ስለሴቶች የሚሠራው ማን ነው?

0
824

የሴቶችን ጉዳይ በሚመለከት እንሠራለን የሚሉ በርካታና ከአገር ውስጥ እንዲሁም ከውጪ ድጋፍ የሚያገኙ ተቋማትና ማኅበራት አሉ። በመሃል ከተማ ተመሥርተው አገልግሎታቸውም በመሃል ከተማ የተወሰነ ቁጥራቸው ቀላል አይደለም። በተለያየ ጊዜም ሴቶችን በሚመለከት ሽልማት ጀምረው ከአንድ ዓመት ወይም ከአንድ ክዋኔ ሳይዘሉ የቀሩ አሉ። አልያም አንዲት ሴት ላይ በደረሰ አደጋ ምክንያት ‹ሆ!› ብለው ተነስተው ተዓምር ፈጠሩ ሲባል በማግስቱ በዝምታ ሆነ የተገኙ።

በጥቅሉ ግን ‹ያገባኛል› ባዩ ብዙ ነው። ስለዚህም ነው መሰለኝ ከአንድ አካል ጠብ ያለ ነገር አይገኝም። በአንድ ጀንበር ሁሉም ይስተካከል ማለት ባይሆንም በጊዜ ርቀት እንኳ በጎ ለውጦችን ማየት ከባድ ነው፣ ትልቅ አጉሊ መነጽር ያስፈልጋል።

አንድ እውነት አለ፤ ለውጥ የመጣባቸው ጉዳዮች አሉ። ለምሳሌ ትምህርት። በየዓመቱ በዩኒቨርሲቲ ገብተው ትምህርታቸውን ጨርሰው የሚመረቁ ሴቶች ቁጥር መሻሻልን እያሳየ ነው። በተለያየ የትምህርት ዘርፍና የሥራ መስክም ሴቶችም እንመለከታለን። ይህ በአንድ ጀንበር የመጣ አይደለም፣ የብዙ ጊዜ ጥረት አለበት።

ግን ጎዳና ላይ ሴቶችን አሁንም እናያለን። አሁንም በሴተኛ አዳሪነት የሚተዳደሩ ሴቶች ቁጥር ቀላል አይደለም። ዛሬም እስከ ሞት የሚያደርስ ጥቃት የሚደርስባቸው ሴቶች አሉ። ሕጻናት አሁንም ይደፈራሉ። ‹ሕጉ ጠበቅ ይበል› የሚሉ አስተያየቶች ዛሬም እንሰማለን። ዛሬም የትምህርት ውጤታቸውን ለመወሰን እውቀታቸው ሳይሆን ሴትነታቸው የሚጠየቅ ሴቶች አሉ። ዛሬም ሥራ አመልክቶ ለማለፍ በ‹ሴትነት› መፈተን አንዱ መስፈርት ነው።

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት፣ በሴቶች ሥም የሚንቀሳቀሱ ማኅበራት፣ ንቅናቄዎች፣ ወቅት ጠብቀውና ክስተትን ተገን አድርገው የሚታዩ ቅስቀሳዎችን እንታዘባለን። የሴቶች ቀን ድል ባለ ድግስ ሲደገስ እናያለን። ለውጦች ግን ቀርፋፋ ናቸው። እርግጥ ነው ጊዜ ሊወስድ ይችላል፤ ግን ምክንያቱ እሱ ብቻ አይመስለኝም።

በኢንግሊዝ አፍ የሚወያዩ ከተሜ የሴት መብት ተሟጋቾች የገጠሯን ሴት በሐሳብ እንጂ በአካል አያውቋትም፣ ባይ ነኝ። የሚጎድላትን ቁስ ያውቁ ይሆናል እንጂ የሚያስፈልጋትን አይረዱም።
ይህን ስል ምክንያት አለኝ። በወሊድ ምክንያት የምትሞት ሴት አሁንም በገጠር አለች። ፌስቱላ ዛሬም በኢትዮጵያ ያልተቀረፈ ችግር ነው። አንዳንዴ አስባለሁ! የኢትዮጵያ አምላክ ሲረዳን ካትሪን ሐምሊን (ነፍሰ ሔር) ባይመጡልን ኖሮ በፌስቱላ ላይ የሚሠራ ሰው ከእኛው ውስጥ እናገኝ ነበርን? ብናገኝስ አንዘገይም ነበር? ከተማ ሳይሆን ገጠር ላለች ሴት ፈተና ነውና፣ ማን ጉዳዩ ትዝ ይለው ነበር?

በከንባታ የሴቶች ግርዛትን በሚመለከት ዶ/ር ቦጋለች ገብሬ (ነፍሰ ሔር) ባይነሱ ኖሮ፣ አሁን ስለሴቶች መብት እንከራከራለን የሚሉ ሰዎች ነገሩ ስለመኖሩስ ያውቁ ነበር? አዎን! መንግሥትን የምንወቅስበት እልፍ ሰበብ አለን። ምክንያቱም መንግሥት ሁሉም ጋር የመድረስ አቅም፣ ሥልጣንና ኃላፊነትም አለበት።

መንግሥትም ግን መቀመጫው ከተማ ብቻ ይመስላል። ከከተማ የሚወጣው ለድግስ ብቻ፤ እናም ለሴቶች መብት የሚሟገቱ ሰዎች ከሁሉም አቅጣጫ ያለውን ችግር አንስተው ካልወተወቱት ለውጥ አያመጣም። እንኳንና እየሆነ እየተደረገ ያለውን ከመቶ ዓመት በፊት ሆኗል ያሉትን አንስተው መንግሥትን እረፍት የሚያሳጡትን እያየን አይደለ?

እየፈረድኩ አይደለም። ሁሉም የሚከራከርበት የየራሱ አንጻር ይኖረዋል። ግን በአንድ ጉዳይ ላይ እሠራለሁ ያለ፣ ሌላውም እንዳይሠራ መሰናክል ሆኖ፣ ራሱም ደኅና አድርጎ ካልሠራ ዋጋ እንደሌለው አምናለሁ። ለዛም ነው ልጠይቅ የወደድኩት፣ የእውነት ስለሴቶች የእውነትም ለሴቶች መብትና ክብር የሚሠራ ማን ነው?
ሊድያ ተስፋዬ

ቅጽ 2 ቁጥር 95 ነሐሴ 23 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here