የእለት ዜና

“ክብር ለሚገባው…”

Views: 546

“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።

ከስኬታማ ወንድ ጀርባ ወይም በተስተካከለ አማርኛ ከስኬታማ ወንድ አጠገብ ሁሌም ሴት አለች። ይህቺ ሴት እናት፣ እህት ወይም ሚስት ልትሆን ትችላለች። ከስኬታማ ሴት አጠገብና ጀርባስ ማን አለ? “ጎበዝ ሴት ሁኚ!” ብላ ከምትመክር ከእናት ባሻገር ወንድ ይገኝ ይሆናል፤ እርሱም ጓደኛ፣ ባል፣ አባት ወይም ወንድም ሊሆን ይችላል።

እነዚህ አንዳንዴ ከጀርባ ሌላ ጊዜ ደግሞ ከጎን አሉ የምንላቸው ሰዎች ለምን በአደባባይ እንደማይሸለሙ ግን ግልጽ አይደለም። በቅርቡ ካየሁት አንድ መልካም የሚባል ተግባር ልነሳ። ከወራት በፊት የተከበረውን የሴቶች ቀንን ምክንያት በማድረግ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሴቶች (UN Women) ወደ በዝዋይ ከተማ አቅንቶ ነበር። ምክንያቱም ቀኑን ባገኙት ድጋፍ ላይ ጥረታቸውን ጨምረው ኑሯቸውን ካሻሻሉ ሴቶች ጋር ለማክበር ነበር።

ታድያ በዕለቱ ምስጋና እና ሽልማት ለሚገባው በየደረጃው ተገቢው ስጦታ ከተበረከተ በኋላ አንድ የቀረ ሽልማት አለ ተባለ። ይህም የትዳር ተጣማሪና የሕይወት አጋራቸው ከሆኑ ሚስቶቻቸው አጠገብ ያልተለዩ ባሎች የተሸለሙበት ነው። እርግጥ ነው ከስኬታማ ሴቶች አጠገብ ወንዶች አሉ። አርዓያ የሆኑ አባቶች፣ ጠባቂ የሆኑ ወንድሞችና “ምን ላግዝሽ?” የሚሉ ባሎች ማለት ነው። ይህ ብዙ ጊዜ የሚከሰትና የሚያጋጥም ነው ወይ? ለጥናት ባለሙያዎች ይቆያቸው። ነገር ግን አንድም ይሁን ዐሥር ሰዎች፤ መመስገን የሚገባቸው ከሆኑ ቢመሰገኑ ለብዙዎች ተምሳሌት መሆን ይችላሉ።

ልጆቻቸውን ለብቻቸው አሳድገው ከፍ ላለ ስኬት ያደረሱ፣ በራሳቸው ጥረት ከምንም ተነስተው ችግርን ‘ምንም’ ያደረጉት ሴቶች ጥቂት አይደሉም። እነዚህም ወገባቸውን ሰብረውና ትከሻቸውን አጉብጠው ሃምሳውን ሎሚ ለብቻቸው መሸከም የቻሉ ናቸው። አንዳንዴ ደግሞ ሎሚውን ሊካፈሉና ሊያግዙ የሚወዱትን ማመስገን ተገቢ ይሆናል።

ከሰውነት ተራ አናጥበው፥ ከገንዘብ እንዳዋደዱን ፊልሞቻችን ሳይሆን በቅርበት በዙሪያችን በምናውቀው እውነት ከምንም ተነስተው አንድ ደረጃ ላይ የሚወጡ ወንዶች አጠገብ ሴቶች አሉ። “ያልፋል! በርታ!” የሚሉ። በሕይወት ፈተና ከታጀቡ ብዙ ሴቶች አጠገብ ግን “በርቺ!” ባይ ወንዶችን በብዛት አናይም። ይህ የሆነው አንዳች የተፈጥሮ ስርዓት ኖሮ ይሆን ወይም በአጋጣሚ? ይህም መጠናት ይፈልጋል።

በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ለሴቶች ያለው አመለካከት ሚዛናዊ ባልሆነበት ዓለም ላይ ልማዱን አልፈው ማሰብ የቻሉ ወንዶች ግን ሊመሰገኑ ይገባል ባይ ነኝ። ሴቶች ለብቻቸውና ያለረዳት ብዙ ስኬቶችን ሊያመጡ ይችላሉ፤ አስመዝግበው አሳይተዋልም። ፍትሕና እኩልነት ግን በሴቶች ኀይል ብቻ የሚመጣ አይደለምና፤ የወንዶች አጋርነት በወንዶች አርዓያነት ሊታይ ይገባል ለማለት ነው።

ሊድያ ተስፋዬ
liduabe21@gmail.com

ቅጽ 1 ቁጥር 42 ነሐሴ 18 2011

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com