የጀነራሉ ከመቀሌ በኀይል መመለስ አንድምታ

0
494

የኢሕአዴግን ጥልቅ ተሃድሶ ተከትሎ ዐቢይ አሕመድ የጠቅላይ ሚኒስትርን መንበረ ሥልጣን በእጃቸው ባስገቡበት ወቅት ሕወሓትን ጨምሮ በአባል ድርጅቶች መካከል ከሞላ ጎደል ስምምነት እንደነበር ይታወቃል። ይሁንና ውሎ አድሮ የሕወሓት በፌደራል መንግሥት ላይ የነበረው ወሳኝ ሚና ከእጁ መውጣት እና ተጽእኖው ከትግራይን የዘለለ አለመሆን ከፍተኛ ቅሬታ አስነስቷል፤ በተለይ በፌደራል መንግሥት እና ትግራይን በሚያስተዳድረው ሕወሓት መካከል።

በኹለቱ መንግሥታት መካከል ያለው ልዩነት ቀን ቀንን፣ ወር ወርን እየተካ በሄደ ቁጥር ልዩነቱ ከመጥበብ ይልቅ መስፋት፣ ክርክሩና ንትርኩ ከመርገብ ይልቅ መጦዝ እንዲሁም ግንኙነቱ ከሰላማዊነት ወደ ፍጥጫ መለወጡ ሰርክ የምንሰማው ጉዳይ ከሆነ ዋል አደር ብሏል። በትግራይ የተደረገውና በማዕከላዊ መንግሥት እውቅና ያላገኘው ምርጫ፣ ድንገተኛ የብር ለውጥ መደረግ እንዲሁም በቅርቡ በመከላከያ ሠራዊት በአጠቃላይ በተለይ ደግሞ ከሰሜን ዕዝ ጋር በተያያዘ የፌደራል መንግሥቱ ያካሄደው ለውጥ ትግራይን የሚያስተዳድረውን ሕወሓት እና የማዕከላዊ መንግሥቱን ግንኙነት ከድጡ ወደ ማጡ እንዲሆን አድርጎታል።

በተለይ በመከላከያ ሥር የሚገኘውን የሰሜን ዕዝ የአመራር ለውጥ ማድረጉን ሕወሓት ባወቀበት ሰዓት በክልሉ ኮሚውኒኬሽን ቢሮ በኩል ባወጣው መግለጫ “ሕገወጡ የፌደራል መንግሥት ትግራይ ውስጥ በሚገኘው የሰሜን ዕዝ ላይ የጦር መሣሪያ ለውጥን ጨምሮ ምንም ዓይነት ለውጥ ማድረግ አይችልም” ሲል በምንም መልኩ ተቀባይነት እንደማይኖር ከማሳሰብ ባሻገር ማስጠንቀቂያ ማስተላፉ ይታወሳል። ብዙዎች የትግራይ መንግሥት ማስጠንቀቂያ የፈሪ ዱላ፣ ባዶ ጩኸት ሲሉ የተቹት ሲሆን ሌሎች ደግሞ ማስጠንቂያቸውን ተግባራዊ ለማድረግ ምንም የሚያግዳቸው ኀይል የለም ሲሉ ተቺዎቹን አጣጥለዋል። ለዚህም እንደ ምሳሌ ከዚህ ቀደም ሕወሓት ዝቶ ያልፈጸመው ምንም ነገር የለም በማለት ክልሉ ያካሄደውን ምርጫ በአስረጂነት ጠቅሰዋል። በመሆኑም የትግራይ መንግሥት ማስጠንቀቂያ እንደዋዛ ፈዛዛ መታየት የለበትም ሲሉ አበክረዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ የትግራይ መንግሥት አመራሮች የሰሜን ዕዝን ለማዕከላዊ መንግሥት እንዳይታዘዝ ብሎም ወደ ክልሉ ልዩ ኀይል ለመቀላቀል ከፍተኛ ሴራ መጎንጎ ብቻ ሳይሆን በተግባር አንዳንድ እንቅስቃሴዎችንም አድርገዋል ሲሉ የሚከሷቸው አሉ። የብር ለውጡን ምክንያት በማድረግ የዕዙ አባላት የሆኑትን ከፍተኛ አመራሮች በገንዘብ ለመደለል የተደረገ ሙከራ መኖሩን እንዲሁም ኹለት በብርጋዴር ጀነራል ማዕረግ ደረጃ ያሉ ከፍተኛ የጦር አመራሮችን ሕወሓት ማስኮብለል መቻሉ ተጠቅሷል። በተቃራኒው ደግሞ ሙከራውን እውቅና የሚሰጡ ነገር ግን ከማስኮብሉ በዘለለ የገንዘብ መደለያው መክሸፉን አስረግጠው የሚናገሩ አሉ።

እንግዲህ ይህ በእንዲህ እንዳለ ነው፤ የመከላከያ የአመራር ለውጥን ተከትሎ የሰሜን ዕዝ አዛዥ የነበሩት ሌፍተናንት ጀነራል ድሪባ መኮንን ከቦታቸው ተነስተው በምትካቸው የምሥራቅ ዕዝ አዛዥ የነበሩት ሜጀር ጀነራል በላይ ስዩም መሾማቸው የተሰማው። የመቀሌው መንግሥት ግን ሳይውል ሳያድር በሹመቱ አለማስደሰቱን ብቻ ሳይሆን ተቀባይነት እንደማይኖረው በግልጽ ቋንቋ አስታውቋል።

በዚህ መካከል ኀሙስ፣ ጥቀምት 19 አዲሱ የሰሜን ዕዝ ምክትል አዛዥ በመሆን የተሾሙት ብርጋዴር ጀነራል ጀማል መሐመድ ወደ ምድብ ቦታቸው በዓየር ተሳፍረው መቀሌ የሚገኘው አሉላ አባ ነጋ አይሮፕላን ማረፊያ እንደደረሱ ወዲያውኑ በክልሉ ባለሥልጣናት ቆፍጣና ትዕዛዝ መሰረት ተሳፍረው በመጡበት አይሮፕላን እንዲመለሱ ተደርጓል የሚል ወሬ በማኅበራዊ ትስስር ገፆች ላይ መናፈስ የጀመረው። ወሬው እውነት ለመሆኑ ብዙም ሳቆዩ መደበኛ መገናኛ ብዙኀን የድርጊቱን እውነትነት በማረጋገጥ ዘግበውታል። የትግራይ መንግሥት የሚናገረውን ተግባራዊ እንዳያደርግ የሚያግደው አንዳች ኀይል የለም ሲሉ የሚከራከሩ ደጋፊዎች አቋም እውነተኛነትንም አረጋገጠ።

ከዚህ በኋላ ትልቁ ጥያቄ የሚሆነው፥ ከዚህ ቀጥሎ ምን ይሆናል የሚለው ነው። የፌደራል መንግሥቱ ለሕወሓት አመራሮች የተለሳሰለሰ አቋም መያዝ የልብ ልብ ሰጥቷቸዋል ከሚሉት ጀምሮ ጠብ አጫሪነቱ ሃይ ሊባል ይገባል ሲሉ የገለጹም አሉ። የሆነው ሆኖ ከዚህ በኋላ የሰሜን ዕዝ አዛዥ የሆኑት ሜጀር ጀነራል በላይ ስዩምስ ደፍረው ወደ መቀሌ ይሄደሉ? የመከላከያ ሠራዊቱስ ለመቀሌው መንግሥት ምን ዓይነት ምላሽ ይሰጣል? የፌደራል መንግሥቱስ እሹሩሩውን ትቶ ምን ዓይንት የመልስ ምት ይሰጥ ይሆን? የሚሉት ጥያቄዎች ምላሽ አጓጊ ብቻ ሳይሆኑ የአገር ህልውናን የሚወስኑ ይሆናሉ።

ቅጽ 2 ቁጥር 104 ጥቅምት 21 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here