ኢትዮጵያ በውሃ ሀብት ሥሟ ቢነሳም በተጨባጭ የውሃ አያያዟና በሀብቷ የመጠቀሟ ነገር ከሥሟ የሚመጣጠን አይደለም። የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ያነቃው የውሃ ሀብት ጉዳይም ብዙዎች ግንዛቤ እንዲያገኙ ከማድረግ አልፎ ተቆርቋሪነት እንዲሰማቸው አድርጓል። የጣና በእንቦጭ መወረርም የተፋሰስ አካላት ያሉበት ሁኔታ እንዴት ነው ብሎ ለመጠይቅ ጋብዟል። አሁንም የውሃ አካላት በደለል መሞላት፣ ብክለትና ብክነት የመሰሉ ፈተናዎች ለኢትዮጵያ የውሃ አካላት ፈተና ናቸው።
የተፋሰስ ውሃ ልማትን በሚመለከት የአዋሽ፣ የአባይና የስምጥ ሸለቆ ተፋሰስ ባለሥልጣናት ተመሥርተው ሲሠሩ ቆይተዋል። በ2011 በመንግሥት ሥራ አስፈጻሚ ተቋማት በተደረገ የአደረጃጀት ለውጥ መሠረት ታድያ እነዚህ ሦስት እንዲሁም ይጨመራሉ ተብለው ይታሰቡ የነበሩ ቀሪ ዘጠኝ የተፋሰሰ ባለሥልጣናት አዲስ በተደራጀው የተፋሰስ ልማት ባለሥልጣን ስር ተካተዋል።
ጌታቸው ግዛው የዚህ ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ናቸው። በውሃ ዘርፍ ለበርካታ ዓመታት ያገለገሉ ሲሆን፣ በሙያጨው የመስኖ መሃንዲስ ናቸው። አስቀድሞም የአዋሽ ተፋሰስ ባለሥልጣን (አሁን የአዋሽ ተፋሰስ ልማት ጽሕፈት ቤት) ዳይሬክተር በመሆን ሠርተዋል። የተቋሙን ምሥረታና ዓላማ፣ የኢትዮጵያ የውሃ ሀብት አጠቃቀምና አያያዝ እንዲሁም ያሉ ተግዳሮቶችን በሚመለከትም ከአዲስ ማለዳዋ ሊድያ ተስፋዬ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርገዋል።
ተፋሰሶቻችን እንዴት ናቸው?
ተፋሰሶቻችን ክረምት ላይ ደኅና ናቸው። አካባቢያቸውም ለምለም ነው የሚሆነው። የውሃ እጥረትም አይኖርም፤ ክረምት ስለሆነ። በጋ ላይ ግን ሕመም የሚሰማቸው ተፋሰሶች አሉ። በጣም አገልግሎት የሰጡ እንደ አዋሽና ስምጥ ሸለቆ ያሉ ተፋሰሶች ጥንቃቄ የሚፈልጉ ሆነዋል።
ያለው ፍላጎት የጨመረበት አቅማቸው ደግሞ ውስን የሆነበት፣ ፍላጎት ከአቅርቦት በላይ የሆነባቸው ተፋሰሶች አሉ። እነዚህ ተጨማሪ መሠረተ ልማት የሚጠይቁ ናቸው። ከዛ ባሻገር ሁሉም ተፋሰሶች ላይ በሚባል ደረጃ የአፈር መሸርሸርና የደለል ስጋት፣ በውሃ አካላት ላይ የመጤ አረም ችግሮች ማንዣበባቸው፣ በተጨባጭ አንዳንዶቹ አስጊ ደረጃ መድረሳቸው፣ በድምር ሲታይ ስጋትም እድልም ያለባቸው ናቸው፤ ተፋሰሶቻችን።
ስጋቱ እንዳልኩት የደለል ክምችት፣ መጤ አረም ወረርሽኝ፣ የፍላጎትና አቅርቦት አለመመጣጠን ጋር ተያይዞ ነው። እንደ እድል የምናያቸው ደግሞ ተፋሰሶቻችን ለእኛ አይደለም ለውጪም አገሮች የውሃ መነሻ ናቸው። የምንሰጠው እንጂ የምንቀበለው ውሃ የለንም። በደንብ ከተንከባከብንና ካለማናቸው ከእኛ ተርፈው ጎረቤትን መመገብ የሚችሉ የውሃ ሀብቶች ይኖሩናል።
ከብክለት እንዲሁም ከብክነት አንጻር ብዙ ጥፋቶች ሲደርሱ እያየን ነው። እንዳሉት ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችል ምን ያህል ግንዛቤ አለ?
ምንአልባት አንዳንድ ቦታ ላይ አንድ ግድብ በመሥራት የምንይዘውን ውሃ ያህል እናባክናለን። የውሃ ብክነት ላይ ብዙ አልተሠራም ማለት ይቻላል። አስተዳደሩ ከልማት እኩል አልሄደም። የውሃ ቁጠባን ማጠናከር ደግሞ ቴክኖሎጂና በጀት ይፈልጋል። እኛ አሁን ማዳረስና ሽፋን ላይ ነው ያተኮርነው።
ትልቅ ሥራ እየሠራን ያለነው መስኖ ውሃ አቅርቦት ላይ ነው። ግን አቅርቦቱን ከአመራሩ ጋር አብረን እኩል ካልመራን ነገ ከነገ ወዲያ መሬቱን ልናጣ እንችላን።
ውሃ ማባከን ብቻ አይደለም። ወደፊት ግንዛቤ ሲያድግ ቴክኖሎጂ ቀይረን ውሃን ልንቆጥብ እንችላለን። መሬቱን ካጣነው ግን ከባድ ነው የሚሆነው። ውሃው የሚባክን ከሆነ፣ አንድ ልማት ከሚፈልገው በላይ ውሃን ከሰጠን፣ ውሃው ወደ ከርሰ ምድር ነው የሚገባው። የከርሰ ምድር ውሃ ወደ ላይ ከጨመረ ለጨዋማነት ያጋልጠናል። በዚህ መሬታችንን ልናጣ እንችላለን።
ይህ ዛሬ ላይ ችግር አይደለም። ዛሬ ተፋሰሶቻችን በቂ ውሃ አላቸው፣ ያለውንም ውሃ አልተጠቀምነውም። በቀጣይ ግን መታሰብ ያለበት ውሃን በቁጠባ መጠቀም የሚያስችል ቴክኖለጂ ማስተዋወቅ፣ የመስኖ ተጠቃሚ ማኅበራትን ማጠናከር፣ አስተዳደሩን አካል እንዲኖረው ማድረግ። ማለትም አደረጃጃት እንዲኖሩት፣ ማኅበራት ጠንካራ ሲሆኑ ወደ ኅብረት ሊያድጉ ይችላሉና። ይህ በአመራር በኩል ሊያግዘን ይችላል። የግንኙነት አግባቡንና የመረጃ ቅብብሉን የተሳለጥ ያደርገዋል። አቅም ለመገንባት የተደራጃ ኃይል ሲኖር ቀላል ይሆናል። እና ውሃን በቁጠባ መጠቀም ላይ መሥራት ይጠበቃል።
በኢትዮጵያ ተፋሰስ ልማትን በሚመለከት አስቀድሞ ሦስት የተፋሰስ ባለሥልጣናት እንደነበሩ ይታወሳል። አሁን ላይ ግን ወደ አንድ እንደታጠፉ ይታወቃልና መች ነው ይህ የተፋሰስ ልማት ባለሥልጣን የተመሠረተው? ዓላማውስ ከቀድሞ በተለየ ምንድን ነው?
የተፋሰሶች ልማት ባለሥልጣን አሁን ያለውን ቅርጽ ይዞ የተደራጀው የፌዴራል መንግሥት በአዲስ መልክ የፌዴራል ሥራ አስፈጻሚ አካላትን ሲያደራጅ ነው። ቀደም ብሎም ግን የተፋሰስ ባለሥልጣን በሚል በ514/1999 የተፋሰስ ባለሥልጣንና ከፍተኛ ምክር ቤት አዋጅ ወጥቷል።
ይህንንም መሠረት አድርጎ የአባይ፣ የስምጥ ሸለቆ እንዲሁም የአዋሽ ተፋሰስ ባለሥልጣን ካለው አጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች በመነሳት ቅድሚያ ተሰጥቷቸው በባለሥልጣን ደረጃ ራሳቸውን ችለው ተዋቅረው፣ የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር ስርዓትን ለማስፈን ተግባራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ገብተዋል።
እነዚህ ቀደም ብለው የተቋቋሙት ባለሥልጣናት የተሰጣቸው ኃላፊነት የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደርን እውን ማድረግ ነው። የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር የምንለው መሬትን፣ ውሃንና ተያያዥ የውሃ ሀብቶችን ለላቀ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እንዲውሉ ማድረግ ነው። ይህ ሲሆን ደግሞ አካባቢውን በማይጎዳ መልኩ ወይም የአካባቢ ደኅንነት ግምት ወስጥ ባስገባ መንገድ የውሃ ሀብቱ የተሻለ ጥቅም እንዲሰጥ ነው።
የተፋሰስ ባለሥልጣን እንዲቋቋም ያስፈለገበት ዋናው ምክንያትም ውሃ የጋራ ሀብት ነው። ተፋሰስ ደግሞ የራሱ የሆነ የውሃ መፋሰሻ ድንበሮች አሉት። ለዚህም ነው በአገራችን 12 ተፋሰስ አለ የምንለው።
የየራሳቸው የሆነ ክልልና ድንበር አላቸው፤ እነዚህ ተፋሰሶች። የክልል አስተዳደር ወሰንን አይከተሉም። የራሳቸውን አስተዳደር ወሰን ግን አይዘሉም። ለዚህም ነው አንዳንዶች የአገር ድንበር አቋርጠው ከጎረቤት አገራት ጋር የምንጋራቸው አሉ። አንዳንዶች ደግሞ አገር ውስጥ ብቻ የሚያልቁ ናቸው።
ከአንድ ክልል በላይ የሆነውን የጋራ ሀብት ፍትኃዊ በሆነ መንገድ ሁሉም እኩል መጠቀም በሚችልበት ይዘትና ከላይ ያሉ ተጠቃሚዎች ከታች ያሉትን ታሳቢ ያደረገ የአጠቃቀም ስርዓት እንዲኖር ለማስቻል፣ የውሃ ሀብት እቅዳችን ተፋሰስን መሠረት ያደረገ እንዲሆን ይታሰባል።
ውሃን ስናቅድም፣ ስናስተዳድርም መለኪያች መስፈርታችን ተፋሰስ ነው። ይህም ራሱን በቻለ አካል መምራት እንዲያስችል፣ በአንድ ክልል ውስጥ ስለማያበቃ፣ ራሱን የቻለ አካል እንዲኖረው ተደርጎ ነው የተዋቀረው።
ዋና ሥራው ማስተባበር፣ ማስተዳደር፣ የውሃ ሀብት ግኝቱ አስማማኝ እንዲሆን፣ ተፋሰሱ እንዲጠበቅ፣ ከብክለት እንዲጸዳ ወይንም ጥራት ደረጃው እና ስነምህዳሩ የተጠበቀ ተፋሰስ እንዲሆን፣ ይህንንም የመጠበቅ ኃላፊነት የተሰጠው ነው።
በዚህ አደረጃጃት ቀደም ብለው የነበሩት ሦስቱ ተፋሰስ ባለሥልጣናት ወደ አንድ መጥተው የተፋሰሶች ልማት ባለሥልጣን በሚል በአዲስ መልክ ተደራጅተዋል። ይህ ማለት የመጀመሪያዎቹ ጠፍተዋል ማለት አይደለም። በጽሕፈት ቤት ደረጃ ሆነዋል። ምክንያቱም በፖሊሲያችን ውሃን የምናስተዳድረው በተፋሰስ ነው ይላል።
ተፋሰሶች የየራሳቸው አስተዳደር ወሰን ስላላቸው፣ መረጃቸው፣ እቅዳቸውና ልማታቸው ተፋሰስን መሠረት ያደረገ ነው። ይህ አደረጃጀት መጥፋት ስለሌለበትና በየተፋሰሱ መረጃዎችን ለማደራጀት እንዲያስችል፣ ቀደም ብለው የነበሩት ተፋሰስ ባለሥልጣን አሁን የተፋሰስ ልማት ጽሕፈት ቤት በሚል በጽሕፈት ቤት ደረጃ ሆነዋል። ተጠሪነታቸውም ለዚህኛው ባለሥልጣን መሥሪያ ቤት ሆኖ በፊት ሲሠሩ የነበረውን ሥራ በዛው ደረጃ ያካሂዳሉ።
ልዩነቱ በፊት የአባይ ተፋሰስ ሲባል አባይ ብቻ፣ ስምጥ ሸለቆ ሲባልም እንደዛው፣ የአዋሽም ሲባል ስለአዋሽ ብቻ ነበር። እነዚህ በተናጠል እያንዳንዱን የሚ ከ ታተሉና የሚያስተዳድሩ ልማት ጽሕፈት ቤቶች እንደተጠበቁ ሆነው፣ ሁሉንም ተፋሰሶች ተደራሽ ለማድረግ ነው።
ይህ አዲስ አደረጃጀት ምን ጥቅም አስገኘ?
ሁሉንም ተፋሰሶች ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል ነው። ቀድሞ ከዚህም በላይ (ከሦስት ተፋሰስ ባለሥልጣን በላይ) የማሳደግና ባለሥልጣን የማቋቋም እቅድ ነበር። አሁን ያንን ለማድረግ ቀለል ያለ መንገድ ተገኝቷል። ባለሥልጣን ለማቋቋም ደንብ ማዘጋጀት፣ ሚኒስትሮች ምክር ቤት ማጸደቅና ወዘተ ያስፈልጋል።
የተፋሰሶች ልማት ባለሥልጣን በተቋቋመበት አዋጅ እና ደንብ ጽሕፈት ቤቶችን የመክፈት ኃላፊነት ተሰጥቶታል። ስለዚህ በቀጣይ ያለውን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ እንቅስቃሴ እንደሁም በየተፋሰሱ ያለውን ሀብት በአግባቡ ለማስተዳደርና ለመምራት ተቋም መፍጠር ባስፈለገበት ጊዜ የኦሞ ጊቢ፣ የዋቢ ሸበሌ፣ የገናሌ፣ የተከዜ፣ የባሮ ወዘተ እያለ የተፋሰስ ልማት ጽሕፈት ቤት መክፈት ይቻላል።
ስለዚህ ሁሉንም ተፋሰሶች ለመምራት፣ ለማስተዳደር፣ መረጃም ለማደረጃት፣ አስተዳደርና ልማቱ በእኩል እንዲሄድ ለማስቻል ይህ አደረጃጀት የተሻለ እድል ፈጥሯል።
የነበሩት እንዳይከስሙ፣ ወደኋላ እንዳይመለሱ የሰው ኃይል ሀብታቸውን በአዲስ አደረጃጀት የማጠናከር ሥራዎች ተሠርተዋል። ጽሕፈት ቤቶቹ በፊት ሲመሯቸው የነበሩ ተግባራትን ይዘው እንዲሠሩ ለማድረግ ተሞክሯል። ሥማቸው ነው የተቀየረው። ተጠሪነታቸው ለዚህ ባለሥልጣን ሆነ እንጂ ከሥራው ላይ ብዙም የቀነሰ ነገር የለም።
ሌላው ተጨማሪ ይህ ተቋም ያስገኘው ጥቅም ለግንኙነቶች ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል። አብዛኞቹ ተቋማትና ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች የሚገኙት አዲስ አበባ ነው። ሌሎች የውጪ አካላት ፈንድ ለማስተባበርና ባለድርሻ አካላት ጋር ለመገናኘት አግዟል። በፊት ተራርቀውና ተበታትነው ስለነበር አሁን ያለው አደረጃጀት ሰብሰብ ያደረገ ነው።
ተሞክሮ በቀላሉ ለመለዋወጥ፣ የሰው ኃይል ለመዋዋስ፣ የጋራ አቅም ለመሆን፣ በጀትም ጭምር አንደኛው መጠቀም ካልቻለ፣ እጥረት ካጋጠመ ያንን ለማመቻቸት ይህ አደረጃጀት የተሻለ ሆኖ አግኝተነዋል።
የጋራ የሆነ ተጨማሪ አቅምም ፈጥሯል። የተፋሰስ ባለሥልጣን መቋቋሙ ለጽሕፈት ቤቶቹ ተደማሪ አቅም የፈጠረ ስለሆነ አደረጃጀቱ በርካታ ጥቅሞች አሉት ብለን መውሰድ እንችላለን። በውጤት ለመገምገም በእርግጥ ገና በአደረጃጀት ሂደት ላይ ነው።
እስከ አሁን ምን ተሠራ፣ ምንስ እየተሠራ ነው?
ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ እቅዶችን ወደ አንድ የማምጣት ሥራ ተሠርቷል። 2012 በርከት ያሉ ሥራዎች ስናከናውን ነበር። በዚህም ዓመት ተግባራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ነበርን። ጽሕፈት ቤቶች በአቅማቸው የሚያደርት እንዳለ ሆኖ፣ እነሱን ማገዝ፣ ማጠናከር፣ ማቀናጀትና ማስተባበር እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በጽሕፈት ቤቶች ያልተሸፈኑ ተፋሰሶች ላይ ሰፋ ያለ የተፋሰስ ልማት እቅድ እያከናወንን ነበር።
የፈቃድ ስርዓት መዘርጋትም እየሠራን ነበር። የከርሰ ምድር ውሃ ሀብትን በጥናት የመለየትና መረጃውን ለአገልግሎት ዝግጁ ማድረግ በስፋት እየተሠራበት ነው። ጽህፈት ቤት በሌለባቸው በተቀሩት ዘጠኝ ተፋሰሶች ላይም ሲሠራ ነው የቆየው።
ከ2012 መጀመሪያ የተዋሃዱት ተቋማት በጀት ወደ አንድ የማምጣት ሥራዎች ሲሠሩ ነበር። 2012 በጀቱ ለባለሥልጣኑ ቀጥታ ስለተመደበ በበጀት የተደገፈ በተፋሰስ ልማት፣ ውሃ ሀብት አስተዳደር፣ መረጃ አስተዳደር፣ በወሰን ተሻጋሪ ወንዞች፣ ከርሰ ምድር፣ ውሃ ፈቃድና ወዘተ ረገድ ሰፋ ያሉ እቅዶች ተይዘው በዛው ልክ ሥራዎች ሲሠሩ ነው የቆዩት።
ውሃ እና መሬት የሚነጣጠሉ አይደሉም። ለምሳሌ ለእርሻ የሚውሉ ኬሚካሎች የውሃ አካላት ላይም ጉዳት ያደርሳሉ። እንዲህ ያሉ ሁኔታዎችን በተለይም የመሬትን አያያዝና አጠቃቀም በመከታተል በኩልስ በቅንጅት የምትሠሩት ሥራ አለ?
የተፋሰስ ልማት ሥራውን በተለይ መሬት ላይ የሚሠራውን ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በጋራ ነው የምንሠራው። እኛ ውሃን ማእከል ያደረገ የውሃ መሠረተ ልማቶች በደለል እንዳይሞሉ፣ የውሃ አካላት በብክለት እንዳይጎዱ የተፋሰስ ልማት ሥራውን በበጀት ደግፈን በስፋት እንሠራለን።
ባለፈው ዓመት ከ80 ሚሊዮን ብር ያላነሰ በተፋሰስ ልማት ሥራዎች ላይ አውጥናል። ከ100 ሚሊዮን ያላነሱ ችግኞችን አፍልተን በጥናት በተለዩና በእቅድ በያዝናቸው በርካታ ንዑስ ተፋሰሶች ላይ የሥነ አካላዊና ሥነ ሕይወት ሥራ እየሠራን ነው የቆየነው።
እነዚህ ሥራዎች እንደተጠበቁ ሆነው ከአካባቢ ጥበቃ፣ ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በተለይ አገራዊ አረንጓዴ አሻራም ላይ በኮሚቴ አብረን ሆነን በማስተባበር በጋራ እየመራንና በቅንጅት እየሠራን ነው ያለነው።
ከውሃ ብክለት ጋር በተያያዘ ውሃ ከተበከለ ሀብት አይደለም። ውሃ ምደባ ውስጥም አናስገባውም። ስለዚህ የውሃ ብክለት ቁጥጥር ሥራ እንሠራለን። ተጋላጭ ቦታዎች አሉ። እነዛን መሠረት አድርገን ናሙና እንወስዳለን።
በዛ ደረጃ የውሃ ጥረት ቁጥጥር ሥራዎች፣ በሚፈለገው ትኩረት መጠን በየወሩ ወይም በየሦስት ወሩ ናሙና ወስደን፣ በቤተሙከራዎቻችን አይተን የትንተና ሥራዎች እንሠራለን። የተጎዱ አካባቢዎች ካሉ መረጃዎችን ለተጠቃሚ የመስጠት፣ ከዛም ባሻገር በካዮችን የመቆጣጠር ሥራ እንሠራለን።
ከአደጋ መከላከል፣ ክሐየራዊ ሜትሮሎጂ ጋር በቅንጅት እንሠራለን። ሃይድሮሊጂውን የምናስተዳድረው እኛ ነን። የሚገባውን ውሃ ከውሃ ፍሰት መከታተያ ጣቢያዎቻችን ነው መረጃዎች የሚገኙት። ከ570 በላይ የውሃ ፍሰት መከታተያ ጣቢያዎች አሉን።
እነዛ ላይ መሠረት አድርገን ቅድመ መከላከልና ግድብ አስተዳደር ሥራዎች፣ አደጋ የሚያስከትሉም ካሉ ከክልሎችና አልፎም ከብሔራዊ አደጋ መከታተል ጋርም በቅንጅት ሆን የምንሠራቸው የጎርፍ መከላከል ሥራዎች አሉን።
ባለፉት ኹለት ዓመታት ምን ፈተና አጋጥሟችኋል?
የተፈጥሮ ሀብትን ስለምናስተዳድር እንከን አያጋጥመም ልንል አንችልም። አሁንም ጎርፍ ውስጥ ነን። ግድቦች በጣም ሞልተዋል። ግድብ ከቁጥጥር ውጪ በሆነ መንገድ ውሃው እንዳይወጣና የጎርፍ አደጋ እንዳያስከትል ያንን የመምራት የማስተዳደር ሥራ አለብን። ይህ ክረምቱ ጫን ሲል ነው። ክረምት አጠር ሲል ደግሞ በቂ ውሃ ያልያዝንባቸው አካባቢዎች ላይ የውሃ እጥረት ተግዳሮት ይሆናል።
በውሃ አካላት ላይ የሚከሰት የእንቦጭና መጤ አረም ችግርም ሌላው ነው። አሁን የምንሠራቸው የተፋሰስ ልማት ሥራዎች ለእንቦጭ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥሩትን የደለል፣ የብክለት ጉዳዮችን ባሉበት ደረጃ በማስቀረት፣ ከምንጩ ችግሩን ለመቀነስ ነው። የውሃ አካላት ላይ ተከስ ቶ ያለውን እንቦጭ ደግሞ ለማስወገድ ክልሎችን በሜካኒካል ሥራዎችም እናግዛለን። በጥናትና ምርምር እየተሠሩ ላሉትም ድጋፍ እናደርጋለን።
ከጎርፍና ውሃ እጥረት ባሻገር ይህ የእንቦጭ ወረርሽኝ በተለያዩ የውሃ አካላት ላይ መከሰቱ ሌላው ተግዳሮት ነው።
ከመሬት ጋር በተገናኘ የከርሰ ምድር ውሃ ይገኝባቸዋል ተብለው የተለዩ አካባቢዎች ላይ ሰዎች ለመኖሪያ እየሰፈሩ ነው የሚሉ ጉዳዮች ይነሳሉ። ይህን ጉዳይ እናንተ አይታችኋል?
አንደኛው እኛም የምንጠብቀው የመሬት ልማት ፖሊሲ ለተፋሰስ አስተዳደር ትልቅ ጥቅምና ሚና አለው። የትኛው አካባቢ ደን ሊለማበት ይገባል፣ የትኛው ለእርሻ፣ የትኛው የውሃ አካላት ስለሆነ ሊከበር ይገባል የሚለው፣ ዝግጅቱ ተጠናቆ ወደ ትግበራ ለመግባት ተፋሰስን ለሚያስተዳድሩ ተቋማት ያስቸግራል።
ወንዙ ጠርዝ ላይ የሚደረጉ ሰፈራዎች አሉ። የወንዝ ዳርቻዎችን እስከ መጨረሻ ተጠግቶ የማረስ ነገር አለ። እነዚህ ለጎርፍና ለውሃ ብክለትን ያጋልጣሉ። መታረስ የሌለባቸው አካባቢዎች ወደ እርሻ ይቀየራሉ። ይሄ ለደለል ክምችት ያጋልጣል። ይሄ አንደኛው ተግዳሮት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፣ የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲ ተጠናቆ ወደ ትግበራ አለመግብቱ።
እዚህ ላይ ለውሃ ሀብት መሠረታዊ ተብለው የተለዩ ነገር ግን ለተለያየ አገልግሎት ግንባታ የተካሄደባቸው የታዘባችሁት ስፍራ አለ?
በትክክል። እዚሁ ከአዲስ አበባ በቅርበት ሱሉልታ አካባቢ ቤቶች የተሠሩበት ትልቅ እርጥብ መሬት (Wet Land) ነው። ለከርሰ ምድር እንደ ትልቅ ሀብት የምንቆጥረው ነው። የዚህ መነሻ የመሬት አጠቃም ፖሊሲ አለመኖሩ ነው። ‹ይህ ቦታ የውሃ አካላት ነውና መነካት የለበትም› ብሎ መከራከር አይቻልም።
እንዲህ ያሉ ብዙ ቦታዎች ይኖራሉ። የቅርብ ስለሆነ እንደምሳሌ ሱሉልታን አነሳን፣ የአቃቂ እርጥብ መሬትም በስርዓት ተይዟል አንልም። ለተለያየ አገልግሎት አካባቢው ላይ ቤቶች ይሠራሉ፣ ያንን ተከትሎ ሌሎች ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች ይጠናከራሉ። ያ ሲሆን ወደ መሬት የሚሰርገው ውሃ በጎርፍ መልክ ይሄዳል። ይህም የከርሰ ምድር ውሃ ላይ መመናመን ያመጣል።
በጥቅሉስ የከርሰ ምድር ውሃ ያለባቸው ስፍራዎች ምን ያህል ተለይተዋል፤ ምን እቅድስ አለ?
እስከ አሁን ያለው ከ20 በመቶ በታች ነው የከርሰ ምድር ውሃ በመረጃ አደራጅተናል የምንለው። የከርሰ ምድር ውሃ ሀብታችን በግልጽ ይህን ያህል ነው ብሎ ለመናገር የሚያስደፍር ተጨባጭ መረጃ የለም። ግምት ነው ያለው። 30 እና 40 ቢሊዮን የሚሉ ቁጥሮች ከማስተር ፕላኖች የተወሰዱ ናቸው። የምንቆፍራቸው ጉድጓዶች የውሃ ሀብትን በመጠንም በጥራትም የመለየት ሥራ ነው፤ በእኛ ደረጃ እየተሠራ ያለው።
ቅድመ ጥናቶች ከተጠናቀቁ በኋላ የማረጋገጫ የውሃ ጉድጓዶች ይቆፈራሉ። በዛ ደረጃ በመረጃ ያደራጀናቸውና ደርሰንበታል የምንለው ሽፋን ከ20 በመቶ በታች ነው። እናም ብዙ ሥራ የሚፈልግ ነው።
የከርሰ ምድር የውሃ ሀብት መጋቢ የሆኑ እርጥብ መሬቶች እየተጎደ ነው፣ የከርሰ ምድር አካባቢዎች በአግባቡ አልተከበሩም ወዘተ የሚሉ፣ አጠቃላይ የውሃ አካላት ዳርቻዎችን ለማስከበር ገና በአዋጅ ደረጃ እያዘጋጀን ያለነው አዋጅ አለ። ሲጠናቀቅ የውሃ አካላት ዳርቻዎችን ያስከብራል ብለን እንጠብቃለን።
በውሃ ሀብትና ልማት ዘርፉ ባለሞያዎች አሉን ማለት ይቻላል?
ክህሎትና አቅም የመገንባት ሥራዎች፣ በውሃ ላይ ያሉ የሙያ አደረጃጀቶችን የማጠናከርና የማገዝ ሥራ መሠራት አለባቸው እንጂ በውሃ ረገድ በርካታ ባለሞያዎች አሉ። የውሃ ባለሞያ የማያስተምር ዩኒቨርሲቲ የለም ማለት ይቻላል። በየዓመቱ ከዩኒቨርሲቲ የሚወጡ የውሃ ጥናት ያጠኑ ባለሞያዎች ብዙ ናቸው።
ከጊዜ ወደ ጊዜም በውሃ ላይ ያለው ግንዛቤ እያደገ ነው ያለው። ስለሕዳሴ ግድብ በፊት በነበረው ምልከታና አሁን ባለው መካከል ያለውን ልዩነት የምናውቀነው ነው። ይህ ከተቆርቋሪነት ብቻ ሳይሆን የውሃን ጥቅም ከመረዳት የመጣ ነው። ‹ውሃ ይጠቅማል፣ በመስኖ ተጠቀሙ› ብሎ ማስተማር አስፋለጊ የማይሆንበት ደረጃ ላይ ደርሷል። ምክንያቱም የውሃ ጥቅም ታውቋል።
ይህን ያደረገው የባለሞያዎች መብዛት ጭምር ነው። በወረዳ ባለ አደረጃጀት ውስጥ ድሮ በዲግሪ የተመረቁ የውሃ ባለሞያዎች ማግኘት ይከብድ ነበር። አሁን ግን ከወረዳ ጀምሮ ባለ አደረጃጀት በውሃ ዘርፍ በርካታ ባለሞያዎች በትንሹ በዲግሪ ደረጃ አሉ። የሰው ኃይል ክፍተት አለ አንልም።
ይህንን ከአጠቃላይ ከፖሊሲውና ነባራዊ ሁኔታ ጋር ማስተዋወቅ፣ አቅም የመገንባት፣ የውሃ ሙያ ማኅበራትን የማደራጀት፣ ባለሞያዎች የሚነጋገሩባቸውን መድረኮች በስፋት የመፍጠር፣ የምርምር ተቋማትን ማብዛት። አነሰ ከተባለ እንደውም ባለሞያ ሳይሆን ተቋም ነው። ባለሞያዎች ሊሳተፉ፣ ሊወያዩ የሚችሉባቸው የጥናት ተቋማት በብዛት ሊፈጠሩ ይገባል።
እንደው ጠቅለል አድርገን ስናነሳ፣ ኢትዮጵያ በአግባቡ የውሃ ሀብቷን በሚገባ ተጠቅማለች ማለት ይቻላል? ባይሆን እንኳ ጥሩ አድርጋ ይዛለች ልንል እንችላለን?
የውሀ ሀብታችንን አልተጠቀምንበትም የሚለውን እንያዘው። ምክንያቱም የመሠረተ ልማት እጥረቱ ከፍተኛ ነው። ለጎርፍ የሚያጋልጠንም ያ ነው። ክረምት ላይ የምናያቸው የጎርፍ አደጋዎች የሚከሰቱት በቂ የሆነ የውሃ መያዣ መሠረተ ልማት ስለሌለን ነው።
የውሃ መሠረተ ልማት መነሻው ላይ በጀት ይፈልጋል። ያለን መሠረተ ልማት በቁጥር ውስን ነው። ከዚህ በላይ ግን የውሃ ሀብት አለን። ከአሁኑ በላይም ማልማትና መጠቀም እንችላለን። በመስኖ እየለማ ያለው ትንሽ ነው፤ ከአቅማችን አንጻር። ስለዚህ ያለንን የውሃ ሀብት ተጠቅመንበታል የምንልበት ደረጃ ላይ አይደለንም።
በርካታ መሠረተ ልማት ይፈልጋል። አሁን ላይ ሰፋ ያሉ ፕሮጀክቶች በየዓመቱ ይተዋወቃሉ። በዚህ ዓመት አሁን የመስኖ ልማት ትልቅ ትኩረት የተሰጠው ነው። ይህ ሆነ ማለት በርካታ በጀት ተመድቧል፣ ብዙ የመስኖ መሠረተ ልማቶች ሊገነቡ ይችላሉ። ይሄ የውሃ ሀብታችንን እንድንጠቀምበት እድል ይሰጠናል።
እንጂ ባለን የውሃ ሀብት ልክ ይዘን እየተጠቀምንበት ነው የሚል ደረጃ ላይ አልደረስንም። ብዙ መሥራት ይፈልጋል። እንደውም አልፎ አልፎ ስጋት እየሆነባቸው፣ ወደ ጎርፍ እየተቀየረ ሕዝብ እያፈናቀለና ልማት ላይ ጉዳት እያደረሰ ነው። ውሃ እንደ ነዳጅ ውድ ሀብት ነው። በዛ ልክ ውድ የሆነውን ሀብታችንን በላቀ ደረጃ ወይም አሟጠን እየተጠቀምን ነው ለማለት አያስደፍርም። የውሃ ሀብትን በመጠቀም ሂደት ገና ጅምር ላይ ነን።
የመረጃ እጥረቶች በተለያየ ጊዜ ይነሳሉ። አዲስ ማለዳም የተለያዩ ዘገባዎችን በጉዳዩ ላይ ስትሠራ በተለይ ቁጥርን በተመለከተ የመረጃ ክፍተቶች እንዳሉ ታዝባለች። ባለሥልጣኑ ይህን ክፍተት ይሞላል?
ባለሥልጣኑ የተቋቋመበት አንደኛውና ዋና ዓላማም የመረጃ ምንጭ እንዲሆን ነው። የመረጃ ምንጮቻችን የሃይድሮሎጂ መረጃዎች የምንላቸው ናቸው። ሃይድሮሎጂ የገጸ ምድሩ እንዲሁም የከርሰ ምድሩም ነው። ስለዚህ የከርሰ ምድሩን ለማጠናከር መረጃዎች እያሰባሰብን ነው። በዚህም ኻያ በመቶ ደርሰናል።
የገጸ ምድሩ ላይም በርካታ የሃይድሮሎጂ ጣቢያዎች በየዓመቱ እናቋቁማለን። የነበሩትን እናጠናክራለን። ይህ የገጸ ምድሩን መረጃ ለማደራጀት ይረዳናል። አሠራሩ አስቀድሞ በተናጠል ሲደራጅ የነበረውን መረጃ ወደ አንድ ቋት እንዲመጣ ያደርጋል።
ይህም መቀላቀል ማለት አይደለም። ግን አገራዊ የሀብት መረጃ የሚያሳይ አንድ ቋት ይኖረናል ማለት ነው። ባለሥልጣኑም በዚህ ደረጃ መቋቋሙ መረጃዎችን በተደራጀ አግባብ አንድ ቦታ ለማግኘት ምቹ ሁኔታን ይፈጥርልናል።
ቅጽ 2 ቁጥር 94 ነሐሴ 16 2012



