ሹመኞች በተመደቡበት ስፍራ ይሰንብቱ!!

0
986

ካለፉት ኹለት ዓመት ተኩል ጀምሮ ለውጥ ንፋስ የምትተነፍሰው ኢትዮጵያ በርካታ አብይ ጉዳዮች ሲሰሙባት እና ሲታዩባት ውላ የምታድር አገር ከሆነች ዋል አደር ብላለች። ከጸጥታ ችግሮች፣ ከፖለቲካዊ ውጥንቅጥ እና መሰል ጉዳዮች ባለፈ የሚንስትሮች እና ካቢኔዎች ሹም ሽር እና በአንድ ስፍራ ረግቶ ያለመቆየት ጥበብንም አቻችላ የምትሔድ አገር አስከመሆንም ደርሰናል። በእርግጥ ወቅቱ ከፍተኛ ውጥረቶች እና ከለውጡ ጋር አብሮ ለመሄድ የማይቻልበት ጉዳዮችም በታታላቅ የአመራር ስፍራ ላይ በተቀመጡ ግለሰቦች ዘንድ እየታየ የሚገኝ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ መንግስትም የከፍተኛ አመራሮችን ስፍራ ወይም የኃላፊነት ሽግሽግ ማድረጉ የሚያስወቅሰው እንዳልሆነ አዲስ ማለዳ ትረዳለች።

በተለይ ደግሞ ከዚህ ቀደም ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አሕመድ (ዶ/ር) ለመግለጽ እንደሞከሩት ለውጡ የመጣላቸው እና የመጣባቸው ሰዎች መኖራቸውን ገልጸው የነበረ ሲሆን ይህም ደሰግሞ ለውጡ ከመጣባቸው የከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችም በመኖራቸው ሽግሽጉ እና ከኃላፊነት የመነሳቱ ጉዳይ ለነገ በይደር የሚቆይ ጉዳይ እንዳልሆነ እና አገርን እና ሕዝብን ከማዳን በተገናኘ ወሳኝ እርምጃም እንደሆነ ለመረዳት የሚያቅት ጉዳይ አይደለም።

ይሁን እንጂ በእነዚህ ኹለት ኣመት ከመንፈቅ ውስጥ ግን ከአንደኛው የሚንስትር መስሪያ ቤት ወደ ሌላኛው የሚንስትር ቢሮ የሚደረገው ዝውውር እና ፈጣን የከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ዝውውር በአሉታዊ ጎኑም የሚነሳበት ጉዳይ ለመኖሩም መንግስት ልብ ሊለው እንደሚገባ አዲስ ማለዳ ታስገነዝባለች። በተለይ አንዳንድ መስሪያ ቤቶች እጅግ የፈጠነ የሚንስትሮች እና ከፍተኛ አመራሮች ሽግሽጎች ተደርገውባቸዋል በዚህም ረገድ ሚንስትሮች የራሳቸውን አሻራ ጥለው እንዳያልፉ እና ለአገር እድገትም የበኩላቸውን ድርሻ እንዳይወጡ እንደሚያደርግም አዲስ ማለዳ በጽኑ ታምናለች።

የጠቅላይ ሚንስትር አብይ አሕመድ መምግስት ወደ ስልጣን ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ ከፍተኛ የሚንስትር እና አመራሮች ዝውውር ከተካሔደባቸው ዋና ዋና መስሪያ ቤቶች ውስጥ የኢፌዲሪ መከላከያ ሚንስቴር እና ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ተጠቃሽ ናቸው። በለውጡ የመጀመሪያ ቀናት ከለውጡ በፊት የነበሩት ሲራጅ ፈጌሳ ተነስተው በምትካቸው የመጀመሪያዋ የሴት ሚኒስቴር በመስሪያ ቤቱ ታሪክ የተመደቡት ኢንጅነር አይሻ መሐመድ ነበሩ። በሙያቸው የምህንድስና ጠበብት የሆኑት አይሻ እምብዛም የስራ ከባቢውን በሚገባ ሳይለምዱ እና ሳይዋሃዳቸው በሞቱማ መቃሳ ተተክተው መከላከያን ለቀው እንዲወጡ ተደርገው ወደ ከተማ እና ኮንስትራክሽን እንዲዛወሩ ተደረገ።

ከለውጡ ወዲህ ሦስተኛ ሚንስትር የሆኑት ሞቱማ መቃሳም በቀድሞው የኦሮሚያ ርዕሰ መስተዳደር እና ለውጡ ፌት መስመር ተሰላፊው ለማመገርሳ ተተክተው ስፍራውን ለተረካቢ አስረክበዋል። እነሆ ታዲያ ጊዜው በከፍተኛ ፍጥነት ነጉዶ ለማ መገርሳም ከፓርቲው ጋር ያላቸው ግንኙነት በይፋ ከተቋረጠ ከጥቂት ቀናት በኋላ በቀድሞው ከታዛዣቸው ቀነዐ ያደታ ተተክተው ቢሮውን ለቀው ሔደዋል።

አምስት ሚንስትሮችን የቀያየረው መከላከያ ሚኒስቴር በአጭር ጊዜ ይህን ያህል የአመራር ለውጥ በመስሪያ ቤቱ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ቀላል እንደማይሆን አዲስ ማለዳ በሚገባ ትረዳለች። አንደዚሁ በተመሳሳይ የፍትህ ስርኣቱ እጅግ በተንጋደደባት ኢትዮጵያ ተቋማዊ ጥንካሬን ለመገንባት በሚል ሰፊ ጥረት ሚያደርገው የአብይ አሕመድ መንግስት በተቅላይ አቃቤ ሕግም በኩል ከፍተኛ የሆነ መተካካቶችን ማድረጉን እና ይህም ለፍትህ ስርዓቱ መሻሻል ሊያመጣ የሚችለው ጠቀሜታ እምብዛም እንደሆነ አዲስ ማለዳ ትገነዘባለች።

በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በመጀመሪያ ጌታቸው አምባየ መስሪያ ቤቱን ሲመሩ እስከ ለውጡ መጀመሪያ ጊዜያቶች ቢቆዩም በኋላ ላይ ደግሞ ብርሀኑ ጸጋየ ስፍራውን ተቆናጠው ተጣለባቸውን ኃላፊነት ለመወጣት ሲንቀሳቀሱም ነበር። ይሁን እንጂ ብሀኑ ጸጋየ ከኃላፊነታቸው ተነስተው በአምባሳደርነት ሹመት ወደ ጎረቤት አገር ጅቡቲ ሲያቀኑ አሁኗ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከገቢዎች ሚንስትርነት ተነስተው ስፍራውን ለመምራት በቁ።

የቅጽበት ያህል በኃላፊነቱ ላይ ቆዩት አዳነች ምንም እንኳን በቆይታቸው ቀላል የማይባል ተግባራትን ቢያከናውኑም ወዲያው ተነስተው በምትካቸው ከአዳነች ስር ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩት ወጣቱ የሕግ ምሁር ጌዴዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ከቀናት በፊት በይፋ የኃላፊነቱን መንበር ተቆናጠውታል። ይህ ከአንድ ስፍራ በወራት ዕደሜ ብቻ የመቆየት አካሔድ ሹመኞች ያሰቡትን ከፍም ሆነ ደግ ሀሳብ ተግባራዊ እነዳያደርጉት እንደሚያደርጋቸው እና በተቋማትም ላይ ሚኖረው ፈጣናዊ የስራ ከባቢ እና አዳዲስ ተመዳቢዎች አሉታዊ ጎናቸው እንዲሰፋ ያደርጋል ስትል አዲስ ማለዳ ታምናለች።

የመንግስት ሹመኞች በአንድ ስፍራ ዘለግ ላለ ጊዜ በሚቆዩበት ጊዜ የስልጣን ሁሉ ባለቤት ሆነው ሕዝብ በደግ ስራቸው ሊያደንቃቸው ወይም በሰሩት ስህተት ደግሞ ሊወቅሳቸው ከፍ ካለም በሕግ ፊት ቀርበው እንዲጠየቁ ማድረግ የሚችለው በሰሩበት የተራዘመ ጊዜ አንድ ስፍራ ላይ መቆየት ሲችሉ እንደሆነም አዲስ ማለዳ ታምናለች።

ከዚህም በመነሳት ከአንግዲህ ወዲያ በሚደረገው አዳዲስ ሹመቶች እና ምደባዎች ላይ መንግስት በመጀመሪያ ደረጃ ለስፍው ተስማሚ የሆነ እና ከትምህር ዝግጅቶቻቸው ጋር በተያያዘ ሰፊ ግምገማ አድርጎ እንዲመድብ ያስፈልጋል ስትል አዲስ ማለዳ ትናገራለች። ከዚህም ቀጥሎ ደግሞ በአንድ ስፍራ በሚመደቡበት ወቅትም ቆይታቸው ቢያንስ ለመመስገን ወይም ለመወቀስ ሚያበቃቸው ጊዜ እንዲቆዩ እና እንዲሰነብቱ ታሳስባለች።

ይህ ባልሆነበት ሁኔታ ግን ከዚህ ቀደም ይታይ እንደነበረው በአጫጭር ጊዜ የሚደረጉት ሽግግሮች ውስጥ ለሚጠፋው ጥፋት እና ብልሹ አሰራር ማንንም በድፍረት ተጠያቂ ማድረግ የማይቻልበትን ሁኔታ መፍጠር ስለሚሆን ጉዳዩ በአጽንኦት መታየት እንደሚኖርበት አዲስ ማለዳ ተስገነዝባለች።

ተጠያቂነቱ በመንግስት ዘንድ ከሌለ እና በሕዝብም በኩል ይህን አይነት ጥፋቶች እየተስተዋሉ አጥፊዎች ለሕግ የማይቀርቡበት አካሔድ ከመጣም ሕዝብ በመንግስት ላይ ሊያሳድረው የሚችለው አመኔታ ከኹሉም በላይ ደግሞ በቅርበት ተመካክሮ የመስራት መንፈስ ስለሚዳከም አገርን አደጋ ላይ የሚጥል ጉዳይ እንደሚኖር ከወዲሁ ሊጤንበት እንደሚገባም እሙን ነው።

በዚህ ብቻ ሳይበቃም የኃላፊነት መሸሽ ተግባራትም እና ከተጠያቂነት ለመዳን አንዱ የስራ ኃላፊ በሌላው የስራ ኃላፊ ላይ ጣት መቀሳስ እና አለመተማመን በመንግስት ካቢኔዎችም ላይ ያለመርጋት እና በአንድ ልብ በአንድ መንፈስ ያለመቆም ሁኔታን እንደሚጥር ከወዲሁ ሊታወቅ የሚገባ ጉዳይ እንደሆነ አዲስ ማለዳ ሀሳቧን ትደመድማለች።

ቅጽ 2 ቁጥር 94 ነሐሴ 16 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here