚንስትር ዲኤታ ዘይኑ ጀማልን ማንሳት ይቻላል።

በርካታ ጸጥታ እና ደኅንነት ተቋማትን በስሩ ያስተዳድራል የሚባልለት ሰላም ሚኒስቴር አብይ አሕመድ ወደ ስልጣን ከመጡበት ጊዜ ጋር ተያይዞ ለመጀመሪያ ጊዜ የተፈጠረ እና የበርካታ ኃላፊነት ባለቤት የሆነ ሚንስትር መስሪያ ቤት እንደሆነ ብዙዎች ይስማሙበታል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ በቀደመው ጊዜ ስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች ኤጀንሲ ምክትል ዳይሬክተር በመሆን ሲያገለግሉ የነበሩት ዘይ ጀማል በለውጡ ማግስት ወደ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራልነት በመዘዋወር ለጥቂት ጊዜያት ካገለገሉ በኋላ ወደ ሰላም ሚኒስቴር በመሔድ ሚንስተር ዲኤታነትን ኃላፊነት ተቀብለው ሲያገለግሉ መቆየታቸው ይታወሳል።

ይሁን እንጂ በአራት የሚኒስቴር ዲኤታ የተዋቀረው ይኸው ግዙፍ መስሪያ ቤት ከአራቱ ዘርፎች ውስጥ አንዱን ሲመሩ የነበሩት ዘይኑ ጀማል ባልታሰበ እና ባልተጠበቀ ሰዓት መልቀቂያቸውን በማስገባት ወደ አንድ አለም አቀፍ ድርጀት ማምራታቸው በቅርብ የሚያውቋቸው ግለሰቦች ለአዲስ ማለዳ ያስረዳሉ።

ዘይኑ ጀማል መልቀቂያ እና ከመንግስት መዋቅር በመውጣት ወደ ሌላ ዓለም አቀፋዊ ድርጅት ማምራት በሕዝብ ዘንድ አልተሰማም፤ አልተስተጋባምም። ከሌሎች በተለየም መልኩ በማኅበራዊ ሚዲያ ወይም ደግሞ በመስሪያ ቤቱ ደረጃ በይፋ ሽኝት አለመደረጉ ደግሞ ጉዳዩን እንቆቅልሽ ማድረጉ አልቀረም።

የዘይኑን መልቀቂያ ማስገባት ተከትሎም በትምህርት ቤት ምገባ መርሃ ግብር ላይ ስማቸው ከፍ ብሎ የሚሰማው ፍሬዓለም ሽባባው ወደ ሰላም ሚኒስቴር ሚንስትር ዲኤታነት መግባታቸውም ይታወሳል። ከዚህ ጋር በተገናኘም በርካታ ግለሰቦች እና የተፎካካሪ ፓርቲ አባላትም ከዚህ ቀደም ምንም አይነት የመንግስት መዋቅር ውስጥ ሰርተው የማያውቁን ሰው መንግሥት መሾሙ አንደምታው ምንድነው የሚል ትችቶችን አሰምተው ነበር።

በሌላ በኩል በኢትዮጵያ ከለውጡ በፊት ባሉት ዓመታት በውል የተለየ እና በይፋ ተሰጠውን የሕዝብ እና መንግስት ኃላፊነትን ባልተመቸ ስራ ከባቢ ውስጥ እንኳን ከመከወን ባለፈ እንዲህ በአደባባይ ስራ መልቀቂያ ሲያስገቡ እንደማይታይ በብልጽግና ፓርቲ ውስጥ ከፍተኛ አመራር የሆኑ እና ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ለአዲስ ማለዳ አስተያየታቸውን ሲሰጡ እንደገለጹት፤

‹‹ሲጀመር ባለፉት ዓመታት ስራ መልቀቂያ ማስገባት እጅግ ሲበዛ ከፍተኛ ጉዳት ሚስከትል እና ከፍ ሲልም ለረጅም አመታት ለዕስር ሚዳርግ ጉዳይ እንደነበር እኮ ኹሉም ሰው የሚያውቀው ጉዳይ ነው›› ሲሉ ይጀምራሉ። በአሁኑ ሰዓት በስፋት ስራ መልቀቂያ ከከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች የሚታየው እንቅስቃሴ በእርግጥም በአደባባይ እና በይፋ መልቀቂያቸውን አስገብተው እና ከነበሩበት የስራ ከባቢ ጋር ተመሰጋግነው መለያየት እኮ ከለውጡ ጋር አብሮ የመጣ ትሩፋት እንደሆነም ያነሳሉ።
‹‹ለውጡ ካመጣቸው ጉዳዮች አንዱ ሰዎች በሜሪት ይሾማሉ፤ ደስ ባላቸው ሰዓት ደግሞ ኃላፊነታቸውን አስረክበው በሰላም ወደ ሚፈልጉበት መስሪያ ቤት በማቅናት መስራት የሚችሉበትን ምቹ እና ሰላማዊ ሁኔታ እንደ ፓርቲ እና እንደ መንግስት መፍጠር ተችሏል›› ሲሉም ይናገራሉ።

ሰላማዊ ስልጣን ሽግግሩን ከዚሁ እየዳበረ እንዲሔድ ከወዲሁ በጅማሬ ደረጃ ሊሰራበት ሚገባው ጉዳይ እዲህ ዓይነት ሐሳብ መሆኑን የሚናሩት የስራ ኃላፊው በተለይም ደግሞ በመንግስት እና በሕዝብ መካከል እንዲሁም ከዚህ ቀደም በመንግስት ስራ ኃላፊነት ለመሳተፍ ፈልገው ነገር ግን ‹‹አንድ ጊዜ ከተገባበት ለመውጣት ያስቸግራል›› የሚል ዕሳቤ ላላቸው እና ብቃታቸውን አገርን እና ሕዝብን ለማገልገል ማዋላ ላልቻሉት ሰዎችም ቀርበው እንዲያግዙ ሚያደርግ መልካም ገጽታንም እንደሚፈጥር ለአዲስ ማለዳ ይናገራሉ።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ካቢኔ ውስጥ አብዛኞቹ ሙያተኞ እና በዕድሜም ወጣቶች መሆናቸው ለስራዎች መቀላጠፍ እና አዳዲስ ሀሳቦች ከማመንጨት ጋር የሚያያዙበት መንገድ እንዳለም ይነገራል። ከእነዚህ የወጣቶች እና ሙያተኞች (ቴክኖክራት) ስብስብ ውስጥ የስራ መልቀቂያን በማስገባት እና የመጀመሪያው የቀድሞው የጤና ሚንስተር ዶክተር አሚር አማን ናቸው።

‹‹ዶክተር አሚር በቋፍ ላይ የነበረውን የጤና ስርኣት ለማስተካከል ያለ ዕረፍት የተጋ ታታሪ ሰራተኛ ነበር›› ይላሉ ዶክተሩን በቅርበት የሚያውቁት የጤና ሚኒስቴር የስራ ኃላፊዎች እና የቅርብ ወዳጆች።

ዶክተር አሚር በለጋነተረ ዕድሜ ወደ ከፍተኛ የመንግስት ስራ ኃላፊነት መጥተው በቆዩበት አጭር ጊዜያትም ከፍተኛ ለውጥን በማምጣት ትልቅ ዕመርታ ያስመዘገቡ እንደሆኑም አዲስ ማለዳ ከጤና ሚኒስቴር እና ከመንግስት እንዲሁም ምንም እንኳን ፓርቲ አባል ባይሆኑም ነገር ግን ከብልጽግና ፓርቲ አመራሮችም ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።

ዶክተር አሚር የኢፌዲሪ ጤና ሚኒስቴርን በሚኒስቴርነትም ሆነ በመካከለኛ ስራ ኃላፊነት ደረጃ ካስተዳደሩት የስራ ኃላፊዎች ውስጥ በዕድሜ እጅግ ለጋው ሚኒስትር እንደነበሩም አዲስ ማለዳ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።

በጤና በኩል በተለይም በአልኮል እና በትንባሆ በኩል በመገናኛ ብዙኃን እንዳይተዋወቁ እንዲሁም የሚጣልባቸውን ኤክሳይስ ታክስ ጭማሪ እንዲኖረው በማድረግ ረገድ ከፍተኛ የሆነ ተጋድሎ ማድረጋቸው እና በተቃራኒው ደግሞ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ የሴቶች ንጽሕና መጠበቂያ ቁሳቁስ ከቀረጥ ነጻ እንዲሆኑ በማድረግ ረገደፍ ከፍተኛ ሚና መጫወታቸው በስራ ዘመናቸው ካስቀመጧቸው አሻራ ውስጥ ይጠቀሳል። በተለይም ደግሞ በሴቶች ዙሪያ የሚሰሩ እና በስርዓተ ጾታ ተሟጋቾች ዘንድ ከፍተኛ ከበሬታንም የቸራቸው ስራ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል።

ከዚህም ባለፈ የቀድሞ የጤና ሚኒስትር ዶክተር አሚር አማን ከግሉ የጤናዉ ዘርፍ ጋር በትብብር በመስራታቸው ላበረከቱት አስተዋጾ ከኢትዮጵያ ጤና ክብካቤ የተለገሳቸውን አንድ ሚሊዮን ብር ለኢትዮጵያ ሥራ ፈጠራ ኮሚሽን ያበረከቱበት የልግስና ስብዕናንም ተላብሰው እንደነበር ማሳያ ነው የሚሉም አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ግለሰቦች አልታጡም።

ዶክተር አሚር መንግስት ከግሉ ዘርፍ ጋር በቅርበትና በትብብር እንዲሰራና በዘርፉ መሻሻሎች በማምጣታቸውና ላበረከቱት አስተዋጾ እውቅና ለመስጠት ተስቦ የተበረከተላቸውን ስጦታ በከፍተኛ ሁኔታ ስራ አጥ ቁጥር ለሚያንገላታት አገራቸው መለገሳቸው አንደኛው መታወሻቸው ሰውነት መለያቸው ነውም ይባልላቸዋል ።
ይሁን እንጂ እንዲህ በከፍተኛ ሞራል እና ሕዝብን የማገልገል ፍላጎት ሲተጉ የነበሩት ወጣቱ ዶክተር ባልታሰበ ሁኔታ ስራ ኃላፊነታቸውን በገዛ ፈቃዳቸው መልቀቃቸውን ሚገልጽ ደብዳቤ በማስገባት ለአጭር ጊዜም ቢሆን የቆዩበትን መስሪያ ቤት በይፋ ተሰናብተዋል።

‹‹ኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚንስትርን አብይ አሕመድን በጤና ሚኒስቴርነት ኢትዮጵያን ሕዝብ እንዳገለግል ዕድልን ስለሰጡኝ በቅድሚያ አመሰግናለሁ›› ሲል ይጀምራል ዶክተር አሚር በወቅቱ የጻፉት የስራ መልቀቂያ ደብዳቤ። አስቀጥለውም እስከ ኃላፊነታቸው ድምዳሜ ድረስ አብረዋቸው ለተጓዙ ስራ በላደረቦቻቸው እና ስላሳኩት በመተጋገዝ ላይ የተመረኮዘ ደረጃ እጅግ ያመሰግናሉ።

በመጨረሻም በሙያቸው እንዲሁም ከነበሩበት ሚኒስትር መስሪያ ቤት ጋር ያላቸው ቁርኝት በዚህ ብቻ እንደማያበቃ እና በሄዱበት ሁሉ ሚንስትር መስሪያ ቤቱን በመወከል ጠንካራ አምባሳደር እንደሚሆኑም በመጠቆም ደምድመዋል። በዚህ ወቅት ከዚህም ከዛም የተለያዩ ውዥንብሮች የተሰሙበት እና በተለይም ደግሞ በማኅበራዊ ትስስር ገጾችም ጽንፍ የያዙ ሀሳቦችን የሚያራምዱ ተንታኞች በአሚር ስራ መልቀቅ ተመረኮዙ ትንታኔዎችንም ሲሰጡ ተስተውለዋል።

በወቅቱም ተሰናባቹ ዶክተር ሚንስትር ይፋዊ መልቀቂያቸው ይህን ያህል ጎራ ለይቶ የተለያዩ ትንታኔዎችን ሲያሰጥ ወደ ሕዝብ በመውጣት ተጨማሪ ማብራሪያቸውን ከመስጠት መቆጠባቸው ደግሞ ጉዳዩን በሚመለከት እየተባለ ያለው ጉዳይ ዕውነት ሊሆንም ላይሆን ይችላል በሚል መንታ መንገድ ላይ እንደጣለም የሚታወስ ነው።
ይህን በሚመለከት ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉት ብልጽግናው ከፍተኛ ስራ ኃላፊ እንደሚሉት አሚርም ሆነ ሰሞኑን በተከታታይ ስራ መልቀቂያ ማስገባታቸው ከተሰማው ስራ ኃፊዎች ውስጥ እንደ መንግስት መሔዳቸው ቢያጎድልብንም ነገር ግን ወደ ተሻለ ደረጃ ነው እና ሚሔዱት ለሚገጥማቸው ዕድል መልካሙን እንመኝላቸዋለን።

ይህን ማድረግ ከተነሳንበት አገረ መንግስትን ከመገንባት አኳያ ከፍተኛውን ድርሻ ሚይዘው ሰዎች በነጻነት ሰርተው ሕዝብን እና አገርን አገልግለው ባሻቸው ጊዜ ደግሞ ለቀው ወደ አሰቡበት መሄድ የሚችሉበትን መንገድ ማመቻቸት ስለሆነ ነው ይላሉ። አዲስ ማለዳም ይህን በሚመለከት ባደረገችው መረጃ መሰብሰብ ስራ የቀድሞው የጤና ሚኒስቴር ሚንስትር ዶክተር አሚር አማን ወደ አገረ አሜሪካ በማቅናት በባለጸጋው ዋረን ባፌት ፋውንዴሽን ውስጥ በከፍተኛ አማካሪነት ደረጃ በመቀጠር ስራ መጀመራቸውም ታውቋል።

በአሚር አማን መልቀቂያ አንድ ሰሞን መነጋገሪያ በኋላ ወደ ነባሩ ዑደት እና በአዲስ እና ሌላ ጠንካራ እንስት መመራት የጀመረው ጤና ሚኒስቴር በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተከሰተው እና በኢትዮጵያም ጭቃ ጅራፉን ማሳረፍ በጀመረው ወረርሽኝ ምክንያት ነገር ዓለሙን ወደዛው ማድረግ ችሎ ነበር።

ዶክተር አሚር አማንን የሸኘው የጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ መንግስትም በማስቀጠል በእርግጥም ወራቶች ተቆጥረው ነበር፤ ከሕወሓት ጋር ባላቸው ቁርኝት እና አባልነት ካሉበት እምብዛም ሳይነኩ ሰነበቱት የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ኬሪያ ኢብራሒም ድንገት መምራት ነበረባቸውን ስብሰባ ሳይታደሙ በይፋ ከስራ ኃላፊነታቸው መልቀቃቸውን አስታወቁ።

በእርግጥም የብልጽግና ፓርቲ አገር ማስተዳደር ከጀመረበት ጊዜ ወዲህ ከኃላፊነታቸው መልቀቅ ጋር በተያያዘ ግልጽ ምክንያትን ማስቀመጥ የቻሉት ኬሪያ ኢብራሒም ናቸው። የመሐል አገር ፖለቲካ እምብዛም ያልጣማቸው ኬሪያ በስራ ቦታ ያለባቸውን ጫና እና ልክ ያልሆነ አሰራር ባሉት ምክንያት ስራቸውንም ለመልቀቃቸው ምክንያት እንደሆነ በመግለጫቸው እንዲህ ሲሉ ተናግረዋል ‹‹ለሕገ መንግስቱ፣ ለሕዝቦች እና ለሕሊናየ የገባሁትን ቃል ኪዳን ለማክበር ስል በፈቃዴ ከኃላፊነቴ ለቅቄያለሁ›› ሲሉም በግልጽ ተናግረዋል።

ከአንድ ወር በፊትም አንድ ዜና ከወደ ኢትዮጵያ ኢንያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር የሆኑትን አምባሳደር ፍጹ አረጋን በመተካት ወደ ኮሚሽኑ መጡት በማኅበራዊ ትስስር ገጾች በተለይም በትዊተር ከፍተኛ የሆነ ተሳትፎ ያላቸው አበበ አበባየሁ በግል ጉዳይ በገዛ ፈቃዴ ስራን መልቀቄን አስታውቃለሁ የሚል መንፈስ ያለው ስራ መልቀቂያቸውን ማስገባታቸውን ይፋ አደረጉ።

በዚህ ወቅትም እጅግ ለበዛው የተንታኞቸች እና መላ ምቶችን ለሚያስቀምጡ ግለሰቦች ሌላ አጀንዳ ሆኖ ሰንብቶም እንደነበር ኹላችንም የታዘብነው ጉዳይ ነው። በኮሚሽነር አበበ ከኃላፊነት መልቀቅ እና ከኮሚሽኑ መሰናበትን ተከትሎ በለጋ ዕድሜዋ ከፍተኛ ስራ ኃላፊነትን ተሸክማለች ስትባል የነበረችው ቀድሞዋ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ሌሊሴ ነሚ በመተካት ኮሚሽር መሆናቸው ታውቋል።

አዲስ ማለዳ ኮሚሽነሩን ለማግኘት ያደረገችው ተደጋጋሚ ስልክ ጥሪ እና የሰደደቻቸው አጭር የጽሑፍ መልዕክቶች ሳይሳኩ ቀርተዋል። ይህ አጋጣሚ በኹሉም ተሰናባች የመንግስት ስራ ኃላፊዎች ዘንድ መፈጠሩ ደግሞ በጉዳዩ ላይ ከግል ጉዳያቸው ባለፈ ሌላ ምክንያት ለመኖሩ ጥርጣሬን የሚፈጥር ጉዳይ መሆኑ ሊጤን ይገባል።

የመልቀቃቸውን ዜና ከተሰማበት ሰኣት አንስቶ ተለያዩ መረጃዎች ሲወጡ የነበረ ሲሆን ኮሚሽነር አበበ አበባየሁ ከኃላፊነታቸው ተነስተው ወደ ዓለም አቀፉ ቁጥር አንድ ባለጸጋ ቢልጌት ፋውንዴሽ ማምራታቸው ታውቋል።

አበበ አበባየሁ ወደ መንግስት የኃላፊነት ስፍራ ከመምጣታቸው በፊትም በግሉ ዘርፍ ሙያዊ አግለግሎት መስጠታቸው የሚታወቅ ሲሆን በፖሊሲ አወጣጥ ዙሪያም የራሳቸው ተሳትፎ በተለይም ደግሞ ካላቸው ሕግ ዕውቀት ጋር ተያይዞ በርካታ ማማከር ስራ ላይም ሲሰሩ እንደነበር የግል ማኅደራቸው ይገልጻል።

በአፍታ ቀድሞው የተባሉት ኮሚሽነር አበበ አበባየሁ የጠቅላይ ሚንስትር አብይ አሕመድ የሕግ አማካሪም በመሆን ያገለገሉ ሲሆን ፍጹም ግል በሆነ ምክንያት ስራቸውን እንደለቀቁ አስታውቀዋል። ከአበበ አበባየሁ ከኃላፊነት መልቀቅ በኋላ ታዲያ ኹለት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በሰዓታት ልዩነት የስራ መልቀቂያ ማስገባታቸውም ነው የተነገረው።

የመጀመሪያው የስራ ፈጠራ ኮሚሽን ኮሚሽነር የነበሩት ዶክተር ኤፍሬም ተክሌ ሲሆኑ ቀጣዩ ደግሞ ስትራቴጂክ ጥናት ተቋም ዋና ዳይሬክተር በመሆን ሲያገለግሉ ነበሩት ቀድሞው ጋዜጠኛ በኋላም ፖለቲካ ተንታኝ እንዲሁም ዓለም አቀፍ አጥኚው ሀሌሉያ ሉሌ ሌላኛው ከፍተኛ ስራ ኃላፊ መሆናቸው ታውቋል።

ስራ ፈጠራ ኮሚሽን ኮሚሽነር የነበሩት እና በሙያቸው የሕክምና ዶክተር የሆኑት ኤፍሬም ተክሌ በስራ ፈጠራ ኮሚሽን ወደ ኹለት ዓመት ገደማ ለሚሆን ጊዜ ያገለገሉበትን ስራ ፈጠራ ኮሚሽንን ዓመታዊ የኮሚሽኑን የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ባቀረቡበት ማግስት መልቀቂያቸውን ማስገባታቸው በበርካቶች ዘንድ ጥርጣሬን ፈጥሯል።

በተለይም ደግሞ ሪፖርቱ ፍጹም ተጋነኑ ቁጥሮች ታይተውበታል በሚል በርካቶች በተለያዩ የማኅበራዊ ትስስር ገጾች እና መገናኛ ብዙኃን ሲነጋገሩበት መቆየታቸው የሚታወስ ሲሆን የመነጋገሪያው ርዕስ ሳይበርድ የዶክተር ኤፍሬም ስራ መልቀቂያ ማስገባት ደግሞ በሪፖርቱ ላይ ከፍተኛ የሆነ ትኩረት እንዲሳብ ማድረጉን ለአዲስ ማለዳ አስተያየታቸውን የሰጡ ትንታኞች ይናገራሉ።

በተለይም ደግሞ በሪፖርቱ ላይ በተጠናቀቀው የ2012 በጀት ዓመት ውስጥ ከፍተኛ ከሦስት ሚሊዮን በላይ የስራ ዕድል መፍጠር እደተቻለ መናገራቸው አገሪቱ በኮቪድ እና ሌሎች ተጓዳኝ ምክንያቶች ምጣኔ ሀብቷ በተዳከመበት ወቅት እንዲህ አይነት ሪፖርት መታየቱ ጥናት ሚያስገልገው ጉዳይ መሆኑን በግልጽ መናገራቸው የሚታወስ ነው።

ዶክተር ኤፍሬም ከወራት በፊት ከዚሁ በተቃራኒ ኮቪድ ወደ አገር ውስጥ መግባትን ተከትሎ በኹሉም ሴክተሮች ላይ የሚሳርፈውን ቻና በመመርኮዝ በቀጣይ ሦስት ወራት በኢትዮጵያ ከሦስት ሚሊዮን በላይ ዜጎች ከስራቸው ሊፈናቀሉ እንደሚችሉ መተንበያቸው እና የአሁኑ ሪፖርታቸው ሊታረቁ የማይችሉ ሀሳብ መሆናቸው ደግሞ ከዶክተሩ በገዛ ፈቃዳቸው የመልቀቅ ውሳ ጋር ሊያያዝ የሚችልበት አዝማሚያ መኖሩም ሳይነሳ የማይታለፍ ጉዳይ ነው።

በሌላ በኩል ደግሞ ከዶክተር ኤፍሬም ጋር በተመሳሳይ ወቅት ከኃላፊነት የመልቀቅ ዜና የተሰማባቸው ኃሌሉያ ሉሌ እንደ ምንጮች ገለጻ ከኹለት ወራት በፊት መልቀቂያ ማስገባታቸው እና ይህም ደግሞ በስራ ከባቢ ላይ ምቹ ያልሆነ ሁኔታ በመፈጠሩ መሆኑን በመልቀቂያ ጽሑፋቸው ላይ አካተዋል። ከሌሎች ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በተሻለ መልኩ የስራ መልቀቂያቸውን ምክንያት አብራርተውታል የሚባልላቸው ኃሌሉያ የስራ ከባቢ ምቹ አለመሆን ማለት ምን ማለት እንደሆነ ሙያዊ ትንታኔያቸውን ባለሙያዎች ያስቀምጣሉ።

በስራ አመራር ዘርፍ አከፍተኛ አማካሪ ሆኑት እና ለአዲስ ማለዳ አስተያየታቸውን የሰጡት አላምረው ሞገስ (ዶ/ር) እንደሚሉት የስራ ከባቢን ምቹ በማድረግ ረገድ ሙሉ ኃላፊነት ያለው አንድ ተቋም አመራር ነው ይላሉ።

አያይዘውም ምቹ በማድረግ ረገድ እንቅፋት በሚገጥመው ጊዜም አፋጣኝ እርምጃን በመውሰድ የአንድን ተቋም አወቃቀር እና ለስራ ምቹ በማድረግ አመራሮች በራሳቸው አምሳል ተቋምን መፍጠር ይችላሉ ሲሉም ይናገራሉ። በመሆኑም ኃሌሉያ ስለ ስራ ቦታ እንደምክንያት ያነሱት ጉዳይ እምብዛም የሚያሳምን እንዳልሆነም ያራራሉ።

ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ በሪፖርተር ጋዜጣ ከፍተኛ አዘጋጅ የሆኑት እና የካበተ ልምድ ያላቸው ጋዜጠኛ ነአምን አሸናፊ እንደሚሉት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የምንመለከተውን የከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች መልቀቅ በተመለከተ ሰዎች (ቶክኖክራት) ከመሆናቸው ጋር ተገናኝቶ በፖለቲካ ውስጥ ባለመግባታቸው ተጽአእኖ ሊደርስባቸው እንደሚችል ያነሳሉ።

ግምታቸውን ሲያስቀምጡ ምንም እንኳን በመስሪያ ቤታቸው ውስጥ ከፍተኛ የስ ድርሻ ወይም ኃላፊነተር ስፍራ ላይ ቢቀመጡም ነገር ግን ከስራቸው ሆነው በሚሰሩ ግን የፖለቲካ አባላት የሆኑ ሰዎች ሰራዎቻቸውን ሊያበላሹባቸው ወይም ላይታዘዟቸው የሚችሉበት አጋጣሚዎች ሊፈጠሩ ስለሚችሉ ሰዎች በመጀመሪያ ለመስራት አስበው የመጡበትን ሞራል በማዳከም ለስራ መልቀቃቸው ዋነኛ ምክንያት ወይም አንዱ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ይጠቁማሉ።

በእርግጥም ነአምንን ሀሳብ የሚጋሩት አላምረው ‹‹አንድ ኃላፊ የመስሪያ ቤቱን ከባቢ ምቹ ለማድረግ ትልቅ ኃለፊነት እና የስራ ድርሻ ቢኖረውም ከታች ኃላፊውን ሀሳብ ተቀብሎ የሚፈጽም እና ሚተገብር ከሌለ ተቋማዊ እንቅስቃሴው ወይም ለስራ ምቹ መሆን አዝማሚያው ምንም ሊሆን አይችልም›› ሲሉ ይናገራሉ። አላምረው ቀጥለውም ‹‹በአሁኑ ሰዓት በአገር ደረጃም እየሆነ ያለው ጉዳይ ይኸው ነው።

በጠቅላይ ሚንስትሩ በኩ የሚቀነቀኑ አገራዊ አንድትን የሚፈጥሩ እና በዜጎቿ መፈቃቀድ ላይ ተመስርታ የቆመች አገርን አውን ለማድረግ በሚተጋበት ወቅት ከታች በየደረጃው ያለው የስራ ኃላፊዎች ተባባሪ ካለመሆናቸውም በላይ በተቃራኒው ከመስራታቸው ተነሳ ኢትዮጵያ ባለፉት እና በአሁን ሰዓት እየሆነች ያለው ጉዳይ መመልክት ይቻላል›› ሲሉም በምሳሌ አገርን እንደ ተቋም በመመሰል ይናገራሉ።

ይሁን እንጂ እንደ አላምረው ገለጻ፤ በከፍተኛ ሁኔታ የከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ከስፍራቸው መልቀቅን ተከትሎ በተቋማት ላይ የተቋማዊ ባህል ለውጥ ሊኖር ስለሚችል እና ይህም ደግሞ በብዛት ተቋማትን እንደገና ከጅማሬ ሊመልስ ሚችል እና በአዙሪት ውስጥ ሊከት የሚችል በመሆኑ ሊታሰብበት እና የለቀቁትን ስራ ኃላፊዎች ሌጋሲ ማስቀጠል የሚቻልበት አካሔድ ቢኖር መልካም እንደሚሆንም በመግለጽ ሀሳባቸውን ይገልጻሉ።

በሌላ በኩል ደግሞ ሰራተኞቸች በአንድ ተቋም ውስጥ ሊለቁባቸው የሚችሉ ምክንያቶችን የሚዘረዝረው እንግሊዛዊው የተቋማዊ ስራ አመራር እና አስተዳደር ተንታኝ ጂም ስሚዝ እንደሚለው በርካታ ምክንያቶች ሰራተኞችን በድንገት ከስራ ገበታቸው እንዲለቁ እና መልቀቃቸውንም ድነገተኛ ሊያደርጉ የሚችሉ ጉዳዮችን ይዘረዝራል።
በዚህም ረገድ ቀድሞ ነበራቸው እና ለሚሰሩበት ወይም በመጀመሪያ ደረጃ ሊሰሩበት ላሰቡበት ተቋም ከፍተኛ ግምት ኖሯቸው በኋላ ግን ገብተው ሲመለከቱት እንደጠበቁት ሳያገኙት ሲቀሩ አንደኛው ለመልቀቃቸው ምክንያት ሊሆን አንደሚችል ይናገራሉ።

ከዚህም ባለፈ ደግሞ በሚያገኙት ጥቅማ ጥቅም እና ለግል ሕይወታቸው ከሚሰጡት ጊዜ ጋር ተያይዞ የሚመጡ የግል ጥያቄዎች ስራቸውን ሊለቁ የሚችሉበት አጋጣሚ እንደሚፈጥርም ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ተቋማት ሰራተኛ ቁጥርን በቀነሱ ሰዓት ደርቦ የሚሰሩ ስራዎችን በመስራት እና ለግል ጉዳይ ጊዜ ማጣት ትልቁ ችግር እንደሚሆንም ይጠቀሳል። ከዛም ባለፈ ከፍተኛ ስ አመራሮች እደፈለጉት ውሳኔዎችን ማሳለፍ ሳይችሉ መቅረታቸውም ከኃላፊነታቸው ለመልቀቀ ግንባር ቀደም ጉዳይ ነው ሲሉም ጂም ስሚዝ በጽሑፋቸው ያትታሉ።
እዚህ ላይ ግን መታወቅ ያለበት የውሳኔ ማሳለፍ ጉዳይ በስራ አመራሮች ድክመት ብቻ ላይሆን የሚችሉባቸው አጋጣሚዎች መኖራቸው የሚጠቀስ ሲሆን በተለያዩ ውስጣዊ እና ውጫዊ ምክንያቶች ውሳኔዎች እንዳይተላለፉ የሚያደርጉ እና የስራ አመራሮቸችንም ስራ ፍላጎት የሚቀንሱ እንደሚሆኑ ጥናቶች ያሳያሉ። በተለይም ደግሞ ፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነት ካለ ደግሞ የአንድ ተቋምን ስራ ኃላፊዎች በተለይም ደግሞ ከፖለቲካ ሹመት ውጭ የሆኑትን በአጭር ጊዜ ስልጣናቸውን ወይም ኃላፊነታቸውን እንዲለቁ የሚያደርግ ጉዳይ እንደሚሆንም ስሚዝ በጽሑፉ ይናገራል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ ታዲያ በኢትዮጵያ ከለውጡ ማግስት ወደ መንበር በመምጣት ሕዝብን እና የመንግስትን ኃላፊነት ለመወጣት ትልቅ አደራ የተቀበሉ ነገር ግንበዛ ከተባለ ኹለት ዓመታትን ለመድፈን ጥቂት የቀራቸው የስራ ኃላፊዎች ኹሉም ሊባሉ በሚችሉ ሁኔታ (ሙያተኞች) በአብዛኛው አጠራር ‹‹ቴክኖክራትስ›› በገፍ ለመልቀቃቸው ጉዳዩን ከላይ የተጠቀሱት ለመሆናቸው በአንድም በሌላም ጉዳይ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ።

በተለይም ደግሞ አላምረው እንደሚሉት የስራ ኃላፊዎች የመልቀቂያቸውን ዜና ይፋ ካደረጉት የመልቀቂያ ወረቀት ባለፈ አለመናገራቸው ፖለቲካዊ ውሳኔ ሊኖር እንደሚችል እና በዚህም ምክነያት ለመናገር አለመድፈራቸው አንዱ ማሳያ ሊሆን እንደሚችልም ያስቀምጣሉ።

ቅጽ 2 ቁጥር 93 ነሐሴ 9 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here