“በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ባልታጠቁ ሲቪሎች ላይ ግድያዎች ተፈጽመዋል” ኢሰመኮ

0
573

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተፈጸሙ ጥቃቶች፣ ባልታጠቁ ሲቪሎች ላይ ግድያዎች መፈፀሙን አስታወቀ። ኮሚሽኑ በጳጉሜ 1/2012 እንዲሁም ከጳጉሜ 2 አስከ መስከረም 3/2013 መካከል ቢያንስ ሁለት ጥቃቶች ማጋጠማቸውን ከክልሉ መንግስት ለማረጋጥ እንደቻለ ጠቅሷል።

ኢሰመኮ ይህን ያለው በቤኒሻንጉል ጉሙዝ የተከሰተውን ግድያ እና መፈናቀል አስመልክቶ ዛሬ ሐሙስ መስከረም 7/2013 ባወጣው ይፋዊ መግለጫ ነው። በክልሉ በአንዳንድ አካባቢዎች የፀጥታ መደፍረሶች መታየታቸውን የጠቆመው የኮሚሽኑ መግለጫ ይህን ተከትሎም ያጋጠሙ ክስተቶች እጅግ እንዳሳሰቡት አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኮሚሽኑ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በአንዳንድ አካባቢዎች እየታዩ ያሉ የፀጥታ መደፍረሶችን ተከትሎ ያጋጠሙ ክስተቶች እጅግ አሳስበውታል። ኮሚሽኑ ከክልሉ ከመተከል ዞን፣ ቡለን ወረዳ ኤጳር ቀበሌ እንዲሁም ከወንበራ ወረዳ መልካን ቀበሌ እጅግ አሳሳቢ መረጃዎች እየደረሱት ነው ሲል በመግለጫው አመላክቷል። በክልሉ ባልታጠቁ ሲቪሎች ላይ የደረሱትን ጥቃቶች፣ ግድያዎች እና መፈናቀሎችን ሙሉ በሙሉ እንደሚወግዝ አስታውቋል።

ኮሚሽኑ አክሎም በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ሕገ-መንግስትና እንዲሁም ኢትዮጵያ ተቀብላ ባጸደቀቻቸው የቃል ኪዳን ሰነዶች ማለትም፡ በአፍሪካ የሰብዓዊና ሕዝቦች መብቶች ቻርተር፣ በአለም አቀፍ የሲቪል እና የፖለቲካ መብቶች ቃል ኪዳን (ICCPR) እና በሌሎች አግባብነት ባላቸው የሰብአዊ መብቶት ሰነዶች የተደነገጉትን በሕይወት የመኖር መብቶች እንዲከበሩ በመግለጫው ጠይቋል።

በአጠቃላይ ኮሚሽኑ ሁሉም የፖለቲካ ቡድኖች እና ባለድርሻ አካላት ገንቢ ውይይት እንዲያደርጉ እና ከማንኛውም ዓይነት የሁከት ድርጊቶች እንዲታቀቡ ጥሪውን አቅርቧል። እንዲሁም በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ-መንግስት እና ኢትዮጵያ ፈርማ የተቀበለቻቸውን ሌሎች አግባብነት ያላቸውን የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎች ውስጥ የተቀመጡ መብቶችን እና ግዴታዎችን እንዲያከብሩ ኮሚሽኑ ገልጾ በቀጣይም ጉዳዩን በንቃት እንደሚከታተል ገልጿል።

ቅጽ 2 ቁጥር 98 መስከረም 9 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here