በራያ ቆቦ ወረዳ የተከሰተውን የበርሃ አንበጣ ለመከላከል በቂ አልባሳትና ኬሚካል እየቀረበ አይደለም

0
775

በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን በራያ ቆቦ ወረዳ ከፍተኛ መንጋ ያለው የበርሃ አንበጣ በዘጠን ቀበሌዎች ተከስቶ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ቢሆንም በቂ የኬሚካል አቅርቦት፣ የኬሚካል ርጭት መከላከያ አልባሳት እና ለርጭት የሚገለግሉ የሄሊኮፕተር አቅርቦት ማግኘት እየተቻለ አለመሆኑን የራያ ቆቦ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ፡፡

 ከአፋር ክልል ከአማራ ክልል አዋሳኝ አቅራቢያ መነሻውን አድርጎ በራያ ቆቦ ወረዳ ከተከሰተ ከ15 ቀን በላይ ያስቆጠረው የበርሃ አንበጣ አሁን ላይ የዕድገት ደረጃውን እየጨረሰ በአየር ላይ እየበረረ በደረሱ ስብል እና  አዝዕርቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ቢሆንም መንጋው የተከሰተበት መጠንና የተሠራው የመከላከል ሥራ በእጅጉ አናሳ መሆኑን የራያ ቆቦ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ ተስፋየ ታረቀኝ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል፡፡

ምክትል ኃላፊው ለአዲስ ማለዳ እንደሚገልጹት የበርሃ አንበጣ መንጋው ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ ሌት ከቀን በመከላከል ሥራ ላይ ተሰማርቶ የነበረው የዘጠኝ ቀበሌ አርሶ አደር አሁን ላይ የድካምና የመሰልቸት ስሜት ውሰጥ መገባቱን ጠቁመዋል፡፡ በመሆኑም ሌሎች መንጋው ያልተከሰተባቸው አካባቢዎች የመከላከል ሥራውን አንዲያግዙ ጥሪ ማቅረባቸውን ጠቁመዋል፡፡

እስከ መሰከረም 20/2013 ድረስ የበርሃ አንበጣው የእድገት ጊዜውን ሙሉ በሙሉ ባለመጨረሱ አንቅስቃሴው ከመሬት በላይ ብዙ የራቀ ባለመሆኑ በሰው ሀይል የመከላከል ሥራ ሲሰራ አንደነበር የጠቆሙት ተስፋየ አሁን ላይ ግን እድገቱ በአየር ከፍታ ላይ መብረር የሚችልበት ደረጃ ላይ በመድረሱ በሰው ኃይል መደረስ የማይችሉ ዛፎች ላይ እየሰፈረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በቦታው ላይ ከተከሰተው የበርሃ አንበጣ መንጋ አደገኝነት አንጻር ከፍተኛ ትብብርና ርብርብ ተደርጎ ባለበት መከላከል ካልተቻለ አንደ አገር ከፍተኛ ጉዳት ሊስከትልና ወደ ሌሎች አካባቢዎች የሚዛመትበት ሁኔታ ሰፊ እንደሚሆን ምክትል ኃላፊው አሳስበዋል፡፡

መንጋውን ባለበት ለመከላከል ከሚያስልጉት የኬሚካልና አልባሳት በተጨማሪ የመከላከል ሥራ ለመስራት የበጀት ድጋፍ አንደሚስፈልግ ተስፋየ ጠቁመዋል፡፡ በአካባቢው መንጋውን ለመከላከል እዚያው እየዋሉና እያደሩ ተሰማርተው የሚገኙ ባለሙያዎች ቢያንስ የምግብ  ወጭ እንኳን መሸፈን የሚቻልበት ሁኔታ አስፈላጊ መሆኑን ምክትል ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡

የበርሃ አንበጣ መንጋው አቅሙ እየጎለበተ መምጣቱን ተከትሎ የወረዳው ግብርና ጽሕፈት ቤት ለፌደራል ግብርና ቢሮ የሂልኮፕተር ድጋፍ ጠይቆ መስከረም 20/2013 ምሽት ላይ እልካለሁ ቢልም አለመላኩን ተስፋየ ተናግረዋል፡፡ ያልተላከበትን ምክንያት ደውለው ሲጠይቁ በአካባቢው ያለው ጭጋጋማ የአየር ጸባይ ምቹ ባለመሆኑ እንደቀረ እንደተነገራቸውና መስከረም 21/2013 ከጥዋቱ 1፡30 ይደርሳል የተባሉ ቢሆንም በተባለው ስዓት ሂልኮፕተር አለመላኩን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ተስፋሁን መንግስቴ በበኩላቸው በቂ የኬሚካል አቅርቦት መኖሩን እና የአልባሳት አቅርቦት እጥረት ቢኖርም 400 የባለሙያዎች አልባሳት አቅርበናል ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡ የሄሊኮብተር አለመቅረብን በተመለከተ በነበረው የአየር ሁኔታ ደመስከረም 20 ደርሶ መመለሱንና መስከረም 21 በቦታው ደርሶ አሰሳ እያደረገ መሆኑን ተስፋሁን ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን የፌደራል መንግስት ለክልሉ ያቀረበው ሄሊኮፕተር አንድ ብቻ በመሆኑ እጠረቱ መኖሩን የገለጹት ተስፋሁን ለፌደራል መንግስት ተጨማሪ ሄሊኮፕተር ለክልሉ እንዲቀርብ መጠየቃቸውን ጠቁመዋል፡፡

የበርሃ አንበጣው አስካሁን የተከሰተባቸው ቀበሌዎች በራያ ቆቦ ወረዳ ሥር ከሚገኙ 42  ቀበሌዎች በዘጠኝ ቀበሌዎች ይሁን አንጅ በአየር ከፍታ ላይ መብረር የሚችለው መንጋ ወደ ሌሎች ቀበሌዎች መዛመት መጀመሩም ተጠቁሟል፡፡ እስካሁን መንጋው ከተከሰተባቸው ቀበሌዎች ውስጥ 09፣ 05፣ 10፣ 35፣ 44፣ 23፣ 24 እና 22 ይገኙበታል፡፡

በዘጠኙ ቀበሌዎች የበርሃ አንበጣው በደረሱ ሰብሎች ላይ ያደረሰው ጉዳት እስከ መስከረም 20/2013 ድረስ ብቻ 632 ሄክታር ሰብል ማወደሙን ተስፋየ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል፡፡ የደረሰው ጉዳት ጤፍ 137 ሄክታር፣ ማሽላ 469 ሄክታር፣ ሰሊጥ 10 ሄክታር አንዱሁም በበቆሎ ሰብል ላይ 15 ኬክታር ሰብል ማውደሙን ምክትል ኃላፊው ተናግረዋል፡፡ የደረሰው ጉዳት በጤፍ እና በሰሊጥ ሰብል ላይ መቶ በመቶ ሲሆን በበቆሎ ስብል ላይ 80 በመቶ እና  በማሽላ ሰብል ላይ 75 በመቶ መሆኑን ተስፋየ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡

 

 

 

 

 

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here