የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተማሪዎች ለይ ተጨማሪ ክፍያ ጠየቀ፤  በዚህ ዓመት የተጨመረ ምንም ዓይነት ክፍያ የለም – የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ

0
390

የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በማታ መርሀ -ግብር የህዝብ ግንኙነትና ስትራቴጂክ ኮሙኒኬሽን ዲፓርትመነት የኹለተኛ ድግሪ ተማሪዎች  ዩኒቨርስቲው  ለመመረቂያ ጽሁፍ የሚውል የመቶ በመቶ  ጭማሪ ክፍያ መጠየቁን ለአዲስ ማለዳ   ገለጹ።

ባለፈው 2012 ዓመት ዩኒቨርስቲው ይቀበል የነበረው 6120 ብር እንደነበረ እና በዚህ ዓመት ግን 13 ሺህ 620 ብር እንዲከፈል መወሰኑ አግባብ አለመሆኑን ቅሬታ አቅራቢዎቹ ገልጸዋል ።

ቅሬታ አቅራቢዎቹ አክለው በአሁን ወቅት ‹‹የግል ትምህርት ቤቶች ቅናሽ ያደረጉ እንዳሉም እናውቃለን አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ግን አሳማኝ ባልሆነ ምክንያት የዋጋ ጭማሪ ማድረጉን ተገቢ አይደለም ሲሉ አስታውቀዋል።

በዚህም ምክንያት የተደረገው ጭማሪ ከሞራልም ይሁን ከህግ አንጻር ተገቢ አይደለም በማለት ለዩኒቨርሰቲው ያሳወቅን ቢሆንም እስካሁን ድረስ ምንም ዓይነት መፍትሔ ማግኘት አልቻልንም ሲሉ ገልጸዋል።

ችግራችንን ለማሳወቅም የአዲስ አበባ ዪኒቨርሲቲ ጋዜጠንኝት እና ኮሙዩኒኬሽን ዲፓርትመንት፣ለሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ብናስገባም እስካሁን ምንም ዓይት ምላሽ አላገኘንም ብለዋል፡፡

ምዝገባው በፈረንጆቹ መስከረም 23 እና 24 እንዲከናወን ዩኒቨርስቲው ቢያሳውቀንም ማንም ተማሪ ሊመዘገብ ፈቃደኛ አለመሆኑን ተመራቂ ተማሪዎቹ አስታውቀዋል፡፡

አብዛኛው ተማሪ ሲጠብቅ የነበረው ከዚህ ቀደም ሲከፈል በነበው ዋጋ  እንጂ በፍጹም ከመቶ በመቶ በላይ ጭማሪ አለመሆኑን እና ይህም ችግር በተለይም በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ጋዜጠኝነት እና ኮሙዩኒኬሽን ፋኩሊቲ ላይ እንደሚበረታም ቅሬታ አቅራቢዎቹ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ  የኮቪድ- 19 ከተከሰተ በኋላ  ከመምህራኖች ጋር የምንገናኘው በኦንላይን ብቻ ነበር የሚሉት ምንጮቻችን ውሳኔው ከዚህ ቀደም የተላለፈ ነው ቢባል  እንኳን አሳማኝ እንዳልሆነ እንደ ማንኛውም የሕብረተሰብ ክፍል ገቢ የቀነሰብን በመሆኑ ዩንቨርሲቲው በድንገት እንዲህ ዓይነት ውሳኔ ማሳለፉ ‹‹መመረቂያ ጊዜያቸው ስለደረሰ ይከፍላሉ ምንም አያመጡም›› የሚል አስተሳሰብ በዩኒቨርስቲው በኩል እንዳለ የሚያመላክት ነው ብለዋል፡፡

ካለአግባብ የተጨመረብን ክፍያ እንዲስተካከለንም ይመለከታቸዋል የተባሉትን ሰዎች ለማናገር ብንሞክርም በኮቪድ ምክንያት ወደ ውስጥ ገብታችሁ ማናገር አትችሉም ተብለናልም ሲሉም አክለዋል።

በአጠቃላይ ቁጥራቸው 43 የሚሆኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የህዝብ ግንኙነትና ስትራቴጂክ ኮሙኒኬሽን ተምህርት ክፍል የኹለተኛ ድግሪ ተመራቂ ተማሪዎች ክፍያው ይስተካከለን በማለት የተማሪዎች ስምና ፊርማ ያለበት ጥያቄያቸውን  ለዩኒቨረስቲው፣ለሳይንስና ክፍተኛ ትምርት ተቋማት ሚኒስቴር ማስገባታቸውን የአዲስ ማለዳ ምንጮች ጠቁመዋለ።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በበኩሉ ስለጉዳዩ የሚመለከተው  ነገር እንደሌለው አስታውቋል።

በሳይንስና ከፍተኛ  ትምህርት ሚኒስቴር የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች  ዳይሬክተር የሆኑት  ደቻሳ ጉርሙ ‹‹እኛ ዩኒቨርስቲዎች ለሚመድቡት ዋጋ ተመን የማውጣት ኃላፊነት የለብንም ነገሩም እኛን አይመከለትም ብለዋል።

ዩኒቨርስቲዎች በግል በሚያስተምሩበት ጊዜ ለክፍያ የሚያስቀምጡት የራሳቸው  ዋጋ ይኖራቸዋል እንጂ  በእኛ በኩል ይህን ማስከፈል አለባችሁ  ብለን ያስቀመጥነው መሥፈርት የለም ብለዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲም ተማሪዎቹ ላቀረቡት ቅሬታ ምላሽ የሰጠ ሲሆን የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ጣሰው ወልደሃና (ፕ/ር) በዚህ ዓመት ያደረግነው ምንም ዓይነት ጭማሪ የለም በማለት አጠር ያለ ምላሻቸውን ለአዲስ ማለዳ ሰጥተዋል።

 

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here