ኤጀንሲው በ1.6 ቢሊዮን ብር ሕንጻ ሊገነባ ነው

0
676

የፌደራል ሰነዶች ምዝገባና ማረጋጋጫ ኤጀንሲ በ1.6 ቢሊዮን ብር ወጪ ለዋና መስሪያ ቤትነት የሚያገለግል ባለ 26 ወለል ህንፃ ሊያስገነባ መሆኑ ተገለፀ።

የኤጀንሲውን ህንፃ ለመገንባትም በፌዴራል መንግስት ህንፃዎች ግንባታ ጽ/ቤት እና በኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን መካከል  ሀሙስ መስከረም 21 ቀን 2013 የኮንትራት ስምምነት ፊርማ ተከናውኗል።

በስምምነቱም መሠረት የሚገነባውን ባለ 26 ወለል (4B+G +21) ህንፃ ከ1.6 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ዋጋ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን በአራት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ሰርቶ እንዲያስረክብ መስማማቱን የፌዴራል ሰነዶች ምዝገባና ማረጋገጫ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙሉቀን አማረ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

ግንባታው በአዲስ አበባ ከተማ ሜክሲኮ አደባባይ በሚባለው አካባቢ 2 ሺህ 758 ካሬ ሜትር ስፋት ባለው ቦታ ላይ እንደሚከናወንም ታውቋል፡፡
ኤጀንሲው በአዲስ አበባ 14 ቅርንጫፍ መስሪያ ቤቶች እንዳሉት የገለፁት ሙሉቀን ዋና መስሪያ ቤቱን ጨምሮ 14ቱም ቅርንጫፍ መስሪያ ቤቶች አገልግሎት የሚሰጡባቸው ህንፃዎች የኪራይ እንደሆኑ ገልፀው ለሁሉም የቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት መስሪያ ቤቶች በአጠቃላይ በየአመቱ ከአርባ ሚሊዮን ብር በላይ የኪራይ ወጪ እየከፈሉ እንደሆነ ኃላፊው ገልፀዋል።

የኤጀንሲው የአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓት በጣም እያደገ መጥቷል የሚሉት ዋና ዳይሬክተሩ ከዚህ አንፃር የሚሰጠውን አገልግሎት በተቀላጠፈ መንገድ መስጠት እንዲቻል አመቺ የሆነ ህንፃ አስፈላጊ መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት ለሁሉም የቅርንጫፍ ፅ/ቤቶች ህንፃ ማስገንባት ባይቻል እንኳን ኤጀንሲው በዋና መስሪያ ቤትነት የሚገለገልበት የራሱ የሆነ ህንፃ እንዲኖረው በመታሰቡ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቦታ እንዲሰጠው በመጠየቅ ሲጠባበቅ መቆየቱን ገልፀዋል።

በዚህም መሰረት ኤጀንሲው ከሚሰጠው አገልግሎት አንፃር የሚያስፈልገው ቦታ መሃል ከተማና ለተገልጋዩ ምቹ መሆን ስለሚገባው ቦታ ሲፈለግ ቆይቶ 2009 መጨረሻ አካባቢ ይኸው ሜክሲኮ አካባቢ የሚገኘው ቦታ ለግንባታ እንደተሰጠው የሚገልፁት ሙሉቀን  ከፍቃድ እና ከጨረታ ሂደት ጋር የተያያዙ ስራዎች እየተሰሩ እስካሁን መቆየቱን ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።

በሚገነባው አዲስ ህንፃ ላይ በዋናው መስሪያ ቤት በአንድ ህንጻ ስር ተሰባስበው የሌሉና ከቦታ ጥበት አንፃር በተለያዩ ቦታዎች ላይ የተበታተኑ አገልግሎቶችን በአንድ ማእከል እንዲሰጡ እንደሚደረግም ገልፀዋል።

ኤጀንሲው በአሁኑ ወቅት ቴክኖሎጂን መሰረት በማድረግ የሚሰራ ተቋም እንደመሆኑ ትልቅ የቴክኖሎጂ ማስፋፊያ ማእከል እንደሚኖረውም የጠቆሙት ዳይሬክተሩ በተጨማሪም የአንድ ማእከል አገልግሎት ከመስጠት አንፃር ከኤጀንሲው ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ሌሎች መሰል ተቋማትን ጭምር በአንድ አምጥቶ ተገልጋዮች የተሳለጠና ምቹ አገልግሎት እንዲያገኙ ለማድረግ መታሰቡንም አስታውቀዋል።

በሌላ በኩል ኤጀንሲው ሁሉም አገልግሎት መስጫ ቅርንጫፍ መስሪያ ቤቶቹን ጨምሮ በአማካኝ በቀን 6100 ተገልጋይ የሚያስተናግድ መሆኑን የሚገልፁት ሙሉቀን የእነዚህን ተገልጋዮች ሰነድ በዘመናዊ መልኩ አደራጅቶ ለመያዝ እና ለማስተዳደር አሁን ሊገነባ የታሰበው ህንፃ ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረውም ገልፀዋል።

የህንፃውም ግንባታ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር እና በስሩ የሚሰራው የፌደራል ተቋማት ህንፃዎች ግንባታ ጽ/ቤት በሚያደርጉት ቁጥጥር እና ክትትል እንደሚሰራ የሚገልፁት ሙሉቀን በዚህ መሰረት የግንባታው ዲዛይን ካለቀ በኋላ ጽ/ቤቱ ለግንባታው ሙሉ አለማቀፋዊ ጨረታ ማውጣቱን በማስታወስ ጨረታውን የተወዳደሩት ሁሉም የቻይና ኩባንያዎች እንደነበሩና አሸናፊው ኩባንያ 2.5 ቢሊየን ብር የሚጠጋ ዋጋ አቅርቦ እንደነበር ገልፀዋል።

ይህንን የዋጋ መጋነን በመመልከት ሌሎች አማራጮችንም ማየት አስፈላጊ ነው ተብሎ በመታመኑ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር እንዲሁም የፌደራል ተቋማት ህንፃዎች ግንባታ ጽ/ቤት በአንድ ላይ ሆነው የመንግስት የግዢ ስርአቶችን በመከተል ህንፃው አገር በቀል በሆነ የኮንስትራክሽን ተቋም አስገንብቶ ወጪን ለመቀነስ በተጨማሪም በራስ ተቋም  ትልልቅ ፕሮጀክቶችን መስራት እንደሚቻልም ጭምር እንደማሳም ሊሆን ይችላል በማለት ለኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን  ግንባታው እንዲከናወን መወሰኑን ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

የፌደራል ሰነዶች ምዝገባና ማረጋጋጫ ኤጀንሲ የፌደራል ተቋም እንደመሆኑ አጠቃላይ የግንባታውን ፕሮጀክት በጀት የሚያዘው በገንዘብ ሚኒስቴር መሆኑንም ሙሉቀን ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

ኤጀንሲው በ2012 በጀት አመት 530 ሚሊዮን ብር መሰብሰብ መቻሉን አንስተው በ2011 ከሰበሰበው የ380 ሚሊዮን ብር ገቢ ጋር ሲነፃፀር በየአመቱ የኤጀንሲው በገቢው እያደገ መሄዱን እንደሚያሳይ ገልፀዋል። በያዝነው የ2013 በጀት አመት 600 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ኤጀንሲው እቅድ መያዙንም ዋና ዳይሪክተሩ ጨምረው ገልፀዋል።

 

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here