የአትሌቷ መጠቃት የኢትዮጵያ መጠቃት ነው!

0
881

ኢትዮጵያ በአለማቀፍ ደረጃ ከምትታይባቸው መድረኮች መኸላአንዱ የአትሌቲክስ ስፖርት ነው፡፡በዚህ መስክ በርካታ ስመጥር አትሌቶችንም ለአለም አስተዋውቃለች ፡፡ ይሁን እንጂ የሁሉም አትሌቶቻችን ሰኬት በቀላሉ የተገኘ ድል አይደለም ፡፡ ግዛቸው አበበ በቅርቡ በአትሌት ለተሰንበት ጊደይ እና አሰልጣኟ ላይ በአንድ የአየር መንገዱ ሰራተኛ የደረሰባቸውን እንግልት እንዲህ አዘጋጅተታል

ትግራይ ለኢትዮጵያ ካበረከተቻቸው ድንቅ ስፖርተኞች እንዷ የሆነችው አትሌት ለተሰንበት ጊደይ በቅርቡ ስፔይን ውስጥ በተካሄደ የ5000 ሜትር ሩጫ ውድድር ለረዥም ጊዜ ጥሩነሽ ዲባባ ተይዞ የነበረ ሪከርድን ሰብራ አሸናፊ መሆኗ ይታወቃል።ለትሽ ድሉን እንዳገኘች የኢትዮጵን ባንዲራ ይዛ ስቴዲየሙን በመዞር ደስታዋን ስትግልጽ፣ የዲባባ ቤተሰቦች ‘እንኳን ደስ አለሽ!’ የሚል የደስታ መግለጫ ላኩ የሚለው ዜናም ወዲያውኑ ነው በማሕበራዊ ሚዲያዎች የተስተጋባው። ለተሰንበትም ‘ከእኛው ወደ እኛው ነው’ ያለችለትን የሪከርዱን ዝውውር የጋራ ድል እና የጋራ ደስታ መሆኑን ተናግራለች።

ለተሰንበት ጊደይ በቀጣዩ የኦሎምፒክ ውድድር የኢትዮጵን የሜዳሊያ ተስፋ ዕውን ያደርጋሉ ተብለው ተስፋ ከተጣለባቸው አትሌቶች አንዷ ናት። ለተሰንበትም ይህን ተስፋ ዕውን ለማድረግ በከፍተኛ ደረጃ ልምምዷን በማድረግ ላይ መሆኗንና የረዥም ጊዜ ሕልሟ የሆነውን የኢትዮጵን ባንዲራ በኦሎምፒክ መንደር ለማውለብለብ የኮቪድ-19 ወቅትን በርትታ እየሰራች ያሳለፈች መሆኑን ትናገራለች። ድሏም ይኸንን ነው የመሰከረው።

ሴት አትሌቶቻችን ብዙ ፈተናወችን እያለፉ፣ እየወደቁና እየተነሱ ይህን የመሰለ ድል ለአገራቸውና ለራሳቸው እንደሚጎናጸፉ ከማንም የተሰወረ አይደለም። አንዳንድ ጊዜ በሚዲያዎች ላይ የሚቀርበው የሴት እትሌቶች ገጠመኝ ጥቂት ሴት አትሌቶች ከባድ ፈተናዎች እንዳሉባቸው የሚያሳዩ ናቸው።

እነዚህን መሰል ፈተናዎች ብዙ አትሌቶች ዜግነታቸው እየቀየሩ ለሌላ አገር እንዲሮጡ ማድረጉ፣ አገራቸውን ጭምር አሸንፈውና ባንዲራዋን ዝቅ አድርገው የሌላ አገር ባንዲራ እንዲውለበልብ እንዲያደርጉም ሰበብ እየሆነ መምጣቱን አይተናል።በእርግጥ ሰበብ ደርድረውም ሆነ ያለ ሰበብ ድርደራ ለጥቅም ብለው፣ የተሸለ ኑሮ ለመኖር ብለው፣ የተሻለ ገንዘብ ለማግኘት ብለው ወዘተ… የሌላ አገር ዜግነትን የሚወስዱ ስፖርተኞች መኖራቸው የሚካድ አይደለም። ይህን መሰሉ ነገር የየግለሰቦቹ መብት ቢሆንም የዜግነትን ትርጉም በሕወሐት/ኢሕአዴጋዊ መዝገበ ቃላት እየፈቱ ወሬ የሚተረትሩ አንዳንድ ጋዜጠኞች፣ ዜግነትን እንደ ተራ ነገር አድርገው በመቁጠር ድርጊቱን የብልጠት እርምጃ አድርገው ሲገልጹት ይሰማል።

የኢቲቪ፣ የኢትዮጵ ሬዲዮ፣ የፋና-ወ-ዋልታ፣ የኤፍ.ኤም ሬዲዮ ጣቢያዎች የስፖርት ጋዜጠኞች ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ/ትውልደ ኢትዮጵያዊው እያሉ ከማዳነቅ አልፈው ድሉ የኢትዮጵያም ጭምር ነው ብለው ሲያቅራሩ የተሰሙበት ጊዜ ቢኖርም ነገሩ ከዚህ የተለየና ለአገር ክብር የማይመጥን መሆኑን መካድ አይቻልም። ዜግነታቸውን ትተው ለውጭ አገር ከሚሮጡ አትሌቶች አንዷ የሆነችው ሲፈን ሃሰን ቢቢሲ ላይ በግልጽ ከተናገረችው ነገር አትሌቷ ይችን አገር በጣም እንድምጠላትና ለሌላ አገር በመሮጧ ትንሽም እንደማትጸጸት በይፋ መናገሯ የስፖርት ጋዜጠኞቹን አባባል ከንቱነት የሚያጋልጥ ነው።

ብዙወቹ የስፖርት ጋዜጠኞች የአትሌቶችን ለጥቅም ብለው ይሁን ችግር አጋጥሞኛል ብለው ዜግነታቸውን ቀይረው ለሌላ አገር መሰለፍን እንደ ብልጠት አድርገው የሚያዩና አጋጣሚውን ካገኙም እየተሸኮረመሙና እየተልፈሰፈሱ የዜግነት ቀያሪውን ታላቅነትና ብልጥነት የሚገልጹበት ቃለ ምልልስ ለማድረግ የሚቸኩሉና ‘ቡራኬ-ዘ-ዳያስፖራ’ ለማግኘት የሚቋምጡ ናቸው።

ከዘመነ ደርግ ጊዜ ጀምሮ አትሌቶችን ብቻ ሳይሆን ሌሎች ስፖርተኞችንም ጭምር ወደ ውጭ ለውድድር በሚሄዱበት ወቅት ፖለቲካንና ዘርን ተንተርሰው ‘ለምን ለኢትዮጵያ ትሮጣለህ?’፣ ‘ለምን ጥገኝነት ጠይቀህ አትቀርም?’ እያሉ የሚወተውቱ ግለሰቦችና ቡድኖች መኖራቸው የአደባባይ ሚስጢር ነው። የሕወሐት/ኢሕአዴጓ ኢትዮጵያ ለታላቁ ጀግና አትሌት ለሻለቃ ምሩጽ ይፍጠር አልስማማው ያለችውና ኋልኛ የሕይወት ዘመኑን በውጭ አገር ለማሳለፍ የተገደደው ከዚህ ቁርሾ ጋር በተያያዘ መሆኑ የታወቀ ነው።

በሴት እትሌቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች ከአንዳንድ የስፖርት ተቋማት ቤተሰቦች የሚሰነዘር የጾታ ተኮር ጥቃትና ተወዳዳሪወችን ለመምረጥ በሚከሰት አድልኦና በመሳሉት የሚገለጽ ብቻ ሳይሆን እነሱም እንደ ወንዶቹ የጎሳ ፖለቲካ የወለደውና ተቋማዊ የሆነ ጥቃትም ይደርስባቸዋል።

በአንድ ወቅት ዘረኛነትንና ጎጠኛነትን መሰረት አድርጎ በተካሄደ ምልመላ፣ የተሻለ አቋም የነበራትን አትሌት ብርሃኔ አደሬን ከውድድር ውጭ በማድረግ ሌላ አትሌትን ተሳታፊ ለማድረግ የተሰራው ዐይን ያወጣ ዘረኛ ድራማ የሚረሳ አይደለም። አትሌት ብርሃኔ አደሬ ይህ አሳፋሪ የዘረኞች ድርጊት በተወሳባት ቁጥር ዜግነቷን ቀይራ ለሌላ አገር ለመሮጥ እስከ ማሰብ ደርሳ እንደነበረ በምሬት ትናገራለች።

በቅርቡ አትሌት ለተሰንበት ጊደይ ወደ ስፔይን ለውድድሩ ለመብረር የደቂቃዎች ዕድሜ ብቻ ሲቀሯት አደገኛ የሆነ እንቅፋት ገጥሟት እንደነበረ ይፋ ሆኗል። አትሌቷንና አሰልጣኟን የገጠማቸው የመጨረሻ ደቂቃ ችግሮች ተደራራቢዎች የነበሩ ቢሆኑም ይህ የአየር መንገድ ባልደረባ የሚባለው ሰው የሚያስቀምጣቸውን ተከታታይ ዕንቅፋት በሙሉ በውጭ ሆነው መረጃዎችን ፈጥነው በሚልኩ የለተሰንበት ጋባዦችና የስልክ ጥሪ እንደተደረገላት እኩለ ለሊት ላይ በፒጃማ ቦሌ አየር መንገድ ፈጥና በደረሰችው በአትሌት ደራርቱ ቱሉ ጥረት ከመስተጓጎል አምልጧል።

የለትሽና የአሰልጣኟ የሃይለ እያሱ ጉዞም የተሳካ ሆኖ የሁላችንንም ልብ በደስታ ያጥለቀለቀ የድል ጉዞ ሆኗል። ይህ ድል ሌላም ትልቅ ትርጉም አለው። በኮቪድ-19 ስጋት ምክንያት ውድድሮች በመቋረጣቸው የአትሌቶች አቋም አጠያያቂ ይሆናል የሚል ስጋት ተፈጥሮ ነበረ። ውድድሮች እንደተጀመሩም የሌሎች የአፍሪካ አገራት አትሌቶች ውድድሮችን ከማሸነፍ አልፈው ሪከርዶችን መስበራቸው መሰማቱ ‘የእኛ አትሌቶችስ እንዴት ሰንብተው ይሆን?’ የሚል ጥያቄ ማስነሳቱ አልቀረም። እናም የለትሽና የአቶ ሃይለ እያሱ ጥረትና ድል አትሌቶቻችን ኮቪድ-19 እንዳይዛመት በተቀመጡ እገዳወች ተዘናግተውና ተዳክመው ይሆን የሚለውን ስጋትም የቀረፈ ነው።

የአየር መንገዱ ሰውዬ ማን ነው? ለምን ዓላማ ያንን ሁሉ ችግር ፈጠረ? ማን ልኮት ነው ችግሮችን የደረደረው? የአየር መንገዱ ሰውዬ የእነ ለትሽን የጎጉዞ ሰነድ እያገላበጠ ጀርመን ላይ ትራንዚት ማድረግ አያስችላችሁም ሲል ጋባዦቿ ከጀርመን ኤምባሲ ጋር ግንኙነት ፈጥረው ኤምባሲው ሰነዱ ላይ ችግር እንደሌለ ገልጾ አንደኛው እንቅፋት ታለፈ፣ የአየር መንገዱ ሰውዬ ሰነዱ ውድድር ወደ ሚካሄድበት የስፔይን ከተማ ሲቪላ ለመግባት አያስችላችሁም ሲልም ፈረንጆቹ የለትሽ ጋባዦች ከስፔይን ባለስልጣናት ጋር ተገናኝተው ነሰዱ ችግር እንደሌለበት የሚገልጽ መልዕክት ልከው ሁለተኛው እንቅፋትም ከሽፏል።

የአየር መንገዱ ሰውዬ ሌላ ሦሰተኛ እንቅፋት አስቀመጠ፤ ቪዛው የቱሪስት እንጅ የአትሌት አይደለም አለ፤ ይህም ሰነዶቹን በማገላበጥ የሰውዬው አባባል ትክክለኛ እንዳልሆነ ተረጋገጠና ሦስተኛው እንቅፋት ተወገደ።

በመጨረሻም የአየር መንገዱ ሰውዬ ምንም ዓይነት ምክንያት መደርደር ሳያስፈልገው፣ ‘ዛሬ መሄድ እትችሉም ነገ ትበራላችሁ’ በማለት የመጨረሻውን እንቅፋት አስቀመጠ።የአየር መንገዱ ሰውዬ እንዳሰበው የለተሰንበት ጊደይ ጉዞ በአንድ ቀን ከተራዘመ ለተሰንበት ያለ እረፍት ከበረራ ወደ ውድድር ለመግባት ትገደዳለች፣ ይህ ደግሞ ለረዥም ጊዜ የታሰበበትንና ተስፋ የተደረገበትን ሪከርድ መስበር ቀርቶ ማሸነፏን አጠራጣሪ የሚያደርግ ነውና የለትሽ አሰልጣኝ ወደ አትሌት ደራርቱ ቱሉ ስልክ መደወሉ የግድ ሆነ።

አትሌት ደራርቱም ፈጥና ቦሌ ደረሰች። ከአየር መንገዱ ሰውዬ ጋር ‘አሁኑኑ መብረር አለባት’ በሚል ክርክር ገጠመች።ክርክሩ የዋዛ የነበረ አይመስልም። ደራርቱ ‘ይህ ጉዞ ከተሰናከለ ነገውኑ ስራዬን እለቃለሁ’ እስከ ማለት መድረሷን የለትሽ አሰልጣኝ አቶ ሃይለ እያሱ ተናገሯል።

የአየር መንገዱ ሰውዬ እንቅፋቶች በሙሉ ከሽፈው፣ የለትሽ ጉዞ ተሳክቶ፣ ለትሽ ጀርመንን ያለ ችግር አቋርጣ፣ ሲቪላ ላይም “እንኳን ደህና መጣሽ”ተብላ፣ ተወዳድራ፣ አሸንፋ፣ ሪከርድ ሰብራ በድል ተመልሳለች።ወደ አየር መንገዱና ወደ ግለሰቡ መደወልን ችላ ያሉ ብዙ የአዲሰ አበባና የመቀሌ ጋዜጠኞች ወደ ለትሽ እና ወደ አሰልጣኟ ስልክ እየደወሉ ነገሩን ለማራገብ ብዙ ሞክረዋል። ለትሽና አሰልጣኟ ችግሩ የአንድ ግለሰብ ጉዳይ መሆኑን፣ የሚካበድ ነገር እንደሌለና ኢትዮጵያን ወደ ምናኮራበት ወደ ቀጣዩ ኦሎምፒክ ብቻ እንመልከት ሲሉ ደጋግመው ተናግረዋል።

አየር መንገዱ እንደ ድርጅት ይቅርታ መጠየቁ፣ አየር መንገዱን የይቅርታ ጥያቄውን የአውሮፕላን ቅርጽ ባለውና አየር መንገዱን በሚወክል ስጦታ አጅቦ ያቀረበ መሆኑን ለትሽና አሰልጣኟ ድምጺ ወያነ ቲቪ ላይ ቃለ ምልልስ ሲያደርጉ ገልጸዋል።አየር መንገዱ ይቅርታ መጠየቁ በዚያች ቀውጢ ሰዓት ሰውዬው ተደጋጋሚ ስህትቶችን መስራቱን ወይም ተደጋጋሚ ተንኮሎችን መራመዱን ወይም ሌሎች ዓይነት ችግሮችን በእንዝህላልነት መፍጠሩ በአየር መንገዱ እንዳታመነበት የሚያሳይ ነው።
ስለዚህ አየር መንገዱ ይህ ግለሰብ ማን መሆኑን፣ ለምን ዓላማ ያንን ጉዞ ለማሰናከል እንደሞከረና ለዚህ ድርጊቱ ምን ዓይነት እርምጃ እንደተወሰደበት በግልጽ በመናገር ግዴታውን ሊወጣ ይገባዋል።አትሌቶች የዚህ ዓይነት ክልከላወችን ፈርተው ኑሯቸውን በውጭ አገራት እንዲደርጉ ወይም ከነ ጭራሹ የሌላ አገር ሯጮች እንዲሁኑ የሚገፋፋ ነውና አየር መንገዱ ነገሩን እንደ ቀላል ነገር ቆጥሮ ችላ ሊለው አይገባም። ጥቃቱ ወይም ስህተቱ
ግዛቸው አበበ / gizachewabe@gmail.com

ቅጽ 2 ቁጥር 103 ጥቅምት 14 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here