የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በዓለማችንም ብሎም በአገራችን ላይ እያደረሰ የሚገኘው ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሥነ ልቦናዊ ጫና ይህ ነው የሚባል አይደለም። በወረርሽኙ ሳቢያ ብዙኀኑ የዓለማችን አገራት የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን በመገደብ መንግሥታዊም ሆነ የግል አገልግሎት መስጫ ተቋማትን ዘግተው መክረማቸውም የሚታወቅ ነው። ሰዎች ሕዝብ ከሚበዛባቸው ስፍራዎች እንዲርቁ መወሰኑን ተከትሎም፣ በእጅጉ ከተጎዱና እንቅስቃሴያቸው ከተቀዛቀዘ ዘርፎች ውስጥ አንዱ ፊልም እና ሲኒማ ነው።
ለወትሮው በሺዎች የሚቆጠሩ ተመልካቾችን ያስተናግዱ የነበሩ የአገራችን ሲኒማ ቤቶች በወረርሽኙ ሳቢያ ተዘግተው ሰንብተዋል። የወረርሽኙ የመዛመት ባህሪም የፊልም ባለሙያዎች አዳዲስ ቀረጻዎችን እንዲያከናውኑ ባለመፍቀዱ በርካታ ባለሙያዎች ፊልሞችን በመሥራት ገቢ ያገኙባቸው የነበሩ መንገዶች ሁሉ ተዘግተውባቸው ለከፍተኛ ችግር ተዳርገው መቆየታቸውም በተደጋጋሚ ሲገለፅ ቆይቷል።
ታዲያ በዚህ ሁኔታ ላለፉት ሰባት ወራት ያለ አንዳች ሥራ በራቸውን ዘግተው የከረሙ ሲኒማ ቤቶች ወረርሽኙ ላልተወሰነ ጊዜ የሚቆይ ከመሆኑ አንጻር፤ ካሳለፍነው ሳምንት መስከረም 29/2013 ጀምሮ አገልግሎታቸውን በአዲስ መልክ ዳግመኛ እንዲጀምሩ አስታውቀዋል። ይህንንም የኢትዮጵያ የፊልም ፕሮዲውሰሮች የዘርፍ ማህበር፣ የሲኒማ ቤቶች ተወካዮች እና የጤና ሚኒስቴር በጋራ በመሆን በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።
ነገር ግን ሲኒማ ቤቶቹ ዳግመኛ አገልግሎታቸውን ሲጀምሩ ቀድሞ ከሚይዙት የተመልካች አቅም በግማሽ መቀነስ እንደሚገባቸውና ከእስከ ዛሬው በተለየ መልኩም የሲኒማ አፍቃሪውን የሚመጥኑ፤ ጥሩ የሚባል የታሪክ ፍሰትን ከሲኒማ ፕሮዳክሽን ጥራት ጋር ያጣመሩ ፊልሞች ብቻ ለዕይታ እንዲቀርቡ መወሰኑም ተገልጿል።
አዲስ ማለዳም ይህን ውሳኔ ተከትሎ የፊልም ባለሙያዎችን አስተያየት እና የሲኒማ ዘርፉን ቀጣይ እጣ ፈንታ በሚመለከት ተከታዩን ጥንቅር አሰናድታለች። በቅድሚያ ግን የአገራችንን የሲኒማ ጅማሮና እድገት ጥቂቱም ቢሆን ለመዳሰስ እንሞክር።
የኢትዮጵያ የሲኒማ ጅማሮ እና እድገት
የአገራችን የሲኒማ ታሪክ ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረ ነው። የመጀመሪያው የሕዝብ ሲኒማ ቤትም በአፄ ምኒልክ ዘመን በ1890 ከአልጄሪያ በመጣ አንድ ፈረንሳዊ አማካኝነት በአዲስ አበባ እንደተከፈተም የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ። በወቅቱም የአገሬው ሰው በሲኒማ ቤቱ የሚታየው የምስል ትዕይንት አንዳች የማይታመን ሴጣናዊ ምትሀት የሚታይበትና የማይጨበጥ ትንግርት መሆኑን በማመን፤ ሲኒማ ቤቱን የ‹የሴጣን ቤት› የሚል ሥያሜ በመስጠት ወደዛ ከመሄድ ራሱን ያቅብ እንደነበር ይነገራል።
ከጊዜያት በኋላም የሲኒማ ቴክኖሎጂውን የሚመለከትና የሚያደንቅ ተመልካች እየቀነሰ በመሄዱና በተለይም በጊዜው የነበሩ የሃይማኖት ሰዎች ሕዝቡ ከሴጣን ቤት እየሄደ ትዕይንቱን እንዳይመለከት በማውገዛቸው ተከፍቶ የነበረው ሲኒማ ቤት ለኪሳራ ተዳረገ። ፈረንሳዊው የሲኒማ ቤት ባለቤትም በወቅቱ የጣሊያን ሚኒስቴር ቢሮ ተወካይ ለነበረ ቺኮዲኮላ ለሚባል ሰው ሙሉ የፊልም ማሳያ መሣሪያዎቹን በመሸጥ ወደ አገሩ ተመለሰ።
ቺኮዲኮላም መሣሪያዎቹን ለአፄ ምኒልክ በስጦታ መልክ በማበርከቱ ንጉሡ በእልፍኝ አዳራሻቸው ውስጥ የተለዩ መንፈሳዊ ፊልሞችን ለመኳንንትና ቀሳውስቱ በማሳየት አዲሱን ቴክኖሎጂ እንዲለማመዱ ማደረጋቸውን ጳውሎስ ኖኞ ‹አፄ ምኒልክ› በተሰኘውና በ1992 ባሳተመው መጽሐፋ ላይ አስነብቧል።
ከዛም በማስከተል ለአስርት ዓመታት ያህል የሲኒማ ቴክኖሎጂው በህዝቡ ዘንድ ተቀባይነትን አጥቶ የዘለቀ ሲሆን በ1901 ከአልጄሪያ በመጡ ሁለት ወንድማማቾች እና ቦይኮቢች በሚባል ሰው አማካኝነት አዲስ አበባ ላይ ሌላ ሲኒማ ቤት ተከፈተ። ይህም ሲኒማ ቤት አንድ አመት ከሰራ በኋላ በፕሮጀክተር መበላሸት ምክንያት መዘጋቱንም ጳውሎስ በመጽሐፉ ያስረዳል።
ታዲያ ይሄ የሲኒማ ቴክኖሎጂ ቀስ በቀስ በማህበረሰቡ ውስጥ ተቀባይነትን እያገኘና ከጊዜ ወደ ጊዜ በአገሪቱ የተለያዩ ሲኒማ ቤቶች እየተከፈቱ በመሄዳቸው የአገራችን የሲኒማ ኢንዱስትሪ አሁን ያለበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ ሆነ።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህም በተለያዩ የዘርፉ ባለሙያዎች አማካኝነት የተለያየ ዘውግ ያላቸው ፊልሞች በብዛት እየተሰሩ ሲሆን የሲኒማ ቤቶች እየተበራከቱ መሄዳቸው የፊልም አፍቃሪው የተለያዩ የመዝናኛ አማራጮችን በአቅራቢያው እንዲያገኝ አስችሎታል። ከዚህም በላይ የሲኒማ ቤቶቹ በቁጥር መበራከት የፊልም ሰሪዎች ሲያጋጥማቸው የነበረውን የማሳያ ቦታ ችግር በመፍታት ለሲኒማው ኢንዱስትሪ እድገት ከፍተኛ የሚባል አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል። ኢንዱስትሪው ካስቆጠረው እረጅም እድሜ አንፃር መድረስ ከሚገባው ደረጃ ላይ ባይደርስም።
የሲኒማ ባለሙያው በዘመነ ኮቪድ
የኮቪድ 19 ወረርሺኝ በአገራችን መከሰቱን ተከትሎ በነበሩት 6 እና 7 ወራት ከፕሮዳክሽን ቡድን፣ እስከ ፕሮዲዩሰር ከፀሃፍት እስከ ተዋንያን በየደረጃው ያሉ የሲኒማው ኢንዱስትሪ ባለሙያዎች ላይ በከፍተኛ ችግር ውስጥ ወድቀው መቆየታቸው ይታወቃል።
በኮሮና ሳቢያ ሲኒማ ተዘግቶ በቆየበት ወቅት የኪነ-ጥበቡ ባለሙያ ሁለት አይነት መንገድን ሲከተል እንደቀየ የሚያስረዳው በፊደል አዳኝ፣ 300 ሺህ፣ ካፖርቱ፣ ዘውድ እና ጎፈር፣ ሰኒኮ፣ የፍቅሬ ፍቅረኛ፣ በቁም ካፈቀርሺኝ እንዲሁም አሁን በመጨረሻ ላይ ባወጣው ግራና ቀኝ በተሰኙ ፊልሞቹ የምናውቀው የፊልም ፀሀፊ፣ ዳይሬክተርና የካሜራ ባለሙያ ቢኒያም ጆን ኦቶ ነው።
ቢኒያም እንደሚለው ጥበቡ ላይ ትኩረት አድርገው ሳይሆን ለገቢ እና ለእንጀራ የሚሰሩ ሰዎች ሲኒማ ቤቶች ተዘግተው በቆዩበት ወቅት እጅግ ተቸግረው እንደነበር በማንሳት በዚህም ምክንያት ትንንሽ ታሪኮችን የያዙና በትንሽ በጀት የሚሰሩ የዩ-ቲዩብ ፊልሞችን በመስራት የፊልሙን ታዳሚ ከፊልሙ ኢንዱስትሪ እንዲሸሽ የሚያደርግ ስራን ሲሰሩ መቆየታቸውን ይገልፃል።
በሌላ በኩል ደግሞ ይሄን ወቅት በአግባቡ የተጠቀሙበትም አሉ የሚለው ቢኒያም ከኮሮናው በፊት ቅንብራቸው በችኮላ ተሰርቶ ሊወጡ የነበሩ ፊልሞችን በደንብ ተብላልተው እንዲወጡ፣ ድጋሚም የሚቀረፁም ድጋሚ እንዲቀረፁ የጊዜ ክፍተትን ስለሰጠ ሲኒማው እስኪከፈት በደንብ ታሽተው ታሪክ ላይም ተረጋግተው እንዲሰሩ እድል መስጠቱን በማንሳት ይህም ለትክክለኛው ባለሙያ ስራው ጥራት እንዲኖረው ማድረጉን ይገልፃል።
‹‹ባለሙያ ሲባል አንድ ፊልም ተበላሸ ከተባለ ሁሉም አንድ ላይ ነው አብሮ የሚነቀፈው።›› የሚለው ደግሞ እውነት ሀሰት፣ ሚስቴን ዳርኳት፣ ወደፊት፣ የፍቅር ሰው ደራሲና አዘጋጅ እንዲሁም በሌሎች በርካታ ፊልሞች ላይ በዝግጅት እና በትወና ሲሳተፍ የምናውቀው በረከት ወረደ ‹ማያ› ነው። በረከት እንደሚለውም በኮሮና ምክንያት የሲኒማ ኢንዱስትሪው በተቀዛቀዘበት ወቅት የተሻለ ነገር ይዘው የሚመጡ ባለሙያዎችን በደንብ የሚያበረታታ፤ በቅርብ የሚግባቡ የፊልም ባለሙያዎችን የያዘ እንደማህበርም አይነት ነገር በማቋቋም በጋራ የተሻለ ነገር ለህብረተሰቡ ለማቅረብ ውይይት እና ምክክሮችን ሲያደርጉ መቆየታቸውንም ይገልፃል።
በረከት አክሎም ባለሙያዎቹ በኮሮና ወቅት እንደመሰባሰባቸው በሰዓቱ በችግር ውስጥ የነበሩ አጋር ባለሙያዎች ሳይፈልጉ የማያምኑበትን ስራ እንዳይሰሩ በማለት እርስ በእርስ ሲረዳዱና ሲደጋገፊ መቆየታቸውን ገልፆ፤ ማህበሩንም ወደፊት በተሻለ እና በተቀናጀ መልኩ የጋራ ስራዎችን ለመስራና ሙያውን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሻገር እቅድ እንዳለም ያስረዳል።
‹‹የሲኒማው ኢንዱስትሪ በኮቪድ ምክንያት ለ7 ወር ተቋረጠ እንጂ እንደ ማህበር አንድም ቀን አላረፍንም እኛ ብዙ ስራዎችን ስንሰራ ቆይተናል››። በማለት ለአዲስ ማለዳ የምታስረዳው ደግሞ የፊልም ባለሙያዋና የኢትዮጵያ የፊልም ፕሮዲውሰሮች ማህበር ዋኛ ፀሀፊ አርሴማ ወርቁ ነች።
እንደ የኢትዮጵያ የፊልም ፕሮዲውሰሮች ማህበር ከባህል እና ቱሪዝም ሚኒሰቴርና ከሌሎች ወደ 17 የሚጠጉ አጋር የኪነ-ጥበብ ማህበራት ጋር አንድ ላይ በመሆን በኮሮና ዙሪያ ትኩረታቸውን ያደረጉ ወደ 18 የሚሆኑ የግንዛቤ ማስጨበጫ ቪዲዮዎች መሰራታቸውን የምታስረዳው አርሴማ ‹‹ከዛ ባለፈ አንዳንድ የንግድ ድርጅቶች በከፊል መከፈት ከጀመሩ በኋላ፤ የእኛም ሲኒማ ቤቶች መከፈት አለባቸው የሚል ምክረ ሃሳብ ለባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አቅርበን እርሱን ስንከታተል ነበር የቆየነው።›› በማለት ባለፉት ወራት እንደ ማህበር ሲሰሩ የነበሩ ስራዎችን ትገልፃለች።
‹‹በተጨማሪም›› ትላለች አርሴማ ‹‹በተጨማሪም ጎን ለጎን ምንድን ነው ኮቪድ ያነቃን! የስርጭት አማራጭ ዘዴዎችን በአፋጥኝ መዘርጋት እንደሚገባን ነው። በዚህም መሰረት ‹‹አርት ዉድ›› የሚባል የኦን ላይን ስርአት ለማስጀመር ከሞላ ጎደል ስራዎችን ያጠናቀቅን ሲሆን ከሰሞኑ ይፋ እናደርጋለን።›› ስትልም ቴክኖሎጂውን በተከተለ መልኩ የሲኒማውን ኢንዱስትሪ ለማሳደግ ስራዎች እየተሰሩ መቆየታቸውን ትናገራለች።
የሲኒማ ቤት ዳግም መከፈት እና የፊልሞች ጥራት
ምንም እንኳን አሁን አሁን በፊልም ባለሙያው በየቀኑ እየተመረቱ ለተመልካች የሚቀርቡ የፊልም ስራዎች ቁጥር እየተበራከተ ቢመጣም ባለሙያዎቹ በፍጥነት እና ለሲኒማ ወረፋ ለማድረስ ብቻ ሲሉ ቶሎ ቶሎ የይድረስ ይድረስ ስራን ስለሚሰሩ፤ ኤዲቲንጋቸው በደንብ ያልተጠናቀቀ፣ የጥራት መጓደል የሚታይባቸውና ማህበረሰቡንም ሆነ ተመልካቹን ያላከበሩ ፊልሞች በብዛት እየተሰሩ መቆየታቸውን ብዙዎች እንደ ቅሬታ የሚያነሱት ጉዳይ ሆንዋል። ይህም ደግሞ ብዙሃኑን የፊልም አፍቃሪ ከአገር ውስጥ ፊልሞች አይኑን በማንሳት ወደ ባህር ማዶ ፊልሞች ትኩረቱን እንዲያደርግ አስገድዶታል ቆይቷል።
አሁን ግን የኢትዮጵያ የፊልም ፕሮዲውሰሮች የዘርፍ ማህበር፣ የሲኒማ ቤቶች ተወካዮች ጋር ባደረገው ስምምነት መሰረት ሲኒማ ቤቶች ዳግመኛ አገልግሎታቸውን ሲጀምሩ የሚታዩት ፊልሞች በሚገባ ተሰርተው ማለቃቸውን፣ ለህብረተሰቡ የሚመጥን የታሪክ ይዘት እና የሲኒማ ጥራትን ማሟላታቸውን በማረጋገጥ የፍቃድ ሰርተፍኬት ካልተሰጣቸው ወደ ሲኒማ እንደማይወጡ ተገልጿል።
ይህም በተመሳሳይ የታሪክ ፍሰትና በሚያሰለች የቅንብር ጥራት መጓደል ምክንያት የተማረረውን የፊልም ተመልካች የሚክስና የፊልሙን ኢንዱስትሪ አንድ እርምጃ ወደ ፊት ያራምዳል ይጠበቃል።
‹‹በእኛ በኩል ፊልሞች እንደ በፊቱ ሳይሆን ለሲኒማ በሚመጥን ደረጃ፤ ጥራታቸውን የጠበቁ ሆነው እንዲመጡ እየሰራን እንገኛለን። ቀደም ሲል በነበረው ጊዜ ከወረፋ መደራርብ ጋር ተያይዞ ፊልሞች ተጠናቀው ሳያልቁ የችኮላ ተሰርተው ነበር በሲኒማ ቤቶች የሚዩት የነበረው። ይህ ደግሞ የፊልሞቹን ጥራት እጅጉን የሚያጎድልና የብዙሃኑን የፊልም አፍቃሪ ስሜት በመጠበቅ የፊልም ፍላጎቱን የሚያረኩ አልነበሩም።›› ስትል የምታስረዳው አርሴማ አክላም ካሁን በኋላ ወደ ሲኒማ የሚወጡ ፊልሞች የተለያዩ መስፈርቶችን በማለፍ ስለሚወጡ የፊልሞች የጥራት መጓደል ችግር እንደሚቀረፍ ገልፃለች።
‹‹በፊት ባህል እና ቱሪዝም ሚኒስቴር ምንም አይነት ፊልም ቢሆን ከፖለቲካና ከሀይማት የፀዳ መሆኑን ካረጋገጠ የማሳያ ፍቃድን ይሰጥ ነበረ። እርሱም አሁን የአብይ መንግስት ከመጣ ወዲህ ቀርቶ ነበር።›› የሚለው ቢንያም አሁን የፕሮዲውሰሮች ማህበር የተለያዩ መስፈትቶችን በማስቀመጥና ፊልሙ ለሲኒማ ብቁ ነው ብሎ ሲያምን የማሳያ ፍቃድ በመስጠት ወደ ሲኒማ እንዲገባ መደረጉ ኮሮና ተከትሎ የመጣ መልካም እንቅስቃሴ ነው በማለት ይገልፃል።
‹‹በኢትዮጵያ የፊልም ፕሮዲውሰሮች የዘርፍ ማህበርና በሲኒማ ቤቶች መካከል የተካሄደው ስምምነት እጅግ በጣም ጥሩ ነው። ምክንያቱም የፊልም ኢንዱስትሪው እንደሚታወቀው ተኝቶ ነበረ። በውሳኔው ትንሽ ይቀሰቀሳል ብዬ አስባለሁ።›› የሚለው ደግሞ በረከት ነው በኮሮና ምክንያት እራሱን ጨምሮ ብዙ ባለሙያዎች ከስራ ውጪ ሆነው እንደ ነበር ይናገራል። ‹‹አሁን ግን ሲኒማ ቤት በመከፈቱ ምክንያት የፕሮዲውሰሮችም ስልክ መደወል ተጀምሯል። ስለዚህ ለውጥ ይኖራል እኛም የተቀመጠውን መስፈርት የሚያሟሉ ስራዎችን በመስራት ዳግም ወደ ኢንዱስትሪው እንመለሳለን ብዬ አስባለሁ።›› ሲልም ለቀጣይ ስራዎች በመነሳሳት ላይ እንደሚገኝ ይገልፃል።
የሲኒማ ቤቶች ዳግም መከፈትና የኮቪድ 19 መመሪያዎች ተፈፀሚነት
የኮቪድ 19 ወረርሺኝ መስፋፋትን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠርና የሚያስከትለውን አስከፊ ጉዳት ለመቀነስ ሲኒማ ቤቶቹ ዳግመኛ በሚከፈቱበት ወቅት ከኮቪድ ጋር ተያይዞ ጤና ሚኒስቴር፣ የማህበረሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እንዲሁም የአለም የጤና ድርጅት ያወጧቸውን መመሪያዎች ሁሉ ሲኒማ ቤቶችም ይሁን ተመልካቾች መተግበር እንደሚገባቸው የጤና ሚኒስቴር ያሳሰበ ሲሆን፤ ሲኒማ ቤቶቹም ከዚህ በፊት ከነበራቸው ተመልካች የመያዝ አቅማቸው በግማሽ መቀነስ እንደሚገባቸውም ተገልጿል።
ስለነዚህን ሲኒማ ቤቶቹም ሆነ የፊልሙ ታዳሚዎች ሊተገብሯቸው ስለሚገቡ መመሪያዎች አርሴማ የሚከተለውን ትላለች ‹‹የሲኒማ ቤቱ ከፍታ ቢያንስ ከ5 ሜትር በላይ መሆን ይጠበቅበታል፣ ለእጅ መታጠብ የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን ሊሟሉ ይገባል፣ ሁሉም የሲኒማ ቤቱ ሰራተኞችም ይሁን ተመልካቹ ማስክ አድርጎ እንዲገባ፣ መቀመጫዎችም አንድ አንድ መቀጫዎች እንዲነቀሉ በማድረግ በደንብ ርቀት እንዲኖር በማድረግና መሰል ቅድመ ሁኔታዎችን ከግንዛቤ ውስጥ የሚያስገቡ፤ እንዲሁም የአየር መቆጣጠሪያ መሳሪያ ያላቸውን ሲኒማ ቤቶች ብቻ ነው እንዲከፈቱ ያደረግነው።›› በማለት ለአዲስ ማለዳ የገለፀች ሲሆን የእነዚህንም መመሪያዎች ተፈፃሚነት የሚያረጋግጡ ከሲኒማ ቤቱና ከፕሮዲውሰር ሀርፍ ማህበሩ የተውጣጣ አንድ ተቆጣጣሪ ቡድን መቋቋሙንም አስረድታለች።
‹‹የሰዉ መቀነስ ግን ትንሽ ጉዳት አለው። ብዙ ጊዜ ፍቅረኛሞች እና ቤተሰቦች ናቸው ሲኒማ ቤት የሚገቡት። አሁን ወንበር ለያዩ እና ፊልም እዩ ብንላቸው የሚመጡ የፍቅረኛሞች እና የቤተሰብ ቁጥር ይቀንሳል።›› የሚለው ቢንያም ይህም ደግሞ የፊልም ፕሮዲውሰሩንም ሆነ የሲኒማ ቤቱን ገቢ በከፍተኛ ደረጃ ሊቀንሰው እንደሚችል ያለውን ስጋት ይገልፃል።
በረከትም በበኩሉ በሲኒማ ቤቶች ዘንድ ያለውን ችግር ሲገልፅ እንዲህ ይላል። ‹‹እንደሚታወቀው ብዙዎቹ ሲኒማ ቤቶች የሲኒማ ቤትነትን መስፈርት አያሟሉም። በአሁን ወቅት የተከፈቱ ሲኒማ ቤቶች ናቸው ትንሽ አየርን የማዘዋወር አቅም ያላቸው፤ ሌሎቹ የተዘጉ አዳራሾች ናቸው። እና ለውጡ ቀስ እያለ በሂደት የሚሄድ ይመስለኛል። በተጨማሪም መስፈርቱን የሚያሟሉት ሲኒማ ቤቶች ላይ የተመልካቹ ቁጥር ከፍ እያለ ቢመጣ ጥሩ ነው። ምክንያቱም ሲኒማው እንደዚሁም ተዳክሟል በዛው እልም ብሎ እንዳይጠፋ።›› በማለት የተመልካች ቁጥርን ለመጨመርም ሆነ ለመቀነስ የሲኒማ ቤቶች የጥራት ደረጃ ሊታይ እንደሚገባ ይናገራል።
የተመልካች ቁጥር መቀነስ የፊልም ኢንዱስትሪው ላይ ተፅእኖ ማምጣቱ እንደማቀር የምታነሳው አርሴማ ነገር ግን ከጤና ሚኒስቴር ጋር በቅርበት በመነጋገር በጊዜ ሂደት የሚሻሻል እንደሚሆን ታስረዳለች። ‹‹ያ እስኪሆን ግን መርሆቹን በተከተለ መልኩ ከፍተን የሚመጡትን ክፍተቶች መሙላት ይሻላል። ምክንያቱም ይሄንንም እንዴት በብቃት እንወጣዋለን፣ ህብረተሰቡን ከወረርሺኙ ጠብቀን የፊልሙን ኢንዱስሪም እያንቀሳቀስን መቀጠል እንችላለን የሚለውን መጀመሪያ ማወቅ አለብን። እርሱ ከሆነ በኋላ ግን ይሄን ያህል የሰው ቁጥር ቢጨመር ወደሚለው እንሄዳለን።
አሁን ግን እንደ አማራጭ ከሲኒማ ቤቶች ጋር በምናደርገው ንግግር የተጋነነ ባይሆን እስከ 30 በመቶ ድረስ የክፍያ ጭማሪ እንዲደረግ በውይይት ላይ ነን። እንዲሁም ፊልሞች የሚታዩበትን ሰዓት በማጠፍ ተጨማሪ እንዲታዩ በማድረግ እንዴት ገቢውን እናቻችለዋለን የሚለውንም እየተነጋገርን ነው ያለነው ገና ስምምነት ላይ ነው ያለነው።›› በማለት የሲኒማ ቤቶቹን አሰራር ለማሻሻል እየተሄደ ያለውን ሂደት ትገልፃለች።
ሲኒማ ቤቶች በተዘጉበት ወቅት ወደ ዩ ቲዩብ ያመራውን ተመልካች ወደ ሲኒማ የመመለሱ ስራ
በኮሮና ወረርሺኝ ሳቢያ የሲኒማ ኢንዱስትሪ ተዘግቶ በቆየባቸው ባለፉት ጊዜያት ውስጥ የፊልም ባለሙያው እንደ አማራጭ ገቢ ማስገቢያ ይዞ ሲሰራበት የቆየው የዩ ቲዩብ ስራዎችን መስራት ነበር። የፊልም አፍቃሪውም ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ የመዝናኛ አማራጩን በዚሁ የዩ ቲዩብ ማህበራዊ ሚዲያ ላይ አድርጎ ሰንብቷል። ታዲያ ይሄን ተመልካች መልሶ ወደ ሲኒማው ለማምጣት ከፍተኛ የሆነ ስራን ይጠይቃል የሚሉ ሃሳቦችም በብዙሃን ዘንድ በስፋት ይንፀባረቃሉ።
‹‹የኛ ስራ ነጋዴ ይበዛዋል ሙያተኛው አሁን የለም! ነጋዴው ደግሞ ብሩን ስለሚፈልግ በምንም በምንም አድርጎ 90ውንም 100 ሺውን ለመቀበል ስለሚፈልግ፤ በግድ በ40 እና በ50 ሺህ ፊልም ለመጨረስ ይጥራል። ይህም የፊልሙን ኢንዱስትሪ ጥሎት ነበር።›› የሚለው ቢኒያም በሲኒማው መቋረጥ ምክንያት ወደ ዩ ቲዩብ ያዘነበለውን ሰው ለመመለስ በዋናነት ፊልሞች ሲኒማ ላይ ከወጡ በኋላ ወደ ቲዩብ የሚወርዱበትን ጊዜ ማስረዘም እንደሚገባ ያስረዳል።
‹‹በፊት አመት ሁለት አመት ያህል ፊልም ወደ ቲዩብም ሆነ ወደ ቪሲዲ አይወርድም። ያ ማለት አንተ ማስታወቂያውን ታየዋለህ አሪፍ ፊልም መሆኑን ካወቅክ ጓጉተህ ለማየት ትገባለህ እቤቴ ይመጣልኛል አትልም። አሁን አንድ ፊልም ተሰርቶ በወር በሁለት ወር ውስጥ እቤት ይመጣል፤ ዩ ቲዩብ ላይ ይመጣል። ስለዚህ ሲኒማ ቤት የሚሄደው ሰው ለምን ሄዶ ተሰልፎ መቶ ብርም ከፍሎ ያያል? እቤቱ በነፃ በአምስት ብር ማየት እየቻለ።›› የሚለው ቢንያም ነገር ግን አሁን ሲኒማ ቤቶች እና የፕሮዲውሰሮች ማህበር የጀመሩት ስራ ማስታወቂያም በጥሩ እየተሰራለት በአግባቡ ከተያዘ እና በትክክል ከተሰራ በደንብ ሰዎችን ወደ ሲኒማ ቤት ይመሳል ብሎ እንደሚያስብም ይገልፃል።
የተሻለ ነገር ይዞ መምጣት የሲኒማውን ተመልካች መመለስ ይችላል። የሚለው ደግሞ በረከት ነው። ‹‹የዩ ቲዩብ ስራዎች ብዙ ጊዜ ከሚመደብላቸው ገንዘብ፣ ከሚሰሩበት ፍጥነትና ከችኮላው አንፃር ብዙ እንደ የጥበብ ስራ የሚያረካ ነገር አይታይባቸውም። ትልቅ ሀሳብን ተሸክመው በችኮላ በመሰራታቸው ምክንያት ሀሳባቸውን ያላወጡ ብዙ ስራዎችን አይተናል። ስለዚህ ሰዉ የሚፈልገውን የተሻለ ነገር መስጠት ነው። እኛም ሲኒማው እንጀራችን እንደመሆኑ የምንወደውም ስራ ነው። ያው ስለምናከብረው ሙያውን ለመጠበቅ እና የተሻሉ ስራዎችን ለመስራት እቅዶች ማውጣት እና በእቅዱ መሰረትም መንቀሳቀስ ይገባል።›› ሲልም ይናገራል።
‹‹እውነቱን ለመናገር የሲኒማ ተመልካች ሌላ ነው እኛ እያለማነው አይደለም እንጂ። የሲኒማው ድባብ እና የኦላይኑ ስሜት የተለያየ ነው። እራሱ ሲኒማውን ፈልጎ የሚመጣ ሰው አለ። አይከፈትም ወይ እያለ ይጠይቅ የነበረ ሰው እንዳለም ከሲኒማ ቤቶች ጋር በቅርበት ስለምንሰራ አውቃለሁ።›› የምትለው አርሴማ የተመልካች ችግር ያጋጥማል ብላ እንደማታስብ በመግለፅ ይልቁኑ ተመልካቹ ናፍቆት የመጣውን ሲኒማ የሚመጥኑ ፊልሞችን ማቅረብ ግን የፕሮዲውሰሮችም ሆነ የሲኒማ ቤቶች ስራ መሆን ይገባል ትላለች።
‹‹የሚመጣውን ፊልም ሁሉ ዝም ብሎ እየተቀበሉ ማሳየት ነበር ተመልካቹንም እያስከፋ ለእንደዚህ አይነት ችግር እየጋለጠን የነበረው። እርሱ ላይ አሁን በስፋት ስለመከርን ሲኒማ ቤቶችም ፊልሞች መምረጥ ላይ ጠንቃቃ እንደሚሆኑም ምንም ጥርጠር የለውም። ስለዚህ አለም እንዳለ በአሁኑ ሰዓት በኮቪድ ምክንት ዩ ቲዩብ ላይ ቁጭ ብሎ ነው የከረመው፤ እንደውም ናፍቆት በጣም ግር ብሎ እንደሚመጣ ነው የምንጠብቀው።›› ስትል ትገልፃለች። አያይዛም እንደውም የሚመጣውን ሰው ከተቀመጡት መመሪዎች አንፃር እንዴት እንቆጣጠረው ነው እንጂ አይመጣም የሚል ሀሳብ እንደሌላት ታስረዳለች።
በሲኒማ ቤቶች በኩል ያለው ችግር መፍትሄው
በሲኒማ ቤቶች በኩል ያለው ችግር ብዙ እንደሆነ የሚናገረው ቢኒያም ብር አለመክፈል፣ ፕሮግራም እንደፈለጋቸው የመለዋወጥ፣ ወረድ ያለ ስራ የሰሩ ፕሮዲውሰሮች በጉቦ ፊልሞቻቸው እንዲታዩ መደረጉና መሰል ችግሮች እንዳሉ ያነሳል። ‹‹ዋናው ችግር ግን ብር አለመክፈል ነው። ውሉ ፊልሙ ለእይታ ከበቃ በኋላ ወሩ በገባ በአስር ቀን ውስጥ ክፍያ ይፈፀማል ነው የሚለው። ብዙዎቹ ግን 6 ወርም አመትም ላይከፍሉ ይችላሉ።›› ሲልም ያስረዳል።
ከሲኒማ ቤቶች ጋር በተደረገው ውይይት አንዱ አጀንዳ የነበረው የፊልሞች በአንድ ጊዜ ተደራርቦ መውጣት እና እርሱን ተከትሎ የሚመጣው የወረፋዎች ሽያጭ ጉዳይ ነው የምትለው አርሴማ ይህም ፕሮዲውሰሮች ላልተፈለገ ወጪና ሙስና ይዳርግ እንደነበረም ታነሳለች።
‹‹ዋናው ነገር የኋላውን ደጋግመን ማንሳት ሳይሆን የፊቱን ማሰብ ነው የያዝነው። ሲኒማ ቤቶች እና ፕሮዲውሰሮች የማይለያዩ እጅ እና ጓንት መሆን ይገባቸዋል ብለን እንደ ማህበር እናምናለን። ምክንያቱም በጎሪጥ እዛና እዛ ሆኖ መተያየት፣ ለችግሮቻችን መፍትሄ ከማምጣት ይልቅ እኔ ከተጠቀምኩና ካልጎዳኝ ምን ቸገረኝ የሚለው አካሄድ እራሱን ሲኒማ ቤቱን እየጎዳው እንደመጣ ተረድተናል።
ምክንያቱም ከዚህ በፊት ጥሩ ጥሩ ፊልሞችን የሚያመርቱ ፕሮዲውሰሮች ከኢንዱስትሪው ሸሽተዋል። ያ ደግሞ የምን ተፅዕኖ እንደሆነ በደንብ ሲኒማ ቤቶቹ ተረድተውታል። ስለዚህ ደጋግመን እሱን ከማንሳት ይልቅ ምን እናድርግ ወደሚለው እየሄድን ነው እኛም። ከዚህ በኋላ ከአስር ቀን በላይ ሲኒማ ቤት ክፍያ ሳይከፍል መቆየት አይችልም ብለን አስምረን ተነጋግረንበታል። ስለዚህ ይሄ ተግባራዊ እንዲሆን ይደረጋል። ካልሆነና በተቀመጠው መሰረት የማይመራ ሲኒማ ቤት ካለ ደብዳቤዎችን ከመስጠት ጀምሮ የተያዩ እርምጃዎችን መውስዳችን የማይቀር ነው።
ቅጽ 2 ቁጥር 102 ጥቅምት 7 2013