የዱለቻ – አዋሽ አርባ መንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ግንባታ ተቋረጠ

0
967

የአዋሽ ወንዝ ሙላት ያደረሰው የጎርፍ ማጥለቅለቅ በኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ተቋራጭነት በግንባታ ላይ የሚገኘውን የዱለቻ አዋሽ አርባ መንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ሥራ መቆሙን የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን አስታወቀ።

በኢትዮጵያ በተለያዩ ቦታዎች በተለይም በአፋር ክልል የክረምት ዝናብ በመብዛቱ ከፍተኛ የሚባል የጎፍ መጥለቅለቅ አጋጥሞ እስካሁንም ድረስ ብዙ ዜጎች ተጎጅ ሆነዋል። በዚሁ የጎርፍ መጥለቅለቅ በአፋር ክልል በአዋሽ ተፋሰስ አካባቢ እየተገነባ ያለው የዱለቻ አዋሽ አርባ መንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ከነሀሴ 26/2012 ጀምሮ የግንባታ ስራው እንደተቋረጠ የኢትዮጵያ ኮንስትራክ ሥራዎች ኮርፖሬሽን የህዝብ ግነኙነት ኃላፊ ጥንፉ ሙጬ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ዘየደ አበራ በበኩላቸው እንደገለጹት የመንገድ ግንባታው ወደ ሚካሄድባቸው አካባቢዎች ሰብሮ የገባው ጎርፍ ከነሃሴ 26/2012 ጀምሮ የፕሮጀክቱን ሥራ አስተጓጉሏል።

የግነባታ ስራው በመቆሙና ኮርፖሬሽኑ የመንግስ የልማት ድርጅት በመሆኑ በአካባቢው በበርካታ አካባቢዎች የጎርፍ መጥለቅለቅ በመከሰቱ በአካባቢው ማህበረሰብ ላይ እየደረሰ ያለውን የንብረትና የሰው ሂወት ማዳን ስራ እያከናወነ መሆኑን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው ጠቁመዋል።

ፕሮጀክቱ በአካባቢው የጎርፍ መጥለቅለቅ በማጋጠሙ ስራው ቢሰተጓጎልም የከፋ ውድምት አላማጋጠሙን ኮርፖሬሽኑ አስታውቋል። ኃላፊው አክለውም በክልሉ በርካታ ወረዳዎች በጎርፍ መጥለቅለቅ በመጠቃታቸው ህብረተሰቡን ለመደገፍ የንብረት ማዳን፣ የሰው ሂወት ማዳን፣ የንጹህ ውሃ አቅርቦት፣ የተከሰተውን ጎርፍ ወደ ተፋሰስ እንዲገባ የቅየሳና የአሽዋ መድፋት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑ አመላክተዋል።

የዱለቻ አዋሽ አርባ መንገድ ግንባታ ፕሮጀክት በአፋር ክልል የአዋሽ ተፋሰስ በሚያልፍበት ረግረጋማ አካባቢ የሚካሄድ በመሆኑ ሰፊ ጊዜና ሀብት የጠየቀ ከፍተኛ የድንጋይ ሙሌት ሥራ ሲከናወንለት የቆየ ሲሆን የ53.13 ኪ.ሜ ርዝመት ካለው ከዚህ መንገድ የ38.20 ኪ.ሜ ግንባታ መከናወኑ እና ፕሮጀክቱ የሚገኝበትን ደረጃ 71.90 በመቶ ማድረስ መቻሉን ለመረዳት ተችሏል።

ስራው መቋረጡን ተከትሎ የኮርፖሬሽኑ የበላይ አመራር በተሰጠ አቅጣጫ መሠረት የኮንስትራክሽን መሣሪያዎች እና የሰው ኃይል አቅሙን በማንቀሳቀስ እና ከተለያዩ አካላት ጋር በመቀናጀት በአካባቢው የጎርፍ መጥለቅለቁ አሁን ካስከተለው በላይ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ የመከላከል ሥራ ወደ ማከናወን መግባቱን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ገልጸዋል።

ኮርፖሬሽኑ በአካባቢው እያከናወነ ነው የተባለው የፕሮጀክቱ 10 ገልባጭ መኪኖችን በማሰማራት ጎርፉ የበለጠ አልፎ እንዳይሄድ ከፍታን የመጨመር እና ተጓዳኝ የመከላከል ሥራዎችን እያከናወነ መሀኑ ተመላክቷል። የፕሮጀክቱን ሠራተኞች እና ቋሚ ንብረቶች ጉዳት ሳይደርስባቸው ከአካባቢው ማውጣት መቻሉንም አስረድተዋል። ቀንና ከሌሊት በተደረገው የመከላከል ሥራ ህይወት ማትረፍና በኮርፖሬሽኑ ቋሚ ንብረት ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ማድረግ ቢቻልም በአሁኑ ወቅት የግንባታ መሣሪያዎችን እና የሰው ኃይልን ከቦታ ቦታ በማንቀሳቀስ መደበኛ ሥራን ለማከናወን የሚያስችል ሁኔታ እንደሌለ የፕሮጀክት ሥራ አስኪያጁ ገልፀዋል።

የጎርፍ መጥለቅለቅ አደጋው የደረሰው የኮርፖሬሽኑ የበላይ አመራር ለፕሮጀክቱ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት እና የቅርብ ክትል በማድረግ፣ የፕሮጀክቱ ሠራተኞችና የሥራ መሪዎችም በከፍተኛ ተነሳሽነት የመንገድ ግንባታውን እስከ መጪው ጥቅምት ወር ድረስ ለማጠናቀቅ ከፍተኛ ርብርብ እያደረጉ በሚገኙበት ወቅት መሆኑ እንዳሳዘናቸው የፕሮጀክቱ ስራ አስኪጅ ተናግረዋል።

በዘንድሮው የክረምት ዝናብ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍል ከስከዛረው የተለየ የመሬት መንሽራተትና የጎርፍ መጠለቅለቅ በማጋጠሙ በርካታ ዜጎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው ንብረታቸውንም አጥተዋል። በተጨማሪም በግድቦች ላይ ያደረሰው ጉዳት እንዳደረሰ የሚታወስ ነው።

ቅጽ 2 ቁጥር 97 መስከረም 2 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here