10ቱ በአዳጊና ወጣቶች በብዛት ወንጀል የተፈጸመባቸው የኢትዮጵያ ክልሎች

Views: 778

ምንጭ: የኢፌዴሪ ሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ ሚኒስቴር አዳጊና የወጣቶች ሁኔታ የ2010 ዘገባ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአዲስ አበባ እና በተለያዩ አካባቢዎች የስርቆትና የዝርፊያ ወንጀሎች በብዛት የመፈጸማቸው ዜና እየተሰማ ነው። እነዚህ ወንጀሎች በብዛት ዝርፊያ ከመሆናቸው ባሻገር በአካልና በሕይወት ላይ ጉዳት ያስከተሉ ናቸው። ባለፈው ዓመት ብቻ በአዲስ አበባ ከተማ 32 ሺሕ 970 ዝርፊያ፣ ስርቆትና መሰል ወንጀሎች ተፈጽመዋል። እነዚህም ወንጀሎች ዕድሜያቸው በ16 እና 30 ዓመት መካከል በሚገኙ አዳጊ እንዲሁም ወጣቶች የተፈጸመ ነው።

የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽንን ጠቅሶ መረጃውን ያስነበበው የ2010ን የኢትዮጵያ አዳጊና ወጣቶች ሁኔታ የሚያስቃኘው ዘገባ እንዳካተተው፤ አኀዙ በ2009 ከነበረው የቀነሰ ነው። ይሁንና እስከ 2009 ድረስ ግን በከፍተኛ ሁኔታ ቁጥሩ ዕድገት እያሳየ እንደነበር ተጠቅሷል።

በኢትዮጵያ በ2010 ከተፈጸሙ ወንጀሎች ከፍተኛው ደረጃ የተመዘገበው በኦሮሚያ ክልል ነው። በተመሳሳይ በሌሎች ክልሎች እንዲሁም በኹለቱ ከተማ መስተዳደሮች በተመዘገበው ወንጀል ተይዘው የሚገኙት ደግሞ ከ90 በመቶ በላይ ወንዶች ናቸው። ለዚህም ሁሉ ምክንያቱ የሥራ አጥነት መሆኑ በተለያየ ጊዜ ይነሳል።

ከኦሮሚያ ቀጥሎ አዲስ አበባ ከተማ፣ አማራ እንዲሁም የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልሎች በወጣቶችና አዳጊዎች ከፍተኛ ወንጀል የሚፈጸምባቸው ሆነው ተመዝግበዋል። በአንጻሩ በአፋርና በድሬዳዋ ዝቅተኛው የተመዘገበ ሲሆን ጋምቤላ እና ትግራይ ክልል ላይ ያለውን መረጃ ሪፖርቱ አላካተተም።

በአሁኑ ሰዓት የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደርን ጨምሮ በተለያዩ ክልሎች ለወጣቶች የሥራ ዕድልን ከመፍጠር አንጻር እየተደረጉ ያሉ እንቅስቃሴዎች እነዚህን ወንጀሎች ይቀንሳሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ቅጽ 1 ቁጥር 41 ነሐሴ 11 2011ጊ

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com