‹‹ከራስ በላይ ለሕዝብ እና ለአገር››

0
1005

ባሳለፍነው ሳምንት መስከረም 19/2013  ማለዳ ላይ ከአንድ ትውልድ ወዲህ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ነበር መስቀል አደባባይ አሸብርቆ የዋለው። ምናልባትም አፍ አውጥቶ ቢናገር ስፍራው ራሱ አብዮት አደባባይ ነኝ የሚል ምላሽም የሚሰጥ ይመስላል በቀድሞው ስያሜው ለመጠራት እየዳዳው።

በዓይነቱ ልዩ ሆነው ዝግጅት ደግሞ በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን አዘጋጅነት የፌደራል ፖሊስ ሰራዊት የተለያዩ ትርዒቶችን ማሳየታቸው ደግሞ በእርግጥም ከብቃታቸው እና ከአስደማሚ ልምምድ ብቃታቸው ባለፈ ምንድነው ሊተላለፍ የፈለገው መልዕክት ከመንግስት ወገን የሚሉ ጥያቄዎችን በስፋት ሲያስነሳ እና ይህንንም ተከትሎ በመገናኛ ብዙኃንም ሲተላለፉ ነበሩ ጉዳዮች ተሰምተዋል። ይሁን እንጂ ከወታደራዊው መንግስት ከስልጣን መወገድ ወዲህ እንዲህ የተደራጀ እና ሰፊ ሽፋን የተሰጠው የአገሪቱ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ የተገኙበት የፖሊስ የሰልፍ እና ልዩ ልዩ እንቅስቃሴ ትርኢት ሲካሔድ ይህ የመጀመሪያው ነው።

‹‹ከራስ በላይ ለሕዝብ እና ለአገር›› በሚል መሪ ቃል የተካሔደው ይኸው ትርዒት የፌደራል ፖሊስ በተለያዩ ምድቦቹ እና የኃይል ክፍሎች ያለውን ኃላፊነት እና ስራ በተግባር ያሳየበት ትዕይንት ነበር። ብሎኬትን በጭንቅላት ከመስበር እስከ ከ12ኛ ፎቅ እስከ መዝለል፤ ከኮማንዶ ትርዒት እሳት ላይ እስከመገለባበጥ የመሳሰሉት ጉዳዮች የታዩበት ደማቅ ክብረ በኣልም ነበር።

ይሁን እንጂ ለዛሬ ጽሑፋችን መነሻ ያደረግነው በርካታ መልኮችን የያዘው ይኸው የፖሊስ ወታደራዊ ትዕይነት እንዴት በአሁኑ ወቅት ያውም ምርጫ ደርሷል በሚባልበት ወቅት መደረጉ ጉዳዩን ከድጡ ወደ ማጡ የሚያስገባ ጉዳይ አይሆንም ወይ የሚሉ የፖለቲካ ምሁራኖች እዚህም እዛም እየተከሰቱ ነው። በተለይም ደግሞ የፖለቲካ ምህዳሩን አስፍተናል በሚል ሰፊ ስራ እና የፖሮፖጋንዳ ጭዋታዎችን ሲያቀነቅን ለነበረው የለውጡ ኃይል በዚህ ወቅት ይህን ጉዳይ ማድረጉ እጅግ የፖለቲካ ኪሳራ የሚያደርስበት እና በዓለም አቀፍ ደረጃ የፖለቲካ ኪሳራ የሚያደርስበት ጉዳይ ነው የሚሉ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ምሑራኖች ለአዲስ ማለዳ ይናገራሉ።

በሌላ በኩል ደግሞ የመንግስትን አካሔድ በመደገፍ አስተያየት የሚሰጡ እና ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር እንደሚሉት በእርግጥ እንዲህ አይነት ነገር በቅርብ አመታት ተደርገው አለመታወቃቸው ግርታን የሚፈጥር ጉዳይ ቢሆንም ቅሉ የተደረገው ግን ፖሊስ ለሕዝብ ዘብ እንደመሚቆም እና የትኛውንም አገር እና ሕዝብ ጠላትን ለመመከት እንዲሁም አጥፊዎችን ላለመታገስ አቋም የሚግልጽበት እንጂ ሌሎች እንደሚሉት አይነት አንደምታ የለውም ሲሉ ይናገራሉ። በትርዒቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት ኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድም ከመላው ኢትዮጵያ ሕዝብ የተወጣጣው እና ስብጥሩ አገርን ለመጠበቅ ጠንካራ ዘብ የሚያደርገው ይኸው ፖሊስ ስብስብ የተጀመረውን ለውጥ ከዳር ለማድረስ አገርን እና ሕዝብን በመጠበቅ ዜጎች ነግደው ሚያተርፉበት፣ ስለነገ የሚያልሙባትን አገር እንዲፈጥሩ እንደሚያደርጉ አውስተዋል።

ከየትኛው የፖለቲካ ፓርቲ ገለልተኛ እንደሆነ እና አገርን እና ሕዝብ ለመጠበቅ ብቻ የቆመ ኃይል መሆኑንም ጠቅላይ ሚንስትሩ ተናግረው፤ ዝናብ እና ቁር ፣ ሐሩር ሳይበግራቸው አገርን ለመጠበቅ ለሚተጉ የፖሊስ አባላትም የፌደራል መንግስት ምስጋና እንደሚያቀርብም ተናግረዋል። የትርዒቱን አላማ በተመለከተ ለአዲስ ማለዳ አስተያየታቸውን የሰጡ ግለሰቦች እንደሚናገሩት ፌደራል መንግስት በክልሎች ላይ እየተካሔደ ያለውን የልዩ ኃይል ፖሊስ ስልጠና እና በብዛትም በጥራትም ከመጨመር ጋር ተያይዞ ስጋት ቢጤ ሳይገባው እንዳልቀረ ይናገራሉ። ከዚህም ጋር ተያይዞ ከሰልፉ አንድ ቀን አስቀድሞ በመስከረም 18/2012 በሸራተን አዲስ በተካሔደው ውይይት ላይ የኢፌዲሪ የሰላም ሚኒስትር ሙፈሪሐት ካሚል በአጽንኦት የክልል መንግስታት ውስጥ የሚገኙ ልዩ ኃይል አባላት ከፌደራል ፖሊስ ጋር በትጥቅ እና በሌሎች ተያያዥ ትጥቆች ያነሰ እንደሚሆን እና ይህም የማያከራክር ጉዳይ እንደሆነ መናገራቸው ይታወሳል።

በአጭር ጊዜ ልዩነት ውስጥ ከፍተኛ ሆነ ወታደራዊ ትርዒት ማካሔዱ ግርምትን የሚያጭር እና መንግስት ምን አይነት መልዕክት ወደ ሕዝብ ሊያስተላልፍ እንደፈለገ ማወቅ እንዳልተቻለም አስተያየት ሰጪዎች ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል። ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የሰላም እና ደኅንነት ባለሙያዎች ለአዲስ ማለዳ ሲናገሩ እንደገለጹት ‹‹ሰላምን ለማምጣት እና ለማስከበር በሚል በመንግስት በኩል እየተወሰደ ያለውን እርምጃ ለመገምገም ወይም ለማድነቅ ያለንበት ሁኔታ የሚፈቅድ አይደለም። በበርካታ አካባቢዎች ያለውን መፈናቀል እና ግድያ እየተመለከትን ባለንበት ሁኔታ አሁን ላይ የፖሊስ ጠንካራ አቋም ለማሳየት ትርኢት ከማድረግ ይልቅ በተግባር የተወሰዱ እርምጃዎች እየተገመገሙ ሕዝብም ቢያያቸው መልካም ይን ነበር ›› ሲሉ ይናገራሉ። አያይዘውም ይህን አይነት ድንገተኛ የወታደራዊ ትርዒት ማካሔድም በሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ መደናገጥን እንደሚፈጥርም አልሸሸጉም።

ዓለም አቀፋዊ ትርጉሙ የወታደራዊ ትርኢት ጽንሰ ሀሳብ እንደሚተነተነው ሴቶች እና ወንዶች የወታደራዊ አባላትን በአንድ ደምብ ልብስ በማልበስ እና በሕዝብ ፊት በማሰለፍ ከሕዝብ ድጋፍን እና ከበሬታን በመልካም ጎን የሚሰጥንም አመለካከት ለመግኘት ያለመ ሀሳብ እንዳለው ባለሙያዎች ይተነትናሉ። ሚሊታሪ ቤኔፊተሰ ኢንፎርሜሽን ተሰነው ድረ ገጽ እንደሚያመለክተው በቀደሙት ጊዜያት በአገረ አሜሪካ እንዲህ አይነት ወታደራዊ ትርኢቶች ይደረጉ እንደነበር እና ይህም የተለመደ ጉዳይ እንደሆነም ያትታል። ይሁን እንጂ በአገራችን ኢትዮጵያ ይህን አይነት ውታደራዊ ትርኢት ስንመለከት ለአብዛኞቻችን በተለይም ደግሞ ወጣት የዕድሜ ክልል ውስጥ ላለው አዲስ እና እንግዳ ነገር እንደሚሆንበት አይጠረጠርም። በእርግጥ በወታደራዊ ትርኢት ወቅት በኢትዮጵያ ቀደም ባሉ ጊዜያት ከሚታየው የወታደራዊው ሰልፍ ባሻገር ለሕዝብ እና ለአገር ሚታየው ከቀላል ሩሲያ ስሪት ክላሽንኮቭ መሳሪያ እስከ ከባባድ መሳሪያዎች ድረስም ለዕይታ የሚቀርቡበት ሁኔታም ነበር።

በካፒታሊስቶች ምድር አሜሪካ ይህን አይነት ሰልፍ እና ትርኢት በማካሔድ ተቀናቃኝ እንዳልነበራት እና በአሁኑ ወቅት በሰሜን ኮሪያ እና ሌሎች ጥቂት አገራት ላይ የሚታየውን እና አምባገነኖች መለያ ነው እስከ መባል የደረሰውን የወታደራዊ ሰልፍ እና ትርኢት በሚገባ ይካሔድባት ነበረ ግንባር ቀደም አገርም እንደሆነች ይነገራል። አንድን ክብረ በዓል መሰረት አድርጎ እንደሚካሄድ ታሪክ ድርሳናት እንዲሁም የወታደራዊ ትርኢትን በሚገባ የሚተነትኑ ዓለም አቀፋዊ ሰዎች ቢናገሩም በኢትዮጵያ በተለይም ደግሞ በመስከረም 19/2013 የተካሔደው ይኸው በፌደራል ፖሊስ በኩል የተካሔደው ይኸው ሰልፍ ግን ምንን መሰረት ያደረገ እንደነበር አለመታወቁም በርካታ ሰዎች ዘንድ ቅሬታን ሲያቀርቡ ነበር። አዲስ ማለዳ ከትርኢቱ አንድ ቀን አስቀድማ ባደረገችው ምልከታ ለኹነቱ የሚደረጉ ጥበቃዎችን እና ጥንቃቄዎችን በሚገባ ተመልክታለች በዚህም እጅግ አድናቆትን የሚስቸር ጉዳይ እንደሆነ ለማየት ተችሏል። ይሁን እንጂ በአንጻሩ የድንገተኛ ሕመምተኞች ማመላለሻ አሙቡላንሶች ግን እንዳያልፉ ሲከለከሉ እና ወደ መጡበት አቅጣጫ ሲመለሱም ለመታዘብ ችላለች። ይህ ደግሞ የሰልፉ አላማ እና መሪ ቃል ‹‹ከራስ በላይ ለሕዝብ እና ለአገር›› በሚል የተሰናዳውን ዝግጅት ጋር በጠና የታመመን እና ታማሚውን ይዞ ሚከንፈውን አምቡላንስ ማስመለስ ጋር የተደረገውን ውሳኔ እንዴት ማስታረቅ እንደሚቻል ምላሽ የሚያሻው ጉዳይ ነው።

በሌላ በኩል ደግሞ አዲስ ማለዳ በድንገት ጥያቄ ካቀረበችላቸው ግለሰቦች መሰብሰብ እንደቻለችው አስተያየት ሰጪዎች ረቡዕ መስከረም 20/2013 በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ የተካሔደው የፖሊስ ትርኢት  በትግራይ ክልል በክልሉ ልዩ ኃይል በተደጋጋሚ የተደረገውን ሰልፍ ምላሽ ለመስጠት ይመስላል የሚል ምላሽ የሰጡም አልታጡም። አስተያየት ሰጪዎች በአንድ በኩልም የፌደራል መንግስት እያደረገ ያለውን የፖሊስ እና ሌሎች የጸጥታ አካላትን የማደራጀት እና የመገንባት ሒደቱን አድንቀው ነገር ግን ከክልሎች ጋር እልህ መጋባትንም ቢያቆም መልካም እንደሆነ ምክረ ሀሳባቸውን ገልጸዋል። ‹‹እኔ በግሌ ፈርቼ ነበር›› የምትለን አስተያየት ሰጪያችን እንደ እኔ አይነት በርካታ ሰዎችም እንደሚኖሩ እና በተደረገው ሰልፍ ፍርሀት እንደተሰማትም አልደበቀችም። ሕዝብን ደኅንነቱ የተረጋገጠ እንዲመስለው እና በእርግጥም ጠንካራ ፖሊስ ኃይል መገንባቱን ለማሳየት የተደረገውን ሰልፍ እና ትርኢት በአደባባይ ባይደረግ እና ለሕዝብ የደኅንነት መረጋገጥ ተብሎ ሕዝብን ስጋት ውስጥ መክተት ተገቢ እንዳልሆንም ይናገራሉ።

አዲስ ማለዳ ካነጋገረቻቸው መንገደኞች እና አስተያየት ሰጪዎችም አንደምታው ምን ይመስላል በሚል ለመለሱት ጥያቄ በበቅርቡ በቀድሞው ምክር ቤት አባል አስመላሽ ወልደስላሴ አማካኝነት የትግራይ ክልል ከመስከረም 25/2013 ጀምሮ ከፌደራል መንግስት የሚወጡ ትዕዛዛትን እንደማይቀበሉ ይፋ መደረጉን ተከትሎ የተላለፈ መልዕክትም ይሆናል ሲሉም መላ ምታቸውን ያስቀምጣሉ።

በርካታ መልኮችን የያዘው የፌደራል ፖሊስ የሰልፍ ትርኢት በርካታ መላ ምቶች የተስተናገዱበት ቢሆንም በመንግስት በኩል ግን በተለይም ደግሞ ከፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል እንዳሻው ጣሰው የተላለፈው መልዕክት በመንግስት በኩል ያለው አቋም እና ሁሉን አቀፍ ለውጥ እያካሔደ የሚገኘውን የፌደራል ፖሊስ አባላትን እና ተቋም የሚያሞካሽ ነበር።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here