የፈረቃ ትምህርት እና የአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች

0
1477

በአገራችን ኢትዮጵያ ዓለም አቀፉን ወረርሽኝ ጉዳይ በሚመለከት መንግስት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ከማወጅ ጀምሮ ረጅም መንገዶችን ተጉዟል። ይህ የሆነበትም ምክንያት የአኗኗራችን ዘዬ እና የበሽታው ፀባይ በእጅጉ የማይጣጣም በመሆኑ ከፍተኛ ዕልቂት በአደጉት አገራት ላይ እንዳደረሰው እኛም ጋር እንዳያደርስ ለማድረግ በመታሰቡ እና ከአደጉት አገራትም ትምህርት በመውሰድ እንደሆነም ይታወቃል።

በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ከተወሰዱት እርምጃዎች ውስጥ በተከሰተ በአጭር ቀናት ውስጥ ትምህርት ቤቶችን መዝጋት ነበር። ይሁን እንጂ ይህን የትምህርት ቤቶችን መዝጋት የበሽታው ፀባይ በቀጣይ ከእኛው ጋር እንደሚቆይ በመታመኑ እና ሕይወትም መቀጠሉ ስለሚኖርበት ትምህርት ቤቶች መከፈት እንደሚኖርባቸው የኢፌዲሪ ትምህርት ሚኒስቴር መግለጫ ሰጥቷል።

በዚህም ረገድ እስከ ሦስት ፈረቃ በሚደርስ የትምህርት አሰጣጥ ሒደት እንዲከወን እና በአንድ ክፍል ውስጥ የሚማሩ ተማሪዎችን ቁጥር ለመቀነስ ዕቅድ መያዙንም ተገልጿል። አዲስ ማለዳ ጉዳዩን በሚመለከት ሰፋ ያለ ትንታኔ ይዛ ቀርባለች ከባለሙያዎችም ጋር ቆይታ አድርጋለች።

ዓለም ባለፉት ሰባት ወራት ድንገት በቻይና ምድር ኮሮን ቫይረስ የተባለ ወረርሽኝ ተከስቶ የምትይዘውን የምትጥለውን አሳጥቷት የከረመው ኮቪድ-19 አሁንም ከእለት ወደ እለት ስርጭቱ እየጨመረ ቢሆነም ህይወት መቀጠል አለባት እና እስካሁን ተገድበው የነበሩ እንቅስቃሴዎች በመጠኑም ቢሆን ለማስጀመር ጥረት እየደረገ ነው፡፡
ኢትዮጵያም አንዷ የዓለም አካል ናት እና ኮቪድ-19 እንደ ሌሎች ወረርሽኙ ክፉኛ ከበረትባቸው አገሮቸ መሐል ባትሆንም የወረርሽኙ ሰለባ በመሆኗ ላለፉት ሰባት ወራት የትምህርት መቋረጥ፣ የትራንስፖርት በግማሽ የመጫን ገደብና መጣል አልፎ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥም ቆይታ ነበ፡፡

ለስድስት ወራት ታወጆ የነበረው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጊዜው በመጠናቀቁ አሁን ላይ አንዳንድ የጸጥታ ችግር ካለባቸው ቦታዎች በስተቀር በመላው ኢትዮጵያ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ነፃ እንቅስቃሴ እንድደረግ ተወስኗል፡፡ በመሆኑም ግማሽ ዓመት ያክል ተቋርጦ የነበረው ትምህርት፣ ኮቪድ-19 እንዳለ ስርጭቱ ሊስፋፋ ከሚችሉ ተግባራት በጥንቃቄ እተገበሩ ሁኔታዎች ማስቀጠል አንደሚቻል የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡ ይህኑ ተከትሎ ከዚህ በላይ ትምህርት ተቋርጦ ከቀጠለ የትምህርት ዓመት ሊዛባ ይችላል፣ የትምህት ዓመት ከተዛባ ደግሞ አንድ ዓመት ወይም አንድ ትውልድ አገሪቱ እንዳታጣ ተሰግቶ ትምህረት መጀመር እንዳለበት ታምኖበታል፡፡

በኢትዮጵያ ብዛት ያለው የሰዎች አንቅስቃሴ የሚበዛባቸው አንደ ትምህርት ቤት የመሳሰሉ እና ሌሎች ቦታዎች ላይ ኮቪድ-19 ባገናዘበ ሁኔታ መከወን ይቻላል የሚል ሀሳብ እንዲቀርብ ሲጠበቅ የነበረ ጉዳይ ነበር፡፡ የጤና ሚኒስቴር የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል እየተወሰዱ ያሉ የጥንቃቄ እርምጃዎችን በአግባቡ በመተግበር ትምህርት ቤቶች ቢከፈቱ የሚል ምክረ ሀሳብ መስከረም 8/2012 ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቧል፡፡

የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምላሽና ቀጣይ እርምጃዎች ላይ ያተኮረ ሪፖርት እና ምክረ ሀሳብ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርበዋል። ሚኒስትሯ ያቀረቡት ምክረ ሃሳብ ወረርሽኙን ለመከላከል እየተወሰዱ ያሉ የጥንቃቄ እርምጃዎችን በመተግበር ትምህርት ቤቶች ቢከፈቱ የሚል ነው፡፡
ትምህርት ለመጀመር ከመወሰኑ በፊት ግን ጠንካራ ግብረ ኃይል በየደረጃው ተቋቁሞ ወደ ሥራ መገባት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ አንደ ጤና ሚኒስቴር ሀሳብ ከሆነ ትምህርት ለማስጀመር ከዚህ በፊት ከነበረው የመማር ማሰተማር ስርዓት ጀመሮ አዳዲስ አሰራሮችን ተግባራዊ ማድረግ ይጠይቃል፡፡ የትምህርት ሚኒስቴር ከሚመለከታቸው አጋር አካላት ጋር በመተባበር ትምህርት ለመጀመር የሚያስችሉ ሁኔታዎች ላይ ጥናቶችን እያካሄደ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

እስካሁን ትምህርት መቋረጡን ተከትሎ ተማሪዎች በቤታቸው አንድቆዩ በመገደዳቸው ተያይዞ ፆታዊ ጥቃትና ያለዕድሜ ጋብቻ ማሻቀብ ተገልጿል፡፡ በመሆኑም የዓለም የጤና ድርጅት ያስቀመጠውን መስፈርት ከግምት ውስጥ በማስገባትና አስፈላጊውን ቅድመ ጥንቃቄዎች በማሟላት እንደ የአካባቢው ተጨባጭ ሁኔታ ትምህርት ቤቶችን መክፈት የሚያስችል ምክረ ሃሳብ በጤና ሚኒስቴር መቅረቡ የሚታወስ ነው፡፡

ኮቪድ-19 በኢትዮጵያ ከ26 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎችን ከትምህርት ገበታ ዉጭ አድርጓል ተብሏል፡፡ ኮቪድ-19 ተማሪዎች አስካሁን ሙሉ በሙሉ ከትምህርት ገበታ ውጭ እንድቆዩ ከማድጉ በተጨማሪ መደበኛ ትምህርት በሚጀመርበት ጊዜ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እስከ ቅድመ መደበኛ ድረስ በተለያዩ ምከንያቶች ወደ ትምህርት ገበታቸው ላይመለሱ ይችላሉ የሚል ስጋት አንዳለ አዲስ ማለዳ ከዚህ በፊት የነጋገረቻቸው የትምህርት ባለሙያዎች ስጋታቸውን መግለጻቸው የሚታወስ ነው፡፡

ትምህርት ሚኒስቴር በበኩሉ በትምህርት ቤቶች አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ትምህርት ለመጀመር ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጿል፡፡ ሚኒስቴሩ እንዳስታወቀው ከሆነ መንግስት በትምህርት ቤቶች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል፣ የውሃ እና የእጅ ማፅጃ አቅርቦቶችን በማሟላት እንዲሁም ትምህርት ቤቶችን የማፅዳት ስራዎችን በማከናወን መደበኛ ትምህርት እንደሚጀመር አስታውቋል፡፡

የትምህርት ሚኒስትሩ ጌታሁን መኩሪያ (ዶ/ር) ትምህርት ቤቶች ሲከፈቱ ተማሪዎች እንደየ ደረጃው ወደ ክፍል ገብተው ትምህርታቸውን እንደሚከታተሉ የገለፁ ሲሆን ትምህርት ሲጀመርም በአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች የሚጀመር መሆኑን እና በቀጣይም ሌሎች የትምህርት ክፍሎች ወደ መደበኛ ትምህርቱ እንደሚገቡ ተናግረዋል፡፡

በትምህርት ቤቶች የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የተቀመጡ ጥንቃቄዎች ሙሉ በሙሉ የሚተገበሩ መሆኑን እና የትምህርት አሰጣጡ ሂደትም በፈረቃ የሚሰጥ መሆኑንም ሚኒስትሩ ጨምረው አብራርተዋል፡፡ የፈረቃ ስርዓቱም እንደየአካባቢው ሁኔታ ከ 2 እስከ 3 ሊሆን እንደሚችልም አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡
የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል በትምህርት ቤት ውስጥ መምህራኖች ትልቁን ሃላፊነት ሊወጡ እንደሚገባ የተገለፀ ሲሆን ወላጆችም ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት ሲልኩ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቧል።

በአዲስ አበባ የሚገኙ የግል ትምህርት ቤቶች ትምህርት ሚንስቴር ያቀረበውን ተማሪዎችን ከ2 እስከ 3 ፈረቃ የማስተማር ስርዓት ወይም ምክረ ሀሳብ እንደማይስማማቸው ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል፡፡ የግል ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች በሦስት ፈረቃ ለማስተማር እንደሚቸገሩ የአዲስ አበባ የግል ትምህርት ቤቶች አሰሪዎች ማህበር ፕሬዝደንት አበራ ጣሰው ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል፡፡

ትምህርት በፈረቃ መሆኑ በተማሪዎች ላይ ምን ተጽእኖ ሊኖረው ይችላል የሚለውን አዲስ ማለዳ ተማሪዎችን አነጋግራ ያኘችው ምላሽ አግኝታለች፡፡
አቅሌሲያ ታምራት በናዝሬት የግል ትምህርት ቤት የሦስተኛ ክፍል ተማሪ ናት፡፡ አቅሌሲያ ትምህርት በፈረቃ በሚለው ሀሳብ ላይ ሀሳቧን ለአዲስ ማለዳ ስትገልጽ “ከዚህ በፊት የምማረው ሙሉ ቀን ነበር፡፡ ሙሉ ቀን ስማር በቂ የእረፍት ጊዜና የመማሪያ ጊዜ ነበረኝ፡፡ አሁን በፈረቃ የተባለው ሀሳብ ተግባራዊ ከሆነ ከጓደኞቼ ጋር የምጫወትበት በቂ ጊዜ አይኖረኝም፡፡ ትምህርቴንም ተነቃቅቼ ልማር አልችልም፡፡” ስትል ሀሳቧል አጋርታለች፡፡ አቅሌሳ አክላም ትምህርት ቤት ላይ ከጓደኞቼ ጋር በደንብ ካልተጫወትኩ ትምህርት አይገባኝም ስትል ትገልጻለች፡፡

የተማሪ አቅሌሲያ ቤተሰቦችም አቅሌሲያ የናፈቃትን ትምህርትና ጓደኞቿን ለማግኘት አንደቸኮለች በመግለጽ ህፃናቶች ትምህርት ቤት ላይ በቂ ጊዜ ማግኘት አንዳለባቸው ሀሳባቸውን ለአዲስ ማለዳ ገልቷል፡፡ የአቅሌሳ ቤተሰቦች እንደሚሉት ትምህርት በቂ እረፍት እና መነቃቃት የሚፈልግ ጉዳይ በመሆኑ ሊታሰብብበት ይገባል ይላሉ፡፡

አንዳንድ ትምህርት ቤቶች ትምህርት በፈረቃ የሚለውን ሀሳብ ለመማር ማስተማር አመቺ አንዳልሆነ በማመናቸው ትምህርት ሲጀመር በቀናት ልዩነት ተማሪዎችን ለማስተማር እቅድ መያዛቸውን አዲስ ማለዳ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል፡፡ ትምህርት ቤቶቹ ያቀዱት አማራጭ የመማር ማስተማር ዘዴ አንድ ቀን የተማሩትን ተማሪዎች በሚቀጥለው ቀን እቤታቸው እንዲቆዩ በማድረግ ሌሎች ተረኛ ተማሪዎችን ለማስተማር የሚል ሀሳብ ያሰበ ነው፡፡

አዲስ ማለዳ ካነጋገረቻቸው ትምህርት ቤቶች ውስጥ “አርኣያ ለትውልድ አጸደ ህፃናት” የግል ትምህርት ቤት ይገኝበታል፡፡ ትምህርት ቤቱ ተማሪዎችን በዕለታዊ ፈረቃ ትምህርት መስጠት አሰቸጋሪ መሆኑን በማመን ተማሪዎቹን በቀናት ፈረቃ ለማስተማር መወሰኑን የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህርት ሰላማዊት አዳሙ ለአዲስ ማለዳ ሀሳባቸውን አጋርተዋል፡፡ መሰረት አንደሚሉት ትምህርት ቤታቸው በሳምንት ስድስት ቀን ቅዳሜን ጨምሮ ተማሪዎችን በሁለት ፈራቃ ለማስተማር አቅደናል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

መሰረት እንደሚሉት ተማሪዎችን በእለታዊ ፈረቃ ለማስተማር ለወላጆችም ሆነ ለህፃናቶች አስቸጋሪ በመሆኑ በሁለት ፈረቃ ሦስት ሦስት ቀን ለማስተማር የወሰኑበትን ሁኔታ ያስረዳሉ፡፡ መሰረት አክለውም ትምህርት ቤታቸው ተማሪዎች በሁለት ፈረቃ በመከፈላቸው ሦስት ቀን እቤታቸው በሚቆዩበት ጊዜ ቤታቸው ከወላጆቻቸው ጋር ወላጆችን ያሳተፈ የቤት ስራ ከወትሮው በተለየ ሁኔታ ለመስጠት መዘጋጀታቸውን ጠቁመዋል፡፡ ይህም የሆነበት ተማሪዎች እቤታቸው በሚቆዩበት ጊዜ እንዳይዘናጉ እና ትምህርት ላይ ያላቸው ጊዜ ሳይቋረጥ አንዲቀጥል ለማድረግ መሆኑን ርዕሰ መምህርቷ ያብራራሉ፡፡ አርኣያ ለትውልድ አጸደ ህፃናት ትምህርት ቤት በተጨማሪም ቴክኖሎጂን በመጠቀም ተማሪዎች እቤታቸው በሚቆዩበት ጊዜ በደምጽና በምስል የተደገፈ የትምህርት ግብዓት ተደራሽ ለማድረግ ዝግጅት ማድረጉን ለአዲስ ማለዳ ይገልጻል፡፡

በሌላ በኩል አዲስ ማለዳ ካነጋገረቻቸው ትምህርት ቤቶች መካከል ሦስት ስማቸው አንዳይጠቀስ የፈለጉ ከአንደኛ አስከ ስምንተኛ ክፍል ትምህርት የሚሰጡ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎቻቸውን በአንድ ቀን ልዩነት ፈረቃ ለማስተማር ዝግጅት ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡ ትምህርት ቤቶቹ ተማሪዎችን አንድ ቀን አለፍ ፈረቃ ለማስተማር የወሰኑበት ምክንያት ተማሪዎችን በአንድ ቀን በሁለት ፈረቃ ከማስተማር የተሻለ መሆኑን በማሰብ መሆኑን ይናገራሉ፡፡

ይህ በእንዲህ አንዳለ አንዳንድ የግል ትምህርት ቤቶች ተማሪዎችን በፈረቃ ለማስተማር እንደሚቸገሩ ያብራራሉ፡፡ የፈረቃ ትምህርትን ተግባራዊ ለማድረግ እንደሚቸገሩ የሚናገሩ ትምህርት ቤቶች በበኩላቸው የግልና የመንግስት ትምህርት ቤቶች በአንድ ከፍል የሚስተምሯቸው የተማሪዎች ቁጥር ተመሳሳይ አይደለም ሰለሆነም የግል ትምህርት ቤቶች ላይ ድሮም የተማሪዎች ቁጥር የተመጠነ ስለነበር በዚያ መቀጠል ይሻላል የሚል ሀሳብ አላቸው፡፡

አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው በአዲስ አበባ በሚገኙ በግልና በመንግስት ትምህርት ቤት የሚስተምሩ መምህራን በበኩላቸው የፈረቃ ትምህረት በተለይም በአንድ ቀን ሁለት ፈረቃ ማስተማር የሚለው ሀሳብ ተማሪዎች ላይ የትምህርት አቀባበል ክፍተት እንሚፈጥ ያስረዳሉ፡፡

ሀሳባቸውን ለአዲስ ማለዳ ያጋሩ መምህራን ውስጥ የመንግስት ትምህርት ቤት በሆነው በአዲስ ህይወት አጸደ ህፃናት መምህርትና የስነ ልቦና አማካሪ ሜላት ካሳሁን ተማሪዎች ትምህርት በንቃት አንዲቀበሉ ለማድረግ ለተማሪዎች ሰፊ ጊዜ መስጠት ወሳኝ ነጥብ መሆኑን ለአዲስ ማለዳ ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን አንደ ሜላት ገለጻ ትምህርት በፈረቃ መሆኑ ተማሪዎችና መምህራን የሚገናኙበት ጊዜ በቂ ሊሆን አይችልም፣ መምህራን ተማሪዎችን ከማስተማር በዘለለ ከተማሪዎች ጋር መግባባትና መርዳት ሊኖር ይገባል ይላሉ፡፡ሜላት እንደሚሉት ተማሪዎችን በፈረቃ ከማስተማር ይልቅ ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎችን እንዲሁም ትምህርት ቤቶችን በመክፍት መደበኛ ትምህርት መስጠት የተሻለ አማራጭ እነደሆነ ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ አመላክተዋል፡፡

በተለይም የግል ትምህርት ቤቶች ተጨማሪ የተማሪዎችን ቁጥር አሳንሶ ለማስተማር ተጨማሪ ጊዜና የሰው ሀይል አስፈላጊ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ለዚህም የተማሪ ወላጆች ተጨማሪ ክፍያ ሊጠይቁ የሚችሉበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል የሚል ሀሳብ ቢኖርም ትምህርት ሚኒስቴር ምንም አይነት የክፍያ ጭማሪ ትምህርት ቤቶች እንዳይጠይቁ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡ በዚህ ተግባር ውስጥ የተገኙ ትምህርት ቤቶች እስከ መዘጋት የሚደርስ እርምጃ እንደሚወሰድባቸው ሚንስቴር መስሪያ ቤቱ አስጠንቅቋዋል፡፡
መንግስት ኮቪድ 19ኝን ለመከላከል የተቀመጡ ቅድመ ሁኔታዎችን በ3 ሳምንታት ውስጥ ያሟሉ ትምህርት ቤቶች ትምህርት መጀመር አንደለሚችሉ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡ ትምህርት ቤቶች የዓለም የጤና ድርጅትና የጤና ሚኒስቴር ወረርሽኙን ለመከላከል ባስቀመጡት ቅድመ ሁኔታ መሰረት ከመከፈታቸው በፊት በመድሃኒት ማፅዳት፣ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብልና የእጅ ማፅጃ ማሟላት እንዲሁም አካላዊ ርቀትን ማስተግበር ይጠበቅባቸዋል፡፡

ትምህርት ሚኒስቴር ባስቀመጠው መስፈርት መሰረት በአንድ ክፍል ውስጥ ከ20 እስከ 25 ተማሪ ማስተማር የሚችሉ መሆንም ይጠበቅባቸዋል ተብሏል፡፡
መንግሰት ካስቀመጠው ውሳኔ በተጨማሪ በገጠር ወረዳና ቀበሌ ከተሞች የሚገኙ ትምህርት ቤቶች በመጀመሪያው ዙር ጥቅምት 9/2013፣ በሁሉም የዞንና የክልል ከተሞች የሚገኙ ትምህርት ቤቶች በ2ኛ ዙር ጥቅምት 16/2013 እንዲሁም

በአዲስ አበባና አዲስ አበባ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ደግሞ በ3ኛ ዙር ጥቅምት 30/2013 ትምህርት እንዲጀምሩ አቅጣጫ ተሰጥቷል፡፡በዚህ መሰረት ኮቪድ 19ኝን ለመከላከል በ3 ሳምንታት ውስጥ አስፈላጊውን ቅድመ ሁኔታ ያሟሉ ትምህርት ቤቶች በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ትምህርት መጀመር ይችላሉ ተብሏል፡፡

በሌላ በኩል የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና እና ምዝገባ በኦንላይን እንደሚሰጥ ትምህርት ሚኒስቴር ትናነት አርብ አስታውቋል፡፡ የኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስቴር የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሐረጓ ማሞ የ12ኛ እና የ8ኛ ክፍል ፈተና በተያዘለት የጊዜ ገደብ እንዲሰጥ በቅድሚያ ትምህርት ቤቶች ኮቪድ-19 መከላከልን መርህ ባደረገ መልኩ ዝግጅት ሙሉ በሙሉ ማጠናቀቅ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል። ከፈተናው አስቀድሞም የትምህርት ቤቶችን ዝግጁነት የማረጋገጥ ስራ በትምህርት ሚኒስቴር እንደሚሰራም ተገልጿል።

የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና እና ምዝገባ በኦንላይን እንደሚካሄድ እና ተማሪዎች የ45 ቀን የማካካሻ እና የቴክኖሎጂ መለማመጃ ጊዜም እንደሚሰጣቸው ዳይሬክተሯ ተናግረዋል። ትምህርት ቤቶች የሚከፈቱት እና ፈተናዎችም የሚሰጡት ትምህርት ቤቶች አስፈላጊውን ቅድመ ጥንቃቄ ማሟላት ሲችሉ ብቻ መሆኑም ተገልጿል። ትምህርት ሚኒስቴር ትምህርት ቤቶች እንዲከፈቱ ያቅስመጣቸው ቅድመ ሁኔታዎች ሳይሸራረፉ እንዲተገበሩ ለሁሉም ባለድርሻ አካላት ጥሪ አቅርቧል።
ከሦስት ሳምንት ብኋላ ይጀመራል የተባለው ትምህርት ቤት በተለይም በህፃናት ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ ካልተደገረ ህፃናቶች ከወረርሽኝ እራሳቸውን የመጠበቃቸውና ከጓደኞቻቸው ጋር የንክኪ እና እርቀት ሊጠብቁ አይችሉም የሚለው ጉዳይ በወላጆች ላይ ከፍተኛ ስጋት እንደደቀነ ከወዲሁ አየተነገረ ነው፡፡ ወላጆች ለዚህ ማሳያ የሚነሱት ህፃናት ተማሪዎች ከአቻ ጓደኞቻቸው ጋር ሲገናኙ ኮቪድ-19 መኖሩን ዘንግተው ለመጫወት ሲሉ ሊቀራረቡ አንደሚችሉ ስጋታቸውን አስቀምጠዋል፡፡
በወላጆች በኩል ያሚታየውን ይህን አይነት ስጋት ለማስቀረት ደግሞ በተለይ የአጸደ ህፃናት ትምህርት ቤቶች ከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚጠይቁ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የአጸደ ህፃናት ትምህርት ቤቶች የስራ ሃላፊዎች ጠቅሰዋል፡፡ ለዚህም ጊዜውን ለማለፍና የወላጆችን ችግር ለማቋለል ተጨማሪ ሞግዚቶችን እና የድጋፍ ሰራተኞችን መቅጠር አስፈላጊ መሆኑን በማመን ለንግድ የተቋቋሙ ቢሆንም ችግሩን ለማለፍ ብቻ ጫናዎችን ለመቻል መወሰኑን ሀሳቡን ለአዲስ ማለዳ የጋራው አርኣያ ለትውልድ አጸደ ህፃናት የግል ትምህርት ቤት ችግሩን ለማለፍ ያሰበውን አማራጭ አመላክቷል፡፡

ትምህርት ሚኒስቴር በዝርዝር ያስቀመጣቸው የመማር ማስተማር ስራን ለማከናወን የተላለፉ ውሳኔዎች በተለይም በአዲስ አበባ የመንግስትና የግል ትምህርት ቤቶች ውጤታው ምን ያክል አመርቂና ትክክለኛ መሆኑን ተማሪዎች ወደ ትምህርት ተመልሰው የመማር ማስተማር ስራዎች ሲከወኑ የሚመዘን ጉዳይ ነው፡፡ የወረርሽኙ ስርጭትስ ከትምህርት መጀመር ብጓላ ምን አይነት መስመር ይከተል ይሆን የሚለው ጥያቄም ወደፊት የሚመለስ ይሆናል፡፡

ቅጽ 2 ቁጥር 99 መስከረም 16 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here