የከተሞች መስፋት ያፈናቀላቸው አርሶ አደሮች ካሣ – መልሶ ማቋቋም – ስጋት

0
1166

ሰሙ ሁንዴ የ103 ዓመት አዛውንት ናቸው። ነዋሪነታቸው በአዲስ አበባ የካ ክፍለ ከተማ መሪ ሎቄ አካባቢ ነው። ከዓመታት በፊት በአርሶ አደርነት ኑሯቸውን ይመሩ የነበሩት የስድስት ልጆች አባት ዕድሜያቸውም ገፍቶ ኑሯቸውም እንደቀደመው አልሆን ብሏቸዋል። እስከ 1990ዎቹ መጀመሪያ ዓመታት ድረስ ለእርሻ ይገለገሉበት የነበሩበት መሬት ለልማት በሚል በመወሰዱ ዛሬ ኑሯቸው ከግብርና ወደ ሰነድ አልባ (ካርታ የሌለው) ቤት አከራይነት ተለውጧል። ከሚያከራዩዋቸው ደሳሳ ቤቶች በወር እስከ ሁለት ሺሕ ብር የሚያገኙ ሲሆን ኑሯቸውን ልጆቻቸው እና መንግሥት በሚሰጣቸው ገንዘብ ይደጉማሉ።

በልማት ሥም ወደ ከተማ አስተዳደሩ የመሬት ባንክ የገባው የእርሻ ቦታ 30 ጥማድ (10 ሔክታር አካባቢ እንደማለት ነው) እንደሆነ የሚገልጹት አዛውንቱ የእርሻ ቦታው በካሬ ሦስት ብር ከ35 ሳንቲም እንዲሁም የግጦሽ መሬቱ ደግሞ በአንድ ብር ከ35 ሳንቲም አካባቢ መገመቱንም ያስታውሳሉ። በአጠቃላይ 70 ሺሕ ብር አካባቢ ካሳ የተከፈላቸው አዛውንቱ በአርሶ አደርነት ሕይወታቸው ሙሉ የነበረው ቤት ዛሬ ላይ መጉደሉን በመጥቀስ በመንግሥት ቅሬታ እንዳላቸው ይናገራሉ። እዚያው ማሳቸው ላይ ሁለት ቦታ የመኖሪያ ቤት ቦታ የነበራቸው ቢሆንም ኹለት አይቻልም ተብለው አንዱን እንዲለቁ መደረጉን በመግለጽም ዛሬ ላይ ሕጋዊ ካርታ በሌለው ቤት እየኖሩ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ከተነሱ በኋላስ?
በተለይም በአዲስ አበባ የልማት ተነሽ አርሶ አደሮች መልሶ ማቋቋም ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት መረጃ እንደሚያሳየው በአዲስ አበባ በተለይም በማስፋፊያ ቦታ ላይ የነበሩ 7327 የልማት ተነሽ አባ/እማወራ አርሶ አደሮች (ቤተሰቦቻቸውን ሲጨምር ቁጥሩ 35 ሺሕ 410 ይሆናል) ተለይተዋል።

ለገሰ ሰሙ፣ ከሰሙ ሁንዴ ልጆች አንዱ ሲሆኑ አሁን ላይ የ61 ዓመት አዛውንት ናቸው። እሳቸውም እስከ 1996 ድረስ በግብርና ሥራ ይተዳደሩ የነበረ ሲሆን በልማቱ ምክንያት 25 ጥማድ ያውል የነበረው የእርሻ ማሳቸው በካሬ ሦስት ብር ከ35 ሳንቲም ተገምቶ በአጠቃላይ 50 ሺሕ ብር ካሣ ተሰጥቷቸው ኑሯቸው ዛሬ ሌላ መልክ እንዲይዝ ሆኗል። ለገሰ እንደሚሉት ከሆነ የእርሻ ማሳቸውን እንዲለቁ ካሣ ሲገመትላቸው በካሬ ሦስት ብር አካባቢ የነበረ ቢሆንም በዚያው ወቅት መንግሥት ግን ለጨረታ ባቀረበው መሬት የመነሻ ዋጋ በካሬ 165 ብር ማስታወቂያ ሲያስነግር ነበር።

የሕግ ባለሙያው አበበ አሳመረ እንደሚሉት ካሣ ግምቱ አናሳ ከመሆኑም ባሻገር ከወቅቱ ገበያ ጋር እየተገናዘበ አለመሰላቱ ችግር ነበር። ለካሳ ማነሱ ምክንያት የሚሆነውም “ምን ያመጣሉ መሬት የመንግሥት ነው” የሚለው የተሳሳተ እሳቤ ላይ የተመሠረተ አካሔድ ነውም ብለው ያምናሉ። በዚህም አርሶ አደሩ ብቻ ሳይሆን ከመሐል ከተማ ሲነሳ የነበረው የልማት ተፈናቃይም ተጎድቷል ይላሉ።

ቀድመን የጠቀስናቸው ጥናቶችም የሚሰጡ የካሣ ክፍያዎች በቂ እንዳልነበሩ የሚያመለክቱ ናቸው። የአምስት ልጆች አባት የሆኑት ለገሰ ለቤት መሥሪያ የከለሉትን ከሁለት ሺሕ ካሬ በላይ ቦታ ለእሳቸውም ጨምሮ ለስድስት ከፍለው ጎጆ የቀለሱ ሲሆን ካርታ ለማውጣት ግን አልቻሉም። ምክንያቱ ደግሞ የሚፈቀደው 500 ካሬ ብቻ ስለሆነ ካርታ ለማውጣት ሲለካ የሚተርፈው ወደ መሬት ባንክ ገቢ ይደረጋል ስለሚባል እንደሆነ ያነሳሉ። የልማት ተነሽ አርሶ አደሮቹ ጥያቄ ደግሞ በያዝነው ቦታ ልክ ካርታው ተሠርቶ ይሰጠን የሚል ስለሆነ በዚህ አለመግባባት እስካሁን ቤታቸው ሰነድ አልባ ነው። ንጉሡ ስለዚህ ሲያስረዱ ሰዎች ሰፊ ቦታ ይዘው ካርታ እንዲሠራላቸው ሊፈልጉ ይችላሉ፤ ይሁንና ከመሬት ውስን ሀብትነት አኳያ መንግሥት ለመኖሪያ ቤት በቂ ነው የሚለውን ለባለይዞታዎቹ ሰጥቶ የተረፈውን ለሌላ ልማት እንደሚወስድ፣ መሬትም የሕዝብና የመንግሥት የጋራ ሀብት መሆኑ መዘንጋት እንደሌለበት ያስገነዝባሉ።

መሬቱ ለልማት ይፈለጋል ተብሎ መኃንዲስ መጥቶ ሲለካ ከአንድም ሁለት ጊዜ መኃንዲሱን አባርሬ ነበር የሚሉት ለገሰ፣ ኋላ ላይ የመንግሥት ውሳኔ ነው በመባሉና የቀበሌው አስተዳዳሪም መጥቶ ስላነጋገራቸው “የመንግሥት ውሳኔ ከሆነማ ምን አደርጋለሁ” ብለው እንደተስማሙ ያስታውሳሉ። ይሁንና በወቅቱ (1996 አካባቢ) የከተማ አስተዳደሩ አርሶ አደሩን ሲያወያይ መሬቱ ሳይወሰድ በፊት አርሶ አደሩን አደራጅቶና አሠልጥኖ ወደ ሥራ በማስገባት በአርሶ አደርነት ከሚያገኘው ገቢ በተሻለ ሕይወቱን መለወጥ እንደሚቻል አሳዩን የሚል ጥያቄን ሲያነሱ፥ አዳራሽ ሙሉ ጭብጨባ እንደተቀበላቸው የሚስታውሱት ለገሰ ያ ባለለመደረጉ ግን ዛሬ ላይ ከአርሶ አደርነት ሕይወታቸው ጋር ‹ሰማይና ምድር› የሆነ የሕይወት ልዩነትን እያስተናገዱ ስለመሆኑ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

በተሰጣቸው ካሣ ምን ምን መሥራት እንደሚቻል ሥልጠና ከመስጠት ይልቅ አንድ ቀን ጠዋት ድንገት የካሣ ብር ውሰዱ ተብለው ገንዘቡን እንደተቀበሉም ያስታውሳሉ፤ ይህም እንዳልጠቀማቸው ነው የሚናገሩት። አርሶ አደር እያሉ በሚያመርቱት ጤፍ፣ ስንዴ፣ ምስርና ጓያ ከራሳቸው አልፈው ለሸማቹ ማኅበረሰብ ለመሸጥ ገበያ ያወጡ እንደነበር በማስታወስ ዛሬ ያ ሁሉ አልፎ በሚያገኟት ሁለት ሺሕ ብር የቤት ኪራይ ላይ መንግሥት ከሐምሌ 2009 ጀምሮ ለምግብ ፍጆታ በሚል በየሦስት ወሩ ከሚሰጣቸው 5175 ብር ጋር እያዳመሩ ኑሮን በመግፋት ላይ እንደሚገኙ ያስረዳሉ።

የወንድወሰን እንደሚሉት የልማት ተነሽ አርሶ አደሮቹ ካሣ ከተከፈላቸው በኋላ በገንዘቡ እንዴት ሠርቶ መለወጥ እንደሚቻል የሚያስገነዝብ ምንም ዓይነት ሥልጠና እንዲወስዱ አለመደረጉ ዛሬ ላይ ለችግር እንዲጋለጡ አድርጓል። ንጉሡም በዚህ ሐሳብ ይስማማሉ፤ የልማት ተነሽዎች የካሣ መተመኛ መመሪያን መሠረት ተደርጎ ካሣ ይሰላ እንጂ መጀመሪያውኑ በካሬ ይከፈል የነበረው ገንዘብ አነስተኛ እንደሆነ (በቂ ነው የሚል እምነት እንደሌላቸው) ያነሳሉ። ይሁንና ከፍተኛ ካሣ ቢከፈለውም እንኳን በአርሶ አደርነት ሕይወታቸው ሲያገኙ ከነበረው ገቢ አንፃር ዝቅተኛ የሚሆንባቸው እንዳሉ፣ እንዲሁም ከተነሱ በኋላ ሥልጠናና በቂ ክትትል ባለመደረጉ ዛሬ ላይ ገንዘቡን ጨርሰው ሌላ ቅሬታ እንዲያነሱ ስለማድረጉም ይገልጻሉ። የወንድወሰንም ቢሆኑ እስከ 700 ሺሕ ብር ካሣ የተከፈለው ተነሽ በገንዘቡ ተጨማሪ ገቢ የሚያስገኝ ሥራ ባለመሥራቱ ገንዘቡን ጨርሶ ዛሬ ላይ ክፍያው ትንሽ ነበር ሊል እንደሚችል ይጠቅሳሉ። የገንዘብ አጠቃቀም ግንዛቤን በማስረዳትና ወደ ሥራ እንዲገቡ በማድረጉ የጎላው እጥረት በመንግሥት በኩል የነበረ መሆኑን በመጥቀስም፥ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ የተቋቋመው ይህን ዓይነት ችግር ይቀርፍ ዘንድ መሆኑን ያስረዳሉ። እዚህ ላይ ግን ሙሉ በሙሉ ጥፋቱ የመንግሥት ብቻ ነው ተብሎ እንደማይወሰድ አስተያየት ሰጭዎች ያሠምሩበታል።

ለገሰ በቀለ ወጣት ሲሆን በመሪ ሎቄ አካባቢ የሚኖር የአርሶ አደር ልጅ ነው። የእሱም ቤተሰብ ተመሳሳይ ሒደት ውስጥ እንዳለፈ በመጥቀስ ለልጅ 105 ካሬ ለቤተሰብ ደግሞ 300 ካሬ የቤት መሥሪያ ተሰጥቷቸው ሌላው ለልማት በሚል መወሰዱን ያስታውሳል። አብዛኞቹ የልማት ተፈናቃዮች በምጣኔ ሀብት በኩል በከባድ ችግር ውስጥ እየኖሩ ነው ብሎ የሚያምነው ወጣት ለገሰ የወጣቱ ጥያቄም ዘላቂ ገቢ በሚያስገኝ ዘርፍ ተደራጅቶ ሕይወቱን መለወጥና የመኖሪያ ቤት የማግኘት ቢሆንም ይህ ባለመሆኑ ለችግር ተጋልጧል፤ ለፖለቲካ ትኩሳትና ፍጆታ ሰለባም ሆኗል ይላል።

የወንድወሰን እንደሚሉት ከ1986 ጀምሮ በልማት የተነሱ አርሶ አደሮችን በአምስት ክፍል ለይተው በዘላቂነት የሚደገፉበትንና በመንግሥትና በራሳቸው ጥረት ሀብት የሚያፈሩበትን መንገድ ለማግኘት ጽሕፈት ቤቱ እየሠራ ይገኛል። ምንም ገቢ ለሌላቸውና መሥራት ለማይችሉት በዘላቂነት እንደየቤተሰባቸው ለምግብ ፍጆታ የገንዘብ ድጋፍ እየተደረገላቸው ነው። በዚህም 5563 የልማት ተነሽ አርሶ አደሮችንና ቤተሰቦቻቸው ዘላቂ የቀጥታ ድጋፍ አገልግሎት እያገኙ ነው የተባለ ሲሆን፣ የገንዘበ ድጋፉ እስከ ሕይወት ፍፃሜ አይቋረጥም። ከእነዚህ ውስጥም የመኖሪያ ቤት ችግር ያለባቸው ከ60 በላይ ተነሽዎች በየወሩ ለቤት ኪራይ በሚል ተጨማሪ ሦስት ሺሕ ብር እንደሚሰጣቸው ታውቋል። ሁለተኛው ክፍል ደግሞ ምንም ገቢ የሌላቸው ግን መሥራት የሚችሉ በሚል የተለዩ ሲሆን በጊዜያዊነት የገንዘብ ድጋፍ ይደረግላቸዋል። በዚህም 3029 ተነሽ አርሶ አደሮችና ቤተሰቦቻቸው በገንዘብ እየተደገፉ ነው። ለዚህም (በሁለቱ ክፍል ለተለዩ ተነሽዎች) ጽሕፈት ቤቱ በ2011 በጀት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ከ11 ሚሊዮን በላይ ገንዘብን ማውጣቱም ታውቋል።

እንደ የወንደወሰን ገለጻ መሥራት ለሚችሉት የሚደረገው የገንዘብ ድጋፍ (ጊዜያዊ የቀጥታ ድጋፍ) ለአንድ ዓመት ብቻ ሰጥቶ ወደ ሥራ ማስገባት እንደሚገባ መመሪያ አለ። ይሁንና ወደ ሥራ የሚገቡበት ሁኔታ ባለመመቻቸቱ ተረጂዎቹ ከአንድ ዓመት በላይ ገንዘብ እየተከፈላቸው ዛሬም ቀጥለዋል። ወደ ሥራ ለማስገባት ካልተቻለባቸው ምክንያቶች መካከል አንዱ የመሥሪያ ቦታን ከመሬት ልማት ማግኘት አዳጋችና ረጅም ቢሮክራሲን የሚፈልግ በመሆኑ ነው። ጽሕፈት ቤቱ አሁን ላይ 64 የተለያዩ ፕሮጀክቶችን (የትምህርት ቤት፣ የዶሮና እንስሳት እርባታ፣ የመሥሪያና መሸጫ ሼድ፣ ወዘተ) ግንባታዎችን በማቀድ ለተነሽዎቹ ዘላቂ የሥራ ዕድል ለመፍጠር እየሠራ መሆኑን በመጥቀስ ቦታው ግን ቶሎ እንደማይገኝ ይጠቅሳሉ።

ንጉሡ ግን በዚህ ሐሳብ አይስማሙም። ምክንያታቸውን ሲያስረዱም “ለተጠቃሚዎች ለማስተላለፍ የሚዘጋጁ ቦታዎችን የሚወስነው ካቢኔው ቢሆንም ቢሮው የተጠየቀውን ቦታ ማዘጋጀት እየቻለ ያልሠራበት መንገድ የለም። ግን የተጠየቁ ጥያቄዎች ሁሉ መቶ በመቶ ይመለሳሉ ባይባልም ቅድሚያ የሚሰጠው ለአርሶ አደር መልሶ ማቋቋም ነው፤ ጽሕፈት ቤቱ ፕሮጀክቶችን ነድፌ ቦታ አላገኘሁም ማለቱ ተገቢ አይደለም” ይላሉ።

ሥጋትስ የለም?
ከተነሽዎች ጋር በተያያዘ “የልማት ተነሽ ሳይሆኑ ተነሽ ነን ብለው የሚመጡ” መኖራቸውን የወንድወሰን ይጠቅሳሉ። ይህም ሌላ ፈተና ሆኗል። የአዲስ ማለዳ ምንጮች እንደሚሉት ደግሞ አቅሙ ያላቸውና የገንዘብ ቀጥታ ድጋፍ የማይገባቸው ሰዎች “ለእኛም” ገንዘብ ካልተሰጠን የሚል ጥያቄን ይዘው በተደጋጋሚ ወደ ቢሮ ይመላለሳሉ፤ ይህም ለመንግሥት ሌላው ስጋት ሆኗል። ይህን ጥያቄ የሚያቀርቡ ሰዎች የበረከቱት አንድም የተለዩ አቅመ ደካሞች ገንዘብ ሲረዱ ማየታቸው ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ ተቋቁሞ ወደ ሥራ በገባበት 2009 ወቅት ለሁሉም ተነሾች ገንዘብ ይሰጣል የሚል የተሳሳተ መረጃ መሰራጨቱ እደሆነ ይነሳል። ተጨማሪው ፈተና ደግሞ በሕይወት ከሌሉ አውራሾች ጋር የተያያዘ ውጣ ውረድ ነው፤ አሁን ላይም በሕይወት ከሌሉ 570 “አውራሾች” ወራሽ እንደሆኑ የሚጠይቁ 2135 “ወራሾች” በፍርድ ሒደት ውስጥ ስለመሆናቸው መረጃዎች ያሳያሉ። እነዚህ ጉዳዮችም ሌላ የስጋት ምንጭ ሆነው የሚታዩበት ሒደት አለ የሚሉ ወገኖች አሉ።

አዲስ ማለዳ ለጉዳዩ እጅግ ቅርብ ከሆኑ ምንጮቿ እንዳገኘችው መረጃ ከሆነም በልማት ተነሽ አርሶ አደሮች መልሶ ማቋቋም ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት (አንድ ማዕከልና አምስት ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች አሉት) አንድን ብሔር ብቻ መሠረት ያደረገ የሥራ ኃላፊዎች ሹመት ተፈፅሟል። ምንጮቻችን ይህ አካሔድም ጤናማ ነው ብለው አያምኑም። በቅርቡም በአቃቂ ከአርሶ አደሮች ለልማት የተወሰደን ቦታ ለመለካት ወደ ሥፍራዎቹ ያቀኑ የመሬት ልማት ባለሙያዎች በነዋሪዎች ማባረርና ማስፈራራት እንዲደርስባቸው በቅርንጫፍ ኃላፊዎች ሳይቀር የማነሳሳትና አርሶ አደር የነበሩ ሰዎች ወደ አመፅ እንዲገቡ የማድረግ ሙከራ ተስተውሎ እንደነበር ምንጮቻችን ጠቁመዋል።

አበበ በአዲስ አበባ አስተዳደር ውስጥ ሲሠሩ በነበረበት ወቅት እንደሚያስታውሱት አርሶ አደሮቹ ለልማት ሲነሱ ለቤት መሥሪያ ቦታ ይሰጡ ነበር። ግን ልጆቻቸው እያደጉ ሲመጡ የቤት መሥሪያ ቦታ ስለሚፈልጉ ጥያቄዎቹ የፖለቲካ መልክ እንዲይዙ እየሆኑ መጥተዋል። ተነሽዎች በተሰጣቸው ቦታ ላይ ደስተኛ አለመሆንም ሌላው ችግር ፈጣሪ ምክንያት ሆኗል ብለው ያምናሉ። በተጨማሪም ለማቋቋሚያ የሚቀረፁ ፕሮጀክቶች ያለበቂ የአዋጭነትና ዘላቂነት ጥናት በስሜት የተጀመሩ ስለነበሩም ፕሮጀክቶቹ ብዙም ሳይጠቅሙ ውድቀት አጋጥሟቸዋል።

ወጣቱ በዘላቂ ሥራ ዘርፍ ተደራጅቶ መሥራት ቢችል መጥፎ ነገር ለማሰብም ጊዜ ስለማያገኝ የፀጥታም ሆነ የሌላ ስጋት እንደማይሆን የሚያምነው ወጣት ለገሰ “ወጣቱ ሥራ በማጣቱ ነው ችግር የሚፈጥረው” ይላል። ይሁንና መንግሥት ለተገቢ ጥያቄዎች መልስ ከመስጠት ይልቅ ማዋከብ ውስጥ ገብቶ እንደነበር ይጠቅሳል። ለአብነት በሚልም ራሱ (ለገሰ) ከተፈናቃዮች ተጠቃሚነት ጋር በተያየዘ ጥያቄ በማንሳቱ ለተደጋጋሚ እስር እንደተዳረገ ይናገራል። ይሁን እንጂ አሁን ላይ በአስተዳደሩ በኩል በተጀመሩ አዳዲስ የልማት ዕቅዶች ተስፋ እንዳለውም አልሸሸገም። ስለሆነም መንግሥት እቅዶቹን ፈጥኖ በመተግበር ወጣቱን ወደ ሥራ ማስገባት እንደሚጠበቅበትም ይመክራል።

ኮንዶሚኒየም ለአዲስ አበቤዎች የተሰቀለ ዳቦ?
የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር በ2009 አድርጎት በነበረው ጥናት በኢትዮጵያ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ቤተሰብ ቤት ይፈልጋል፤ ሚኒስቴሩ እንደሚለው በየዓመቱ ተጨማሪ 100 ሺህ ቤት ፈላጊዎች እየተፈጠሩ ነው። ይህም አንድ ዓመት በጨመረ ቁጥር የመኖሪያ ቤት ፍላጎቱ ላይ ተጨማሪ መቶ ሺህ ፍላጎት እተደመረ ነው ማለት ነው። አዲስ አበባ በተለየ የቤት ችግር ሰለባ ስትሆን ከ2009 ጀምሮ የአዳዲስ የጋራ መኖሪያ ቤት ግንባታን አቋርጣለች፤ ቀድመው የተጀመሩ 132 ሺህ ገደማ ቤቶችንም እስካሁን ገንብታ ማጠናቀቅ አልቻለችም። ለመጨረሻ ጊዜ 30 ሺህ የመኖሪያ ቤቶችን በዕጣ ሐምሌ 2008 ካስተላለፈች በኋላ እስካሁን የተላለፈ ቤት የለም። አስተዳደሩ ጥቅምት 30/2011 አስተላልፋቸዋለሁ በሚል ቃል ገብቶ የነበሩ 42 ሺህ ቤቶችንም ለማይታወቅ ጊዜ አራዝሟል። ይህም በጋራ መኖሪያ ቤቶች ላይ ጥያቄዎችን እንደአዲስ ማስነሳት ጀምሯል።

አዲስ አበባና የቤት ጥያቄ
ለአዲስ አበባ ነዋሪዎች ከተጋረጡ ፈተናዎች መካከል ትልቁ የመኖሪያ ቤት አቅርቦት ነው። የነዋሪው በቤተሰብ ደረጃ የነፍስ ወከፍ ቤት ባለቤትነት እንደማይሳካ መንግሥት በቅርቡ ያሳወቀ ሲሆን ‹‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ›› እንዲሉ ቢያንስ የቤት ኪራይን በተመለከተ ሕጋዊ ማዕቀፍ አዘጋጃለሁ ያለውንም ቃል ሳይፈፀም ዓመታት ነጉደዋል።
የአዲስ አበባ አስተዳደር ላለፉት 14 ዓመታት የጋራ መኖሪያ ቤት ልማት በማካሄድ የቤት ችግርን ለመፍታት ሞክሯል። ይሁንና ከ1997 ጀምሮ ተገንብተው የተላለፉ የጋራ መኖሪያ ቤቶች 183 ሺህ 221 ገደማ ናቸው። በየወሩ ከዕለት ኑሯቸው ቀንሰው እየከፈሉ ለሚቆጥቡትና ቤታቸውን ለሚያስገነቡት አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ተመዝጋቢዎች በዕጣ የተላለፉት ቤቶች ቁጥር ከ167 ሺህ 605 መብለጥ አልቻለም።

ቀሪዎቹ ከ15 ሺህ 616 በላይ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግን ለልማት ተነሺዎች፣ ለመንግሥት ሹመኞች፣ ለመከላከያ ሠራዊት እና ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በጨረታ፣ በአነስተኛ ኪራይና በሽያጭ ተላልፈዋል። የንግድ ቤቶችም ይገኛሉ። በተመዝጋቢው ቁጠባ በሚገነቡ ቤቶች ላይ የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍና መመሪያ በማውጣት ላልተመዘገቡ ሰዎች ቤት የመስጠቱ ሂደት ሕጋዊነት ጥያቄ የሚነሳበት አስተዳደሩ እስካሁን አጥጋቢ ምላሽ አልሰጠም። ይሁንና ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የመንግሥት ሠራተኞችና ነዋሪዎቹ የሚሆኑ አንድ ሺህ 718 የኪራይ ቤቶችን እየገነባ እንደሆነ አስታውቋል።

አሁን አዲስ አበባ ላይ ተመዝግበው ቤት ከደረሳቸው ይልቅ ገና በመጠባበቅ ላይ ያሉት ከአምስት እጥፍ በላይ ናቸው። አስተዳደሩም ቢሆን ተመዝጋዎቹ በጉጉት እየጠበቁኝ እንደሆነ አውቃለሁ ይላል።

በቤቶች ግንባታ ላይ ምን ሲካሄድ ነበር?
የቀድሞው የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳደር የነበሩት ነፍስሔር አምባቸው መኮንን (ዶ/ር) የከተማ ልማትና ቤቶች ሚንስትር በነበሩበት ወቅት እየተገነቡ ያሉ ቤቶችን ጎብኝተው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ምዝገባው ቀድሞውኑ ችግር የነበረበት መሆኑን አንስተው መንግሥት አንድ ሚሊዮን ለሚሆን ተመዝጋቢ ቤት ገንብቶ የመስጠት ዕቅድም አቅምም እንደሌለው መናገራቸው ይታወሳል። አዲሱ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴርም በዚህ ሐሳብ ይስማማል። ኅዳር 4/2011 ሚንስቴር መስሪያ ቤቱ ቤቶችን በግል የቤት አልሚዎችና በመንግሥት ትብብር በፍጥነትና ብዛት ገንብቶ ለነዋሪዎች ለማስረከብ በሚያስችሉ አሠራሮች ዙሪያ ከቤት አልሚዎች ጋር መክሯል። ይሁንና በዚህ ዘርፍ ለመሳተፍ የሚፈልጉ ባለሀብቶች መነሻ ካፒታላቸው 50 ሚሊዮን ዶላር ይሁን መባሉ በባለሃብቶቸ በኩል ቅሬታን አሰነስቶ ነበር።

ቤት መገንባቱ ጉዳይ የሚመለከተው የፌደራሉን መንግሥት ሳይሆን እኔን ነው ሲል የነበረው የአዲስ አበባ አስተዳደር ግን ለሁሉም ተመዝጋቢዎች ቤት እገነባለሁ የሚል ተስፋን ሲሰጥ ነበር። ድሪባ ኩማ ከንቲባ በነበሩ ጊዜም በየዓመቱ እስከ 50 ሺህ አዳዲስ ቤቶችን ግንባታ መጀመር የሚል ዕቅድ አስቀምጠው ነበር፤ አልተሳካም። የበጀት እጥረት አላሰራ አለኝ ላለው አስተዳደር ለቤት ግንባታ እንዲውል በ2009 ዓ.ም 16 ቢሊዮን በ2010 ደግሞ 20 ቢሊዮን ብር ተበጅቶለትም ግንባታዎችን አልጀመረም፤ የጀመራቸውንም አልጨረሰም። በ2010 እጀምራቸዋለሁ ያለውን 25 ሺህ ቤቶች መጀመሩ ቀርቶ እስከ 2009 ሰኔ ወር በግንባታ ላይ ያሉ ቤቶችን አፈፃፀም 80 በመቶ ለማድረስ ያለመው አስተዳደሩ አንድ ዓመት ዘግይቶም 80 በመቶ አለማድረሱን የቢሮው የዕቅድ ሪፖርቶች ያመለክታሉ። እነዚህ ቤቶች ገና ወደፊት 80 በመቶ ደርሰው ይተላለፋሉ ተብሎ እየተጠበቀ ነው።

ሌላው ችግር የተላለፉ ቤቶች ላይ የመሠረተ ልማት አለመሟላት ነው፤ የአዲስ አበባ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ በዋልታ ሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬት ያስጠናው ጥናት በቤት ዕድለኝነታቸው የተደሰቱ ሰዎች ቤታቸው ሲገቡ ባጧቸው የመብራትና ውሃ እንዲሁም ሌሎች መሠረተ ልማት አቅርቦቶች እየተማረሩ እንዳሉ የሚያሳይ ነው።

ጥቅምት 30 ዕጣ ይወጣባቸዋል ተብሎ ላልታወቀ ጊዜ ከተራዘሙት 42 ሺህ ቤቶች ውስጥም ከታህሳስ እስከ ሰኔ 2011 መሠረተ ልማታቸው የሚሟላላቸው ሲኖሩ ኮዬ ፈቼ ላይ ዕጣ የሚወጣባቸው ቤቶች ላይ ግን መሠረተ ልማት ማሟላቱ እስከ ዛሬ ሁለት ዓመት ድረስ ሊቆይ እንደሚችል የአዲስ አበባ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ምክትል ኃላፊ ጀማል ሃጂ ይገልጻሉ።

ቤት የሚጠባበቁት አዲስ አበቤዎች እጣ ፈንታና መፍትሔ
ባለፉት ሦስት ዓመታት አዳዲስ ግንባታዎች አለመጀመራቸውን ተከትሎ ተመዝጋቢዎች ዕጣ ፈንታ ምንድነው የሚል ጥያቄ ከአዲስ ማለዳ የቀረበላቸው የአዲስ አበባ ቤቶቸ ልማትና አስተዳደር ቢሮ ሌላኛው ምክትል ኃላፊ ዘሪሁን አምደማሪያም ‹‹አዳዲስ ግንባታዎች መጀመራቸው አይቀርም›› ብለዋል፤ መቼ ለሚለው ግን ቁርጥ ያለ ምላሽ አልሰጡም።

ችግሮች የበዙበት የአዲስ አበባ የጋራ መኖሪያ ቤት ግንባታ መጨረሻ ምንድን ነው ለሚለው ጥያቄ የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር መንግሥት ፕሮግራሙን የጀመረው ለሥራ ዕድል ፈጠራና ግንባታ ዘርፉ እድገትም ጭምር በመሆኑ አይቋረጥም ብሏል። ጎንደር ለይ ለተካሄደው የከተሞቸ ፎረም አዘጋጅቶት የነበረው ሰነድ ግን በመንግሥት በጀት የጋራ መኖሪያ ቤትን ማስቀጠል የማይቻልበት ደረጃ ላይ መደረሱን ያትታል። ቤት ገንብቶ ሊያስረክብ ነዋሪዎችን መዝግቦ የሚያስቆጥበው የአዲስ አበባ አስተዳደርም አይቋረጥም ሲል ኖሮ ዛሬ ላይ ለተመዝጋቢዎች ቤት ለማዳረስ የሚስችለኝን ሌላ ስልት ከሚኒስቴሩ ጋር እያማተርኩ ነው ብሏል። እንደ ምክትል ቢሮ ኃላፊው ዘሪሁን ገለጻ ስልቶቹ ቀድሞ ቤት ሊደርሳቸው የሚችሉ ሰዎችን እየለዩ በግንባታው እንዲሳተፉ ማድረግንም ይጨምራል። በሌላ በኩል በማኅበራት እየተደራጁ ቤት የመገንባትን ሥራ መስከረም 2010 ላይ በሚጀመሩ 20 ሺህ የመንግሥት ሠራተኞች የማኅበራት ቤት አሟሻለሁ ብሎ የነበረው አስተዳደሩ መርሃ ግብሩን ሳይጀምረው አንድ ዓመት አልፎታል። አሁንም ግን ይህ የቤት ልማት አማራጭ እንዳለ መሆኑን የሚናገረው ቢሮው መቼና እንዴት ያስጀምረዋል የሚለውን ግልጽ ማድረግ አልቻለም። መርሃ ግብሩ መቼ እንደሚጀመር ባይታወቅም የኮንዶሚኒየም ተመዝጋቢዎችም እየተደራጁ የራሳቸውን ቤት እንዲገነቡ ያለመ ነው።

አሁን ባለው የጋራ መኖሪያ ቤቶች አዝጋሚ ግንባታ አካሄድ ሲሰላ የተለየ ነገር ካልተፈጠረ በቀር ቤት እየጠበቀ ያለውን ተመዝጋቢ የቤት ባለቤት ለማድረግ 50 ዓመታትም አይበቁም። በምሳሌ ካየነው በ14 ዓመት 168 ሺህ ቤት ገደማ ብቻ ያስተላለፈ አስተዳደር 974 ሺህ ተመዝጋቢን የቤት ባለቤት ለማድረግ 81 ዓመት ይፈልጋል ማለት ነው። በ2005 ምዝገባ ወቅት አንድ ተመዝጋቢ ቢያንስ 18 ዓመት መሆን ይጠበቅበት ነበር፤ ስለዚህ በወቅቱ የተመዘገበ የ18 ዓመት ወጣት አሁን 24 ዓመት ሞልቶታል። በዚህ ስሌት የመጨረሻው በእድሜ ትንሹ ተመዝጋቢ ቤት የሚያገኘው የ105 ዓመት አዛውንት ሆኖ ነው ማለት ነው።

የዜጎቼ በሕይወት የመኖር የእድሜ ጣሪያ 65 ዓመት ደርሷል የሚለውን የመንግሥት መረጃ ስንመለከት ደግሞ የተለየ ስልት ተፈልጎ የቤት ግንባታው ካልፈጠነ በስተቀር አብዛኛው ተመዝጋቢ ቤቱ ሳይደርሰው ሕይወቱ ያልፋል እንደማለት ነው።

አዲሱ የከተማ አስተዳደር – ተስፋና ስጋት
በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 አካባቢ አዲስ ማለዳ በዐይን ለመታዘብ እንደቻለችው በሰውነት ተክለ ቁመናቸው ግዙፍ የሆኑ ወጣቶች በአካባቢው በመምጣት እና በጭነት መኪና አጣና እና ብዛት ያላቸው ወጣቶችን በማምጣት ክፍት ሆነው የቆዩ መሬቶችን ማለትም በማኅበር ለተገነቡ መኖሪያ መንደሮች አረንጓዴ ስፍራ ተብለው የተለዩ ቦታዎችን በጉልበት ሲያጥሩ ታዝባለች። ይህም ሲከወን ደግሞ የወረዳው ከፍተኛ አመራሮች በስፍራው መገኘታቸውን ለመመልከት ችላለች።

ወደ ወረዳው መሬት አስተዳደር ክፍል ኃላፊ ወደሆኑትና እምሩ ወደሚባሉ ግለሰብ በመቅረብ ስለ ጉዳዩ ለማናገር ብትምክርም በግለሰቡ ፈቃደኛ አለመሆን ምክንያት ሙከራዋ ሳይሳካ ቀርቷል።
በዚሁ ወቅት አዲስ ማለዳ ከዚህ ቀደም አሰሳ አድርጋ በነበረባቸው እና ሕገ ወጥ መሬት ወረራዎች በብዛት ተንሰራፍቶባቸዋል በተባሉ ቦሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ውስጥ በሚገኙ ስፍራዎች ዘንድ በመሔድ ከመመሪያው ወዲህ ያሉትን እንቅስቃሴዎች ለመቃኘት ሞክራለች። ነዋሪዎችን፣ በማጠር ላይ የነበሩ ግለሰቦችን እንዲሁም ሌሎች አስተያየት ሰጪዎችን አነጋግራለች።

በተለይም ደግሞ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ለዓመታት ክፍት በተተወ መሬት ላይ በአንድ አዳር ከፍተኛ የሆነ የመሬት ወረራ እንደተከናወነ የታዘበችው አዲስ ማለዳ፣ ከዚህ ወረራ ጀርባ ማን እንዳለ ለማወቅ የተለያዩ የመረጃ ማሰባሰብ ሥራዎችንም ስትሠራ ቆይታለች። በዚህም ረገድ መሬቶች በሚታጠሩበት ወቅት እና ከታጠሩ በኋላ በተደጋጋሚ እየተመላለሱ መሬቱ የአያቶቻቸው እንደነበር እና በቅርቡም የእርሻ ሥራ እንደሚጀምሩበት የሚናገሩ አርሶ አደር ቁመና ያላቸው ግሰለብ መሆናቸውን መረዳት ችላለች። ተጨማሪ ጥቆማዎች ግን በአርሶ አደር ነኝ ባዩ ሰው ተገን አድርጎ መሬቶቹ ከታጠሩበት አካባቢ እምብዛም ሳይርቅ የሚኖር ከበርቴ እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል።

በከንቲባ ጽሕፈት ቤት መመሪያው ከወጣ በኋላ መሬት ወረራው እንዲስፋፋ ምክንያት የሆነው ደግሞ በኦዲት እና ምዝገባ ሰበብ ቀድሞ የተያዙ መሬቶች ወደ ሕጋዊነት ይዘዋወራሉ የሚል መረጃዎች በሰፊው መሰራጨታቸው እንደሆነ የአዲስ ማለዳ ምንጮች ተናግረዋል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ አዲስ ማለዳ በተዘዋወረችባቸው አካባቢዎች ከዚህ ቀደም በሕገ ወጥ መንገድ ታጥረው የነበሩ እና በኋላ ላይ በተደረገ ዘመቻ ወደ መሬት ባንክ ተመልሰው የነበሩ መሬቶች እንደ አዲስ ወረራ እንደተደረገባቸው፤ ለዚህ ደግሞ የየወረዳዎች ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኃላፊዎች በዋናነት ተዋናይ መሆናቸው አዲስ ማለዳ ከነዋሪዎች ያገኘችው መረጃ ያመላክታል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8፣ 9 እና 10 የተባሉ አካባቢዎች የወረዳ ሥራ አስፈጻሚዎች ሳይቀሩ በአካል በመገኘት ሰዎችን እንደሚያስፈራሩም ለመረዳት ተችሏል።

የመሬት ወረራውን ያስቀራል ተብሎ በመስተዳደሩ ይፋ የሆነው ይኸው መሬት ኦዲት እና ምዝገባ ታዲያ ጥሎት ባለፈው የሕገ ወጥ ወረራ ጉዳይን መሰረት ያደረጉ ተግባራት ከመታየታቸውም በላይ ለምን የአረንጓዴ ስፍራቸው እንደሚታጠር በጠየቁ ነዋሪዎች ላይም ዛቻ እና ማስፈራራት ‹‹ቤታችሁንም እንቀማችኋለን›› የሚል ሕገ ወጥ እንቅስቃሴ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ባሉ ሰዎች መሰማቱም አቤት ሊባልበት የታጣበት ሁኔታ ሆኗል። ነዋሪዎች በመንግሥት ላይ አመኔታን እንዲያጡ የሆነበት ደረጃ ላይ መድረሳቸውን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም አዲስ ማለዳ ተዘዋውራ በጎበኘችባቸው አካባቢዎች ያነጋገረቻቸው ሰዎች ታዲያ አሁንም በከፋ ሁኔታ የመሬት ወረራው ተጠናክሮ መቀጠሉንም ነው አጽንዖት ሰጥተው የሚናገሩት።
ከስምንት ዓመታት በላይ ክፍት መሬት እንደሆነ እና ቤትም እንዳልተሠራበት አዲስ ማለዳ የታዘበችው መሬት ላይ ከሰሞኑ በሰፊው ስለታጠሩት እና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ጦም እንዳያድሩ በተባሉ መሬቶች ዙሪያ ስለተፈጸሙ ሕገ ወጥ ወረራዎችም ነዋሪዎች ያስረዳሉ። በእርግጥ አዲስ ማለዳ ተዘዋውራ መመልከት እንደቻለችው ከባለ አንድ እስከ ባለ ሦስት ፎቅ ቤቶች በአካባቢው ተገንብተው ሰዎችም እንደሚኖሩበት ለማየት ይቻላል።

ጉታ በቀለ የተባሉ አርሶ አደር ለእርሻ በሚጠቀሙበት ስፍራ ግን እምብዛም ቤቶች አይታዩም። ይሁን እንጂ የሚታረሰው መሬት ለእርሻ የተከለለ መሬት ለመሆኑ ጥርጣሬን የሚያጭር ነው። እነዚህን ስፍራዎች በሚመለከት አዲስ ማለዳ ከዚህ ቀደም በነበሯት ዕትሞች መጥቀሷ ይታወሳል። ይህንንም ተከትሎ በርካታ ስፍራዎች እርምጃ ተወስዶባቸው አካባቢውም ነዋሪዎች ደስታቸውን የገለጹባቸው አጋጣሚዎች ቢኖሩም በቅርቡ የተገላቢጦሽ እንደሆነ ማየት ተችሏል።

የደስታ ድምጻቸውን ያሰሙት የአካባቢው ነዋሪዎች ከሰሞኑ የከተማዋ አስተዳደር በመሬት ዙሪያ ላለው የኦዲት እና ምዝገባ ጋር በተገናኘ ባወጣው መመሪያ በመመርኮዝ በአንድ አዳር የመኪና መተላለፊያ ብቻ ሲቀር ከቀድሞው በበለጠ መልኩ በገፍ እንደታጠረ እና ለዚህም ምክንያቱ ደግሞ የመሬት ኦዲት እና መምዝገባው በውስጥ ለውስጥ በሕገ ወጥ መንገድ የተያዙትን ስፍራዎች ሕጋዊ ለማድረግ ነው የሚል መረጃዎች መሰራጨታቸው እንደሆነ ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

አዲስ ማለዳ በስፍራው በሬ ጠምደው እርሻ ሲያርሱ የነበሩትን ጉታ በቀለን ከእርሻ መሬታቸው ቀጥሎ በእንጨት ታጥሮ የተከለለው ባዶ መሬት ተመልክታም ጥያቄ አቅርባ ነበር። ‹‹ምን እንደሆነ አላውቅም ግን ይህን መሬት እረስበት ተብዬ ሲሰጠኝ በማግስቱ የተወሰኑ ሰዎች መጥተው አጥረውት ሄዱ›› ሲሉ መልሰዋል።

አዲስ ማለዳ ቅኝቷን ከአርሶ አደሮች ወደ አካባቢው ነዋሪዎች መልሳ ጥያቄዎችን ስታቀርብ ቆይታለች። የአካባቢው ነዋሪ የሆኑት ዜና ዓለማየሁ ለአዲስ ማለዳ እንደሚናገሩት፣ ስፍራው ከዓመታት በፊት ለቤት መሥሪያነት ለማኅበራት ተሰጥቶ የነበረ ሲሆን፣ የተወሰኑት ሠርተው ቀሪዎቹ ደግሞ መሥራት ባለመቻላቸው ክፍት እንደተተወ ይናገራሉ። ይህንም ተከትሎ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከሦስት እና አራት ጊዜ በላይ ወጣት ልጆች በመምጣት አጥረውት እንደነበርና በተደጋጋሚ መንግሥትም እንደሚያስፈርሳቸው አስረድተዋል።

ነዋሪዋ አክለውም ከዛሬ 10 ዓመት በፊት በአካባቢው ቤት ሠርተው ሲገቡ እምብዛም ሰው ያልነበረበት አካባቢ ሲሆን፣ አርሶ አደሮች በርከት ብለው ይኖሩ እንደነበርና ካሳ ተከፍሏቸው መነሳታቸውን ግን መስማታቸውን ያስታውሳሉ። ይህንንም ተከትሎ በርካታ ገንዘብ ፈሰስ እንደተደረገም እንደሚያውቁ ተናግረው፣ ነገር ግን አብዛኞቹ እዛው አካባቢ የጭቃ ቤቶችን ሠርተው መኖር እንደመረጡ ለአዲስ ማለዳ ጠቅሰዋል።

አዲሲቷ ከንቲባ ተስፋ ወይስ ስጋት?
‹‹አዲሷ ከንቲባ ካላቸው ልምድ እና ከፍተኛ የሥራ አፈጻጸም የተነሳ አዲስ አበባን በሚገባ ያስተዳድራሉ የሚል ግምት አለኝ›› ሲሉ ይጀምራሉ። አያይዘውም በተሰናባቹ ከንቲባ አስተዳደር ዘመን የተፈጠሩ አስቸጋሪ ጉዳዮችን ለማጥራት ከፍተኛ የሆነ ሥራ ቢጠበቅባቸውም አቅም ያንሳቸዋል የሚል ጥርጣሬ እንደማይገባቸውም ይናገራሉ።

‹‹በዋናት ግን በከተማዋ ውስጥ ያለውን ሕገ ወጥ የመሬት ወረራን እንደሚያስቆሙልን ከፍተኛ የሆነ ተስፋ አለኝ›› የሚሉት ዜና፣ በተለይ ደግሞ በተደጋጋሚ እየፈረሰ በድጋሚ ለሚታጠረው የመኖሪያ መንደሮች አረንጓዴ ስፍራዎች መላ የሚበጅለት ጊዜ እንደሚሆንም ባለ ሙሉ ተስፋ መሆናቸውን ለአዲስ ማለዳ ይናገራሉ። በገቢዎች ሚኒስቴር ውስጥ የነበራቸውን ከፍተኛ ሥራ አፈጻጸም በአንክሮ ይከታተሉ የነበሩት ዜና፣ በአዳማ ከተማም የነበራቸውን የሥራ ተነሳሽነት በዝና መስማታቸው ለዚህ ለሞላው ተስፋቸው ዋነኛ ምክንያት እንደሆነም ነው የሚናገሩት።

በሌላ በኩል ደግሞ የሰላ ትችት በአዲስ አበባ አዲሷ ከንቲባ ላይ የሚሰነዝሩት አስተያየት ሰጪ፤ ‹‹በአዳነች የሥራ ችሎታ ምንም አልጠራጠርም፤ የሚመጡ ለውጦችም መኖራቸው አይቀሬ ነው›› ሲሉ ይጀምራሉ። ቀጥለውም ነገር ግን አዲስ አበባ ጉዳይ ከፍተኛ ፖለቲካዊ ውሳኔ የሚያሻው እና ከባድ አገራዊ ትኩረትን የሚስብ ውስብስብ ችግሮች ባለቤት የሆነች ከተማ በመሆኗ ይህ ነው የሚባል ለውጥ እንደማይመጣ ከወዲሁ ሊታወቅ እንደሚገባ ይናገራሉ።

‹‹አዲስ አበባ የመሬት ቅርምት በዋናነት የሚነሳ እና ሊነሱ ከሚገባቸው ጉዳዮች ውስጥ ትንሹ ነው። ምክንያቱም ቀላል እርምጃ የሚወሰድበት እና ቁርጠኝነት ካለ ሊፈታ የሚችል የአስተዳደራዊ እና ሕጋዊ ጉዳዮች ጥምረት የሚፈታው ችግር ነው። አንድ ሰው መሬት ያለ አግባብ ከያዘ ሕጋዊ አይደለህም ተብሎ እርምጃ ሊወሰድበት ከፍ ሲልም በሕግ ሊጠየቅበት የሚችል ጉዳይ ነው›› ይላሉ።
በዋናነት ግን አዲስ አበባ ውክልና ጉዳይን እና ፍትሀዊ ያልሆነ የሀብት እና የጥቅማ ጥቅም ክፍፍልን በሚመለከት ሰፊ ርዕሰ ጉዳዮች ተነስተው ሊፈቱ የማይችሉ አዳጋች ሐሳቦች ከፍተኛ የፖለቲካ ውሳኔ የሚያሻቸው ጉዳዮች ስለሚኖሩ አዳነች አቤቤ ምንም እንኳን ጥንካሬያቸው ቢታወቅም ቅሉ፣ እነዚህን መፍታት ግን እንዲህ በቀላል ይሆንላቸዋል የሚባል እንዳልሆነ አስተያየታቸውን ይሰጣሉ።

አዲስ ማለዳ ተዘዋውራ በታዘበችው አካባቢዎች በተለይም ከሹመቱ ማግስት ከፍተኛ የሆነ እንቅስቃሴ በኹለት አቅጣጫ ሲካሔድም ነበር። በዚህም መሰረት የመሬት ወረራው በአስቸኳይ ይቁም የሚል ትዕዛዝ የተሰጠ በሚመስል አኳኋን በረጃጅም እንጨቶች ታጥረተው የነበሩ የመንደር ውስጥ ክፍት ቦታዎች በአንድ አዳር ሲፈራርሱ በሌላ በኩል ደግሞ ከዚህ ቀደም ታጥረው የማያውቁ መሬቶች ከእንጨትም በተጨማሪ በቆርቆሮዎች እንዲታጠሩ ሲደረጉም ለማየት ተችሏል።

አሁንም አዲስ ማለዳ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን የተስፋ እና ስጋት ሁኔታ ለመታዘብ የቻለች ቢሆንም ፍርዱን ለጊዜ ትተዋለች። በእርግጥ ከፊት ለፊት የሚመጣው አዲሱ ዓመት በከተማዋ እና በነዋሪዎቿ ላይ ከፍተኛ ሆነ መነቃቃት እንዲሁም ሕዝብ እና መንግሥት በቅርበት ተነጋግረው እና ተማምነው የሚኖሩበት ይሆን ወይስ እንደዚህ ቀደሙ ሁሉ ጥቂቶች ብቻ በሕጋዊም ሆነ በሕገ ወጥ መንገድ እየመዘበሩ ሌሎች የበይ ተመልካች የሚሆኑባት አዲስ አበባ ትሆን? የሚለው ጉዳይ ጊዜ ፈራጅ ነው።

ቅጽ 2 ቁጥር 96 ነሐሴ 30 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here