ፕሮጄክት X

0
1001

ኢትዮጵያ 23 ዓመታትን መጠነኛ ማሻሻያ በተመረጡ የገንዘብ ኖቶች ላይ በማድረግ በተዘረጋው የምጣኔ ሀባት ስርዓት ላይ እንቅስቃሴ ሲደረግ ቆይቷል። የገንዘብ ቅየራው በተደረገበት ከኹለት አስርት አመታት በፊት ከምጣኔ ሀብት አንደምታው ይልቅ ፖለቲካዊ መነሻው እጅግ ያመዝን ስለነበር እና በወቅቱም እየተካረረ በመጣው የኢትዮ ኤርትራ ጉዳይ ላይ ጉልህ አስተዋጽኦ የነበረው እና በኋላም ላይ ወደ ለየለት የጦርነት ውድመት የተገባበት ምክንያትም እንደሆነ ሕያው ምስክሮች አሉ።

ከ23 ዓመታት በኃላ ደግሞ በምስጢር የተያዘው እና ፕሮጄክት ኤክስ የሚል ስያሜ የተሰጠው የብር ቅየራ ሒደት በመጨረሻም ይፋ ሆኗል።
ከመደበኛ የባንክ ስርዓት ይልቅ መደበኛ ያልሆነ የባንክ አሰራሮችን ያልተከተለ የብር መጠን ይዘዋወርባታል ለምትባለው ኢትዮጵያ የምጣኔ ሀባት ስብራቷን ይጠግናል የተባለው ይኸው አካሔድ ከሰሞኑ በድንገት ይፋ መደረጉ ትልቅ መነጋገሪያ ርዕስ ሆኗል። ጉዳዩን በሚመለከትም የአዲስ ማለዳው ኤርሚያስ ሙሉጌታ የሐተታ ዘማለዳ ጉዳይ አድርጎታል።

ከዘመን ጋር አብሮ የሚዘምነው ወይም ዘመናትን በልኩ የሚያዘምነው ሰው ልጅ፤ በእለት ተእለት መስተጋብሩ ውስጥ ከሚያከናውናቸው ተግባራት አንዱ ግብይት ነው። መሸጥ መለወጥን ማዕከል ያደረገው ግብይት መገበያያን ገንዘብ ብሎ ሰይሞ ሒደቱን ሲያሳልጥ ይኖራል። በዚህም ሒደት ታዲያ ከጥንት የዕቃን በቃ መለዋወጥ ጀምሮ እስከ አሁኑ ዘመን ጥሬ ገንዘብን እስከ አለመያዝ እና በኤሌክትሮኒክስ ግብይት ድረስ ታዲያ ረጅም እና የተለያዩ ደረጃዎችን ያለፈ ሒደቶችን መሄድ ተችሏል።
ዕቃን በዕቃ በሚለዋወጥበት ወይም (ባርተር ትሬዲንግ) ወቅት እንድን ዕቃ ለመግዛት በምትኩ ከራሳችን የሆነ ዕቃ ለልዋጭ ማዘጋጀት የግዴታ የነበረበት አንዱን ለማግኘት ወይም በአንዱ ዕቃ ለመገልገል በነበረን ዕቃ የመገልገል ፍላጎታችን ሊገታ ግድ ይል የነበረበትም ዘመን ነበር።

እቃን በእቃ ከመለዋወጥ ወደ አሞሌ ጨው ከፍ ያለው የግብይት ሒደት አሁን ላይ ለደረሰበት የገንዘብ እና የገንዘብ አልባ የኤሌክትሮኒክስ ግብይት አንዱ መሰረት እንደሆነ ይታመናል።

መንግስታት ፣ አገራት ብሎም ስርወ መንግስታት የራሳቸውን ልዕለ ኃያልነት በተግባር ከሚያሳዩበት እና እለት እለት በስራቸው በሚያስተዳድሩት ሕዝብ ስነ ልቦና ውስጥ ያላቸውን የገዢነት ወይም በላይነት ከሚያስተጋቡበት መንገድ አንዱ ገንዘብ ነው። ነገስታት ራሳቸውን ገንዘብ በማተም እና የንግስናቸውን ምልክት ወይም የራሳቸውን ነገስታቱን ምስል በገንዘቡ ላይ በማተም በሚያስተዳድሩት ግዛታቸው ውስጥ መገበያያ ሆኖ እንዲያገለግል ያደርጉታል።

ገንዘብ ከመገበያያነቱ እና በአገር ኢኮኖሚ ካለው ጉልህ ጠቀሜታ ባለፈ የባህል አምባሳደር በመሆንም በዘመናዊው ዘመን እንደሚያገለግልም ብዙዎች የሚስማሙበት ጉዳይ ነው። አገራት ያላቸውን የተፈጥሮ ሃብት፣ ዕምቅ እና ስብጥር ባህል፣ አገራት ሚወከሉበት የእንስሳ አይነት እና መሰል አርማዎች በገንዘቦቻቸው ላይ ይታተማል በቀላሉም ለመለየት የሚቻልበት ጉዳይ ይኖራል።

ከሰሞኑ ታዲያ ጉዳይ ተከስቶ ነበር እርሱም ድንገተኛው የኢትዮያ መገበያያ ገንዘብ የመቀየር ጉዳይ እና አዲስ ባለ 200 ብር ኖት ወደ ገበያ መግባቱ ነው። ከኹለት አመት ከመንፈቅ አካባቢ የጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ መንግስት ወደ መንበሩ በመጣበት ወቅት ከሕዝብ ዘንድ የተዘረፈው ገንዘብ ማስመለስ የሚቻልበት ሁኔታ ላይ ባላመሆናችን የመገበያያው ገንዘብ ተቀይሮ ዘራፊዎቹም ጉድ ይሰሩ የሚል ሙግት እና አስተያየት የተቀላቀለበት ጉዳይ ሲሰማ ነበር። በወቅቱ ታዲያ በርካታ ተደራራቢ ችግሮች እንዲሁም ታፍኖም ነበረ ሀሳብ ሲንሻራሸር ስለነበር ወደ አስፈጻሚው አካል የሚደርሰው ሀሳብ እጅግ የበዛ ነበር። ይነሱ ከነበሩት ሃሳቦች አንዱ ታዲያ ሕገ መንግስት እና መገበያያ ገንዘብ ይቀየር የሚል ነበር።

የጉዳዩ ጩኸት በዝምታ የተዘጋው በአንድ አፍታ ሲሆን በተለይም ደግሞ ኹለተኛ ድጋሚ ሳይነሳ መቅረቱ የጉዳዩ ተድበስብሶ መቅረቱን አመላካች ነበር። ይሁን እንጂ ባሳለፍነው ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ላይ ሰኞ መስከረም 4/2012 በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ለማንም ግልጽ ባልሆነ መንገድ የስብሰባ ግብዣ ከተላከ በኋላ በስፍራው ማልደን እነ3ድንገኝ ተደርጎ ነበር። በዚህ ወቅት ታዲያ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት መሰብሰቢ አዳራሽ የሚዲያ አካላት እና የካቢኔ አባላት እንዲሁም በገንዘብ ዘርፉነላይ የሚሰሩ የባንክ እና ኢንሹራንስ ከፍተኛ ስራ ኃላፊዎች ተገኝተው ከሰብሳቢው የሚመጣውን ጉዳይ ለመታደም በጉጉት ሲጠበቅ ነበር።

ለረጅም ሰዓት ከተሰብሳቢው ዘንድ በለሆሳስ ከጎን ከተቀመጠ ሰው ጋር የስብሰባውን ይዘት በግምት ሲተነተን ለመታዘብም የተቻለበት ሁኔታ ነበር። ይሁን እንጂ ስብሰባው ሒደት ከመጀመሩ ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት አንድ ጉዳይ ተከሰተ። የኢትዮያ ብሔራዊ ባንክ ገዢ ሆኑት ይናገር ደሴ (ዶ/ር) ከተቀመጡበት ወንበር ላይ የነበረ ወረቀት ተነስቶ በአራት ስፍራዎች ላይ በታዳጊዎች መለጠፍ ጀመረ ። ያን ጊዜ የተሰብሳቢው ሁሉ ግምት ገደል የገባበት እና ያልታሰበው ጉዳይ ስጋ ለብሶ መጣበት አጋጣሚ ተፈጠረ። አራት የገንዘብ ኖቶች ያሉበት ማስታወቂያ ሲለጠፍ የገንዘብ ቅየራ ጉዳይ መሆኑ ነበር የተሰማው። በጉዳዩ ላይ ምንም አይነት ፍንጭ እንዳልወጣ እና በጥቂት ሰዎች የተያዘ ምስጢር እንደሆነ እና በአስቸኳይ የሚከናወን ጉዳይ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አበሰሩን። ‹‹ኢትዮያ ባለፉት ኣመታት የኢኮኖሚ ስብራት ደርሶባት ነበር›› ሲሉ ክቡር ጠቅላይ ሚንስትሩ ጀምረው ነበር። በዚህም ደግሞ የኢኮኖሚ ስብራቱን ለመተገን ይህ ገንዘብን የመቄር ተግባር እጅግ አይነተኛ መፍትሔ እንደሚሆን የሚታሰብ ጉዳይ እንደሆነ ይናገራሉ።

በሙስና እና በስርቆት ላይ የሚገኙ ግለሰቦች እና መንግስት መዋቅር ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን በጆንያ እና በፌስታል ገንዘብ እየተቀባበሉ ግብይት የሚፈጽሙትን ሰዎች ጉዳይ ለመቆጣጠር እና እንደ ጠቅላይ መሚንስትሩ አባባል ‹‹ሌቦች ኢንቨስት ስለማያደርጉ›› ገንዘብ በሕገ ወጥ መንገድ ስለሚዘዋወር ይህን ሁሉ ለመቆጣጠር እና ኢትዮያ ካጋጠማት የኢኮኖሚ ስብራት የምታገገምበትን ጉዳይ እንዲፋጠን በምስጢር የተያዘው ብር ቅየራው ጉዳይ መፋጠኑን ተናግረዋል። ‹‹ኮቪድ ባያዘገየን ኖሮ እና ሕትመት ስራው ባይጓተት ኖሮ ከዚህ ቀደም ብለን መቀየር እንችል ነበር›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የምስጢር ገንዘብ የመቀየር ሒደቱ ከኮቪድ በፊት ማለትም ከመንፈቅ እድሜ በላይ ምናልባትም ወደ አንድ ዓመት የሚጠጋ ጊዜ መውሰዱን አመላካች ነው። የብር ለውጡን ለማድረግ ዋናው ምክንያት ከሁለት ዓመታት ወዲህ በአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ለመለወጥ እየተሞከረ ያለውን የኢኮኖሚ ስብራት መጠገን እንደሆነ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከለውጡ በኋላ በተደረገ ዳሰሳ ኢኮኖሚው ከፍተኛ የሆነ የማክሮ ኢኮኖሚ ማዛባት እንዳለበት በመረጋገጡ ቁልቁል ሲሄድ የነበረውን ኢኮኖሚ ማስቆም ዋናው ዓላማ ነው ብለዋል።

የብር ኖቶቹን መቀየር አስፈላጊነት አክለው ያስረዱት የብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ኖቶቹን መቀየር ያስፈለገባቸው በርካታ ምክንያቶች እንዳሉት ተናግረዋል። የመጀመርያው ምክንያት በርካታ ገንዘብ ከባንክ ውጪ በመኖሩ ሕገወጥ ተግባራት፣ ሙስናና ኮንትሮባንድ ስለተስፋፉ ያንን ለመከላከል ነው ብለዋል። ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ከባንኮች ውጪ ያለው ገንዘብ ሲበራከት የጥሬ ገንዘብ እጥረት ስለሚያጋጥማቸው ያንን ለመከላከል ታስቦ እንደሆነ አስረድተዋል።

ባለ 10፣ 50፣ 100 እና አዲስ ደግሞ ባለ 200 ብር ኖትን ያካተተው አዲሱ የብር ኖት አገሪቱ ለ23 ዓመታት ከ1990 ጀምሮ የተጠቀመችባቸው ገንዘቦች እንደተቀየሩ ታውቋል። የብሔራዊ ባንክ ገዢው ይናገር ደሴ እንደሚሉት በ1996 አካባቢ የተወሰነ ማሻሻያ የተደረገበት የተወሰኑ የብር ኖቶች መኖራቸውን አውስተው ነገር ግን በዚህ ወቅት የተደረገው የብር ቅራ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ተደረገ እንደሆነ እና ከፍተኛ ወጪ የወጣበት እንደሆነ ይፋ አድርገዋል።

አሁኑን የብር ለውጥ ልዩ የሚያደርገው ከዘመኑ ጋር አብሮ የዘመነ መሆኑ እና በተለይም ደግሞ ገንዘቡ ውስጥ የተቀበሩት የመጠበቂያ እና ትክክለኛነት ማረጋገቻዎቹ ዘመኑ የደረሰበትን ቴክኖሎጂ ተጠቅመው የተሰሩ መሆናቸው እና ለሐሰተኛ የብር ኖት ሕትመት እንዳይጋለጡ ሆነው መሰራታቸው አዳዲሶቹን ብሮች ዘመናዊነት በእጅጉ የሚገልጹ ናቸው። በተጓዳኝም ከዚህ በፊት ያለነበሩ እና ማየት ለማይችሉ ወገኖችም ታሳቢ ተደርገው ተሰሩ ሲሆን ይህም በተለይም ደግሞ በብሮች ዳር እና ዳር ላይ በእጅ ሲዳሰሱ የሚጎረብጡ መስመሮች እንዲኖራቸው ተደርጓል።

በዚህም መሰረት በ200 ብር ኖት ላይ ስምንት ክርክራት ፣ በ100 ብር ኖት ላይ ስድስት ክርክራት፣ በ50 ብር ኖት ላይ አራት ክርክራት፣ እንዲሁም በ10 ብር ኖት ላይ ኹለት ክርክራት እንዲኖራቸው ተደርጓል። ይህ አዲስ አሰራር ከዚህ ቀደም ያልነበረ እና አካል ጉዳተኞችን በዋናነት አይነስውራንን ታሳባቢ ያላደረጉ እንደነበሩ ተነግሯል። በዚህ የገንዘብ ኖት ቅየራ ወቅት በአዲስ ማሻሻያ እና ዲዛይን ያልመጣው ባለ አምስት ብር ኖት ሲሆን ይህም ከጊዜ በኋላ እንደ አንድ ብር በሳንቲም የመተካት ሀሳብ በመኖሩ እና ይህም ደግሞ ሳንቲሙ በስራ ላይ እስኪሆን ና በጊዜ ሒደት የወረቀት ገንዘቡ ከስራ እስኪወጣ ድረስ ባለ አምስት ብር ኖት በስራ ላይ እንደሚቆይ ተነግሯል። በአሁኑ ወቀት 2 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብዛት ያለው አዲስ ብር ኖት ታትሞ በብሔራዊ ባንክ ካዝና ውስጥ እንደሚገኝ የኢትዮያ ብሔራዊ ባንክ በዋና መስሪያ ቤቱ ያስታወቀ ሲሆን የባንኩ ገዢ ይናገር ደሴ ለአዲስ ማለዳ በሰጡት መረጃም 262 ቢሊዮን ብር ታትሞ እና ወደ አገር ውስጥ ተጓጉዞ በብሔራዊ ባንክ ካዝና ውስጥ እንደሚገኝ እና ለመከፋፈልም ዝግጁ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል። ይናገር ጨምረውም ስድስት ወራት ለሕትመት እና ወደ አገር ውስጥ ለማጓጓዝ ፈጀው ይኸው የብር ኖት ጠቅላላ ወጪው 3. 6 ቢሊዮን ብር እንደሆነም አውስተዋል።

አዲሱን ብር ቅየራ እና ወደ ክልሎች በሚደረግ የማጓጓዝ ረገድ ከብሄራዊ ደኅንነት፣ ከመከላከያ እና ከፌደራል ሊስ ጋር በቅንጅት የሚሰራ ስራ ሲሆን በተለይም ደግሞ ክልሎች በዚህ ወቅት ዕዝ ጣቢያ (ኮማንድ ፖስት) የማቋቋም ስልጣን እንደሚኖራቸው እና በዚህም ወቅት ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ከብሔራዊ ባንክ የተገነው መረጃ ያመላክታል።

የገንዘብ ቅየራውን እና አዲስ የገንዘብ ኖት ማስተዋወቅን በተመለከተም በርካታ አስተያየቶች ሲሰነዘሩ እና አስተያየት ሲሰጥባቸውም ተሰምቷል። ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር ቆይታ ያደረጉት የኦሮሚያ ፕላንና ኢኮኖሚ ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ተሾመ አዱኛ እንደሚናገሩት ኢትዮጵያ ከ23 ዓመታት በኋላ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ የቀየረችውን መገበያያ ገንዘብ በተመለከተ ሀሳባቸውን እንዲህ ይገልጻሉ።
‹‹ገንዘብ የአንድ አገር ኢኮኖሚ ደም ስር ነው፤ ሰዎች የሚፈልጉትን ማግኘት እንዲችሉ የጋራ መለኪያ ሆኖ ያገለግላል።

ኢኮኖሚን በመለካት፤ በማጠራቀም እና ልውውጥ እንዲካሄድ በማስቻል ገንዘብ የአንድን አገር ኢኮኖሚያዊ ህልውና አስጠብቆ እንዲሄድ ያደርጋልም።
አሁን የተደረገው የብር ኖቶች ለውጥም እነዚህን ነገሮች በማጠናከር ከዚህ በፊት በህገወጥ መንገድ ተይዞና ተደብቆ የነበረን ብር በመቆጣጠር ህጋዊ እንዲሆን ያስችላል።

አሁን አገልግሎት ላይ ያለው የብር ኖት በግለሰብ እጅ በብዛት በመኖሩ የተከሰተውን ህገ-ወጥ ንግድ ለመቆጣጠር እና ህገ ወጥ የገንዘብ ምንዛሬን ለማስቆም ትልቅ አቅም ይፈጥራል ።

የብር ኖቶቹ መቀየር ኢኮኖሚ በማረጋጋት ባለሃብቶች በኢትዮጵያ የሚያካሂዱትን ኢንቨስትመንት በማስፋፋት የምጣኔ ሃብት አመኔታን ያሳድጋል።
ሰዎች የአሜሪካን ዶላር በብዛት የሚጠቀሙት ዋጋው ባለበት ስለሚቆይና ባለመዋዠቅ ኢኮኖሚያዊ አመኔታን ስላተረፈ ነው። አሁን ላይ መንግስት የፋይናንሱን ሴክተር ደህንነት ባጠናከረ ቁጥር ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ብር መዋዕለ ንዋይ ያፈሳሉ። ንብረቶችን በመግዛትም የኢትዮጵያን ብር የግብይትና የሽያጭ መጠቀሚያቸው እንዲሆን ያደርጋሉም።

ይህም በተለያዩ ዘርፎች የሚካሄዱ የስራ እድል ፈጠራዎችን ለማሳካት እድል የሚፈጥር ነው።
በሌላ በኩል የብር ኖቶቹ በህጋዊ መስመር ስር ስለሚሆኑ የመንግስትን የገንዘብ ፖሊሲ ውጤታማ ለማድረግና በገንዘብ ዝውውር ላይ የሚወሰኑ ጉዳዮችን ለማስፈጸም ያስችላል።

በቀጣይ አዲሱን የብር ኖት በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች እንዲዳረስ ባንኮችን፤ አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማትንና ህብረት ስራ ማህበራትን በሰፊው መጠቀም የሚያስፈልግ ሲሆን ከፍተኛ የገንዘብ ዝውውር የሚፈጸምባቸውን አካባቢዎች በመለየት ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ ደግሞ ዋናው አስፈላጊው ጉዳይ ነው፤
የኢኮኖሚ ባለሙያዎችም በጥናት ላይ የተመሰረተ ውጤታማ ሃሳብ በማምጣት ከመንግስት ጋር ሊሰሩ ይገባል›› ሲሉ ሃሳባቸውን ይሰጣሉ።

ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውርን ለመግታት
አዲሱ የገንዘብ ኖት ቅየራ እንደምክንያት ከተጠቀሱት ውስጥ አንደኛው እና ቀዳሚው የኢኮኖሚ ስብራቱን ለመጠገን እና ለታሰበው የምጣኔ ሀብት ዕድገት ግስጋሴ ለማሳለጥ እንደሆነ ይነገራል። ይሁን እንጂ ከዚህም ባለፈ ደግሞ በአገር ውስጥ ያለውን ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር እና ከባንክ ውጭ የሚንቀሳቀሰውን ሕገ ወጥ ገንዘብን በተመለከተ ለመቆጣጠር እና ወደ አገር ምጣኔ ሀብት ላይ እንዲገባ ለማድረግ እንደሆነም ተነግሯል።

በአሁኑ ወቅት ከብሔራዊ ባንክ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ከባንክ ውጭ የሚንቀሳቀስ ያልተመዘገበ 113 ቢሊዮን ብር መኖሩን እና ይህም በአገር የምጣኔ ሀብት እድገት ላይ ከፍተኛ የሆነ አሉታዊ ተዕዕኖ እንዳለው ተመላክቷል። ከተጠቀሰው 113 ቢሊዮን ብር በተለየ የብሔራዊ ባንክ የቅርብ ሪርት እንደሚያመለክተው 139 ቢሊዮን ብር ከሚዘዋወረው ውስጥ 109 የሚሆነው ከባንክ ስርዓት ውስጥ ያልተካተተ እንደሆነ እና አሁንም ትኩረት የሚያሻው ጉዳይ እንደነበር አስታውቋል። ከዚህም ጋር ተያይዞ ከመንፈቅ በፊት የኢትዮያ የባንኮች ማኅበር በዚህ ሳምንት ይፋ የደረገውን የብር ቅየራን በተመለከተ ተግባራዊ እዲደረግ መንግስትን ሲወተውት እንደነበርም የአዲስ ማለዳ በቅርብ ጉዳዩን ስትከታተል የነበረችው ጉዳይ ነበር።

‹‹ከባንክ ውጭ ሚዘዋወረው ከፍተኛ መጠን ያለው የገንዘብ መጠን ሕገ ወጥ ንግድን፣ ሐሰተኛ የብር ሕትመትን እና አጠቃላይ መደበኛ ያልሆነውን ንግድ ይደጉመዋል። ይህ ደግሞ በገቢ አሰባሰቡ ላይ ከፍተኛ የሆነ ማነቆ ነው›› ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐብይ አሕመድ የገንዘብ ቅየራውን ይፋ ባደረጉበት ወቅት ተናግረዋል። ይህም ታዲያ በባለሙያዎች ዘንድ እንደሚነገረው በኢመደበኛ እና ሕጋዊነትን ባልተከተለው መልኩ የሚካሔደውን የንግድ እንቅስቃሴ በተገቢው ደረጃ ይቆጣጠረዋል የሚል እምነት እንዳላቸው ይናገራሉ።

በ20ኛው ክፍለ ዘመን የተደራጀ እና ዘመናዊ መሳሪያ የተጠቀመ ጦርነት የተባለለት የኢትዮ- ኤርትራ ጦርነት ወቅት ላይ ነበር ኢትዮያ የኢህአዲግ ዘመን የመጀመሪያ የመገበያያ ገንዘቧን የቀየረችው። በወቅቱ ከምጣኔ ሀብት አንደምታው ይልቅ በኹለቱ አገራት መካከል ነበረው መካረር እና አለመግባባት ጉዳይ ነበር ለመቀየሩ ዋነኛ ምክንያት። ድንገተኛው የብር ቅራ ጉዳይ ታዲያ በወቅቱ ለነበሩ እና ባለሀብቶች እና ከፍተኛ ገንዘብ በእጃቸው ላይ ለነበረ ግለሰቦች ከፍተኛ መደናገጥን የፈጠረ ነበር። ነገር ግን ከፍተኛ ድንጋጤ የተፈጠረው እና በኋላም ላይ ወደ ጦርነት እንዲያመራ ያደረገው ጉዳይ ከግማሽ በላይ የሚሆነው በአገሪቱ የሚገኘው ገንዘብ በያኔው የኤርትራ መንግስት ዕጅ ውስጥ መግባቱ እና በወቅቱ ደግሞ በኤርትራ ውስጥም ከናቅፋ ጎን ለጎን ብርም መገበያያ ስለነበር ነው። ድነገተኛው የብር ቅየራ ታዲያ ከፍተኛ ሆነ ብስጭት እና ቁጭት በኤርትራ በኩል በመፍጠሩ መካረሩ ወደ ጦርነት አመራ።

ከሃያ ዓመታት በኋላም በሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ናላዋ የዞረው ኢትዮያ ከበርካታ ወራት ውጣ ውረድ በኋላ ገንዘብ ኖቶችን ስር ነቀል በሚባል እና በእርግጥም በአዳዲስ የደኅንነት መጠበቂያዎች ያሸበረቁ መሆናቸው ደግሞ እጅግ ውድ ወጪ እንደወጣባቸው አሳባቂዎች ናቸው። ከሀያ ዓመታት በፊት እንደ ዓለም አቀፉ ገንዘብ ተቋም መሰረት በኤርትራ መንግስት በኩል ተከማችቷል የተባለ የብር መጠን ከ1983 እስከ 1985 ባለው የኹለት እና ሦስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ 1ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር እንደነበር ለማወቅ ተችሏል።

ይኸው ከፍተኛ ገንዘብ ማለትም በሰኔ ወር 2012 በብሔራዊ ባንክ እንደተገለጸው 113 ቢሊዮን ብር ከባንክ ስርዓት ውጪ የሚዘዋወር ሲሆን ይህም ከአመት በፊት ከነበረው የ92 ቢሊዮን ብር ከባንክ ውጪ ይዘዋወር እንደነበር ታውቋል። ይህ ከባንክ ስርዓት ውጪ በመዘዋወር በኢመደበኛው ንግድ ሒደትን በከፍተኛ ሁኔታ ሲደጉም ነበረው ገንዘብ እና በፍጥነት እያደገ የመጣበትም ጉዳይ ካለው ከፍተኛ የሆነ የብድር ፍላጎት አንጻር እንደሆነ መረጃዎች ያመላክታሉ።

በ2007 እና 2008 ላይ 66 ቢሊዮን የነበረው ከባንክ ስርዓት ውጪ ይዘዋወር የነበረው ገንዘብ በቀጣዩ አኣመት በ10 በመቶ ዕድገት በማሳየት ከፍ ብሎ ነበር። ነገር ግን ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ ከባንክ ውጪ ወጣው እንደ ብሔራዊ ባንክ ገለጻ አገሪቱ ከፍተኛ የሆነ አለመረጋጋት እና ውጣ ውረዶች በነበሩበት የ2008 እና 2009 ላይ እንደነበር ታውቋል። እነዚህን እና መሰል ጌዜያቶችን በመጠቀም ከባንክ ስርዓት ውጪ ሲንቀሳቀሱ ነበሩት ገንዘቦች ሔደው ሔደው 113 ቢሊዮን ብር ደርሰዋል።
ከሰሞኑ ታዲ ይፋ በተደረጉ የገንዘብ ኖቶች ባንክ የማያውቃቸው እና ሕገ ወጥ ዝውውሮች እና ግብይቶችን የሚያጠናክሩ ገንዘቦች የአገልግሎት ዘመናቸው የተጠናቀቀ ይመስላል። ለሦስት ወራት መቀሪያ ጊዜ የተሰጣቸው ገንዘብ በእጃቸው ሚገኝ ግለሰቦች የሚከተሏቸውን ቅደም ተከተሎችንም ይፋ ተደርጓል። ከ 10 ሽህ ብር በላይ ይዞ ወደ ባንክ በመሔድ ለመቀየር የፈለገ ግለሰብ የባንክ አካውንት እንዲኖረው እንደሚያስፈልግ እና መክፈትም እንደሚኖርበት ይደነግጋል። በዚህ ሒደት የሌላ ሰው ገንዘብ መመንዘር እንደማይቻል እና ገንዘቡን ይዞት መጣው ግለሰብ ገንዘቡን በስሙ በተከፈተ አካውንት ውስጥ ማስገባት እንደሚኖርበት በሚገባ ተነግሯል። ከዚሁ ከገንዘብ ቅራው ጋር በተገናኘ አንዳንድ ባንኮች ሐሰተኛ የብር ኖቶችን ሲቀበሉ እንደነበሩ በጠቅላይ ሚንስትሩ የተነገረ ሲሆን ከዚህ በኋላ በየትኛውም ባንክ አማካኝነት ወደ ብሔራዊ ባንክ የሚፈሰው ሐሰተኛ የብር ኖት ባንኩን እስከ ማዘጋት የሚደርስ ጠንከር ያለ እርምጃ እንደሚያስወስድ ዐብይ አሕመድ ተናግረዋል።

በአፈጻጸም ሒደት ላይም ቢሆን የባንክ ሬዘዳንቶች እና ቦርድ አባላት ጠንካራ እርምጃ እንዲወስዱ እና ይህ ባልሆነበት ደረጃ መንግስት እርምጃ ሲወስድ ምንም አይነት ቅሬታ እንደማይቀበል ከወዲሁ እንዲያውቁት በሚገባ የተነገረ ሲሆን የካቢኔ አባላትም በዚህ ጉዳይ እደከዚህ ቀደሙ በአፈጻጸም መስነፍ መንግስት ሊታገሰው የማይችል ሁኔታ እንደሆነ በጠቅላይ ሚንስትሩ በኩል የተላለፈ ጠንካራ መልዕክት ነበር።

በጥሬ ገንዘብ ዕጦት ሲሰቃዩ የነበሩት ባንኮችም በአዲሱ የብር ኖት መቀየር በኋላ ከፍተኛ የሆነ መሻሻል እንደሚታይባቸው ተገምቷል። ብሔራዊ ባንክ ገዢው ይናገር ደሴ (ዶ/ር) በአንድ በተወሰነ አካል ብቻ ተይዘው እና ተከማችቶ የነበረው የገንዘብ መጠን በንግድ ባንኮች ላይ ታይቶ ለነበረው የጥሬ ገንዘብ ዕጥረት አይነተኛ ሚና መጫወቱን እና ይህንንም ተከትሎ በምስጢር የተካሔደው ቅየራ ይፈታዋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተስፋቸውን አስቀምጠዋል። ከዚህ በቀጣይም ከባንክ ስርዓት ውጪ ሚንቀሳቀሱ ገንዘቦች እንደማይኖሩ አስታውቀዋል መንግስትም በትኩረት እንደሚከታተል ተናግረዋል።

ከመስከረም 6/2013 ጀምሮ በተለያዩ ባንኮች ዘንድ መቀየር የጀመረው አዲሱ የብር ኖት ከቀኑ 9፡30 ጀምሮ በአዲስ አበባ ባሉ የተለያዩ ባንኮች ተከፋፍሏል። በዝግጅቱ ላይም የብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶ/ር ይናገር ደሴ እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቤ ሳኖ የተገኙ ሲሆን፤ ዛሬ ከቀኑ 9፡30 ጀምሮም በአዲስ አበባ አካባቢ ባሉ ባንኮች ብር መቀየር ተጀምሯል ሲልም ቢቢሲ አመርኛ ዝግጅት ክፍል አስነብቧል።

በመሆኑም የብሔራዊ ባንክ ባስቀመጠው መመሪያ መሠረት፤ 100 ሺህ ብር እና ከዚያ በላይ ገንዘብ በእጃቸው ላይ ያለ ግለሰቦችና አካላት በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ብቻ ወደ ባንክ በመሄድ ገንዘቡን መቀየር እንደሚችሉም ታውቋል።

አገልግሎቱ በማንኛውም የባንክ ቅርንጫፍ እንደሚሰጥ የተጠቆመ ሲሆን ሥራ አስኪያጁ፤ ግለሰቦችም ሆኑ ድርጅቶች እጃቸው ላይ ያለውን ብር ወደ አዲሱ መቀየር አሊያም ከሒሳብ ቁጥራቸው አዲሱን የብር ኖት ማውጣት እንደሚችሉ ተነግሯል።

እጃቸው ላይ ከ100 ሺህ ብር በታች ያላቸው ግለሰቦችም እስከ 2 ወር ከግማሽ ድረስ ገንዘባቸው እንዲቀይሩ ቀነ ገደብ ተቀምጧል።
ከ100 ሺህ ብር በላይ ያላቸው ግን በዚህ አንድ ወር ብቻ ቅየራውን ማጠናቀቅ ያለባቸው ሲሆን፤ ከዚያ በኋላ የሚመጣ በየትኛውም ባንክ እንደማይስተናገድ መንግስት ጠንከር ያለ ማስጠንቀቂያ አውጥቷል። በሕገ ወጥ መንገድም እየተዘዋወረ የሚገኘውን ገንዘብ ለመቆጣጠር ያለመ ከመሆኑ ጋር ተዳምሮ ሰሞኑን የብር ቅየራው ይፋ ከሆነ ጀምሮ በድንበር አካባቢዎች በርካታ ገንዘብ በሕገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወር በቁጥጥር ስር መዋል ጀምሯል።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ በኢትዮጵያ ክልል ውስጥ የሚንቀሳቀሰውን ሕገ ወጥ ገንዘብ በተመለከተ በቁጥጥር ስር በሚውልበት ወቅት በቁጥጥር ስር ያዋለው አካል እንዲወስደው ትዕዛዝ ሰጥተዋል። ይህንንም ተከትሎ መከላከያ፣ ፌደራል ፖሊስ ወይም ብሔራዊ ደኅንነት በዚህ የክትትል እና ቁጥጥር ሒደት ላይ ስለሚሳተፉ ከሦስቱ ጸጥታ አካላት ውስጥ በለስ የቀናው መስሪያ ቤት በቁጥጥር ስር የሚያውለው ገንዘብን ራሱን ለማጎልበት እና ተቋማዊ አቋሙን ለመገንባት እንደሚያውለው ይጠበቃል።

በባለሙያ ዓይን ጉዳዩ እንዴት ይታያል?
በኢትዮያ ውስጥ ያለውን የማክሮ ኢኮኖሚክስ በአንክሮ ለረጅም ዓመታት የሚከታተሉት እና ሰፊ ሙያዊ ትንታኔም በመስጠት የሚታወቁት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አብዱልመናን መሐመድ ከአዲስ ማለዳ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሙያዊ ምላሻቸውን እንዲህ ያስቀምጣሉ። ‹‹ከባንክ ውጪ የሚዘዋወረውን 113 ቢሊዮን ብርን በተመለከተ አዲሱ የገንዘብ ለውጥ ሊቆጣጠረው ይችላል ወይ ? በጀመሪያ ደረጃ ከዚህ ገንዘብ መጠን ጋር ተያይዞ ብዥታ አለ።ኢኮኖሚ ውስጥ የሚሸከረከር ገንዘብ ስንል በብሄራዊ ባንክ እውቅና ያለው እና በየግዜው በሚያወጣ ሪፖርቶች ላይ የሚጠቀስ ነው።በግለሰቦች፣በድርጅቶች እና በባንኮች ካዝና ያለ ብር ማለት ነው።የሚሽከረከረው ገንዘብ በዝቷል ወይስ ስንል አልበዛም።የ አስር አመት መረጃ ተመልክቻለው ምንም አዲስ የተፈጠረ ነገር የለም።በአማካኝ በመቶ ሲያድግ ባለፉት ሁለት አመታት ግን በ በመቶ ነው ያደገው።

በለውጡ ምክንያት አዲስ ኖቶች ወደ ኢኮኖሚው ይገባሉ እንጂ ሙሉ ገንዘቡ ወደ ባንክ ተጠቅልሎ ሊገባ አይችልም። የመተካት ስራ ነው የሚሆነው። ፎርጅድ የሆነ ገንዘብ ካለ ከጥቅም ውጭ ይሆናል ማለት ነው። 2. አዲሱ ገንዘብ ለውጥ አሁን መደረጉ ትክክለኛው ሰዓት ነው ብለህ ታምናለህ? ካልሆነስ መቼ መሆን ነበረበት? ግዜ ወስዶ መታሰብ የነበረበት ጉዳይ ነው።አላማው ምንድ ነው? አላማው ይሳካል ወይ? ጥቅሙ ምንድ ነው ጉዳቱስ? የሚሉት መታሰብ ነበረበት። ሃገሪቱ ያለችበት ሁኔታም ከግንዛቤ መግባት ነበረበት። 3. ለገንዘብ ማሳተሚያ የወጣው ወጪ አዋጪነቱንስ በሚመለከት እንዴት ታየዋለህ? የወጣው ወጪ ቀላል የሚባል አይደለም።እንዲሁም በቅየራ ወቅት ላይ ሌላ ትልቅ ወጪ ይጠይቃል።ከሎጀስቲክ ጋር በተያያዘ ማለቴ ነው።ኢኮኖሚውም ላይ የሚያሳድረው ጫና ይኖራል።ለውጡ ባግባቡ ካልተተገበረ የንድግድ ዲስረፕሽን ነው የሚፈጥረው።ጥቅም ተብሎ የቀረበ አሳማኝ የሆነ ነገር ብዙም አላየሁም።

ከትልልቅ ዲኖሚኔሽኖች ጀምሮ በሂደት መቀየር ይቻል ነበር።ወጪውም በተወሰነ አመታት ውስጥ ይሆን ነበር።ሽግ ግሩም ቀለል ያለ ያደርገዋል። 4. የብር መቀየር እንደተባለው የኢኮኖሚ ስብራቱን ይጠግነዋል ወይ? በፍጹም።የሃገሪቱ ኢኮኖሚ ችግር መጠነ ሰፊ እና ከብር መቀየር ጋር ግን ኙነት የለውም።
ለምሳሌ ብር ተቀየረ አልተቀየረ የሃግሪቱ እዳ ጫና አይቀንስ፣የውጭ ምንዛሪ ችግሯ አይፈታ ወዘተ። 5. በሌሎች አገራት ልምድ መገበያያ ገንዘብ በየስንት ጊዜው ይቀየራል? ብዙዎች ረጅም ጊዜ ተጠቅመናል ይላሉ ። ሙሉ ቅየራ አልፎ አልፎ ነው የሚካሄደው።በየግዜ ከስር ከስር መቀየር ግን የተለምደ ነው።በጠንካራ እና ለፎርጀሪ በማይመች ኖቶች መተካት የተለመደ ነው።

ለምሳሌ እንግሊዝ እእአ ከ2016 ጀምሮ በወረቀት የተሰሩ አምስት፣አስር እና ሃያ ፓውንድ በፕላስቲክ ኖቶች ኖቶችን እየቀየረች ነው።በዘመቻ ግን አይደለም። 6. ሙሉ በሙሉ ገንዘብ ለመቀየር የተሰጠው የ3 ወራት ጊዜ በተመለከተ የእርስዎ አስተያየት ምንድነው? ይበዛል ወይስ ያንሳል? በመጀመሪያ ደረጃ ርጅም ግዜ መስጠት ያስፈልጋል።በሁለተኛ ደረጃ መቀየሪያ ግዜው አልፎ አሮጌዎቹ ኖቶች ከገበያ ቢወጡም ብሄራዊ ባንክ የመቀየር ግዴታ ሊኖርበት ይገባል።የሰጠውን ኖት አልቀበልም ሊል አይችልም›› ሲሉ ሐሳባቸውን ያስቀምጣሉ።

ቅጽ 2 ቁጥር 98 መስከረም 9 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here