በአዲስ አበባ በግንባታ ሥራ ቦታዎች ላይ የሚደርሰው አደጋ በእጥፍ ጨመረ

0
770

በአዲስ አበባ ከተማ በግንባታ ቦታዎች ላይ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በ2011 ከነበረው በ2012 መጠናቀቂያ ላይ ከእጥፍ በላይ መጨመሩ ተገለጸ።
አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ የኢንዱስትሪ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ካሳ ስዩም እንደተናገሩት፣ በ 2011 ተመዝግቦ ከነበረው 30 የሟቾች ቁጥር 2012 በጀት ዓመት ላይ የሟች ቁጥር 68 መድረሱን አስታውቀዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ በአሰሪና ሠራተኛ ዘርፍ ጥቅምት 3/2013 በካፒታል ሆቴል ከባለድርሻ አካላት ጋር ባካሄደው የምክክር መድረክ ላይ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሠረታቸውን ካደረጉ ድርጅቶች መካከል ከፖሊስ በደረሰው መረጃ ከ68 ድርጅቶች 68 ሰዎች በግንባታ ሥራ ላይ እያሉ መሞታቸው ተነግሯል።

የቢሮው የኢንዱስትሪ ግንኙነት ዳይሬክተር ካሳ ስዩም ለአዲስ ማለዳ እንዳሉት፣ አብዛኞቹ የሞት አደጋዎች በተለያዩ ምክንያቶች ከ ፎቅ በመውደቅ፣ ከአሳንሰር ላይ በመውደቅ፣ በድልድይ መሰበር ሞት መከሰቱን ተናግረዋል፡፡

ይህም የሆነው ከአሠሪ ድርጅቶች ግንዛቤ እጥረት ጥንቃቄ ጉድለት የደኅንነት መጠበቂያ መሣሪያዎችን ባለማቅረብ በቸልተኝነት የተነሳ እንደሆነ አስረድተዋል።
እንደ ዳይሬክተሩ ንግግር የቁጥጥር ሥራው አነስተኛ በመሆኑ ምክንያት ቸልተኛ የሆኑ ድርጅቶች መኖራቸው ይህም የሆነው በተቋሙ የሰው ኃይል እጥረት ምክንያት እንደሆነ በቀጣይም ይህንን ችግር ለመቅረፍ እንደታቀደ ተናግረዋል።

በቀጣይም የሠራተኞችን ሞት ለመቀነስ አሠሪ ኢንዱስትሪዎች ለሠራተኞቻቸው ትኩረት ሰጥተው ደኅንነታቸውን ማስጠበቅ እንዲችሉ በጥናት የተደገፈ ሥራ እንደሚሠራ አሳውቀዋል፡፡

እንደ ካሳ ገለጻ፣ የጉዳት ካሳን በተመለከተ በአሠሪ እና ሠራተኛ አዋጅ አንቀፅ 109 ቁጥር 11 56/ 2011 በተጠቀሰው መሰረት የካሳ ክፍያን በጊዜው መክፈል የቀብር ሥነ ስርአት ማስፈፀምን ምንም ዓይነት ቅሬታ ወደ ቢሮው አለመላኩን አስመልክቶ ለሟች ቤተሰቦች ካሳ እንደተከፈለ ጠቁመዋል።

በጉዳዩ ላይ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸዉ መታገስ ውለታው የተባሉ የሕግ ባለሙያ የአሠሪ እና ሠራተኛ ሕጉ ስለ የሥራ ቦታ ደኅንነትን በተመለከተ በተሻሻለው የአሠሪና እና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 11 56/2011 መሰረት በክፍል ሰባት ከአንቀጽ 92-112 ድረስ የሥራ ቦታ ደኅንነትን በተመለከተ አሠሪ እና ሠራተኛ ምን ማድረግ አለበት የሚለው በግልጽ ተቀምጧል ብለዋል።

እንደ መታገስ ገለፃ ጉዳት ካሳ ጉዳይን በተመለከተ የአሠሪና እና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 11 56/2011 በአንቀጽ 109 ንዑስ አንቀጽ 4 ንዑስ አንቀጽ ሀ ላይ በአራት ደረጃዎች የጉዳት መጠኑ እንደሚከፍለውና ከመጀመሪያ እርዳታ ጀምሮ እስከ ማስታመም ብሎም ከፍተኛ ጉዳት ለደረሰበት መሥራት ለማይችልና የሞተ ሰው የዓመት ደሞዝ በአምስት ተባዝቶ ይከፈላል እንደሚል ጠቅሰዋል።

የአሠሪና እና ሠራተኛ ጉዳይ ሕጉ እየተተገበረ ነው ማለት ይቻላል ያሉት የሕግ ባለሙያው ነገር ግን ከፍተኛ ጉዳትና ሞት ለደረሰባቸው ሰዎች ሕጉ መሻሻል እንዳለበት ጠቁመዋል። አዲስ ማለዳ ባደረገችው ምልከታ ግን በግንባታ ስፍራዎች ላይ የሚሠሩ ሠራተኞች በተገቢው መንገድ የሥራ ላይ ደኅንነትን በተጠበቀ መልኩ ሲያከናውኑ መመልከት አልተቻለም።

በአዲስ አበባ በግንባታ ስፍራዎች ላይ ከሚደርሰው ጉዳት ባለፈም በእግረኞች መንገድ ላይ ክፍት በተተዉ ጉድጓዶችም ምክንያት ከፍተኛ የሆነ ጉዳት እንደሚደርስ መረጃዎች ያመላክታሉ።

ቅጽ 2 ቁጥር 102 ጥቅምት 7 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here