‹ተናጋሪዎች› ዝም በሉ፤ ዝም ያላችሁ ተናገሩ

0
562

ተቋማትን ለመገንባት እና ጠንካራ አገረ መንግስትን ለማቆም በሚል መልካም በሚመስል ግን ደግሞ ገደብ ባልተበጀለት አካሔድ በርካታ ጥፋቶች ሲሰነዘሩ እና በንጹሀን ዜጎች ላይ ከፍተኛ የሆነ ዕልቂት ሲካሔድ መታዘብ የዕለት ተዕለት ድርጊት ከሆነ ዋል አደር ብሏል። በእርግጥ በለውጥ ንፋስ ተገፍቶ አገር ከጭቆና ልትወጣ እና ወደ አንጻራዊ ዲሞክራሲ እንድትገሰግስ በኩላቸውን ድርሻ በመወጣት አገርን እና ሕዝብን ለማገልገል ወደ ፊት የመጣው አመራር ከመጣበት እና ከተነሳበት ወቅት አንጻር ከፍተኛ የሆነ ተግዳሮች ቢያጋጥሙት ባይገርምም ነገር ግን አፍንጫው ስር በሚደሰኮሩ ያልተኖረባቸው ታሪኮች ግን አሁንም የጥቃት መነሻዎች እየሆኑ ይገኛል።

ከመጀመሪያው ወቅት ጀምሮ በዚች አገር ኹለት ኣይነት መንግስት ነው ያለው በሚል በመገናኛ ብዙኃን ሲለፈፍ መንግስት ከጀርባው ያሰበው ነገር ለሕዝብ ግልጽ ባይሆንም ነገር ግን ዝምታን በመምረጥ ቀስ በቀስ እየጎለበተ ለመጣው የስርዓት አልበኝት እና የዜጎች ደኅንነትን አደጋ ላይ መጣልን ያስከተለ ጉዳይ መሆኑ አይነተኛ ሚና ለመጫወቱ የማይካድ እንደሆነ አዲስ ማለዳ ትገነዘባለች።

በእንቁላሉ ጊዜ ያልተገታው ስርዓት አልበኝነት በርካቶችን ለሞት፣ ለንብረት መውደም እና ከቤት ንብረት ለመፈናቀል ለዳረገው የቅርብ ጊዜው ድምጻዊ ሀጫሉ ሁንዴሳ ሕልፈት ድረስ መድረስ ችሏል። በዚህም ብቻ ሳይበቃ አሰቃቂ፣ ለሰው መናገር የማይመች፤ ማሰብም የማያስፈልግ ነው የተባለት በጠቅላይ ሚንስትሩ የተገለጸ ድርጊት መፈጸሙ የእነዚህ ኹሉ የተንከባለለ ድምር እንደሆነ ማሰብ ያስፈልጋል።

በዚህ ብቻ ሳይበቃ ደግሞ ከድምጻዊው ሞት በኋላ መርገብ ያቃተው እና አንዱ ሲረግብ ሌላው እያፈሰሰ ያለበት ወቅት ላይ ታዲያ በአንድ በኩል በገዢ ፓርቲ ውስጥ ሆነው ጉዳዩን ሲያራግቡ የሚገኙ የስራ ኃላፊዎች በሰዎች ሕይወት እና ንብረት ላይ መቀለዳቸውን እንዲያቆሙ አዲስ ማለዳ ታሳስባለች። በተለያዩ አካባቢዎች በሚቀሰቀሱ ችግሮች እና በሚጠፋው ንጹሀን ሕይወትና ንብረት ላይ ዕጃቸው እንዳለበት ታመኑ ስራ ኃላፊዎች ያውም በመንግስት መዋቅር ውስጥ ሲሰሩ ነበሩ ሰዎች ቁጥራቸው ቀላል አለመሆኑ አዲስ ማለዳ ትታዘባለች። ይህም ታዲያ ገና በማለዳው ባልተወሰዱ ዕርምት ዕርምጃዎች ምክንያት እዚህ ለመድረሱም ምክንያት እንደሆኑ ሊታወቅ ይገባል።

እነዚህ በመንግስት መዋቅር ውስጥ ሆነው በማን አለብኝነት ሲናገሩ እና በአመራር ላይ ላለው ለራሳቸው መንግስት ጸር የሆኑ ከፍተኛ መንግስት ኃላዎቸችም ሀይ ሊባሉ የሚገባው ከአሁኑ ሰዓት ጀምሮ ሊሆን ይገባል ስትል አዲስ ማለዳ ታስገነዝባለች። ከሰሞኑ ኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ የኦሮሞ ልሒቃንን ከሰባት ወር በፊት ሰብበው ተናግረዋል የተባለው መረጃ በማኅበራዊ ትስስር ገጾች ሲዘዋወር እና በርካቶችን እንዳስከፋ መታዘብ ተችሏል።

ከዚህም ባሻገር ነሐሴ 5/2012 ጀምሮ በ6/2012 የተደመደመው የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ውይይትም በዚህ ዙሪያ ሰፊ ውይይት ማድረጉ የተሰማ ሲሆን በውይይቱ ማጠቃለያ ላይም የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ በባህር ዳር ከተማ በመገነት የተባለው ነገር ብልጽግናን ወይም ኦሮሚያን ብልጽግናን የማይወክል ከመሆኑንም በላይ ርዕሰ መስተዳደሩ ማለትም ሽመልስ አብዲሳ የሚገመገሙበት ጉዳይ መሆኑንም ይፋ ማድረጋቸው ይታወቃል።

ለውጡ ዋና አቀንቃኝ ናቸው ከሚባሉት የብልጽግና ዋና አመራር የሚባሉት ሽመልስ አብዲሳ በግልጽ ቋንቋን መሰረት ባደረገ እና ‹‹አማረኛን ገለነዋል፤ ኦሮምኛን እያሳደግን ነው›› በሚል የተናገሩት ሕዝብ እና ሕዝብን ከማቃቃር ባለፈ ሕዝብ በመንግስት ላይ ከፍተኛ የሆነ አመኔታ እንዳይኖረው የሚያደርግ ድርጊት በመሆኑ ሊታረም ይገባል ስትል አዲስ ማለዳ ታስገነዝባለች።

ሽመልስ አብዲሳ በ2012 መስቀል አደባባይ ላይ ኢሬቻ በኣል በሚከበርበት ወቅትም አንድን ቡድን በሚያጥላላ መልኩ ንግግር በማድረግ በርካቶችን ሲያስቆጣ መቆየቱ ሚታወስ ነው። በዚህም ዝም ተብሎ በመታለፉ ወይም ተንከር ያሉ ድርጅታዊ እርምጃዎች ባለመወሰዱ ዘፈቀደ ንግግሮች አሁንም ወደ ሕዝብ መድረሳቸው ሕዝብን የሚያቃቅር በመሆኑ ዝም ተብሎ ሊታለፍ አይገባም ስትል አዲስ ማለዳ ታሳስባለች።

ከዚህም በተጨማሪ እስከዛሬ በአደባባይ እያወሩ ለሕዝብ አብሮነት ምንም ፋይዳ ያልነበራቸው እና በተቃራኒው ሕዝብን ወደ ግችት የሚመሩ ግለሰቦች አንደበታቸውን እንዲገሩ እና በአንጻሩ ደግሞ ዝምታን መርተው የአገር አንድነትን ባለመናገራቸው እንደጠበቁ የሚሰማቸው ሰዎች ወደ አደባባይ በመውጣት አገርን የሚያቆም ሀሳባቸውን እንዲሰነዝሩ አዲስ ማለዳ ጥያቄ ታቀርባለች። እስከዛሬው በመናገር ነፃነት ሰበብ በርካታ አፍራሽ ንግግሮች የተሰሙበት የኢትዮጵያ ሰማይ ከዚህ በኋላ ግን ሕዝብን ወደ ዕድገት እና አንድነት የሚያሸሽ እንጂ የማይከፋፍሉ ንግግሮችን ወይም ተናጋሪዎችን ማግነን ይኖርበታል ስትል አዲስ ማለዳ ትናገራለች።

በአራቱም ኢትዮጵያ ማእዘን አንድነትን ጠብቀው ፤ በአገር እና በሕዝብ ላይ ተስፋ ሳይቆርጡ የቆዩ ‹‹ብንናገር ሰሚ አናገኝም ›› በሚል ምጡቅ ሀሳባቸውን ሰበሰቡ ግለሰቦች ወደ አደባባይ መምጣት እንደሚኖርባቸው ዕሙን ነው። ጽንፍ ወጣን ጉዳይ በሌላ ጽንፍ በያዘ እና ‹‹እኛ እና እነሱ›› በሚል ጎራ ተለይቶ በመጠዛጠዝ ሳይሆን ከረረ ዘውጌነትን በበሰለ አገራዊ ስሜት በመሸፈን እያቆጠቆጠ ያለውን ጽንፈኝነት ጎምርቶ ፍሬ ሳያፈራ ከወዲሁ ሚቀጭበት መንገድ እንዲፈጠር አዲስ ማለዳ ታሳስባለች።

ከዚህም ባለፈ መንግስት በውጭ ያሉትን ወይም በነጻነት ሰበብ ሚናገሩትን የማይመርጡት ላይ ዕርምጃ ከመውሰዱ ጎን ለጎን በውስጡ ያሉትን ሕጸጾች ነቅሶ በማውጣት ተጀመረውን የዲሞክራሲ ግንባታ አካሔድ ማጎልበት እንደሚኖርበትም አዲስ ማለዳ ታሳስባለች። በቅርቡ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ በኦሮሚያ ክልል ከተከሰተው አለመረጋጋት ጋር ተያይዞ በቁጥጥር ስር ከዋሉት በብዙ ሽሕ ሚቆጠሩ ሰዎች ውስጥ ከ1 ሽ በላይ የሚሆኑት በክልሉ ውስጥ የመንግስት መዋቅር ውስጥ የሚሰሩ ሰዎች እና የጸጥታ ሰራተኞች መሆናቸው ጉዳዩን እጅግ አሳሳቢ ያደርገዋል።

ለዚህ መነሻው ደግሞ ገና ከጅምሩ ብልጽግና እንደ ፓርቲ እና አገር እንደሚያስተዳድር መንግስት በአባላቶቹ ላይ ስርጸት በበቂ ሁኔታ አለመስራቱ ጉዳዩን ስር እንዲሰድ እንዳደረገው መታዘብ ትልቅ ምርምር የሚተይቅ ጉዳይ እንዳልሆነ አዲስ ማለዳ ትረዳለች። የተሰሩት አገራዊ እና መንግስታዊ ስራዎች አዲስ ማለዳ ብታደንቅም ነገር ግን አሁን እንደ አገር ለደረስንበት ጥፋት ደረጃ ግን ትልቅ ኪሳራ መሆኑን አዲስ ማለዳ ትገነዘባለች።

እስካሁን ለባከነው እና በባከነው ጊዜ ላይ ተክዘን መቆም ሳይሆን መናገር ያለባቸው ሰዎች ወደ ፊት በመምጣት እና በመናገር ሕዝብን በማንቃት እንዲሁም በማረጋጋት ረገድ ከፍተኛ ሚና እንዲጫወቱ እና በመንግስት መዋቅር ላይ ሆነው እንደፈለጉ በመናገር እና አንድን ወገን ለማስደሰት ሌላው ማስከፋት ግን ከአንግዲህ ወዲህ ሊቆም ይገባል ስትል አዲስ ማለዳ ታሳስባለች። በተለያዩ አካባቢዎች የሚከሰቱ እዚህ ግባ የማይባሉ ግጭቶችን ችላ ባለማለት እና ትክክለኛው መረጃንም ወደ ሕዝብ ማድረስ ከሚፈጠረው ውዥንብር እና ተዛባ መረጃ ለመታደግ አይነተኛ መፍትሔ መሆኑንም አዲስ ማለዳ ትገነዘባለች።

በመሆኑን ከዚህ በኋላ ኹሉም ከሕግ እና ከኢትዮጵያ በታች ነው በሚል ለሚነገረው መፈክር በተግባር ማሳያ የሆኑ የዕርምት ዕርምጃዎች ነገ ዛሬ ሳይባል ሊወሰዱ ይገባል ስትል ጋዜጣዋ ሀሳቧን ትደመድማለች።

ቅጽ 2 ቁጥር 93 ነሐሴ 9 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here