ወቅታዊውን ሀገራዊ ሁኔታ የዳሰሰው ሪፖርት

0
1122

የጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ መንግሥት ወደ ስልጣን ከመጣ በወራት ጊዜ ውስጥ በትግራይ ክልል እና በፌደራል መንግሥቱ መካከል የተስተዋለው ጤናማ ያልሆነ ግንኙነት ከቃላት ጦርነት አልፎ ወደ ግጭት የማምራት እድሉ እየሰፋ በመሄድ ላይ ነው።የሃይማኖት አባቶችን ያካተተው የሀገር ሽማግሌዎች ቡድን ተቀራርቦ መነጋገር ይቻል ዘንድ ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው።

ይህ ጥረት ፍሬ አልባ የመሰለው የአለም አቀፉ ክራይስስ ግሩፕ ከሰሞኑ ወቅታዊውን ሀገራዊ ሁኔታን አስመልክቶ ባለ 14 ገፅ ሪፖርት ማጠናከሩን መነሻ በማድረግ የኢትዮጵያ ፖለቲካን በቅርበት የሚከታተሉትንና በርከት ያሉ ጥናቶችን ጽሁፎችን በመጻፍ የሚታወቁትን ኖርዌያዊውን የግጭት ማስወገድ ሰላምና ደህንነት መምህር እና ተመራማሪ የሆኑትን ፕሮፌሰር ከጅትል ትሩንቨልን የሌሎችንም ወገኖችን ሃሳብ በማካተት አዲስ ማለዳ ሪፖቱን ለማየት ሞክራለች፡፡
የኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕ ሪፖርት ጭብጥ

የኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕ ሪፖርት ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ወቅታዊ የሀገራችንን ሁኔታ በማስመልከት ባለ14 ገፅ ሪፖርት ያወጣ ሲሆን ሪፖርቱ በጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ(ፌደራል መንግሥት) እና በትግራይ ክልላዊ መንግስት(ህወሓት) መካከል ሊፈጠር የሚችለውን ግጭት ለማስቀረት መሆን ይገባዋል ያለውን ምክረ ሃሳብ አትቷል።

ሪፖርቱ የማዕከላዊ መንግስቱና በህወሓት መካከል የተፈጠረውን ውጥረት ለማርገብ የደቡብ አፍሪካው ፕሬዜደንት ሲሪል ራማፎዛ በአሽማጋይነት እንድሳተፉ መክረ ሀሳብ አቅርቧል።

የኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕ ሪፖርት ወቅቱን የጠበቀ እና የተሟላ ነው ከሚሉ አንስቶ የሀገሪቱን ችግሮችን አሳንሶ በትግራይ ክልላዊ መንገስት(ህወሓት) እና በፌደራል መንግስቱ(ብልፅግና) መካከል እርቅ በማውረድ ይፈታል ብሎ ያመነ ውስንነት የታየበት ሪፖርት ነው እስከሚሉት ሃሳቦችን እያስተናገደ ይገኛል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ ጥቂት ወራት በኋላ የአራት ክልላዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች ግንባር የሆነውና ለሦስት አስርት ዓመታት ያህል አገሪቱን ያስተዳደረው ገዢ ፓርቲ ኢህአዴግ ከስሞ አንድ ወጥ አገራዊ ፓርቲ እንዲመሰረት ሆናል። ይህም በአንድ ግንባር ስር ለ25 ዓመታት ሲሰሩ የነበሩት ድርጅቶች ትስስር ላልቶ በአደባባይ መዘላለፍ አና መጎነታተል ከጀመሩ ሰነባብተዋል። ሁኔታው ከቃላት ባለፈ ወደ ግጭት ሊያመራ የመቻሉ እድል ሰፊ ሆናል።
የህወሓትና ብልጽግና የቃላት ጦርነቱ ጉዳይ

በተለያየ ጊዜ በመካከላቸው ያለው ግንኙነት በተካረረ የቃላት ጦርነት በመታጀበ እንደቀጠለ ነው። የሚያስተዳድሩዋቸውን የመገናኛ ብዙሃን በመጠቀም ከመወጋገዝ አልፎ ከመደበኛው የመገናኛ ብዙሃን አጠቃቀም ዘይቤ ዝቅ ብለው ስም ማጥፋት እና ማጠልሸት ላይ ሰንብተል፡፡አሁንም የተቀየረ ነገር የለም።ቢብስ እንጂ የተሻለ ሁኔታ አይታይም፡፡

ብልጽግናም ሆነ ህወሓት እርስ በርስ በቃላት ከመሸነቐቆጥ አለመውጣታቸው አጠቃላይ የአገሪቱን ደህንነት ሁኔታ ስጋት ላይ ጥሎታል፡፡አሁናዊ ሁኔታውን ይበልጥ ያወሳሰበው ደግሞ ሊካሄድ የነበረው ሀገራው ምርጫ መራዘሙ ነው፡፡

ኮቪድ-19 በኢትዮጵያ መከሰቱን ተከትሎ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ አገራዊ ምርጫ ለማካሄድ የሚስችል ዝግጅት ለማድረግ አልችልም በማለቱ 6ኛው አገራዊ ምርጫ መራዘሙን ተከትሎ በኹለቱ ፓርቲዎች በኩል እርስ በእርስ የመካሰስና የመወቃቀስ አባዜ የተጠናወታቸው እስኪመስል ድረስ በየእለቱ ሲነታረኩ ማየት የተለመደ ተራ ነገር ሆኗል።

በኹለቱ ፓርቲዎች መካከል አሁን ላይ የሚታየው የቃላት ንትርክና መወቃቀስ ችግርራቸወን ተቀራርበውና ተነጋግረው ከመፍታት ይልቅ በየእለቱ መካሰሱ ለኢትዮጵያ አሁናዊ የፖለቲካ ስላም እጦት አንዱ መንስኤ ተደርጎ ከአገሪቱ አልፎ ለአለም ሀገራት ግልጽ የሆነ ጉዳይ በመሆኑ ይመስላል አለም አቀፍ ተቋማት ችግሩ መፈታት አለበት የሚል ምክረ ሀሳባቸውን የሰነዘሩት፡፡

የፓርቲዎቹ የቀን ተቀን ውሎ በሚዲያዎች ላይ ቢመዘን በመካከላቸው የተፈጠረውን ችግር ተነጋግሮ ከመፍታት ይልቅ ባለፈ ነገር መነቃቀፍ ለኢትዮጵያ ህዝብ ሰላም የፈየደው ሚና መታየት የሚችል አይመስልም፡፡

የምርጫ መራዘምን ጉዳይ ተከትሎ ምርጫ ለማድረግ በሕገ መንግሥቱ ላይ በሰፈረው ህግ መሰረት ብቻ ነው መመራት ያለብን ማንም አካል ቢሆን ምርጫውን የማራዘም ህጋዊ ነት የለውም በሚለው ሕወሓት እና በኮረና ወረርሽኙ ምክንያት የታወጀ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መሰብሰብን ስለሚከለክል ሕገ መንግስታዊ ትርጉም ይሰጥበት እና ምርጫው ይራዘም በሚለው የፌደራሉ መንግስት መካከል ከረር ያለ እንኪያ ስላንቲያ ሰላምታ አለዋውጧል።

የፌደሬሽን ምክር ቤትን ህገ መንግስታዊ ትርጉሜውን በመቀበል ስድስተኛውን ሀገራዊ እና ክልላዊ ምርጫ በአንድ ዓመት እንዲራዘም ማድረጉ እና የሁሉም ምክር ቤቶች የስልጣን ዘመን ለአንድ ዓመት ጊዜ አራዝሟል፡፡

የትግራይ ገዚ ፓርቲ ህወሓት ውሳኔውን አምርሮ የተቃወመው ሲሆን በሚያስተዳድረው ክልል ውስጥ የተናጠል ምርጫ አካሂዳለሁ በማለቱ አለመግባባቱ እየተባባሰ ሄዷል።የፌደሬሽን ምክር ቤት ውሳኔን ወደ ጎን በመተው የትግራይ የክልል ምክር ቤት ምርጫን ለማካሄድ ለጳጉሜ 4/2102 ድምፅ ለመስጠት ቀነ ቀጠሮ ተይዞለታል።

የትግራይ መንግስትም ምርጫ ለማራዘም ምንም አይነት ህገ መንግስታዊ ማሻሻያ አያስፈልግም ስልጣንን ለማራዘም ካልሆነ በስተቀር በሚል ውሳኔውን አጣጥሎታል።ይልቁን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ የነበሩት የህወሃት ስራ አስፈጻሚ አባል ኬሪያ ኢብራሂም ውሳኔው ከመጽደቁ ጥቂት ቀናት በፊት ህገ መንግስቱ እየተጣሰ ነው በማለት ከሃላፊነታቸው እንዲለቁ ሆነ፡፡

የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሕገ መንግሥት ትርጉም የመስጠት ስልጣን ስላለው ክልሎች በራሳቸው ምርጫ ማካሄድ አለባቸው ወይስ የለባቸውም በሚለው ጉዳይ ላይ ቅሬታ ቢኖረው ግን የሕግ መስመርን ብቻ እንዲከተል ክራይስስ ግሩፕ መክሯል።

የትግራይ ክልላዊ መንግስት አካሂደዋለሁ ያለው ምርጫ ቀጣዩ ከባድ የግጭት መንስኤ ሊሆን ይችላል ብሎ አለም አቀፉ የክራይስስ ቡድን የአፍሪካ ሪፖርት አስቀምጧል ። የተቋሙ ስጋት የትግራይ ክልል ምርጫውን የሚያካሄድ ከሆነ የጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ መንግሥት ከፌደራል መንግሥት እውቅና ፈቃድ ውጪ ምርጫ አካሂዳችዃል ብሎ የትግራይን ክልላዊ መንግሥት በህገወጥ ይፈርጃል። የህገወጥነት ፍረጃውን ተከትሎ የክልሉን አመታዊ በጀት ከመልቀቅም ሆነ በሌሎች አላስፈላጊ እርምጃዎችን ሊወሰድ ሥለሚችል በመካከላቸው ግጭት ሊጋብዝ ይችላል።

ፕሮፌሰር ትሩንቨልም በትግራይ ክልል ገዢ ህውሃት እና በጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ መንግሥት መካከል ሊፈጠር የሚችለው ዋነኛው የግጭት መንስኤ ይሄው ጉዳይ ሊሆን ስለሚችል ገዳዩን በምክክር ለመፍታት ተቀምጦ መነጋገር እንደሚገባ አንስተዋል።

እንደ ክራይስስ ግሩፕ ሪፖርት የጉዳዩን አሳሳቢነት የሚጨምረው የክልሉ መንግስትም የመገንጠልን ጥያቄ በማራገብ ከወሰንተኛው የአማራ ክልል ጋር እንዲሁም ከዐብይ አህመድ መንግሥት ጋር ግጭት ውስጥ ሊገባ የሚችልበት እድልን ሰፊ ያደርገዋል ይላል።

ትሮንቨልም ግጭቱ ቀጠናዊ ይዘት እና አደጋ ሊኖረው ስለሚችል እንደ አፍሪካ ህብረት ያሉ ተቋማት ተነሳሽነቱን ቢወስዱ የሚለውን የክራይስስ ግሩፕ ሀሳብን እንደሚጋሩ ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል ።

የአገር ልጅ ሽምግልናው ነገር
በማዕከላዊው መንግሥትና በህወሓት መካከል ያለውን ፍጥጫና መከራር ለማለዘብ በሰኔ ወር አጋማሽ የሀገር የሽማግሌዎች ቡድን ወደ ትግራይ አቅንቶ እንደነበር እና ሂደቱም እንቅፋት አንደገጠመው ይታወቃል።ሀገራዊ ውይይት እንጂ የተናጠል ውይይትን አንቀበለውም በሚለው የህወሃት ሃሳብ ምክንያት፡፡

የፖለቲካል ሳይንስ ፕሮፌሰር የሆኑት ጀትል ትሮንቨል እንደሚሉት በሀገር ሽማግሌዎች የተጀመረው የማሸማገል ጥረት ተስፋ አስቆራጭ አለመሆኑን ጠቅሰው አለም አቀፉም ማህበረሰብ የማሸማገሉን ሚና ቢወስድ ተቀባይነት ያለው አካሄድ መሆኑን አንስተው በተጨማሪ ሪፖርቱም የሀገር ሽማግሌዎች ሚና የሚያኮስስ አለመሆኑን ተናግረዋል።

እንደ ክራይስስ ግሩፕ እምነት ግን በሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ እና በሀገር ሽማግሌዎች ሁለቱን ወገኖች ለማወያየት እስከ አሁን የተሄደበት ርቀት ተስፋን ዉጤት ሊያስገኝ ባለመቻሉ እና የጉዳዩ እሳሳቢነት የውጭ ኃይል ሽምግልናን የሚጠይቅ ነው ብሎ እንደሚያምን የክራይስስ ግሩፕ ከፍተኛ ተንታኝ የሆኑት ዊሊያን ዳቪሰን ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል ።

የደብረፂዮን መራሹ የትግራይ ክልል መንግሥት ከብልፅግና ፓርቲ መመስረት ወዲህ ልዩነታቸው እየተንቦረቀቀ መጥቶ አስጊ የሆነ የግጭት አፋፍ ላይ ቆመው ባሉበት ጊዜ የወጣው ባለ 14 ገፁ የአለም አቀፉ ክራይስስ ግሩፕ ሪፖርት የአህጉራዊውን ድርጅቱ መሪ የወቅቱ የህብረቱ ሊቀመንበር የሆኑትን የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ስሪል ራማፎዛን ጠቁማል፡፡

እንደ አቶ ጌታቸው ረዳ የትግራይ ክልላዊ መንግስት አማካሪ እና የህወሃት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አስተያት ግን የኛን ቋንቋ የማይሰማ አሸማጋይ አያስፈልግም በማለት ምክረ ሃሳቡን አጣጥለዋል።ጌታቸው አክለውም ሃይሌ ገብረስላሴ እያለ የምን ራማፎዛ ብለው ይጠይቃሉ፡፡

የጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ መንግሥት ምንም አይነት ወታደራዊ እርምጃ የመወሰድ ፍላጎት እንደሌላቸው በግልፅ የተናገሩ ሲሆን ከዚህ ውጪ ቢሆን ግን ትልቅ ስህተት መስራት ነው ብለዋል። ቃላቸውንም በተግባር እንዲያውሉ መክረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ የኖቤል ተሸላሚ መሆናቸው ተጨማሪ ኃላፊነት ስለሚጥልባቸው ገዳዩን በምክክር ለመፍታት ረጅም ርቀት መሄድ ይጠበቅባቸዋል ሲል ሪፖርቱ ያመላክታል። የሀገር ሽማግሌዎች ሁለት ወራት በፊት መቀሎ በመጡበት ጊዜ ተነጋግረን የነበረው ብሄራዊ መግባባትን ለማምጣት አጠቃላይ የብሄር ብሄረሰብ ውክልና ያላቸው ሁሉም ወገኖች የሚሳተፉበት መድረክ ይኑር ብለን እየጥበቅን ነበር።

ጌታቸው በበኩላቸው የሽምግናወን ጉዳይ “አባሎቻችንን ወክለን እንደዚህ አይነቱን ብሄራዊ የመግባባት መድረክ እየጠበቅን ባለንበት ሁኔታ ግን ከ15 ቀናት በፊት ሌሎች ድርጅቶች ስለሌሉ ብልፅግና እና ህወሃት እነጋገር ብለውን ነበር። ህወሓት ግን አስረግጦ ያንፀባረቀው አቋም ቢኖር የሀገሪቱን ችግሮች ለመፍታት የገመገምንበት አግባብ የኹለቱ ወገኖች ተሰናስሎ በመስራት ብቻ የሚፈታ ስላልኆነ አይሆንም ብለናቸዋል። የሁሉንም ድርጅት አመራር በሚባል መልኩ አስሮ እንደራደር ማለት ማላገጥ ነው፡፡” ሲሉ ለአዲስ ማለዳ አስታውሰዋል።ስለሆነም ችገርችንን ለመፍታት ብሔራዊ መግባባትና ውይይት ያስፈልጋል ባይ ናቸው፡፡
ጌታቸው አክለውም አሁን ላይ በአገሪቱ በተለያዩ ቦታዎች ለሚፈጠሩ ችግሮች ህወሓትን መክሰስና መወንጀል ለውጥ አያመጣም ትክክልም አይደለም ሲሉ ይገልጻሉ፡፡

ቅጽ 2 ቁጥር 94 ነሐሴ 16 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here