በ‹‹ፕራይቬታይዜሽን›› ላይ ገርበብ ያለው በር

0
1065

በኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ያልታየ በሚመስል አኳኋን በመንግስት ይዞታ ስር የሚገኙ የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል የማዞር ጉዳይ በስፋት ሲወራ እና ሲነሳ ከርሟል። ጎራዎችን ከፍሎም ሲያከራክር እና ሲያደራድር የቆየው ይህ ጉዳይ ታዲያ፣ በአሁኑ ሰዓት ለክፍለ ዘመን አንድ ለእናቱ ሆኖ ሲያገለግል የቆየውን ኢትዮ ቴሌኮምን በከፊል ወደ ግል ይዞታ ለማዘዋወር ጫፍ ላይ የደረሰ ጉዳይ ሆኗል። ይሁን እንጂ በስፋት ተከፍቶ የነበረው ወደ ግል ይዞታ የማዛወር ሒደት በሩ ወደ መገርበቡ እየደረሰ እንደሆነ ከሰሞኑ በገንዘብ ሚኒስትር መግለጫ ላይ ለመታዘብ የተቻለ ጉዳይ ነው።

በዚህ ሒደት ላይ እንደ ትልቅ መከራከሪያ የነበረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ጉዳይ ነበር። እነዚህን እና መሰል ኹነቶችን ከዓለም አቀፍ ጉዳዮችና ጥናቶች ጋር በማዛመድ እና የተጻፉ ጽሑፎችን በማገላበጥ የአዲስ ማለዳው ኤርሚያስ ሙሉጌታ ሐተታ ዘ ማለዳ ጉዳይ አድርጎታል።

በሕዝብ እና በመንግስት የባለቤትነት ስር ሲተዳደሩ የነበሩ ድርጅቶችን ወደ ግል የማዛወር ጉዳይ በቀደሙት ዓመታት እና በቀረው ዓለማት ላይ ማየት የተለመደ ጉዳይ ነው። በተለይ ደግሞ በካፒታሊዝም ርዕዮተ ዓለም ላይ በግል ባለሃብቶች ስር የሚገኙ ታላላቅ ድርጅቶች እና ኩባንያዎች ለዚህ ምስክር ናቸው። እንዲህ ዓይነት አካሔድ ባለባቸው አገራትም ግለሰቦች ላይ ያለው ሀብት በእጅጉ እስከ የተመነደገ እና መንግስትም በታማኝነት የሚከፍሉትን ግብር እየተቀበለ ተመጋጋቢ በሆነ መንገድ አገርን ገንብቶ ሕዝብን ያስተዳድራል።

ታዲያ በኹለት የተለያዩ እና ጽንፍ የያዙ አመክንዮዎች የሚሞገተው የመንግስት ድርጅቶችን ወደ ግል ይዞታ የማዘዋወር ጉዳይ ሊነሱ የሚችሉበት አንደኛው፤ ትርፍን ከማግኘት ጋር ተያይዞ በመንግስት እና በሕዝብ ይዞታ ስር ያሉ ድርጅቶች ወደ ግል መዞር እንደሚኖርባቸው እና በሙሉ አቅማቸው ተንቀሳቅሰው ምርት እና አገልግሎት መስጠት እንደሚኖርባቸው መከራከሪያ ያነሳሉ። ከዚህ በተቃራኒው የሚቆሙት ደግሞ ወደ ግል ይዞታ በሚዞሩት ድርጅቶች እና ኩባንያዎች ምክንያት የግሉ ባለሀብቶች አብዛኛውን የንግድ እና የምጣኔ ሀብት ዘርፍ ተቅልለው በግላቸው በመያዝ ሰለ ሰፊው ማኅበረሰብ ያለማሰብ ጉዳይ ይኖራል የሚል ደግሞ መከራከሪያ ይሰማል ሲል ‹ኢኮኖሚክስ ኸልፕ› ያስነብባል። በአገረ እንግሊዝ መንግስት በፈረንጆች 1980 እና 1990ዎቹ ላይ ከፍተኛ የሆነ በመንግስት ይዞታ ስር ነበሩ ግዙፍ ኩባንያዎችን ወደ ግል የማዞር እንቅስቃሴ ያደረገበት ጊዜ እንደነበር የነገራል። በዚህም መሰረት የእንግሊዙ የነዳጅ አምራች እና ዋጋ ቆራጭ ድርጅት ‹ብሪቲሽ ፔትሮሊየም›፣ የቴሌኮም ኩባንያው ቢቲ ፣ የብሪታኒያ አየር መንገድን እንዲሁም የጋዝ ኩባንያዎችን እንዲሁም የባቡር መስመሮችንም ወደ ግል ይዞታ ማስተላፉ በታሪክ ይነገራል።

ይህ ታዲያ በተለያዩ አገራት የተለመደው እና በተለይም ደግሞ በምዕራባዊያን ዘንድ የቆየው ይኸው የመንግስት ይዞታ ስር ቆይተው ወደ ግል ይዞታ የመዛወር ሂደት በኢትዮጵያም የቅርብ ጊዜ ትውስታ ወይም ክስተት አይደለም። በአብዮታዊ ዲሞክራሲ የሚመራው ኢህአዲግ በትረ ሥልጣኑን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ በመንግስት ይዞታ ስር ነበሩ የልማት ድርጅቶች በሙሉ እና በከፊል ወደ ግል ሲዛወሩ ኖረዋል እየተዛወሩም ይገኛሉ። በመጀመሪያዎቹ ኢህአዴግ ዘመን 1983 እና 84 ላይም የሦስት ዓመታት ፖሊሲ ማዕቀፍ ተዘጋጅቶ የነበረ ሲሆን በዚህም ረገድ የዓለም አቀፉ ገንዘብ ተቋም እና የዓለም ባንክ ተስማሙበት ሰነድ እንደነበርም ታሪክ ያስረዳል።
የምጣኔ ሀብት ለውጥ (ሪፎርም) ተከትሎ በርከት ያሉ ውሳኔዎች እንዲወሰኑ እና ነባር አካሄዶች እንዲለወጡ ያስገደደበት ወቅትም ነበር በመጀመሪያዎቹ ኢህአዴግ ዘመነ መንግስት። በዚህም ተያይዞ ታዲያ ከዕዝ ገበያ በአንድ ጊዜ ተመንጭቃ የወጣችው ኢትዮጵያ በመንግስት ይዞታ ስር የነበሩ ኩባንያዎችን በሙሉ እና በከፊል እንዲዘዋወሩ የሪፎርሙ አንዱ አስገዳጅ ሁኔታ እንደነበር በፈረንጆች 2007 በጀት ዓመት የተጻፈው Privatization Programme in Ethiopia የተሰኘው ጽሑፍ ያስረዳል።

የሽግግር መንግስት የምጣኔ ሀብት ፖሊሲውን ቀረጸው የያኔው ኢህአዴግ ታዲያ በመንግስት ይዞታ ስር ነበሩ ኩባንያዎችን በሙሉ እና በከፊል ወደ ግል ይዞታ ሲያዘዋውር በወቅቱ 211 ትላልቅ እና መካከለኛ በመንግስት ይዞታ ስር ነበሩ ድርጅቶች የነበሩ ሲሆን እስከ ፈረንጆች 2002 እና 2003 ድረስ ታዲያ በርካታ ቁጥር ያላቸው ድርጅቶች ወደ ግል ተዛውረው ነበር። በዚህም የተነሳ 141 ትላልቅ እና መካከለኛ ኩባንያዎች በሕዝብ እና በመንግስት ይዞታ ስር እንዳሉ የቆዩበት ጊዜ ሲሆን ቀሪዎቹ ግን በገፍ ወደ ግል ይዞታ በሙሉ እና በከፊልም ተዘዋውረው እንደነበር ዋቢ ጽሑፉ ይጠቅሳል።

በኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓትም በተለይም ደግሞ ካለፉት ኹለት ዓመታት ተኩል ወዲህ ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ በሚመስል ሁኔታ በመንግስት ይዞታ ስር ነበሩ ኩባንያዎችን ወደ ግል የማዞር ሂደትን በአዲስ መልክ ሲስተጋባ ቆይቶ ነበር። በእርግጥ በዚህ ወቅት በአትራፊነታቸው በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ ኩባንያዎች (በግልም ሆነ በመንግስት) ቀርቶ በአፍሪካ እንኳን ተወዳዳሪ ማይገኝለትን እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድን ጨምሮ ሌሎች ታላላቅ የመንግስት የልማት ድርጅቶችን በሙሉ እና በከፊል ወደ ግል በማዞር የገቢ ምንጭ በመጨመር እና ተጨማሪ የስራ ዕድል በመፍጠር የኢትዮጵያን የምጣኔ ሀብት ግስጋሴን የማሳለጥ ሒደትን ታሳቢ ያደረጉ ውሳኔዎች ተደርገዋል። ከዚህም ጎን ለጎን ታዲያ በኢትዮጵያ ብቸኛው የአገልግሎት ሰጪ ሆኖ ሲያገለግል ዘመናትን ተሸገረው ኢትዮ ቴሌኮምም ወደ ግል ለማዞር በተደረገ ውሳኔም በርካታ ዓለም አቀፋዊ ድርጅቶች ፍላጎት አሳይተው እና ግዙፍ ረብጣ ገንዘቦችንም አቅርበዋል። በተመሳሳይም ለተጨማሪ ሕዝብ አማራጭም ሆነው ለመቅረብም አስበዋል።

በተያዘው ወር የ40 በመቶ የኢትዮ ቴሌኮም ድርሻ ለጨረታ እንደሚቀርብም አቅጣጫ ተቀምጦለት በመስራት ላይም የሚገኝ ሲሆን ይህንንም በቅርቡ ወደ ተግባር እንደሚገባም ይጠበቃል። ከዚሁ ጋር በተያያዘም የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚንስቴር አብይ አሕመድ (ዶ/ር) 40 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ ለዓለም አቀፍ ባለሀብቶች ለሽያጭ ሚቀርብ ሲሆን 5 በመቶ የሚሆን ተጨማሪ ድርሻ ደግሞ ለአገር ውስጥ ባለሀብቶች እንደሚተላለፍ አስታውቀዋል።

ኢትዮ ቴሌኮምን ድርሻዎችን ወደ ግል ከማዞር ባለፈ ወደ አገር ውስጥ በመግባት አገልግሎት መስጠት እንዲጀምሩ በመንግስት ደረጃ አስፈላጊውን ቅድመ ሁነታ ያሟሉ ዓለም አቀፍ የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪዎችም በዚሁ ዓመት 2013 የካቲት ላይ እንደሚገቡም ብሎምበርግ መዘገቡ ይታወሳል። በእረግጥም ወራቶችን ወደ ኋላ እንዲገፋ ያደረገው በዓል አቀፍ ደረጃ የተከሰተው ኮቪድ 19 ወረርሽኝ እንደሆነ እና ከዚህ ቀደም ብሎ መደረግ ይገባው እንደነበርም በዘገባው ተካቷል።

የመንግስት የልማት ድርጅቶች ይዞታ እና አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ሆኑት በየነ ገብረ መስቀል ከአዲስ ማለዳ ጋር ባደረጉት ቆይታ በኢትዮ ቴሌኮም ላይ የሚደረገውን ወደ ግል ማዛወር ሁኔታን እንዴት ይመለከቱታል የሚል ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ፤ ጉዳዩን በኹለት ክፍለው እንደሚመለከቱት እና ኹለት ዓይነት አቅጣጫ እንዳለው ያስረዳሉ። በየነ እንደሚሉት አንደኛው እና የመጀመሪያው አዳዲስ ተወዳዳሪዎች ወደ ዘርፉ እንዲገቡ በማድረግ ኢትዮ ቴሌኮም ወደ ውድድር ውስጥ እንዲገባ በማድረግ እና ለተጠቃሚው መልካም ነገር ማቅረብ እንደመሚቻል ይናገራሉ። ‹‹ውድድር ከሌለ የተሸለ ነገር አይፈጠርም፤ ድክመትንም ማሻሻል አይኖርም›› የሚሉት በየነ ኢትዮ ቴሌኮም አዳዲስ አሰራሮችን በማስተዋወቅ ዕድገት እያሳየ እንደሚሄድም ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ከዚሁ በተጓዳኝ ታዲያ በቅር መግለጫ የሰጡት የገንዘብ ሚኒስቴር አሕመድ ሽዴ በቴሌኮም ዘርፍ በአገር ውስጥ ለመሰማራት ፍላጎት ያሳዩ ድርጅቶች መኖራቸውን እና አዲስ ሦስተኛ ድርጅትም በዚህ ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት ማሳየቱም ተገልጿል። የቀድሞው የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ የነበሩት አንዱአለም አድማሴ (ዶ/ር) በመጀመሪያው ድርጅቶችን ወደ ግል የማዞር ሀሳብ ብልጭ ባለበት ወቅት ከአዲስ ማለዳ ጋር ባደረጉት ቆይታ የቀድሞው የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ አንዷለም አድማሴ (ዶ/ር) መንግሥት የቴሌኮሙን ገበያ ለግል ውድድር ክፍት ማድረጉ በጥንቃቄ ከተተገበረ ውጤቱ ትልቅ ይሆናል ሲሉ መናገራቸው ሚታወስ ነው፡፡

“ህብረተሰቡ ማግኘት የሚፈልገውን ያህል አገልግሎት አልሰጠነውም ነበር፣ እነዚህ ተቋማት ሲመጡ እና ውድድር ውስጥ ስንገባ በአንድ አመት ምን ያህል ለውጥ እንደሚያመጡ የሚገመት ነው። ነገር ግን ቴሌኮም ማለት መደበኛ አገልግሎት ማለት ብቻ ሳይሆን የአገር ደኅንነት ጉዳይ ማለትም ጭምር ነው” ሲሉ አንዷለም መወሰድ ስላለበት ጥንቃቄ አፅንኦት ይሰጣሉ፡፡

ድርጅቶችን ወደ ግል ማዛወሩ ጉዳይ እንዴት እየሔደ እንደሆነ እና የስኳርኢንተርፕራይዝ፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በተለይም ደግሞ የኢትዮጵያ ኤልክትሪክ ኃይል ጉዳይ ገዢ ያገኛል ብለው ያምኑ እንደሆነም ጥያቄ ቀርቦላቸዋል። በየነ ለአዲስ ማለዳ ምላሽ ሲሰጡ፤ የኢትዮጵያ ኤልክትሪክ ኃይልን ወደ ግል ማዛወር ሒደት በጅማሬ ላይ እንዳለ እና ገና በሚባል ደረጃ ላይ እንደሆነ በማስታወስ ተናግረዋል። አያይዘውም በጣም አጣብቂኝ ውሳኔዎች ከሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ውስጥ በጣም ግዙፍ ዕዳ ያለባቸውን ድርጅቶች ወደ ግል የማዛወር ጋር የተያያዙ ጉዳዮች እንደሆኑ ጠቅሰው ይህም ከእነ ዕዳቸው ወደ ግል ይዛወሩ ወይስ ከዕዳቸው ውጪ የሚለው ጉዳይ ትልቅ ውሳኔ የሚያሻው ጉዳይ እንደሆነ አስቀምጠዋል። በመንግስት ይዞታ ስር የሚገኙ ድርጅቶች ባሉበት ከእነ ዕዳቸው ትርፋማ ሚሆኑ ከሆነ ከእነ ዕዳቸው የሚተለላለፉ ሲሆን ካልሆነ ግን ከዕዳቸው ውጪ እንደሚተላለፉ አስቀምጠዋል። ይሁን እንጂ በስኳር ኮርፖሬሽ ዙሪያ ያለውን ወደ ግል የማዛወር ተግባር በተመለከተ በርካታ ስራዎች እና ጥናቶች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰው ጥናቶች ከተጠናቀቁ በኋላ ዋና ዋና ውሳኔዎች እንደሚተላለፉም አስቀምጠዋል። ነገር ግን በመጀመሪያ ደረጃ የስኳር ፋብሪካዎችን ወደ ግል ለማዛወር በመጀመሪያ ደረጃ ቁጥጥሩን እና በስኳር ገበያ ላይ ያለው ጫና ማንሳት እንደሚገባ እና በዚህ በኩል ለዘመናት የቆውን በገፍ አጠቃሎ መያዝ አካሔድን መቆም እንደሚኖርበት አስቀምጠዋል። ይህ ጉዳይ ታዲያ ፋብሪካዎች ወደ ግል ይዞታ ከተዘዋወሩ በኋላም መተግበር የሚገባው ጉዳይ እንደሆነም በየነ ይናገራሉ። ከዚህም ጋር ተያይዞ በቅርቡ አንድ ፖሊሲ የስኳር ኩባንያዎች ወደ ግል ከዞሩ በኋላ ሊተዳደሩ ሚገባበትን ጉዳይ የሚመለከት እንደሚቀርብ ለማወቅ ተችሏል።

መንግስት ግዙፍ ዕዳ ያለባቸውን ድርጅቶች እንዴት ወደ ግል ይዞታ ማዛወር እንደሚችል ለቀረበላቸውም ጥያቄ በየነ ሲመልሱ ለምሳሌ የተወሰኑ የስኳር ፋባሪካዎች ዕዳ እንኳን ቢኖርባቸው በቋሚነት ምርት እያመረቱ ስለሚገኙ እና ይህም ትርፋማ ስለሚያደርጋቸው ወደ ግል ማዛወሩ እምብዛም ሊከብድ እንደማይችል ይናገራሉ። ይሁን እንጂ ካላቸው የገዘፈ ዕዳ ምክንያት ወደ ግል የማዛወሩ ጉዳይ ከባድ እንደሚሆንም አልሸሸጉም። በዚህም ምክንያት ምዕራፍ በምዕራፍ መታየት እንደሚኖርበትም ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ወደ ግል ይዞታ የማሸሸጋገሩ ጉዳይ ግን ከሰሞኑ በአሕመድ ሽዴ በኩል የመቀዛቀዝ እና ወደ ኋላ ማፈግፈግ ጉዳይ እያሳየም እንደሆነ ለመታዘብ ተችሏል። ይህም ከዚህ ቀደም በግንባር ቀደምትነት ሲጠቀሱ ከነበሩ ጉዳዮች ውስጥ ኢትዮጵያ አየር መንገድን ወደ ግል የማዛወር ጉዳይ አንዱ ነው። ስለዚህም ጉዳይ አሕመድ ሲናገሩ አየር መንገዱ ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪ ከመሆኑም ባሻገር ራሱን እና አገርን ከማቆም አንጻርም ችግር ስለሌለበት ላልተወሰነ ጊዜ ወደ ግል ማዞሩ ጉዳይ በይደር እንደቆመ አስታውቀዋል። አያይዘውም በሎጂስቲክ ዘርፍ ወደ ግል ለማዛወር እና አገልግሎቱን ከማሳለጥ አኳያ ያለውን ተደራሽነት ለመጨመር ሲታሰብእንደነበርም የሚታወቅ ነው። ነገር ግን ይህ ጉዳይ የግል ባለሀብቶች በደረቅ ወደብ እና በሌሎች ዘርፎች መሳተፍ የሚችሉበትን አግባብ ብቻ ከመንግስት ወገን እንደተመቻቸ ነው አሕመድ ሽዴ በመግለጫቸው ያብራሩት።

ገርበብ ብሏል ለተባለለትድርጅቶችን ወደ ግል ይዞታ የማዘዋወር ጉዳይ የተለየ አስተያየት ያላቸው ምጣኔ ሀብት ተንታኙ አብዱልመናን መሐመድ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት ወደ ግል እንዲዛወሩ ቀረቡት ድርጅቶች ላይ ገዢዎች ፍላጎታ ማጣታቸው እንጂ መንግስት እንደሚለው እንዳልሆነ ያስቀምጣሉ። ሐሳባቸውን ሲያጠናክሩም ኢትዮ ቴሌኮም አትራፊ እና በደህና ቁመና ላይ ያለ ድርጅት ከመሆኑ ጋር ተዳምሮ በርካታ አካላት ፍላጎት ማሳየታቸውን ገልጸው በሌሎች ዘርፍ ግን ድፍረት ማጣተቸው እና ፍላጎታቸውም እንደጠፋ ያሰምሩበታል።

ቀጥለውም በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው አለመረጋጋት እና የሰላም ዕጦት ገዢዎች ወደ ኢትዮጵ መጥተው ኢነቨስት እንዳያደርጉ እንዳስፈራቸው እና መተማመኛ ማጣታቸው እንደሆነም ይናገራሉ። በኢትዮጵያ አየር መንገድም ረገድ ሲያነሱ፤ ሚኒስቴሩ እንዳሉት ብቻ ሳይሆን በኮቪድ 19 ምክንያት ከፍተኛ ድቀት ውስጥ የሚገኘው የአቪየሽን ኢንዱስትሪ ወደ ግሉ ዘርፍ ለመዛወር ደፍሮ የሚገባ ሰው አለመኖሩን ጠቁመዋል። በተመሳሳይም ገዢ ቢኖር እንኳን በዝቅተኛ ወጋ ስለሚቀርብ አዋጪ እንደማይሆን ስለታሰበበት ይሆናል ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።

ኹለት ጎራዎችን የፈጠረው ‹ፕራይቬታይዜሽን› በኢትዮጵያ
የመንግስት እና በሕዝብ ይዞታ ስር የነበሩ ታላላቅ እና መካከለኛ ድርጅቶችን ወደ ግል ይዞታ የማዞር ጉዳይ በስፋት መነሳት ከጀመረበት የ2010 የመጨረሻ ወራት ጀምሮ በርካታ ግለሰቦች እና በንግዱም ዘርፍ ረጅም ዓመታትን ያሳለፉ ግለሰቦችም በድጋፍ እና በመንቀፍ ውስጥ ሀሳብ ሲሰነዝሩም የተስተዋሉበት ትልቁ ጉዳይ ነበር። በአንዱ ወገን በመንግስት ይዞታ ስር ያሉ ድርጅቶችን ወደ ግል ማዛወር ማለት ከባድ የሆነ ችግር በአገር ደረጃ የሚያደርስ እና አገርን እና ሕዝብን በጥቂት ባለሀብቶች ቁጥጥር ስር ውስጥ የሚከት ጉዳይ እንደሆነ በማስገንዘብ አመክንዮዎችን በማንሳት ይሚሞግቱ አሉ። ከዚሁ በተቃራኒው ደግሞ ኢትዮጵያ ካለችበት አንዳንድ ችግሮች በተለይም ደግሞ በውጭ ምንዛሪ እና ባለው የንግድ አለመመጣጠን ረገድ ከፍተኛ የሆነ ክፍተትን የመሙላት እና የማጥበብ ስራ እንደሚሰራ በማንሳት ጠቃሚነቱን እና ወደ ግል ማዛወርም ጊዜ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ እንዳልሆነ በትልቅ መነሳሳት ሲያነሱ ይሰማል።

ኩባንያዎች እና ድርጅቶች ከመንግስት ይዞታ ወደ ግል የማዞር ተግባርን አምረርረው ከሚቃወሙት ውስጥ የምጣኔ ሀብት ተንታኙ እና የንግድ ሰው ክቡር ገና አንዱ ናቸው። ክቡር ከካፒታል ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቆይታም ‹‹ወደ ግል ይዞታ ከማዛወር ጋር በተገናኘ እርስዎ በተቃራኒው የቆሙ ነዎት?›› የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው ሲመልሱም ‹‹ በመጀመሪያ ሊጠየቅ ሚገባው ድርጅቶችን ወደ ግል ማዞር በእርግጥ የሰፊውን ሕዝብ ጥቅም የሚያስጠብቅ ተግባር ነው ወይ ተብሎ መጠየቅ ይኖርበታል ›› ሲሉ ይጀምራሉ።

ድርጅቶችን ወደ ግል ይዞታ የማዛወርን ጉዳይ አግዝፈን ልናየው ሚገባ ጉዳይ እደሆነ ክቡር ያስቀምጣሉ። ምክንያቱ ደግሞ ድርጅቶች ወደ ግል ይዞታ ሲዘዋወሩ የአንድን ፍላጎት ከማስጠበቅ ሙሉ በሙሉ ወደ ሌላ ወገን ፍላጎትን ወደ ማስጠበቅ የመዞር ጉዳይ ሰለሚሆን ትልቅ ጉዳይ እንደሆነ ይመልሳሉ። ይህንንም ሲያስረዱ የሕዝብን ፍላጎት እና ጥቅም ከማስጠበቅ በተለየ ወደ ግል በሚዛወሩበት ወቅት ለማስቀጠል እና ለማጠናከር ሚተጉት ግለሰቦችን እንደሚሆን እና ይህም ጎጂ እንደሚሆን ነው።

በሌላ በኩል ደግሞ ክቡር ሲናገሩ ወደ ግል ማዞር ማለት የስራ ኃላፊዎች ወይም ግል ባለሀብቶች ስራቸውን በገቢው መንገድ በማሳለጥ ድርጅቶች በሙሉ አቅማቸው ስራቸውን እንዲፈጽሙ ያደርጋሉ ማለት እንዳልሆነ ይናገራሉ። ይልቁንስ ደግሞ የግሉ ዘርፍ ባለሀብቶች ትርፍ የሚያገኙበትን አካሔድ በምንም አይነት መንገድ ቢሆን ተግባራዊ ለማድረግ የማያቅማሙ መሆናቸው ደግሞ ጉዳዩን ይከብደዋል ሲሉም ይሞግታሉ ክቡር ገና። ‹‹ለምሳሌ ትርፍ የማግኘት አካሔድን በተመለከተ በቴሌኮም ዘርፍ ለምሳሌ ኢንተርኔት አገልግሎት አለመስጠት ትርፍ የሚያስገኝ ከሆነ አገልገሎቱን ሊያቋርጡ ሚችሉበት አጋጣሚ ይኖራል›› ሲሉም ትርፍን ብቻ መሰረት አድርገው ስለሚንቀሳቀሱ ግሉ ዘርፍ ለመግለጽ ሞክረዋል።

ድርጅቶችን ወደ ግል ይዞታ የማዘዋወር ጉዳይ ጥቅም እና ጉዳት በዋናነት በድርጅቶች የስራ አመራሮች አመለካከት ላይ ነው መለካት ሚገባው ሲሉ ሚደመጡት ክቡር፤ የድርጅቶች የስራ ኃላፊዎች በመንግስትም ሆነ በግል የባለአክሲዮኖቻቸውን ጥቅም ከማስጠበቅ አኳያ እየሰሩ የሚገኙበት መንገድ ሊታይ ሚገባ ሲሆን በትክክልም ለባለአክሲዮኖቻቸው ጥቅም ላይቆሙም ይችላሉ ይላሉ።

ከጊዜያት በፊት በአዲስ ማለዳ 37ኛ ዕትም ላይ ለንባብ በበቃው ጽሑፍ ላይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቀድሞ ዋና ሥራ አስፈፃሚ የነበሩት ግርማ ዋቄ ሰጡትን አስተያየት እና በቀጠናው የፖለቲካ እና ምጣኔ ሀብት ላይ በትኩረት ሚተነትነው እዮብ ባልቻ (ዶ/ር) እንዲሁም ከላይ ለማስቀመጥ እንደሞከርነው ቀደም ሲልም ለአዲስ ማለዳ አስተያየታቸውን ሰንዝረው የነበሩት ክቡር ገናም በዚሁ ላይ ሀሳባቸውን እናገኘዋለን እና ሀሳባቸውን እንዲህ ለማውሳት ወደናል። ግርማ ዋቄ እንደሚሉት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ትርፋማ ከመሆኑ ባሻገር የአገሪቱን የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ማንቃቱን እና የእቃ ማመላለሻ ክንፉም ለወጪ ንግዱ ያለውን አበርክቶ ለአየር መንገዱ ስትራቴጂአዊነት እንደ ማስረጃ ያነሳሉ፡፡ ግርማ አክለውም የአገሪቱ የወጪ ንግድ የማያመጣውን የውጪ ምንዛሬ የሚያመጣው አየር መንገዱን መሸጥ ማለት በብር የሚሰበስበውን ትርፍ ሳይቀር በዶላር ይዘው ለሚወጡ ባለሀብቶች አሳልፈን እንሽጥ ማለት ነው ሲሉ ይሞግታሉ።

ክቡር በግርማ ሐሳብ ባለመስማማት ይዘው የሚወጡት የውጪ ምንዛሬ አሳሳቢ አይደለም ይላሉ። “እንደቴሌኮም እና አየር መንገድ ያሉ ዓለማቀፍ ንግድን የሚያካትቱ ሥራዎች ከውጪ የሚገኘው ገቢ ይዘው የሚወጡትን ወጪ የሚሸፍን ይመስለኛል” ሲሉ ይናገራሉ። “የአገሪቱ የብሮድባንድ ኢንተርኔት ሥርጭት ከዜሮ በታች አምስት በመቶ ነው። ይህ ማለት መቶ ሚሊዮን ሕዝብ፣ ከዚህም 70 በመቶ ወጣት ሃይል ይዘን ፍጠኑ [እና] ወጣቶችን በአንድ ላፕቶፕ እና በፈጣን ኢንተርኔት ወደ ዓለማቀፍ ገበያ ይቀላቀሉ ነበር መባል የነበረበት” ሲሉ ያብራራሉ። ከዚህ አንጻርም የኮሚኬሽን አዋጁ ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከመላኩ በፊት የገንዘብ ሚኒስቴር የቴሌኮም ሪፎርም ቡድን አቋቁሞ ይህንን ማጥናቱን እና ይህም በቂ የሚባል ጥንቃቄ ተደርጎ መሠራቱን ያመላክታል የሚል እምነት እንዳላቸው ብሩክ ጨምረው ተናግዋል።

ለእዮብ ግን ይህ ጉዳይ የቴክኒክ ሥራ እና አግባብ ባለው ሕግ የመወጣት ብቃት ሳይሆን መሰረታዊ የኢኮኖሚ ችግሮችን መፍታት ችግር ነው። “ጥያቄው በዝናብ ላይ ለተመሰረተው ግብርና ወይም ለ80 በመቶ ገበሬ መፍትሔ የሌለው እና ለዚች ትልቅ አገር ለምትፈልገው የልማት አቅጣጫ ማን የበለጠ ይቃኘው የሚለው ጥያቄ ነው አንገብጋቢ” ሲል በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት በተዘጋጀው ውይይት ላይ ያቀረቡት ጽሑፍ ያትታል። ‹‹የከተማው ሰው ጥያቄ ጥሩ ኢንተርኔት የገጠሩ ሰው ደግሞ ልጁንን የሚያስተምርበት ትምህርት ቤት ነው የሚፈልገው፡፡››

በሌላ በኩል ክቡር ተቋማቱ ካላቸው የኢኮኖሚ ዋጋ በበለጠ በገንዘብ የማይተመነው የብሔራዊ ማንነት ላይ የሚያመጣው ጫና ቀላል አይደልም ሲሉ ይከራከራሉ። “በአፍሪካ ውስጥ ስጓዝ የማየው አፍሪካዊያን ወንድሞቻችን በከሰረ አየር መንገድ ካላቸው ሼር ይልቅ ስኬታማ በሆነው የኢትየጵያ አየር መንገድ ላይ ያላቸው የእኔ ነው የሚለው ስሜት እና ኩራት ይበልጣል፡፡ አሁን ካለንበት ከፋፋይ የፖለቲካ ዓለም ውስጥ አንድ ብሔራዊ ማንነትን ለመፍጠር እነዚህ አገራዊ ኩራቶች ትልቅ ሚና አላቸው።”

እነዚህ እንደ አገር የሚያስማሙን እና በጋራ አሉን የምንላቸው ተቋማት ከተሸጡ አገሬ ውስጥ ምን አለኝ ወደሚለው መሔድ ይመጣል ሲሉ ክቡር ያነሳሉ። አክለውም በአውሮፓ ስላሉ እና ከመንግሥት እጅ ስለወጡ መሰረታዊ የሕዝብ አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች ሲያስረዱ ‹‹የድርጅቶቹ ባለቤቶች የጡረታ ባለሥልጣኑ፣ የከተማ አስተዳደሮች ወይም ባንኮች ናቸው፤ ያ ማለት ደግሞ ድርጅቶቹ የሕዝብ ናቸው ማለት ነው።››

የአፍካን ፖለቲካል ኢኮኖሚ መምህሩ እዮብ በበኩላቸው በሚኖሩበት አገረ እንግሊዝ መሪው የሠራተኞች ፓርቲ ትልቁ ማኒፌስቶ በግለሰብ እጅ ያለውን መሰረታዊ አገልግሎት ወደ መንግሥት መመለስ ወይም በየክፍለ አገራቱ አዳዲስ የሕዝብ አገልግሎቶችን መዘርጋት መሆኑን አንስተው እኛስ ለምን ወደኋላ እንሄዳለን ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ “በእንግሊዝ ሃገር የባቡር አገልግሎቱ ምንም ዓይነት የአገልግሎት መሻሻል ሳያሳይ ዋጋው ግን በየዓመቱ እስከ 15 በመቶ ጨምራል፣ ስድስቱ የኤሌትሪክ አቅራቢዎችም እንደፈለጉ ዋጋ ይጨምራሉ መንግስታቸውም ይህንን ለመቀየር እየሰራ ነው” ሲሉ ያነጻጽራሉ።

ጥቅም እና ጉዳቱ
ድርጅቶችን ወደ ግል ይዞታ ከማዛወር ጋር ተያይዞ የተለያዩ ወገኖች ያሻቸውን ሀሳብ ቢያወሩም በሳይንሳዊ መንገድ አመክንዮዎችን በማንሳት እንዲህ ይቀመጣል። የግል ኩባንያዎች ትርፍን መሰረት ያደረገ አካሔድ ስለሚከተሉ ወጪን በመቀነስ ረገድ ሰፊ ስራ ከመስራታቸው ጋር ተዳምሮ ወደ ግል የማዛወር ሂደት ጥቀሜታው የጎላ እንደሆነ የምጣኔ ሀብት ተንታኙ ቴጅቫን ፔቲንገር በጽሑፉ ያትታል። የስራ ኃላፊዎች በመንግስት ይዘዞታ ስር ያሉ ድርጅቶችን በሚመሩበት ወቅት የትርፍ ተካፋይ አለመሆናቸው እና በግሉ ዘርፍ ግን ይህ ባለመሆኑ ለኩባንያዎች ዕድገት የሚገቡ ሰዎች መኖራቸውን ይነገራል።

በዋናነት እና ትልቁን ስዕል ስንመለከትም ተንታኙ እንደሚያስቀምጠው የተለያዩ ታላላቅ እና መካከለኛ የመንግስት ይዞታ ስር ያሉ ድርጅቶችን ወደ ግል ይዞታ በሚዛወሩበት ወቅት መንግስት ከፍተኛ ሆነ ገንዘብ እንደሚያገኝ እና ለዚህም ደግሞ በፈረንጆች 1984 በአገረ እንግሊዝ ይህ አይነት አጋጣሚ ተፈጥሮ እንደነበር ያወሳል።

በሌላ በኩል ደግሞ በመንግስት ይዞታ ስር ቆይተው ወደ ግል የተዛወሩ ኩባንያዎች ትርን ከማካበት ጋር ተያይዞ የዋጋ ጭማሪዎችን ማድረጋቸው እንደሚያጋጥም እና ተጠቃሚዎች ላይ ከፍተኛ ጫና እንደሚያሳድሩ በጉዳት መልክ ተቀምጧል። በጣም አንገብጋቢ የሕዝብ ግልጋሎትን የሚሰጡ እና ወደ ግል የዞሩ ድርጅቶችን በማንሳት ጉዳቱን የሚያስቀምጠው ትንታኙ በጤና ዘርፍ ላይ ተሰማሩ ድርጅቶች ትርፍን መሰረት አድርገው ከመስራታቸው ጋር ተዳምሮ የሰዎችን ጤንነት ከማስጠበቅ እና በተገቢው መንገድ ሕክምና ከማድረግ ጋር ተያይዞ ደካማ አገልግሎት ሊሰጡ ይችላሉ ተብሎ እንደሚታመንም ይገልጻል። በጥቅሙ ረገድ መንግስት ወደ ግል ይዞታ የሚያሸጋግራቸው ድርጅቶች ከፍተኛ የሽያጭ ገንዘብ እንደሚያገኝ ተቀምጦ ነበር። ይሁን እንጂ ወደ ግል ከተዛወሩ ድርጅቶች ከትርፋቸው ላይ ምንም አይነት የትርፍ ክፍፍል እንደሌለበት እና ይህም እንደሚጎዳው ይናገራል። ኢንዱስትሪዎች በተለያዩዘርፎች ላይ በመሰማራት በስራዎቻቸው ላይ ጥራት ከመጉደል ባለፈም ለሚከሰተው ጥራት ማነስ ኃላፊነት የሚወስድ አካል ሊኖር የማይችልበት አጋጣሚ እንዳለም በጉዳት መልኩ ይቀመጣል።

ቅጽ 2 ቁጥር 102 ጥቅምት 7 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here