ከብር ለውጡ ጋር በተያያዘ በኢትዮ- ጅቡቲ ድንበር ላይ  የዋጋ ንረት አጋጠመ፤1ነጥብ 5 ሊትር የታሸገ ውሃ እስከ 40 ብር እየተሸጠ ነው

0
1542

በኢትዮጵያ የብር ኖት መቀየሩ ይፋ ከተደረገበት ጊዜ አንስቶ  በኢትዮጵያ እና ጅቡቲ ድንበር ላይ በሚደረገው ግብይት ላይ  የዋጋ ጭማሪ መታየቱን ምንጮች ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።

ከኢትዮጵያ ወደ ጅቡቲ የሚመላለሱ ምንጮቻችን እንደገለጹት ከሆነም የዋጋ ጭማሪው ከብር ለውጡ ጋር ተያይዞ  መታየቱንም  ገልጸዋል።

ከዚህ ቀደም አንድ ነጥብ አምስት ሊትር ውሃ እስከ 20 ብር ይሸጥ የነበረ ሲሆን በአሁን ወቅት ደግሞ በእጥፍ ጭማሪ በማድረግ  እስከ 40 ብር እየተሸጠ እንደሆነ የአዲስ ማለዳ ምንጮች ጠቁመዋል።

ውሃ ብቻ ሳይሆን የለስላሳ መጠጦችም ቢሆን የመቶ በመቶ  ጭማሪ እንደተደረገባቸው ምንጮች  ጨምረው ገልፀዋል።

ባለ አምስት ሊትር ፈሳሽ ዘይትም ቢሆን ከዚህ ቀደም እስከ 280 ሲሸጡ የነበረ ሲሆን በአሁን ወቅት ደግሞ በ380 ብር ከመሸጣቸው ጋር ተያይዞም  የምግብ ዋጋዎችም መናራቸውን ለማወቅ ተችሏል።

ለስራ ከኢትዮጵያ ወደ ጅብቲ የሚያቀኑ ሹፌሮችም ወደ ጅቡቲ ሲገቡ ለኮቴ ተብለው ከዚህ ቀደም ከ400 ብር  እስከ 600 ብር እንደሚቀበሏቸው የገለጹ  ሲሆን በአሁን ወቅት ደግሞ እስከ 1200 ብር እንደሚቀበሏቸውም ጠቁመዋል።

ከላይ የተጠቀሱት የዋጋ ጭማሪዎች ከሰሞኑን ቅናሽ ተደርጎባቸው የተሻሻሉ መሆናቸውን ምንጮቻቸን ገልጸዋል።

በዚሁ ሳምንት ለሥራ ጉዳይ ጅቡቲ ደርሰው የተመለሱት ምንጫችን እንደሚሉት ከሆነ   ‹‹በኢትዮጵያ የብር ኖት ላይ ለውጥ ከተደረገ በኋላ ነጋዴዎቹ የዋጋ ጭማሪ ከማድረጋቸው  በተጨማሪም በአሮጌው  ብር መገበያየት የለብንም፤ ከዚህ በኋላም በአዲሶቹ  የብር ኖቶች  ብቻ ነው የምንገበያየው እስከማለት ደርሰዋል›› ብለዋል።

ምንጮቻችን እንደሚሉት ከሆነም  ይህም ሆነ ተብሎ የሚሠራ ነገር ነው ፤በተለይ በጅቡቲ የሚገኙ አንዳንድ ነጋዴዎች  ከዚህ በፊት የነበረውን   የኢትዮጵያን ብር በማከማቸታቸው ምክንያት አሁን ላይ  ብሩን እንዴት ለመቀየር ግራ ስለገባቸው አንዱ መንገድ ይህ ይሆናል ብለው እንዳደረጉት እንገምታለን ነው ያሉት።

አዲስ ማለዳም የዛሬ ሳምንት ባወጣችው በ99 እትሟ ላይ የብር ለውጡን ተከትሎ በአንዳንድ የአማራ እና ትግራይ አዋሳኝ አካባቢዎች በሕገወጥ መንገድ ገንዘብን በአይነት የመቀየር እንቅስቃሴዎች እየተስዋሉ መሆኑ የአማራ ክልል መንግሥት ኮምዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ግዛቸው ሙሉነህ ማስታወቃቸውንም ዘግባ ነበር።

በዚህም  ‹‹አንዳንድ ግለሰቦች ነባሩን ገንዘብ በርከት አድርገው ከሚገባው በላይ ይዘው ስለነበረ አዳዲሶቹ የብር ኖቶች ይፋ ሲደረጉ በነባሩ ብር ንብረቶችን በውድ ዋጋ የመግዛት እንቅስቃሴዎችን ሲያደርጉ ተስተውለዋል›› ያሉት ኃላፊው፣ አንድ በግ እስከ 10 ሺሕ እና 15 ሺሕ ብር ድረስ እገዛለው ብሎ ለማጭበርበር መሞከር እና ይህን መሰል እንቅስቃሴዎች በተለያዩ አካባቢዎች መስተዋላቸውን ለአዲስ ማለዳ መግለጻቸውም አይዘነጋም።

ኃላፊው እንዳስታወቁት ነባሩን ገንዘብን በአይነት የመለወጥ እንቅስቃሴዎቹ እየተስተዋሉ ያሉት በወሰን አካባቢዎች ሲሆን፣ ክልሉ ከትግራይ ጋር በሚዋሰንባቸው በሰሜን ወሎ፣ ራያና ቆቦ አካባቢዎች እና በሌሎች የክልሉ ጫፍ አዋሳኝ አካባቢዎች መሆኑንም አንስተዋል።

እንደ ክልል የአዳዲስ ብር ኖቶቹ ስርጭት ዘግየት ብሎ መጀመሩን የሚገልጹት ግዛቸው፣ ካሳለፍነው ሰኞ መስከረም 10/2013 ጀምሮ እንደ ክልል ከሁሉም የከተማ ባንኮች ጀምሮ እስከ ወረዳ ድረስ ስርጭቱ እንዲከናወን ይፋዊ እንቅስቃሴ ተጀምሯልም ብለዋል።

ነዋሪዎች በተሳሳቱ የብር ኖቶች እንዳይጭበረበሩ የማሳወቅ እንቅስቃሴ የክልሉ ፕሬዝዳንት ተመስገን ጥሩነህ በተገኙበት ለማድረግ ተሞክሯል የሚሉት ኃላፊው፣ የብር ኖቶቹን በተመሳሳይ መልኩ ሠርቶ በማምጣት ደረጃ እስካሁን የተገለፀ ነገር አለመኖሩን ጠቅሰዋል።

በአገር ዐቀፍ ደረጃ ከመስከረም 5/2013  ጀምሮ የአዳዲስ የብር ኖቶችን ይፋ መደረጉም ይታወሳል፡፡

 

 

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here