የዐቢይ መንግሥት የኢኮኖሚ ማሻሻያ (Abiynomics) “ስኬቶች”

0
1302

በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከሰት ምክንያት ዓለም የተለያዩ ችግሮችን በስፋት አስተናዳለች። የምጣኔ ሀብት ጉዳይም በዚህ የፈተና ወጀብ ውስጥ የተገኘ ሲሆን፣ በዚህም ካደጉ አገራት ይልቁ ጫናው በደሃና አዳጊ አገራት ላይ ሊበረታ እንደሚችል ገና በማለዳው ነበር ሲተነበይ የነበረው። ሽመልስ አረአያ (ዶ/ር) ይህን የኢትዮጵያን የምጣኔ ሀብት ሁኔታ መነሻ በማድረግ እንዲሁም የአገር ቀበል ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ጠቅሰው፤ የሴፊየስ ካፒታል ጥናት መሠረት በማድረግ ሐሳባቸውን አካፍለዋል።

በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ዓለም ብዙ ተግዳሮቶች እያጋጠማት በመሆኑ የንግድ ልውውጡ ቀንሷል፣ በሺዎች የሚቆጠሩ የሥራ እድሎች ጠፍተዋል፣ በሚሊየን የሚቆጠሩ ኑሯቸው በከፍተኛ ሁኔታ ተናግቷል። በተለምዶ ፊት ለፊት የሚከናወኑ ስብሰባዎችና ኮንፈረንሶች ተሰርዘው መረጃ ልውውጡ ዲጂታል ተደርጓል። በመሆኑም ኮንፍረንስ ቱሪዝም ተገትቷልና ኢኮኖሚያቸውን በዘርፉ የመሰረቱ አገራት በከፍተኛ ደረጃ ተጎድተዋል።

በወረርሽኙ መስፋፋት የዓለም ሕዝብ በሩን ዘግቶ እንዲቀመጥ ስለተገደደ፣ በበለፀጉት አገራት ገበያ ጥገኛ የሆኑ የአዳጊ አገራት ኢኮኖሚ ከሌላው በተለየ ቁልቁል እንደሚወርድ፣ በዚህም እነዚህ አገራት ለማሕበራዊና ፖለቲካዊ አለመረጋጋት የመዳረግ እድላቸው ከፍተኛ እንደሚሆን መላ ምቶችም ሲቀመጡ ነበር።
ነገር ግን የሴፊየስ ካፒታል (Cepheus capital) በነሐሴ ወር ይፋ ያደረገው የተጠናቀቀው በጀት ዓመት ዝርዝር የኢኮኖሚ አፈፃፀም ጥናት ሪፖርት እንደሚያመለክተው፣ በኢትዮጵያ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ የተነሳ የኢኮኖሚ ማነቃቂያ ማሻሻያዎች ተግባራዊ ተደርጎም በተወሰኑ የኢኮኖሚ ዘርፎች መጠነኛ መንገራገጮች ቢያጋጥምም እንደአጠቃላይ የበጀት ዓመቱ ዝርዝር የኢኮኖሚ አመላካቾች ‹ስኬት› አሳይተዋል ይላል።

የጥናቱ ሪፖርትም በግብርና ምርት፣ በግብርና ቀረጥ አሰባሰብ፣ በባንክ ብድር አቅርቦት፣ በወጪ ንግድ (Exports) አፈፃፀም፣ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ምርት፣ ወዘተ… በመሳሰሉት ላይ ከባለፈው በጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀር ‹እድገት› መመዝገቡን በዝርዝር ሪፖርቱ አካቷል።

በጥናት ተቋሙ በየጊዜው የሚወጡ ወቅቱን የጠበቁና በመረጃ የተደገፉ ጥናቶች የፖሊሲ ትግበራ ጉድለት ከማመላከት አልፎ በቀጣይነት ለሚወሰዱ የትግበራ እርምቶች መንግሥት በመረጃ ላይ የተመሠረቱ ውሳኔዎችን እንዲያስተላልፍ የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ እጅግ ከፍተኛ ነው። ከዓመታት በፊት ተመሳሳይ የጥናት ውጤቶችን እያወጣ የፖሊሲ ክፍተቶችን በማመላከት ገንቢ ትችት ያቀርብ የነበረው አክሰስ ካፒታል (Access Capital) የተሰኘ ተቋም በሂደት ትችትን አጥብቆ በሚፈራው የወቅቱ መንግሥት ምን አይነት እጣ ፈንታ እንደገጠመው የጥናት ተቋሙ መሥራች የነበረውና በስራ ፈጣሪነቱ የሚታወቀው ኤርሚያስ አመልጋ በአንድ ወቅት ለአንድ የቴሌቨዥን ጣቢያ በሰጠው ቃለ-ምልልስ ተመልክቻለሁ።

እንዲህ ገለልተኛ የሆኑ የጥናትና ምርምር ተቋማት የሚያቀርቡት ሪፖርት መንግሥት ከሚያወጣው ሪፖርት ጋር ሲነፃፀር የበለጠ ተዓማኒ ስለሚሆኑ ለመንግሥትም ክፍተቱን በማመላከት ፍተሻ እንዲያደርግ የሚያግዝ ነው። በመሆኑም ትችትን በመፍራት በጠላትነት ከማየት ይልቅ ለጥናቱ በግብዓትነት የሚያገለግለው ተዓማኒነት ያለው መረጃ እንዲያገኙ ጭምር ማድረግ አለበት።

ወረርሽኙን ተከትሎ አገራት ጊዜውን የዋጀ የኢኮኖሚ ማሻሻያ እያደረጉ መሆኑን በማውሳት በኢትዮጵያም በከፋ ሁኔታ የሚጎዱ ዘርፎችና የህብረተሰብ ክፍሎችን ለይቶ ለመደገፍና ለመምራት እንዲያስችል ‹ወረርሽኙ ጥላ ያጠላበት ኢኮኖሚና ተጠባቂ የመንግሥት እርምጃዎች› በሚል ርዕስ አንድ ጽሑፍ በዚህ ጋዜጣ ላይ አስነብቤ ነበር። በዚያ ጽሑፍ መንግሥት እንደሌሎች አገራት የገንዘብና የፊስካል ፖሊሲ ማስፈፀሚያ መሣሪያዎች አቀናጅቶ በመጠቀም ኢኮኖሚውን የባሰ እንዳይንሸራተት ለመታደግ የማነቃቂያ እርምጃዎች በጊዜው እንዲያደርግ መረጃ የሚጠቁም ነበር።

በዚህም የታክስና ግብር ማሸጋሸግ፣ የባንክ ብድር መክፈያ ጊዜን እፎይታ፣ ብሔራዊ ባንክ ለባንኮች የሚያበድርበትን ተመን መቀነስ፣ የባንኮች አስገዳጅ የተቀማጭ ተመን መቀነስና በባንኮች እጅ የሚገኙ ሰነዶችን ግዥ በመፈፀም ንግድ ባንኮች የጥሬ ገንዘብ ችግር እንዳይገጥማቸው የኢኮኖሚ ማነቃቂያ (Economic stimulus) እርምጃዎች በድፍኑ የተመላከቱበት ነበር። እነዚህ ማነቃቂያዎች እድገትን ለማምጣት የሚያግዙ በዚያውም የሥራ እድል ፈጠራን የሚጨምሩ በመሆናቸው ‹Expansionary policies› ይሰኛሉ።

እንዲህ ያሉ የማነቃቂያ እርምጃዎች የጎንዮሽ ጉዳትም አላቸው። ይኸውም የዋጋ ግሽበት እንዲባባስ የማድረጋቸው ጣጣ ነው። በመሆኑም ወደ ኢኮኖሚው በብዛት የሚረጨው የገንዘብ አቅርቦት (Money supply) የተነሳ በየግዜው እየጨመረ የመጣው የዋጋ ግሽበት ከፍ ባለ ደረጃ ሊያባባስ የሚችልበት እድሉ ሰፊ እንደሆነም በጽሑፉ ተብራርቶ ይገኛል።

ባለፉት ወራት ከኢኮኖሚው ባሻገርም በፖለቲካውና ዲፕሎማሲው መስክ እንዲሁ የሚታዩ ለውጦች ተመልክተናል። ወቅቱን ጠብቆ መካሄድ የነበረበት ምርጫ ተስተጓጉሏል። በፖለቲከኞች መካከል በሚፈጠር ሌላ ዙር መካረር ኢትዮጵያ ቀውስ ውስጥ እንዳትገባ ሁሉም አካላት አገርንና ሕዝብን በማስቀደም በሰከነ ሁኔታ ሐሳብን በማንሸራሸር መፍትሔ ማግኘት አለባቸው። በተጨማሪም የቫይረሱን ስርጭት ተከትሎ መንግሥት በመከላከል ሥራ ቢጠመድም፣ ለጉዳዩ ልዩ ትኩረትና ክትትል በማድረግ በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት የህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት ማሳካት መቻሉን እንዲሁ አድናቆት መስጠት ያስፈልጋል።
የሲፊየስ ካፒታል ጥናት ግኝት ‹ስኬቶች›

በዝርዝር የቀረበው የአፈፃፀም ግምገማ ጥናት ውጤት በየዘርፉ የተከፋፈለና ለመረዳትም ግልፅ የሆነ ነው። በዚህም መሰረት በበጀት ዓመቱ መዝጊያ አካባቢ በወረርሽኙ የተነሳ የእንቅስቃሴ ገደብ የነበረ ቢሆንም፣ የግብርናው ዘርፍ ሥራዎች ሳይስተጓጎሉ የተከናወኑ በመሆኑ በሰብል የተሸፈነ መሬትና የተመቸው የዝናብ አቅርቦት መረጃ ላይ በመመርኮዝ የግብርና ሚኒስቴር ባወጣው ትንበያ በቀጣዩ ዓመት የ6.2 በመቶ የግብርና ምርት እድገት እንደሚኖር ተቀምጧል።

የእርሻ መሬት ሽፋን ታሳቢ ሲደረግ በቀዳሚነት የሚቀመጡት የሰብል አይነቶች ማለትም ስንዴ፣ ጤፍና በቆሎ ከባለፈው በጀት ዓመት የምርት መጠን ጋር ሲነፃፃር የላቀ እድገት እንደሚያስመዘግቡ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱን ትንበያ ታሳቢ በማድረግ በጥናቱ ተመልክቷል።

ከግብርናው ዘርፍ ባሻገር በሌሎች ዘርፎችም እንዲሁ ‹በስኬት› የሚገለፁ አፈፃፀሞች ቀርበዋል። የታክስና ቀረጥ መሰብሰብ እንደተጠበቀው በበጀት ዓመቱ መዝጊያ በቫይረሱ የተነሳ ቢቀንስም፣ በአጠቃላይ የበጀት ዓመቱ አፈፃፀም የ18 በመቶ እድገት አሳይቷል። እንደዚሁም የባንክ ተቀማጭ በ16 በመቶ ሲያድግ የባንክ ብድር አቅርቦት በ29 በመቶ ጨምሯል።

በተመሳሳይ የመንግሥት ኢንቨስትመንት በ9 በመቶ አድጓል። በዚህም የመንግሥት እዳ አምና በተመሳሳይ ወቅት ከነበረበት በአንድ ቢሊየን ዶላር ጨምሮ በጠቅላላው አገሪቷ የተሸከመችው እዳ 54.7 ቢሊዮን ዶላር እንዲደርስ ምክንያት ሆኗል። ቢሆንም የአገሪቱ ጥቅል ዓመታዊ ምርት እድገት ተከትሎ የእዳው ከጠቅላላ የአገራዊ ገቢ/ምርት ስብጥር (Debt-to-GDP ratio) ከኹለት ዓመታት በፊት ከነበረበት 60 በመቶ ወደ 54 በመቶ አሽቆልቁሏል። በዚህም ተጨማሪ ብድር የመሸከም አቅም እንዳላት ስለሚያመላክት ለልማት የሚያስፈልጉ ብድር እንድታፈላልግ እድል ይሰጣታል።

በቫይረሱ ምክንያት የምግብና የሕክምና ቁሳቁስ ግብይት ካልሆነ በቀር ሁሉም መስመሮች መቆላለፋቸውን ታሳቢ በማድረግ በተለይ የአፍሪካ አገራት የገበያ ችግር ገጥሟቸው የወጪ ንግዳቸው በከፋ ሁኔታ እንደሚጎዳ ተተንብዮ ነበር። ቢሆንም የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ (Exports) በ12 በመቶ ‹እንዳደገ› በጥናቱ ተገልጾ ይገኛል።

በሌሎች ዘርፎች ደግሞ ማሽቆልቆል ተመዝግቧል። ከነዚህም መካከል እንደተገመተው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት (FDI) በ19 በመቶ፣ ቱሪዝም በ29 በመቶ እንዲሁም የገቢ ንግድ በ8 በመቶ ቀንሷል። በዚህም በጥቅሉ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት የኢኮኖሚ እድገቱ 6 በመቶ ሊደርስ እንደሚችል የጥናት ተቋሙ ትንበያ ያመላክታል።

ወቅታዊ ፈተናውን ተቋቁሞ የኢኮኖሚው መቀዛቀዝ እንዳያጋጥም ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት መንግሥት አቀናጅቶ የተጠቀማቸው የፖሊሲ እርምጃዎች ውጤት ናቸው። በዚህም በበጀት ዓመቱ መዝጊያ ወቅት እንደሚገመተው ከእቅዱ ሲነፃፀር በእጥፍ የሚለካ የገንዘብ አቅርቦት ቢጨምርም ዓመታዊ የእድገት ምጣኔው ግን እንዲቀንስ ተደርጓል።

ይህም መንግሥት የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር የወሰደው የማረጋጋት እርምጃ አንድ አካል ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። ነገር ግን የዋጋ ግሽበቱ በባሰ ሁኔታ ወደላይ ቢምዘገዘግ እንጂ ዘንበል ሲል አልታየም። በዚህም በግንቦት ወር የመቀነስ አዝማሚያ ካሳየ በኋላ በበጀት ዓመቱ መዝጊያ ወራት ግን ቀደም ብሎ ወደነበረበት በፍጥነት የመጨመር አዝማሚያ ተመልሷል።

በዚህም እንደጥናቱ በሠኔ ወር 21.5 በመቶ እንዲሁም በሐምሌ 22.3 በመቶ አሻቅቧል። በጥቂት መሠረታዊ በሆኑ የምግብና ፍጆታ እቃዎች ላይ በሚቆለሉ ዋጋዎች የተነሳ አሁንም የዋጋ ግሽበቱ በእነዚህ እንዲወሰን ምክንያት እንደሆነ ነው። እነኚህም የአትክልት ዋጋ (እንደአብነት የሽንኩርት ዋጋ መወደድ) በ36 በመቶ፣ በሰብልና ጥራጥሬዎች ላይ በ23 በመቶ እንዲሁም የቤት ኪራይና የኤሌክትሪክ ወጪዎች በ22 በመቶ ጨምሯል።

ከአምናው የተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በእነኚህ መሠረታዊ ቁሳቁሶች ላይ የዋጋ ጭማሪ ሳይከሰት ባሉበት ቢቀጥሉ ኖሮ አጠቃላይ የዋጋ ግሽበቱ “ከ10 በመቶ አይዘልም ነበር” ሲል ሪፖርቱ ያብራራል። በዚህም በየወሩ ሽቅብ እየተጓዘ የሚገኘው የዋጋ ግሽበት በመደበኛ የፖሊሲ ማስፈፀሚያ መሣሪያዎች ለመቆጣጠር ከሚደረገው ጥረት ባሻገር የተጠቀሱት መሠረታዊ ቁሳቁሶች ምርት አቅርቦት በከፍተኛ መጠን እንዲያድግ በማድረግ የዋጋ ግሽበት በሚገባ በቁጥጥር ስር ማድረግ የሚቻል በመሆኑ መንግሥት ችግሩን ከመሰረቱ ለመፍታት አቅጣጫ ማስቀመጥ አለበት።

ምንም እንኳን በብዙ የአፍሪካና በማደግ ላይ ባሉ አገራት እንቅስቃሴ የተገደበ በመሆኑና በተወሰኑ ምርትና አገልግሎቶች የአገር ውስጥ ፍላጎቶች በከፍተኛ ሁኔታ ማሽቆልቆላቸውን ተከትሎ የዋጋ ግሽበቱ ወደታች ቢወርድም፣ ‹በኢትዮጵያ ግን ከአፍሪካ አገራት እንዲሁም ከዓለም አቀፍ ሁኔታ አንፃር ሲታይ የተለየ ነው› ሲል ጥናቱ ያክላል።

የብዙኀኑን የህብረተሰብ ክፍል የኑሮ ሁኔታ ለማቃወስ ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱት መሠረታዊ የሆኑት ቁሳቁሶች በአገር ውስጥ የሚመረቱ እንደመሆናቸው አምራች ዘርፎች ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ የሚመሩ ቢሆኑ ኖሮ ኢትዮጵያ በምግብ ራስን በመቻል ከራሷም አልፋ ለክፍለ-አህጉሩ በተረፈች ነበር። ለመንግሥት ታማኝ ለሆኑ ሹማምንት ምቾት ሲባል ብዙኀኑ የከፋ የኑሮ ዋጋ እንዳይከፍል በተለይ የግብርናው ዘርፍ ሳይንሱን ጠንቅቀው በተማሩና በሚያውቁ ብቁ ባለሙያዎች እንዲመሩ መደረግ አለበት። አለበለዚያ ነገረ ሥራችን ውሃ የመውቀጥ ጨዋታ መሆኑ ነው።

ለዋጋ ግሽበቱ ትልቁን አስተዋፅኦ የሚያበረክተው የብር የመግዛት አቅም ከሌሎች አገራት ገንዘብ አንፃር በየጊዜው የሚደረገው የትመና ማሻሻያ እንዲሁ በከፍተኛ ፍጥነት እያሽቆለቆለ እንደሚገኝ ጥናቱ ጠቁሟል። ከዓመት በፊት በተመሳሳይ ወቅት ከነበረው ተመን ጋር ሲነፃፀር የብር መግዛት አቅም አሁን ከአሜሪካ ዶላር በ21 በመቶ ቀንሷል። የብር የመግዛት አቅም ቅነሳው በዩሮና በእንግሊዝ ፓውንድ ላይ የበለጠ እንደሆነም ታይቷል።

ይኸውም በኹለቱም ወደ 30 በመቶ ገደማ ቀንሷል። ይህም ከኹለቱ ከፍተኛ ከሆኑት የንግድ አጋሮች ጋር ትልቅ የሆነ የውጭ ምንዛሬ ተመን ማስተካከያዎችን እንዲያደረጉ ያስገድዳል። በሪፖርቱ ሲጠቃለል ‹የምንዛሬ ተመኑ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ውስጥ በአማካኝ በየወሩ በ50 ሳንቲሞች ወደላይ እየተምዘገዘገ በአሁኑ ወቅት ከተመዘገበው ዓመታዊ የዋጋ ግሽበት ጋር መሳ ለመሳ እየተጓዘ ይገኛል› ይላል ጥናቱ።

በመቀጠል የኢኮኖሚያችን መሠረታዊ ችግር የሆነው የውጭ ምንዛሬ ጉዳይና ይህን ተከትሎ የሚያበረክተው የዋጋ ግሽበት ሚና እንዴት ሊቀረፍ እንደሚችል ከመንግሥትና ከዜጎች የሚጠበቅ ውሳኔዎች እንመለከታለን።

ዋናው ማነቆ ችግራችን:- የውጭ ምንዛሬ እጥረት
ከፍጆታ እቃዎች በተጨማሪ አብዛኛው አምራች ተቋማቶቻችን ከውጭ በሚገቡ ጥሬ እቃዎች ላይ ጥገኛ እንደሆኑ እሙን ነው። የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መንግሥት ከመምጣቱ በፊት የወጪ ንግድ ገቢ ለተከታታይ ዓመታት በማሽቆልቆሉ አገሪቱ ለፈታኝ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ተዳርጋለች። ከውጭ የሚገቡ ጥሬ ዕቃዎችን ለሚጠቀሙ አምራቾችም የውጭ ምንዛሬ ፍላጎታቸውን ማሟላት አዳጋች እንደነበረ በወቅቱ ከቀረበ ሪፖርት መረዳት ይቻላል።

የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ በወቅቱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የወጪ ንግድን በተመለከተ በዘመኑ እያጋጠመ ስለነበረው ተግዳሮት ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት ‹‹የወጪ ሸቀጦች ገቢ ማሽቆልቆል ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ፈታኝ የሆነው የውጭ ምንዛሬ እጥረት እንዳይቀረፍ አድርጓል። በመሆኑም የውጭ ጥሬ ዕቃዎችን የሚጠቀሙ አምራች ኢንዱስትሪዎች ፍላጎት በሚጠበቀው ደረጃ ማሟላት አልተቻለም። በተጨማሪም በኤክስፖርት ገቢው መዳከም የተነሳም አገሪቱ የውጭ ብድር የመክፈል አቅም ላይ ተፅዕኖ በማሳደሩና የአገሪቱ የውጭ ዕዳ ጫና ስጋት እንዲጨምር በማድረጉ፣ ተጨማሪ የልማት ብድር ለማግኘት እንዳልተቻለና በዚህም የተነሳ መንግሥት የጀመራቸው የልማት ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ተስተጓጉሏል›› ብለዋል።

ከዚሁ ከውጭ ምንዛሬ እጥረት ጋር በተገናኘም የገቢ ዕቃዎች መጠንና የመንግሥት ኢንቨስትመንት እንዲቀንስ በማድረጉ ኢኮኖሚው እንደተቀዛቀዘም አብራርተው ነበር።

በመሆኑም በአብዛኛው የሸቀጦች ዋጋ ላይ ንረት መፈጠሩ ሲነገር ነበር። ቀደሞ በነበረው አስተዳደር ተመዝግበዋል የተባሉ የኢኮኖሚ እድገት ‹ስኬቶች›ን ለማስቀጠል እንዲሁም ወቅታዊ ተግዳሮቶችን ለማስተካከል በሚል ‘አገር-በቀል’ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ተብሎ የተሰየመውና ለሦስት ዓመታት ይተገበራል የተባለለት ዝርዝር የኢኮኖሚ ሪፎርም ሰነድ መቅረቡ ይታወሳል። የአገሪቱ ማክሮ ኢኮኖሚያዊ፣ የዘርፍና መዋቅራዊ ተግዳሮቶች ማስተካከል የፖሊሲው ቁልፍ ተደርገው የቀረቡ ሲሆኑ በቋሚነት እየተንፏቀቀ የነበረውን ኢኮኖሚ ወደሃዲዱ ለመመለስ በሚል የቀረቡ ‹መሠረታዊ› የችግር ትንተናዎች ነበሩ።

ሆኖም በአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ሐሳባቸውን የሚሰነዝሩ የምጣኔ ሀብት ምሁራን ሪፎርሙ እንደሥሙ ለእውነተኛ አገራዊ የኢኮኖሚ ችግሮች ትክክለኛ መፍትሔ ከመስጠት ይልቅ በመንግሥት ቁጥጥር ስር ያሉ የኢኮኖሚው ሞተር የሆኑ ተቋማትን ለውጭ ኩባንያዎች በመክፈት ስር የሰደደውን የውጭ ምንዛሬ ችግር ለመፍታት ታስቦ የተሠራ እንደሆነ ሲተቹ ነበር። አሁንም እንደዚያው እየተተቸ ይገኛል።

እንግዲህ ከአንድ ዓመት የፖሊሲው ትግበራ በኋላም የወቅቱ ማነቆ የነበረው የውጭ ምንዛሬ ችግር አሁንም ድረስ ፈተና ደቅኖ ይገኛል። በመሆኑም በውጭ ምንዛሬ እጥረቱ የተነሳ በሚፈለፈሉ ሌሎች ችግሮች (ለምሳሌ የኑሮ ውድነት) ዜጎች ከፍተኛ የሆነ የኑሮ መስዋዕትነት እንዲከፍሉ ምክንያት ሆኖ ይገኛል። እየታዘብን እንዳለውም የውጭ ምንዛሬ እጥረቱ የልብ ልብ የሰጣቸው አበዳሪ ተቋማትና ለጋሽ አገራት እየፈጠሩበት ባለው ጫና መንግሥትም የፖሊሲ ነፃነት እንዳይኖረው እንቅፋት ሆኖበታል።

የብር የመግዛት አቅምን በማዳከም የወጪ ንግድ ተወዳዳሪነት እንደሚጨምር በዚህም የንግድ ሚዛን ጉድለትን ለማሻሻል እንደሚያግዝ በሚል በመንግሥት ላይ እየቀረቡ ያሉ ግፊቶች ሲፈተሹ እንደሚባለው የማይጨበጡ ናቸው። ለዚህ ምክንያቱም ከምናቀርባቸው ምርቶች አይነት የተነሳ ‹ምክሩ› የተሳሳተ ነው። የወጪ ንግዳችን የተንጠለጠለው በግብርናውና ማዕድናት ዘርፍ ላይ ቢሆንም ከእኛ በለጠ በአነስተኛ ወጪ የሚያመርቱ አቅማቸው ከፍ ያሉ ተወዳዳሪዎች አሉብን።

በተጨማሪም በእነዚህ ምርቶች ላይ ያለው የዋጋ ለውጥ ተከትሎ የሚኖረው ምላሽ በዘርፉ አገላለፅ ‹demand and supply inelastic› ተብለው ከሚመደቡት ውስጥ ናቸው። ይኸውም ምንም እንኳን የምንዛሬ ተመን አስተካክለን ተወዳዳሪነት አሳድገን ብዙ እንድንሸጥ በሚል የዋጋ ቅናሽ ብናደርግላቸውም ተጠቃሚዎች ብዙም አይደነቁም። ምክንያቱም የክብሪት ዋጋ መቀነስ አስፈንድቆት ለሸመታ ወደ ገበያ የሚተም ቁጥሩ እምብዛም ነው።

በኹለተኛነትም እንደተባለው የፍላጎት መጨመር ቢከሰት በመጋዘን ያከማቸነው ካልሆነ በቀር የግብርና ሥራ ወቅታዊ እንደመሆኑ እንደፋብሪካ ዕቃ ቶሎ ተዘርቶ፣ ተሰብስቦ፣ ተጓጉዞ ለተጠቃሚው ማቅረብ አዳጋች ነው። ነገሩ ይሄ ከሆነ ዘንዳ እንግዲያውስ መፍትሔዎቹ ምንድናቸው የሚል አንባቢ አይጠፋም።

መፍትሔውስ?
ብዙ መፍትሔዎች ቢኖሩም የሚከተሉት እርምጃዎች የሚታዩበት ሁኔታ ካለ በዘላቂነት ውጤት ያመጣሉ የሚል እምነት አለኝ። በዋናነት የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ማፋጠን ነው። ፈረንጆቹ ‹No more vegetarian tiger› ይላሉ። ይኸውም በግብርና ላይ ብቻ በመንጠልጠል ተፈላጊውን የኢኮኖሚ ብልፅግና (Development) ማምጣት አይቻልም። ነገር ግን ካለንበት ዘለን ወደኢንዱስትሪ ማስፋፋት መሄድ ሳይሆን የግብርና እድገት የወለደው የኢንዱስትሪ ሽግግር ቢሆን ይመረጣል።

ለዚህም የሰሜን ምሥራቅ እስያ አገራትን ምሳሌ መከተል ነው። አለበለዚያ የውጭ ምንዛሬ ሀብታችን ጠቅለሎ የሚወስድብን ከውጭ የሚደረገው የምግብ ሸመታ ይቀጥላል ማለት ነው።

ሌላው ከህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ ከለጋሽ አገራትና አበዳሪ ተቋማት ጋር የገባችበት የተካረረ ግንኙነት በብልሃት በመያዝ የአገር ሉዓላዊነት ጉዳይ እንደሆነ በማስገንዘብ በሰከነ ዲፕሎማሲ አግባብ በመፍታት ከእነኚህ የሚጠበቁ ኢኮኖሚያዊ ድጋፎች ማስቀጠል ያስፈልጋል። ይህ ሳይሆን በመካረር የበለጠ እንድንነጠል ተደርገን የኢራን፣ የሰሜን ኮርያ፣ የሱዳን እጣ ፈንታ እንዳይደርሰንና በአጉል ጀብደኝነት ብዙ ኢኮኖሚያዊ ዋጋ መክፈል የለብንም።

እንደዚሁም በአውሮፓና አሜሪካ የሚገኙ የውጭ ምንዛሬ ‹ኮማሪቶች› በሕገ-ወጥ በሚደረግ ልውውጥ አገሪቷ በሬሚታንስ መልክ ታገኘው የነበረው ውጭ ምንዛሬ እንድታጣ እየተደረገ ነው። የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ማዕከል ያዘጋጀው የአማርኛ መዝገበ ቃላት ‘ኮመረ’ ወይም ‘ኮመረች’ የሚለው ቃል በባህላዊ መንገድ የመጠጥ ቸርቻሪዎችን እንደሚያመለክት ይገልፃል። የውጭ ምንዛሬ በሕገ-ወጥ ገበያ እየተቸረቸረ ነው።

በዚህ ጥቁር ግብይት የመንግሥት ሰዎች እንደሌሉበት ለመገመት ይከብዳል። ሥራው በተደራጀ ሁኔታ የሚሠራ ይመስላል። በአውሮፓ በዚህ እንቅስቃሴ ላይ ኑሮአቸውን የመሰረቱ ብዙዎች ናቸው። የውጭ ምንዛሬው አገሪቷ እንዳታገኘው ለማድረግ ያለመ ይመስላል። በዚህ ዙርያ ወደፊት በሰፊው የምለው ያለኝ ቢሆንም፣ ለጊዜው የኢትዮጵያ መንግሥት መደነኛ የሆነው የምንዛሬ ገበያ ከማስተካከል እርምጃ ባሻገር ከአውሮፓ መንግሥታት (በተለይ ከጀርመን) ጋር በመረጃ ልውውጥ ሕገ-ወጥ የሆነው የገንዘብ ዝውውር እንዲቆም ቁጥጥር ማድረግ ያስፈልጋል። አለበለዚያ ከምንዛሬ ክምችት መመናመን የተነሳ ሁሌም ከውጭ ለሚጫንብን የፖሊሲ ሉዓላዊነት ጫና መጋለጣችን አይቀርም።

ሌላው አገራዊ ጠቀሜታቸው ከፍተኛ ለሆኑ አምራች ዘርፎች ላይ ለተሰማሩ የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት አቅጣጫ መከተል ነው። ከተለያዩ ምንጮች የተገኘው የውጭ ምንዛሬ ለግብርናና ኢንዱስትሪ ልማት ብቻ እንዲውል ከፍተኛ የፋይናንስ ቁጥጥር ማድረግ ያስፈልጋል። የፋይናንስ ግኝቱም ሆነ ቀጣይ ኢንቨስትመንቱ በዋናኝነት በኹለቱ የኢኮኖሚ ምሰሶዎች ላይ ብቻ እንዲያተኩር አድርጎ መምራት ያሻል።

ሌላውና ዋናው ቁልፍ መፍትሔ ከውጭ የሚገቡ እቃዎችን በሂደት በአገር ውስጥ የማምረት አቅጣጫ መከተል ነው። በተወሰነ መልኩም ቢሆን ለአምራች ተቋማት የገበያ ከለላ ማድረግ አለብን። ይህን ስናደርግ ከዓለማቀፍ የፋይናንስ ተቋማት የሚደርሰው ጫና ቀላል እንደማይሆንልን ግልፅ ነው። ነገር ግን ተቋቁመን የግድ መተግበር አለብን። ቀጥሎ የምናየው ይህንኑ ነው።

የጨቅላ-ኢንዱስትሪ ከለላ (Infant Industry Protection)
የጨቅላ-ኢንዱስትሪ ከለላ ፅንሰ-ሐሳብ በማደግ ላይ ባሉ አገራት የሚገኙ አዳዲስ ኢንዱስትሪዎች ተፎካካሪዎቻቸውን በራሳቸው ለመጋፈጥ አቅም እስኪያዳብሩ ድረስ ከተፎካካሪ ኩባንያዎች ጫና ጥበቃ ሊደረግላቸው ይገባል የሚል ነው። የጨቅላ ኢንዱስትሪ ፅንሰ-ሐሳብ ጠንሳሽ ጀርመናዊው የምጣኔ ሀብት ተመራማሪ ፍሬድሪክ ሊስት (Friedrich List) ነው። በ19ኛው ክፍለ ዘመን አገሩ ጀርመን አሁን ኢትዮጵያ ባለችበት ተቀራራቢ ደረጃ የምትገኝ የነበረ ሲሆን፣ በወቅቱ የበለፀገች ከነበረችው እንግሊዝ የሚመረቱ እቃዎች የጀርመን ገበያ አጥለቅልቀው በማቆጥቆጥ ላይ የነበሩት ጨቅላ ኢንዱስትሪዎች በፉክክር ተሸንፈው እንዳይዘጉ ለወቅቱ መንግሥት ምክር የሰጠበት ነበር።

እንግዲህ እነኚህ አገራት ለእድገታቸው የተጠቀሙትን መሣሪያ ለእኛ ሲሆን ‹‹አይጠቅማችሁም፤ እኛ የምንላችሁን ብቻ ስሙን›› የሚሉን። በማደግ ላይ ያሉ አገራት ጨቅላ-ኢንዱስትሪያቸው እንዲዳብር ለማገዝ መንግሥት ከሚሰጣቸው ማበረታቻዎች መካከል የገቢ ዕቃዎች ላይ ቀረጥ መጣል፣ ኮታዎች እና የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት ቁጥጥር ያሉ እርምጃዎችን በመውሰድ ከውጭ የሚገቡ እቃዎች እንዲወደዱ በማድረግ ተጠቃሚው ወደአገር ውስጥ ምርት ፊቱን እንዲያዞር ለማስቻል ያለመ ነው።

በመሆኑም ታዳጊ ኢንዱስትሪዎች ከውጭ ከሚመጣባቸው የገበያ ውድድር ተፅዕኖ ለመታደግ ጥብቅ ከለላ በማድረግ በሂደት ትምህርት እየተቀሰመ አቅም መገንባት ያስፈልጋል። ለአደጉ አገራት የኢንዱስትሪ ምርቶች ድንበር ክፍት እንድናደርግና ለነፃ ንግድ ስምምነት ተገዢ እንድንሆን ግፊቱ ቢበዛም ወደድንም ጠላንም ዘላቂ የሆነ ልማት ማምጣት የሚቻለው መንግሥት እንደሚለው ብልፅግና ሊያመጣ የሚችለው ‹መካሪ› በሆኑት ተቋማት የተባለውን የሚፈፅም ሳይሆን የመሪነት ሚናውን መጫወት የቻለ እንደሆነ ብቻ ነው።

የዓለማቀፍ የፋይናንስና ንግድ ተቋማት አማካሪዎች ዋነኛ የፖሊሲ ምክረ ሐሳቦችን (Liberalize, privatize, and stabilize) በተመለከተ የድሃ አገራት መሪዎች ሊከተሉት ስለሚገባ የዲፕሎማሲ ጥበብ ጆ ስቱድዌል የተባለ እንግሊዛዊ ጸሐፊ “How Asia Works” በሚል ርዕስ በፃፈው ድንቅ መጽሐፉ የደቡብ ኮርያው መሪ የነበረው የጄነራል ፓርክን አካሄድ አስቀምጧል። በዚህም ጄነራሉ ድምጹን አጥፍቶ ለአገሩ የሚፈልገውን እየሠራ የሚናገረው ግን ‹መካሪ› ተቋማት የሚፈልጉትን ነበር።

ይኸውም ሰዎች ትኩረት ሰጥተው የሚያዩት የምትሠራውን ሥራ ሳይሆን የምትናገርው ነው ለማለት ነው። ስለዚህም ሌሎች የሚፈልጉትን እየተናገራችሁ እናንተ የምትፈልጉት/የሚያስፈልጋችሁን ድምፅ አጥፍታችሁ ሥሩት ሲል ይመክራል። በዚህም ስቱድዌል እንደሚለው ድሃ አገራት ሊከተሉት ስለሚገባው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ከራሳቸው ነባራዊ ሁኔታ አንፃር የተቃኘ ከመሆን ባለፈ የነፃ ንግድ አቀንቃኝ ተቋማት የፖሊሲ ምክረ-ሐሳብ ለመተግበር መሞከር ከጥቅሙ ጉዳቱ እንደሚያመዝን አሳስቧል።

ስለዚህ ጉዳይ እንዳነሳ ምክንያት የሆነኝ በቅርቡ በአማራ ክልላዊ መንግሥት ከተገነቡት ግዙፍ የምግብ ዘይት አምራች ኢንዱስትሪ የሙከራ ምርት እንደጀመረ የሚያሳይ ዜና በተመለከትኩ በቀናት ልዩነት መንግሥት ከውጭ በሚገባው የምግብ ዘይት ላይ ጥሎት የነበረውን ቀረጥና ታክስ የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት ሲል በማንሳት ከቀረጥ ነፃ እንዲገባ ወስኗል የሚል ሌላ ዜና አገኘሁ። ይህ እራስን እንደማጥፋት መቆጠር አለበት።

ይህ የመንግሥት ውሳኔ የዋሽንግተን ስምምነት በሚል የሚታወቁት ባለዐስር ነጥብ ዝርዝር የፖሊሲ ፓኬጆች እዛው በሚገኙ ተቋማት የሚተገበሩ ምክረ-ሐሳቦች አንዱ ነው። በጥቅሉ ሲቀመጥ ቤታችሁን ክፈቱ፤ እኛም እንገባለን የሚል ነው።

እንደሚታወቀው ቀደም ተብሎ ሙሉ ለሙሉ በሚያስብል ደረጃ የምግብ ዘይት ፍጆታችን የሚሸፈነው በእርዳታና በግዢ ከውጭ በሚገባ እንደሆነ ግልፅ ነው። ኤርሚያስ አመልጋ ገና ወደንግድ ሥራ ሲገባ የዘይት ፋብሪካ ገንብቶ እንደነበር ከሰጠው ቃለ-ምልልስ ሰምቻለሁ። የታሪኩ ገራሚው አካል ግን በዚያን ወቅት የአገሪቷን ገበያ ያጥለቀልቃል የተባለለት ለማምረት ዝግጁ የተደረገው የምግብ ዘይት ፋብሪካ ከጥቅም ውጭ እንዲሆን የተደረገበት ተንኮል ነው።

የአሁኑ አካሄድም ለመረዳት ይህንን ቃለ-ምልልስ ከዩቲዩብ ፈልጎ ማየት ነው። የአሁኑ አካሄድም በተመሳሳይ ጨቅላ ኢንዱስትሪዎቻችን ከለላ ሳይደረግላቸው ከግዙፍ የውጭ ኩባንያዎች ጋር በውድድር ሜዳ ተዘርረው ከጨዋታ ውጪ ሲሆኑ ለዘመናት በምርት አቅርቦት የውጭ ጥገኛ እንድንሆን ነው፣ ከፍም ሲልም ኢትዮጵያ መሰል አገራት የፖሊሲ ነፃነት እንዳይኖራቸው ለመከላከል ያለመው የዋሽንግተን ተቋማት የሚያስፈፅሟቸው ሴራዎች አካል ነው።

አማተር ቦክሰኛ እና የዓለም ሻምፒዮና ማጋጠም በምንም መመዘኛ ፍትሃዊ ሊሆን አይችልም፤ ውጤቱም ከጨዋታው ቀድሞ ይታወቃል። በአጠቃላይ ከዓለማቀፍ ተቋማትና ምዕራባውያን መንግሥታት በማደግ ላይ ባሉ አገራት ላይ የሚደርሰው የፖሊሲ ነፃነት የማሳጣት ሴራ ድቡብ ኮርያዊው የምጣኔ ሀብት ምሁር ዮን ቻንግ “Kicking Away the Ladder” በሚል ርዕስ የጻፈው ድንቅ መጽሐፍ መቃኘት ብቻውን ይበቃል። ይኸው ነው።

ሽመልስ አርአያ በጀርመን አገር ጊሰን ዩኒቨርሲቲ በግብርና ኢኮኖሚክስ፣ ባዮኦኮኖሚ እና በገጠር ልማት የዶክትሬት ዲግሪ አግኝተዋል። በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ በኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል በመምህርነትም አገልግለዋል። በአድራሻቸው araya.gedam@gmail.com ማግኘት ይቻላል።

ቅጽ 2 ቁጥር 98 መስከረም 9 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here