አሸንዳና ማህበራዊ ቱሩፋቶቹ

0
2599

አገራችን ኢትዮጵያ የብዙ ባህላዊ ክውን ጥበባት እና ሀይማኖታዊ ስርዓቶች ባለቤት ናት። ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ ትርጓሜን ይዘው በድምቀት የሚከበሩ በዓላትም አሏት። እነዚህ ክዋኔዎችም በተለያየ ወቅት እና ጊዜ የሚከናወኑ ሲሆኑ በተለይ በክረምት ወራት የሚከናወኑት አሮጌው ዓመት አልፎ በአዲሱ ሊተካ የቀናቶች እድሜ መቅረቱን፤ የአሮጌውን ዘመን መገባደድ እያበሰሩ የአዲሱን ዘመን መግባት በአዲስ ተስፋና ስሜት እንድንቀበለው ያደርጋሉ።

ከእነዚህ ክዋኔዎች መካከል አሸንዳ/አሸንድዬ ተጠቃሽ ነው። ይህ የሴቶች ውበት፣ነጻነት እና ክብር ማሳያ ተደርጎ የሚወሰደው በዓል ሴቶች በተለይም ለትዳር ያልደርሱ ልጃገረዶች በተለያዩ የውበት መጠበቂያዎች ተውበው፣ ፀጉራቸውን በወግ እና በስርአቱ መሰረት ሹሩባ ተሾርበው፣ በልዩ ልዩ ባህላዊ አልባሳትና ጌጣ ጌጦች አምረውና ደምቀው በየአደባባዩ የሚታዩበት ነው።

በጋራ ሆነው ከበሮ በመምታት የሚጨፍሩበት፣ የመሰላቸውን ሐሳብ በዜማና ግጥሞቻቸው በነፃነት የሚገልፁበት በዓል በመሆኑም በበዓሉ አክባሪዎች ዘንድ በተለየ ጉጉት የሚጠበቅ እና በልዩ ስሜት የሚከበር በዓል እንደሆነም ይገለጻል።

መጠሪያ ሥሙን በሚመለከት በአገራችን በክረምት ወቅት ከሚበቅለው ቅጠለ ሰፋፊና ረጅም ተክል እንደወረሰ የሚነገርለት ይህ የአሸንዳ በዓል፣ በአገራችን በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በተለይም በትግራይ እና አማራ ክልሎች ላይ በስፋት እና በድምቀት ከነሐሴ 16 እስከ ነሐሴ 21 ባለው ጊዜ ውስጥ በልዩ ሀይማኖታዊ እና ትውፊታዊ ክዋኔዎች ታጅቦ ይከበራል።

በዓሉ በአብዛኞቹ የትግራይ አካባቢዎች ‹አሸንዳ›፣ በአክሱም እና አካባቢዋ ‹ዓይነ ዋሪ›፣ በዋግ ኽምራ ‹ሻደይ›፣ በሰሜን ወሎ/ ላስታ ‹አሸንድዬ›፣ በቆቦ ‹ሶለል› እንዲሁም በጎጃም ‹እንግጫ ነቀላ› የሚሉ ሥያሜዎችን በመያዝ ይከበራል። በእነዚህ አካባቢዎች ታዲያ በዓሉ በተለያየ ሥም ይጠራ እንጂ እንደየ አካባቢው የበዓሉ ጅማሬ እና ፍጻሜ ቀኖች ከመለያቸው እና ከልጃገረዶች አለባበስና ፀጉር አሰራር ውጪ በሁሉም አካባቢዎች ለበዓሉ የሚሰጠው ትርጓሜና የአከባበር ስርዓቱ ተመሳሳይ መሆኑን የተለያዩ መዛግብት ያስረዳሉ።

የአሸንዳ/ሻደይ በዓል
የአሸንዳ/ሻደይ በዓል የአከባበር ሰርአት ቀደምት የሆነ ሀይማኖታዊና ትውፊታዊ መሰረት እንዳለው የሚነገር በዓል ነው። የዚህ በዓል ሀይማኖታዊ መሰረትን በሚመለከት አዳም እና ሄዋን ከገነት ከተባረሩበት፣ ከኖኅ ዘመኑ የጥፋት ውሃ ኖህ እና ቤተሰቡ ከተረፉበት፣ ከመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ አንገት ከተቆረጠበት እንዲሁም የመስፍኑ ዮፍታሄ ልጅ በመስዋዕትነት በአባትዋ ከቀረበችበት እለታት ጋር በማያያዝ የሚነሱ ታሪኮች አሉ።

በተለየ መልኩ በብዙኀኑ የሚነገረው ደግሞ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን እምነት መሠረት፣ ከቅድስት ድንግል ማርያም ትንሳኤ (ፍልሰታ ማርያም) ጋር የተያያዘው ታሪክ ነው። ድንግል ማርያም አካላዊ ሥጋዋ ከጌተሰማኔ ወደ ገነት ያረገበት እንዲሁም በገነት በዕፀ-ሕይወት ሥር ከነበረበት የተነሳበትን እለት ጋር ተያይዞ የበዓሉን መከበር መጀመሩን የሃይማኖቱ ሊቃውንት ያወሳሉ።

ድንግል ማርያም በመላዕክት ሽብሸባ፣ እልልታና ዝማሬ ታጅባ ከምድር ወደ ሰማይ ያረገችበትን እለት ለማስታወስ ታዲያ ልጃገረዶች የመላእክቱን ሥርዓት መነሻ በማድረግ ባህላዊ ነጫጭ ልብሶችን ይለብሳሉ። ለምለም፣ ረጃጅምና ቅጠለ ሰፋፊ የአሸንዳ ሳሮችን በወገባቸው በማሰር እንደ መላአክቱ ሽብሸባ ወገባቸውን ከግራ ወደ ቀኝ በማሽከርከር እያሸበሸቡ፣ ልዩ ልዩ መዝሙሮችን እየዘመሩና በእጆቻቸው እያጨበጨቡ በአንድነት ተሰባስበው በፍቅርና በደስታ እለቱን ያከብሩታል።
በአሸንዳና በሌሎች በወርሃ ነሐሴ አጋማሽ ላይ በሚከናወኑ በዓላት ዙሪያ ጥናትን ያካሄዱት እና በአሸንዳ በዓል አከባበር እና ታሪካዊ መሰረት ዙሪያ ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታን ያደረጉት መብራኽተን ገብረማርያም፣ የበዓሉን አከባበር በተመለከተ በእርግጠኝነት በዚህ ወቅት ተጀመረ የሚሉና ስለአጀማመሩ በግልፅ የሚያስረዱ የተቀመጡ መረጃዎች እና የታሪክ ሰነዶች እስከ አሁን አለማግኘታቸውን ገልፀዋል።

‹‹ነገር ግን ዞሮ ዞሮ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተወራረሰ የመጣ እና ባህላዊ ይዘቱ በጣም የጎላ እንዲሁም ሀይማኖታዊ መልክ ያለው በዓል መሆኑ ሁሉንም ሊያግባባ የሚችል ነው።›› ሲሉ ያስረዳሉ።

አክለውም ‹‹በአንዳንድ መጽሐፍት ላይ ለምሳሌም የሀብተማሪያም አሰፋ (ዶ/ር) ‹የኢትዮጵያ ታሪክ ባህሎች እና ጥያቄዎች› የሚል መጽሐፋቸው፣ አሸንዳ ከክርስትና በፊት ተጀምሮ ሊሆን እንደሚችል የተቀመጠ ጽሑፍ አለ።›› የሚሉት መብራኽተን ‹‹መጽሐፉ አከባበሩ፣ የጭፈራው አይነት እና ልጃገረዶቹ የሚያጌጡባቸው ጌጣጌጦች በቅድመ ክርስትና ወቅት የነበሩ ሊሆን እንደሚችል ያስቀምጣል። የጌጣጌጦቹ አይነት ከቀደሙት ጋር የሚገናኝ ባህሪ አላቸው በማለት የሚጽፉም አሉ።›› በማለት ጌጣጌጦቹ የቆየ የታሪክ እድሜ ያላቸው ከመሆናቸው አንፃር በቅድመ ክርስትና ወቅትም የነበረ በዓል ሊሆን እንደሚችልም ያነሳሉ።

በሌላ በኩል የሀይማኖት አባቶች ‹‹አይ! በዓሉ ሀይማኖታዊ መልክ ያለው ስለሆነ ክርስትያናዊ በዓልም ነው›› ስለሚሉ ብዙ ጊዜ ከክርስትና መጀመር በኋላ በዓሉ መከበር መጀመሩን የሚያስቀምጡት ነገር እንዳለም አያይዘው ጠቅሰዋል። ‹‹ይሄ ትልቅ የታሪክ አጀንዳ እና የማንነት ጉዳይ በመሆኑ ስለበዓሉ አጀማመር ደፍሮ የሆነ እልባት ላይ ለመድረስና ድምዳሜ ለመስጠት የሚያዳግት ነው። ስለዚህም የበለጠ ጥናት ቢደረግበት ጥሩ ነው የሚል እሳቤ ነው ያለኝ።›› በማለት አጽንዖት ይሰጣሉ።

‹‹ሁልጊዜ ክረምት ሲገባ አሸንዳን ነው የማስበው።›› የምትለው ደግሞ ሰናይት አወጣኸኝ ስትሆን የአክሱም ከተማ ነዋሪ እና የአሸንዳ በዓል ሲደርስ የበዓሉን መጀመር በጉጉት ከሚጠባበቁ ልጃገረዶች ውስጥ አንዷ ናት። ታዲያ ሰናይት አሸንዳ ስታስብ ቀድሞ በህሊናዬ የሚመጣው ጭፈራው፣ አለባበሱ፣ ሽሩባ መሠራቱ ነው ትላለች።
‹‹የአሸንዳ በዓል ከሀይማኖት ጋር የሚያያዝ ነገር እንዳለው አውቃለሁ። ነገር ግን ለእኔ አሸንዳ ሲቃረብ ከሁሉ ነገር በላይ ቅድሚያ በመስጠት ከጓደኞቼ ጋር የምመርጠውን ልብስ፣ የምንሠራውን ሹሩባ የምናደርጋቸውን ጨዋታዎች ሁሉ መናፈቅ እጀምራለሁ።›› ስትል ለበዓሉ ያላትን ከፍተኛ ፍቅር ታስረዳለች።
ሰናይት ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራት ቆይታ በአሁኑ ሰዓት በኮቪድ 19 ምክንያት ‹‹ኮሮናን ለመከላከል አሸንዳን በቤታችን›› በሚል መሪ ሐሳብ ሁሉም እራሱን በመጠበቅ አሸንዳን በየቤቱ እንዲያከብረው በመወሰኑ፤ እንደወትሮው ለበዓሉ ምንም አይነት ቅድመ ዝግጅት አለማድረጓን ትናገራለች።

‹‹በዓሉ እንዳይጠፋና ወግ እና ስርዓቱን ለመጠበቅ ሁላችንም በየቤታችን ባህላዊ ልብስ ለብሰን፣ ሹሩባ ተሠርተን በዓሉን በማስመልከት የሚዘጋጁ ፕሮግራሞችን በቴሌቭዥን እየተመለከትን የምናከብረው እንጂ እንደቀድሞዉ ጊዜ ደማቅ ድባብ ኖሮት የሚከበር አለመሆኑ አስከፍቶኛል። በአጭሩ የሆነ ነገር እንደጠፋብኝ እንደጎደለብኝ አይነት ስሜት እየተሰማኝ ነው። አሸንዳ ከዚህ በኋላ የማይከበር እስኪመስለኝ ድረስ የሚያስከፋ ስሜት ነው የፈጠረብኝ።›› ስትል ስሜቷን አካፍላለች።

የበዓሉ አከባበር
‹‹መፀት መፀት አሸንዳ ዕምባባ መፀት››
(መጣች መጣች፣ አሸንዳ አበባ መጣች)
የነሐሴ ወር ሲገባ የአሸንዳ ጨዋታ ተሳታፊ ልጃገረዶች ከበዓሉ ቀደም ብለው እርስ በእርስ እየተሰባሰቡ ቡድን ይመሰርታሉ። የቡድኑ አመሰራረት ጓደኝነትን እና ሰፈርን መሠረት ያደረገ ነው። አንድ ቡድን ከ12 እስከ 20 የሚደርሱ አባላትን በውስጡ ይይዛል። የአሸንዳ ባህላዊ ጨዋታ ተሳታፊዎች በየእድሜ እርከናቸው የሚሰባሰቡ ሲሆን ሕጻናት፣ ልጃገረዶች እንዲሁም እናቶች ከበዓሉ አስቀድመው ለጨዋታው እራሳቸውን በቡድን በቡድን ያደራጃሉ። የጨዋታው ዋንኛ ባለቤቶች ግን ያላገቡ ሴቶች ወይንም ልጃገረዶች ናቸው።

‹‹ለበዓሉ አንድ ወር ሲቀረው ምን አይነት ሹርባ እንደምንሠራ፣ ምን አይነት ልብስ እንደምንለብስ፣ ምን አይነት የጆሮና የአንገት ጌጦች እንደምንገዛ በመወያየት እንወስናለን። እንዲሁም በብዛት ምን አይነት ዘፈን እንደምንዘፍን ለምሳሌ መጀመሪያ ሰው ቤት ስንሄድ የሚዘፈን ዘፈን አለ። ገንዘብ ሲሰጠን ሰጪዎቹን ለማመስገኛ የምናዘጋጀው ዘፈን አለ። እነርሱን እየተወያየን እንዘጋጃለን።

ከዛም በዓሉ በሚከበርባቸው ተከታታይ ቀናት የመጀመሪያ ቀን ምን እናደርጋለን፣ በሚቀጥለው ቀን ምን እናደርጋለን በማለት እስከ በዓሉ ማብቂያ ቀን ድረስ የምናደርጋቸውን ነገሮች ሁሉ ተነጋግረን እና ተስማምተን በዚህ መልኩ ዝግጅታችን እናጠናቅቃለን።›› ስትል ሰናይት ከጓደኞቿ ጋር ለበዓሉ የምታደርገውን ቅድመ ዝግጅት ታስታውሳለች።

የአሸንዳ ልጃገረዶች የበዓሉ ዋዜማ እለት የአሸንድየውን ቅጠል ካለበት ቦታ ፈልገው በመቁረጥ በወገባቸው ልክ በመጎንጎን ካበጃጁት በኋላ ለሚቀጥለው ቀን እንዳይጠወልግ ጤዛ ሳር ስር ያሳድሩታል። የበዓሉ እለትም የተጎነጎነውን አሸንድዬ በወገባቸው ላይ በማሰር ልዩ የሆነ ቦታን ወደሚሰጡት የአሸንድዬ ጨዋታቸው ያቀናሉ።

የሹሩባ አሠራራቸው እንደ እድሜና የጋብቻ ሁኔታ የተወሰነ በመሆኑ በዛ መሰረት ያገባች ሴት፣ ያላገባች እንዲሁም ሕጻናት ምን አይነት ሹሩባ መሠራት እንዳለባቸው ተለይቶ ይታወቃል። ሰናይት አያይዛም ‹‹የበዓሉ እለት በማለዳው በቅድሚያ ቤተክርስትያን (በብዛት ማርያም ቤተክርስትያን) በመሄድ ዓመት ከዓመት እንኳን አቆየሺኝ በማለት ምስጋናችንን በዜማ ካደረስን በኋላ፤ ‹መፀት መፀት አሸንዳ ዕምባባ መፀት› እየተባለ ቤት ለቤት እየተዞረ ከበሮ እየተመታ እየተጨፈረ እንጫወታለን። ከዛም ስጦታ ሲሰጠን የምስጋና ዜማችንን እያሰማን ወደሌላ ቤት፣ ወደሌላ መንደር እናቀናል›› ስትል የበዓሉን የአከባበር ልምድና ስርዓት ታስረዳለች።

በዚህ መልኩ የበዓሉ ቀናት እስኪገባደዱ ድረስ ባሉት ቀናት ሁሉ የአሸንዳ ልጃገረዶች ተመሳሳይ ተግባር ይፈጽማሉ። በጭፈራ እና በጨዋታው ሲደሰቱ እና በየሄዱበት ቦታ ሁሉ የሚያገኙትን የማኅበረሰብ ክፍል ሲያስደስቱ ሰንብተው፣ አሮጌውን ዓመት ሸኝተው፣ አዲሱን በልዩ መንፈስ ይቀበላሉ።

የአሸንዳ/ሻደይ በዓል በሴቶች አንጻር
የአሸንዳ በዓል ሴቶች በተለይም ልጃገረዶች ነፃነታቸውን የሚያውጁበት፣ በየአደባባዩ በኩራት የሚመላለሱበት እና የሚነግሡበት ጥብቅ ከነበረው የቤተሰብ ቁጥጥር ፋታ የሚያገኙበት እለት ነው። እናም የበዓሉ መከበር ለሴቶች የሚያመጣው ሁለንተናዊ ጥቅም ይህ ነው የሚባል አይደለም።

ሴቶች አብዛኛውን ጊዜ በማኅበረሰባችን፣ በአገራችን እና በመላው ዓለም ለማለት በሚያስችል ሁኔታ የሚገባቸውን ቦታ አግኝተዋል ተብሎ አይታመንም። በአሁኑ ሰዓት የሴቶች እኩልነት ትልቅ አጀንዳ ነው። በእኛም ማኅበረሰብ ይህ ጉዳይ ተመሳሳይ ነው የሚሉት መብራኽተን፣ ስለዚህ አሸንዳ በተለየ መልኩ ለሴቶች ልዩ ትኩረት፣ ልዩ አክብሮት ያለው በዓል ሆኖ እናገኘዋለን ይላሉ።

‹‹ሴቶች በሌሎች ቀናት በቤት ውስጥ የሚሠሯቸው አድካሚና ማለቂያ የሌላቸው ሥራዎች እንዳሉ ሆነው፣ ከዛ ወጣ ባለ መልኩ የክረምት ወቅት እንደመሆኑ የአረም እና መሰል እርሻ ነክ ወንድ ሊሠራቸው ይችላሉ ተብለው የሚገመቱ ሥራዎችንም ሊሠሩ ይችላሉ። ስለሆነም በዚህ ምክንያት ሰውነታቸው፣ አካላቸው አዕምሯቸው በሙሉ ደካክሞ የሚቆይበት ወቅት ነው።

ከዛ በኋላ የአሸንዳ በዓል መጥቶ ሙሉ ነፃነትን በመስጠት አካላቸውንም አዕምሯቸውንም የሚያድሱበት፣ በነፃነት የሚቦርቁበት የሚጫወቱበት ነው። በክረምቱ ምክንያት ተለያይተዋቸው ከነበሯቸው ከሚወዷቸው ጓደኞቻቸው ጋርም በተለየ መልኩ በጋራ አብሮነታቸውን መልሰው የሚያድሱበት ወቅት ነው።›› ይላሉ።
በእነዚህ የአሸንዳ ቀናትም ልጃገረዶቹ ቤት ለቤትም እየዞሩ እንኳን አደረሳችሁ በማለት መልካም ምኞታቸውን ይገልፃሉ። ማኅበራዊ ኃላፊነትን ይወጣሉ፣ ገንዘብ ሰብስበው ለቤተ-ክርስትያን ይሰጣሉ። በየቤቱ እየዞሩ በሚጫወቱበት ወቅትም የገንዘብ፣ የቁሳቁስ፣ የምግብ እና መሰል ስጦታዎችን የሚይዝላቸውን፣ አጠቃላይ ቡድናቸውን በማስተባበር የሚመራላቸውን ሰው አስቀድመው ይመርጣሉ።

መብራኽተን እንዲህ ሲሉ ከሐሳባቸው ያካፍላሉ፤ ‹‹በተጨማሪም በማኅበረሰቡ ላይ የሚያዩት እና ከአሸንዳ ውጪ ባለ ጊዜ ውስጥ ቢናገሩት የሚያስጠይቃቸው ማኅበራዊም ሆነ ፖለቲካዊ እንከኖች፤ አሸንዳ ስለመጣና ሙሉ ነፃነትን ስለሰጣቸው ያለፍርሀት ትችት የሚያቀርቡበት በዓል ነው። እና እነዚህ ነገሮች በሙሉ በጣም የተሻለ ነፃነት፣ አቅም እና አውድ ይፈጥርላቸዋል።›› በማለት አሸንዳ የሴቶች የችሎታቸው፣ የብቃታቸው የአብሮነትና የአንድነታቸው ተምሳሌትም የነፃነታቸው አርማም ነው ቢባል ማጋነን እንደማይሆን ይናገራሉ።

ከማኅበራዊ ትስስር አንጻር?
በዓሉ የሚከበርበት ወቅት በክረምት ወር ማብቂያ ላይ እንደመሆኑ ወቅቱ ራሱ የዝናብ፣ የመብረቅ፣ የነጎድጓድ ጎርፍም ጭምር የሚበዛበት ወቅት ስለሆነ ሌላው ቀርቶ ማዶ ለማዶ ያሉ ሰዎችን ወንዝ ተሻግረው ለመገናኘት ያዳግታል። በተለይም በገጠሩ አካባቢ በሚኖሩ ሰዎች መካከል ይህ ይፈጠራል።
ታዲያ በዚህ ሁኔታ ተለያይተው የሚከርሙ ይኖራሉ። እናም የአሸንዳ በዓል ዝናቡን የሚያባራበት ወቅት አካባቢ ስለሆነ ሲገናኙ በከባድ ናፍቆት ነው። ይህም ማኅበራዊ ትስስራቸውን መልሰው የሚያድሱበት ነው።

‹‹በተፈጥሮም ምክንያት ይሁን በሥራ ጫና መብዛት ምክንያት ተለያይተው የነበሩ ሴቶች፣ ጓደኛሞች እና ቤተሰቦች እርስ በራሳቸው የሚገናኙበት፣ መልሰው ማኅበራዊ ትስስራቸውን የሚያጠነክሩበትና እንኳን አደረሳችሁ በመባባል መልካም ምኞታቸውን የሚገልፁበት ነው። ከሕጻን እስከ አዋቂ በጋራ ቤት ለቤት እየዞሩ በመጫወት ማኅበራዊ ትስስራቸውን የሚያጠነክሩበት በዓል ነው።›› ሲሉ መብራኽተን ይገልጻሉ።

በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ማኅበራዊ ርቀትን ለመጠበቅ ሲባል አሸንዳ ዘንድሮ እንደ ወትሮው አይከበርም። ኮሮና ባይኖር ኖሮ ግን አከባበሩ ደማቅ ሊሆን እንደሚችል ይጠበቅ ነበር። ‹‹አሁን የጎደለው ማኅበራዊ ትስስሩ ነው። አሸንዳን ከማኅበራዊ ትስስር ነጥሎ ማየት አይቻልም። ስለዚህ ማኅበራዊ ትስስር በትክክል የበለጠ የሚገለፅበት አንዱ መድረክ ነው።›› እንደ መብራኽተን ገለጻ።

ከዚህ ጋር በተገናኘ በአንድ አገር በተለያዩ ብሔር ተወላጅ የሆኑ ሰዎች በዚህ ስርዓት እንዴት አንድ እንደሚሆኑ ያስረዳሉ። እንዲህም አሉ፤ ‹‹እንደምሳሌም የአማራ እና የትግራይ ሕዝብን ብናነሳ፣ ከአሁን በፊት ሰቆጣ ላይ እየተገናኙ እንዲሁም በጋራ መቀሌ እየሄዱ ሲያከብሩ እንደነበር ሁላችንም እናውቃለን። ከኹለቱም ወገን ያለው የፖለቲከኞች አለመስማማት እንደዚህ ባያደርገው ኖሮ በእርግጠኝነት የባህሉ የማንነቱን የበለጠ ምን ያህል አስተሳሳሪ ይሆን እንደነበረ መገመት ይቻላል።

ሕዝብ ዞሮ ዞሮ ሕዝብ ነው። ምናልባትም ነገ ጠዋት የየፖለቲካው አቧራ ሲጠራ በእርግጠኝነት ቀድሞ የሚመጣው አሸንዳ ሊሆን ይችላል። የነበረም ያለም የሚኖርም እሱ ስለሆነ። የፖለቲካው አለመረጋጋት ሁልጊዜ አሁን ባለበት ይቀጥላል ማለት አይደለም። እንደ ሌሎቹ በዓላት ሁሉ አሸንዳ በተለየ መልኩ ማኅበራዊ ትስስርን ያጠናክራል የሚል እምነት አለኝ።››

በማይዳሰስ ቅርስነት ስለማስመዝገብ?
በዚሁ ባለንበት ዓመት የታህሳስ ወር ማብቂያ ላይ የአሸንዳ በዓል በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የማይዳሰስ ቅርስ ሆኖ እንዲመዘገብ የማስመረጫ ሰነድ ዝግጅት መጠናቀቁን የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ማስታወቁ የሚታወስ ነው። በአሁን ሰዓት ይህ ምን ደረጃ ላይ ደረሰ በማለት አዲስ ማለዳ ለመብራኽተን ጥያቄ አቅርባ ነበር።

በዓሉን የማይዳሰስ ቅርስ ሆኖ እንዲመዘገብ ጥረት የሚያደርገው ኮሚቴ ውስጥ አባል እንደሆኑ የገለፁት መብራኽተን፣ ጉዳዩ ትኩረት ተሰጥቶት ሥራ ተጀምሮ ጥሩ የሚባሉ ማስረጃዎች ተዘጋጅተው መላካቸውን ይገልፃሉ። ‹‹ድርጅቱም ሐሳቡን ተቀብሎት በዓሉ እንዲታይ እና እንዲጠና በማለት በዘንድሮው በዓል አከባበር ላይም በመገኘት እና ስርአቱን በመታደም ውሳኔን ለመስጠት እቅድ ነበረው›› ያሉት ሲሆን፣ በዓሉ የሚከበርበት ወቅት የዓለም አቀፍ ስጋት ከሆነው ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ ጋር በመገጣጠሙ ይህን ማድረግ እንዳልተቻለ ያስረዳሉ።

እንደ አሸንዳ አይነት የአንድነት በዓላት ዝም ብለው ተራ በዓላት አይደሉም የሚሉት ባለሞያው፣ የሆነ ወቅት ላይ ብቻ ሊወጡ የሚችሉ ግን የብዙ ዘመን የትውልዱን እሴቶች በአንድ ላይ አጭቀው የያዙ ትልልቅ ማስተማሪያ መድረኮች ናቸው ይሏቸዋል። አክለውም ‹‹ሕጻንዋ ልጅ ከታላላቆቿ ምንድን ነው የምትማረው? ሁላችንም የምናውቀው ነገር ነው። ምን ይባላል ምን አይባልም፣ ምን ይደረጋል ምን አይደረግም? ወዘተ የሚለውን በትክክል ተረድታ ለቀጣይ ትውልድም የምታስተላልፍበት ትምህርት ቤትም ነው አሸንዳ በዓል።›› ሲሉ ይገልፃሉ።

ስለሆነም እንደዚህ አይነት መድረኮች መልካም የሆኑ እሴቶችም ያሏቸው እንደመሆናቸው መጠን የአንድነት፣ የነፃነት፣ የእኩልነት፣ የመተሳሰብ የፈጠራ አቅማቸውን የሚያጎለብቱበት፣ የልግስና፣ መልካም ሥራን የመሥራትና የሰላምም ጭምር ተምሳሌቶች ናቸው። ግጭትም ሲያጋጥም በቀላሉ የሚመልሱበት ሙዚቃ ወይም ዘፈን አላቸው። እነዚህ በቀላሉ እንዴት ግጭቶችን መፍታት እንደምንችል ማስተማሪያዎች ናቸውና፣ በትክክል ትኩረት ሰጥተን ካየናቸው ብዙ የታመቀ አቅም ያላቸው በዓሎች ናቸውም ብለዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 94 ነሐሴ 16 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here