የኢሬቻ በዓል ገጽታዎች

0
1343

በርከት ካሉ ሺሕ ዓመት በፊት እንደሆነ የሚነገርለት አንድ አፈ ታሪክ አለ። እንዲህ ነው፤ አቴቴ ኹለት ወንድሞች ነበሯት። እነዚህ ወንድሞቿ በመካከላቸው ጸብ ይፈጠርና ይጣላሉ። አንዱም አንደኛውን ገድሎ ይጠፋል። አቴቴ ታድያ በእጅጉ ታዝናለች፤ ሟች ወንድሟ በተቀበረበት ቦታ ላይም ኦዳ ትተክላለች። ኦዳውን እየተንከባከበች በየዓመቱም በኦዳው ስር ለወንድሟ መታሰቢያ ታደርግ ቀጠለች።

ከዓመታት በኋላ ሌላው ወንድሟ ተመልሶ ወደ ቤቱ መጣ። እርቅም ተደረገ፣ ይህም የሆነው በኦዳው ስር ነው። እናም አቴቴ በምታደርገው ጸሎትና ለቅሶ እርቅ ሆኗልና፣ አቴቴ የቤተሰብ ጠባቂ ነች ተባለች። ኦዳም የሕግ ማርቀቂያና የስምምነት ቦታ ሆነ። የኢሬቻ መሠረትም ከዘህ አፈ ታሪክ እንዲሁም ከገዳ ስርዓት ጋር በአንድም በሌላም መንገድ ይገናኛል።

የኢሬቻ አጀማመር በገዳ አቆጣጠር (አንድ ገዳ 7 ዓመት ከ8 ወር ወይም 8 ዓመት) ከ6 ሺሕ 660 ዓመት በፊት የተጀመረ እንደሆነ አዋቂዎች ይናገራሉ። የገዳ ስርዓት ባለበት፤ የኦሮሞ ሕዝብ በሚገኝበት ሁሉም ኢሬቻ አለ። በዓሉ ዋቄፈንና ከተባለውና ከጥንቱ የኦሮሞ ሕዝብ እምነት የፈለቀ እንደሆነም ይጠቀሳል።

ለምን ይከበራል?
የኦሮሞ ሐይማኖት ማዕከል የሚያጠነጥነው ዝናብ፣ ሰላም እና ትውልድ ዙሪያ ነው። እናም ኢሬቻ ለምን ይከበራል የተባለ እንደሆነ፤ ዝናብ፣ ሰላምና ትውልድ የሚሰጥ ፈጣሪን ለማመስገን ነው፤ ቀኑም የምስጋና ቀን ነው የሚባለው። ይህም ለፈጣሪ የሚቀርብ ምስጋና ሲሆን በኦሮሞ ባሕል ማዕከል የኦሮሞ ታሪክ ጥናት ቡድን መሪ እና የታሪክ ተመራማሪ ዓለማየሁ ኃይሌ ይህን ሲያብራሩ፤ “አንድ ሰው ታምሞ ሳለ መድኃኒት ሌላ ሰው ቀርቦ ቢሰጠው በምላሹ ዝም ብሎ አይሔድም፤ ይልቁንም ካለው ዐሥር ሳንቲምም ይሁን ለበረከት ብሎ ምስጋና ወይም ስጦታ ከሣር ጋር ይሰጣል።

ሣር እርጥበ ነው፤ ልምላሜ ማለት ነው። ይህም ‘ኢሬቻ ሰጠኝ’ ይባላል። ከዛ ተነስቶ እስከ ትልቁ የኢሬቻ በዓል ድረስ ትርጉሙ ምስጋና ነው። ይህኛው ደግሞ ለፈጣሪ ምስጋና ማቅረቢያ ነው።

የኦሮሚያ ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ኢሬቻን በተመለከተ ባሰራጨው በራሪ ወረቀት፤ ኢሬቻ የኦሮሞ ሕዝብ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ የኢኮኖሚያዊና የሃይማኖት (የእምነት) ተቋማትን በውስጡ የያዘው የገዳ ስርዓትን፣ ጠቅሶ የኢሬቻ በዓል በዚህ ስር ከሚከበሩ ትልልቅ በዓላት መካከል አንዱ ነው ይላል። ኢሬቻ ማለት ጥንታዊ የአባይ ሸለቆና መስክ የኦሮሞ ሕዝቦች ዘንድ ፈጣሪ አምላክን (ዋቃን) ለማመስገን፣ ምልጃ ለመጠየቅ የሚከናወን ስርዓት ነው ሲል ያብራራዋል።

የጋራ የምስጋና በዓል የሆነው ኢሬቻ በኹለት ትልልቅ ቦታዎችና ወቅቶች ይከበራል፤ በሐይቅና ወንዞች (ኢሬቻ መልካ) እንዲሁም በተራራዎች ላይ (ኢሬቻ ቱሉ)። የዓመቱ የመጀመሪያው የሚባለውና መስከረም 23 እና 24/2013 ይከበራል የተባለው አንደኛው ነው። ይህም “ከክረምቱ አስፈሪ ነጎድጓድ እንኳን ወደ ብርሃኑ አወጣኸን። ብራውን ዘመን የሰላም አድርግልን” ሲሉ ተሰባስበው በሐይቆችና በጅረቶች ዙሪያ ሆነው የሚያመሰግኑበት በዓል ነው።

በዓሉ በአንዳንድ ቦታዎች ‘የብራ በዓል’ ይሉታል። ይህን የሚሉት ወቅቱ የክረምቱ ጨለማ አልፎ በብርሃንና በአበባ ወራት የሚተካው በመስከረም ወር ስለሆነ ነው።
ኹለተኛው ደግሞ የበጋ ወራቶች አልፈው በበልግ ወቅት መግቢያ ላይ የሚከበረው በተራራ ላይ የሚፈጸመው ኢሬቻ ነው፤ ኢሬቻ ቱሉ። ይህም ከፍተኛ ፀሐይ የሚታይበትና የውሃ እጦት የሚከሰትበት በመሆኑ፣ መጋቢት ወር ላይ የኦሮሞ ማኅበረሰብ ተሰብስቦ ፈጣሪ (ዋቃ) ዝናብ እንዲያዘንብላቸው የሚጠይቁበት ነው። ‹ውሃ እና እርጥቡን አትንሳን› ሲሉ ፈጣሪን የሚለምኑበት ነው። ይህም ብዙ ጊዜ በተራሮች አናት ላይ የሚደረግ መሆኑን ዓለማየሁ ይናገራሉ።

ተራራ ላይ ለምን ሆነ? ተራራ የደመና መገኛና እርጥበታማ በመሆኑ ነው። ‹‹በተራራ ላይ ወጥቶ አምላክን በጋራ መማጸንና መለመን ከጥንታዊው የኩሾችና የአባይ ሸለቆ ሕዝቦች የእምነት አተገባበር ጋር በእጅጉ የተቆራኘና የተሳሰረ ባሕላዊ ድርጊት ነው ይባላል።›› ሲል የባሕልና ቱሪዝም ቢሮው ኅትመት ያክላል።

ኢሬቻ የሚከበረው አዲስ ዓመት በሚገባበት ዓመት ይልቁንም ከመስቀል በዓል ሦስት ቀናት በኋላ ነው። ይህ ቀን ሰኞ፣ ረቡዕ እና አርብ እስካልዋለ ድረስ በዓሉ ይከበራል። በኦሮሞ ባሕል አንድ በዓል ከተከበረ በኋላ ለሦስት ቀናት ማረፍ የሚጠይቅ ባሕል በመኖሩ ነው ከመስቀል በኋላ ሦስት ቀን የሚጠበቀው። ያም ብቻ አይደለም፤ ሁሉም ቦታ በእኩል ቀን ነው የሚከበረው።

የኢሬቻ በረከቶች
ሰለሞን ሲናገሩ፤ ኢሬቻ አንድነት በማምጣት ረገድ፣ ሌሎችን በመከተል ሞዴል መሆን አይቻልምና ሰው ወደ ማንነቱ እንዲሔድ በማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው ይላሉ። ኢትዮጵያም እርሷ ጋር ብቻ የሚገኙ፣ የራሷ የሆኑ እንደ ኢሬቻ ያሉ ሀብቶቿን ቀድማ ነበር ማውረስ የነበረባት ባይ ናቸው።

የአንድነት የስበት ኃይል በርትቶ የሚታይበት የኢሬቻ በዓልም፤ ባለው ማኅበራዊ ፋይዳ ምክንያት ሃይማኖታዊ መሠረቱ እንዳለ ሆኖ ባሕላዊ ገጽታው ጎልቶ ሊወጣ ችሏል። ሰለሞንም በዚህ ያምናሉ፤ እንዲህም አሉ፤ ‹‹በተለይ ጊዜያዊ ለሆኑ ስሜቶች ባለመገዛት፣ ፖለቲካዊ አንድምታ ባለመስጠት የሚከበር ከሆነ፣ ኢሬቻ የሚያስተሳስር እሴት ነው። የሌሎችን የማንነት መገለጫ የራስ በማድረግ አየተሳሰርን እንሔዳለን የሚል ሐሳብ አለኝ።›› ብለዋል።

ታድያ ግን ይህን ጥያቄ ለማንሳት አንድም ምክንያት የሚሆነው በዓሉን ከተለያዩ ሰው ሠራሽ ተግባራት ጋር እኩል በመታየቱ ምክንያት ነው የሚሉ አሉ።
ኢሬቻ በኦሮሞ እምነት የሚከበር የአንድ ቀን በዓል ብቻ ሳይሆን ብዙ ማኅበራዊ ፋይዳ አለው። የታሪክ ተመራማሪው ዓለማየሁ እንደጠቀሱት ደግሞ አራት ዋና ዋና ክስተቶች በዓሉን ይከተላሉ። ቀዳሚው በክረምቱ የወንዞች ሙላት ምክንያት ተቆራርጠው የነበሩ ቤተ ዘመዶችና ልዩ ልዩ ጎሳዎች የሚገናኙበት በዓል ነው፤ ኢሬቻ። ብዙ ጊዜ ጋብቻ ሲደረግ በጎሳ መካከል ስለሚሆን በጋብቻ የተዛመዱ ቤተሰቦች ከወንዝ ወዲያና ወዲህ ስለሚሆኑ፤ የወንዙ መጉደል የብስራት ዜና ነው። በዓሉ የአዲስ ዓመት መጀመሪያ ተደርጎ ስለሚቆጠርም ‘መልካም አዲስ ዓመት’ የሚል የመልካም ምኞት መግለጫም ኢሬቻን ተከትሎ ይጎርፋል።

ሌላው ደግሞ የኦሮሞ አባቶች ከዋርካ ሥር ተቀምጠው የሕግ ጉዳዮችን ማየት የሚጀምሩት ከኢሬቻ በኋላ ነው። አንዳንድ ቦታ በዓሉን ‘ የችሎት መክፈቻ’ የሚሉት ሲሆን፤ በዚህ የተነሳ ነው። መደበኛ የሚባሉ ችሎቶች በክረምቱ ወር ተዘግተው ሚከፈቱት የብራ ወር መግቢያ ላይ ነውና።
ሦስተኛው ከብቶች ጨዋማ ውሃ የሚፈልጉበት ወቅት ነውና ይህን የሚያገኙበት ነው። ወደ ሆራ ስምሪት የሚያደርጉበት ነው ይባላል። ይህም ለከብቶች መራባት የሚጠቅም መሆኑ ይነገራል።

የመጨረሻው ዋና ኩነት የመተጫጫ ወቅት መሆኑ ነው። አንዱ የኦሮሞ ጸሎት ዘር አብዛልን ነውና ልጃገረዶች እንዲሁም ቄሮዎችም (ያላገቡ ወንድ ወጣቶች) ከዕድሜ እኩዮቻቸው የሚተያዩበትና ለፍቅር የሚተጫጩበት ነው። በዚህ የተነሳ ዓመቱ ዞሮ መምጣቱን የበለጠ የሚያደንቁትና የሚወዱት እነዚህ ወጣት ሴቶችና ወንዶች ሳይሆኑ አልቀሩም።

ሴቶች በኢሬቻ
‹‹ኢሬቻ የሚጀምረው ከሴቶች ነው፤ የበዓሉ ምክንያት አንድም የእርቅ መነሻነት ነውና ነው።›› ሲሉ የገለጹት የታሪክ ተመራማሪው ዓለማየሁ፤ በተለይ የአቴትን ድርሻ ያነሳሉ። ታድያ በኢሬቻ በዓል ላይም በኦሮሞ የባሕል ልብሶች ያጌጡና የተዋቡ ሴቶች፣ ሲቄ የያዙ እናቶች ትንንሽ ሴት ልጆችን ጨምሮ ከፊት ቀድመው እንዲሰለፉ ይደረጋል። ይህ ማለት በዓሉ ቅድሚያ የሚሰጠው ለወጣት ሴቶች፣ ለልጃገረዶች፣ ለእናቶችና ለአባ ገዳ ሚስቶች ነው ማለት ነው።

በገዳ ስርዓትና ፍልስፍና ሴቶች እንደ ጻድቃን ይቆጠራሉ፤ ስለዚህ ቅድሚያ ይሰጣቸዋል ማለት ነው። ለባልቴቶችና ለሕጻናት ቅድሚያ የሚሰጠውም ለዚሁ ሆኖ በተጨማሪ ፈጣሪ ለእነርሱ ምህረት እንደሚያደርግም ይታመናል። ቄጠማ የሚሰጡትም እናቶችና ልጆች የሆኑት ለዛ ነው። ከኢሬቻ ባሻገር ስለ ሲቄ ያነሱት ዓለማየሁ፤ ሰዎች ቢጣሉና ጥሉ ምን ያህል የከረረና የበረታ የሚባል ቢሆን ሴቷ ሲቄዋን ይዛ “እልልልል…” እያለች ከመካከል ከገባች ሁሉም ጥል ያቆማል፤ ኹከትም ካለ ይረጋጋል። ይህም ሴትን ምክንያት ያደረገ አንዱ የሰላምና የእርቅ መንገድ ነው።

ከዚህ ባሻገር አባ ገዳ ከብቶችን ነድቶ ወንዝ ሲያሻግር መጀመሪያ በቅርብ ያለች ልጃገረድ ወንዙን እንድትመታው (በመቀነት ወይ በቀሚሷ) ያደርጋል፤ ከብቶቹን ይዞ የሚሻገረውም ከዛ በኋላ ነው። በድምሩ ሴቶች በፈጣሪ ፊት ሞገስ ማግኘታቸውን የገዳ አብዛኛው ስርዓት የሚያሳይና ያንንም የሚናገር ነው።
ታድያ እንዲህ በኢሬቻ በዓልም ሴቶች ከፊት ሆነው ‘ማሬዎ’ እያሉና የተለያዩ ዜማዎችን እያሰሙ ነው ወደ በዓሉ ማክበሪያ ስፍራ የሚያቀኑት። ይህም ዓመቱ ዞሮ መጣ፤ ብራ ሆነ የሚል ትርጓሜ ያለው ነው።

ኢሬቻ በ2013
ዘንድሮ ምንም እንኳ ከአሮጌው 2012 የተሻገረው የኮሮና ቫይረስ ስጋቱ ባይቀንስም፣ ማኅበራዊ እንዲሁም ዓመት ጠብቀው የሚከወኑ ክዋኔዎች ቀጥለዋል። በተያዘው አዲስ ዓመትም ታድያ የ2013 ኢሬቻ በዓል መስከረም 23 እና 24 ቀን እንደሚውል አባገዳዎች መስከረም 6 ቀን 2013 በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል። በዚህም የሆራ ፊንፊኔ ኢሬቻ በዓል መስከረም 23 በአዲስ አበባ እንዲሁም የሆራ አርሰዲ ኢሬቻ በዓል በማግስቱ በቢሾፍቱ ይከበራል ብለዋል። በዓሉም ወረርሽኙን ባለመዘንጋትና በጥንቃቄ እንዲደረግ አባገዳዎች ለሕዝቡ መልዕክትና አደራ አስተላልፈዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 98 መስከረም 9 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here