የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ውጤት አነጋገረ

Views: 623

ረቡዕ፣ ነሐሴ 7 በይፋ የተለቀቀው የዘንድሮው የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ውጤት መደበኛ የሆኑትንም ሆነ ማኅበራዊ መገናኛ ብዙኀንን ስቧል፤ የብዙዎችም መነጋገሪያ ርዕሰ ጉዳይ ሆኗል።

በአንድ በኩል በአገር ዐቀፍ ደረጃ 645 ነጥብ በማስመዝገብ ብሩክ ዘውዱ የተባለ በባሕር ዳር የአየለች ደገፉ (የታዋቂው አትሌት ኀይሌ ገብረሥላሴ) ትምህርት ቤት ተማሪ መሆኑ ተሰምቷል። ብሩክ ከእናቱ ጋር ሆኖ ስልክ ሲያወራ የሚያሳይ እንዲሁም ገና ትምህርት ቤት ከመግባቱ በፊት በእህቱ የወላጆች ሥነ ስርዓት ከአትሌት ኀይሌ ገብረሥላሴ ጋር አብሮ የተነሳው ፎቶግራፎች የማኅበራዊ ትስስር አውታሮችን አጨናንቋል።

በሌላ በኩል ደግሞ በተለይ ስኮላስቲክ አፕቲቲዩድ የትምህርት ዓይነት የበርካታ ተማሪዎች ውጤት ዝቅ ማለቱን ተከትሎ ብዙዎችን አነጋግሯል፤ የበርካታ ተማሪዎች ቅሬታም ተደምጧል። ብዙዎቹ ቅሬታ አቅራቢዎች ለፈተናው ካደረጉት ዝግጅት አንጻር የማይገባቸውን ውጤት ማስመዝገባቸውን በሐዘኔታ ገልጸዋል። የአንዳንድ ተማሪዎች ውጤት ከበጣም ዝቅተኛ ውጤት በታች ዜሮ ማስመዝገባቸውም ተነግሯል።

የትምህርት ሚኒስትሩ ጥላዬ ጌቴ (ዶ/ር) በትዊተር ገጻቸው ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች የእንኳን ደስ ያላችሁ ባስተላለፉበት መልዕክታቸው የሚመለከተው አካል በተለይ ከስኮላስቲክ አፕቲቲዩድ ውጤት ጋር በተያያዘ ለተነሳው ቅሬታ ምርመራ በማድረግ ምላሽ እንደሚሰጥበት ተስፋቸውን ገልጸዋል።

ሌሎች ታዋቂ ከሆኑ ግለሰቦች መካከል በተለይ ከዚህ ቀደም የተሰጡ ብሔራዊ ፈተናዎች ፈተናው ከሚሰጥባቸው ቀኖች በፊት ሾልከው እንዲወጡ በማድረግ ለፖለቲካ ተቃውሞ መግለጫ ጥቅም ላይ አውሏል ተብሎ በአንዳንዶች የሚሞገሰው፤ በሌሎች የሚወገዘው ጃዋር መሐመድ በትዊተር ገጹ ላይ የዘንድሮው የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ውጤት “የሆነ ችግር አለበት” ሲል የጻፈ ሲሆን የፈተናዎች ኤጀንሲ ግልጽነትና ኀላፊነት በተሞላበት መልኩ የእርምት እርምጃ መውሰድ ይገባዋል ሲልም መልዕክቱን አስተላልፏል።

የአገር ዐቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ ሥራ አስኪያጅ አርዓያ ገብረእግዚአብሔር በተለያዩ መገናኛ ብዙኀን ላይ የቀረበውን ቅሬታ በሚመለከት ምላሽ የሰጡ ሲሆን በውጤቱ ላይ ቅሬታ ያለው ማንኛውም ተማሪ በአካል፣ በስልክ ወይም በድረ ገጽ ቅሬታውን ማቅረብ እንደሚችል፤ ኤጀንሲውም ቅሬታውን መርምሮ ምላሽ እንደሚሰጥ አስታውቀዋል። አርዓያ በተለይ ከስኮላስቲክ አፕቲቲዩድ ውጤት ጋር በተያያዘ የቀረበውን ቅሬታ እውቅና እንደሚሰጡ፤ የሚቀርቡ ቅሬታዎችን አጣርቶ አግባብ የሆነ ምላሽ የሚሰጥ ኮሚቴም መቋቋሙን ጨምረው አስታውቀዋል።
መጪዎቹ ሳምንታት የተማሪዎችን ቅሬታ በመፍታት ምላሽ ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ቅጽ 1 ቁጥር 41 ነሐሴ 11 2011

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com